ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች » ኤፌሶን » ጥናት 10 (ኤፌሶን 3፣14-21) ሁለተኛው የጳውሎስ ጸሎት
Email this page to a friend Printer-friendly   Tuesday, 20 October 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦“
(የዮሐንስ ራእይ 3:14)

rss

Today's verse

ጥናት 10 (ኤፌሶን 3፣14-21) ሁለተኛው የጳውሎስ ጸሎት

pdf version

 

·       ሀ)ለምን እና በምን ሁኔታ እንደሚጸልይ ቁ. 14-15

·       ጳውሎስ ይህን ክፍል ሲጀምር “ስለዚህ ምክንያት” ብሎ ነው:: ይህም ከላይ ከኤፌ 3፣1 ጀምሮ ሲገልጽ የነበረውን ሃሳብ በመቀጠል ነው:: አሕዛብ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ቤተሰብና አብረው ወራሾች ስለሆኑና ለታላቅ ጥሪ ስለተጠሩ፣ ጳውሎስም እነርሱን የማገልገል ኃላፊነትና አደራ ስለተሰጠው፣ ስለ እነርሱ ይጸልያል:: የተሰጠው ኃላፊነት ለእነርሱ መስበክና ለራሱ አገልግሎት መጸለይ ብቻ ሳይሆን፣ ለእነርሱም መማለድ ነው:: ይህን አይነቱን በጸሎት የተደገፈ አገልግሎት በጌታም ሕይወት እንመለከታለን ሉቃ 22፣31-32 ዮሐ 17፣6-26:: ጳውሎስ ጸሎቱን በምን ሁኔታ እንደሚያቀርብ ሲጸልይ “በሰማይና በምድር ያለ አባትነት ሁሉ ከሚሰየምበት ከአብ ፊት እንበረከካለሁ” ይላል:: ይህ “አባትነት” የሚለው ቃል በግሪኩ ቤተሰብ ከሚለው ቃል ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው:: ስለዚህ ይህ ክፍል በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “በሰማይና በምድር ያለ ቤተሰብ ሁሉ ከሚሰየምበት ወይም መጠሪያ ከሚያገኝበት” ተብሎ ተተርጉሞአል (አዲሱን መደበኛ ትርጉም  ይመልከቱ):: ይህም ማለት በሰማይም ያለ ቤተሰብ፣ በምድርም ያለ ቤተሰብ የሚጠራው በአብ ነው ወይም “የእግዚአብሔር ቤተሰብ” ነው ለማለት ነው:: በኤፌ 2፣19 ላይ ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ቤተሰብ እንደሆነች ተመልክተናል:: በኤፌሶን መልእክት ውስጥ የሰማዩ ቤተስብ ምን እንደሆነ ባይጠቀስም፣ በቤተክርስቲያን በክርስቶስ አሕዛብም አይሁድም አንድ የእግዚአብሔር ቤተሰብ ወይም የአንድ አባት ልጆች እንደሆኑ ተጠቅሶአል:: መጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ በአብ ስለሚጠራ ቤተሰብ ብዙም ባይገልጽም፣ በኢዮብ 2፣1 እና 38፣7 ላይ መላእክት የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ሲጠሩ እንመለከታለን:: ስለዚህ የእግዚአብሔር የሆኑት በሰማይም ይሁን በምድር ያሉት ቤተሰቦች መጠሪያ ወይም አንድ አባት አብ ብቻ ነው:: እንግዲህ ጳውሎስ የሚጸልየው ወደ አብ ነው:: ጸሎት ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው የሚደረግ ነገር አይደለም ማቴ 6፣5-6:: ስለዚህ አድራሻን ጠንቅቆ ማወቅ በጣም ያስፈልጋል:: ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ ጸሎቱን የሚጸልየው በአብ ፊት ተንበርክኮ ነው:: ተንበርክኮ መጸለይ በአይሁድ ብዙ የተለመደ አይደለም:: ነገር ግን በአዲስ ኪዳን በጌታም ይሁን በጳውሎስ ሕይወት የምንመለከተው፣ ለእግዚአብሔር ያለ አክብሮትን የሚያሳይ፣ በፊቱ የሚገባ ትህትናና ራስን ማዋረድ ነው ሉቃ 22፣41 የሐዋ 20፣36:: በአሁኑ ዘመን በክርስቲያኖች ዘንድ መንበርከክ ልምድ ከመሆኑ የተነሳ፣ ለእግዚአብሔር የሚገባ አክብሮትንና በፊቱ በትህትናና በመዋረድ መቅረብን ከማሳየት ይልቅ፣ ብዙ ጊዜ መቆም ሲደክመን ብቻ ለማረፍ የምናደርገው ድርጊት እየሆነ ነው::

