ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች » ኤፌሶን » ጥናት 11 (ኤፌሶን 4፣1-16 ሀ) ለጥሪው የሚገባ አካሄድ - ክፍል 1
Email this page to a friend Printer-friendly   Tuesday, 20 October 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦“
(የዮሐንስ ራእይ 3:14)

rss

Today's verse

ጥናት 11 (ኤፌሶን 4፣1-16 ሀ) ለጥሪው የሚገባ አካሄድ - ክፍል 1

pdf version

ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ በኤፌሶን መልእክቱ ላይ እስከ አሁን በተመለከትናቸው ክፍሎች ውስጥ ማለትም ከምዕራፍ 1 እስከ ምዕራፍ 3 መጨረሻ ድረስ እግዚአብሔር በምን ያህል ዘላለማዊ ጥሪ እንደጠራንና በታላቅ ፍቅሩም ምን ያህል እንዳደረገልን ዘርዝሮአል:: በነዚህ ክፍሎች ውስጥ ሁሉ የእግዚአብሔር ሥራ እንጂ የአማኞች ሥራ አልተጠቀሰም:: ከምስጋና ሌላ አማኞች ሊያደርጉት የሚገባ ነገር ወይም ትእዛዝ አልተጻፈም:: ከአሁን በኋላ በምንመለከታቸው ክፍሎች ማለትም ከምዕራፍ 4፣1 እስከ ምዕራፍ 6፣9 ድረስ ደግሞ እንደ ክርስቲያን አኗኗራችንና አካሄዳችን ምን መምሰል እንዳለበት እንመከራለን:: ከዛሬው ጥናታችን እስከ ምዕራፍ 6፣9 ድረስ የምንመለከተውም እንግዲህ ይሄንኑ ማለትም ተግባራዊ የሆነውን የአኗኗራችንን ጉዳይ ነው::

 

ይህን የጥናታችንን ክፍል ማለትም ጳውሎስ “ለተጠራችሁበት መጠራት እንደሚገባ” ብሎ የጠቀሰውን ሃሳብ እንደሚከተሉት በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ከፍለን እናጠናለን::

 

1.              የጥሪው ምንነት

2.              የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ መትጋት

3.              ሰባቱ የአንድነት መሠረቶች

4.              የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማውቅ ወደሚገኝ አንድነት ማደግ

 

በዚህ በክፍል 1 ጥናታችን ላይ ቁጥር አንድንና ሁለትን የምንመለከት ሲሆን፣ በሚቀጥሉት ተከታታይ ጥናቶቻችን ደግሞ ቁጥር ሶስትንና አራትን እንመለከታለን::

 

1.             የጥሪው ምንነት ቁ. 1

 

ከዚህ በፊት በነበሩት ክፍሎች ውስጥ እግዚአብሔር በምን ያህል ፍቅር እንደወደደንና እኛን የጠራበትም ዘላለማዊ አላማውና ጥሪው ምን ያህል ታላቅ እንደ ሆነ ጳውሎስ ገልጿል:: ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔር የዘላለም አሳቡ በክርስቶስ በሰማይና በምድር ያሉትን መጠቅለልና አንድ ማድረግ እንደሆነ በኤፌ 1፣10 ላይ ተመልክተናል:: በኤፌ 2 ላይም፣ ሊታረቁ እንደማይችሉ ሆነው የተለያዩትንና በመካከላቸው የጥል ግድግዳ የነበረውን አሕዛብንና አይሁድን በክርስቶስ አንድ ማድረግ የዚህ የዘላለም አሳቡ አንዱ ክፍል እንደሆነም ተመልክተናል:: እነርሱንም ከጥል ወደ እርቅና ሰላም፣ ከመጻተኛነትና ከእንግድነት ወደ ቤተሰብነትና የአንድ አገር ሰው ወደ መሆን፣ ወደ አንድ አካልነትና አብሮ ወደሚሠራ አንድ ሕንጻነት ወዘተ በክርስቶስ እንደለወጣቸው ተመልክተናል (ጥናት 7-8):: ስለዚህም የእግዚአብሔር ዋና ጥሪ ለአንድነት፣ ለቤተሰብነትና ለሰላም ነው:: ጳውሎስ እንግዲህ በዚህ ክፍል ይህንን የአንድነትና የሕብረት ጥሪ የሚመጥን ወይም ለዚህ የቤተሰብነትና አንድ አካል ለመሆን መጠራት የሚገባ አኗኗር እንድንኖር ይመክረናል::

