አንድ ሰው ከዳነ በኋላ ደህንነቱን ሊያጣ እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምራል።
Quote:
የዮሐንስ ራእይ 3
1 በሰርዴስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስትና ሰባቱ ከዋክብት ያሉት እንዲህ ይላል። ሥራህን አውቃለሁ ሕያው እንደ መሆንህ ስም አለህ ሞተህማል። 2 ሥራህን በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትምና የነቃህ ሁን፥ ሊሞቱም ያላቸውን የቀሩትን ነገሮች አጽና። 3 እንግዲህ እንዴት እንደ ተቀበልህና እንደ ሰማህ አስብ፥ ጠብቀውም ንስሐም ግባ። እንግዲያስ ባትነቃ እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ በማናቸውም ሰዓት እንድመጣብህ ከቶ አታውቅም። 4 ነገር ግን ልብሳቸውን ያላረከሱ በሰርዴስ ጥቂት ሰዎች ከአንተ ጋር አሉ፥ የተገባቸውም ስለ ሆኑ ነጭ ልብስ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ። 5 ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጐናጸፋል፥ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም፥ በአባቴና በመላእክቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ። 6 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።
ከላይ የተቀመጠው ክፍል ጌታ ኢየሱስ ለሰርዴስ ቤተ ክርስቲያን የላከውን መልዕክት የያዘ ነው። በራእይ 1
:11 እንደተገለጸው ይህ መልዕክት ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ራእይ በእስያ ለሚገኙት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ከላከው መልዕክት ውስጥ አንዱ ነው። መልዕክቱ እንግዲህ
ለአብያተ ክርስቲያናት ማለትም በክርስቶስ አምነው ለዳኑና ክርስቶስም የእኔ ናቸው ለሚላቸው አማኖች የተላከ ነው።
በዚሁ ለአማኞች በተላከ መልዕክት ጌታ ሲናገር "ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጐናጸፋል፥
ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም" ይላል። ይህ ክፍል ያለ ጥርጥር የሚያሳየን በሕይወት መጽሐፍ መጻፍ እንዳለ ሁሉ፡ ከሕይወት መጽሐፍ መደምሰስም እንዳለ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን የሕይወት መጽሐፍን የዳኑ ሰዎች የሚጻፉበት መጽሐፍ እንደሆነና በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፉ ደግሞ እንደሚጠፉ ይነገረናል። የዳኑ ሰዎች ብቻ የሚጻፉበት መጽሐፍ ስለሆነም "የበጉ ሕይወት መጽሐፍ"ም ተብሎ ይጠራል።
Quote:
የዮሐንስ ራእይ
20፥15 በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ።
21፥27 ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር፥ ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኵሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ እርስዋ ከቶ አይገባም።
ስለዚህ ከሕይወት መጽሐፍ መደምሰስ ማለት ደህንነትን ማጣትና ፍርድን መቀበል ማለት ነው።
ደህንነትን ከማጣት ጋር በተያያዘ የምንመለከተው ሌላው ክፍል የዮሐንስ ወንጌል 15ን ነው።
Quote:
የዮሐንስ ወንጌል15
1 እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው። 2 ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል። 3 እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፤ 4 በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም። 5 እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። 6 በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል።