 

·       ለ)የጸሎቱ ይዘት ቁ. 16-19

·       በኃይል እንድትጠነክሩ:- በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በኃይል እንዲጠነክሩ ጳውሎስ የሚጸልየው ስለ ውስጥ ሰውነታቸው/ሰዋቸው/inner man ነው:: ይህ የውስጥ ሰውነት ወይም የውስጥ ሰው የሚባለው እውነተኛው የውስጥ ማንነታችንና እግዚአብሔርም አብዝቶ የሚገደው ማንነታችን ነው ኤፌ 4፣22-24 1ጴጥ 3፣4:: ጥንካሬ የሚለካና የሚሞከር ነገር ነው:: አንድ ነገር ከውጪ የሚገፋውን ኃይል መቋቋሙና በውጪ ተጽእኖ አለመሸነፉ ጥንካሬው ነው:: የውስጥ ሰውነታችንም ሲጠነክር ከውጪ የሚመጣብንን የዕለት ተለት ግፊትና ተጽእኖ ለመቋቋምና ለመቆም ያስችለናል:: “ስለዚህ አንታክትም ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል:: የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፣ ቀላል የሆነ የጊዜው መክራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና የሚታየው የጊዜው ነውና የማይታየው ግን የዘላለም ነው::” 2ቆሮ 4፣16:: ልክ እንደዚሁ ባለፈው ጥናታችን በኤፌ 3፣13 በጳውሎስ መከራ ምክንያት የኤፌሶን ሰዎች እንዳይታክቱ/እንዳይዝሉ/ተስፋ እንዳይቆርጡ ሲያሳስባቸው ተመልክተናል:: ከላይ በተጠቀሰውም በ2ቆሮ 4፣16 ላይ የማያታክተውና ተስፋ የማያስቆርጠው አንዱ ምክንያት የውስጥ ሰውነት ዕለት ዕለት መታደሱ ነው:: የውስጥ ሰውነታቸው በመንፈስ ቅዱስ የጠነከረ ሰዎች በቀላሉ በመከራ ቶሎ አይዝሉም:: እዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገባን ጥንካሬው የሚመጣው ከመንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ነው:: እውነተኛ የውስጥ ጥንካሬ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለ የዕለት ተለት ሕብረት ውጤት ነውና::

 

·       ክርስቶስ በልባችሁ እንዲኖር:- “ልብ” እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ ጥልቅ የሆነው የሰው የውስጠኛው ክፍል ነው:: ክፉውም መልካሙም የሰው ማንነት የሚመነጨው ከልብ ነው:: “ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ መጎምጀት፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ መዳራት፣ ምቀኝነት፣ ስድብ፣ ትዕቢት፣ ስንፍና ናቸውና ይህ ክፉው ሁሉ ከውስጥ ይወጣል ሰውንም ያረክሰዋል::“ ማር 7፣21-23:: ልብን የሞላው ነገር ማንነትን እና ሕይወትን ይወስናል:: “...በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና:: መልካም ሰው በልቡ መልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፣ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል::” ማቴ 12፣34-35:: ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ልባችንን ለሁሉ ነገር እንዳንከፍት ይልቁን ግን አጥብቀን እንድንጠብቅው ይመክረናል “አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፣ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና::” ምሳ 4፣23:: ሌላው ጳውሎስ “ክርስቶስ በልባችሁ በእምነት እንዲኖር” ሲል፣ ይህ እንዲኖር የሚለው ቃል የሚያመለክተው ቤቱ ማድረግን፣ ቋሚ መኖሪያው ማድረግን ወይም በእንግሊዝኛው dwell, habitation, place of residence የሚለውን ነው:: ይህም ጌታ በአንደበታችን፣ በመዝሙራችንና በአእምሮአችን መኖሩ ብቻ በቂ እንዳልሆነና፣ ነገር ግን ውስጠኛውን የሕይወት ክፍላችንን ቋሚ መኖሪያውና ማደሪያው እንዲያደርገው ነው ዮሐ 14፣23:: ልቡን የገንዘብ ምኞት መኖሪያ ያደረገ ሰው፣ ወሬውም ሩጫውም ሃሳቡም የገንዘብ እንደሚሆን፣ እንዲሁ ልቡን ሙሉ የክርስቶስ ማደሪያ ያደረገ ሰው፣ ሃሳቡና ሩጫው፣ ምኞቱም የክርስቶስ ነገር ይሆናል::

