ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » ጥያቄና መልስ
Email this page to a friend Printer-friendly   Thursday, 23 May 2013
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

በሮሜ 1፡ 16 ላይ በወንጌል አላፍርም ሲል ምን ማለቱ ነው;

10 ወራቶች በፊት መንፈሳዊ ስም-አልባ የተጠየቀ

1 መልስ

0 ድምጾች
እኛ በአሁኑ ዘመን የምንኖር ሰዎች፤ እነ ጳውሎስ በኖሩበት ዘመን የተሰቀለ መሲህ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ብዙም ላይገባን ይችላል። ነገር ግን በዚያን ዘመን በመስቀል የሚሰቀል ሰው እጅግ ወንበዴና ወሮበላ ወይም ዓመጸኛ ሰው ነው። እንዲያውም የሮም ዜግነት ያለው ማንኛውንም ሰው በመስቀል መቅጣት የተከለከለ ነበር። ምክንያቱም ሰውነቱ ተገርፎ እርቃኑን በሰው ሁሉ ፊት ተዋርዶ መሞት በጣም የውርደትም ውርደት ሞት ነበርና። እጅግም አሳፋሪ ነበር። እንዲያውም በአብዛኛው በዚህ ቅጣት ይቀጡ የነበሩት ከሰው በታች ናቸው ተብለው የሚታዩ ባሪያዎች ነበሩ (በዚያን ዘመን ባሮች በአብዛኛዎቹ ጀርመኖች፣ አይሁዶች፣ እንግሊዞች፣ ግሪኮች ወዘተ ነበሩ)። ስለዚህም ሮማውያን የመስቀልን ቅጣት "የባሪያ ቅጣት" ወይም በላቲን "supplicium servile" ብለው ይጠሩት የነበረው። የመስቀል ቅጣት ለጨዋ ልጆች (ባሪያ ያልሆኑ) የማይገባ አሰቃቂና አዋርጅ ቅጣት ነበር። የባሪያም ቅጥት ስለነበር ነው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 2፡7-8 ላይ ኢየሱስ "የባሪያን መልክ" እንደያዘና "ለመስቀል ሞት እንኳን" እንደታዘዘ የሚናገረው። በመስቀል መሞት ከሰው በታች እንደሆኑ የሚታዩትን የባሪያዎችን ቅጣት መቀጣትና የባሮችን ሞት መሞት ነውና።

ስለዚህም የተሰቀለ የሃይማኖት መሪ አለኝ የሚል ሰው እንደ እብድ ነበር በአህዛብ ዘንድ የሚታየው፤ ይባስ ብሎም ከሞት ተነስቶአል ማለት ደግሞ የለየለት እብደት ነበር። በተለይ ዘመኑ የግሪክ እውቀትና ፍልስፍና እየተስፋፋ የሄደበት ዘመን ስለነበር፤ እንዲህ ያለ የሴቶች ወሬና ርባና የሌለው ተረት ተረት የሚመስል ታሪክ እንደ ቅዥት ይታይ ነበር። ለዚህም ነው ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮ 1፡18-31 ላይ የተሰቀለው ክርስቶስ በአህዛብ ዘንድ ሞኝነት እንደሆነና ምን ያህል የሰው ጥበብን ደግሞ እግዚአብሔር ሞኝ በሆነ ነገር ሊያሳፍር እንደፈለግ የሚናገርው።
Quote:
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1
18 የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።
19 የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና።
20 ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን?
21 በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና።
22 መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥
23 እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው
24 ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው።
...

እዚህ ከላይ ቁጥር 23 ላይ "ለአሕዛብም ሞኝነት ነው" የሚለው ቃል ወደ እብደት የሚጠጋ ሞኝነትንም ነው የሚያሳየው። ጨርሶ ትርጉም የማይሰጥ absurd ወይም nonsense ወይም madness የሆነ ነገር ነው ማለታቸው ነው። ራሱን ሊያድን ያልቻለ ወንበዴና ወሮበላ እግዚአብሔር የመረጠውና ሰዎች ሁሉ ሊድኑበት የሚችሉበት መፍትሔ ነው ብሎ መናገር እጅግ አሳፋሪ ነበር። ይባስ ብሎም የግሪክ ፍልስፍና በተስፋፋበት ዘመን ይሄን እንደ ወንበዴና ወሮበላ በሰው ፊት እርቃኑን ተዋርዶ የሞተን ሰው እግዚአብሔር ከሙታን አስነሳው ማለት ጭራሽ ጨርቅ መጣል ነበር።
Quote:
የሐዋርያት ሥራ 17
32 የሙታንንም ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኵሌቶቹ አፌዙበት፥ እኵሌቶቹ ግን። ስለዚህ ነገር ሁለተኛ እንሰማሃለን አሉት።

