| 13፥16 | የእግዚአብሔርም መልአክ ማኑሄን፦ አንተ የግድ ብትለኝ መብልህን አልበላም የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ማዘጋጀት ብትወድድ ለእግዚአብሔር አቅርበው አለው። ማኑሄም የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አላወቀም ነበር። |
| 13፥17 | ማኑሄም የእግዚአብሔርን መልአክ። ነገርህ በደረሰ ጊዜ እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው? አለው። |
| 13፥18 | የእግዚአብሔርም መልአክ። ስሜ ድንቅ ነውና ለምን ትጠይቃለህ? አለው። |
| 13፥19 | ማኑሄም የፍየሉን ጠቦትና የእህሉን ቍርባን ወስዶ በድንጋይ ላይ ለእግዚአብሔር አቀረበው። መልአኩም ተአምራት አደረገ፥ ማኑሄና ሚስቱም ይመለከቱ ነበር። |
| 13፥20 | ነበልባሉም ከመሠዊያው ላይ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ የእግዚአብሔርም መልአክ በመሠዊያው ነበልባል ውስጥ ዐረገ ማኑሄና ሚስቱም ተመለከቱ፥ በምድርም በግምባራቸው ተደፉ። |
| 13፥21 | የእግዚአብሔርም መልአክ ዳግመኛ ላማኑሄና ለሚስቱ አልተገለጠም ያን ጊዜም ማኑሄ የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አወቀ። |
| 13፥22 | ማኑሄም ሚስቱን፦ እግዚአብሔርን አይተናልና ሞት እንሞታለን አላት። |
| 13፥23 | ሚስቱም። እግዚአብሔርስ ሊገድለን ቢወድድ ኖሮ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ከእጃችን ባልተቀበለን፥ ይህንም ነገር ሁሉ ባላሳየን፥ እንዲህ ያለ ነገርም በዚህ ጊዜ ባላስታወቀን ነበር አለችው። |
| 13፥24 | ሴቲቱም ወንድ ልጅ ወለደች፥ ስሙንም ሶምሶን ብላ ጠራችው ልጁም አደገ እግዚአብሔርም ባረከው። |
| 13፥25 | የእግዚአብሔርም መንፈስ በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ባለው በዳን ሰፈር ውስጥ ሊያነቃቃው ጀመረ። |
| 14፥1 | ሶምሶንም ወደ ተምና ወረደ፥ በተምናም ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አየ። |
| 14፥2 | ወጥቶም ለአባቱና ለእናቱ። በተምና ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አይቻለሁ አሁንም እርስዋን አጋቡኝ አላቸው። |
| 14፥3 | አባቱና እናቱም። ካልተገረዙት ከፍልስጥኤማውያን ሚስት ለማግባት ትሄድ ዘንድ ከወንድሞችህ ሴቶች ልጆች ከሕዝቤም ሁሉ መካከል ሴት የለምን? አሉት። ሶምሶንም አባቱን፦ ለዓይኔ እጅግ ደስ አሰኝታኛለችና እርስዋን አጋባኝ አለው። |
| 14፥4 | እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያን ላይ ምክንያት ይፈልግ ነበርና ነገሩ ከእርሱ ሆነ አባቱና እናቱ ግን አላወቁም። በዚያን ጊዜም ፍልስጥኤማውያን በእስራኤል ላይ ገዦች ነበሩ። |
| 14፥5 | ሶምሶንም አባቱና እናቱም ወደ ተምና ወረዱ፥ በተምናም ወዳለው ወደ ወይኑ ስፍራ መጡ እነሆም፥ የአንበሳ ደቦል እያገሣ ወደ እርሱ ደረሰ። |