ጥያቄው እንደሚገባን በዮሐንስ 6፥37 ላይ ኢየሱስ ማንንም ከቶ ወደ ውጭ እንደማያወጣ ይናገራል በሌላ በኩል ደግሞ ለ
አንድ ሰው ከዳነ በኋላ ደህንነቱን ሊያጣ አይችልም ወይ? ጥያቄ በተሰጠው መልስ ላይ ሰዎች ከዳኑ በኋላ ደህንነታቸውን
(ድነታቸውን
) ሊያጡ እንደሚችሉ መልስ ተሰጥቶአል። ታዲያ እነዚህ አይጋጩም ወይ የሚል ይመስላል።
የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ስናጠና ዋናው መገንዘብ ያለብን የጥቅሶቹን ዓወድ
(context) እና ሙሉውን ሃሳብና መልእክት ለመያዝ ነው። ሁለት ጥቅሶችን ብቻ ለብቻቸው ለይተን ስናነጻጽር የሚጋጩ የሚመስሉ ብዙ ጥቅሶችን ማግኘት እንችላለን። የተነጠሉ ጥቅሶችን ብቻ ግን ማነጻጻር ሙሉውንና ደጋግሞ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ትልቁን መሠረታዊውን አስተምህሮት እንድንስተው ሊያደርገን ይችላል።
ኢየሱስ በእርግጥ በዮሐንስ 6፥37 ላይ "...ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም" ብሎአል። ታዲያ ይሄ ማለት ምን ማለት ነው
? ማንም ሰው እንደፈለገው በኃጢአትና በዓመጻ እየኖረ ይድናል ምንም ችግር የለም ማለት ነው
? በእርግጥ ይህ ክፍል አንዴ ደህንነትን ካገኙ በኋላ በኃጢትና በዓመጻ ስለሚኖሩ ሰዎች ነው የሚናገረው
? አይደለም!
Quote:
35 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም።
36 ነገር ግን አይታችሁኝ እንዳላመናችሁ አልኋችሁ።
37 አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም፤
38 ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና።
39 ከሰጠኝም ሁሉ አንድን ስንኳ እንዳላጠፋ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣው እንጂ የላከኝ የአብ ፈቃድ ይህ ነው።
40 ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።
ከላይ እንደምንመለከተው ክፍሉ የሚያወራው ከዳኑ በኋላ በኃጢአትና በዓመጻ መንገድ ስለሚመላለሱ ሰዎች ሳይሆን፤ ወደ ጌታ የሚመጡ ስለተገባላቸው ተስፋ ነው። ከቶ እንደማይራቡና እንደማይጠሙ እንዲሁም በመጨረሻው ቀን በትንሳኤ ተነስተው የዘላለም ሕይወት ወራሾች እንደሚሆኑ የሚናገር ነው። ስለዚህ ይህ ክፍል ጌታን በሚያሳዝን ህይወት ስለሚኖሩ አማኞች የተጻፈ ስላልሆነ፤ ይህን ክፍል አንዴ ድነው በኃጢአት መንገድ ስለሚመላለሱ ሰዎች ወይም ደህንነትን እንዳያጡ መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠንቀቂያ ስለሚሰጣቸው ሰዎች መጠቀም አንችልም።
ለ
አንድ ሰው ከዳነ በኋላ ደህንነቱን ሊያጣ አይችልም ወይ? ጥያቄ በሰጠነው መልስ ላይ የጠቀስናቸው ጥቅሶች ግን በቀጥታ አንድ አማኝ ደህንነቱን ሊያጣ እንደሚችል የሚናገሩና የሚያስጠነቅቁ ጥቅሶች ናቸው። የመልእክታቸው ዋና ሃሳብና ርዕስ ይሄንኑ ሰዎች ከዳኑ በኋላ ሊያጡት ስለሚችሉት ደህነነት የሚመለከት ስለሆነ እነዚያን በቀጥታ ስለዚሁ ርዕስ የሚያወሩትን መውሰድ ይኖርብናል እንላለን።