 

በዚህ ክፍል በአማርኛ መመላለስ ተብሎ የተተረጎመው ቃል፣ የዕለት ተዕለት አኗኗርን፣ አካሄድን፣ ጠባይን ወዘተ የሚያመለክት ነው:: እንግዲህ ጳውሎስ የኤፌሶን ሰዎች የየዕለቱ አኗኗራቸው የተጠሩበትን የአንድነትና የቤተሰብነት ጥሪ የሚመጥን እንድሆን ይለምናቸዋል::

 

በዚህ ቁጥር ላይ ከጳውሎስ አነጋገር ልብ ልንል የሚገባን አንዱ ነገር፣ እንዴት አድርጎ ወይም በምን አይነት አነጋገር ይህንን ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው ነው:: ምንም እንኳን ጳውሎስ ሐዋርያ ቢሆንም፣ በዚህ ክፍል ግን ሐዋርያዊ ሥልጣኑን ተጠቅሞ ለማዘዝ ወይም በሥልጣኑ ለማስፈራራት አልሞከረም:: ነገር ግን በትሕትና ሲለምናቸውና እናት ልጇን በፍቅር እንደምታሳስብ ሲያሳስባቸው እንመለከታለን 1ተሰ 2፣7:: በሥልጣንና በግድ ምናልባት ውጪያዊ ነገርን ማስደረግ ይቻል ይሆናል፣ ልብን ማግኘት ግን የሚቻለው በፍቅርና በትሕትና ብቻ ነው:: ከጌታ ጊዜ ጀምሮ በአዲስ ኪዳን የምናየውም መታዘዝ ከእውቀት፣ ከእምነትና ከፍቅር የሚመነጭ መታዘዝ እንጂ፣ ከበላይ ትዕዛዝ የሚመነጭ አይደለም:: “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል” ዮሐ 14፣23:: “እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፣ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላቸው::” ዮሐ 15፣10 ሮሜ 1፣5:: ምንም እንኳን የቤተክርስቲያንን ጤንነት ለመጠበቅ ሲባል፣ የቤተክርስቲያን ስልጣን ቢኖርም፣ በታላቅ ቁጠባና ጥንቃቄ በሥራ ላይ የሚውል ብቻ ነው እንጂ መደበኛ አሠራሩ አይደለም:: 1ጴጥ 2፣11/13::

 


 

2.             የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ መትጋት ቁ. 2-3

 

ጳውሎስ በዚህ ክፍል ለተጠራችሁበት መጠራት የሚገባ/የሚመጥን ኑሮ/አካሄድ ብሎ የሚጠቅሰው ዋና ነገር የአንድነትና የሕብረት ጉዳይ ነው:: ጥሪያችን ራሱ ለታላቅ ሕብረትና አንድነት ስለሆነ፣ ያንን የሚመጥን ኑሮ እንድንኖር ነው የምንመከረው:: ጥሪውን የሚመጥን ኑሮ ተብለው ከተጠቀሱት አኗኗሮች ውስጥ በመጀመሪያ ደረጃ የሚከተሉት ይገኙበታል:-

 

ሀ)ትሕትና ሁሉ (with all humility)

