| ኦሪት ዘዳግም 4 |
| 1 | አሁንም፥ እስራኤል ሆይ፥ እንድታደርጉአቸው በሕይወትም እንድትኖሩ፥ የአባቶቻችሁም አምላክ እግዚአብሔር ወደሚሰጣችሁ ምድር ገብታችሁ እንድትወርሱ፥ የማስተምራችሁን ሥርዓትና ፍርድ ስሙ። |
| 2 | እኔ ያዘዝኋችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትጠብቃላችሁ እንጂ ባዘዝኋችሁ ቃል ላይ አትጨምሩም፥ ከእርሱም አታጎድሉም። |
| 3 | ብዔልፌጎርን የተከተሉትን ሰዎች ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ከመካከላችሁ እንዳጠፋ፥ እግዚአብሔር በብዔልፌጎር ያደረገውን ዓይኖቻችሁ አይተዋል። |
| 4 | እናንተ ግን አምላካችሁን እግዚአብሔርን የተከተላችሁ እስከ ዛሬ ድረስ ሁላችሁ በሕይወት ትኖራላችሁ። |
| 5 | እነሆ፥ እናንተ ገብታችሁ በምትወርሱአት ምድር ውስጥ እንዲህ ታደርጉ ዘንድ አምላኬ እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ ሥርዓትንና ፍርድን አስተማርኋችሁ። |
| 6 | ጠብቁአት አድርጉአትም ይህችን ሥርዓት ሁሉ ሰምተው። በእውነት ይህ ታላቅ ሕዝብ ጠቢብና አስተዋይ ሕዝብ ነው በሚሉ በአሕዛብ ፊት ጥበባችሁና ማስተዋላችሁ ይህ ነውና |
| 7 | አምላካችን እግዚአብሔር በምንጠራው ጊዜ ሁሉ እንደሚቀርበን፥ አምላኩ ወደ እርሱ የቀረበው ታላቅ ሕዝብ ማን ነው? |
| 8 | በዓይናችሁ ፊት ዛሬ እንደማኖራት እንደዚህች ሕግ ሁሉ ጽድቅ የሆነች ሥርዓትና ፍርድ ያለው ታላቅ ሕዝብ ማን ነው? |
| 9-10 | እግዚአብሔር፦ ሕዝቡን ወደ እኔ ሰብስብ፥ በምድርም በሕይወት በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ እኔን መፍራት ይማሩ ዘንድ፥ ልጆቻቸውንም ያስተምሩ ዘንድ ቃሌን አሰማቸዋለሁ ብሎ በተናገረኝ ጊዜ፥ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት በኮሬብ በቆምህበት ቀን ዓይኖችህ ያዩትን ነገር እንዳትረሳ፥ በሕይወትህም ዘመን ሁሉ ከልብህ እንዳይወድቅ ተጠንቀቅ፥ ነፍስህንም በትጋት ጠብቅ ለልጆችህም ለልጅ ልጆችህም አስታውቀው። |
| 11 | እናንተም ቀርባችሁ ከተራራው በታች ቆማችሁ ነበር እስከ ሰማይም መካከል ድረስ አሳት በተራራው ላይ ይነድድ ነበር ጨለማና ደመና ድቅድቅ ጨለማም ነበረ። |
| 12 | እግዚአብሔርም በእሳት ውስጥ ሆኖ ተናገራችሁ የቃልን ድምፅ ሰማችሁ፥ መልክ ግን አላያችሁም ድምፅን ብቻ ሰማችሁ። |
| 13 | ታደርጉትም ዘንድ ያዘዛችሁን ቃል ኪዳን አሥሩን ቃላት ነገራችሁ በሁለቱም በድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው። |
| 14 | ትወርሱአት ዘንድ ተሻግራችሁ በምትገቡባት ምድር የምታደርጉአትን ሥርዓትና ፍርድ አስተምራችሁ ዘንድ እግዚአብሔር በዚያን ጊዜ አዘዘኝ። |
| 15 | እግዚአብሔር በኮሬብ በእሳት ውስጥ ሆኖ በተናገራችሁ ጊዜ መልክ ከቶ አላያችሁምና እጅግ ተጠንቀቁ |
| 16 | እንዳትረክሱ፥ የተቀረጸውን ምስል የማናቸውንም ነገር ምሳሌ፥ በወንድ ወይም በሴት መልክ የተሠራውን፥ |