 

·       ሥርና መሠረታችሁ በፍቅር ይጸና ዘንድ:- በዚህ ክፍል “ሥር” የሚለው ቃል የአትክልት አይነት ሥርን የሚያመለክት ሲሆን፣ “መሠረት” የሚለው ቃል ደግሞ የቤት ወይም የሕንጻ አይነት መሠረትን የሚያመለክት ነው:: የAmplified መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ይተረጉመዋል:- “May you be rooted deep in love and founded securely on love”:: ይህም ማለት ልክ አንድ አትክልት ሥሩን በአፈር ውስጥ እንደሚሰድድና እንደሚጸና፣ የኤፌሶንም ሰዎች በፍቅር ሥር የሰደደ ሕይወት እንዲኖራቸው፣ እንዲሁም አንድ ሕንጻ የሚቆምበትና የሚጸናበት መሠረት እንዳለው ሁሉ እነርሱም የሕይወታቸው መሠረት ፍቅር እንዲሆንና በፍቅር ላይ ተመሥርቶ የጸና ሕይወት እንዲኖራቸው ነው የጳውሎስ ጸሎት:: ይህም በፍቅር ላይ የተተከለና በፍቅር ላይ ተመሥርቶ የተገነባና የጸና ሕይወት ማለት ነው:: አንድ አትክልት ሥሩን የሚሰድድበት ቦታ ወይም የመሬት አይነት ለአትክልቱ እድገትና ጽናት እጅግ ወሳኝ ነው:: ምክንያቱም በድንጋያማና ብዙ አፈር በሌለው መሬት ላይ የተተከለ ተክል ብዙ ሥሩን ሊሰድድና ሊጸና አይችልም:: “ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ (ድንጋያማ መሬት) ላይ ወደቀ፣ ጥልቅ መሬትም ስላልነበረው ወዲያው በቀለ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፣ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ::” ማቴ 13፣5-6:: ልክ እንደዚሁ አንድ ቤትም የሚመሠረትበት መሠረት ለቤቱ ጽናት ከፍተኛ አስተዋጾ አለው:: በደህና መሠረት ላይ ያልተመሠረተ ቤት ብዙ ውጫዊ ግፊቶችን ተቋዋቁሞ መጽናት አይችልምና:: “ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል:: ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፣ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም:: ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን የመስላል:: ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት መታው ወደቀም፣ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ::” ማቴ 7፣24-27:: በፍቅር ላይ ሳይሆን ነገር ግን በራስ ወዳድነት ወይም በጥላቻ ወይም በአገልግሎት ወዘተ ላይ የተመሠረተ ሕይወት በጌታ ዘንድ ሊጸና አይችልም:: ለምናደርገው ሁሉ መሠረቱና የምናደርገውን እንድናደርግ የሚያነሳሳን ነገር/motive ፍቅር ካልሆነ በእግዚአብሔር ሚዛን ላይ እንቀልላለን:: እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ከመሆንም አናልፍም 1ቆሮ 13፣1-3:: ምንም እንኳን የኤፌሶን ሰዎች ፍቅር እንዳላቸው የተገለጸ ቢሆንም (ኤፌ 1፣15) ይበልጥ በፍቅር ሥር እንዲሰድዱና ሕይወታቸው የቆመበት ዋና መሠረት ፍቅር እንዲሆን ጳውሎስ ይጸልይላቸዋል::

