ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » ጥያቄ መጠያየቂያ
Email this page to a friend   Friday, 4 December 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ፥ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።“
(መዝሙረ ዳዊት 27:14)

rss

Today's verse

ሰለ ስላሴ አስተምሮት ብታብራራልን ?

ዩሀንስ
May 30, 2011 መንፈሳዊ ስም-አልባ የተጠየቀ
ስላሴ መጽሃፍ ቅዱስ የማያውቀው አስተምህሮ ነው። አንድም ቦታ ላይ "ስላሴ" የሚል ቃል ወይም "አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ" የሚል አናገኝም። አንዱና ብቸኛው አምላክ፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት የሆነው፡ እግዚያብሄር አብ ነው። እግዚያብሄር አብ አይሞትም፤ ታይቶ አያውቅም፤ እኩያም የለውም። በራእይ 1፡1-2 ላይ ለጌታ ኢየሱስ ራእይ የሰጠው ይሄ ሁሉን የሚችለው አምላክ (አብ) ነው። በብሉይ ኪዳንም ይሁን በአዲስ ኪዳን ምንም አይነት ስላሴያዊ አስተምህሮ አልቀረበም። እሰራኤል የሚያውቀው አንድ አምላክ ብቻ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚያብሄር ልጅ እንጂ እግዚያብሄር አደለም።
ወንድሞች / እህቶች ይህን የተሳሳተ ትምሕርት አምብባቹሁ አትረበሹ በየጊዚዜው የ ክርስቶስን አምላክነት የ ሚክዱ ክርስቲያን ነን የሚሉ ይመጣሉና።
ይህ ደሞ የ ዘመናችን የ ወች ታወር ተከታይ ሆኖ ክርስቶስን ይክዳል እና ፤ ፈጣሪ ክርስቶስ እንዲገልጸለት እንጸልይ።

በ ትንቢተ ኢሳይያስ ፈጣሪ ይህን ይላል

5፤6፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም ሌላ ማንም የለም፤ ከእኔም በቀር አምላክ የለም፤ በፀሐይ መውጫና በምዕራብ ያሉ ከእኔ በቀር ማንም ሌላ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ አስታጠቅሁህ፥ አንተ ግን አላወቅኸኝም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔም ሌላ ማንም የለም።
40፡25፤ እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ።

ክርስቶስም በ የዮሐንስ ወንጌል 10፡30 "እኔና አብ አንድ ነን" ያለውን እናስብ።

በ የዮሐንስ ወንጌል 1፡1 ክርስቶስ እግዚአብሔር እንደሆነም ያለ እሱም ምንም ምን እንደሌለ ተጸፎል።

1፡1 በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ቃልም እግዚአብሔር ነበረ
2 ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ።
3 ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።

እናም ወንድሞች / እህቶች እዚ ድረ ገልጽ ላይ በተደጋጋሚ የ ክርስቶስን አምላከነት ሊያጎሉ የሚጥሩ አሉና ክርስቶስ ይቅር እንዲላቸው
ጸልዩላቸው። [/color]
“በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ።” ዮሐ.1፡1-2
ዓሣ አጥማጁ ሐዋርያ ጌታ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደውን ደኃራዊ ልደቱ በሌሎች ወንጌላውያን የተነገረ ስለሆነ ቀዳማዊ ልደቱን ይነግረን ዘንድ ይቻኰላል፡፡ በእርግጥም “የድንግል ማርያም ልጅ” ብሎ የሚያቆም ካለ እኛ እርሱን አንሰማውም፤ “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” ሊለንም ይገባዋል እንጂ፡፡ አንዳንድ ሰዎች “ወልድ ልጅ ሆኖ ሳለ እንዴት ከአባቱ አያንስም?” ብለው ይጠይቁናል፡፡ እኛም የማይመረመር መሆኑንና የነብዩን ቃል ጠቅሰን እንዲህ ብለን እንመልስላቸዋለን፡- “መኑ ይነግር ልደቶ- ከአብ ያለ እናት የተወለደበት ቀዳማዊ ልደቱን ማን ይናገራል? እንዴትስ ሊመረመር ይችላል? እኛ፡ አብ ለልጁ አባት ሲባል አገኘነው እንጂ እንደምን እንደወለደው አናውቅም” /ኢሳ.53፡8/፡፡ ሐዋርያው “በመጀመርያው” ብሎ ሲነግረንም ከእርሱ በፊት ማንም እንዳልነበረ ለመግለጽ ነውና፡፡ ምንም እንኳን “በመጀመርያ” የሚለው አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ የተለያየ ትርጕም ቢኖረውም አሁን ወንጌላዊው እየነገረን ያለው ግን ቀዳማዊ ቃል ተራሮች ሳይወለዱ፥ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፥ ከዘላለም አንሥቶ እንደ ነበረ ነው /መዝ.90፡2/፡፡ ዮሐንስ “በመጀመርያው” የሚል ደካማ አገላለጽ ከመጠቀም ውጪ ሌላ የተሻለ ቋንቋ ማግኘት አልቻለም፡፡ ሊቀ ነብያት ሙሴ “በቀዳሚ ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድረ- በመጀመርያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” ካለው ጋር ንባብ ቢያሳብረውም ምሥጢር አያሳብረውም፡፡ ነብዩ “በቀዳሚ ዕለት፣ በቀዳሚ ሰዓት ሰማይና ምድር ተፈጠሩ” እያለን ነው፡፡ ይህም ማለት ለእነዚህ ፍጥረታት በዕለተ እሑድ መነሻ፣ መጀመርያ አላቸው፤ ቀዳማዊ ቃል ወልደ እግዚአብሔር ግን ለዘመኑ ጥንት፣ መነሻ፣ መጀመርያ ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም፤ እርሱ አልፋና ኦሜጋ ነው /ዕብ.7፡3፣ ራዕ.22፡13/፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው “ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” በማለት ለዓይን ጥቅሻ ታህል ቅጽበት እንኳን የባሕርይ አባቱ የባሕርይ ልጁን በዘመን እንደማይቀድመው የነገረን፡፡ መሴም ቢሆን “በመጀመርያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” አለን እንጂ (ሎቱ ስብሐትና) “ወልድን ፈጠረ” አላለንም /ዘፍ.1፡1/፡፡ አካለዊ ቃል ወልድማ ሁሉንም የፈጠረ እግዚአብሔር ነው /ቆላ.1፡16/፡፡ የማያምኑበት ባያምኑበትም እኛስ ሙሴ ስለ እርሱ የጻፈለትን ቀዳማዊ ቃል ያህዌ-Johovah እንደ ሆነ እናምናለን /ዮሐ.5፡46፣ ዮሐ.8፡25/፡፡

