ጳውሎስ በዚህ ክፍል ሊናገር የፈለገው ልክ በገላትያ 3፥13 "ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ" እንደሚለው አይነት አባባል ይመስለኛል። ክርስቶስ እኛን ለመዋጀት የእኛን ኃጢአት መሸከም ነበረበት። በመስቀል ላይ የተሸከመው ኃጢአት ግን እርሱ ራሱ የሠራው አይደለም። ኃጢአትን የሚያደርግ ኃጢአተኛ ነው፤ የሌሎችን ኃጢአትን ግን የሚሸከም ምን ይባላል። ጳውሎስ እንግዲህ እግዚአብሔር ክርስቶስን ኃጢአተኛ አደረገው ሊል ስለማይችል ኃጢአት እንዳላደረገ ነገር ግን የእኛን ኃጢአት እንደተሸከመ ለማሳየት የተጠቀመበት አገላለጽ ነው።
በተመሳሳይ ሁኔታ ክርስቶስ እኛን ከህግ እርግማን ሊዋጀን እርግማን እንደሆነ ገላትያ 3፥13 ላይ ይናገራል። በራሱ ሥራ ርግማን የሚገባው ሰው የተረገመ ነው። ክርስቶስ ግን የሰዎችን እርግማን ተሸከመ እንጂ የተረገመ ግን አይደለም። ስለዚህም በተመሳሳይ ሁኔታ ጳውሎስ ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆነ ነው የሚለው።
Quote:
3፥13 በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤
እነዚህ ሁሉ የቃላት አገላለጾች እንጂ ዋናው መልእክቱ ያው በመጽሐፍ ቅዱስ ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ ሲነገር የነበረው የክርስቶስ በእኛ ፈንታ የተቀበለው የእኛን በደልና ኃጢአት፤ እግማንና ቅጣትን የሚያሳይ ነው። እርሱ ባልሠራው ኃጢአት የእኛን ኃጢአት እንደተሸከመ፤ እኛም እንደዚሁ ባልሠራነው ጽድቅ የእርሱን ጽድቅ ተቀብለናል።