ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች » ኤፌሶን » ጥናት 12 (ኤፌሶን 4፣1-16 ለ) ለጥሪው የሚገባ አካሄድ - ክፍል 2
Email this page to a friend Printer-friendly   Tuesday, 20 October 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦“
(የዮሐንስ ራእይ 3:14)

rss

Today's verse

ጥናት 12 (ኤፌሶን 4፣1-16 ለ) ለጥሪው የሚገባ አካሄድ - ክፍል 2

pdf version

ጳውሎስ “ለተጠራችሁበት መጠራት እንደሚገባ” ብሎ የጠቀሰውን ሃሳብ እንደሚከተሉት በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ከፍለን ማጥናት ጀምረናል::

 

1.              የጥሪው ምንነት

2.              የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ መትጋት

3.              ሰባቱ የአንድነት መሠረቶች

4.              የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማውቅ ወደሚገኝ አንድነት ማደግ

 

በክፍል 1 ጥናታችን ላይ ቁጥር አንድንና ሁለትን የተመለከትን ሲሆን፣ በአሁኑ ደግሞ ሶስትን በሙሉና አራትን በከፊል እንመለከታለን::

 

3.             ሰባቱ የአንድነት መሠረቶች ቁ. 4-6

በዚህ ክፍል ሐዋርያው ጳውሎስ አንድነታችን የተመሠረተባቸውን ሰባት ዋና ዋና የአንድነት መሠረቶች እንደሚከተለው ይዘረዝራል:-

 

ሀ)አንድ ተስፋ

አንድ ተስፋ ማለት አንድ መዳረሻ፣ አንድ ግብ፣ አንድ ፍጻሜ፣ አንድ እድል ፈንታ ወዘተ ማለት ነው:: በጌታ የዳኑ ቅዱሳን ሁሉ የሚካፈሉትንና እግዚአብሔር ያዘጋጀላቸውን የወደፊት መልካም ነገሮችን በሙሉ የሚያጠቃልል ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ የሚከተሉት ይገኙባቸዋል:-

·       ትንሳኤ፣ መነጠቅና ሁል ጊዜ ከጌታ ጋር መሆን 1ተሰ 4፣13-18 1ቆሮ 15፣20-23

·       ወራሽነትና ርስትን መቀበል ኤፌ 1፣13-14/18-19 ሮሜ 8፣17

·       ክርስቶስን መምሰል 1ዮሐ 3፣2-3 ሮሜ 8፣29

·       ወዘተ

ቤተክርስቲያን አንድ አካል እንደመሆኗ የተጠራችውም እንግዲህ ለአንድ መዳረሻና ለአንድ እድል ፈንታ ነው:: በሥጋ ምንም እንሁን ምን በጌታ የተዘጋጀልን የምጨረሻ ዕጣ አንድ ነው:: ሁላችን የተጠራነው በአንድ አይነት ጥሪ ለአንድ ግብና ለአንድ እድል ፈንታ ነው:: በጌታ የሆንን ሁሉ አላማችንም በአንድ መንገድ ላይ ተጉዘን፣ ያንን ተስፋ ለማግኘት ነው:: ዛሬ በአጠገባችን የምናየውን ወንድም ገና በክርስቶስ ፊት፣ ለዘላለምም በክብር እናየዋለን:: ከወንድማችን ጋር እኛ እንደሚመስለን በቀላሉ የምንለያየው ሳይሆን፣ ጉዞአችንና ዕድል ፈንታችን ለዘላለም የተሣሠረ ነው::

 

ለ)አንድ አካል (ጥናት 8 ይመልከቱ)

 

ሐ)አንድ መንፈስ (ጥናት 8 ይመልከቱ)

 

