| መጽሐፈ ምሳሌ 14 |
| 16 | ጠቢብ ሰው ይፈራል ከክፉም ይሸሻል ሰነፍ ግን ራሱን ታምኖ ይኰራል። |
| 17 | ቍጡ ሰው በስንፍና ይሠራል አስተዋይ ግን ይታገሣል። |
| 18 | አላዋቂዎች ሰዎች ስንፍናን ይወርሳሉ ብልሆች ግን እውቀትን እንደ ዘውድ ይጭናሉ። |
| 19 | ኃጢአተኞች በደጎች ፊት ይጐነበሳሉ፥ ኀጥኣንም በጻድቃን በር። |
| 20 | ድሀ በባልንጀራው ዘንድ የተጠላ ነው የባለጠጋ ወዳጆች ግን ብዙዎች ናቸው። |
| 21 | ባልንጀራውን የሚንቅ ይበድላል ለድሀ ግን የሚራራ ምስጉ ነው። |
| 22 | ክፉ የሚያደርጉ ይስታሉ ምሕረትና እውነት ግን መልካምን ለሚያደርጉ ናቸው። |
| 23 | በድካም ሁሉ ልምላሜ ይገኛል ብዙ ነገር በሚናገር ከንፈር ግን ድህነት ብቻ አለ። |
| 24 | የጠቢባን ዘውድ ባለጠግነታቸው ነው የሰነፎች ስንፍና ግን ስንፍና ነው። |
| 25 | እውነተኛ ምስክር ነፍሶችን ያድናል በሐሰት የሚናገር ግን ሸንጋይ ነው። |
| 26 | እግዚአብሔርን ለሚፈራ ጠንካራ መታመን አለው፥ ለልጆቹም መጠጊያ ይኖራል። |
| 27 | ሰው ከሞት ወጥመድ ያመልጥ ዘድን እግዚአብሔርን መፍራት የሕይወት ምንጭ ነው። |
| 28 | የንጉሥ ክብር በሕዝብ ብዛት ነው በሰው ጥቂትነት ግን የገዥ ጥፋት አለ። |
| 29 | ለትግሥተኛ ሰው ብዙ ማስተዋል አለው ቍጡ ግን ስንፍናውን ከፍ ከፍ ያደርጋል። |
| 30 | ትሑት ልብ የሥጋ ሕይወት ነው ቅንዓት ግን አጥንትን ያነቅዛል። |