ይህንን ቃል የግሪኩ ሌክሲከን እንደሚከተለው ይተረጉመዋል:- complete lowliness of mind፣ simple, having a humble opinion of one's self, a deep sense of one's (moral) littleness, modesty. ይህም ማለት ስለ ራስ ዝቅ ያለ አስተሳሰብ መኖር፣ የራስን ዝቅተኝነት ወይም ትንሽነት መገንዘብ፣ ስለ ራስ ዝቅ ያለ የልብ አቋም መኖር ማለት ነው:: ስለዚህ ትሕትና በዋነኛ ደረጃ አንድ ሰው ስለ ራሱ ያለውን አስተሳሰብንና የልቡን አቋም የሚመለከት ነው:: ስለ ራሱ አንድ ሰው ምን አይነት አመለካከት አለው? ልቡ ስለ ራሱ ምን አይነት አቋም ነው ያለው? የሚለው ላይ ያተኮረ ነው:: ይህ ደግሞ ለተጠራንበት የአንድነትና የቤተሰብነት ጥሪ እንደሚገባ ለመኖር አንዱ ወሳኝ ነገር ነው:: በሕብረት ውስጥ ትሕትና ከሌለ፣ በዚያ ፈንታ ግን ትዕቢትና እኔ እበልጣለሁ የሚል የልብ አቋም ካለ፣ እውነተኛ ሕበረት፣ መስማማት፣ መግባባት ወይም harmony እንዳይኖር ያደርጋል:: ትሕትና የሌለው ሰው ስለ ራሱ ያለው አመለካከት በጣም የተዛባ ስለሚሆንና ሌሎች ከእርሱ እንደሚያንሱ ስለሚያስብ፣ እርሱ ያልነካው፣ የእርሱ ሃሳብ ያልሆነ፣ እርሱ የሌለበት ነገር ሁሉ በትክክል ይሠራል ብሎ አይገምትም፣ ስለዚህም የሌሎችን አገልግሎትና ጸጋ ለመቀበል ይቸገራል::  ሌሎችም ደግሞ በልቡ ራሱን ከፍ አድርጎ ከሚያስብ ሰው ጸጋውንና አገልግሎቱን ከልብ ለመቀበል እጅግ ይከብዳቸውል:: ትሕትና አለመኖር መቀባበልንና መደጋገፍን የሚከለክል ስለሆነ እውነተኛውን ሕብረት ለማድረግ ትልቅ እንቅፋት ነው:: ስለዚህ በጥናት 9 ላይ በጳውሎስ ሕይወት እንደተመለከትነውና ጳውሎስ ራሱን ከቅዱሳን ጋር ሲያለካካ “ከቅዱሳን ሁሉ ለማንስ” ብሎ እንደተናገረ፣ እንዲሁ እኛም ስለራሳችን ያለን አመለካከትና የልብ አቋም ዝቅ ያለ ሊሆን ይገባል:: ራስን ከፍ አድርጎ መቁጠር፣ ያለ እኔ ማን አለ ማለት፣ ሌሎች ሁሉ ከራስ እንደሚያንሱ አድርጎ መመልከት በጌታ ክቡር ደም የተፈጠረውን ቅዱስ አንድነትና ሕበረት ለማናጋት ዋና መሣሪያ ነው:: ጳውሎስ በዚህ ክፍል ትሕትናችን በሁሉ አቅጥጫ እንዲሆን ነው የሚመክረን (በትሕትና ሁሉ):: ማለትም በሁሉ ነገር ሌሎች ከእኛ እንደሚሻሉ እንድናስብ:: “...ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቁጠር” ፊልጵ 2፣3:: “እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፣ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ::” ሮሜ 12፣16::

 

ለ)የዋህነት (meekness, gentleness, mildness)