በአይሁድም ዘንድ ቢሆን በእንጨት የሚሰቀል የተረገመ ነው ተብሎ በብሉይ ኪድን ስለ ተጻፈ፤ የሚሰቀል መሲህ ማለት እግዚአብሔር የተጣላውና የቀጣው ሰው እንጂ እግዚአብሔር የሚወደው ሰው ተደርጎ አይወሰድም ነበር።
Quote:
ኦሪት ዘዳግም
21፥23 በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና ሬሳው በእንጨት ላይ አይደር ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ የሰጠህን ምድር እንዳታረክስ በእርግጥ በዚያው ቀን ቅበረው።

ከኢየሱስ በፊትም ይሁን በኋላ አንዳንድ የአይሁድ መሲሆች ነን ባዮች ተነስተው ነበር። ነገር ግን ሮማውያን ሲሰቅሏቸው ወይም ሲገድሏቸው የሚከተላቸው ሁሉ ነበር የሚተዋቸው፤ ምክንያቱም ተሰቅለው መሞታቸው ራሱ በእግዚአብሔር የተረገሙ እንጂ መሲህ እንዳልሆኑ የሚያሳይ ምልክት ነበርና። ለዚህም ነው ገማልያል በፈሪሳውያን ሸንጎ መሲህ ነኝ ይሉ የነበሩ ሰዎችን ጠቅሶ፤ ሃዋርያትን እንዲተዋቸው የተናገረው።
Quote:
የሐዋርያት ሥራ 5
34 ነገር ግን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ በሸንጎ ተነሥቶ ሐዋርያትን ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው አዘዘ፥
35 እንዲህም አላቸው፦ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ስለ እነዚህ ሰዎች ምን እንደምታደርጉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።
36 ከዚህ ወራት አስቀድሞ ቴዎዳስ፦ እኔ ታላቅ ነኝ ብሎ ተነሥቶ ነበርና፥ አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተባበሩ፤ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበተኑ እንደ ምናምንም ሆኑ
37 ከዚህ በኋላ ሰዎች በተጻፉበት ዘመን የገሊላው ይሁዳ ተነሣ ብዙ ሰዎችንም አሸፍቶ አስከተለ፤ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበታተኑ

38 አሁንም እላችኋለሁ። ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤
39 ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፥ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ።

ስለዚህ ነው እንግዲህ ኢየሱስ መሲህ እንዳልሆነ ተከታዮቹ ሁሉ እንዲያውቁ የአይሁድ ካህናት አለቆችና መሪዎች የግድ እንዲሰቀል የፈለጉት፤ ምንም እንኳን ጲላጦስ ገፍሮ ብቻ ሊተወው ቢያስብም፤ እነርሱ የግድ እንዲሰቀል የፈለጉበትም ምክንያት፤ መስቀል ኢየሱስ መሲህ እንዳልሆነና እግዚአብሔርም እንዳላዳነው የሚያሳይ ተከታዮቹን መበተኛ ግልጽ መሳሪያ ስለነበር ነው። ኢየሱስ ከመሰቀሉ በፊትም ይሁን በመስቀል ላይ እያለም አይሁዶችም ይሁን ሮማውያን ወታደሮች የሚያሾፉበትም ለዚህ ነው። እግዚአብሔር ከወደደህ እስቲ ያድንህ፤ እስቲ መሲህ ከሆንክ ከመስቀል ወረዳ ወዘተ እያሉ የሚያሾፉበት የነበረው።

ባጠቃላይ በዚያን ዘመን በመስቀል ዙሪያ የነበረውን የአይሁድንም ይሁን የአህዛብን መረዳት ስንመለከት በመስቀል ተሰቅሎ እርቃኑን የተዋረደን ሰው እንደ ጌታና የዓለም መድሃኒት አድርጎ መስበክ ማፌዣና መቀለጃ መሆን ነው።

እንግዲህ ይህንን የታሪክ ጀርባና ዓውድ ስንመለከት ነው ጳውሎስ በወንጌል አላፍርምና ብሎ የሚናገረው ቃል ይበልጥ ትርጉም የሚሰጠን። ምንም እንኳን በአይሁድም ይሁን በአህዛብ ዘንድ እንደ እብደትና ሞኝነት ወዘተ ቢቆጠረም፤ ወንጌል ግን ሰዎችን የሚያድን ሃይል ነው፤ ስለዚህ ወንጌልን ለመስበክ አላፍርበትም እያለ ነው ጳውሎስ። አዎ የሚያሳፍር ነው የሚመስለው ሆኖም እኔ አላፍርበትም፤ ሰውን የሚያድን ሃይል ስለሆነ እያለ ነው።
Quote:
ወደ ሮሜ ሰዎች 1
14 ለግሪክ ሰዎችና ላልተማሩም፥ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉም ዕዳ አለብኝ፤
15 ስለዚህም በሚቻለኝ መጠን በሮሜ ላላችሁ ለእናንተ ደግሞ ወንጌልን ልሰብክ ተዘጋጅቼአለሁ።
16 በወንጌል አላፍርምና፤ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው፥ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና።
10 ወራቶች በፊት ስም-አልባ የተመለሰ

የተዛመዱ ጥያቄዎች

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2013 by iyesus.com
Terms of use | Contact us