ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » ጥያቄ መጠያየቂያ
Email this page to a friend   Monday, 14 June 2021
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ፥ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።“
(መዝሙረ ዳዊት 27:14)

rss

Today's verse

ሰለ መላእክ ብታብራሩልን!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!

Apr 4, 2014 መንፈሳዊ ስም-አልባ የተጠየቀ

2 መልሶች

+1 ድምጽ
መላእክት—“የሕዝብ አገልጋዮች የሆኑ መናፍስት”

“ሁሉም መዳን የሚወርሱትን እንዲያገለግሉ የሚላኩ የሕዝብ አገልጋዮች የሆኑ መናፍስት አይደሉም?”—ዕብ. 1:14

ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹን ሊያሰናክል የሚችልን ማንኛውንም ሰው አስመልክቶ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ “በሰማይ ያሉት መልአኮቻቸው ዘወትር በሰማይ ያለውን የአባቴን ፊት ስለሚያዩ ከእነዚህ ከታናናሾቹ መካከል አንዱንም እንዳትንቁ ተጠንቀቁ” ብሏል። (ማቴ. 18:10) ሐዋርያው ጳውሎስ ጻድቅ ስለሆኑ መላእክት ሲናገር “ሁሉም መዳን የሚወርሱትን እንዲያገለግሉ የሚላኩ የሕዝብ አገልጋዮች የሆኑ መናፍስት አይደሉም?” በማለት ጽፏል። (ዕብ. 1:14) እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ለመርዳት ሰማያዊ ፍጥረታትን እንደሚጠቀም የሚያረጋግጡ በመሆናቸው ግሩም ማጽናኛ ይሆኑናል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መላእክት ምን ይላል? መላእክት የሚረዱን እንዴት ነው? ከእነሱስ ምን ልንማር እንችላለን?

በሰማይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ታማኝ መላእክት አሉ። ሁሉም ‘ትእዛዙን የሚፈጽሙ ኀያላን’ መላእክት ናቸው። (መዝ. 103:20፤ ራእይ 5:11) እነዚህ የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች አምላካዊ ባሕርያትን የሚያንጸባርቁ ሲሆን የራሳቸው የሆነ አመለካከትና የመምረጥ ነፃነትም አላቸው። መላእክት በላቀ መንገድ የተደራጁ ከመሆኑም ሌላ በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን አላቸው፤ የመላእክት አለቃ ደግሞ ሚካኤል ነው። (ዳን. 10:13፤ ይሁዳ 9)

በመላእክት አለቃ ሥር ሱራፌል የሚባሉ መላእክት አሉ። እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት የእግዚአብሔርን ቅድስና የሚያውጁ ከመሆኑም ሌላ የአምላክ ሕዝቦች መንፈሳዊ ንጽሕናቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ ይረዷቸዋል። በተጨማሪም ሉዓላዊነቱን የሚደግፉ ኪሩቦች አሉ። (ዘፍጥረት 3:24፤ ኢሳይያስ 6:1-3, 6, 7) ሌሎች መላእክት ወይም መልእክተኞች ደግሞ የአምላክን ፈቃድ በማስፈጸም ረገድ የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናሉ።—ዕብ. 12:22, 23

ሁሉም መላእክት ‘ምድር ስትመሠረት’ ሐሴት ያደረጉ ከመሆኑም ሌላ በዓይነቷ ልዩ የሆነችው ይህች ውብ ፕላኔት ለሰው ልጆች ምቹ መኖሪያ እንድትሆን ተደርጋ በተዘጋጀችበት ጊዜ የተሰጣቸውን ሥራ በደስታ አከናውነዋል። (ኢዮብ 38:4, 7) እግዚአብሔር ሰውን ‘ከመላእክት በጥቂት ያሳነሰው’ ቢሆንም በእሱ ‘መልክ’ የፈጠረው በመሆኑ ሰዎች የፈጣሪን ድንቅ ባሕርያት ማንጸባረቅ ይችላሉ። (ዕብ. 2:7፤ ዘፍ. 1:26) አዳምና ሔዋን የተሰጣቸውን የመምረጥ ነፃነት በአግባቡ ቢጠቀሙበት ኖሮ እነሱም ሆኑ ልጆቻቸው የማሰብ ችሎታ ያላቸውን ፍጥረታት ያቀፈው የእግዚአብሔር ጽንፈ ዓለማዊ ቤተሰብ አባል ሆነው በገነት ውስጥ ለዘላለም መኖር ይችሉ ነበር።

