ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » ትምህርቶች » በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው? » ማን መሆኑንስ ብታውቂ
Email this page to a friend Printer-friendly   Tuesday, 25 July 2017
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“ቸር ሰው ይራራል ያበድራልም፥ በፍርድም ነገሩን ይፈጽማል።“
(መዝሙረ ዳዊት 112:5)

rss

Today's verse

ማን መሆኑንስ ብታውቂ

pdf version

     አሁን ደግሞ አንድን ታሪክ ደረጃ በደረጃ አብረን እንመለከታለን:: አንድ ቀን ኢየሱስ ሰማርያ በምትባል ከተማ ከመንገድ ለማረፍ በአንድ የውሃ ጉድጓድ አጠገብ ይቀመጣል::

 

"ከሰማርያ አንዲት ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች:: ኢየሱስም:- ውኃ አጠጪኝ አላት፣ ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበርና:: ስለዚህ ሳምራዊቲቱ:- አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ? አለችው አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና:: ኢየሱስም መልሶ:- የእግዚአብሔርን ስጦታና:- ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር አላት::" ዮሐ 4፣7-10

 

     ሳምራዊቷን ሴት ጌታ ውኃ አጠጪኝ ሲላት ተገረመች:: እንዴት አንተ አይሁድ ስትሆን ከእኔ ውኃ ትለምናለህ? ጌታ ግን አንድ ነገር እንዳላስተዋለች አውቋል:: በእውነት የተጠማው ጌታ ሳይሆን እርሷ ናት:: ውኃ ፍለጋ መቅጃ ይዛ የመጣች እርሷ እንጂ ጌታ አይደለም::

 

     ኦ! የእግዚአብሔርን ስጦታና ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑን ብታውቂ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ:: የእግዚአብሔርን ስጦታ ብታውቂ! ለሰው ልጆች ሁሉ እግዚአብሔር የሰጠውን ድንቅ ስጦታ ብታውቂ! ኦ የሚያነጋግርሽ ማን መሆኑን ብታውቂ! እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ሁሉ መፍትሄ ይሆንላቸዋል ብሎ ወዷቸው የሰጠውን ስጦታ ብታውቂ! "በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና::"

 

ዮሐ 3፣16 ከእግዚአብሔር ለዓለም ሁሉ የተሰጠውን ታላቅ ስጦታ ብታውቂ! ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን እንደሆነ አይንሽን ከፍተሽ ብታዪና ብታውቂ ኖሮ አንቺ ራስሽ ትለምኚው ነበር፣ እርሱም የሕይወትን ውኃ ይሰጥሽ ነበር::

 

"ሴቲቱ:- ጌታ ሆይ:- መቅጃ የለህም ጉድጓዱም ጥልቅ ነው፣ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ?" ዮሐ 4፣11

 

አንቺ ሴት አሁንም ገና የሚያናግርሽ ማን መሆኑን አላወቅሽም:: የሕይወት ውኃ መቅጃና ጉድጓድ አያስፈልገውም:: ከጉድጓድ ተምሶ የሚወጣ በመቅጃ የሚቀዳ አይደለም:: አንቺ ሴት ገና አልገባሽም::

 

ወገኔ ሆይ አንተም እንዲህ ትል ይሆናል:: የሕይወት ውኃ እንዴት ሊሰጠኝ ይችላል? በየት አድርጎ እንዴትስ ብሎ ሕይወቴን የሚያረካ ውኃ ይሰጠኛል? አንድ ነገር እነግርሃለሁ:: የእስራኤል ሕዝብ በምድረ በዳ ውኃ በሌለበት ምድር በጥማት ውስጥ ሲንከራተቱ እግዚአብሔር እንዴት ነበር ያጠጣቸው? እንዴትስ አረካቸው? ጉድጓድ ቆፍሮ ነውን?

