| መጽሐፈ መሣፍንት 14 |
| 1 | ሶምሶንም ወደ ተምና ወረደ፥ በተምናም ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አየ። |
| 2 | ወጥቶም ለአባቱና ለእናቱ። በተምና ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አይቻለሁ አሁንም እርስዋን አጋቡኝ አላቸው። |
| 3 | አባቱና እናቱም። ካልተገረዙት ከፍልስጥኤማውያን ሚስት ለማግባት ትሄድ ዘንድ ከወንድሞችህ ሴቶች ልጆች ከሕዝቤም ሁሉ መካከል ሴት የለምን? አሉት። ሶምሶንም አባቱን፦ ለዓይኔ እጅግ ደስ አሰኝታኛለችና እርስዋን አጋባኝ አለው። |
| 4 | እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያን ላይ ምክንያት ይፈልግ ነበርና ነገሩ ከእርሱ ሆነ አባቱና እናቱ ግን አላወቁም። በዚያን ጊዜም ፍልስጥኤማውያን በእስራኤል ላይ ገዦች ነበሩ። |
| 5 | ሶምሶንም አባቱና እናቱም ወደ ተምና ወረዱ፥ በተምናም ወዳለው ወደ ወይኑ ስፍራ መጡ እነሆም፥ የአንበሳ ደቦል እያገሣ ወደ እርሱ ደረሰ። |
| 6 | የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ በኃይል ወረደ ጠቦትን እንደሚቆራርጥ በእጁ ምንም ሳይኖር ቈራረጠው ያደረገውንም ለአባቱና ለእናቱ አልነገረም። |
| 7 | ወርዶም ከሴቲቱ ጋር ተነጋገረ እጅግም ደስ አሰኘችው። |
| 8 | ከጥቂትም ቀን በኋላ ሊያገባት ተመለሰ፥ የአንበሳውንም ሬሳ ያይ ዘንድ ከመንገድ ፈቀቅ አለ እነሆም፥ በአንበሳው ሬሳ ውስጥ ንብ ሰፍሮበት ነበር፥ ማርም ነበረበት። |
| 9 | በእጁም ወስዶ መንገድ ለመንገድ እየበላ ሄደ ወደ አባቱና ወደ እናቱ መጣ፥ ማሩንም ሰጣቸው፥ እነርሱም በሉ ማሩንም ከአንበሳው ሬሳ ውስጥ እንደ ወሰደ አልነገራቸውም። |
| 10 | አባቱም ወደ ሴቲቱ ወረደ ጎበዞችም እንዲህ ያደርጉ ነበርና ሶምሶን በዚያ በዓል አደረገ። |
| 11 | ባዩትም ጊዜ ከእርሱ ጋር ይሆኑ ዘንድ ሌሎች ሠላሳ ሰዎች ሰጡት። |
| 12 | ሶምሶንም። እንቆቅልሽ ልስጣችሁ በሰባቱም በበዓሉ ቀኖች ውስጥ ፈትታችሁ ብትነግሩኝ፥ ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ልውጥ ልብስ እሰጣችኋለሁ |
| 13 | መፍታትም ባትችሉ ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ልውጥ ልብስ ትሰጡኛላችሁ አላቸው። እርሱም፦ እንድንሰማው እንቆቅልሽህን ንገረን አሉት። |
| 14 | እርሱም፦ ከበላተኛው ውስጥ መብል ወጣ፥ ከብርቱም ውስጥ ጥፍጥ ወጣ አላቸው። ሦስት ቀንም እንቈቅልሹን መተርጎም አልቻሉም። |
| 15 | በአራተኛውም ቀን የሶምሶንን ሚስት። እንቈቅልሹን እንዲነግረን ባልሽን ሸንግዪው፥ አለዚያም እንቺንና የአባትሽን ቤት በእሳት እናቃጥላለን ወደዚህ ጠራችሁን ልትገፉን ነውን? አሉአት። |