
ማሳሰቢያ:-
መንፈሳዊ በረከቶች
ብለን በሰየምነው
በዚህ ጥናት ውስጥ በዝርዝር
ልናይ የምንፈልገው
መንፈሳዊ በረከቶቹን
ብቻ ነው:: ይህም ማለት
በረከቶቹን በማን
በኩል
እንደተባረክንና
ይህንንስ ለማድረግ
እግዚአብሔርን
ያነሳሳው (motive) ምን
እንደሆነ አሁን
አንመለከትም::
እነዚህን ነገሮች በኋላ
ላይ
እንመለከታቸዋለንና::
1.
በዚህ
ክፍል ውስጥ
የሚከተሉት መንፈሳዊ
በረከቶች
ተዘርዝረዋል:-
1.
አለም
ሳይፈጠር መረጠን
2.
አስቀድሞ
ወሰነን (የእርሱ
ልጆች እንሆን ዘንድ)
3.
ቤዛነትና
የበደል ስርየት
አገኘን
4.
ጸጋውን
አበዛልን/አትረፈረፈልን
·
በጥበብና
በአእምሮ ሁሉ
·
የፈቃዱን
ምስጢር አስታወቀን
5.
ርስትን
ተቀበልን
6.
በመንፈስ
ቅዱስ ታተምን
ማሳሰቢያ:-
ከዚህ በላይ
ከተዘረዘሩት
በረከቶች ውስጥ በዚህ
በክፍል 2 ደግሞ ከ4-6
ያሉትን
እንመለከታቸዋለን::
2.
ጸጋውን
አበዛልን/አትረፈረፈልን
·
ሀ)
ጸጋውን አበዛልን
·
ጸጋ
ተቀባዩ
የማይገባው ሆኖ ሳለ
ሰጪው በበጎ ፈቃዱ
በነጻ የሚሰጠው
ስጦታ፣ እንዲያው
የሚያደርገው
ቸርነትና መልካም
ሥራ:: ከሥራ የሚገኝ
ነገር ሁሉ ለሠራው
ሰው ደመወዙ፣
ለአሠሪው ደግሞ
ሊከፍለው የሚገባ ዕዳ
እንጂ ጸጋ አይደለም
(ሮሜ 4፣4):: ጸጋ የሚለው
ቃል በአዲስ ኪዳን
በተለይ ሰው ከሰው
ጋር ያለውን ግንኙነት
የሚያመለክት
ሳይሆን፣
እግዚአብሔር በበጎ ፈቃዱ
እንዲያው በነጻ
ያደረገልንና
የሰጠንን ስጦታ ሁሉ
የሚያመለክት ነው::
እዚህ ላይ ልብ ማለት
የሚገባን ነገር
ቢኖር፣ ነጻ የሆነና
ምንም ሳይከፈልበት
የሚገኝ ነገር ሁሉ
ብዙ ጊዜ ርካሽ
የሆነን ነገር ነው
የሚያሳየው::
በክርስቶስ የተሰጠን
የእግዚአብሔር ነጻ
ስጦታ ወይም ጸጋ ግን፣
በምንም ዋጋ ሊከፈል
የሚችል ያልሆነ፣
ነፍሳችንን እንኳን
ብንሰጥ የማይበቃ፣
በምድር ላይ ያለ
ነገር ሁሉ ተሰብስቦ
ሊገዛው የማይችል
ነው:: ዋጋ
የማይገኝለት ውድነቱ
ራሱ እግዚአብሔር
ለእኛ በነጻ
እንዲሰጠን ካደረገው
አንዱ ምክንያት ነው:: 1
ጴጥ 1፣18-19
·
ማብዛት
(abound)
ከሚያስፈልገው
ወይም ከሚበቃው በላይ
መጨመር፣
ማትረፍረፍ፣ ማባከን
የእግዚአብሔር
ጸጋ የሚያድን ብቻ
ወይም የበደል ይቅርታ
የሚያስገኝ ብቻ ወይም
ከፍርድ የሚያስመልጥ
ጸጋ ብቻ አይደለም፣
ነገር ግን
የተትረፈረፈ ጸጋ
እንጂ:: ከማዳንና
ከይቅርታ በላይ
የዘላለምን ክብር፣
ልጅነትና ርስትን
ከጥበብና ከአእምሮ
ሁሉ ጋር የሚጨምር፣
ከበቂ በላይ የሆነ
የተትረፈረፈ ጸጋ
ነው:: ለሰው ልጆች የኃጢአት
ይቅርታና ምሕረት ራሱ
በቂ ነበርና::
በሉቃ
15፣11-32 ላይ ባለው
የጠፋው ልጅ ታሪክ
ላይም የምንመለከተው
ተመሳሳይ
የእግዚአብሔርን
ጸጋና ምሕረት ነው::
ለጠፋው ልጅ እንደ
ሌሎቹ የአባቱ
ባሪያዎች መሆን ብቻ
በጣም በቂው ነበር::
ቢበዛ ቢበዛ ደግሞ
የአባቱን ምሕረት
አግኝንቶ የተማረ ልጅ
መሆን ብቻ ራሱ ትልቅ