ቅዱሳን መላእክት፣ በአምላክ ቤተሰብ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓመጽ በተነሳበት ወቅት በጣም ደንግጠው እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ከመካከላቸው አንዱ እግዚአብሔርን እያወደሰ መኖር ስላላስደሰተው እሱ ራሱ መመለክ ፈለገ። የእግዚአብሔር አገዛዝ ትክክለኛ ስለመሆኑ ጥያቄ በማስነሳትና የአምላክን ሉዓላዊነት የሚቀናቀን አገዛዝ ለማቋቋም በመሞከር ራሱን ሰይጣን (ማለትም “ተቃዋሚ”) አደረገ። ሰይጣን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ የሚገኘውን የመጀመሪያውን ውሸት በመናገር አዳምና ሔዋን አፍቃሪ በሆነው ፈጣሪያቸው ላይ እንዲያምጹና ከእሱ ጋር እንዲተባበሩ መሠሪ የሆነ ዘዴ ተጠቅሞ አግባባቸው።—ዘፍ. 3:4, 5፤ ዮሐ. 8:44

እግዚአብሔር የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በመናገር ወዲያውኑ በሰይጣን ላይ የሚከተለውን የፍርድ ብያኔ አስተላለፈ፦ “በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ።” (ዘፍ. 3:15) በሰይጣንና በእግዚአብሔር ‘ሴት’ መካከል ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ጠላትነት ይኖራል። አዎን፣ እግዚአብሔር ታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈችውን ሰማያዊ ድርጅት ከእሱ ጋር በጋብቻ እንደተሳሰረች ተወዳጅ ሚስት አድርጎ ይመለከታታል። ይህ ትንቢት ደረጃ በደረጃ የሚገለጡ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ “ቅዱስ ሚስጥር” ሆኖ የቆየ ቢሆንም ለተስፋችን አስተማማኝ መሠረት ጥሏል። የአምላክ ዓላማ፣ በድርጅቱ ሰማያዊ ክፍል ውስጥ ካሉት መንፈሳዊ ፍጥረታት አንዱ ዓመጸኞችን በሙሉ እንዲያጠፋ ማድረግ እንዲሁም በእሱ አማካኝነት “በሰማያት ያሉትን ነገሮችና በምድር ያሉትን ነገሮች” አንድ ላይ መጠቅለል ነው።—ኤፌ. 1:8-10

በኖኅ ዘመን አንዳንድ መላእክት በራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረተ ደስታ ለማሳደድ ሲሉ “ትክክለኛ መኖሪያቸውን” በመተው ሥጋዊ አካል ለብሰው ወደ ምድር መጡ። (ይሁዳ 6፤ ዘፍጥረት 6:1-4) እግዚአብሔር ዓመጸኞቹን መላእክት ወደ ድቅድቅ ጨለማ ጥሏቸዋል፤ እነዚህ መላእክት ከሰይጣን ጋር በማበር “ክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች” እንዲሁም የአምላክ አገልጋዮችን የሚጻረሩ ጠላቶች ሆነዋል።—ኤፌሶን 6:11-13፤ 2 ጴጥሮስ 2:4

መላእክት የሚረዱን እንዴት ነው?

