43፥1-2 | ራብም በምድር ጸና። ከግብፅም ያመጡትን እህል በልተው ከፈጸሙ በኋላ አባታቸው፦ እንደ ገና ሂዱ፤ ጥቂት እህል ሸምቱልን አላቸው። |
43፥3 | ይሁዳም እንዲህ አለው፦ ያ ሰው፦ ወንድማችሁ ከእናንተ ጋር ካልሆነ ፊቴን አታዩም ብሎ በብርቱ ቃል አስጠነቀቀን። |
43፥4 | ወንድማችንን ከእኛ ጋር ብትሰድደው እንወርዳለን፥ እህልም እንሸምትልሃለን፤ |
43፥5 | ባትሰድደው ግን አንሄድም፤ ያ ሰው፦ ወንድማችሁ ከእናንተ ጋር ካልሆነ ፊቴን አታዩም ብሎናልና። |
43፥6 | እስራኤልም አላቸው፦ ለምን በደላችሁኝ? ለዚያውስ፦ ሌላ ወንድም አለን ብላችሁ ለምን ነገራችሁት? |
43፥7 | እነርሱም አሉ፦ ያ ሰው ስለ እኛና ስለ ወገናችን ፈጽሞ ጠየቀን እንዲህም አለን፦ አባታችሁ ገና በሕይወት ነው? ወንድምስ አላችሁን? እኛም እንደዚሁ እንደ ጥያቄው መለስንለት፤ በውኑ፦ ወንድማችሁን አምጡ እንዲለን እናውቅ ነበርነን? |
43፥8 | ይሁዳም አባቱን እስራኤልን አለው፦ እኛና አንተ ልጆቻችንም ደግሞ እንድንድን እንዳንሞትም ብላቴናውን ከእኔ ጋር ስደደው፥ እኛም ተነሥተን እንሄዳለን። |
43፥9 | እኔ ስለ እርሱ እዋሳለሁ ከእጄ ትሻዋለህ፤ ወደ አንተ ባላመጣው፥ በፊትህም ባላቆመው፥ በዘመናት ሁሉ አንተን የበደልሁ ልሁን። |
43፥10 | ባንዘገይስ ኖሮ አሁን ሁለተኛ ጊዜ በተመለስን ነበር። |
43፥11 | እስራኤልም አባታቸው እንዲህ አላቸው፦ ነገሩ እንዲህ ከሆነስ ይህንን አድርጉ፤ ከተመሰገነው ከምድሩ ፍሬ በዓይበታችሁ ይዛችሁ ሂዱ፥ ለዚያም ሰው እጅ መንሻ፥ ጥቂት በለሳን፥ ጥቂት ማር፥ ሽቱ፥ ከርቤ፥ ተምር፥ ለውዝ ውሰዱ። |
43፥12 | ብሩን በአጠፌታ አድርጋችሁ በእጃችሁ ውሰዱ በዓይበታችሁ አፍ የተመለሰውንም ብር መልሳችሁ ውሰዱ ምናልባት በስሕተት ይሆናል። |
43፥13 | ወንድማችሁንም ውሰዱ፥ ተነሥታችሁም ወደዚያ ሰው ተመለሱ። |
43፥14 | ሁሉን የሚችል አምላክም ሌላውን ወንድማችሁንና ብንያምን ከእናንተ ጋር ይሰድድ ዘንድ በዚያ ሰው ፊት ምሕረትን ይስጣችሁ፤ እኔም ልጆቼን እንዳጣሁ አጣሁ። |
43፥15 | ሰዎቹም በእጃቸው ያችን እጅ መንሻና አጠፌታውን ብር ብንያምንም ወሰዱ፤ ተነሥተውም ወደ ግብፅ ወረዱ፥ በዮሴፍም ፊት ቆሙ። |
43፥16 | ዮሴፍም ብንያምን ከእነርሱ ጋር ባየው ጊዜ የቤቱን አዛዥ እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ እነዚያን ሰዎች ወደ ቤት አስገባቸው፥ እርድም እረድ አዘጋጅም፥ እነዚያ ሰዎች በእኩለ ቀን ከእኔ ጋር ይበላሉና። |