ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » ትምህርቶች » በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው? » የመረጥኩት ሰው...
Email this page to a friend Printer-friendly   Tuesday, 25 July 2017
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“ቸር ሰው ይራራል ያበድራልም፥ በፍርድም ነገሩን ይፈጽማል።“
(መዝሙረ ዳዊት 112:5)

rss

Today's verse

የመረጥኩት ሰው...

pdf version

     አንዳንድ ጊዜ በሕይወታችን እጅግ ከባድና የሚያሻማ ምርጫ ይኖርብናል:: ትክክለኛውን ከተሳሳተው ለይተን ካላወቅንና ካልመረጥን መጨረሻው እጅግ አስከፊና አሳዛኝ የሚሆንበት ጊዜ አለ:: ስለዚህ በመጨረሻ ከመቆጨታችን በፊት በምርጫችንና በውሳኔአችን ላይ አጥብቀን ልንጠነቀቅ ይገባል:: እውነተኛውን ወርቅ ከአርቴፊሺያሉ፣ እውነተኛውንም  ገንዘብ (እውነተኛ ካልሆነው) ለይተን ለመምረጥ የምንገደድበት ጊዜ ይኖራል::

 

     ወገኔ ሆይ፣ ምናልባት አርቴፊሺያል ወርቅ ተሳስተህ ብትገዛ ጉዳቱ ይህን ያህል ከባድ ላይሆን ይችላል:: የሕይወትህ ምርጫ የተሳሳተ ከሆነ ግን መጨረሻህ እጅግ የሚያሳዝንና የሚቆጭ ነው የሚሆነው:: ስለዚህ ትክክለኛውን የደህንነት መንገድ መምረጥና መያዝ ልናስብበት የሚገባን ዋና ጉዳይ ነው::

 

     ሰዎች ዛሬ በተለያዩ አሻሚ ምርጫዎች መካከል ተደነጋግረው ይገኛሉ:: ስለዚህ በተለያዩ የሕይወት መንገዶች መካከል ግድ መምረጥ ይኖርባቸዋል:: በዘመናት በዓለም ላይ ከእግዚአብሔር የተላክን ነብያት ነን፣ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ነን፣ የመዳንን መንገድ የምናሳያቸው እኛ ነን የሚሉ ብዙ የሃይማኖት መሪዎችና ነብያት ተነስተዋል:: በዚህም ሳቢያ ብዙዎች ግራ ሲጋቡ ይታያሉ:: መቼም የሚያብረቀርቅ ሁሉ ወርቅ እንዳይደለ፣ እንዲሁ ነብያትና የሃይማኖት መሪዎች ነን የሚሉ ሁሉ ከአንዱ ከእግዚአብሔር የተላኩ አይደሉም:: የሚናገሩትና የሚያስተምሩት የአንዱ ከሌላው እጅግ የሚለያይና የሚጋጭ መሆኑ ራሱ፣ ሁሉም ከአንድ አምላክ እንዳልተላኩ በግልጽ ያሳየናል:: ይህ ምርጫ ሁሉም ሐሰተኞች ናቸው ብለን የምንተወው ነገር አይደለም:: ወይም ሁሉም ትክክል ናቸው ተብሎም የሚደመደም ጉዳይ አይደለም:: አርቴፊሺያል ወርቅ ስላለ እውነተኛ የለም ማለት አይደለም:: የተሳሳተ ገንዘብ መኖሩም በእውነተኛው ብር ከመጠቀም እኛን አያግደንም:: ቁም ነገሩ ግን ትክክለኛውን ለይቶ ማወቁና መምረጡ ነው:: ስለዚህ በግዴታ በእግዚአብሔር እርዳታ ትክክለኛውን መምረጥ ይኖርብናል:: የተሳሳተ የሕይወት ምርጫና ውሳኔ እጅግ የሚያሳዝን ይሆናልና::

 

     ብዙዎች ከእግዚአብሔር የተላክን ነን ይላሉ እውነተኛው ግን ማነው? የእግዚአብሔር ቃል ራሱ፣ ነብይ ወይም የሃይማኖት መሪ ሁሉ ከእግዚአብሔር እንደማይላክ ነገር ግን ብዙ ሐሰተኞች ነብያትም እንዳሉ ያስጠነቅቀናል::

 

„የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነብያት ተጠንቀቁ::“ ማቴ 7፣15

 

     እንግዲህ እግዚአብሔር የላከው እውነተኛ የእግዚአብሔር መልዕክተኛ ማነው? በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ሊቆም የሚችል እውነተኛ በእግዚአብሔር የተመረጠ ማነው? እንዴት እውነተኛውን ከሐሰተኛው፣ በእግዚአብሔር የተላከውን ካልተላከው፣ የመዳንን መንገድ ከጥፋት መንገድ ለመለየት እንችላለን? መፈተኛውስ ምንድነው? የብዙዎቻቸን ጥያቄ ይሄ ነው::