ነገር ነው:: አባቱ ግን
ከነቆሻሻው ከማቀፍ
ጀምሮ፣ አዲስ
ልብስንና ቀለበትን
እንዲሁም በቤት
ለነበረው ልጅ እንኳን
አድርጎ የማያውቀውን
ታላቅ ድግስ አደረገለት::
ይህም አባቱ ልጁን
እንዲያው ይቅር ብቻ
ብሎ በዚያ ብቻ
ሊያበቃ እንዳልወደደና
ምሕረቱና ጸጋው፣
ፍቅሩም የተትረፈረፈ
እንደ ሆነ ያሳየናል::
·
ለ)
በጥበብና በአእምሮ
ሁሉ
·
ጥበብ
ጥበብ
የሚለው ቃል በተለያዩ
የመጽሐፍ ቅዱስ
ክፍሎች ውስጥ
በተለያየ ሁኔታ
ስለተገለጠ፣ የቃሉን
ፍቺ እንደ ምንባቡና
እንደ ክፍሉ መረዳት
ይገባል::
እንደ
ጳውሎስ አገላለጽ፣
ጥበብ ማግኘት ማለት
ከዘመናት በፊት
በክርስቶስ ተሰውሮ
የነበረው
የእግዚአብሔር
የማዳን እቅድን ወይም
ፕላንን በሙላት
ማወቅና መረዳት ነው::
“...እግዚአብሔር
አስቀድሞ ከዘመናት
በፊት ለክብራችን
የወሰነውን፣
ተሰውሮም የነበረውን
የእግዚአብሔርን
ጥበብ በምስጢር
እንናገራለን::” 1ቆሮ
2፣6-7
“...የእግዚአብሔርን
ምስጢር እርሱንም
ክርስቶስን
እንዲያውቁ እጋደላለሁ፣
የተሰወረ የጥበብና
የእውቀት መዝገብ ሁሉ
በእርሱ ነውና::” ቆላ
2፣2-3
“...ከእግዚአብሔር
ዘንድ ጥበብና ጽድቅ
ቅድስናም ቤዛነትም
በተደረገልን
በክርስቶስ የሆናችሁ
ከእርሱ ነው:: ” 1ቆሮ 1፣30
በዚህም
ክፍል ጥቂት ወረድ
ብሎ በኤፌ 1፣9 ላይ
“በክርስቶስ ለማድረግ
እንደ ወደደ እንደ
አሳቡ፣ የፈቃዱን
ምስጢር
አስታውቆናልና”
ይላል:: ስለዚህ በዚህ
ክፍል አገላለጽ ጥበብ
የሚለው እንግዲህ
የእግዚአብሔር
የፈቃዱን ምስጢር
ማወቅን፣
እግዚአብሔር
በክርስቶስ ለማድረግ
ያሰበውን ዘላለማዊ
ፈቃዱን መረዳት ነው::
·
አእምሮ
ማስተዋል፣
መረዳት፣ ማገናዘብ፣
ማመዛዘን፣ ማጤን
ወዘተ
እግዚአብሔር
እንግዲህ ከመዳንና
ከይቅርታ በላይ
በክርስቶስ ያለውን
የእርሱን ጥበብ
እንድናስተውልና እንድንረዳ፣
በመረዳትም ባለጠጎች
እንድንሆን ይወዳል
ማለት ነው:: የሰማያዊ
ምስጢር መረዳት ድሆች
እንድንሆን
የእግዚአብሔር አላማ
አይደለም::
·
ሐ)
የፈቃዱን ምስጢር
አስታወቀን
·
ምስጢር
ምስጢር
ማለት:- ያለ፣ ነገር
ግን ለሁሉም ያልታወቀ
ወይም ያልተገለጠ ጉዳይ
ማለት ነው:: ከዘመናት
በፊት በእግዚአብሔር
ብቻ ይታወቅ የነበረ
አሁን ግን ለእኛ
የተገለጠ:: ምስጢር
ለቀረቡና ለታመኑ
ወዳጆች የሚገለጥ
ጉዳይ ነው::
እግዚአብሔርም
ምስጢሩን ለእኛ
ከመግለጡ በፊት እኛን
ወደ እርሱ ማቅረብ
ነበረበት:: ስለዚህ
እግዚአብሔር
የሚመቸውን ጊዜ ጠብቆ
ነው ማለት ነው
ምስጢሩን
የገለጸው::
·
የዘመን
ፍጻሜ
መጽሐፍ
ቅዱስ የዘመን ፍጻሜ
ብሎ የሚጠራው
ክርስቶስ ወደ አለም
ከመጣበት ጊዜ አንስቶ
ያለውን ዘመን ነው::
ዕብ 1፣2 1ጴጥ 1፣20
·
የእግዚአብሔር
አሳብ/ፈቃድ
·
በሰማይና
በምድር ያለውን ሁሉ
በክርስቶስ መጠቅለል
በእንግሊዘኛው:-
head up, sum up, bring together, unify etc in christ.