ይህ የተሰወረባቸው ሰዎች የማይቀላቀለውን ሲቀላቅሉ “ነበረ” እና “ተፈጠረ” አንድ ነው ሊሉን ይሞክራሉ፡፡ ነገር ግን “ነበረ” የሚለው አገላለጽ ለሰዎች ሲቀጸል ኃላፊ ጊዜን የሚያመለክት ሲሆን ለእግዚአብሔር ሲቀጸል ግን ዘላለማዊነትን የሚያለመክት መሆኑን እንነግራቸዋለን፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ከጊዜና ከቦታ ቀመር ውጪ ነውና፡፡ ይህንንም የምናውቀው ሐዋርያው “በመጀመሪያው ቃል ነበረ” እያለን መልሶ ደግሞ “ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም ራሱ እግዚአብሔር ነበረ” ስለሚለን ነው፡፡

ወንጌላዊው እየነገረን ያለው ዓይነት “ቃል” እኛ እንደምንናገረው ዓይነቱ ዝርው (ብትን) ቃል ሳይሆን አካል ያለውን ቃል ነው፡፡ የእኛ ቃል ወዲያው እንደተናገርነው ወደ አለመኖር ይለወጣል፤ አካላዊ ቃል ወልደ እግዚአብሔር ግን ሁሌ ያው ነው፤ አይለወጥም /ሚል.3፡6/፡፡ የእኛ ዝርው ቃል ከልብ ተገኝቶ ህልው ሆኖ ሲኖር አማርኛም ይሁን ትግርኛ አይታወቅም፡፡ ነገር ግን ልገለጽ ባለ ጊዜ በአንደበት እንደሚገለጽ ሁሉ አካላዊ ቃል ወልድም ከአብ ተገኝቶ በአብ ህልው ሆኖ ሲኖር ልገለጽ ባለ ጊዜ በሥጋ ተገልጧል /ዮሐ.14፡9፣ ገላ.4፡4/፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ከዘላለም አንሥቶ ከባሕርይ አባቱ ጋር አለ፤ ነገር ግን አሁን እየተመለከትን ያለነው በሥልጣን ሳይሆን በአካል ከአባቱ የተለየ መሆኑን ነው፡፡

እንዴት ይደንቃል?! ሙሴ በጊዜ ውስጥ ተወስኖ ይጽፋል፤ ይህ ዓሣ አጥማጅ ሐዋርያ ግን ከምናየው ሰማይና ምድር ያልፍና በደቂቃና በሴኮንድ ወደማይቆጠረው ዘላለማዊነት ያስገባናል፤ ሙሴ ከነገረን መጀመርያ አስወጥቶም መጀመርያ ወደሌለው መጀመርያ ይወስደናል፡፡ ወደዚያ ስንሄድም አካላዊ ቃል አምላክ ወልደ አምላክ፣ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከጥበብ የተገኘ ጥበብ፣ ከእውነት የተገኘ እውነት፣ ከማይቸገር የተገኘ የማይቸገር፣ ከማይጠፋ የተገኘ የማይጠፋ፣ ከማይፈርስ የተወለደ የማያረጅ፣ ከማያንቀላፋ የተገኘ የማይተኛ፣ ከማይጨልም የተገኘ የማይጠቁር፣ ከማይመረመር የተወለደ የማይለይ፣ ድካም ከሌለበት የተወለደ የማይደክም፣ ከማይበቀል የተወለደ የማይቀየም፣ ከማይጐድል የተወለደ የማይጐድል፣ ከማያድፍ የተገኘ የማይረክስ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ይህ ምን ማለት እንደ ሆነ ግን በእኛ ደካማ ቃላት መግለጽ አይቻለንም፡፡ የምናውቀው ሁሉ በከፊል ነውና /1ቆሮ.13፡12/፡፡ በእምነት መሠላል ብቻ ወደዚህ እንደርሳለን፡፡
“ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም።” ዮሐ.1፡3-5

አዎ! የወንጌላዊው ዓላማ ሥነ-ፍጥረትን ሳይሆን የየሥነ-ፍጥረት ሁሉ ምንጭ ማን እንደሆነ ማስተዋወቅ ነው፡፡ እነዚህ ፍጥረታት ከመፈጠራቸው በፊት አልነበሩም፤ እርሱ ግን ከዘላለም አንሥቶ በእግዚአብሔር ዘንድ አለ /ዘጸ.3፡14/፡፡ ሁሉንም የፈጠረ ፈጣሪ “ፍጡር ነው” ይሉት ዘንድ አንዳንዶች እንዴት ደፈሩ?!፡፡ ወልድ ፍጡር ከሆነስ ከእርሱ በፊት የነበረችውን ጊዜ ማን ሊፈጥራት ነው? ወንጌላዊው ግን “ከተፈጠረውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ የተፈጠረ የለም” ነው ያለን፡፡ በአመክንዮም (By Logic) ሸክላ ከሸክላ ሠሪው አይቀድምም /ዕብ.1፡8/፡፡

አንድ ነገር ግን ታስተውሉ ዘንድ እንማልዳችኋለን፡፡ ወንጌላዊው፡-“ሁሉ በእርሱ ተፈጠረ፥ ከተፈጠረውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልተፈጠረም” ስላለ ጣዖት፣ ኃጢአትና ክፋት ሁሉ በእግዚአብሔር ተፈጠሩ ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሁሉ የኃጢአት ውጤቶች ናቸውና፡፡ ስለዚህ ፈጣሬ ዓለማት አካላዊ ቃልን ማመን ሕይወትን ይሰጣል፡፡ አዎ! እርሱ ከሕይወት የተገኘ የሕይወት ሁሉ ምንጭ ነው፤ ከእውነት የተገኘ እውነት እንጂ እውነትን ቆይቶ የተማረ ፍጡር አይደለም፡፡ እርሱ፡ ሲሞት እንኳን ሕይወትን የሚሰጥ ዕፀ ሕይወት ነው፡፡ ዕፀ ሕይወቱም እንበላው ዘንድ አደለን፤ ይኸውም እኛን ስለ መውደድ መጥቶ ያዳነን ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው፤ በበላነው ጊዜም ክፋንና ደጉን የምናውቅበት ዕውቀትን አገኘን፡፡
እርሱ ብርሃን ብቻ ሳይሆን ብርሃን ሰጪም ነውና በአካላዊ ቃል ሞትና ትንሣኤ ብርሃን ወጣልን፡፡ ዐይነ ስውር የሆነ ሰው (የማያምን) ፀሐይ ብትኖርም እርሱ ስለማያያት እስከ አሁን ድረስ በጨለማ ውስጥ አለ፡፡ እኛም ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን ቀድሞ ጨለማ ነበርን፥ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ነን /ኤፌ.5፡8/፡፡ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ “ወልድ ፍጡር ነው” ከሚሉት ጋር በጨለማ ውስጥ አንኖርንም፡፡ አካላዊ ቃልን ስናምን ጨለማ ከእኛ ተገፎ ይጠፋል፤ ሞት ከእኛ ይርቃል፣ ክህደት ከእኛ ይወገዳል፤ በአማናዊው ብርሃን ተሸንፏልና ሞት በእኛ ላይ ድል የሚያደርግበትን ሥልጣን ያጣል /1ቆሮ.15፡55-57/፡፡

