1) የጥምቀት ትርጉሙ በአጭሩ
Quote:
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች
10፥2 ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፤
የሐዋርያት ሥራ 19
1 አጵሎስም በቆሮንቶስ ሳለ ጳውሎስ በላይኛው አገር አልፎ ወደ ኤፌሶን መጣ፥
2 አንዳንድ ደቀ መዛሙርትንም አገኘ። ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን? አላቸው። እርሱም፦ አልተቀበልንም መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ስንኳ አልሰማንም አሉት።
3 እንኪያ በምን ተጠመቃችሁ? አላቸው። እርሱም፦ በዮሐንስ ጥምቀት አሉት።
4 ጳውሎስም፦ ዮሐንስስ ከእርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድ ለሕዝብ እየተናገረ በንስሐ ጥምቀት አጠመቀ አላቸው።
5 ይህንም በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ፤
በቅድሚያ ጥምቀት የሚለው የግሪክ ቃሉ የሚያሳየው በውሃ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ መስጠምን/መጥለቅን ነው እንጂ በውሃ መረጨትን አይደለም። በውሃ መስጠምና መጠመቅ በክርስትና የተጀመረ ብቻ አልነበረም። ለምሳሌ አንድ አሕዛብ የአይሁድን እምነት ለመከተል ሲወስን ይጠመቅ ነበር። ማለትም አሮጌውን ሕይወት ትቶ አዲስ ሕይወትና መንገድ እንደጀመረ የሚያሳይ ነገር ነው።
መጥምቁ ዮሐንስም ቢሆን ሰዎች ከድሮ ክፉ ሥራቸው ንስሐ ገብተው አዲስን ሕይወት እንዲጀምሩ ነበር የንስሐ ጥምቀት ያጠምቅ የነበረው።
ከላይ ባለው 1ቆሮ ክፍል ላይም ጳውሎስ የእስራኤል ሕዝብ ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በባሕር እንደተጠመቁ ይናገራል። ያም ባህር ቀይ ባህር ነው። በግብጽ ይኖሩበት ከነበረው አሮጌ ሕይወታቸው ወጥተው አሁን እግዚአብሔርን ለመታዘዝ አዲስ ኑሮ እንደጀመሩ የሚያሳይ ጥምቀት ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ጥምቀት መተባበርን ወይም መሪውን መከተልን ያመለክታል። እስራኤላውያን ሲጠመቁ ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ
(baptised into Moses ) ተጠመቁ።
የዮሐንስንም ጥምቀት የተጠመቁት እርሱ ከእግዚአብሔር እንደተላከ በማመን እርሱን በመተባበር ነበር።
ኢየሱስን በማመንም የሚጠመቁት እንዲሁ እርሱን በማመን፤ አሮጌ ኑሮአቸው ሞቶ አዲስ ሕይወት እንደሚኖሩ በማመንና ከክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ጋር እንደተባበሩ በማመን የሚጠመቁት ነው።
2) በማን ስም እንጠመቀ?
እንግዲህ ከላይ እንደጠቀስኩት ጥምቀት መሪውን ተባብሮ አዲስ ሕይወትን ለመጀመር የሚደረግ መስጠም ነው። ስለዚህም በሃዋርያት ሥራ እንደምንመለከተው ሁሉም ጥምቀቶች የተካሄዱት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። ማለትም ከክርስቶስ ጋር እንተባበራለን፤ አሮጌው ሕይወታችን በመስቀሉ ከክርስቶስ ጋር ሞቶ፤ ከክርስቶስ ጋር በአዲስ የትንሳኤ ሕይወት እንኖራለን የሚል ነው። በኢየሱስ እናምናለን፤ እርሱንም እንከተላለን በሚል እምነት የሚደረግ ነው። ስለዚህ በሐዋርያት ሥራ ላይ ያሉትን ደቀመዛሙርቱ ያካሄዱትን ጥምቀቶች በሙሉ ስንመለከት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተደረገ ጥምቀት ነው።
Quote:
የሐዋርያት ሥራ
2፥38 ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።
8፥16 በጌታ በኢየሱስ ስም ብቻ ተጠምቀው ነበር እንጂ ከእነርሱ በአንዱ ላይ ስንኳ ገና አልወረደም ነበርና።
10፥48 በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው። ከዚህ በኋላ ጥቂት ቀን እንዲቀመጥ ለመኑት።
19፥5 ይህንም በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ፤
ይሄ ትክክልና ደግሞ የጥምቀትን ምንነት ለሚረዱ ለዚያ ዘመን ሰዎች ምንም ጥያቄ የሚፈጥር አልነበረም። ኢየሱስን ተከትዬ አዲስ ሕይወት ጀምሬአለሁ ማለት ነው ትርጉሙ። ስለዚህም የሚጠመቁት በኢየሱስ ስም ነበር።
ብዙ ጊዜ ጥያቄ የሚፈጥረው በማቴዎስ ወንጌል 28፡19
-20 ያለውና "እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው" የሚለው ስንኝ ነው። አንዳንዶች ይህ ስንኝ የስላሴ ትምህርት ከመጣ ከብዙ ዓመታት በኋላ የተጨመረ ስንኝ ነው እንጂ ኢየሱስ እንዲህ አልተናገረም ይላሉ። እንዲህ ተናግሮ ቢሆን ኖሮ ደግሞ ደቀመዛሙርቱ በኢየሱስ ብቻ አያጠምቁም ነበር ይላሉ። የሚያስኬድ ማብራሪያ ይመስላል። ሆኖም ግን ርግጠኛ ሆኖ ለመናገር አይቻልም።
አንዳንዶች ደግሞ ይህ የሚያሳየው የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ ስም ኢየሱስ ነው ብለው ያምናሉ። በእኔ ግምት ይህ ጨርሶ የሚያስኬድ አይደለም። ይህንን አንድ ጥቅስና ሐዋርያት ሥራ ላይ ያለውን በኢየሱስ ስም መጠመቅ አንድ ላይ አገናኝቶ የእግዚአብሔር ስም ኢየሱስ ነው ወደሚል ድምዳሜ መድረስ በፍጹም መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጓምን የተከተለ አይደለምና በእኔ እምነት የተሳሳተ መደምደሚያ ነው።
3) ጥምቀት ያድናል ወይ?