 

"የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እግዚአብሔር እንዳዘዘ ከሲን ምድረ በዳ ሊጓዙ ተነሡ፣ በራፊዲምም ሰፈሩ፣ ሕዝቡም ይጠጡ ዘንድ ውኃ አልነበረም:: ሕዝቡም ሙሴን ተጣሉት:- የምነጠጣውን ውኃ ስጠን አሉት::..." ዘጸ 17፣1-6

 

"እግዚአብሔርም ሙሴን:- በሕዝቡ ፊት እለፍ፣ ከእስራኤል ሽማግሌዎች ከአንተ ጋር ውሰድ ወንዙንም የመታህበትን በትር በእጅህ ይዘሃት ሂድ:: እነሆ እኔ በዚያ በኮሬብ ዓለት ላይ በፊትህ እቆማለሁ ዓለቱንም ትመታለህ፣ ሕዝቡም ይጠጣ ዘንድ ከእርሱ ውኃ ይወጣል አለው::..." ዘጸ 17፣5-6

 

የእስራኤል ሕዝብ በተጠማበት ጊዜ ከጥማት የተነሣ ባንጎራጎሩበትና የውኃ ያለህ ባሉ ጊዜ እግዚአብሔር ከዓለት ውስጥ ውኃን አፍልቆ አጠጣቸው:: እግዚአብሔር ሙሴን:- "...ዓለቱንም ትመታለህ፣ ሕዝቡም ይጠጣ ዘንድ ከእርሱ ውኃ ይወጣል አለው::..." ዘጸ 17፣6 አዎን ዓለቱን ምታ ከእርሱም ሕዝቡን የሚያረካ ውኃ ይወጣል:: የተመታው ዓለት ውኃን ያፈልቃል:: የተመታው ዓለት ራሱ የሕይወት ውኃ ምንጭ ነው:: ጉድጓድና መቅጃ አያስፈልግም:: የተመታው ዓለት ይበቃል:: ስለተመታው ዓለት አዲስ ኪዳን ምን ይላል?

 

"ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፣ ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ ዓለት ጠጥተዋልና፣ ያም ዓለት ክርስቶስ ነበረ::" 1ኛ ቆሮ 10፣4

 

ያም ዓለት ክርስቶስ ነበረ:: ወገኔ ሆይ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ስለተመታ እውነተኛ የሕይወት ውኃ ከእርሱ ይወጣል::

 

     "ዓለቱንም ትመታለህ፣ ሕዝቡም ይጠጣ ዘንድ ከእርሱ ውኃ ይወጣል"

 

አዎን የተጠማ ሁሉ ይጠጣ ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ የሆነው ክርስቶስ ለአንተና ለእኔ ሲል በመስቀል ላይ ተመትቷል:: ተጠምተሃል ወይ? እንግዲህ እውነተኛ የሕይወት ውኃ ከጉድጓድ አይቀዳም፣ ከተመታው ዓለት ከኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ:: ዮሐ 7፣37

 

"በእውኑ አንተ ይህን ጉድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? ራሱም ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል አለችው::" ዮሐ 4፣12

 

     ኦ አንቺ ሴት የእግዚአብሔርን ስጦታ ብታውቂ ኖሮ! ጌታ እኔ እበልጣለሁ ወይም አልበልጥም ብሎ አልመለሰላትም፣ ነገር ግን ራሷ እንድትመዝነው ፍርዱን ተወላት::

 

"ኢየሱስም መልሶ:- ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደገና ይጠማል እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፣ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት::" ዮሐ 4፣13-14

 

     አንቺ ሴት እስኪ ራስሽ ፍረጅው፣ አባቶችሽ እነ ያዕቆብ ጠማኝ ስትያቸው የሰጡሽ የውሃ ጉድጓድ ነው:: ከውኃውም ብትጠጪ ደግመሽ ትጠሚያለሽ፣ ሰውንም ጠማኝ ብትዪው በመቅጃ ውኃ ይሰጥሽ ይሆናል:: ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ለዘላለም በውስጥሽ የሚፈልቅ ምንጭ ይሰጥሻል::ጥማትሽንም ለዘላለም ይቆርጣል:: የአባቶችሽ ጉድጓድ አላረካሽም፣ ቢያረካሽ ኖሮማ መቼ ትመላለሺ ነበር! አዎ መመላለስ ሰልችቶሻል "እንዳልጠማ ውኃም ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ ይህን ውኃ ስጠኝ..." ዮሐ 4፣15 ያልሽውም ለዚህ ነው:: ወንድሜ ሆይ፣ እንግዲህ ማናቸው ይበልጣል? የማያረካ ውኃ ወይስ የሕይወት ርካታን የሚሰጥ:: አንቺ ሴት እንግዲህ ማናቸው ይበልጣል? አባቶችሽ ወይስ የሚያነጋግርሽ? ኢየሱስ የሕይወትን ጥማት የሚያስታግስ ብቻ ሳይሆን የሕይወት ርካታ ሰጪ ነው::