እንግዲያስ ተወዳጆች ሆይ! ይህ አካላዊ ቃል፣ ከዘላለም አንሥቶ ከአባቱ ጋር የነበረው ወልድ፣ ከጊዜና ከቦታ ከመታየትም ውጪ የሆነው አምላክ፣ አሁን ስለ እኛ ብሎ የእኛን ሥጋ ለብሶ ስለ ታየ፤ ልዑል ሲሆን ዝቅ ስለ አለ፤ ያድነንም ዘንድ በጊዜና ቦታ ተወስኖ ስለ መጣ፤ ከፀሐይና ከጨረቃ አቆጣጠር ውጪ ሆነን ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንኖር ዘንድ ዘመን ስለ ተቆጠረለት በእርሱ ዘንድ ጽርፈትን (ስድብን) ከመናገር እንቆጠብ፡፡
ገ/እግዚአብሔር ኪደ (ለበለጠ መረጃ mekrez.blgspot.com ይጐብኙ). ጌታ ይባርካቹ!

3 መልሶች

+2 ድምጾች
ስላሴ ወይም በእንግሊዝኛው Trinity የሚለው ቃል ሶስነትን የሚያሳይ ቃል ነው። የስላሴ ቃል ወይም ትምህርቱ በቀጥታ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም፤ ሆኖም በብዙ የክርስትና ሃይማኖቶች ከዋናዎቹ አተምህሮቶች (doctrines) እንደ አንዱ የሚታይ ነው።

ይህ ትምህርት በመጀመሪያው የኒሲያ ጉባዬ ላይ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ325 ዓመተ ምህረት (እ.ኤ.አ) እንደ መሠረታዊ አተምህሮት የተወሰደ ትምህርት ነው።

የትምህርቱ መነሻ የሆነው በተለይ በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር፣ ኢየሱስ ክርስቶስና መንፈስ ቅዱስ አብረው የተጠቀሱባቸውን ክፍሎች ከሌሎች እግዚአብሔር አንድ ብቻ እንደሆነ ከሚናገሩ ክፍሎች ጋር እንዴት ማሳታረቅ ይቻላል ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ እግዚአብሔር አንድ ብቻ እንደሆነ ይናገራል። ለምሳሌ፦
Quote:
ኦሪት ዘዳግም 6፡4 "እስራኤል ሆይ፥ ስማ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው "

የማርቆስ ወንጌል 12፥29 "ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፤ እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው"፥

በሌላ በኩል ደግሞ እግዚአብሔር፣ ኢየሱስ ክርስቶስና መንፈስ ቅዱስ አብረው የተጠቀሱባቸው ቦታዎች በአዲስ ኪዳን ይገኛሉ። ለምሳሌ፦
Quote:
2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡14 "የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።"

የማቴዎስ ወንጌል 28፡19-20 "እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ። "

የስላሴ ትምህርት እንግዲህ እንደዚህ ያሉትን ሁለት አይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ለማስማማትና ለማስታረቅ የሚሞክር ትምህርት ነው። የትምህርቱም ይዘት የሚከተለውን ይመስላል፦

እግዚአብሔር አንድ ነው ሆኖም ሶስት ስብእናዎች (persons) አሉት። ስለዚህ አንድ እግዚአብሔር የሚባለው አብን፣ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን አጠቃልሎ ነው የሚል ትምህርት ነው። ሶስቱም ራሳቸውን የቻሉና የማይበላለጡ እኩል ስብእናዎች (persons) ናቸው። ማለትም አብ ወልድ አይደለም ወይም ወልድ መንፈስ ቅዱስ አይደለም ወዘተ። እንዲሁም አብ ከወልድ አይበልጥም ወልድም ከመንፈስ ቅዱስ እኩል ነው ወዘተ። እናም አንድ እግዚአብሔር ሲባል ሶስቱን አጠቃልሎ ነው ብሎ የሚያምን ትምህርት ነው። ለዚህም ነው ይህን የሚያምኑ ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድ እና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እያሉ የሚጠሩት። ምንም እንኳን እንዲህ ያለ አባባል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይገኝም።

የስላሴ ትምህርት ከዚህ በተጨማሪ የክርስቶስን መለኮታዊነት (divinity) ለማይቀበሉም መከላከያ የታሰበ ትምህርት ነው። ኢየሱስ ሰው ብቻ ነው ወይም ፍጥረት ብቻ ነው እንጂ አማላካዊ ባሕርይ የለውም የሚሉትንም ለመቃወም ኢየሱስን ከእግዚአብሔር እኩል አስተካክሎ በማስቀመጥ መልስ የሰጠ ትምህርት ነው።

የግሌ አስተያየት

በነገራችን ላይ የስላሴ ትምህርት ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከ325 ዓመት በኋላ የመጣ ትምህርት መሆኑን ስለማያውቁ፤ ብዙ ክርስቲያኖች ይህ ትምህርት የደህንነት ዋናው ትምህርት ይመስላቸዋል። እናም በትምህርቱ ላይ ጥያቄ ያለው ሰው ልክ በክርስቶስ እንደማያምንና ከክርስቶስ ደህንነት እንደወደቀ አድርገው ነው የሚያዩት። ይሄ በእኔ አመለካከት ትክክል አይደለም። የትም ቦታ በመጽሐፍ ቅዱስ፤ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ ላይ አንድ እግዚአብሔር ናቸው ብለህ ካላመንክ አትድንም የሚለ ነገር የለም። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ባደረገ እንዲሁም በትህትና ለመማር በሚፈልግ ልብ ሊጠየቅና ሊመረመር ይችላል ባይ ነኝ።

የስላሴ ትምህርት በአንድ ጎኑ፤ አንድ የታወቀ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ሊቅ "የስላሴ ትምህርት ባይኖር ኖሮ ትምህርቱ መፈጠሩ አይቀርም ነበር" ብሎ እንዳለው፤ በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያሉ አንዳንድ ፍንጮች ወደ ስላሴ ትምህርት የሚያመለክቱ ይመስላሉ።

ሆኖም እንደ እኔ አመለካከት፤ ልክ የመጽሐፍ ቅዱስን አንድ ጫፍ ብቻ ይዘው "ኢየሱስ የተፈጠረ ሰው ብቻ ነው፤ ምንም መለኮታዊ ባሕርይ የለውም " እንደሚሉትና ወደ አንድ ጎን እንደሚለጥጡት፤ የስላሴ ትምህርት ደግሞ በተቃራኒው የተለጠጠ ነው ብዬ አምናለሁ።