የመላእክትን እርዳታ ካገኙ ሰዎች መካከል አብርሃም፣ ያዕቆብ፣ ሙሴ፣ ኢያሱ፣ ኢሳይያስ፣ ዳንኤል፣ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ጳውሎስ ይገኙበታል። ጻድቅ የሆኑ መላእክት የአምላክን ፍርድ ያስፈጸሙ ከመሆኑም ሌላ የሙሴን ሕግ ጨምሮ ትንቢቶችንና መመሪያዎችን አስተላልፈዋል። (2 ነገስት 19:35፤ ዳንኤል 10:5, 11, 14፤ የሐዋርያት ሥራ 7:53፤ ራእይ 1:1) በአሁኑ ጊዜ ሙሉው የአምላክ ቃል ስላለን መላእክት መለኮታዊ መልእክቶችን ለእኛ ማስተላለፍ ላያስፈልጋቸው ይችላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ይሁን እንጂ መላእክት ለሰው ልጆች በማይታይ ሁኔታ በትጋት የእግዚአብሔርን ፈቃድ በማከናወንና አገልጋዮቹን በመርዳት ላይ ይገኛሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርን በሚፈሩት ዙሪያ የእግዚአብሔር መልአክ ይሰፍራል፤ ያድናቸዋልም” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (መዝሙር 34:7፤ 91:11) ንጹሕ አቋምን ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ ጥያቄ በመነሳቱ እግዚአብሔር፣ ሰይጣን የተለያዩ ፈተናዎችን በእኛ ላይ እንዲያደርስ ፈቅዷል። (ሉቃስ 21:16-19) ይሁንና እግዚአብሔር ለእሱ ታማኝ መሆናችንን ለማሳየት እስከምን ድረስ መፈተን እንዳለብን ያውቃል። (1 ቆሮንቶስ 10:13) መላእክት ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ጣልቃ በመግባት እርምጃ ለመውሰድ ምንጊዜም ዝግጁዎች ናቸው። ሲድራቅን፣ ሚሳቅን፣ አብደናጎን፣ ዳንኤልንና ጴጥሮስን ከሞት ታድገዋቸዋል፤ እስጢፋኖስንና ያዕቆብን ግን በጠላቶቻቸው እጅ ከመገደል አላዳኗቸውም። (ዳንኤል 3:17, 18, 28፤ 6:22፤ የሐዋርያት ሥራ 7:59, 60፤ 12:1-3, 7, 11) ይህ የሆነው ሁኔታዎቹም ሆኑ ከግለሰቦቹ ጋር ተያይዘው የተነሱት ጉዳዮች ስለሚለያዩ ነው።

ቅዱሳን መጻሕፍት በምድር ላይ ያለ እያንዳንዱ ሰው የራሱ የሆነ ጠባቂ መልአክ አለው ብለው አያስተምሩም። “የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ” አምላክ እንደሚሰማን በመተማመን መጸለይ እንችላለን። (1 ዮሐንስ 5:14) እርግጥ ነው፣ እግዚአብሔር እኛን ለመርዳት መልአክ ሊልክልን ይችላል፤ ይሁንና ከሌላ አቅጣጫም እርዳታ ልናገኝ እንችላለን። የእምነት አጋሮቻችን እኛን ለመርዳትና ለማጽናናት ሊነሳሱ ይችላሉ። አምላክ፣ ‘በሰይጣን መልአክ’ የተመታን ያህል የሚያሠቃየንን ‘ሥጋችንን የሚወጋውን እሾህ’ መቋቋም እንድንችል ጥበብና ውስጣዊ ጥንካሬ ሊሰጠን ይችላል።—2 ቆሮንቶስ 12:7-10፤ 1 ተሰሎንቄ 5:14

የኢየሱስን ምሳሌ ተከተሉ

እግዚአብሔር ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ በመላእክት የተጠቀመው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። መላእክት የኢየሱስን መወለድም ሆነ ከሞት መነሳት ያስታወቁ ከመሆኑም ሌላ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት አገልግለውታል። በጠላቶቹ እጅ እንዳይወድቅና በአሰቃቂ ሁኔታ እንዳይገደል ሊከላከሉለት ይችሉ ነበር። ሆኖም ይህን ከማድረግ ይልቅ አንድ መልአክ መጥቶ አበረታቶታል። (ማቴዎስ 28:5, 6፤ ሉቃስ 2:8-11፤ 22:43) ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ መሥዋዕታዊ ሞት በመሞት፣ ፍጹም የሆነ ሰው ከባድ ፈተና ቢደርስበትም ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ ከአምላክ ጎን መቆም እንደሚችል አሳይቷል። በመሆኑም እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሞት አስነስቶ የማይሞት ሰማያዊ ሕይወት በማጎናጸፍ ‘ሥልጣንን ሁሉ’ የሰጠው ከመሆኑም ሌላ መላእክት እንዲገዙለት አድርጓል። (ማቴዎስ 28:18፤ ሥራ 2:32፤ 1 ጴጥሮስ 3:22) በዚህ መንገድ ኢየሱስ የአምላክ ‘ሴት’ ዋነኛ ‘ዘር’ ሆኗል። — ዘፍጥረት 3:15፤ ገላትያ 3:16

