ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » ትምህርቶች » በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው? » በእኛ አደረ
Email this page to a friend Printer-friendly   Thursday, 17 August 2017
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“እንግዲህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ የዚህ ተስፋ ቃል ካለን፥ በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ።“
(2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7:1)

rss

Today's verse

በእኛ አደረ

pdf version

 

     አንድ ጊዜ ኢየሱስን ሊሰሙትና ከእርሱ ሊማሩ፣ ከበሽታቸውና ካለባቸው ስቃይ ሁሉ ነፃ ሊወጡ ወደ እርሱ ብዙ ሕዝብ ይቀርቡ ነበር:: ከእነዚህም ውስጥ የታወቁ ኃጢአተኞች ይገኙበት ነበር:: ጌታም እነዚህን ሲቀበላቸው፣ ከእነርሱም ጋር ሲበላና ሲጠጣ የዚያን ዘመን የሃይማኖት ሰዎች አይተው እርስ በርሳቸው አንገራገሩ "ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል፣ ከእነርሱም ጋር ይበላል" አሉ:: ሉቃ 15፣1-2 እስከ ዛሬ ድረስም የተለያዩ የሃይማኖት ተከታዮችን ወይም ሃይማኖተኞችን ግራ የሚያጋባቸውና የሚገርማቸው አንዱ ነገር ይሄ ነው:: እንዴት ታላቅ ነብይ በኃጢአተኞች መካከል ይቀመጣል? እንዴት የእግዚአብሔር ልጅ በተናቁ መካከል ያስተምራል? እንዴት ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ከኃጢአተኞች ጋር ይበላል? እንዴትስ ከእነርሱ ጋር ይጠጣል? ይሄ ነው እንግዲህ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጸውን አምላክ ከሌሎች አማልክቶች የሚለየው:: ለሰው አዕምሮ ከባድ የሆነውና ሊቀበለው የሚያስቸግረው፣ ዮሐንስም ደግሞ ሊገልጽልን የሚፈልገው ትልቅ ቁም ነገር ይህ ነው::

 

"ቃልም ሥጋ ሆነ ጸጋንና እውነትንም ተሞልቶ በእኛ አደረ፣ አንድ ልጅም  ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን::" ዮሐ 1፣14

 

     እጅግ የሚገርመው ነገር ቃል ከሁሉ በፊት ከእግዚአብሔር ጋር መኖሩና ሁሉ ነገር በእርሱ መፈጠሩ ብቻ አይደለም:: በጣም የሚያስደንቀው፣ ለብዙ የሃይማኖት ሰዎችም ግራ የሚያጋባውና ለመረዳት የሚከብደው፣ ይህ ራሱ አምላክ የሆነው ቃል (ኢየሱስ ክርስቶስ) ሥጋ መሆኑ ነው:: አምላክ እንዴት ሰው ይሆናል? እንዴት ሥጋ ይሆናል? እንዴትስ በኃጢአተኞች መካከል ይመላለሳል? የእግዚአብሔርን ፍቅር የተለየና ከመታወቅም በላይ የሚያደርገው አንዱ ነገር እንግዲህ ይህ ነው::

 

     ጌታ ኢየሱስ በወቅቱ ስለ ሁኔታው ተገርመው ሲያጉረመርሙ ለነበሩት ሃይማኖተኞች የመለሰላቸው በምሳሌ ነበር::

 

"መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፣ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ከእናንተ ማነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል፣ ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጎረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ:- የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላቸዋል:: እላችኋለሁ፣ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል::" ሉቃ 15፣3-7

 

እዚህ ላይ ጌታ:- እናንተ በግ ሲጠፋባችሁ የጠፋውን ለመፈለግ የሄደበት ድረስ ተከትላችሁ ትሄዱ የለምን? ራሱ ወደ ቤቱ አውቆ መምጣት ስለማይችል እናንተ ሁሉን ነገር ትታችሁ አንድ በግ ፍለጋ የምትሄዱ ከሆነ፣ እግዚአብሔርማ ከእርሱ የተለዩትንና እንደ በግ የተቅበዘበዙትን ስዎች ሊፈልግ ያሉበት ድረስ ቢመጣ ይህ ለምን ያስገርማችኋል ማለቱ ነበር::

 

"እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም!" ማቴ 12፣12

 

ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው እንዲሆንና ከሰዎች ጋር አብሮ እንዲኖር፣ እንዲበላና እንዲጠጣ፣ በመካከላቸው እየተመላለሰ ችግራቸውንና እንቆቅልሻቸውን ሁሉ እንዲፈታ ያደርገው እንግዲህ ይህ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ነው::

