ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » ትምህርቶች » በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው? » የደም መሥዋዕት
Email this page to a friend Printer-friendly   Tuesday, 25 July 2017
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“ቸር ሰው ይራራል ያበድራልም፥ በፍርድም ነገሩን ይፈጽማል።“
(መዝሙረ ዳዊት 112:5)

rss

Today's verse

የደም መሥዋዕት

pdf version

     እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ሊያደርግላቸው ከሚፈልገው ነገሮች ሁሉ ዋናውና ትልቁ ነገር ኃጢአትን ማስወገድ ነው:: ኃጢአት የሰዎች የችግራቸውና የመከራቸው ዋነኛ ሥርና ምክንያት ነውና:: የሕይወትና የበረከት ምንጭ ከሆነው ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር ያለያያቸውና ያጣላቸው ዋናው ነገር ኃጢአት ነው:: ኃጢአት በሰዎች ታሪክ ሁሉ የሰው ልጆች የሞትና የመከራ፣ የሃዘንና የለቅሶ ምንጭ ነው:: የሰዎችን ከእግዚአብሔር መራቅ ስለዚህም ደግሞ የሕይወት እርካታ አለማግኘታቸውና የመቅበዝበዛቸው፣ እርስ በርስ ፍቅር የማጣታቸው፣ በመጨረሻም ለዘላለም ፍርድና ስቃይ ለሲኦልም የሚያበቃቸው ዋነኛ ክፉ የሰዎች ጠላት ኃጢአት ነው::

 

     ስለዚህ ኃጢአትን ማስወገድ ለሰው ልጆች ከሚያስፈልጋቸው እርዳታ ሁሉ በፊት በቀደምትነት የሚጠቀስ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው:: ከምግብና ከመጠጥ በፊት ከሥጋ ጤንነት ሁሉ በፊት የነፍስ መዳን ቀዳሚነት ያለው ነገር ነው:: ለዚህም ደግሞ ኃጢአት መወገድ አለበት:: ኃጢአት እያለ ከፍርድ መዳን የለም፣ ኃጢአት እያለ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅና የዘላለም ሕይወት፣ የእግዚአብሔርንም መንግስት መውረስ የለም:: የጥያቄአችን ሁሉ መልስ ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅ በመጀመርያ ደረጃ የሰው ልጆች የኃጢአት ችግር መፍትሔ ማግኘት አለበት:: ሌላው ሁሉ ከዚያ በኋላ የሚመጣ ነው:: ብዙ ሃይማኖቶች ለዚህ የሰው ልጆች ሁሉ የችግር ሥር ለሆነው ለኃጢአት በቂ መልስ የላቸውም:: አንዳንዶቹ እንዲያውም ፈጽመው አያነሱትም:: ነገር ግን ሰውንና እግዚአብሔርን ለለየው የሰዎች ዋነኛ ችግር መልስ እስካልተገኘ ድረስ የሞተ የሃይማኖት ሥርዓት ብቻ ለሰዎች መፍትሄ አይሆንም::

 

     ሐኪሞች የሚሰማንን የሕመም ስሜት ስንነግራቸው ሕመማችንን ብቻ ለማስታገስ አይሞክሩም:: ነገር ግን የበሽታችንን መንስኤና ሥር ለማወቅና ለማስወገድ ነው የሚፈልጉት:: እግዚአብሔርም ሰዎች የሚያጋጥማቸውን ስቃይ ለማስታገስ ብቻ አይሞክርም:: በሰዎች ላይ የምናያቸው መልካም ያልሆኑ ነገሮች ሁሉ አንድ ትልቅና ሥር የሰደደ ችግር እንዳለ ነው የሚያሳየን፣ ይህም የሰው ልጆች ኃጢአት ነው:: መግደልና ማመንዘር፣ ጥላቻና ጠብ፣ ክፋትና ምቀኝነት፣ ስርቆትና ውሸት፣ ስካርና ዝሙት፣ ገንዘብን መውደድና ስስት...ወዘተ እነዚህና የመሳሰሉት ናቸው እንግዲህ የሰው ልጆችን ወደ ጥፋት የሚነዱት፣ የመከራውና የዕንባው መንስኤ የሆኑት፣ ከአምላኩ ያራቁትና ለዘላለም ፍርድ የሚዳርጉት:: የትኛውም ሃይማኖት ለዚህ ጥያቄ መልስ የለውም:: በማንም የሃይማኖት መሪና ነብይ ዘንድ ለኃጢአት መፍትሔ አይገኝም:: የዚህ ምድር የሃይማኖት መሪዎችና ጠቢባን፣ በኃጢአት ምክንያት ለሚደርስብን ሕመም ምናልባት ማስታገሻ ይሰጡን ይሆናል እንጂ ኃጢአትን ራሱን ማስወገድ የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው::