ኢየሱስ መላእክት ያድኑኛል በሚል ኃላፊነት በጎደለው መንገድ ሕይወቱን አደጋ ላይ በመጣል እግዚአብሔርን መፈታተን እንደማይገባው ተገንዝቦ ነበር። (ማቴዎስ 4:5-7) ስለዚህ እኛም ስደትን በልበ ሙሉነት የምንጋፈጥ ቢሆንም እንኳ “ጤናማ አስተሳሰብ” ይዘን በመኖር ይኸውም ሳያስፈልግ ሕይወታችንን ለአደጋ ከማጋለጥ በመቆጠብ የኢየሱስን ምሳሌ እንከተል።—ቲቶ 2:12

ታማኝ ከሆኑት መላእክት ምን ልንማር እንችላለን?

ሐዋርያው ጴጥሮስ የእግዚአብሔርን አገልጋዮች ‘የሚሳደቡ’ ሰዎችን በወቀሰበት ጊዜ ጻድቃን የሆኑ መላእክት የተዉትን ግሩም ምሳሌ ጠቅሷል። መላእክት ታላቅ ኃይል ያላቸው ቢሆንም “ለእግዚአብሔር ካላቸው አክብሮት የተነሳ” በሌሎች ላይ ከመፍረድ በመቆጠብ ትሑት መሆናቸውን አሳይተዋል። (2 ጴጥሮስ 2:9-11) እኛም በሌሎች ላይ አላግባብ ከመፍረድ እንቆጠብ፤ እንዲሁም የራሳችንን እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ነገሮችን የሁሉም ፈራጅ ለሆነው ለእግዚአብሔር እንተው።—ሮሜ 12:18, 19፤ ዕብራውያን 13:17

የእግዚአብሔር መላእክት አገልግሎታቸውን በትሕትና በማከናወን ረገድ ግሩም ምሳሌ ትተውልናል። አንዳንድ መላእክት ስማቸውን ለሰዎች ለመናገር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። (ዘፍጥረት 32:29፤ መሳፍንት 13:17, 18) በሰማይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ፍጥረታት ቢኖሩም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው የሚካኤልና የገብርኤል ስም ብቻ ነው። ይህም ለመላእክት ተገቢ ያልሆነ ክብር ከመስጠት እንድንቆጠብ ሊረዳን ይችላል። (ሉቃስ 1:26፤ ራእይ 12:7) ሐዋርያው ዮሐንስ በአንድ መልአክ ፊት ተደፍቶ አምልኮ ለማቅረብ በሞከረ ጊዜ ‘ተጠንቀቅ! ፈጽሞ ይህን እንዳታደርግ! እኔኮ ከአንተም ሆነ ከወንድሞችህ ጋር አብሬ የማገለግል ባሪያ ነኝ’ የሚል ማሳሰቢያ ተሰጥቶት ነበር። (ራእይ 22:8, 9) ጸሎቶቻችንን ጨምሮ አምልኮ ማቅረብ ያለብን ለእግዚአብሔር ብቻ ነው።—ማቴዎስ 4:8-10።

መላእክት ትዕግሥት በማሳየት ረገድም ምሳሌ ይሆኑናል። የአምላክን ቅዱስ ሚስጥር የማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ቢኖራቸውም ከዚህ ጋር በተያያዘ አንዳንድ የማያውቋቸው ነገሮች አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “መላእክትም እነዚሁኑ ነገሮች በቅርበት ለማየት ይጓጓሉ” በማለት ይገልጻል። (1 ጴጥሮስ 1:12) ታዲያ ይህን ሚስጥር ለማወቅ ምን ያደርጉ ይሆን? “ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል” ግልጽ የሚሆንበትን እግዚአብሔር የወሰነውን ጊዜ በትዕግሥት ይጠባበቃሉ። — ኤፌሶን 3:10, 11