 

     ወገኔ ሆይ፣ እስራኤላውያንም በምድረ በዳ ይህን የመሰለ ችግር ገጥሞአቸው ነበር:: ምንም እንኳን ለእስራኤል ሕዝብ ካህናት ይሆኑ ዘንድ፣ እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እያስታረቁ ያገለግሉ ዘንድ     እግዚአብሔር የመረጣቸው ከእስራኤል ነገድ ውስጥ የአሮንን ዘሮች ብቻ ቢሆንም ሌሎች ለዚህ ስራ ያልተመረጡና በእግዚአብሔርም ያልተሾሙ ሰዎችም ይህንን የክህነት አገልግሎት ሲፈልጉ እንመለከታለን:: በዚህም ህዝቡን ግራ ያጋቡታል:: እግዚአብሔር ሳይልካቸውና ሳይሾማቸው:- እኛም ከእግዚአብሔር የተላክን ካህናት ነን ብለው ይነሳሉ:: ወርቅስ በእሳት ይፈተናል፣ እውነተኛው ካህንና ከእግዚአብሔር የተላከው ግን በምን ይታወቃል?

 

     ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን! ለእግዚአብሔር የሚሳነው የለምና:: እግዚአብሔር ከነገዶች ሁሉ ለክህነት የመረጠውን ህዝቡ እንዲያውቁ እንዴት እንዳደረገና እውነተኛውን ከሐሰተኛው እንዴት እንደለየ ታውቃለህ? እያንዳንዱን ነገድ የሚወክል አንዳንድ በትር ከነገዶች አለቃ ወደ እርሱ እንዲያመጡ አዘዘ:: ከዚያም በአሥራ ሁለቱ በትሮች ላይ የአሥራ ሁለቱን የእስራኤል ነገድ ስሞች እንዲጽፉባቸው ካደረገ በኃላ በእርሱ ፊት እንዲያኖሯቸው አደረገ:: ከእስራኤልም ነገድ የተመረጠው ካህን የአሮን በትር በበትሮች መካከል ነበረች:: እግዚአብሔርም እንዲህ አላቸው::

 

„እንዲህም ይሆናል፣ የመረጥሁት ሰው በትር ታቆጠቁጣለች፣ በእናንተም ላይ የሚያጉረመርሙባችሁን የእስራኤልን ልጆች ማጉረምረም ከእኔ ዘንድ አጠፋለሁ::“ ዘኁ 17፣5

 

     ሕዝቡ ግራ በተጋባበት ወቅት እግዚአብሔር የሰጣቸው መፍትሔ እንዴት ድንቅ ነው:: የመረጥሁት ሰው በትር ታቆጠቁጣለች! ወገኔ ሆይ፣ እውነተኛውና ሐሰተኛው ካህን የሚለየው በዚህ ነው:: ከእግዚአብሔር የተላከውንና ያልተላከውን መለያ ይሄ ነው:: ደረቅ በትር በሚያቆጠቁጥበት ጊዜ፣ የሞተ እንጨት ሕይወት በሚዘራበት ጊዜ፣ ይህ ከእግዚአብሔር የተላከ ካህን ለመሆኑ ምልክት ነው:: ምንም እንኳን አሥራ ሁለቱም በትሮች፣ ቢተክሏቸው የማይበቅሉ ሕይወት የሌላቸው በድኖች ቢሆኑም ከእግዚአብሔር የሆነው ግን ይለመልማል::

 

"እንዲህም ሆነ፣ በነጋው ሙሴ ወደ ምስክሩ ድንኳን ውስጥ ገባ፣ እነሆም ለሌዊ ቤት የሆነች የአሮን በትር አቆጠቆጠች፣ ለመለመችም፣ አበባም አወጣች፣ የበሰለ ለውዝም አፈራች::" ዘኁ 17፣8

 

     ይህ ድንቅ ነገር አይደለም? የአሮን በትር አቆጠቆጠች:: በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል ሊቆም የተመረጠው ካህን የአሮን በትር ለመለመች:: የሞተ በድን በትር ሕይወት ዘርቶ አበበ ፍሬም አፈራ::

 

     ወገኔ ሆይ፣ በእግዚአብሔር የተመረጠውን ሰው ማወቅ ትፈልጋለህ? ለዓለም ሕዝብ ሁሉ መዳኛ የሆነውን በእግዚአብሔር የተሾመው ማን እንደሆነ ለማወቅ ትወዳለህ? በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለ የነፍስ ጠባቂና ታላቁን ካህን ከሌሎች ለይተህ ለማወቅ ትፈልጋለህ? ከሞተ በኋላ ሕይወት የሚዘራው እርሱ ነው:: አዎን በእግዚአብሔር የተመረጠው ሰው ከበድንነት በኋላ ሕያው የሚሆን፣ ከሞት በኋላ በትንሣኤ የሚነሣ፣ ሞትን አሸንፎ ለዘላለም በሕይወት የሚኖረው ነው:: እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው::