 

     እግዚአብሔር ለመሆኑ ኃጢአትን የሚያስወግደው እንዴት ነው? በተለያዩ የሃይማኖት ሥርዓቶች ነው? የተለያዩ ቦታዎች ሄደው ሰዎች እንዲሰግዱ በማድረግ ነው? ወይስ በጸሎት ርዝመት? በጾምና ራስን በተለያዩ ነገሮች በመጉዳት ይሆን? ወይስ እንዲያው ስለ ኃጢአት ምንም ባለማንሳትና እንደሌለ በመቁጠር?

 

     በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ (ሊሽር) የሚችል አንድ ነገር ብቻ እንደሆነ እናነባለን::

 

"የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፣ ደሙም ከሕይወቱ የተነሳ ያስተሰርያልና በመሠዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተሰረያ ይሆን ዘንድ እኔ ለእናንተ ሰጠሁት::" ዘሌ 17፣11

 

"...ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም::" ዕብ 9፣22

 

እግዚአብሔር ለሰዎች ኃጢአት የሰጠው ብቸኛ ማስተሰረያ ደም ነው:: ያለ ደምም የኃጢአት ስርየት የለም:: ደም የሌለው መስዋዕት ኃጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ፣ ሰውንና እግዚአብሔርንም ያስታርቅ ዘንድ ብቁ አይደለም:: ኃጢአት እጅግ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል ድርጊት ነውና:: ኃጢአትን የሚሠራ ሁሉ በራሱ ሕይወት መክፈል አለበት:: ኃጢአት የሠራ ሰው ከሞት ባነሰ ቅጣት አይቀጣም:: ኃጢአት መሥራት በሕይወት ላይ መፍረድ ማለት ነው::

 

     "የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና..." ሮሜ 6፣23

 

ከደም በስተቀር ምንም አይነት ሃይማኖታዊ ሥርዓት፣ ስግደትና ጾም ረጅምም ጸሎት...ወዘተ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ አይችልም::

 

"የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፣ ደሙም ከሕይወቱ የተነሣ ያስተሰርያልና..." ዘሌ 17፣11

 

ስለዚህም በብሉይ ኪዳን ሰዎች ኃጢአት ሲሠሩ ኃጢአታቸው ይሰረይ ዘንድ የተለያዩ የከብቶች መስዋዕትን ለእግዚአብሔር ማቅረብ ነበረባቸው::

 

"...ማናቸውም ሰው ሳያውቅ ኃጢአት ቢሠራ፣ እግዚአብሔርም:- አትስሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፍ ...ስለ ሠራው ስለ ኃጢአቱ ነውር የሌለበት ወይፈን ለእግዚአብሔር ለኃጢአት መስዋዕት ያቀርበዋል:: ወይፈኑንም ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያመጣዋል፣ እጁንም በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭነዋል፣ ወይፈኑንም በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል:: የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወስዶ ወደ መገናኛው ድንኳን ያመጣዋል፣ ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመቅደሱ መጋረጃ ፊት ደሙን ሰባት ጊዜ ይረጨዋል::" ዘሌ 4፣2-6

 

በብሉይ ኪዳን ማንኛውም ሰው ለኃጢአት መሥዋዕትን ሲያቀርብ ሊያስተውል የሚገባው ሶስት ዋና ዋና ነገሮች አሉ::

 

     በመጀመሪያ የሚቀርበው መስዋዕት ነውር የሌለው መሆኑን ማረጋገጥ ነው:: ይህም ማለት የሚቀርበው እንስሳ፣ አንካሳ ወይም እውር ያልሆነ ወይም የቆዳ በሽታ የሌለበትና ፍጹም ጤነኛ መሆኑን ማረጋገጥ ነው:: ምክንያቱም ነውር ያለበትን መስዋዕት ለእግዚአብሔር ማቅረብ በጥብቅ የተከለከለ ነው:: ቢቀርብም ኃጢአትን ሊያስተሰርይ አይችልም::