 

·       የክርስቶስን ፍቅር ታውቁ ዘንድ:- ከላይ ከተጠቀሰው ጋር አብሮ ለእነዚህ ቀድሞውንም ፍቅር እንዳላቸው ለተመሰከረላቸው ለኤፌሶን ምእመናን ጳውሎስ የሚጸልየው ሌላው ጸሎት፣ “ከመታወቅ የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ እንዲበረቱ” ነው ቁ. 18-19:: እዚህ ላይ መጀመሪያ ቃሉ ሲነበብ ትንሽ የማይገባና የተቃረነ ነገር ያለ ይመስላል:: ምክንያቱም ቀድሞውንም ከመታወቅ የሚያልፍን ነገር ወይም ታውቆ ሊጨረስ የማይችልን ነገር እንዲያውቁ መጸለይ ይገርማል:: ይህ አባባል ግን ሊያመለክት የፈለገው፣ ይህን ከመታወቅ በላይ የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር ራሳቸው ተለማምደው፣ ከአእምሮ በላይ መሆኑን እንዲገነዘቡና እንዲረዱ ነው:: ምሳሌ ለመስጠት ያህል:- የውቅያኖስን ትልቅነትና በውስጡ ያዘለውንም የሕይወትን ብዛት ሰው በርቀት ሆኖ ሲሰማና ራሱ ደግሞ የውቅያኖስ ውስጠኛው ክፍል ድረስ ገብቶ የሚያገኘው ግንዛቤ የተለያየ ነው:: የውቅያኖስን ትልቅነት ራሱ ሄዶ ማየቱ፣ ውቅያኖስን በሙሉ እንዲያውቅ አያደርገውም:: ነገር ግን የውቅያኖስን እጅግ ትልቅነት የበለጠ እንዲገነዘብ ያደርገዋል:: ጳውሎስም በዚህ ክፍል የሚጸልየው የተለያዩ ገጽታዎች/dimensions ያሉትን የክርስቶስን ፍቅር ተለማምደው የፍቅሩን ታላቅነትና ከመታወቅ የሚያልፍ መሆኑን ራሳቸው እንዲገነዘቡ ነው:: የAmplified መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ክፍል እንደሚከተለው ይተረጉመዋል:- “[That you may really come] to know [practically, through experience for yourselves] the love of Christ, which far surpasses mere knowledge [without experience]”:: በዚህ ክፍል ስለ ክርስቶስ ፍቅር ሌላው የተጠቀሰው ነገር ከአንድ አይነት ያለፈ የተለያዩ ገጽታዎች/dimensions ያሉት መሆኑ ነው:: “ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል” ይላል ቁ. 18:: በዚህ ክፍል የእነዚህ  ገጽታዎች ምንነትና ትርጉም ባይጠቀስም፣ የተለያዩ የክርስቶስን የፍቅር ገጽታዎችና ባሕርያት ግን ማስተዋል የሚቻለው ከቅዱሳን ጋር አብሮ እንጂ ለብቻ እንዳልሆነ ተገልጿል:: “ከቅዱሳን ሁሉ ጋር” የሚለው አባባል ከቅዱሳን ጋር አብራችሁ፣ በጋራ ማለት ነው:: ይህም ከቅዱሳን ጋር አብራችሁ፣ በጋራ የክርስቶስን ፍቅር የተለያዩ ገጽታዎች/dimensions ለማስተዋል ትችሉ ዘንድ ማለት ነው:: በተለይ ክርስቶስ (ወደ ጎን) ሰውን ከነድካሙ እንዴት እንደወደደ፣ በከበረ ደሙ ለዋጃት ቤተክርስቲያንም ያለውን ፍቅር ወዘተ ከቅዱሳን ጋር አብረን እንጂ ለብቻችን የምንለማመደውና የምንገነዘበው ነገር አይደለም:: ለብቻችን ምናልባት ጌታ እኛን በግል (ከላይ ወደ ታች) የወደደበትን ፍቅር ትልቅነት እንገነዘብ ይሆናል:: የፍቅሩን ሙሉውን ገጽታዎች ግን ለማስተዋል የምንችለው ከቅዱሳን ጋር አብረን ነው:: የጠፋውን ልጅ አባቱ አዝኖ በእቅፉ በፍቅር እንደተቀበለው (ሉቃ 15፣20)፣ “ስለዚህ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር እንደ ተቀበላችሁ እንዲሁ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ” (ሮሜ 15፣7) የሚለውን የጌታን ቃል ለመረዳትና በተግባርም የጌታን ፍቅር ለመለማመድ የሚቻለው ከቅዱሳን ጋር ብቻ ነው::