በእንግሊዝኛው መዝገበ ቃላት የዚህን ቃል ትርጉም እንደሚከተለው እናገኛለን:- unprotesting, contrary of self-assertive [contrary of making a claim to one's right, contrary of insisting upon the recongnition of one's rights]. ይህም ማለት እያወቁ የራስን መብት መተው፣ የራስን መብት ለማስከበር አለመቆም ወይም አለማመጽ ወዘተ ማለት ነው:: የዋህነት፣ መብት እንዳለውና እርሱ ትክክል እንደሆነ እያወቀ እንኳን ለሕብረትና ለአንድነት ለፍቅር ሲል ያንን መብት ሳይቆጥር መብት እንደሌለው፣ እንዳላወቀ ነገሮችን ማለፍን የሚያመለክት ነው:: የየዋህነት ተቃራኒ ብልጠት፣ ሁል ጊዜ መብትን ማስከበር፣ ሁል ጊዜ የራን ጥቅም (advantage) መፈለግና “አራድነት” ነው:: ይህም ብቻ አይደለም ነገር ግን የየዋህነት ተቃራኒ፣ ለራስ ጥቅም ሲባል ነገሮችን ሁሉ በመቀመር (calculate በማድረግ) መመላለስና የራስን ጥቅም ብቻ የሚያስከብር ብልጠት ነው:: የራስን ጥቅም ለማስከበር የሚደረግ ብልጠትና “አራድነት”፣ ወይም እንደ ዳማና ቼዝ ጨዋታ ገና ለገና ከሩቅ ለሚገኝ ለራስ ጥቅም ዛሬ በብልጠት ሰዎችን መደለልና በቅምር (calculation) መመላለስ በጌታ ቤት አይሠራም:: ይህ እውነተኛ የፍቅር ሕብረት እንዳናደርግ ትልቅ እንቅፋትና ወንድሞችም እርስ በርስ እንደ ቆቅ እንዲተያዩና እንዳይተማመኑ የሚያደርግ ዋና ጠንቅ ነው:: በጌታ ዘንድ የሚሠራው ግን፣ ከልብ የሆነ የዋህነት ነው:: በብልጠትና የራስን ጥቅም በማግኘት የሚመላለሰውን ወንድም እንኳን እያወቁ በትዕግሥት ማለፍ ነው:: እያወቁ ለመታረድ እንደሚነዳ በግ በወገኖች መካከል መመላለስ ነው:: ይህ እውነተኛ መተማመን ያለበት ሕብረትና አንድነት እንደናድርግ የሚያስችል ዋና መንገድ ነው:: በተቃራኒው ደግሞ ብልጣብልጥነትና የቆቅ ኑሮ፣ ሕብረታችንና ግንኙነታችን አርቴፊሻል እንዲሆን ያደርግብናል:: “...ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና...” ማቴ 11፣28:: የዋህነት እያወቁ የራስን መብት በመተው፣ ነገሮችን ለእግዚአብሔር አሳልፎ መስጠት ነው:: “...ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፣ መከራንም ሲቀበል አልዛተም፣ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ” 1ጴጥ 2፣23::

 


 

 

ሐ)ትዕግሥት (patience)

የዚህን ቃል ምንነት የግሪኩ ሌክሲከን እንደሚከተለው ያስቀምጠዋል:- longsuffering, endurance, constancy, steadfastness, bearing troubles. ይህም ማለት ችርግንና መከራን መቻልን፣ መጽናትን፣ መቋቋምን ወዘተ የሚያመለክት ነው:: ይህ ቃል በግሪኩ ሁለት ቃላቶችን ያቀፈ ነው እነዚህም:- makros “long” እና thumos “temper” የሚሉት ናቸው:: በአማርኛም “ለቁጣ የዘገየ፣ ቶሎ የማይናደድ፣ ለረጅም ጊዜ ሳይበሳጭ የሚቆይ” ማለት ነው:: የትዕግሥት ምንነት ዋና መለኪያ ጊዜ ነው:: ለእኛ የማይመችን ወይም የማይስማማን ነገር ለረጅም ጊዜ ችሎ ማሳፍን የሚገልጽ ነገር ነው:: ለመልካም ሕብረት ትዕግሥት በጣም ወሳኝ ነገር ነው:: በሕብረት ውስጥ መጎሰምና መገፋት ሊኖር ይችላል:: በሕብረት ውስጥ ብዙ የሚያናድድና የሚያበሳጭ ነገር ይኖራል፣ ስለዚህ ችሎ ማለፍና ንዴትን መቆጣጠር እጅግ አስፈላጊ ነው:: በዚህ ሁሉ በመጽናትና ለረጅም ጊዜ መከራን በመቀበል መኖር ሕብረታችን እንዳይናጋ ያደርጋል:: በተቃራኒው ግን እኛ የምንበደልበትና የምንጎሰምበት ትንሽ ችግር በመጣ ቁጥር ቶሎ የምንበሳጭ፣ የምንናደድ ወይም ቱግ የምንል ከሆነ እርስ በርስ ለመቆሳሰልና ለመቀያየም ትልቅ በር እንከፍታለን:: እውነተኛ ትዕግሥት ማለት:- ጉዳትን እየቆጠሩ፣ እየተነጫነጩና እያጉረመረሙ ጊዜን ማሳለፍ ማለት ሳይሆን፣ ነገር ግን በጌታ ተስፋ እያደረጉ በእምነትና በምስጋና በድልም ውጪያዊውን ሁኔታ በመቻል ማሸነፍ ማለት ነው::