 

     "...በእኔ የሚያምን ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም::" ዮሐ 6፣35

 

ምናልባት አንተም ርካታ ለማግኘት ብዙ ጉድጓዶችን ምሰህ ይሆናል፣ መቅጃህን ይዘህ ሰዎች ወደ ማሱትም ጉድጓዶች ተንከራትተህ ይሆናል:: ወደ ግራም ወደ ቀኝም ሄደህ ጥልቅ ጉድጓዶችን ሳይቀር የሕይወትን ርካታ ለማግኘት ደክመህ ይሆናል:: አንድ ነገር እነግርሃለሁ አንተም ሆንክ ሌላ ሰው የማሰው ጉድጓድ ፍጹም እረፍትና የነፍስ ርካታ አይሰጥህም:: ከተጠማህ ወደ ተመታው ዓለት መጥተህ ጠጣ:: ያም ዓለት የተሰቀለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው:: እርሱም ለተጠሙ ሁሉ ርካታን የሚሰጥ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው::

 

     "ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ"! ዮሐ 7፣37

 

"ኢየሱስ:- ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ነይ አላት:: ሴቲቱ መልሳ:- ባል የለኝም አለችው:: ኢየሱስ:- ባል የለኝም በማለትሽ መልካም ተናገርሽ፣ አምስት ባሎች ነበሩሽና፣ አሁን ከአንቺ ጋር ያለው ባልሽ አይደለም በዚህስ እውነት ተናገርሽ አላት::" ዮሐ 4፣16-18

 

     ለምን ይሆን ኢየሱስ ስለ ባሏ የጠየቃት? ይህቺ ሴት ብዙ የሕይወት ርካታ የፈለገችና የተጠማች ሳትሆን አትቀርም:: ምናልባት በትዳር ርካታ ይገኛል ብላ ከአንድም ሁለት ከሁለትም ሶስት አራትና አምስት ባሎች ያፈራረቀች፣ አሁንም ባሏ ካልሆነ ሰው ጋር የምትኖር፣ ሞክራ ሞክራም ያልረካች ሴት ሳትሆን አትቀርም:: ወገኔ ሆይ፣ አንተም ብዙ ሞክረህና ጥረህ ሊሆን ይችላል:: ምናልባት በትምህርት ርካታ አገኛለሁ ስትል ሳታገኝ፣ አንድ ባል፣ ሥራ ነው ብለህ ስትሞክር ሁለተኛ ባል፣ ትዳር ባገኝ በቃ ነፍሴ ትረካለች ብለህ ስትሞክር ሶስተኛ ባል፣ መጠጥና ሲጋራን ስትል አራተኛ ባል፣ ዝሙት አምስተኛ ባል አሁንም ከአንተ ጋር ያለው ስድስተኛው ምን እንደሆነ ባለማወቅም እርሱም ርካታን አይሰጥህም:: ትምህርትም፣ ትዳርም ሥራም መልካም ነው ርካታ ግን በክርስቶስ ብቻ ነው:: ኦ የእግዚአብሔርን ስጦታ ብታውቅ ኖሮ!

 

"ሴቲቱ:- ጌታ ሆይ አንተ ነብይ እንደ ሆንህ አያለሁ:: አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ እናንተም:- ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በእየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው:: ኢየሱስም እንዲህ አላት:- አንቺ ሴት፣ እመኚኝ፣ በዚህ ተራራ ወይም በእየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል:: እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን:: ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፣ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፣ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል::" ዮሐ 4፣19-24

 