በዚህ ክፍል ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን እንደ እውነተኛ የወይን ግንድ ይመስላል። አብን ደግሞ እንደ የወይኑ ገበሬ። አማኞችን ደግሞ በወይኑ ግንድ ማለትም በክርስቶስ ላይ እንዳሉ ቅርንጫፎች። በዚህ ክፍል ጌታ ሊያስተላልፈው የሚፈልገው መልዕክት ያለ ክርስቶስ አማኞች ከግንዱ እንደ ተለየ ቅርንጫፍ ብቻቸውን ሕይወት ሊኖራቸው እንደማይችልና ያለ ክርስቶስ ሊያፈሩ እንደማይችሉ ነው።
በቁጥር ሁለት ላይ ጌታ "
ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል“ ይላል። ልክ ቅርንጫፍ ከግንዱ ሊቆረጥ እንደሚችል እንዲሁ ከክርስቶስ መወገድ ወይም መቆረጥ እንዳለ በግልጽ ያሳየናል። መወገድ ብቻ ሳይሆን ከመወገድ ጋር ተያይዞ ደግሞ መድረቅና ተሰብስቦ ወደ እሳት መጣል እንዳለም በቁጥር 6 ያስጠነቅቃል። "
በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል።" እዚህ ጋር ልብ ማለት ያለብን ከክርስቶስ ስለመወገድ፡ ወደ ውጭ ስለመጣል እንዲሁም በእሳት ስለመቃጠል ጌታ የሚያወራው በዓለም ስላሉ ዓለማውያን ሳይሆን በክርስቶስ ስላሉ ቅርንጫፎች ማለትም ስለ አማኞች ነው።
ሰው ወንጌልን ተቀብሎ ከዳነ በኋላ ደህንነቱን ሊያጣ እንደሚችል የሚያስጠነቅቀን ሌላው ክፍል የሚገኘው ደግሞ በዕብራውያን 10 ላይ ነው።
Quote:
ወደ ዕብራውያን 10
26 የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርልንምና፥ 27 የሚያስፈራ ግን የፍርድ መጠበቅ ተቃዋሚዎችንም ሊበላ ያለው የእሳት ብርታት አለ። 28 የሙሴን ሕግ የናቀ ሰው ሁለት ወይም ሦስት ቢመሰክሩበት ያለ ርኅራኄ ይሞታል፤ 29 የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኵስ ነገር የቆጠረ የጸጋውንም መንፈስ ያክፋፋ፥ እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል? 30 በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ያለውን እናውቃለንና፤ ደግሞም፦ ጌታ በሕዝቡ ይፈርዳል። 31 በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነው።
ይህ ክፍል ከዳኑ በኋላ ወደው ወይም ሆን ብለው ኃጥያትን ለሚለማመዱ ሰዎች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ ነው። ወንጌልን ተቀብለው ንስሐ ከገቡና በክርስቶስ መሥዋዕት ምህረትን ካገኙ በኋላ ወደው ኃጥያትን የሚለማመዱ ከእንግዲህ ወዲህ መሥዋዕት እንደማይቀርላቸውና ይልቁንም የሚያስፈራ ፍርድ እንደሚጠብቃቸው የሚያሳይ ክፍል ነው። እንደነዚህ አይነት ሰዎች ስለሚጠብቃቸው ፍርድም ሲናገር "
ተቃዋሚዎችንም ሊበላ ያለው የእሳት ብርታት“ ይላል። አዲሱ መደበኛ ትርጉም ይህን ክፍል "
የሚቀረው ግን የሚያስፈራ ፍርድና የእግዚአብሔርን ጠላቶች የሚበላ ብርቱ እሳት መጠበቅ ብቻ ነው።“ ይለዋል።
Quote:
ወደ ዕብራውያን 10 (አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
26 የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ሆን ብለን በኅጢአት ጸንተን ብንመላለስ፤ ከእንግዲህ ለኅጢአት የሚሆን ሌላ መሥዋእት አይኖርም። 27 የሚቀረው ግን የሚያስፈራ ፍርድና የእግዚአብሔርን ጠላቶች የሚበላ ብርቱ እሳት መጠበቅ ብቻ ነው።
ይህ ማለት እንግዲህ እነዚህን ሰዎች የሚጠብቀው ፍርድ እኛ ብዙ ጊዜ እንደምናስበው ለአማኞች ብቻ የሆነ ለስለስ ያለ ፍርድ ሳይሆን፡ ልክ የእግዚአብሔር ጠላቶች/ተቃዋሚዎች ወይም ያልዳኑ ሰዎች የሚያገኙትን እኩል ፍርድ እንደሆነ ነው። ይህም ደህንነታቸውን እንደሚያጡ በግልጽ ያሳየናል።
ይቀጥላል ...