ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » ትምህርቶች » በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው? » ሲያያት በሕይወት ይኖራል
Email this page to a friend Printer-friendly   Tuesday, 25 July 2017
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“ቸር ሰው ይራራል ያበድራልም፥ በፍርድም ነገሩን ይፈጽማል።“
(መዝሙረ ዳዊት 112:5)

rss

Today's verse

ሲያያት በሕይወት ይኖራል

pdf version

     ወገኔ ሆይ፣ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ:- ታምመህ ታውቃለህ? በእርግጥ የበሽታን ምንነት በሕይወትህ ቀምሰህ ይሆን? መልስህ አዎን እንደሚሆን እገምታለሁ:: በሽታን የማታውቅ ከሆንክ ደግሞ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን:: በሽታ መልካም አይደለምና:: የሰውን ሙሉ ጤንነት እያናጋ፣ ሰዎች እንደሚገባው እንዳይኖሩና እንዳይሠሩ የሚያደርግ ትልቅ እንቅፋት ነው:: ብርታትን ወደ ድካም፣ ውፍረትን ወደ ክሳት፣ ደስታንም ወደ ሃዘን የሚለውጥ በመጨረሻም ለሞት የሚያበቃ ክፉ የሰዎች ጠላት ነውና::

 

     በአሁኑ ዘመን ግን ለብዙ በሽታዎች መድኃኒት ስላለ እግዚአብሔር ይመስገን:: ያለ መድኃኒት እንዴት እንሆን ነበር? ያለ መድኃኒትና ያለ እርዳታ እናቶች የልጆቻቸውን በሽታና ስቃይ እየተመለከቱ እንዴት ይሆኑ ነበር? የምንወዳቸው ወገኖቻችን በትንሹም በትልቁም በሽታ ሲሰቃዩና ሲረግፉ ማየት እንዴት ያሰቅቃል:: ዛሬም መድኃኒትና ሕክምና በሌለባቸው ቦታዎች፣ ሕጻናት ገና በለጋ እድሜያቸው በበሽታ ይቀጫሉ:: ሕክምናና መድኃኒት ባለማግኘት ሕይወታቸው የሚያልፈው የወጣቶችና የጎልማሶች ቁጥር ጥቂት አይደለም::

 

     ሕክምና ባለበት አካባቢ ግን የሰዎች እድሜ የረዘመና ሽማግሌዎችና አዛውንት የበዙበት ይሆናል:: ሕጻናት በጤንነት ሲጫወቱና ሲቦርቁ ማየት እንዴት ደስ ይላል:: ሰዎች ያለ ስቃይ ሲወጡና ሲገቡ በደስታም ሲመላለሱ ማየት እንዴት መልካም ነገር ነው::

 

     ነገር ግን መድኃኒት በሌለበት ቦታ መርዛም እባብ የነደፈው ሰው እንዴት ይሆናል? ሕይወቱንስ ያለ መድኃኒት እንዴት ሊያተርፍ ይችላል? የእባብ መርዝ ይገድላልና:: የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር እግዚአብሔር ካወጣቸው በኃላ በበረሃ ያጋጠማቸው አንዱ ክፉ ነገር ይሄ ነበር:: በእግዚአብሔር ላይ ስላመጹና ስላጉረመረሙ መርዛም የበረሃ እባቦች ሕዝቡን መንደፍ ጀመሩ:: በዚህም ምክንያት ከሕዝቡ ብዙዎች ሞቱ:: በእባቡ ተነድፎ ማን ሊድን? ነገር ግን ከተነደፉት ውስጥ ገና በሕይወት ያሉት ወደ ሙሴ መጥተው:- እግዚአብሔርንና አንተን በድለናልና እባክህን እባቦችን ከእኛ ያርቅልን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን አሉት:: ዘኁ 21፣5-7 ሙሴም ወደ እግዚአብሔር በጸለየ ጊዜ እግዚአብሔር ምን መልስ የሰጠው ይመስልሃል? በእባብ ተነድፎ በሕይወትና በሞት መካከል ላለ ሰው ምን መፍትሔ ይገኛል?