ፈተና እየደረሰባቸው ያሉ ክርስቲያኖች ‘በመላእክት ፊት እንደ ትርዒት ይታያሉ።’ (1 ቆሮንቶስ 4:9) መላእክት በታማኝነት የምናከናውናቸውን ነገሮች ሲመለከቱ በጣም የሚደሰቱ ከመሆኑም በላይ አንድ ኃጢአተኛ ንስሐ በሚገባበት ጊዜም ሐሴት ያደርጋሉ። (ሉቃስ 15:10) ክርስቲያን ሴቶች የሚያሳዩትን አምላካዊ ባሕርይ መላእክት በትኩረት ይከታተላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “በመላእክት ምክንያት ሴት በሥልጣን ሥር መሆኗን የሚያሳይ ምልክት በራሷ ላይ ታድርግ” ይላል። (1 ቆሮ. 11:3, 10) አዎን፣ ክርስቲያን ሴቶችም ሆኑ በምድር ላይ ያሉ ሌሎች የአምላክ አገልጋዮች የአምላካዊ አገዛዝ ሥርዓትንና የራስነትን ሥልጣን ሲያከብሩ መላእክት ይደሰታሉ። እንዲህ ያለው ታዛዥነት በሰማይ ለሚገኙት ለእነዚህ የአምላክ ልጆች ጥሩ ማሳሰቢያ ሆኖ ያገለግላቸዋል።
Apr 10, 2014 ስም-አልባ የተመለሰ
thank you my beloved for your powerful answer!betam iwedachualehu.
+1 ድምጽ
በሌላ በኩል

መላእክት እውነተኛውን አምላክ (እግዚአብሔርን) ወክለው የሚቆሙ በመሆናቸው መጽሐፍ ቅዱስ መላእክት ራሳቸውን እግዚአብሔር ብለው እንደጠሩ ወይም እግዚአብሔር እንደሆኑ ተደርገው የተገለጹባቸው ጥቅሶች ትኩረት ልንሰጣቸው ይገባል።ዘፍጥረት 16፡7-11፡ አንድ መልአክ የሳራን ገረድ አጋርን ሲያነጋግር
Quote:
"7 የእግዚአብሔር መልአክም በውኃ ምንጭ አጠገብ በበረሀ አገኛት ምንጩም ወደ ሱር በምትወስደው መንገድ አጠገብ ነው።
8 እርሱም፦ የሦራ ባሪያ አጋር ሆይ፥ ከወዴት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጃለሽ? አላት። እርስዋም፦ እኔ ከእመቤቴ ከሦራ የኮበለልሁ ነኝ አለች።
9 የእግዚአብሔር መልአክም፦ ወደ እመቤትሽ ተመለሺ፥ ከእጅዋም በታች ሆነሽ ተገዥ አላት።
10 የእግዚአብሔር መልአክም፦ ዘርሽን እጅግ አበዛለሁ፥ ከብዛቱም የተነሣ አይቆጠርም አላት።
11 የእግዚአብሔር መልአክም አላት፦ እነሆ አንቺ ፀንሰሻል፥ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ ስሙንም እስማኤል ብለሽ ትጠሪዋለሽ፥ እግዚአብሔር መቸገርሽን ሰምቶአልና።"


ዘፍጥረት 21፡17-18፡ ከአጋር ጋር ሲነጋገር
Quote:
"17 እግዚአብሔርም የብላቴናውን ድምፅ ሰማ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ ሲል ጠራት፦ አጋር ሆይ፥ ምን ሆንሽ? እግዚአብሔር የብላቴናውን ድምፅ ባለበት ስፍራ ሰምቶአልና አትፍሪ።
18 ተነሺ፥ ብላቴናውንም አንሺ፥ እጅሽንም በእርሱ አጽኚው ትልቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና።"


ዘፍጥረት 22፡11-12፡ አብርሃም ይስሐቅን ሊሰዋ ሲል
Quote:
"11 የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ጠራና። አብርሃም አብርሃም አለው
12 እርሱም፦ እነሆኝ አለ። እርሱም፦ በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፥ አንዳችም አታድርግበት አንድ ልጅህን ለእኔ አልከለከልህምና እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደ ሆንህ አሁን አውቄአለሁ አለ።"

ዘፍጥረት 31፡11-13፡ "የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ"
Quote:
"11 የእግዚአብሔርም መልአክ በሕልም። ያዕቆብ ሆይ አለኝ እኔም። እነሆኝ አልሁት።
12 እንዲህም አለኝ፦ ዓይንህን አቅንተህ እይ በበጎችና በፍየሎች ላይ የሚንጠላጠሉት የበጎችና የፍየሎች አውራዎች ሽመልመሌ መሳዮችና ዝንጕርጕሮች ነቁጣ ያለባቸውም ናቸው ላባ በአንተ ላይ የሚያደርገውን ሁሉ አይቼአለሁና።
13 ሐውልት የቀባህበት በዚያም ለእኔ ስእለት የተሳልህበት የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ አሁንም ተነሥተህ ከዚህ አገር ውጣ፥ ወደ ተወለድህበትም ምድር ተመለስ።"


