ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » ጥያቄ መጠያየቂያ
Email this page to a friend   Friday, 4 December 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ፥ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።“
(መዝሙረ ዳዊት 27:14)

rss

Today's verse

ተአምራዊ ፈውስ ሁሉ ምንጩ እግዚአብሔር ነውን?

ተአምራዊ ፈውስ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እንደሚደረግ ይሰማል። እውነታው ምንድነው? ፈውስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነውን?

አመሰግናለሁ
Aug 13, 2013 መንፈሳዊ ኦፍቲ (1,250 ነጥቦች) የተጠየቀ

3 መልሶች

0 ድምጾች
በዘመናችን ‘ተአምራዊ ፈውስ’ የሚከናወነው በአምላክ ኃይል ነው?


በአንዳንድ አገሮች፣ ሃይማኖተኛ የሆኑ ሰዎች “በማይድን” በሽታ የተያዙ ብዙዎች ፈውስ እንዳገኙባቸው ወደሚታሰቡ ቅዱስ ስፍራዎች ሲጓዙ ማየት የተለመደ ነው። በሌሎች አገሮችም፣ መለኮታዊ ኃይል በመጠቀም በሽተኞችን እንደሚፈውሱ የሚናገሩ ሰዎች አሉ። በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ በአንዳንድ መንፈሳዊ ፕሮግራሞች ላይ፣ የታመሙ ሰዎች ፈውስ እንዳገኙ በመናገር ከተሽከርካሪ ወንበራቸው ላይ ተነስተው ሲዘሉ አሊያም ምርኩዛቸውን ሲወረውሩ ይታያሉ።


እንዲህ ያሉትን ፈውሶች የሚያከናውኑት ሰዎች በአብዛኛው ሃይማኖታቸው የተለያየ ነው፤ ብዙውን ጊዜም አንዳቸው ሌላውን ከሃዲ፣ ሐሰተኛና አረማዊ እንደሆነ አድርገው ይመለከታሉ። በመሆኑም ‘አምላክ እርስ በርስ በሚቃረኑ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ተጠቅሞ ተአምር ይሠራል?’ የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ፣ “እግዚአብሔር የሰላም አምላክ እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 14:33) ታዲያ እንዲህ ያሉት ‘ተአምራዊ ፈውሶች’ የሚከናወኑት በእርግጥ በአምላክ ኃይል ነው? ፈውስ የሚያከናውኑ አንዳንድ ሰዎች ይህን የሚያደርጉት በኢየሱስ ኃይል እንደሆነ ይናገራሉ። እስቲ ኢየሱስ ሰዎችን እንዴት እንደፈወሰ እንመልከት።


ኢየሱስ ሰዎችን የፈወሰው እንዴት ነበር?


ኢየሱስ በሽተኞችን የፈወሰው በዘመናችን ፈውስ ከሚያከናውኑ ሰዎች ፍጹም በተለየ መንገድ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ እርዳታ ፈልገው ወደ እሱ የመጡትን ሕመምተኞች በሙሉ ፈውሷል። ከታመሙ ሰዎች መካከል የተወሰኑትን ፈውሶ የተቀሩትን እንዲሁ አልተዋቸውም። ከዚህም በተጨማሪ ሰዎችን የፈወሰው ሙሉ በሙሉ ከመሆኑም ሌላ ሁልጊዜ ማለት ይቻላል ሰዎቹ ከበሽታቸው የሚድኑት ወዲያውኑ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ኀይል ከእርሱ እየወጣ ሁሉንም ይፈውስ ስለ ነበር፣ ሰዎቹ ሁሉ እርሱን ለመንካት ይፈልጉ ነበር” በማለት ይናገራል።—ሉቃስ 6:19


አንድ የታመመ ሰው ካልተፈወሰ ይህ የሆነው ግለሰቡ እምነት ስለሌለው እንደሆነ በመናገር ሰበብ ከሚደረድሩት በዘመናችን የሚገኙ ፈዋሾች በተቃራኒ ኢየሱስ በእሱ ላይ እምነት የሌላቸውን አንዳንድ ሰዎችን እንኳ ፈውሷል። ለአብነት ያህል፣ ማየት የተሳነው አንድ ሰው እንዲፈውሰው ባይጠይቀውም ኢየሱስ ግን ፈውሶት ነበር። በኋላም ኢየሱስ “በሰው ልጅ ታምናለህን?” ሲል ጠየቀው። ሰውየውም መልሶ “ጌታዬ፤ አምንበት ዘንድ እርሱ ማን ነው?” አለው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “ከአንተ ጋር የሚነጋገረው እርሱ ነው” በማለት መለሰለት።—ዮሐንስ 9:1-7, 35-38


‘ኢየሱስ ሰዎችን የሚፈውሰው እምነታቸውን መሠረት አድርጎ ካልሆነ የፈወሳቸውን ሰዎች ብዙውን ጊዜ “እምነትህ አድኖሃል” ይላቸው የነበረው ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። (ሉቃስ 8:48፤ 17:19፤ 18:42) ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ሲናገር እንደሚፈወሱ አምነው ወደ እሱ የመጡት ሰዎች እንደተፈወሱና ይህን ያላደረጉት ግን አጋጣሚውን ሳይጠቀሙበት እንደቀሩ መግለጹ ነበር። ከበሽታቸው የዳኑት ሰዎችም ቢሆኑ የተፈወሱት በእምነታቸው ሳይሆን በአምላክ ኃይል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር . . . በመንፈስ ቅዱስና በኀይል ቀባው፤ እርሱም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ በደረሰበት ሁሉ መልካም እያደረገ በዲያብሎስ ሥልጣን ሥር የነበሩትን ሁሉ ፈወሰ።”—የሐዋርያት ሥራ 10:38


በዘመናችን፣ ያለ ገንዘብ ‘ፈውስ’ ማግኘት የሚቻል አይመስልም። ፈውስ የሚያከናውኑ ሰዎች ገንዘብ በመሰብሰብ ረገድ የተዋጣላቸው ናቸው። ከእነዚህ ፈዋሾች መካከል አንዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባከናወነው ሥራ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ850 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንዳገኘ ተገልጿል። አብያተ ክርስቲያናትም ፈውስ እንደሚያገኙ ተስፋ በማድረግ ቅዱስ ወደሆኑ ስፍራዎች ከሚመጡ ሃይማኖተኛ ሰዎች ከፍተኛ ትርፍ ያጋብሳሉ። በአንጻሩ ግን ኢየሱስ ከፈወሳቸው ሰዎች ፈጽሞ ገንዘብ አልጠየቀም። እንዲያውም በአንድ ወቅት የፈወሳቸውን ሰዎች መግቧቸው ነበር። (ማቴዎስ 15:30-38) ደቀ መዛሙርቱን ለስብከት ሲልካቸው እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “በሽተኞችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አስወጡ፤ በነጻ የተቀበላችሁትንም በነጻ ስጡ።” (ማቴዎስ 10:8) ታዲያ በዘመናችን ፈውስ የሚያከናውኑ ሰዎች የሚያደርጉት ነገር ከኢየሱስ የተለየ የሆነው ለምንድን ነው?


ገጽ 23“ፈውስ” የሚያከናውኑት በማን ኃይል ነው?


ባለፉት ዓመታት፣ በሕክምና መስክ የተሰማሩ አንዳንድ ሰዎች በአምላክ ኃይል ፈውስ እንዳከናወኑ የሚናገሩ ሰዎች አደረግን የሚሉት ነገር እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ሞክረዋል። ታዲያ ምን ውጤት አገኙ? በለንደን የሚታተም ዴይሊ ቴሌግራፍ የተባለ ጋዜጣ በዚህ ጉዳይ ላይ ለ20 ዓመታት ጥናት ያካሄዱ በእንግሊዝ የሚገኙ አንድ ሐኪም የሰጡትን ሐሳብ ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ “ተአምራዊ ፈውስ እናከናውናለን የሚሉ ሰዎች የሚናገሩት ነገር እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ በሕክምናው መስክ የተገኘ አንድም ማስረጃ የለም።” ያም ሆኖ በርካታ ሰዎች እንደ ቅዱስ ተደርገው የሚታዩ ነገሮችን በመጠቀም፣ ቅዱስ ወደሆኑ ቦታዎች በመሄድ ወይም የአምላክ ኃይል እንዳላቸው በሚናገሩ ሰዎች አማካኝነት እንደተፈወሱ በቅንነት ያምናሉ። ታዲያ እነዚህ ሰዎች ተታልለው ይሆን?