ይሄን ያልኩበት መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑ ምክንያቶች አሉኝ።
 • መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ መለኮታዊ ወይም አማላካዊ ባሕርይ እንዳለው በግልጽ ያስተምራል። እናም ኢየሱስ ልክ እንደ እግዚአብሔር አምልኮና ውዳሴ እንደሚቀበል ተጽፎአል። ሆኖም የኢየሱስን አማላካዊ ባሕርይ የጻፉት እነ ጳውሎስ ራሳቸው ግን አንድ እግዚአብሔር ሲሉ የትም ቦታ አብን፣ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን በአንድ ላይ አድርገው አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ እግዚአብሔር ብሎ የሚጠራው ሁል ጊዜም ቢሆን አብን ብቻ ነው።
  Quote:
  „1ኛ ጢሞቴዎስ 2፣5 "አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው“

  1ኛ ቆሮንቶስ 8፣5-6 „መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፤ ነገር ግን በሰማይ ሆነ በምድርም ሆነ አማልክት የተባሉ ምንም ቢኖሩ፥ ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።“

  ኤፌሶን 4፣4-6 „በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ።“

  የማርቆስ ወንጌል 10፣18 „ኢየሱስም፦ ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም።“

  1ኛ ጢሞቴዎስ 1፣17 „ብቻውን አምላክ ለሚሆን ለማይጠፋው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን።“

  1ኛ ጢሞቴዎስ 6፣16 „እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም፤ ለእርሱ ክብርና የዘላለም ኃይል ይሁን፤ አሜን።“

  ስለዚህ አንድ እግዚአብሔር ማለት ሶስቱን ማለትም አብን፣ ወልድንና ኢየሱስን በአንድነት አጠቃልሎ ነው የሚለው የስላሴ ትምህርት ፈጽሞ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የለም። መጽሐፍ ቅዱስ ሁሌም አንዱ እግዚአብሔር እያለ የሚጠራው አብን ብቻ ነውና።

  እነ ጳውሎስ ታዲያ በአንድ በኩል ኢየሱስ መለኮታዊና አምላካዊ ባሕርይ እንዳለው ይጽፋሉ፤ ይህም ሆኖ ግን አንዱ እግዚአብሔር የሚባለው ግን አብ ብቻ እንደሆነም ይናገራሉ። ኢየሱስ መለኮታዊ ባሕርይ ስላለው፤ ያ ከብሉይ ኪዳን ዘመን ጀምሮ አንዱ እግዚአብሔር እየተባለ ሲጠራ የነበረው አብ ውስጥ ኢየሱስንና መንፈስ ቅዱስን ደምረው በአንድነት ነው አንዱ እግዚአብሔር የሚባለው ወደሚል መደምደሚያ አልደረሱም። ኢየሱስ መለኮታዊና አምላካዊ ባሕርይ አለው? አዎ ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን አንዱ እግዚአብሔር ብለው እነ ጳውሎስ የሚጠሩት አብን ብቻ ነው። ይህ ከስላሴ ትምህርት ይለያል።

 • አብም፣ ኢየሱስም፣ መንፈስ ቅዱስም የማይበላለጡ እኩል ናቸው የሚለው የስላሴ ትምህርት በእኔ አመለካከት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽና በማያወላውል ሁኔታ ኢየሱስ ከአብ እንደሚያንስና አብ ኢየሱስን መብለጥ ብቻ ሳይሆን የኢየሱስ አምላክም እንደሆነ ተጽፎአል።

  ይህ ደግሞ ብዙዎች እንደሚመስላቸው ኢየሱስ በምድር እንደ ሰው ሲመላለስ ብቻ አይደለም። ኢየሱስ "ከእኔ አብ ይበልጣል" ሲል ብዙ የስላሴ አማኞች የሚመስላቸው ኢየሱስ በአምላክነቱ ሳይሆን በሰውነቱ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር እያወዳደረ ይመስላቸዋል። ሰውማ ከእግዚአብሔር እንደሚያንስ እንኳን አይሁዳዊ የሆኑ ደቀመዛሙርቱ ይቅርና አሕዛብም ያውቃሉ። ኢየሱስ ወልድን ወይም አማላካዊ ባሕርይውን ነው ከአብ ጋር የሚያወዳድረው። ይህ ብቻ አይደለም ከሙታን ተነስቶ በአብ ዘንድ በክብርም ከሆነ በኋላ አሁንም ከአብ እንደሚያንስ የሚያሳዩ ነገሮች በራእይ መጽሐፍ ላይ ተጽፈዋል።

  እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት፦
  Quote:
  የዮሐንስ ወንጌል
  5፥26 አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና።

  Amplified Bible
  John 5:26 "For even as the Father has life in Himself and is self-existent, so He has given to the Son to have life in Himself and be self-existent."

  በዚህ ክፍል የምንመለከተ ወልድ የአብ አይነት self-existent ሕይወት እንዳለው የሚናገር ነው። ማለትም ሕይወት በራሱ ያለውና ሕይወትን ማመንጨት የሚችል ሕይወት አብ እንዳለው እንዲሁ ወልድ አለው። ይህን መቼም ኢየሱስ የሚናገረው ስለ ምድራዊ ሕይወቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ታዲያ ይህን የአብ አይነት self-existent የሆነ ሕይወት እንኳን ለኢየሱስ የሰጠው አብ እንደሆነ ነው የሚናገረው።

  ይህም ብቻ አይደለም የሚከተለቱም ክፍሎች ሁሉ የሚያሳዩት አብ የኢየሱስ የበላይ ጌታና አምላክ እንደሆንና ኢየሱስ ደግሞ የአብ ታዛዥ ልጅና የበታች እንደሆነ ነው።
  Quote:
  1ኛ ቆሮንቶስ 11፡3 „ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፥ የሴትም ራስ ወንድ፥ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ።“

  ዮሐንስ 5፡19 „ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና።“

  የዮሐንስ ወንጌል 14፥28 "እኔ እሄዳለሁ ወደ እናንተም እመጣለሁ እንዳልኋችሁ ሰማችሁ። የምትወዱኝስ ብትሆኑ ከእኔ አብ ይበልጣልና ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር።"

  ኢየሱስ ራሱ ሲናገር ስለ ዓለም ፍጻሜ፤ ስለዚያች ቀንና ሰዓት ከአብ በስተቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ወልድም ቢሆን እንደማያውቅ ተናገሮአል። ይህም ብቻ አይደለም፤ በራእይ መጽሐፍ ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ ራሱ፤ አብ ለኢየሱስ የሰጠው ራእይ እንደሆነ ተጽፎአል።
  Quote:
  የማቴዎስ ወንጌል 24፣36 „ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም።“

  የዮሐንስ ራእይ 1፡1 "ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፥ "