አንድ እዚህ ጋር ግልጽ ማድረግ ያለብን ነገር ያለ ይመስለኛል። በአዲስ ኪዳን ሰዎች ሲያምኑ ነበር የሚጠመቁት። ማለትም ባመኑበት ቀን ይጠመቃሉ እናም ጥምቀቱ እምነታቸውን የሚገልጹበት ነገር ነበር። እምነታቸውና ጥምቀታቸው ወዲያው አብሮ የሚሆን ነገር ነበር። ስለዚህ ተጠመቁ ማለት እምነታቸውን ገለጹ ማለት ነው እንጂ የጥምቀት ትምህርት ተምረው መጨረሳቸውን ማሳያ አልነበረም። ስለዚህ ጥምቀት የማመናቸው ምልክት ነው እንጂ በራሱ የመዳኛ መንገድ አይደለም።
መዳን በእምነት እንደሆነ የሚያሳዩ እጅግ በጣም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ አሉ። ስለዚህ መዳን በኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኛ አዳኝነትና በመስቀሉ ሥራ ማመን እንደሆነ ምንም የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም። ከክርስቶስ ጋር ተሰቅሎ የነበረው ወንበዴን ለምሳሌ ብንወስድ በክርስቶስ አምኖ ድኗል ነገር ግን አልተጠመቀም። የቆርኔሌዎስ ቤተሰዎችን በሐዋርያት ሥራ 10 ላይ ብንመለከት መንፈስ ቅዱስ የተሞሉት ገና ሳይጠመቁ ቃሉን ስላመኑ ብቻ ነው። ስለዚህ ጥምቀት በልብ ያለን እምነት መግለጫ እንጂ ድርጊቱ በራሱ አያድንም።
ጳውሎስ ራሱ በ1ቆሮንቶስ 1፡17 ሲጽፍ "ለማጥመቅ ክርስቶስ አልላከኝምና፥ ወንጌልን ልሰብክ እንጂ" ይላል። ማለትም ጥምቀት ዋና የመዳኛ መንገድ ቢሆን ኖሮ ጳውሎስ እንዲህም ባለለ ምክንያቱም የሰዎች መዳን ነበረና የእርሱ ዋናው የአገልግሎቱ እምብርት።
ከማዳን ጋር የተጠቀሰበትንም ቦታዎች በአዲስ ኪዳን ስናነብብ ማሰብ ያለብን፤ ባመኑበት ቀን እንደሚጠመቁ ነው። ስለዚህ ስለ ጥምቀት ማዳን የሚናገረው ስለ እምነቱ ነው። ለምሳሌ በማርቆስ 16፡16 ላይ "ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል" ይላል። ይሄ ያመነና የተጠመቀ የሚለው አንድ ነገር ነው። ያመነ ወዲያው ይጠመቃልና ስለዚህ የሚለያይ ነገር አይደለም። እምነቱን በጥምቀቱ ስለሚገልጸው ማለት ነው። ነገር ግን የሚፈረድበት ያልተጠመቀ አይደለም ነገር ግን ያላመነ ነው። ሰው በእምነት እንደሚድን ከሚናገሩት ከአብዛኛው የአዲስ ኪዳን ክፍሎች ጋር ይሄም ይስማማል። ያመነ ይድናል ያላመነ ይፈረደብታል። ያመነ ማለት ደግሞ ወዲያው ይጠመቃል።
ከዚህ ባለፈ ግን ጥምቀቱን ራሱን የመዳኛ ሥርዓት አድርገን የምንወስድ ከሆነ የአዲስ ኪዳንን ፍሬ ነገር አልተረዳነውም ማለት ነው። አዲስ ኪዳን የልብ ኪዳን ነው እንጂ የውጪያዊ ሥርዓት ኪዳን አይደለም። በውጪያዊ መገረዝ፤ ወይም ውሃ ውስጥ በመጠመቅ ወዘተ የመዳንና ያለመዳን ነገር የሚወሰንበት ኪዳን አይደለም። አዲስ ኪዳን በልብ አምኖ የሚዳንበትና የልብና የመንፈስ ለውጥ የሚደረግበት ኪዳን ነው።
Quote:
ትንቢተ ኤርምያስ 31
31 እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር
32 ከግብጽ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፦
33 ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል እግዚአብሔር ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል።
34 እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን፦ እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ አያስተምርም ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል እግዚአብሔር፦ በደላቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና።
ወደ ሮሜ ሰዎች
10፥10 ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና።