| ኦሪት ዘዳግም 31 |
| 16 | እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ እነሆ፥ ከአባቶችህ ጋር ትተኛለህ ይህም ሕዝብ ይነሣል፥ ይቀመጥባትም ዘንድ በሚሄድባት ምድር መካከል ያሉትን ሌሎችን አማልክት ተከትሎ ያመነዝራል፥ እኔንም ይተወኛል፥ ከእነርሱም ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን ያፈርሳሉ። |
| 17 | በዚያም ቀን ቍጣዬ ይነድድባቸዋል፥ እተዋቸውማለሁ፥ ፊቴንም እሰውርባቸዋለሁ፥ ለአሕዛብ መብል ይሆናሉ በዚያም ቀን፦ በእውነት እግዚአብሔር በእኛ መካከል የለምና ይህ ክፉ ነገር ሁሉ አገኘን እስኪሉ ድረስ ብዙ ክፉ ነገርና ጭንቀት ይደርስባቸዋል። |
| 18 | ሌሎችን አማልክት ተከትለዋልና ስላደረጉት ክፋት ሁሉ እኔ በዚያ ቀን ፈጽሜ ፊቴን እሰውራለሁ። |
| 19 | አሁንም ይህችን መዝሙር ለእናንተ ጻፉ፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተምሩአቸው ይህችም መዝሙር በእስራኤል ላይ ምስክር ትሆንልኝ ዘንድ በአፋቸው አድርጓት። |
| 20 | ለአባቶቻቸው ወደ ማልሁላቸው፥ ወተትና ማር ወደ ምታፈስሰው ምድር ካገባኋቸው በኋላ፥ ከበሉም ከጠገቡም ከደነደኑም በኋላ፥ ሌሎችን አማልክት ተከትለው ያመልካሉ፥ እኔንም ይንቃሉ፥ ቃል ኪዳኔንም ያፈርሳሉ። |
| 21 | ዛሬ ወደ ማልሁላቸው ምድር ገና ሳላገባቸው የሚያስቡትን አሳብ አውቃለሁና፥ ከልጆቻቸውም አፍ አትረሳምና ብዙ ክፉ ነገርና ጭንቀት በደረሰባቸው ጊዜ ይህች መዝሙር ምስክር ሆና በፊታቸው ትመሰክራለች። |
| 22 | ሙሴም በዚያ ቀን ይህችን መዝሙር ጻፈ፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተማራት። |
| 23 | የነዌንም ልጅ ኢያሱን፦ የእስራኤልን ልጆች ወደ ማልሁላቸው ምድር ታገባለህና ጽና፥ አይዞህ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ ብሎ አዘዘው። |
| 24 | እንዲህም ሆነ ሙሴ የዚህን ሕግ ቃሎች በመጽሐፍ ከጻፈ ከፈጸመም በኋላ፥ |
| 25 | ሙሴ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት የሚሸከሙትን ሌዋውያንን እንዲህ ብሎ አዘዘ፦ |
| 26 | ይህን የሕግ መጽሐፍ ውሰዱ፥ በዚያም በእናንተ ላይ ምስክር እንዲሆን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት አጠገብ አኑሩት። |
| 27 | እኔ ዓመፃችሁንና የአንገታችሁን ድንዳኔ አውቃለሁና እኔም ዛሬ ከእናንተ ጋር ገና በሕይወት ሳለሁ እናንተ በእግዚአብሔር ላይ ዐምፃችኋል ይልቁንስ ከሞትሁ በኋላ እንዴት ይሆናል? |
| 28 | ይህን ቃል በጆሮአቸው እናገር ዘንድ፥ ሰማይንና ምድርንም አስመሰክርባቸው ዘንድ የነገዶቻችሁን ሽማግሌዎች ሁሉ አለቆቻችሁንም ሰብስቡልኝ |
| 29 | ከሞትሁ በኋላ ፈጽማችሁ እንድትረክሱ፥ ካዘዝኋችሁም መንገድ ፈቀቅ እንድትሉ አውቃለሁና። በእጃችሁም ሥራ ታስቈጡት ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ስላደረጋችሁ በኋለኛው ዘመን ክፉ ነገር ያገኛችኋል። |
| 30 | ሙሴም በእስራኤል ጉባኤ ሁሉ ጆሮ የዚህች መዝሙር ቃሎች እስኪፈጸሙ ድረስ ተናገረ። |