 

     እግዚአብሔርን በሌሎች ሃይማኖቶች ካሉ አማልክት የሚለየውም አንዱ ነገር ይሄ ነው:: ፍጥረትን ሁሉ ከፈጠረ በኋላ፣ በተመቻቸና በከበረ ቦታ፣ ችግር፣ መከራና ሥቃይ፣ ለቅሶና ሃዘን በሌለበት ስፍራ ራሱን ያስቀመጠና የሰው ልጆች ችግር የማይገባውና ስለ እነርሱም ግድ የማይሰጠው አይደለም:: እግዚአብሔር ሰዎች በለቅሶና በችግር፣ በሃዘንና በስቃይ ውስጥ ሆነው፣ እርሱ ግን ከላይ በተመቻቸ ቦታ ሆኖ ችግራቸውና ስቃያቸውን ሳያይ ትዕዛዝንና ፍርድን ብቻ የሚሰጥ አምላክ አይደለም:: ሲያጠፉ ብቻ እየተከታተለ የሚቀጣ፣ ነገር ግን ያሉበትን ችግር የማይረዳና የማይገባው ለእነርሱም መፍትሔ የማይሰጥ፣ ለቅሶአቸውንና ዕንባቸውን የማይመለከት አምላክ አይደለም:: ከሰው ልጆች ችግር ሁሉ ራሱን አግልሎ፣ በተደላደለ ቦታ የተቀመጠ አምላክ የለንም:: ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም አምላክና ፈጣሪ ቢሆንም የሰውን ልጆች ለመፈለግና ለችግራቸውም መፍትሔ ሊሆናቸው ራሱን ዝቅ አደረገ::

 

"እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም፣ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፣ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፣..." ፊል 2፣6-8

 

ብናውቅም ባናውቅም፣ ብንረዳም ባንረዳም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ታላቅና ልዩ ፍቅር አለው:: በቃላት ልንገልጸው የማንችለውና ከመታወቅም የሚያልፍ ጥልቅ ፍቅር:: ይህ ፍቅር ነው እግዚአብሔር ሰው ሆኖ የሰዎችን ችግር እንዲካፈልና መፍትሔ እንዲሆናቸው ያደረገው:: ይህ ፍቅር ነው ከከበረበት ሰማያዊና አምላካዊ ስፍራ ዝቅ አድርጎ ወደ ምድር እንዲመጣ አደረገው::

 

     በጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ወድቆ የተሰበረውን ሰው ከጉድጓዱ አፋፍ ላይ ሆኖ እንዴት እንደሚወጣ ብልሃትንና መመሪያን የሚሰጥ ሳይሆን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ በጉድጓድ ውስጥ ገብቶ የተሰበረውን ጠግኖና ተሸክሞ የሚያወጣ ነው:: አምላካችን ሕዝቡ በሚያልፍበት መንገድ ሁሉ አብሮ የሚካፈል የቅርብ እንጂ የሩቅ አምላክ አይደለም::

 

     "ቃልም ሥጋ ሆነ ጸጋንና እውነትንም ተሞልቶ በእኛ አደረ::"

ዮሐ 1፣14

 

     በዚህ ክፍል የኢየሱስ ክርስቶስን በእኛ መካከል መኖርና መመላለሱን ለማሳየት ዮሐንስ የተጠቀመው "በእኛ ኖረ" የሚለውን ሳይሆን "በእኛ አደረ" የሚለውን ቃል ነው:: "አደረ" (tabernacled among us) የሚለው ቃል፣ በግሪክ ቋንቋ ሰው ድንኳን ዘርግቶ (ተክሎ) ሲኖር (ሲያድር) ያለውን ዓይነት ትርጉም ነው ያለው:: ልክ በዚሁ አይነት አባባል በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ መካከል እንደሚኖር ሲገልጽ እንዲህ ይላል:-

 

"ማደሪያዬን በእናንተ መካከል አደርጋለሁ፣ ለፍሴም አትጸየፋችሁም:: በመካከላችሁም እሄዳለሁ፣ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፣ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ::" ዘሌ 26፣11-12

 

እግዚአብሔር በሕዝብ መካከል እንደሚኖር ሲገልጽ:- "ማደሪያዬን በእናንተ መካከል አደርጋለሁ" ይላል:: ማለትም በመካከላችሁ እኖራለሁ፣ አድራለሁ፣ እመላለሳለሁ፣ በእናንተ መካከል እሆናለሁ ማለቱ ነው:: በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ መካከል ለመኖር በመጀመሪያ የተጠቀመበት ድንኳን፣ የመገናኛ ድንኳን ወይም ማደርያ በመባል ይታወቃል::

 

"ደመናውም የመገናኛውን ድንኳን ከደነ፣ የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ሞላ:: ደመናውም በላዪ ስለነበር የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ስለ ሞላ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ይገባ ዘንድ አልቻለም::" ዘጸ 40፣34-35

 

እግዚአብሔር በዚያ ድንኳን ስለሚያድርና ሕዝቡም ችግርና ጥያቄ ሲኖረው እግዚአብሔርን ለመገናኘት የሚሻ ሁሉ ወደ ማደሪያው ስለሚሄድ ያ ድንኳን ማደሪያ ወይም የመገናኛ ድንኳን ይባል ነበር:: በተጨማሪም እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል የሚኖርበት የማደሪያው ድንኳንና የእግዚአብሔር ክብር እንደማይነጣጠሉና ማደሪያውም በእግዚአብሔር ክብር የተሞላ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል::

 

"...የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ስለ ሞላ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ይገባ ዘንድ አልቻለም::" ዘጸ 40፣35

 

ማደሪያው አንደኛ እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል የሚኖርበትና የሚመላለስበት እንዲሁም ጥያቄአቸውን ሁሉ የሚፈታበት ቦታ ነው:: በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በእግዚአብሔር ክብር የተሞላና፣ የእግዚአብሔር ክብር የሚታይበት ቦታ ነው::

 

     ዮሐንስ እንግዲህ በዮሐ 1፣14 ላይ ሊነግረን የሚሞክረው ነገር፣ ልክ በብሊይ ኪዳን እግዚአብሔር በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አድሮ በሕዝቡ መካከል ይመላለስና በማደሪያውም ክብሩን ይገልጽ እንደነበር፣ በአዲስ ኪዳንም ያ በመጀመሪያ የነበረው ቃል፣ ያ በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረውና ራሱም እግዚአብሔር የሆነው ቃል፣ ሥጋ ሆኖ በመካከላችን አደረ፣ ኖረ፣ ተመላለሰ እኛም የእግዚአብሔርን ክብር በእርሱ አየን ማለቱ ነው::

 

"ቃልም ሥጋ ሆነ ጸጋንና እውነትንም ተሞልቶ በእኛ አደረ፣ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን::"

ዮሐ 1፣14

 

ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነብይ ወይም አስተማሪ ወይም ፈዋሽ ብቻ ሳይሆን ራሱ እግዚአብሔር በሰዎች መካከል ማለት ነው:: ለዚህም ነው የኢየሱስ ክርስቶስ አንዱ ስም አማኑኤል የሚባለው::

 

"እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፣ ትርጓሜውም:- እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው::" ማቴ 1፣23

 

ነብያት በዘመናት ነበሩ፣ አስተማሪዎችና ተዓምራት አድራጊዎችም እንደዚሁ፣ ኢየሱስን ለየት የሚያደርገው፣ ከዓለም ፍጥረት በፊት የነበረውና የፍጥረት ሁሉ ምንጭ የሆነው፣ በማደሪያው ድንኳን አድሮ በሕዝቡ መካከል ሲመላለስ የነበረው እግዚአብሔር በአዲስ ኪዳን ሰው ሆኖ በሰው ልጆች መካከል መኖሩና እግዚአብሔር ራሱ ሕዝቡን ለመፈልግ በክርስቶስ ራሱን መግለጡ ነው:: እውነተኛው የእግዚአብሔር ማደሪያ ክርስቶስ ነውና::

 

"በእርሱ (በኢየሱስ) የመለኮት [የአምላክነት] ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራል::" ቆላ 2፣9

 

እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን በማደሪያው ወይም በመገናኛው ድንኳን ሆኖ በሕዝቡ መካከል በሚኖርበት ጊዜ:- "ነፍሴ አትጸየፋችሁም እኔም በመካከላችሁ እኖራለሁ" ብሎ ሕዝቡን ይናገር ነበር:: በችግራቸው ሁሉ እርሱ መልስ ይሆንላቸው ነበር:: የሚያስፈልጋቸውንም ይሰጣቸውና ያደርግላቸው ነበር:: በሚደርስባቸው ማናቸውም ችግርና መከራ፣ ስቃይና ሃዘን ሁሉ እየደረሰና ለእንቆቅልሻቸውም ሁሉ መፍትሄ እየሆነ በመካከላቸው ይኖርና ይመላለስ ነበር::