ኢየሱስ ዝነኛ በሆነው የተራራ ስብከቱ ላይ፣ አስመሳይ የሆኑ የሃይማኖት ሰዎች “ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በስምህ . . . ብዙ ታምራት አላደረግንምን?” እንደሚሉት ተናግሯል። እሱ ግን መልሶ “ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንት ክፉዎች፤ ከእኔ ራቁ!” ይላቸዋል። (ማቴዎስ 7:22, 23) ሐዋርያው ጳውሎስ ተአምር እንደሚፈጽሙ የሚናገሩ ሰዎች ኃይል የሚያገኙት ከማን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “የዐመፀኛው አመጣጥ በሰይጣን አሠራር ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ ይህም በሐሰተኛ ታምራት በምልክቶችና በድንቅ ነገሮች ሁሉ ይሆናል፤ እንዲሁም . . . በሚያታልል በተለያየ የክፋት ሥራ ይመጣል።”—2 ተሰሎንቄ 2:9, 10


በተጨማሪም እንደ ቅዱስ ተደርገው በሚታዩ ነገሮች፣ በጣዖታትና በምስሎች አማካኝነት የሚከናወኑት “ፈውሶች” በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም። እንደዚህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የአምላክ ቃል “ከጣዖት አምልኮ ሽሹ” እንዲሁም “ራሳችሁን ከጣዖቶች ጠብቁ” የሚል ግልጽ መመሪያ ይሰጣል። (1 ቆሮንቶስ 10:14፤ 1 ዮሐንስ 5:21) እንዲህ ያሉት “ፈውሶች” ዲያብሎስ ሰዎችን ከእውነተኛው አምልኮ ለማራቅ ከሚጠቀምባቸው መሠሪ ዘዴዎች መካከል የሚመደቡ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለዋውጣል” ይላል።—2 ቆሮንቶስ 11:14


ኢየሱስና ሐዋርያቱ ሰዎችን የፈወሱት ለምን ነበር?


በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙ እውነተኛ ተአምራዊ ፈውሶች ኢየሱስና ሐዋርያቱ የአምላክ መልእክተኞች እንደሆኑ በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው። (ዮሐንስ 3:2፤ ዕብራውያን 2:3, 4) ኢየሱስ ያከናወነው ተአምራዊ ፈውስ ሲሰብክ የነበረውን መልእክት የሚደግፍ ነበር፤ “በምኩራቦቻቸው እያስተማረ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ፣ በሕዝቡ መካከል ማንኛውንም ደዌና ሕመም እየፈወሰ በመላው ገሊላ ይዘዋወር ነበር።” (ማቴዎስ 4:23) ኢየሱስ የታመሙትን መፈወስን ብቻ ሳይሆን በርካታ ሰዎችን መመገብን፣ የተፈጥሮ ኃይላትን መቆጣጠርንና ሙታንን ማስነሳትን ጨምሮ ያከናወናቸው ሌሎች ታላላቅ ነገሮች ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር ምን እንደሚያደርግላቸው የሚያሳዩ ናቸው። በእርግጥም ይህ የምሥራች ነው!


ኢየሱስና ሐዋርያቱን ጨምሮ በዚያ ዘመን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ተቀብለው የነበሩ ሰዎች በሙሉ ከሞቱ በኋላ አምላክ እንዲህ ያሉ ተአምራትን የመፈጸም ችሎታን ወይም የመንፈስ ስጦታዎችን ለሰዎች መስጠት አቁሟል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ነገር ግን ትንቢት ቢሆን ይሻራል፤ [ተአምራዊ በሆነ መንገድ የሚነገር] ልሳንም ቢሆን ይቀራል፤ [በመለኮታዊ ኃይል የሚገለጥ] ዕውቀትም ቢሆን ይሻራል።” (1 ቆሮንቶስ 13:8) ለምን? መፈወስን ጨምሮ እነዚህ ተአምራት ዓላማቸውን ካከናወኑ ማለትም ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ መሆኑን እንዲሁም የክርስቲያን ጉባኤ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱን ካረጋገጡ በኋላ ቀርተዋል ወይም ‘ተሽረዋል።’


ያም ቢሆን ኢየሱስ ያከናወናቸው ተአምራዊ ፈውሶች ለእኛ ትልቅ ትርጉም አላቸው። ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት ላስተማራቸው ትምህርቶች ትኩረት የምንሰጥና በትምህርቶቹ ላይ እምነት የምናሳድር ከሆነ ‘በዚያ ተቀምጦ “ታምሜአለሁ” የሚል አይኖርም’ የሚለው በመንፈስ መሪነት የተነገረ ተስፋ በመንፈሳዊም ሆነ በአካላዊ ፍጻሜውን የሚያገኝበትን ጊዜ በጉጉት መጠባበቅ እንችላለን።—ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6፤ ራእይ 21:4
ምንጭ፦
http://wol.jw.org/am/wol/d/r93/lp-am/2008887?q=%E1%8D%88%E1%8B%8D%E1%88%B5&p=par
Aug 27, 2013 ስም-አልባ የተመለሰ
ስለ መልሱ በጣም አመሰግናለሁ

በዚህ ርዕስ ላይ የተመለሰ ሌላም መልስ እዚህ ጋር http://iyesus.com/q-and-a/74/በእርግጥ-በዚህ-ዘመንም-እግዚአብሔር-ይፈውሳል#a76 ማግኘት ችያለሁ።

እኔ ግን አንድ ሐሳብ አለኝ፦ ተአምራዊ ፈውሶች በሙሉ ለራስ ጥቅም የሚውሉ ሳይሆን ለማያምኑ እንደ ምልክት ነው፣ ያውም እግዚአብሔር አስፈላጊ እንደሆነ ከቆጠረው።

ኢየሱስ ብዙ ተአምራትን ያደረገ (ሰዎችን በተአምር የፈወሰ) ሲሆን ለራሱ ጥቅም ግን ያን ያደርግ እንዳልነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል።

ብዙ ጊዜ ሰዎችን በተአምር የመገበ ቢሆንም በዮሐንስ ምዕራፍ 4 ላይ እንደምናነበው ግን ምግብ እንዲገዙ ደቀመዛሙርቱን ልኳል።

የሉቃስ ወንጌል 5፥17 "አንድ ቀንም ያስተምር ነበር፤ ከገሊላና ከይሁዳ መንደሮችም ሁሉ ከኢየሩሳሌምም መጥተው የነበሩ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ይቀመጡ ነበር፤ እርሱም እንዲፈውስ የጌታ ኃይል ሆነለት።"

2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12:9 "እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ።" - ብዙዎች እንደሚስማሙት ሃዋርያው ጳውሎስ የዓይን ህመም ነበረበት፤ ይሁንና በዙሪያው ያሉት ያመኑ ሰዎች ቢሆንም ማንም አልፈወሰውም።

1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 5፡23 "ስለ ሆድህና ስለ በሽታህ ብዛት ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ እንጂ፥ ወደ ፊት ውኃ ብቻ አትጠጣ።" በማለት ሃዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ መክሮታል። 'ጸልይና ትፈወሳለህ' አይደለም ያለው። በመሆኑም ጢሞቴዎስ ለበሽታው መድሃኒት መውሰድ አስፈልጎታል።

በአጠቃላይ ተአምራዊ ፈውስ ለራስ ወይም ለወገን ጥቅም የሚደረግ አይደለም። የፈውሱ ውጤትም ዘላቂ አይደለም። (ከሞት የተነሱትም፣ እንደ አልአዛር ያሉ፣ በኋላ ሞተዋል)። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል 'በዚያም የሚቀመጥ፦ ታምሜአለሁ አይልም' በማለት በአዲሱ ዓለም የሚኖር ዘላቂ ፈውስ እንደሚኖር የሚናገረው የኢሳይያስ 33፡24 እና የራዕይ 21፡1-5 ጥቅሶች ትልቅ ተስፋ ይሰጡናል።