 

"በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነውና ነውር ወይም ክፉ ነገር ያለበትን በሬ ወይም በግ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አትሠዋ::"

ዘዳ 17፣1

 

"ነውረኛ ወይም አንካሳ ወይም ዕውር ቢሆን፣ ወይም አንዳች ክፉ ነውር ቢኖረው ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አትሠዋው::" ዘዳ 15፣21

 

ስለዚህ ማንኛውም ሰው ለመሥዋዕት የሚያቀርበው እንስሳ አንዳች ነውር እንደሌለው ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው:: ለመሥዋዕት የሚቀርበው እንስሳ ነውር የሌለው ንጹህ መሆኑ ከተረጋገጠ ወደ እግዚአብሔር ፊት ወደ መሠዊያው ያመጣዋል:: በድብቅ የሚታረድ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የለውምና::

 

     በሁለተኛ ደረጃ እንስሳውን ወደ መገናኛው ድንኳን ካመጣ በኃላ የሚቀጥለው ድርጊት ኃጢአት የሠራው ሰው እጁን በወይፈኑ ላይ መጫን ነው:: ይህም ሰውዬው የሠራውን ኃጢአት እንስሳው እንደሚሸከም የሚያሳይ ነው:: የሰውዬውን ኃጢአት የተሸከመው እንስሳ እንግዲህ ሰውዬው ሊቀበለው የነበረውን የሞት ፍርድ ይቀበላል ማለት ነው:: ስለዚህም በእርሱ ፋንታ እንስሳው ይታረዳል::

 

     በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ካህኑ የከብቱን ደም ወስዶ በእግዚአብሔር ፊት በመገናኛው ድንኳን ይረጨዋል:: ይህም እግዚአብሔር መሥዋዕቱን እንደተቀበለና የሰውዬውም ኃጢአት እንደተሰረየለት፣ ሰውዬውም ከእግዚአብሔር ዘንድ ምህረትን እንደተቀበለ ያመለክታል:: ይህንንም ሥርዓት ኃጢአት በሠሩ ቁጥር ያደርጉ ነበር::

 

     "...ደምም ሳይፈስ ስርየት የለምና"

 

     ነገር ግን በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር የዓለምን ኃጢአት ሁሉ በአንድ ጊዜ የሚያስወግድ የራሱን በግ ነው ያዘጋጀልን:: እርሱም ሰማያዊው የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው::

 

"በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፣ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ::" ዮሐ 1፣29

 

ኃጢአትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው:: በብሉይ ኪዳን ለመሥዋዕት ይቀርቡ የነበሩት ኮርማዎችና ፍየሎች በጎችም ሁሉ የእውነተኛው የእግዚአብሔር በግ የኢየሱስ ምሳሌዎች ብቻ ናቸው እንጂ ኃጢአትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ አይችሉም::

 

"ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል፣ እርሱ (ኢየሱስ) ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ" ዕብ 10፣11-12

 

ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ የሆነ መሥዋዕት፣ ይኸውም ራሱን በማቅረቡና ደሙን በማፍሰሱ ለሰው ልጆች ሁሉ ኃጢአት ስርየት ብቸኛ መንገድ ነው:: ከእግዚአብሔር በግ በስተቀር ኃጢአትን ሊያስወግድ የሚችል ምንም ነገር የለም::

 

     ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰዎች ኃጢአት ከመሠዋቱ በፊት ልክ እንደ ብሉይ ኪዳን መስዋዕቶች ነውር የሌለበት መሆኑ መረጋገጥ ነበረበት:: ነውር የሚያመለክተው ኃጢአትንና መተላለፍን በእግዚአብሔር ፊትም መርከስንና ተቀባይነት ማጣትን ነው:: ኢየሱስ ግን ያለ ኃጢአት የኖረ በመሆኑ ለመሥዋዕትነት ብቁ ነው:: ኢየሱስ በኖረበት ዘመን የነበሩ የእርሱ ተቃዋሚዎች ፈልገውና መርምረው ያላገኙት ነገር ኃጢአት ነው:: ስለዚህም ኢየሱስ ራሱ እንዲህ ብሎ ይጠይቃቸው ነበር:-

 

     "ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው?" ዮሐ 8፣46

 

