| መዝሙረ ዳዊት 119 |
| 1 | በመንገዳቸው ንጹሐን የሆኑ፥ በእግዚአብሔርም ሕግ የሚሄዱ ምስጉኖች ናቸው። |
| 2 | ምስክሩን የሚፈልጉ፥ በፍጹም ልብ የሚሹት ምስጉኖች ናቸው |
| 3 | ዓመፅንም አያደርጉም፥ በመንገዶቹም ይሄዳሉ። |
| 4 | ትእዛዛትህን እጅግ እንጠብቅ ዘንድ አንተ አዘዝህ። |
| 5 | ሥርዓትህን ለመጠበቅ መንገዶቼ ይቀኑ ዘንድ እወድድ ነበር። |
| 6 | ትእዛዝህን ሁሉ ስመለከት በዚያን ጊዜ አላፍርም። |
| 7 | አቤቱ፥ የጽድቅህን ፍርድ ስማር በቅን ልብ አመሰግንሃለሁ። |
| 8 | ሥርዓትህን እጠብቃለሁ በፍጹም አትጣለኝ። |
| 9 | ጕልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው። |
| 10 | በፍጹም ልቤ ፈለግሁህ፥ ከትእዛዝህ አታርቀኝ። |
| 11 | አንተን እንዳልበድል፥ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ። |
| 12 | አቤቱ፥ አንተ ቡሩክ ነህ ሥርዓትህን አስተምረኝ። |
| 13 | የአፍህን ፍርድ ሁሉ በከንፈሬ ነገርሁ። |
| 14 | እንደ ብልጥግና ሁሉ በምስክርህ መንገድ ደስ አለኝ። |
| 15 | ትእዛዝህን አሰላስላለሁ፥ መንገድህንም እፈልጋለሁ። |