     ሴትዮዋ ያልረካች ብቻ ሳትሆን በጥያቄም የተሞላች ብዙ መልስ የምትፈልግ፣ እንቆቅልሽ ያላት ናት:: ከአጠያየቋም እጅግ ግራ የተጋባች ትመስላለች:: አባቶቻችን በዚህ ሰገዱ እናንተ በኢየሩሳሌም ትሰግዳላችሁ:: እውነተኛው የመስገጃ ቦታ የት ነው? እያለች ግራ የገባትን ትጠይቃለች:: ዛሬም ብዙዎች የመስገጃው ቦታ የት ነው? እግዚአብሔር የሚገኝበት ስፍራ የት ነው? እያሉ ይጠይቃሉ:: አንተም ምናልባት ትጠይቅ ይሆናል:: የትኛው ነው ትክክለኛው ሃይማኖት? የት ነው እግዚአብሔር የሚገኘው? አባቶቻችን እዚህ ነው ይላሉ ሌሎች ደግሞ እዛ ነው ይላሉ፣ ግራ ተጋብቻለሁ እግዚአብሔርን የማገኘው የት ነው? አንድ ነገር እነግርሃለሁ:: በዚህም ወይም በዚያም እግዚአብሔርን አታገኘውም:: እግዚአብሔር መንፈስ ነውና:: የትኛውም ሃይማኖት ወደ እግዚአብሔር አያደርስህም:: ቁም ነገሩ እዚህ ወይም እዛ ሆኖ መስገዱ ሳይሆን ከልብ በእውነትና በመንፈስ እግዚአብሔርን መፈለጉ ነው:: ያባቶችህም የመስገጃ ስፍራ ሌላም የማምለኪያ ቦታ ቢሆን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር የመዳን መንገድ አይሆንህም፣ "መዳንም በሌላ በማንም የለም እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና::" ሐዋ 4፣12

 

"ሴቲቱ:- ክርስቶስ የሚባል መሢሕ እንዲመጣ አውቃለሁ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል አለችው:: ኢየሱስ:- የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ አላት::" ዮሐ 4፣25-26

 

     ከክርስቶስ በስተቀር ጥያቄሽንና እንቆቅልሽሽን ሊፈታ የሚችል ማነው? አዎን እርሱ ነው የጥያቄሽ ሁሉ መልስ፣ የእንቆቅልሽሽ ሁሉ ፍቺ፣ የነፍስሽ እረፍት፣ የጥማትሽ ርካታ! አዎን እርሱ ነው:: ግን አይተሽዋል ወይ? አንተስ ወገኔ አውቀኸዋል ወይ? አዎን እንቆቅልሽን የሚፈታ ጥያቄን የሚመልስ! ኦ የእግዚአብሔርን ስጦታ ብታውቂ ኖሮ! "ይሄ የምናገርሽ እርሱ እኔ ነኝ::" የሚናገርህ እርሱ ነው::

 

     "ሴቲቱም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ሄደች" ዮሐ 4፣28

 

ሴትዮዋም እንስራዋን ጥላ ሄደች:: ውኃ ልትቀዳ መጥታ መቅጃዋን ምን የሚያስጥል ነገር መጣ? ውኃ ባትቀዳ እንኳን እንስራዋን እንዴት ጥላ ትሄዳለች? እስከ ዛሬ ውኃ የምትይዝበትን የሚያስጥል ምን ነገር አገኘች? ወገኔ ሆይ፣ መቅጃን የሚያስጥል የህይወት ርካታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው:: የአባቶችን የማያረካ ጉድጓድ የሚያስጥል፣ ፍለጋን የሚያስቆም፣ ጥማትን የሚያረካ ኢየሱስ ብቻ ነው:: የሚያረካ ውኃ ፍለጋ ብዙ ጊዜ ተንከራትተህ ይሆናል፣  ትጠጣለህ ነገር ግን አትረካም:: እንደገና ርካታን ፍለጋ ትሄዳለህ፣ መቅጃህ ከእጅህ ሳይለይ ብዙ ጊዜ ሆኖህ ይሆናል:: ከጊዜያዊ ርካታ በስተቀር ነፍስህ እፎይ አላለችም:: ና ወደ ኢየሱስ የማያረካ ነገር የምትቀዳበትን እንስራህን ያስረሳሃል:: በጥማት የተንከራተተች ነፍስህን ያረካል:: እፎይ! ከእንግዲህ መቅጃ ለምኔ ትላለህ:: የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን::

 


“በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ ከፍ ከፍም ያደርጋችኋል።“
(የያዕቆብ መልእክት 4:10)

rss

Today's proverb

OR

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2017 by iyesus.com
Terms of use | Contact us