 

 

መ)እርስ በርስ በፍቅር መታገሥ/መቻቻል (to bear with one another in love)

ሕብረት ወይም ቤተሰብነት ራሱ ከአንድ ሰው በላይ የሆኑ ሰዎች ያሉበት ስለሆነ፣ እንደራሳችን ያልሆኑ ብቻ ሳይሆን ትክክል ያልሆኑም ብዙ አይነት አስተሳሰቦች፣ አኗኗሮች፣ አሠራሮች ወዘተ ያሉበትና ወደፊትም የሚኖርበት ነገር ነው:: ስለዚህ እንደኛ አይነት ያልሆነ የሌላውን አስተሳሰብና አመለካከት እንዲሁም አኗኗር መቻል ለተጠራንለት ታላቅ ጥሪ የሚመጥን አንዱ አኗኗር ነው:: በዚህ ክፍል እንደተጠቀሰው እርስ በርስ ለመቻቻል ዋናው መሠረት ፍቅር ነው:: በሥጋ ወንድምና እህት የሆኑንን ስለምንወዳቸውና ከእነርሱም በምንም ሁኔታ ስለማንለይ፣ ለብዙ ዓመታት ጸባይቸውን አውቀን እንችላቸዋለን እነርሱም ይችሉናል:: በትዳር ውስጥ ሚስትን ወይም ባልን ከመውደድ የተነሳና አብሮ በመልካም ለመኖር አንዱ የሌላውን ጸባይና ባህርይ መቻቻል አማራጭ የሌለው ነገር ነው:: በተሳሳተ መንገድና አስተሳሰብ ላይ ያሉ ሰዎችን እንኳን፣ በአንድ ስብከት ወይም በአንድ መልእክት ወይም በአንድ ምክር ወዲያው ስለማይለወጡ፣ ጌታ እስከሚለውጣቸውና ወደ መረዳት እስኪያመጣቸው መታገስ የሕብረታችንን ሰላም ወይም harmony የሚጠብቅ ነው ሮሜ 14፣1-4:: ጌታ እኛን በብዙ ነገር እንደሚታገሰንና እንዳለን እንደሚቀበለን ሌሎችን መቀበልና መታገሥ ይጠበቅብና:: “እኛም ኃይለኞች የሆንን የደካሞችን ድካም እንድንሸከም ራሳችንንም ደስ እንዳናሰኝ ይገባናል::” ሮሜ 15፣1:: “ስለዚህ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር እንደ ተቀበላችሁ እንዲሁ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ::” ሮሜ 15፣7:: እርስ በርስ አለመቻቻል፣ አለመሸካከምና ጌታ እኛን በብዙ ነገር እንደታገሠን ሌሎችን አለመታገሥ፣ ብዙ የቤተክርስቲያን ሕብረቶችን ያናጋና በዛም ቤተክርስቲያን መጥፎ ምስክርነት እንዲኖራትና ለወንጌልም ትልቅ እንቅፋት የሆነ ነገር ነው:: ነገሮችን እያለፉ ከመቻል ይልቅ፣ ነገሮችን መቁጠርና አለማለፍ ለሕብረታችን ትልቅ ጠንቅ ነውና::