  ከትንሳኤም በኋላ እግዚአብሔር የኢየሱስ አምላክ እንደሆነና ከኢየሱስ የሚበልጥ እንደሆነ ብዙ የሚያሳዩ ጽሑፎች በአዲስ ኪዳን እናገኛለን። ሁለቱን ለመጥቀስ ያህል፦
  Quote:
  1ኛ ቆሮንቶስ 15፣27-28 „ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና። ነገር ግን፦ ሁሉ ተገዝቶአል ሲል፥ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው። ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል።“

  የዮሐንስ ራእይ 3፣12 „ድል የነሣው በአምላኬ መቅደስ ዓምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ፥ ወደ ፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም፥ ማለት ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን፥ አዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ።“


ማጠቃለያ

መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ኢየሱስ መለኮታዊና አምላካዊ ባሕርይ ያለው የዛ የአንዱ እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ያስተምራል። ኢየሱስ የዛ የአንዱ እግዚአብሔር የማይታየው ባሕርይ መገለጫና የክብሩ መንጸባረቂያም እንደሆነ ተጽፎአል። ሆኖም ግን ያ አንዱ እግዚአብሔር፤ አብን ወልድንና መንፈስ ቅዱስን በአንድነት አጠቃልሎ ነው የሚል ነገር አያስተምርም። ይባስ ብሎ ደግሞ አብና ኢየሱስ አይበላለጡም የሚባል ትምህርት ፈጽሞ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም።

በአንድ በኩል ኢየሱስ አማላካዊ ባሕርይ እንደሌለውና ሰው ብቻ እንደሆነ የሚል ትምህርት በተቃራኒው በሌላ በኩል ደግሞ አንዱ እግዚአብሔር የሚባለው ሶስቱም በአንድነት ነው እናም ኢየሱስም ከአንዱ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ነው የሚል ትምህርት ሁለቱም የተለጠጡና ሚዛናዊውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚያንጸባርቁ አይደሉም እላለሁ።

እነ ጳውሎስ አንዱን እግዚአብሔርን አብን፤ ብቸኛ አምላክ እያሉም እንዲሁ ደግሞ የኢየሱስን አምላካዊ ባሕርይ ይቀበሉ ነበር። እኛም እንዲህ ልናደርግ ይገባል እላለሁ።
Quote:
ወደ ዕብራውያን 1፥3 "እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤"

ቆላስይስ 1፣15 „እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው።“
May 30, 2011 ስም-አልባ የተመለሰ
May 30, 2011 ታርሟል
የጌታ ሰላም ይብዛልህ!

ፈረንጆች back to square one የሚሉት ነገር አለ። እናም የእኔና የአንተ ምልልስ እንደዚያ ሆነብኝ። ማለትም ዞሮ ዞሮ ወደ ተነሱበት መመለስ ማለት ነው።

እኔ የመጀመሪያውን ከላይ ስለ ስላሴ የሚያብራራውን መልስ ስሰጥ አንድ ያልኩት ነገር ነው አሁንም ዞሮ ዞሮ የሚሆነው ነገር። ይሄውም የስላሴ ትምህርት ተለጥጦ አንድ ጫፍ ላይ ያለ ትምህርት እንደሆነ ሁሉ አንተና የኢየሱስን አምላካዊ ባሕርይና ከመወለዱ በፊትና ዓለም ሳይፈጠር መኖሩን የማትቀበሉ ሰዎች ደግሞ ሌላኛው ጫፍ ላይ ናችሁ።

ሁለታችሁም የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን የግድ እንደ እንጀራ ልጅ በማየት ማፈን አለባችሁ እንጂ በሁለቱም አቅጣጫ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በሙሉ ለመቀበል በፍጹም አትችሉም። ስለዚህ ሚዛናዊ ያልሆነና ወደ አንድ ጎን በእጅጉ ያጋደለ መደምደሚያ ላይ ትደርሳላችሁ።

አንተ ኢየሱስ ዓለም ሳይፈጠር በፊት ስለመኖሩና አምላካዊ ባሕርይውን የሚያሳዩትን ክፍሎች ስታነብብ allegory (ስዕላዊ) የሚባለውን አተረጓጎም ትጠቀማለህ። በመጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ለሆነው ላልሆነው ሁሉ allegorymethod መጠቀም፤ የምንባቡና የመጽሐፉ ትርጉም ከጸሐፊው ነጥቆ አንባቢው እንደመሰለው እንዲተረጉመው በር ይከፍታል። የትርጉሙና የመልዕክቱ ባለስልጣን ጸሐፊው መሆኑ ይቀርና አንባቢው ይሆናል።

አንተን የሚደግፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ስትተረጉም literal method ትጠቀማለህ፤ ማለትም ያው የተጻፈውን እንዳለ ትቀበላለህ እንጂ፤ "ይሄ ስዕላዊ አባባል ነው" ወዘተ አትልም። ከአንተ ጋር የማይሄዱ ዓረፍተ ነገሮችንና ስንኞችን ግን፤ ጸሐፊው ለምን ጻፈ? ምናልባት እኔ የማላውቀውና ያልገባኝ ነገር ሊያስተላፍ ፈልጎ ይሆን? ብለህ ከመመርመር ይልቅ allegory method በመጠቀም "አይ ዓለም ሳይፈጠር በፊት ማለት ዓለም ሳፈጠር በፊት ማለት አይደለም፤ የሆነ ስዕላዊ አባባል ነው፤ ቃል አምላክ ነው የሚለውንም አይ ቃል አምላክ አይደለም ማለቱ ነው" ወዘተ እያልክ ሁለት የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ መተርጎሚያ methods ትጠቀማለህ። አንተን የሚደግፈህን ክፍሎች ሁሉ በliteral method ትተረጉመዋለህ፤ አንተን የማይስማማህን ደግሞ ከliteral ወጥተህ allegory method ትጠቀማለህ።

የሚገርምህ ነገር፤ የስላሴ አማኞችም እንዲሁ እንዳንተ ነው የሚያደርጉት። ኢየሱስ አምላክነቱን የሚያሳዩና ዓለም ሳይፈጠር በፊት መኖሩን የሚናገሩትን ክፍሎች በliteral method ነው የሚተረጉሟቸው፤ ሆኖም ግን "አብ ከእኔ ይበልጣል" የሚለውን ወይም ራሱ ኢየሱስ አንዱ እግዚአብሔር ብሎ የሚያምነው አብን እንደሆነ የሚያሳየውንና "ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም" ወዘተ የሚሉትን ከፍሎች literal ሳይሆን allegory method ነው የሚጠቀሙት። "አይ በሥጋ ሰው ስላለ ነው እንጂ በአምላክነቱ ከአብ አያንስም፤ በአምላክነቱ ሁሉን ያውቃል፤ ስለዚህ ክፍሉ ስለ ሥጋው ወራት ብቻ ነው የሚያወራው" ወዘተ የሚል ግራ ወደተጋባ ማብራሪያ ውስጥ ይገባሉ።

Now, እባክህን መጽሐፍ ቅዱስ ሥዕላዊ ቋንቋ አይጠቀምም እያልኩ አይደለምና ስዕላዊ በሆነ መንገድ ልንረዳቸው የሚያስፈልጉ ክፍሎችን እንዳትደረድርልኝ። ጉዳዩ እዚህ ጋር አይደለም። ነገር ግን ከእኛ አመለካከት ጋር ስላልሄዱ ብቻ የግድ በሥዕላዊ መንገድ መተርጎም አለባቸው የምንለው ነገር ትክክል አይደለም።

በሥዕላዊ ካልሆነ በስተቀር በሌላ ፈጽመው ሊተረጎሙ የማይችሉ ክፍሎች ካልሆኑ በስተቀር፤ መጽሐፍ ቅዱስን በቅድሚያ ሁል ጊዜ በliteral መንገድ ነው መተርጎም ያለብን። ማለትም ኢየሱስ "አብ ብቻ የሚያውቀው ልጁ የማያውቀው" ነገር አለ ካለ፤ አለ ማለት ነው። ያንን መቀበል ነው፤ ሌላ ስዕላዊ ምናምን እያልን መዋዠቅ አያስፈልገንም። እንዲሁም "ዓለም ሳይፈጠር በፊት" ካለ ዓለም ሳይፈጠር በፊት ብለን ነው በቅድሚያ መቀበል ያለብን እንጂ፤ አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት ወዘተ እያልን መዋዠቁ አያዋጣም። Even በሥዕላዊ አተረጓጎም መተርጎም ያለባቸው እንደ ራእይ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን፤ ያ ሥዕል ወይም ምሳሌ ምን ማለት እንደሆነ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው የሚተረጉመው እንጂ፤ ከሆዳችን የፈለግነውን እየፈጠርን አይደለም። ስለዚህ ጉዳይ ምሳሌዎችን ሰጥቼ በጣም ብዙ ማለት እችል ነበር፤ ሆኖም እዚህ ልቋጨው።

በጣም የሚገርመው አዲስ ኪዳን ራሱ ብሉይ ኪዳን ያሉትን ጽሑፎች ከ99% በላይ የሚተረጉመው literal በሆነ መንገድ ነው። ይህ ደግሞ ለአይሁድ ከባድ የሆኑትንም ክፍሎችን ያጠቃልላል። በብሉይ ኪዳን "አማልክት ናችሁ አልኩ" ብሎ ከተናገረ፤ አዲስ ኪዳን ያንን ክፍል "አይ ስዕላዊ ነው፣ እንዲህ ማለቱ አይደለም" ወዘተ እያለ ወደ በallegory method ሊተረጉመው አይሞክርም። ልብ በል ይህ ክፍል ምንም እንኳን ለአይሁዶች ከባድና "አንድ አምላክ ያሕዌ" ነው ከሚለው የእስራኤላውያን እምነት ጋር የሚጋጭ ቢመስልም።

ስለዚህ ለአንተም የምመክረው፤ ለስላሴ አማኞች የምመክረውን ነው። ከእምነታችን ጋር የሚጋጭ መሆኑ ብቻውን በliteral መንገድ ከመተርጎም ወጥተን ወደ ስዕላዊ አተረጓጎም እንድንገባ ማድረግ የለበትም። እንዲያውም እነዚህ literally ሲነበቡ ከእምነታችን ጋር የሚጋጩ የሚመስሉት እግዚአብሔር እኛን ወደ ተሻለ የእርሱን መረዳት ሊያስገባን የሚችልበት መንገዶች ናቸውና ቻሌንጅ እንዲያደርጉን መፍቀድ አለብን እላለሁ።

እንዳየኸው የጻፍኩት ስለ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም እንጂ ጥቅሶችን ለማብራራት አይደለም። ምክንያቱም ያ ዞሮ ዞሮ መጀመሪያ እንደተናገርኩት ወደ አንዱ ጎን የማዘንበልና ወደ አንዱ ብቻ የመለጠጥ አዝማሚያ እስካለ ድረስና ሁለት የተለያዩ methods እንዳሻን ስለምንጠቀም መተማመን አንችልም። ስለዚህ ጥቅስ እየጠቀሱ የምንፈልገውን በዚህ method የማይስማማንን ደግሞ በሌላ method መተርጎም እስካለ ድረስ ስንሽከረከር መዋላችን ነውና እዚህ ጋ አበቃለሁ።

በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎምህ እኔን ጨርሶ ልታሳምነኝ በፍጹም ስለማትችል፤ እኔም አንተም እዚሁ ብናበቃ መልካም ነው እላለሁ።
Quote:
የማቴዎስ ወንጌል 16
13 ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፦ ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ።
14 እርሱም፦ አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት።
15 እርሱም፦ እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው።


እግዚአብሔር አፍ ለአፍ ተናግሮት ለሙሴ የሰጠውን ሕግጋት እስኪያሻሻል ድረስ "ሙሴ እንዲህ ብሎ ነበር፤ እኔ ግን እላችኋላሁ" የሚል እርሱ ማን ነው?

አጋንንት ሲያዩት የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አውቀው "ያለ ጊዜው ልታሰቃየን መጣህን" እያሉ በቃሉ የሚታዘዙለት ማነው?

እግዚአብሔር ብቻ በመቅደስ የማንጻት ሥርዓት የሰዎችን ኃጢአት ይቅር የሚል መሆኑ በሙሴ ሕግ ታውቆ እያለ፤ ያለ መቅደስ ሥርዓት በራሱ ስልጣን "እነሆ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ" ብሎ እንደ እግዚአብሔር ኃጢአትን የማስተሰረይ ስልጣን ያለው ማነው?

የእግዚአብሔር ማደሪያ ከሆነው ከእግዚአብሔር መቅደስ የሚበልጥ እርሱ ማነው?

ሰው ወይም ማንም ፍጡር ሊያደርገው የማይደፍረውን፤ "ከእኔ አብ ይበልጣል" እያለ ራሱን ከያሕዌ ጋር የሚያለካካ እርሱ ማነው?

ከእግዚአብሔር ጎን የሚቀመጥ፤ መላእክቱና ኪሩቤሉ በሰማይና በምድር ያለ ፍጥረት ሁሉ ከያሕዌ ጋር ምስጋናና ክብር የሚሰጡት፤ ከእግዚአብሔር ጎን ከእግዚአብሔር ጋር ውዳሴ የሚቀበል እረ እርሱ ማነው?

ሁሉን ካስገዛለት ከእግዚአብሔር በስተቀር በሰማይም ይሁን በምድር ያለ ፍጥረት ሁሉ ከእርሱ በታች ሆነው የሚገዙለት እርሱ ማነው?

በሰማይም ይሁን በምድር ያለ ፍጡር እንኳን ሊከፍተው ይቅርና ሊመለከተው የማይችለውን መጽሐፍ ይከፍት ዘንድ የቻለ እርሱ ማነው?

እንደ ያሕዌ መላእክቱን የሚያዝዝና የሚልክ እርሱ ማነው?

እርሱ ራሱ ከእግዚአብሔር ጋር የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም መቅደስ የሆነ እርሱ ማነው?

ከእግዚአብሔር ክብር ጋር አብሮ የአዲሲቷ ኢየሩሳሌም ብርሃን የሆነ እርሱ ማነው?

ከእግዚአብሔርና ከእርሱ ዙፋን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቅ የሕይወት ውኃ ወንዝ የሚወጣ እርሱ ማነው?


...

ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? እናንተስ?


የጌታ ጸጋ ይብዛልህ!
እኔ እንኳን ድምጽ ሰጥቼህ ስላልረካሁ በቃላት ላመሰግንህ ወዳለሁ። እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ድንቅ መማማር!

በግሌ መ/ቅ ሲጠና (ማንኛዉም መጸሃፍ) ጸሃፍቱ ማለት የፈልጉትን ማወቅ ተቀዳሚ ተግባራችን መሆን እንዳለበት አስተምረህኛልና ሳላመሰግነህ ማለፍ አልችልም። ከእንግዲህ ሳነብ በተለየ አቀራረብ እንዲሆን እና ማብራሪያ ብፈልግም ፍጹም ገለልተኛ ወይንም ግራ/ቀኝ ዘመም ካልሆኑ ግለሰቦች እንዲሆን ተምሬበታልሁ። በርግጥም በየግላችን ፍለጋችን እውነትን እና እውነትን ብቻ ሆኖ ሳለ እንዳለመታደል ሆኖ ብዙወቻችን ፍቅራችን ከእምነት ድርጅቶች ጋር ይመስላል።
ለኔ በትልቁ ተምሬበታልሁና በጣም እግዚያብሄር ይስጥልኝ!!
በተነገሩት ነገሮች እስማማለሁ። ነገር ግን ሁላችሁም አንድን መሰረታዊ ሃሳብ እየሸሻችሁ እንደሆነ እያየሁ ነው። ራዕይ 3፡14 "በእግዚአብሔር ፍጥረት መጀመሪያ" (the beginning of creation by God) እያለ እንዲሁም ቆላስይስ 1፡15 "የፍጥረት በኩር" (the first-born of all creation) የሚሉ አገላለፆችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ይጠቀማሉ። እነኚህን የመሳሰሉ ጥቅሶችን ከግንዛቤ ብታስገቡ ትምህርቱ ምሉዕ ይሆን ነበር።

አንድ ጸሐፊም በተመሳሳይ ጉዳይ እንዲህ ዓይነት ሃሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ የለም ብሎ አፉን ሞልቶ ሲናገር ገርሞኛል።

ይህ ነጥብ የክርስቶስን ክብር የሚያወርድባችሁ መስሏችሁ እንዳለፋችሁት ወይም አርዮሳዊ ትምህርት ታስተምራላችሁ እንዳትባሉ የሰጋችሁበት ነጥብ ይመስለኛል።

መድረኩን ላዘጋጁት ግን አክብሮቴን ሳልገልጽ አላልፍም።
አንድ እርማት ልሰጥ እወዳለሁ፦

የውይይቱ ተካፋይ የጆቫ (የይሖዋ ምስክሮች) እምነትን የሚያራምድ አይደለም። በችኮላ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ አትድረስ እንዲሁም ለሌሎች የተሳሳተ መረጃን አታስተላልፍ። የይሖዋ ምስክሮች አንተ እንደምትለው ነው ስለኢየሱስ የሚያስተምሩት። ኢየሱስ ከማርያም ከመወለዱ በፊት በሰማይ ከአባቱ ጋር እልፍ አእላፍ ዘመናት እንደኖረ ያምናሉ። የኢየሱስ ህይወት የጀመረው በዚህች ምድር ላይ ነው የሚል እምነት የላቸውም።

ይሁንና ከመልዕክትህ እንደተረዳሁት ከአንተ ጋር የሚለያዩት ኢየሱስ "የፍጥረት መጀመሪያ ነው" የሚለውን በመቀበላቸው ነው። (ራዕይ 3፡14፤ እና ቆላስ. 1፡15፣16) አንተስ እነዚህን ጥቅሶች እንዴት ትመለከታቸዋለህ?

ከዌብ ሳይታቸው ስለኢየሱስ የሚያስተምሩትን ለማየት ይህንን http://www.jw.org/am/የይሖዋ-ምሥክሮች/ተየጥ/በኢየሱስ-ማመን/ መመልከት ትችላለህ።

አመሰግናለሁ።
0 ድምጾች
ይህን ለሚያነቡ ሁሉ የጌታ ሰላም ይሁን። አሜን!!!

ስላሴ የሚለው ቃል በመሰረቱ የግዕዝ ቃል ነው የሚያመለክተውም ሶስት የመሆን ነው። ክርስትና በአብ በውልድ በመንፍስ ቅዱስ አካልት በመለኮት ደግሞ አንድ እግዚአብሔር ብለን እናምናለን።

ይህን የአንድ እና የሶስት መሆን ምስጥር በራሳቸው ጭንቅላት ማየትና ማሳብ ሲጀምሩ ስለማይገባቸው ከክርስትና ለየት ያለ የእምነቶችን ፈሊጥ የመሰረቱ ብዙ ናቸው። እግዚአብሔርና አላህ አንድ አይደሉም ምክንያቱም እኛ ክርስቲያኖች አንድያ ልጁን ለመራራ የጎልጎታ መስቀል ሞት አሳልፎ በመስጠት በልጁ ክቡር ደም ዋጅቶ ዕርቅን ከአብ ጋር በኢየሱስ አገኘን ብለን የምናምን ነን።

በአላህ የሚያምኑ ደግሞ እላህ አይወለድም አይወልድም ይላሉ። ትልቅ ልዩነት ስለሆነ የተለያዩ እንጂ አንድ አይደሉም። እግረ መንገዴን ጠቀስኩት እንጂ ከጥያቄው ጋር የተየያዘ እንዳልሆነ ስቸው አይደለም።

በዘፍጥረት ምዕራፍ አንድ ላይ እግዚአብሔር ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍተር ይላል። እዚህ ላይ ከነማን ጋር ነው እግዚአብሔር ይህን ውይይት የሚያደርገው ያለ ብሎ መጠየቅ ግዴታ ነው። ከምላዕክት ጋር አይደለም እግዚአብሔር ከመላዕክት ልዩ ነውና ታድያ ከማን ጋር ነው? ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ ሌላ ሊሆን አይችልም። በዘመናት ስናይ ሶስቱ ስራቸውን አንድ ላይ እንድሚሰሩ የምንረዳበት መንገድ ብዙ አለ።