 

ልክ እንደዚሁ እግዚአብሔር በኢየሱስ ሆኖ በሰዎች መካከል እየተመላለሰ የሰዎችን ችግርና እንቆቅልሽ ሁሉ እየፈታ ይመላለስ ነበር:: ኢየሱስ በሄደበት ሁሉ ሃዘንና ለቅሶን ወደ ደስታ፣ ጨለማን ወደ ብርሃን፣ ሞትን ወደ ሕይወት እየለወጠ፣ ልባቸው የተሰበረውን እየጠገነ፣ ተስፋ የቆረጡትን አዲስ ተስፋ እየሰጠ፣ በአጋንንትና በበሽታ የታሰሩትን እየፈታ፣ ኃጢአተኞችንም ከእግዚአብሔር ጋር እያስታረቀና እየማረ፣ "...በአመድ ፋንታ አክሊልን፣ በለቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፣ በኅዘንም መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጎናጸፊያ..." እየሰጠ በሰዎች መካከል ተመላለሰ:: ኢሣ 61፣3

 

"ቃልም ሥጋ ሆነ ጸጋንና እውነትንም ተሞልቶ በእኛ አደረ::"

 

በችግረኞች መካከል አደረ:: በድውዮች መካከል አደረ፣ በሃዘንተኞች መካከል አደረ፣ ልባቸውም በተሰበረ መካከል አደረ:: እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ በሰዎች መካከል እየኖረ ለችግራቸው ሁሉ መፍትሄ ሆናቸው:: አምላካችን እግዚአብሔር ከሰዎች ለቅሶና ችግር ራሱን የሚያገልል አይደለምና::

 

     የት ነው እግዚአብሔር የሚገኘው? የት ነው ለመሆኑ እግዚአብሔር ሰዎችን የሚገናኘው? የት ነው ፍጹም መልስ ከእግዚአብሔር የምናገኘው? ወገኔ ሆይ፣ እግዚአብሔርን የምትፈልግ ከሆነ ወደ ኢየሱስ ቅርብ:: እግዚአብሔርና ሰው የሚገናኙበት ቦታ፣ የመገናኛው ድንኳን ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና:: እግዚአብሔር የሰዎችን ችግር የሚፈታበት፣ በመካከላቸው የሚኖርበትና የሚያድርበት፣ የማንነቱና የክብሩም መግለጫ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው:: ወደ ኢየሱስ የሚጠጋ ወደ እግዚአብሔር ይጠጋል:: ከኢየሱስም የሚርቅ ከእግዚአብሔር ይርቃል:: ኢየሱስን የሚያውቅ እግዚአብሔርን ያውቃል:: ኢየሱስንም ያየ እግዚአብሔርን አይቶአል::

 

     "...እኔን ያየ አብን አይቶአል" ዮሐ 14፣9

 

     ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ትፈልጋለህ? እግዚአብሔርን በጥልቀት ማወቅ ትፈልጋለህ? ማንነቱንና ክብሩን ማየት ትፈልጋለህ? እንግዲስ መጥተህ እይ!

 

ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ:- ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተናዋል አለው:: ናትናኤልም:- ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን? አለው:: ፊልጶስ:- መጥተህ እይ አለው::" ዮሐ 1 46፣47

 

    የምትነግረኝ በሙሉ እውነት ነውን? መጥተህ እይ! በእውነት የሰዎችን ጥያቄ እግዚአብሔር የሚመልሰው በኢየሱስ ነውን? መጥተህ እይ! የእግዚአብሔርስ ክብር መግለጫ እርሱ ነውን? መጥተህ እይ! ኢየሱስስ አማኑኤል ነውን? መጥተህ እይ!

 

    ምናልባት ስለ ኢየሱስ እንዲህ የመሰሉ ብዙ ጥያቄዎች ይኖሩህ ይሆናል:: እኔም እንደ ፊልጶስ የኢየሱስን ማንነት ራስህ በቅርበት እንድትመለከትና እንድታይ እጋብዝሃለሁ:: መጥተህ እይ!

 


“ለአንተ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም ይሆን ዘንድ፥ አምላክህም እግዚአብሔር ለዘላለም በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ ይረዝም ዘንድ፥ እኔ ዛሬ የማዝዝህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ጠብቅ።“
(ኦሪት ዘዳግም 4:40)

rss

Today's proverb

OR

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2017 by iyesus.com
Terms of use | Contact us