 

 

ሠ)በሰላም ማሠሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ መትጋት

እዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገቡን አንዳንድ ነገሮች አሉ:: የመንፈስ አንድነትን እንድዳይናጋና እንዳይበላሽ እንደንጠብቅ እንጂ የመንፈስን አንድነት እንድንፈጠር አይደለም ምክሩ:: በክርስቶስ ሁላችን አንድ መንፈስ ከመጠጣታችን የተነሳ የመፈሱ አንድነት እግዚአብሔር የፈጠረውና ያለ እንጂ ገና በትግል የምንፈጠረው አይደለም 1ቆሮ 12፣13:: ነገር ግን ይህ በእግዚአብሔር የተፈጠረው የመንፈስ አንድነት፣ በመንፈስ የሆነ ስምምነት፣ በመንፈስ የሆነ ወንድማማችነትና ቤተሰብነት፣ ሊናጋ የሚችል ስለሆነ አጥብቀን እንድንጠብቀው እንመከራለን:: መጠበቅ የሚለውን ቃል በግሪኩ የሚከተለው ፍቺ ነው ያለው:- to attend to carefully, take care of, to guard, to observe, to keep, not to leave, not to throw away. ይህም ማለት አንድን ነገር በቅርበት መከታተልን፣ ስለዛ ነገር መጠንቀቅን፣ ያንን ነገር መንከባከብን፣ ከአይን አለመለየትን፣ አለመተውን፣ ለአደጋ አለማጋለጥን የሚያሳይ ነው:: ስለዚህ ጳውሎስ በዚህ ክፍል የሚናገረው፣ የመንፈስ አንድነትን ልንከባከበው፣ ሁል ጊዜ ልንጠነቀቅለት፣ እንዳይበላሽ በቅርበት ልንከታተለው የሚገባ ነገር እንደሆነ ነው::

 

ጳውሎስ በዚህ ክፍል እንዴት አድርገን የመንፈስን አንድነት መጠበቅ እንዳለበን ሲናገር “ትጉ” የሚለውን ቃል በመጠቀም ነው:: “...የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ” ቁ.3:: የዚህ ትጉ የሚለው ቃል ትርጉም:- to exert one's self, endeavor, give diligence ወይም በአማርኛ ከልብ የሆነ ሙሉ ጥረትና የሚቻለውን ሁሉ ማድረግን የሚያመለክት ነው:: በተቻላችሁ ትጋት ሁሉ የመንፈስ አንድነት እንዳይናጋ አጥብቃችሁ ጣሩ ማለት ነው:: ስለዚህ የምናደርገው ነገር በራሳችን አይን ትክክል ነው የሚለው ብቻ አይበቃም ነገር ግን የመንፈስን አንድነትስ ሊያናጋ ይችላል ወይ? ተብሎም መታሰብ አለበት:: በምናደርገው ሁሉ አንድነቱ አንዳይናጋ የተቻለንን ጥረት ሁሉ ማደርግ ይገባናል ማለት ነው:: በሕብረት ውስጥ ትክክል መሆን የሚለው ብቻ አይሠራም ነገር ግን ሌላውን ማነጽ እንጂ:: “...እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንጻል” 1ቆሮ 8፣1:: ጌታ በደሙ ለፈጠረው አንድነትና ሕብረት ግድየለሾች መሆን የለብንም::

 

የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ስንል የሚቻለንን ሁሉ ማደረግ ወይም መትጋት ሲል እንግዲህ፣ የራስንም ፈቃድና ፍላጎት ለአንድነቱ ሲባል መተውንም ያካትታል:: ጌታ ትልቅ ስፍራ ለሰጠው ለዚህ አንድነት ሲባል የግልን ነገር ወደ ኋላ በማድረግ፣ ነገር ግን በጌታ ልብ ያለውን የሕብረቱን ጉዳይ ማስቀደም አስፈላጊ ነው:: በተቃራኒው ግን የራስን ሃሳብና ፈቃድ በሌሎች ሁሉ ላይ መጫን (impose ማደረግ) አልሆን ሲል ደግሞ መለየት ይህ የሥጋ ሥራ ነው:: “መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፣ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል::” ምሳ 18፣1:: ስለዚህ ሰላምንና ሕብረትን ከእኛ ፈቃድ ይልቅ በማስቀደም አንድነቱ በእኛ ምክንያት እንዳይናጋ መጠንቀቅ ይገባናል:

 

የመንፈስ አንድነቱ እንዳይናጋ እንደ ዋነኛ መሣሪያ ጳውሎስ የሚጠቅሰው የሰላም ማሰሪያን ነው:: በዚህ ክፍል ማሰሪያ ተብሎ በአማርኛው የተተረጎመው ቃል በግሪኩ በዋነኝነት የሚያሳየው ብዙ ነገሮችን እንደ ችቦ በጅምላ ስለሚያስር አንድ ገመድ ሳይሆን፣ በዋናነት የሚመለክተው በእንግሊዝኛው ligament ወይም ጅማት ተብሎ የሚጠራውን የሰውነት ክፍል አይነት ነው:: ligament ማለት:- band of tough, strong tissue that holds two or more bones together in the body. ይህም ማለት የሰውነት አጥንቶችን ወይም ክፍሎችን እርስ በርስ ወይም አንዱን ከአንዱ ጋር የሚያይዝ ወይም የሚያስር ነገር ማለት ነው:: ስለዚህ ጳውሎስ ለማሳየት የሚፈልገው በሰላም የሆነ ግንኙነታችን በጅምላ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ የአካል ክፍል ከሌላው ጋር ሊኖረው ስለሚገባ ግንኙነት የሚያመለክት ነው:: የእግዚአብሔር ዋና አላማ ሕብረትና አንድነት እንደሆነ፣ አሕዛብንና አይሁድን አንድ አድርጎ በክርስቶስ ሰላምን እንደሰበከላቸው፣ ሰላም፣ መስማማት፣ ሕብረትና ፍቅር ጌታ ለእርስ በርስ ያሰበልን የግንኙነት አይነትና፣ የተፈጠረውንም ሕብረት የምንጠብቅበት መሣሪያ ነው::

 

ማጠቃለያ

እግዚአብሔር እንግዲህ ለታላቅ አንድነት፣ ቤተሰብነትና አንድ አካል ለመሆን፣ ለዘላለማዊ ሕብረት ጠርቶን ሳለ ከትሕትና ይልቅ እኔ እበልጣለሁ በሚል ትዕቢት፣ ከየዋህነት ይልቅ የራስን ጥቅምና advantage በመፈለግ፣ ከትዕግሥት ይልቅ ቶሎ በመቆጣትና ግልፍተኛ በመሆን፣ እርስ በርስ ከመቻቻልና ከመሸካከም ይልቅ እርስ በርስ ባለመቻቻል እንዲሁም የመንፈስንም አንድነት ለመጠበቅ የተቻለንን ጥረት ባለማደረግ መመላለስ የተጠራንበትን ጥሪ የማይመጥን፣ ከጥሪያችን ጋር የማይሄድና የማይገባ አካሄድ ነው:: የእግዚአብሔር ጥሪ የሕብረት፣ የመስማማት፣ የፍቅርና የሰላም ጥሪ እንጂ የጸብ፣ የሁከትና የመለያየት ጥሪ አይደለምና::


“ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ።“
(መጽሐፈ ምሳሌ 3:3-4)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us