ገብረኤል መልአክ ወደ ማርያም ከእግዚአብሔር ተልኮ እንደምጣና እንደ ምትፀንስና ወንድ ልጅም እንደምትወልድ ነገራት። እኔ ወንድ አላውቅም እንዴት ብላ ስትጠየቅው የመልአኩ መልስ ታይቶ ተሰምቶ የማያውቅ ነበር። መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህም ካንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል አላት (ሉቃ1፡26-36)

ኢየሱስ ደግሞ ስለ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ክቡርና በታም ቅዱስ መሆኑን ሲያስተምረን በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም ይላል ማቴ 12፡32።

መቸም በስጋ እስካለን ድረስ ይህ የስላሴ አንድነት ምስጥር እንደሆነ ይቀራል። እንግዲህ ይህ አጭር ቅምሻ ጣፈጠ´ኝ ድገምኝ የሚያሰኝ ሆኖ በግል ቃሉን ከምልጃና ጸሎት ጋር እየቀረብን በተጨማሪ ሌላ መጻህፍት በማየት እንዲያስተምረን እንትጋ እላለሁ።

ጌታ ይባርካቹህ
ወንድማችሁ
Jun 14, 2011 ስም-አልባ የተመለሰ
ግን እኮ አንተ ያልከውንም የብሉይ ኪዳኑን "እንፍጠር" የሚለውንም እያነበቡም ቢሆን አይሁዳውያን ሁልጊዜም ሲነገራቸው የነበረውና የሚያምኑት "እግዚአብሔር አምላክ አንድ አምላክ ነው" በሚለው ነው እንጂ፤ አሁን አንተ እንደምትለው አይነት፤ ምስጢር ነው ምናምን ወደሚል መረዳት አልደረሱም።

ስለ መንፈስ ቅዱስም ቢሆን በዘፍጥረት ላይ "የእግዚአብሔርም መንፈስ በውሃ ላይ ሰፍፎ ነበር" እና በኢዮብ "የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ" የሚለውንም እያነበቡም ቢሆን ስላሴ ወደሚል አስተሳሰብ ወይም እግዚአብሔርና መንፈስ ቅዱስ የተለያየ ስብዕና አላቸው ወደሚል መረዳት አልደረሱም። እነዚያን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እያነበቡም ቢሆን፤ ኢየሱስም ይሁን ጳውሎስ ወይም አይሁዳውያን አንድ ብቸኛ አምላክ እግዚአብሔር ነው ነበር የሚሉት እንጂ ምስጢር ነው ስላሴ ነው ወዘተ ወደሚል መረዳት አልመጡም።

እናም ስላሴ የሚለው ሃሳብና መረዳት ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከ325 ዓመታት በኋላ በቲዎሎጂያኖች የመጣ ጽንሰ ሃሳብ እና concept ነው እንጂ ከዚያ በፊት የሚታወቅ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምሮት አይደለም። ስለዚህም ነው የስላሴ ትምህርት የእግዚአብሔርን ማንነት ጥያቄ ከሚመልስ ይልቅ ይባስ ብዙ ጥያቄዎችን ለአይሁድና ለእስላሞች ብቻ ሳይሆን ለክርስቲያኖችም የሚፈጥረው።

ብዙም የስላሴ አማኞችም ጭምር ለመረዳት የሚከብቻቸው ጽንሰ ሐሳብ ስለሆነ ነው፤ ሁልጊዜ ይህ ጥያቄ ሲነሳ፤ ኦ ከባድ ነው፣ በመገለጥ ነው፣ አይገባም፣ ምስጢራዊ ነው፣ ለመረዳት አይቻልም ወደሚል ሽሽት የሚገቡት። በመጽሐፍ ቅዱስ የሌለ የቲዎሎጂያኖች ጽንሰ ሃሳብ ስለሆነም እንዲሁ በቀላሉ ለመረዳት የሚከብድ ምስጢራዊ አስተሳሰብ የሆነው።

እንዲህም ሆኖ ግን፤ ብዙ ክርስቲያኖች ያልተረዱትን ይህንን ጽንሰ ሃሳብ ካለመኑ የሚድኑ አይመስላቸውም። መረዳት አይቻልም፣ ምስጢራዊ ነው ይላሉ በአንድ በኩል፤ ነገር ግን ይሄንን ከ325 ዓመታት ከክርስቶስ ልደት በኋላ የመጣ ትምህርትን ካላመንክ ደግሞ በቃ አልዳንክም ይላሉ። የትም ቦታ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የስላሴን ትምህርት ጽንሰ ሃሳብ ማለትም እግዚአብሔር በሶስት እኩል በሆኑ ስብዕና ይገለጣል ብለህ ካላመንክ አትድንም የሚባል ነገር የለም።

ቲዎሎጂያኖች ነገሩን አወሳሰቡትና ምስጢራዊ አደረጉት እንጂ፤ ብሉይም ይሁን አዲስ ኪዳን አንዱ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል አምላክ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ አባት አብ እንደሆነ በግልጽ አስቀምጦታል በቃ! ምንም ምስጢራዊ ምናም ነገር የለውም።

ጌታ ይባርካችሁ!
እየሱስ አያማልድም ወይ?
0 ድምጾች
ሰላም ይብዛላችሁ። ከሁሉ አስቀድሜ የምገልፀው ነገር ቢኖር ከጥንት እስራኤል እንዲህ ተብለው ነበር። "አምላካችሁ እግዚሃብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው "። ይህ ማለት አምላካችንን ብንቆጥር አንድ እግዚአብሔር ወይም አንድ አምላክ ብቻ ሆኖ እናገኝዋለን። ይህ አምላክ መንፈስ ነው። ይህ አምልክ ቅዱስ ነው። ይህ አምላክ አልፋና ኦሜጋ ነው። ይህም ማለት ከ እርሱ በፊት ማንም አልነበረም፥ እርሱንም አሳልፎ የሚመጣ ማንም የለም። ይህ አምላክ በሰማይ ዙፋኑ ላይ ይኖራል። ይህ አምላክ በመንፈሱ ሰማይንና ምድርን ሞልቷል። ይህ አምላክ እራሱ በስጋ ተገልጧል። ስለዚህ ጌታ እንዲህ ኣለ። አብ በእኔ እንዳለ እኔም በአብ እንዳለሁ. . . ልክ አንዲሁ መንፈስ ቅዱስም የ እግዚአብሔር መንፈስ እንደተባለ ሁሉ የኢየሱስ መንፈስም ተብሏል። ሁሉ የእግዚአብሔር ማንነቱና መገለጫው ነው ብዬ እረዳለሁም አምናለሁም። አባትም፥ ልጅም፥ መንፈስ ቅዱስም የሆነው ኤርሱ አንዱ እግዚአብሔር እንጂ ሌላ የለምና። ሁሉ ከእርሱ በእርሱ ለእርሱ ሆነ። አሜን።
Dec 3, 2012 ስም-አልባ የተመለሰ
“እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ።“
(መዝሙረ ዳዊት 33:12)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us
...