ማነው እየሱስን ስለ ኃጢአት የሚወቅስ? ኃጢአት ሠርቷል ብሎ ወደ ኢየሱስ እጁን የሚጠቁም ማን ነው? ስህተትና ነውር ተገኝቶበታል ብሎ በኢየሱስ ላይ የሚነሳ ማን ነው? በሰማይም በምድርም ኢየሱስን ስለ ኃጢአት የሚወቅስ ማንም የለም:: በምድርም ላይ ያለአንዳች ኃጢአት (ነውር) የኖረ ብቸኛ ሰው እርሱ ብቻ ነውና::

 

"እርሱም ኃጢአት አላደረገም፣ ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም..." 1ኛ ዼጥ 2፣22-23

 

ኢየሱስ ነውርና ነቀፋ የሌለበት የሰው ልጆችን ኃጢአት ሊያስተሰርይ የሚችል የእግዚአብሔር በግ ነው ! የሌላ ሰው ደም ግን እንኳን የዓለምን ይቅርና የራሱንም ኃጢአት ሊያስተሰርይ አይችልም::

 

"ልዩነት የለምና፣ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል..." ሮሜ 3፣22-23

 

ሌላው ልክ የብሉይ ኪዳን እንስሳት እጅ ተጭኖባቸው የሰውን ኃጢአት እንደሚሸከሙ፣ ኢየሱስም የሰዎችን ኃጢአት መሸከም ነበረበት:: አንድ ከብት የሚሸከመው የአንድን ሰው ኃጢአት ብቻ ነበረ፣ ኢየሱስ ግን የዓለምን ኃጢአትና በደል ሁሉ በራሱ ላይ ተሸክሞ በእኛ ፋንታ መከራንና ሞትን ተቀበለ:: ለእኛም ሲል ተሠዋ::

 

     "...እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ::"

ኢሳ 53፣6

"...ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፣ ኃጢአታቸውንም ይሸከማል::" ኢሳ 53፣11

"...እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ..." 1ዼጥ 2፣24

 

ነውርና እንከን የሌለበት የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ ብቸኛ የመስዋዕት በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው:: አምላክ ሰው ሆኖ ወደ ምድር የመጣበት ዋነኛ ምክንያት እንግዲህ ለችግራችን መንስኤ መፍትሔ ለመስጠት ነው::

 

"...እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ::" ! ዮሐ 1፣29

 

     ኢየሱስ መስዋዕት ሲሆንና ለእኛም ደሙን ሲያፈስ በድብቅና በድንገተኛ ሞት አልነበረም:: ነገር ግን ነግሥታትና የሃይማኖት መሪዎች፣ ካህናቱም ሕዝቡም ሁሉ እያወቁና እያዩ በእግዚአብሔር ፊት መስዋዕት ሆነ:: ንጹህ የሆነውንም ደሙን አፈሰሰልን::

 

     በመጨረሻም በብሉይ ኪዳን የከብቶችን የመሥዋዕት ደም ሊቀ ካህናት ወስዶ ወደ እግዚአብሔር እንደሚያቀርብና የመገናኛውንም ድንኳን እንደሚረጭ፣ የመሥዋዕት በግም ሊቀካህናትም የሆነው ኢየሱስ ከሙታን በመነሳት የራሱን ደም ይዞ ወደ እውነተኛው የእግዚአብሔር መኖሪያ ወደ ሰማይ በመሄድ በደሙ ይቅርታንና የኃጢአትን ስርየት ከእግዚአብሔር ዘንድ አስገኘልን:: እግዚአብሔርም ይህንን መሥዋዕት በደስታ ተቀብሎታል:: ኢየሱስ አንዳች ተጨማሪ የማያስፈልገው የዓለምን ኃጢአት ሁሉ የሚያነጻና ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ በቂ የመሥዋዕት በግ ነው::

 

     ከጥንት ጀምሮ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር የተስተካከለ ግንኙነት ለማድረግ የተለያዩ መሥዋዕቶች ያቀርባሉ:: አንዳንዶች እግዚአብሔር ያዘዛቸውን ሌሎችም በራሳቸው የገመቱትንና የመሰላቸውን ያቀርባሉ:: ቁም ነገሩ ግን እግዚአብሔር መሥዋዕትን ሁሉ ይቀበላል ወይ? ለኃጢአት ስርየት ይሁን ወይም ወደ እርሱ ለመቅረብ በሚደረግ ድርጊት ሁሉ እግዚአብሔር ደስ ይሰኛል ወይ? ልንጠይቅ የሚገባን ዋና ነገር ይሄ ነው::