 

·       እስከ እግዚአብሔር ፍጹም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ:- ይህ አባባል በእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ መሞላትን፣ በሁሉም አቅጣጫ እግዚአብሔር እስካሰበላቸው ድረስ በእርሱ ማንነትና ባሕርይ ተሞልተው እርሱ ያሰበላቸው የእድገት ደረጃ ላይ መድረስን የሚያሳይ ነው:: ይህም እስከ አሁን የጸለየው ጸሎት ዓላማና ግብ ነው ነው:: ማለትም መንፈስ ቅዱስ በሙላት በኤፌሶን ሰዎች ሕይወት ውስጥ ኖሮ የውስጥ ጥንካሬ እንዲሰጣቸው፣ ክርስቶስም ልባቸውን ቋሚ መኖሪያውና ቤቱ እንዲያደርግ፣ ሕይወታቸው በፍቅር ላይ የተተከለና የጸና እንዲሆን፣ ከቅዱሳንም ጋር አብረው የጌታን ፍቅር ገጽታዎች ሁሉ ማስተዋል እንዲችሉና በሁሉም ነገር እግዚአብሔር እስካሰበላቸው የእድገትና የሙላት ደረጃ እንዲደርሱ፣ በአንድም አቅጣጫ እግዚአብሔር ካሰበላቸው ሙላት እንዳይጎድሉ የጳውሎስ ጸሎት ነው::

 

·       ሐ)በእምነት የተደረገ ጸሎት ቁ. 20:-

·       እስከ አሁን ከላይ የተዘረዘሩትን የጳውሎስን ጸሎቶች ስንመለከት እጅግ ዋና ዋናና እግዚአብሔርም ብቻ ሊያደርጋቸው የሚችሉ፣ ሰው ወይም አገልጋይ ሊያከናውናቸው የማይችሉ ነገሮች ናቸው:: ምክንያቱም ይዘታቸው በሙሉ መንፈሳዊና የሰውን ሕይወት ለውጥ የሚመለከቱ ነገሮች ናቸውና:: ጳውሎስ ግን ሰው ፈጽሞ ሊያደርጋቸው የማይችላቸውን ነገሮች ይዞ በጸሎት ወደ አብ ፊት ተንበርክኮ ሲያቀርብ አንድ ድንቅ የሆነ የአብን ባሕርይ ተረድቶና አምኖ ነው:: ይሄውም አብ “በእኛ እንደሚሠራው ኃይል መጠን ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ” እንደሚቻለው አምኖ ነው ቁ. 20:: በዚህ መረዳትና እምነት ላይ ያልተመሠረተ ጸሎት ንግግርና የጸሎት ፕሮግራም ብቻ ከመሆን አያልፍም:: አብ በእኛ እንደሚሠራው ኃይል መጠን ወይም ክርስቶስን ከሙታን እንዳስነሳው መንፈስ ኃይል መጠን (ሮሜ 8፣11) ሁሉን ሊያደርግ የሚችል፣ የእኛንም ይሁን የሌሎችን ሕይወት ሊለውጥና “ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ” የሚችል አባት ነው:: እንደዚህ አይነት የአብ መረዳት ከሌለን ጸሎታችንንና ሸክማችንን ይዘን ወደ እርሱ ፊት ለመቅረብ ብዙ አንበረታታም:: ጽሎት ቅዱሳን ሁሉ ሊያደርጉት የሚገባ የሃይማኖት ሥርዓት አይደለም:: ነገር ግን ልመናችንን ይዘን ወደሚሰማንና ሰምቶም ወደሚመልስ፣ ሁሉንም ወደሚችል ወደ አባታችን ፊት በእምነት የምንቀርብበት እንጂ:: እንዲህ የአብን ማንነትና የጸሎትን ኃይል ብንረዳ፣ ብዙ እንቆቅልሾቻችንን ለመፍታት የምናደርገውን የሥጋ ትግል፣ የሥጋ ዘዴና የሥጋ ሩጫ አቁመን በአብ ፊት እንምበረከክ ነበር::