 

"...ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፣ ሞቼም ነበርሁ እነሆም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ::" ራእይ 1፣17-18

 

     ወገኔ ሆይ፣ ብዙ የሃይማኖት መረዎችና ብዙ ነብያት በምድር ላይ ተነስተዋል፣ ብዙ ሕዝብም ተከትሎአቸዋል:: ዛሬ ግን በሙሉ በድኖችና ሬሳዎች ናቸው:: ሕይወት የሌላቸው ሙታን ናቸው:: ወገኔ ሆይ፣ ኢየሱስም በአንድ ወቅት ከእነርሱ መካከል ነበረ:: "...የአሮንም በትር በበትሮቻቸው መካከል ነበረች::" ዘኁ 17፣6 ኢየሱስ ግን እንደሞተ አልቀረም:: እንደገና ሕያው ሆነ እንጂ:: ሌሎች እንደ ደረቁ በሙታን መቃብር ሲቀሩ እርሱ ግን ሞትን ድል አድርጎ በትንሣኤ ለመለመ:: ከዘላለም እስከ ዘላለም ሕያው ነው:: እንግዲህ እግዚአብሔር የመረጠው በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የተሾመው ብቸኛ ታላቅ ካህን ጌታ ኢየሱስ ነው::

 

     "የመረጥኩት ሰው በትር ታቆጠቁጣለች"!

 

     ሙሴ ከሕዝቡ ያመጣው ከእንደገና ሊያቆጠቁጡ የማይችሉና ፈጽመውም የደረቁ በትሮችን ነበር:: በነጋታው ሲመለስ ግን በእግዚአብሔር የተመረጠው ሰው በትር ከበትሮቹ መካከል ለምልማና አፍርታ ሕይወትም ዘርታ ነበር::

 

"እንዲህም ሆነ፣ በነጋው ሙሴ ወደ ምስክሩ ድንኳን ውስጥ ገባ፣ እነሆም፣ ለሌዊ ቤት የሆነች የአሮን በትር አቆጠቆጠች፣ ለመለመችም፣ አበባም አወጣች፣ የበሰለ ለውዝም አፈራች::" ዘኁ 17፣8

 

     በነጋው ሙሴ ያገኘው በበድኑ የአሮን በትር ፋንታ የለመለመ ሕያው በትር ነበረ:: የደረቀው እንጨት የለም! የሞተው በትር የለም! በምትኩ ሕያውና የለመለመ በትር እንጂ:: ወገኔ ሆይ፣ ወደ ኢየሱስ መቃብር ገና በማለዳ የሄዱት ሰዎች ያጋጠማቸው ይህን የሚመስል ሁኔታ ነበር::

 

"በሰንበትም መጨረሻ መጀመርያው ቀን ሲነጋ መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ:: ...መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው:- እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና እንደተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ::" ማቴ 28፣1-6

 

     ሲነጋ፣ ተሰቅሎ የሞተው ኢየሱስ የለም! ሲነጋ፣ የሞተው የኢየሱስ ሬሳ የለም:: ሲነጋ፣ ኢየሱስ እንደተናገረ ተነስቷልና::

 

     "የመረጥኩት ሰው በትር ታቆጠቁጣለች"!

 

     ብዙ ነብያትና የሃይማኖት መሪዎች በሞት ተሸንፈው እንደ ደረቀ በትር ዛሬም በመቃብር ይገኛሉ:: በእግዚአብሔር የተመረጠው ኢየሱስ ግን በእነርሱ መካከል አይገኝም:: እርሱ ሞትን ድል አድርጎ የተነሣ ለዘላለምም ሕያው ሆኖ የሚኖር በእግዚአብሔር የተመረጠ ብቸኛ ካህን እና የደኅንነት መንገድ ነውና::

 

"...ሕያውን በሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጉታላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም::" ሉቃ 24፣5

 

     ወገኔ ሆይ፣ ሕያው የሆነውን ኢየሱስን በሙታን መቃብር ከሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች ጋር ስለ ምን ትመድበዋለህ? እነርሱ በሚገኙበት በሙታን ሠፈር እርሱ የለም:: በትንሣኤ ከሙታን ተነሥቶ ለዘላለም ሕያው ሆኖ በእግዚአብሔር ቀኝ ይገኛል እንጂ:: በእግዚአብሔር የተመረጠው ያቆጠቁጣልና::

 

"ኢየሱስ:- ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፣ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል" ዮሐ 11፣25

 


“በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ ከፍ ከፍም ያደርጋችኋል።“
(የያዕቆብ መልእክት 4:10)

rss

Today's proverb

OR

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2017 by iyesus.com
Terms of use | Contact us