 

     በመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቀረቡት አቤልና ቃየን የተለያዩ መሥዋዕቶችን እንዳቀረቡ እንመለከታለን::

 

"ከብዙ ቀንም በኋላ ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፣ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኩራትና ከስቡ አቀረበ::"

ዘፍ 4፣3-4

 

አቤልም ቃየንም መሥዋዕትን አቅርበዋል፣ ነገር ግን እግዚአብሔር የሁለቱንም መሥዋዕት ይቀበላል ወይ? መሥዋዕቶቻቸውም፣ አንዱ በውስጡ ደም ያለው የሚንቀሳቀስ በግ፣ ሌላውም በድን የሆነ የምድር ፍሬ፣ እግዚአብሔር በሁለቱም መሥዋዕቶች ይደሰታል ወይ? አይኖቹስ ወደ ሁለቱም ይመለከት ይሆን?

 

"እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፣ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም:: ቃየንም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ::" ዘፍ 4፣4-5

 

ሰዎች እንደመሰላቸው ወደ ሚያቀርቡት መሥዋት ሁሉ እግዚአብሔር አይመለከትም:: ለኃጢአት ሥርየት የማይሆን በድን መሥዋዕትን እግዚአብሔር አይቀበልም:: ለኃጢአታችን ሥርየት ይሆናል፣ ወደ እግዚአብሔርም ያቀርበናል ብለን እንደፈቃዳችን በምናደርገው ድርጊት ሁሉ እግዚአብሔር ደስ አይሰኝም::

 

     "...ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም::" !

 

     ኃጢአትን ያስተሰርያል ብለን ወደምናቀርበው፣ ወደ ሞተና በድን ወደ ሆነ የተለያየ የስግደትና የጸሎት ሥርዓት ሁሉ እግዚአብሔር አይመለከትም ! ነገር ግን ሕያው ወደ ሆነ፣ ነውርና እንከን ወደ ሌለው የደም መሥዋዕት እግዚአብሔር ይመለከታል::

 

     አንተስ ለኃጢአት ስርየት በእግዚአብሔር ፊት የምታቀርበው መሥዋዕት ምንድነው? የሞተ የሃይማኖት ሥርዓት ነው? ወይስ የተለያዩ መልካም የሚመስሉ የሰው ሥራዎች? ወገኔ ሆይ፣ እግዚአብሔር ወደዚህ አይመለከትም ! አንተም እንደ አቤል የደም መሥዋዕት ያስፈልግሃል:: አንተንም እንደ አቤል የበግ መሥዋዕት ያስፈልግሃል:: እግዚአብሔር የተመለከተውና የተቀበለው የደም መሥዋዕት እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ያስፈልግሃል::

 

     እነሆ፣ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ !

 

     በአዲስ ኪዳን ኮርማዎችንና ፍየሎችን ለእግዚአብሔር አናቀርብም:: ነገር ግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ነውር የሌለው የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ስለ ኃጢአታችን ታርዷል:: ዛሬ እግዚአብሔር፣ ራሱ ካዘጋጀው በግ ከኢየሱስ ሌላ ወደ ማናቸውም መሥዋዕቶች አይመለከትም፣ በየትኛውም ደስ አይሰኝም፣ በእርሱም ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም:: እግዚአብሔር ኢየሱስ ከሙታን አስነስቶ በራሱ ቀኝ ያስቀመጠውም የኢየሱስን መሥዋዕትነት ስለተቀበለ ነው::

 

"...እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መስዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ" ዕብ 10፣12

 

     እንደ ቃየን በበድን መሥዋዕት አትታመን ! ሊያድን በማይችል የሃይማኖት ሥርዓትና የሰው ፍልስፍና ተስፋ አታድርግ ! ነገር ግን የዓለምን ኃጢአት ሁሉ በሚያስወግደው በኢየሱስ ተማመን ! በእርሱ የሚያምን አያፍርምና::

 


“በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ ከፍ ከፍም ያደርጋችኋል።“
(የያዕቆብ መልእክት 4:10)

rss

Today's proverb

OR

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2017 by iyesus.com
Terms of use | Contact us