 

„እግዚአብሔርም ሙሴን:- እባብን ሠርተህ በዓላማ ላይ ስቀል የተነደፈውም ሁሉ ሲያያት በሕይወት ይኖራል አለው::“ ዘኁ 21፣8

 

     ምን ዓይነት መፍትሔ ነው እግዚአብሔር የሰጠው? ምን ዓይነትስ መድኃኒት ነው? እንደ ክኒን የማይዋጥ፣ እንደ መርፌ የማይወጋ፣ እንደ ሲሮፕ የማይጠጣ፣ ነገር ግን በዓይን ብቻ የሚታይ መድኃኒት! ሰዎቹ የተነደፉት በመርዛም እባቦች ነው:: ብዙዎቹም ሊሞቱ እያጣጣሩ ነው:: ታድያ በዓላማ ላይ የተሰቀለ የእባብ ምስል ከበሽታቸው ጋር ምን አገናኘው? ከፍ ባለ ቦታ ላይስ የተሰቀለ ምስል እንዴት መድኃኒት ሊሆን ይችላል? ያንንስ የተሰቀለ እባብ ማየት ወይስ አለማየት ምን ለውጥ ያመጣል? ወገኔ ሆይ፣ እጅግ ለውጥ ያመጣል::

 

„ሙሴም የናሱን እባብ ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ እባብም የነደፈችው ሰው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ::“ ዘኁ 21፣9

 

     የእግዚአብሔር ጥበብ እንዴት የሚገርም ነው! በበረሃም ስፍራ እግዚአብሔር ለእባብ መርዝ እንኳን መፍትሄ አለው:: ምንም መርዙ ገዳይ ቢሆንም የእግዚአብሔር መድኃኒት በሕይወት ያኖራል:: ብቻ ሕዝቡ አንድ ነገር ማድረግ ነበረበት:: ይሄውም ወደ ተሰቀለው የናስ ምስል መመልከት ነው:: ሕዝቡስ እሺ ብሎ መታዘዙ አያስገርምም? አንተስ በዚያ ቦታና ሁኔታ ብትሆን ያ የተሰቀለው የናስ እባብ ያድነኛል ብለህ ወደ እርሱ ትመለከት ይሆን? አላውቅም:: ብቻ እግዚአብሔር ያድናል ካለ ያድናል!

 

     ወገኔ ሆይ፣ አንተስ በእባብ ተነድፈህ ታውቅ ይሆን? ለሞት የሚያደርስስ መድኃኒት የሌለው በሽታ ይዞህ ይሆን? አንድ እውነት ግን አለ፣ ይሄውም የሰው ዘር በሙሉ በማይድን የኃጢአት በሽታ የተነደፈና የተያዘ ነው:: ለሥጋ ሞት ብቻ ሳይሆን ለአሰቃቂና ለዘላለማዊ ሞት የሚያደርስ ትልቁ የሰው ልጆች በሽታ! በዚህች ምድር ላይ በኃጢአት ያልታመመ አንድም ሰው የለም:: ነገር ግን ብዙዎች መታመማቸውን እንኳን አያውቁም:: ምናልባት ለሞት በሚያደርስ በሌላ ምድራዊ በሽታ አልታመምክ ይሆናል:: ነገር ግን ኃጢአት በሚባል ሰውን ከእግዚአብሔር ለይቶ ወደ ዘላለም ጥፋት በሚያደርስ በሽታ እንደተያዝክ እርግጠኛ ነኝ:: ቃሉ እንዲህ ይላልና:-

 

"ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፣ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም::" 1ዮሐ 1፣8

"...ልዩነት የለምና፣ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፣" ሮሜ 3፣22-23

 

ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም አንስቶ አሁን በዚህ ዘመን እስከምንኖር ድረስ እያንዳንዳችን በዚህ በሽታ የተያዝን ነን:: ወገኔ ሆይ፣ ይህ አንተንም ይጨምራል:: ለእኛስ ታድያ መድኃኒት ከየት ይምጣ? እኛስ እንደ እስራኤላውያን አይተነው እንድን ዘንድ እግዚአብሔር የሰጠን በዓላማ የተሰቀለ ነገር ምንድነው? ወገኔ ሆይ፣ ዛሬም ሊድን የማይችለውን የሰው ልጆችን የኃጢአት በሽታና መርዝ የሚያድን መድኃኒት እግዚአብሔር አዘጋጅቷል:: ዛሬም እግዚአብሔር ከጥፋት የሚያድን መድኃኒት አለው:: እርሱም በናስ የተሠራ እባብ ሳይሆን በእንጨት ላይ የተሰቀለው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው::

 

"ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ሊሰቀል ይገባዋል::" ዮሐ 3፣14-15

 

     ወገኔ ሆይ፣ ሰዎች አምነው ይድኑ ዘንድ እግዚአብሔር የሰጠው የዓለም መድኃኒት የተሰቀለው ኢየሱስ ነው:: ኃጢአት ወደ ዘላለም ጥፋትና ስቃይ የሚወስድ በሽታ ነው:: ስለዚህ አንተም በዓላማ የተሰቀለው የእግዚአብሔር መድኃኒት ያስፈልግሃል:: በናስ የተሠራውን እባብ አይተው የእስራኤል ሕዝብ በሕይወት እንደኖሩ፣ አንተም በተሰቀለው ኢየሱስ እመን በሕይወትም ትኖራለህ::

 

     ምናልባት የተሰቀለው ኢየሱስና የሰው ልጆች ኃጢአት ምን አገናኘው? እንዴትስ በእርሱ በማመን ብቻ ከጥፋት ድኜ የዘላለም ሕይወት አገኛለሁ? ትል ይሆናል:: ወገኔ ሆይ፣ እግዚአብሔር እይ ወደሚልህ እይ! እርሱ እመን በሚልህ እመን! እግዚአብሔር:- ያየ በሕይወት ይኖራል ካለ በሕይወት ይኖራል::

 

     "...የተነደፈውም ሁሉ ሲያያት በሕይወት ይኖራል"! ዘኁ 21፣8

 

     እንግዲህ በኃጢአት የተነደፈ ሰው ሁሉ አንድ ነገር ማድረግ አለበት:: ይሄውም በተሰቀለው ኢየሱስ ማመን ነው:: እንዲህ በየዋህነት የሚያደርግ ሁሉ በሕይወት ይኖራል::

 

"በልጁ (በኢየሱስ) የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም::" ዮሐ 3፣36

 

     ወገኔ ሆይ፣ በየዋህነት ሳትጠራጠር እንደ ሕጻናት በተሰቀለው ኢየሱስ እመን::

 

"...የእግዚአብሔርን መንግስት እንደ ሕጻን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትምና" ማር 10፣15

 

     ለኃጢአት መፍትሄና መድኃኒት ለማግኘት ወደ ተለያዩ ቦታዎች እየሄድክ አትድከም፣ የኃጢአት መድኃኒት በሰሜንም በደቡብም፣ በምስራቅም በምዕራብም አይገኝምና:: ነገር ግን ዓይኖችህን አንሳና በዓላማ ወደ ተሰቀለው የእግዚአብሔር መድኃኒት ተመልከት! በተሰቀለው ኢየሱስ የሚያምን ሁሉ በሕይወት ይኖራልና::

     የተነደፈውም ሁሉ ሲያያት በሕይወት ይኖራል!

 


“በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ ከፍ ከፍም ያደርጋችኋል።“
(የያዕቆብ መልእክት 4:10)

rss

Today's proverb

OR

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2017 by iyesus.com
Terms of use | Contact us