ሰላም
iyesus kerestose telanetenam zareme eseke lezelealeme yawe New amen

kelaye leteteyekewe teyake yetesetew melashe betekekele selaletemelese ena yetesasate hasabe seletesafe lemesale ኢየሱስና ሐዋርያቱን ጨምሮ በዚያ ዘመን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ተቀብለው የነበሩ ሰዎች በሙሉ ከሞቱ በኋላ አምላክ እንዲህ ያሉ ተአምራትን የመፈጸም ችሎታን ወይም የመንፈስ ስጦታዎችን ለሰዎች መስጠት አቁሟል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ነገር ግን ትንቢት ቢሆን ይሻራል፤ [ተአምራዊ በሆነ መንገድ የሚነገር] ልሳንም ቢሆን ይቀራል፤ [በመለኮታዊ ኃይል የሚገለጥ] ዕውቀትም ቢሆን ይሻራል።” (1 ቆሮንቶስ 13:8) ለምን? መፈወስን ጨምሮ እነዚህ ተአምራት ዓላማቸውን ካከናወኑ ማለትም ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ መሆኑን እንዲሁም የክርስቲያን ጉባኤ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱን ካረጋገጡ በኋላ ቀርተዋል ወይም ‘ተሽረዋል።’
ende enezi ayenete sehetete yemolabachew melashoche endihume tsehafiew eyanesebareke yalewe ye jova witenes temeherete bemehonu teneshe lemalete emokeralehu

ተአምራዊ ፈውስ ሁሉ ምንጩ እግዚአብሔር ነውን
hulume menchawe ke እግዚአብሔር ayedeleme honome gene be ahunu zemeneme hone geta iyesuse eskemimeta derese ke እግዚአብሔር yehone meleketoche ena fewese ale
iysuse yetebareke getana amelake New amen
0 ድምጾች
በብሉይም ይሁን በአዲስ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር ሰዎችን ከበሽታ እንደፈወሰ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል። በተለይ ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት ፈውስ ትልቅ ቦታ እንደነበረው መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። ከኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ በኋላም እግዚአብሔር በክርስቶስ ተከታዮች አማካኝነት ሰዎችን ሲፈውስ በሐዋርያት ሥራ ላይ እናነባለን። ስለዚህ ባጠቃላይ እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በሽታን የሚፈውስ አምላክ ነው።


Quote:

ኦሪት ዘጸአት 15
26 እርሱም፦ አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ፥ በፊቱም የሚበጀውን ብታደርግ፥ ትእዛዙንም ብታደምጥ፥ ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ፥ በግብፃውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና አለ።

ምንም እንኳን ዛሬም እግዚአብሔር ቢፈውስም፤ በዚያው መጠን ደግሞ በዚህ ባለንበት ዘመን ብዙ ያልተጣሩና ያልተረጋገጡ ፈውሶች በተለያዩ የእምነት ተከታዮች ስብሰባዎች ላይ ሲነገሩ ይሰማል። ሳይፈወሱ ተፈውሰሃል የተባሉና በኋላ ያዘኑና የተሰበሩ፤ በማያምኑ ዘንድ ምስክርነታቸው የተበላሸ ወዘተ ብዙ ሰዎች አሉ። ከዚህም ጋር በተያያዘ ብዙ ችግሮች በአሁኑ ዘመን ጎልተው እየታዩ ነው። በተለይ ደግሞ በአሁኑ ዘመን ሰዎች ተፈውሰዋል የሚባለው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጻፉት ለየት ባለ ሁኔታ በአብዛኞቹ ውስጣዊ በሽታዎች ስለሆኑ እውነትነታቸውን ለማረጋገጥ ይከብዳል። በእኛ ግምትም እንደነዚህ ያሉትን ፈውሶች ያለ ሐኪም ማስረጃ ለማረጋገጥ ያስቸግራል እንላለን።

ፈውስንም ይሁን ሌሎች ትንቢቶችና መገለጦችን በተመለከተ፣ የኢየሱስ ተከታዮች ነን የምንል ሁሉ እውነትንና እውነትን ብቻ መውደድ ይኖርብናል እንላለን። ከእውነተኛ ፈውስ ያነሰ፤ እንዲያው በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ በስሜት ብቻ የሚነገር ምስክርነት እግዚአብሔርን የማያስደስትና በመጨረሻም የሰዎችን እምነት የሚጎዳ ነው። ስለዚህ እንደ እኛ አስተያየት ከሆነ፤ በተለይ ውስጣዊ ከሆኑ በሽታዎች ተፈውሻለሁ የሚል ሰው በመድረክ ወጥቶ ከመመስከሩ በፊት፤ የሚከተሉት መስፈርቶችን ቢያሟላ ይመረጣል እንላለን፦
•በእውነት ተፈወስኩ የሚለው በሽታ ነበረበት ወይ? ለዚህም ከሐኪም የተረጋገጠ ማስረጃ አለው? ይህን የምንለው ብዙ ስዎች በራሳቸው ግምት ያለ ምንም የሐኪም ማስረጃ ጉበት አለበኝ፤ ደም ብዛት አለበኝ ወዘተ ስለሚሉ ነው። ታዲያ እንደዚህ አይነት ሰዎች በአንድ ጉባዬ ላይ በስሜት ተነስተው ከጉበት በሽታ እግዚአብሔር ፈወሰኝ ቢሉ፤ ቀድሞውንም የሌለባቸውን በሽታ እንደተፈወሱ ማቅረብ ሊሆን ይችላል።