በአማርኛ:-
ጠቅልሎ መግዛት፣
አንድ አድርጎ መግዛት
ወይም በክርስቶስ አገዛዝ፣
ራስነት፣ ሥልጣን ሥር
መሰብሰብ፣ ማያያዝ፣
አንድ ማድረግ፣ ማገጣጠም፣
ማቀራረብ፣ ማዋሃድ፣
ማስማማት ወዘተ
እዚህ
ላይ እንግዲህ ልብ
ልንል የሚገባው
የእግዚአብሔር
ዘላለማዊ እቅድና
አላማ:-
1.
በምድር
እና በሰማይ ያሉትን
ሁሉ በክርስቶስ
ራስነት ወይም ስልጣን
ሥር ማድረግ ፊል 2፣9-11
ማቴ 28፣18
2.
እርስ
በርስ ማዋሃድ፣
ማስማማት፣ አንድ
ማድረግና ሰላምን
መፍጠር ነው::
በክርስቶስ ራስነት
ሥር የሆነ ሰላምና
መስማማት (harmony)
እንግዲህ አንዱ የእግዚአብሔር
ዋነኛው ዘላለማዊ
እቅዱ ነው:: አይሁድ
ከአሕዛብ፣ ባሪያና
ጨዋ፣ ሴትና ወንድ፣
ወዘተ ገላ 3፣28 ኤፌ 1፣11-17
3.
ርስትን
ተቀበልን
·
ርስት
ርስት
ብሎ እዚህ ላይ
የጠቀሰው፣ ውርስን
ለማመልከት ነው::
ከመዳን
ባሻገር የምንወርሰው
የዘላለም ርስት
እግዚአብሔር
እንዳዘጋጀልን
መጽሐፍ ቅዱስ
ይናገራል::
“ልጆች
ከሆንን ወራሾች ደግሞ
ነን፣ ማለት
የእግዚአብሔር
ወራሾች ነን...” ሮሜ 8፣17
የማይጠፋ፣
እድፈትም የሌለበት፣
የማያልፍና በሰማይ
የተዘጋጀ ርስት 1ጴጥ
1፣3-5
ርስት
ምንም እንኳን የተሰጠንና
የተዘጋጀልን ቢሆንም
ሙሉ በሙሉ
የምንወርሰው ግን
ወደፊት ነው:: ስለዚህ
ርስት የቅዱሳን ተስፋ
ነው:: እግዚአብሔር
ለደህንነት ብቻ አልጠራንምና
ነገር ግን ለርስትና
ለታላቅም ተስፋ
እንጂ::
4.
በመንፈስ
ቅዱስ ታተምን
·
ማኅተም
የባለቤትነት
ምልክትና
የእውነተኝነት
ማረጋገጫ ሲሆን፣
ከማኅተም ጀርባ አንድ
ሥልጣን እንዳለ
ያሳያል::
·
መያዣ
ቀብድ (down
payment)፣ እዚህ ላይ ሰለ
መያዣ ወይም ስለ
ቀብድ ሲናገር ሰለ
ግማሽ ዋጋ ለመናገር
ሳይሆን በተለይ
መያዣነትን፣ ማረጋገጫነትንና
ዋስትናን ለማሳየት
ነው:: ስለዚህ
እግዚአብሔር እንግዲህ
መያዣ የሰጠን፣ ርስት
ወይም ውርስ
እንዳዘጋጀልንና
ይህንንም ርስት
በርግጥ እንደምናገኝ
ለማረጋገጥና ዋስትና
ለመስጠት ነው:: በሮሜ
8፣23 ላይ “የመንፈስ
በኩራት ያለን”
የሚለው ቃል፣
የመንፈስ የመጀመሪያ
ስጦታ፣ ሊመጣ ላለው
ለዋናው ስጦታ ቅምሻ
ማለት ነው:: ስለዚህም
እዚህ ቦታ መንፈስ
ቅዱስ፣ የተስፋው
መንፈስ ተብሎ
ይጠራል::
ሌላው
እዚህ ላይ ልብ
ልንለው የሚገባን
ነገር፣ ይህንን መያዣ
የሰጠን እግዚአብሔር
እንጂ እኛ
ለእግዚአብሔር
የሰጠነው አይደለም::
ስለዚህ በዚህ ክፍል
ጳውሎስ መያዣ
የሚለውን ቃል፣ እኛ
መዳናችንን ለመፈጸም
የሚቀረንን ሩጫ
ለማመልከት
የተጠቀመበት
አይደለም::