ዘጸዐት 3፡2፡ ሙሴን በቁጥቋጦ ውስጥ ሆኖ ሲያነጋግር
Quote:
"2 የእግዚአብሔርም መልአክ በእሳት ነበልባል በእሾህ ቍጥቋጦ መካከል ታየው እነሆም ቍጥቋጦው በእሳት ሲነድድ ቍጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ።
3 ሙሴም፦ ልሂድና ቍጥቋጦው ስለ ምን አልተቃጠለም ይህን ታላቅ ራእይ ልይ አለ።
4 እግዚአብሔር እርሱ ይመለከት ዘንድ እንደ መጣ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር ከቍጥቋጦው ውስጥ እርሱን ጠርቶ። ሙሴ፥ ሙሴ ሆይ አለ።
5 እርሱም፦ እነሆኝ አለ። ወደዚህ አትቅረብ አንተ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ አለው።
6 ደግሞም፦ እኔ የአባትህ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ አለው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ያይ ዘንድ ፈርቶአልና ፊቱን ሸፈነ።"


መሳፍንት 2፡1-3፡ "እኔ ... ለአባቶቻችሁ ወደማልሁላቸው ምድር ... ያደረግሁትን ቃል ኪዳን አላፈርስም"
Quote:
"1 የእግዚአብሔርም መልአክ ከጌልገላ ወደ ቦኪም ወጥቶ እንዲህ አለ፦ እኔ ከግብፅ አውጥቻችኋለሁ፥ ለአባቶቻችሁም ወደ ማልሁላቸው ምድር አግብቻችኋለሁ እኔም። ከእናንተ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን ለዘላለም አላፈርስም
2 እናንተም መሠዊያቸውን አፍርሱ እንጂ በዚህች ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን አታድርጉ አልሁ። እናንተ ግን ቃሌን አልሰማችሁም
3 ይህንስ ለምን አደረጋችሁ? ስለዚህም። ከፊታችሁ አላወጣቸውም፥ ነገር ግን ያስጨንቋችኋል፥ አማልክቶቻቸውም ወጥመድ ይሆኑባችኋል አልሁ።"

መሳፍንት 6፡11-16፡ ከጌድዮን ጋር ሲያወራ የእግዚአብሔር መልአክ -> እግዚአብሔር ...
Quote:
"11 የእግዚአብሔርም መልአክ መጥቶ በዖፍራ ባለችው ለአቢዔዝራዊው ለኢዮአስ በነበረችው በአድባሩ ዛፍ በታች ተቀመጠ ልጁም ጌዴዎን ከምድያማውያን ለመሸሸግ በወይን መጥመቂያው ውስጥ ስንዴ ይወቃ ነበር።
12 የእግዚአብሔርም መልአክ ለእርሱ ተገልጦ። አንተ ጽኑዕ ኃያል ሰው፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው አለው።
13 ጌዴዎንም። ጌታዬ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን? አባቶቻችንስ። እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶናል ብለው ይነግሩን የነበረ ተአምራቱ ወዴት አለ? ወዴት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፥ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል አለው።
14 እግዚአብሔርም ወደ እርሱ ዘወር ብሎ። በዚህ በጕልበትህ ሂድ፥ እስራኤልንም ከምድያም እጅ አድን እነሆ፥ ልኬሃለሁ አለው።
15 እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ እስራኤልን በምን አድናለሁ? ወገኔ ከምናሴ ነገድ ከሁሉ ይልቅ የተጠቃ ነው እኔም በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ አለው።
16 እግዚአብሔርም፦ በእርግጥ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ ምድያምንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታለህ አለው።"
Apr 10, 2014 ስም-አልባ የተመለሰ
Apr 24, 2014 ታርሟል
thank you my beloved for your powerful answer!betam iwedachualehu.
“እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ።“
(መዝሙረ ዳዊት 33:12)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2021 by iyesus.com
Terms of use | Contact us
...