| የማቴዎስ ወንጌል 5 |
| 1 | ሕዝቡንም አይቶ ወደ ተራራ ወጣ፤ በተቀመጠም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ |
| 2 | አፉንም ከፍቶ አስተማራቸው እንዲህም አለ፦ |
| 3 | በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። |
| 4 | የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መፅናናትን ያገኛሉና። |
| 5 | የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና። |
| 6 | ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና። |
| 7 | የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፥ ይማራሉና። |
| 8 | ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና። |
| 9 | የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና። |
| 10 | ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። |
| 11 | ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። |
| 12 | ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና። |
| 13 | እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። |
| 14 | እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። |
| 15 | መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። |