 

·       መ)በምስጋና የተደረገ ጸሎት ቁ. 21:-

·       በጳውሎስ ጸሎት አንዱ የሚገርመው ነገር፣ የአብን ማንነት ከማውቁ የተንሳና በአብ ላይም ካለው ታላቅ እምነት የተነሳ፣ ገና ከጸሎቱ ጋር አብሮ ምስጋናውንም ጨምሮ ነው ለአብ የሚያቀርበው:: ምክንያቱም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አብ ዘንድ የቀረበና አብ የሰማው ነገር እንደሚፈጸም ስለሚያውቅ፣ ለምስጋና የጸሎቱን መልስ ፍጻሜ መጠበቅ አላስፈለገውም:: ጸሎት በአብ ፊት በመንበርከክ/በትሕትና/ራስንም በፊቱ ዝቅ በማድረግና አብንም በማመስገን የሚቀርብ እንጂ እንደ ይገባኛል ጥያቄ በማጉረምረምና እግዚአብሔርን በመክሰስ የሚቀርብ አይደለም::

 

·       ሠ)ማጠቃለያ:-

·  ለኤፌሶን ሰዎች የጸለየው የመጀመሪያው የሐዋርያው ጳውሎስ ጸሎት ማየት፣ መረዳትና ማወቅ ላይ ያተኮረ ሲሆን (ኤፌ 1፣15-19)፣ በዚህ ክፍል የተመለከትነው ሁለተኛው ጸሎቱ ደግሞ በፍቅር ላይ ያተኮረ ነው:: በዚህ ሁሉ ልብ ልንል የሚገባን የመጀመሪያው ነገር፣ ጳውሎስ አገልግሎቱ እጅግ በጸሎት የተደገፈ እንደነበረ ነው:: ለብዙ አብያተ ክርስቲያናትም ይጸልይ ነበር:: የሚጸልየውም በጊዜው ለሚያገለግላቸው አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ሳይሆን፣ ቀድሞ ላገለገላቸውና እንዲያውም ጨርሶ ከዚህ ቀደም ላላገለገላቸውም ጭምር ነው ሮሜ 1፣8-10 1ተሰ 1፣2 ቆላ 1፣3 ቆላ 2፣1 ፊልጵ 1፣3-4:: ሁለተኛው ልናስተውል የሚገባን ነገር ጸሎቱ ብዙ ጊዜ እንዲሁ በጥቅሉ “ባርካቸው” ብቻ ከሚል ያለፈና ስለ እነርሱ የሚማልደውን ነገር በስሙ እያንዳንዱን ነገር እየጠራ የሚጸልይ መሆኑ ነው:: ይህም በተለይ በሁለቱ ለኤፌሶን ሰዎች በጸለየው ጸሎቶቹ ላይ ጎልቶ ይታያል:: ሳናስተውል የማናልፈው ሌላው ነገር ደግሞ ጸሎቱ ያነጣጠረው መንፈሳዊ ሕይወት ላይ እንጂ ሥጋዊና ምድራዊ ነገር ላይ አለመሆኑን ነው:: እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነና በአብ ፊት የሚሰማ ጸሎት እንድንጸልይ እግዚአብሔር ይርዳን::


“ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ።“
(መጽሐፈ ምሳሌ 3:3-4)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us