•ከውስጣዊ በሽታ ተፈወስኩ የሚለው ሰው ይህን ፈውሱን ወደ ሐኪም ሄዶ ማረጋገጣና ማስረጃ ይዞ፤ ፈውሱን በማስረጃ ቢያረጋግጥ ይመረጣል። ብዙ ሰዎች በጉባዬ ላይ፣ ከኤድስም እንኳን እንደተፈወሱ ይመሰክራሉ፤ እንደዚህም አይነት መገለጥ የሚናገሩ ሰባኪዎችም አሉ። እግዚአብሔር እንኳን ከኤድስ መፈወስ ይቅርና ከሙታምን የሚያስነሳ አምላክ ነው። ሆኖም እንዲህ ያለውን የውስጥ ሕመም፤ ታማሚውም እንኳን መፈወሱን በእርግጠኛነት ማወቅ አይችልም። በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው የሐኪም ምርመራ ውጤት ሲመጣ ብቻ ነው።
በቤተክርስቲያን የሚነገሩ ትንቢቶችንና መገለጦችን በተመለከተም እንደዚሁ ለዚሁ ጉዳይ በተመደቡ ወገኖች ትንቢቶቹና መገለጦቹ መፈጸማቸውን ወይም አለመፈጸማቸውን ተከታትሎ ማጣራትና ውጤቱን ይፋ ማድረግ ይገባል እንላለን።


Quote:

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 14
29 ነቢያትም ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ ሌሎችም ይለዩአቸው፤

በዚህ ክፍል "ሌሎችም ይለዩአቸው" ተብሎ የተተረጎመው ቃል፤ ሰዎቹ የሚናገሩትን ሌሎች በጥንቃቄ ይመርምሩ/ይፈትኑ/ይመዝኑ ወይም በእንግዚኛው others should evaluate/weigh carefully/pass judgment what is said ማለት ነው።

እንዲህ አይነቱ ትንቢቶችንና መገለጦችን የማጣራትና ውጤቶችንም ይፋ የማድረግ አሠራር፤ ገለባውን ከፍሬው እንድንለይና፣ እግዚአብሔርን በእውነትና በእውነት ብቻ እንድናከብረው፤ ለዓለም የምንሰጠውም ምስክርነት በፈተና የሚያልፍና የማያሳፍር እንዲሆን ይረዳል። ከዚህ በተጨማሪ፤ አገልጋዮችም ቶሎ እንዲታረሙና ሳያጣሩ ትንቢትን ወይም መገለጥን እንዳይናገሩ ለጥንቃቄ ያግዛል። እውነትና ውሸቱን መመርመርና፣ መተራረም በሐዋርያት ሥራ ላይ ባለች የጥንቷ ቤተክርስቲያንም የተለመደ ተግባር ነው። እንደ ጴጥሮስ ያሉ ዋና ሐዋርያት እንኩዋን ሳይቀሩ ያለ አግባብ ሲሄዱ በሌሎች ይታረሙና ይመረመሩ ነበር። መመርመርንና መተራረምን ከናካቴው አውጥታ የጣለች ቤተክርስቲያን ግን፤ ለብዙ ስህትቶችና ስሜታዊና እውነት ያልሆኑ ፈውሶችና መገለጦች ራሱዋን ማጋለጡዋ አይቀርም።

በመጨረሻም፤ ፈውስ ወይም ተዓምር የእምነትን ወይም የትምህርትን ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ እንዳልሆነ መረዳት አለበን። እውነተኛው የእግዚአብሔር መንፈስ መሆኑና አለመሆኑን የምናውቀው፤ መንፈሱ የተሰቀለውን ክርስቶስን ማእከላዊ ያደረገ መልእክትንና ወንጌልን አብሮ ሲያበስርና፤ የመንፈስ ፍሬ በሰዎች ሕይወት ሲታዩ ነው። እነዚህ ሁለቱን፤ ማለትም የተሰቀለውን ኢየሱስን ማወጅ/ማስተማርና የመንፈስን ፍሬ ማፍራት ሰይጣንና ሥጋ ሊሠሩዋቸው የማይችሉት፤ የመንፈስ ቅዱስ ዋና ሥራዎች ናቸውና።


Quote:

1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ
3፥15 ብዘገይ ግን፥ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው።

የዮሐንስ ወንጌል
4፥23 ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤
4፥24 እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።
Sep 7, 2013 ስም-አልባ የተመለሰ
አመሰግናለሁ ስም አልባ፣ ይህ መልስ ከሁለት ዓመት በፊት ከታች ባለው የመጀመሪያ ጥያቄ ላይ የተመለሰ ነው። ስላስታወስኸኝ አመሰግናለሁ።

ነጥቤን ግልጽ ለማድረግ ያህል በቀጣዩ መልስ ላይ አስፍሬያለሁ።

ሰላም
+1 ድምጽ
እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ዘመን በአንዳንድ ወሳኝ ጊዜያት ተአምራዊ ፈውስ እንዳከናወነ እናውቃለን። እዚህ ላይ ኢየሱስ የተናገረውን አንድ ቁም ነገር ልብ ልንል ይገባል።
Quote:
የሉቃስ ወንጌል 4፡27 "በነቢዩ በኤልሳዕ ዘመንም በእስራኤል ብዙ ለምጻሞች ነበሩ፥ ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር ከእነርሱ አንድ ስንኳ አልነጻም።"

በአዲስ ኪዳን ዘመንም እንዲሁ ብዙ ተአምራዊ ፈውሶች ተካሂደዋል። ይህንን እማናምን ካለን መጽሐፍ ቅዱስ በዞረበት አልዞርንም ማለት ነው።

ይሁንና "በመጨረሻም" ብለህ ያስቀመጥከው ሐሳብ ላይ ማተኮር እፈልጋለሁ። ይህም ተአምራዊ ፈውስ በእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር እንደማይደረግ፣ ቢደረግም በሐኪም ምስክር ካልተረጋገጠ በቀር እውነት ላይሆን እንደሚችል ከጻፍከው አጠቃላይ መልእክት መረዳት ይቻላል። (ከተሳሳትኩ አርመኝ)

አንድ ጥቅስን በአጽንዖት እንድታነብ እመክርሃለሁ።
Quote:
ማቴዎስ 7፡21-23፡
"21 በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።

22 በዚያ ቀን ብዙዎች። ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምንበስምህስ አጋንንትን አላወጣንምንበስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል።

23 የዚያን ጊዜም። ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።"

አስተውል እነዚህ ኢየሱስ "ጌታ" መሆኑን በሚገባ የተረዱ ሰዎች ናቸው። "ጌታ ሆይ፣ የሚለኝ" ነው ያለው ኢየሱስ። በዚህም "ትንቢት መናገር"፣ "አጋንንትን ማውጣት"፣ እንዲሁም "ተአምራትን ማድረግ" በኢየሱስ ስም የተደረጉ መሆናቸውን እንረዳለን። የኢየሱስ መልስ ግን አስደንጋጭ ነው "ከቶ አላወቅኋችሁም!"።

ሌላም ጥቅስ እንጨምር፡
Quote:
የማቴዎስ ወንጌል 24፡24 "ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ።"

በመሆንም ተአምራዊ ፈውስ ከእግዚአብሔር ውጭም ሊደረግ ይችላል። ይህ ለተጠየቀው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ይመስለኛል።

በውይይቱ መካከል የተነሳው ሌላ ጥያቄ "ዛሬስ እግዚአብሔር ተአምራዊ ፈውስ ያካሂዳል ወይ?" የሚለው ነው።

አንተ 'አዎን ያካሂዳል' አልህ፤ የመጀመሪያው መላሽ ደግሞ 'የለም! ተአምራዊ ፈውሶች አላማቸውን ካሳኩ በኋላ ቀርተዋል፣ ዛሬ እግዚአብሔር አያካሂድም' በማለቱ ሁለት ተቃራኒ ሐሳቦች ተነስተዋል።

ወደ ዕብራውያን 2፥4 "እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ እንደ ፈቀደ በምልክትና በድንቅ ነገር በልዩ ልዩ ተአምራትም፥ መንፈስ ቅዱስንም በማደል አብሮ መሰከረለት።" ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አንጻር ሳየው የቀደመው መልስ ሚዛን ይደፋብኛል።

ምክንያቱም እኔም በአስተያየቴ እንዳልሁት እግዚአብሔር ለአንድ አላማ ካልሆነ በቀር ምልክትን አያደርግም። "ምልክት" ማለት በራሱ እንደሚያሳየው ስለ አንድ ነገር የሚያስረግጥ ማስረጃ እንጂ የነገሩ ዋና ነገር አይደለም። በመሆኑም በኢየሱስም ሆነ በሐዋርያት የተከናወኑት ተአምራዊ ምልክቶች ለኢየሱስ እውነተኛ የክርስቲያን ህብረት መስራች መሆን እንዲሁም አዲስ የተቋቋመው የክርስቲያን መንገድ እውነተኝነት የሚያረጋግጡ ምልክቶች ነበሩ።

በብሉይ ኪዳን የመገናኛው ድንኳን፣ ከርሱም ጋር ለእስራኤል ሕዝብ የተሰጠው ስርዓት ለአዲስ ኪዳን ጥላ ነበሩ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደጠቀሰው ጥላ የሆነለቱ "እውነተኛው ነገር ሲመጣ" ጥላ የነበረው ነገር ቀርቷል። (ዕብራውያን 7፡18-19፤ 8፡5፣ 7፣ 13፤ 9፡9-10፤ 10፡1) ቢሆንም አንዳንዶች ይህንን ግልጽ ትምህርት እንደማይቀበሉ የታወቀ ነው። ዛሬም ያንን ስርዓት ሊያስቀምጡ ይወዳሉ።

የዚህም ጉዳይ (ተአምራዊ ፈውስ ዛሬም በእግዚአብሔር ይካሄዳሉ የሚለው) ለእኔ ተመሳሳይ ነው። ጎበዝ፣ ይህን ጉዳይ ከእግዚአብሔር ችሎታ ጋር አናያይዘው። እንዲያማ ከሆነ ዛሬ ሙታን የማይነሱት ለምንድነው? ዛሬስ እግዚአብሔር ሰዎችን በመላእክት አማካኝነት የማያናግረው ለምንድነው? ዛሬስ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍት የማይጻፉት ለምንድነው?

ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠው መልስ ለተነሳው ጉዳይም መልስ ይሆናል።

ዛሬም ፈውስ አለ የሚለው ሃሳብ የሰዉን ስስ ብልት የሚነካና እርስ በርስ የማይስማሙ አብያተ ክርስቲያናት ሰዎችን የማሳመኛ መንገድ አድርገው መውሰዳቸው ትልቅ ግምት ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።

ሌላው ልንዘነጋው የማይገባን ነገር ሰይጣን መጠቀሚያ እንዳያደርገን መጠንቀቅ ነው።
Quote:
2 ቆሮንቶስ 11፡14-15
"14 ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና።

15 እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።"

ከዚህም በላይ እግዚአብሔር ባዘጋጀው አዲስ ዓለም ውስጥ ሊኖር ያለው ተስፋ ላይ "በዚያም የሚቀመጥ ታምሜአለሁ አይልም"፣ እግዚአብሔር "እንባዎችን ሁሉ ከአይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ" በሚናገርበት ጊዜ የሚኖረውን እውነተኛና ዘላቂ ፈውስ መጠበቅ ምንኛ መልካም ነው!

Quote:
ትንቢተ ኢሳይያስ 33፥24 "በዚያም የሚቀመጥ። ታምሜአለሁ አይልም፥ በእርስዋም ለሚቀመጡ ሰዎች በደላቸው ይቅር ይባልላቸዋል።"
Quote:
የዮሐንስ ራእይ 21፥4 "እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።"
Sep 9, 2013 ኦፍቲ (1,250 ነጥቦች) የተመለሰ
“እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ።“
(መዝሙረ ዳዊት 33:12)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us
...