መ)አንድ ጌታ

ይሄ አንድ ጌታ የሚለው ስንኝ የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ የሆነውን የናዝሬቱን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያመለክት ነው 1ቆሮ 8፣6:: ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይና በምድር ሥልጣን ሁሉ የተሰጠው፣ ጠላትን ድል ያደረገና ሁሉ ከእግሩ በታች የተገዛለት፣ የቤተክርስቲያንና የእያንዳንዱም አማኝ ራስና አለቃ ነው ማቴ 28፣18 ኤፌ 1፣19-22 ፊል 2፣9-11:: ይህም ብቻ አይደለም መንፈስ ቅዱስም ኢየሱስን የሚገልጥበት አንዱ ገጽታ ጌትነቱን ነው 1ቆሮ 12፣3:: የኢየሱስን ጌትነት ማመናችን የድነታችን ዋናም መሠረት ነው ሮሜ 10፣9:: ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ የምንመለከታቸው የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ኢየሱስን በአዳኝነቱ ብቻ ሳይሆን በጌትነቱም የተረዱት ነበሩ:: የአዲስ ኪዳን መልእክቶችንም ስናነብ ይሄንኑ እንመለከታለን:: በዘመናችንም በእርግጥ የኢየሱስ ተከታዮች የሆኑት ኢየሱስን እንደ ጌታ ያዩታል ይጠሩታልም:: ስለዚህም ጌታ እያሉ ኢየሱስን መጥራት ይታይባቸዋል::

 

የጌታ ተከታዮች የሆንን ሁላችን እንግዲህ፣ ለኃጢአታችን ሥርየት የተሰቀለልንና የሞተልን፣ በትንሳኤውም እኛንም ከሙታን ያስነሳን አንድ መድኃኒትና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን:: በግል ሕይወታችንና በቤተክርስቲያን ሕብረታችን ሁሉ አለቃ የሆነ አንድ መሪ ነው ያለን:: ሁለት መሪ፣ ሁለት አለቃ፣ ሁለት አዛዥ ወይም ሁለት ክርስቶስ ወዘተ የለንም! የእኛ ጌታ፣ የወንድሞቻችንና የእህቶቻችንም ጌታ ነውና 1ቆሮ 1፣13::

 


 

ሠ)አንድ እምነት

በዚህ ክፍል በአማርኛው “አንድ ሃይማኖት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል፣ በግሪኩ pistis የሚለው ቃል ሲሆን ይህም አንድን ነገር ሰምቶ ማመንን ወይም ሰው በእግዚአብሔርና በክርስቶስ ያለውን እምነትን የሚያመለክት እንጂ ሃይማኖትን ወይም ሃይማኖታዊ ድርጅቶችን ወዘተ የሚያመለክት አይደለም:: ስለዚህ ትክክለኛ ትርጉሙ እምነት (faith) ማለት ነው:: በዚህ ክፍል የተጠቀሰው እምነት በጌታ የዳኑ ሁሉ ያላቸውና ለድነት ያበቃቸውን እምነት ነው ኤፌ 2፣8-9:: ይህም በኢየሱስ ብቸኛ አዳኝነትና ጌትነት ማመናቸው ነው ሮሜ 3፣21-22/26 ዮሐ 3፣16 ዮሐ 3፣36 ሮሜ 10፣9::

 

ረ)አንዲት ጥምቀት

በዚህ ክፍል “አንዲት ጥምቀት” ብሎ ጳውሎስ የሚናገረው ስለ መንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ሳይሆን ስለ ውሃ ጥምቀት  ሳይሆን አይቀርም:: ምክንያቱም ሁላችን ስለምንጠጣው አንድ መንፈስ ቀድሞ ጠቅሶታል (ሐ):: ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጥምቀት ሲናገር አብዛኛውን ጊዜ የውሃ ጥምቀትን የሚያመለክት ነው የሐዋ 2፣38/2፣41 የሐዋ 8፣12/8፣14-16 የሐዋ 19፣5-7:: ጳውሎስም ራሱ በሌሎች መልእክቶቹ ላይ ስለ ጥምቀት ሲናገር የውሃ ጥምቀትን ለማመልከት ነው ሮሜ 6፣3-4 1ቆሮ 1፣13-16 ቆላ 2፣12::  የመንፈስን ጥምቀት መጻሐፍ ቅዱስ “በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ” ብሎ ነው ብዙ ጊዜ የሚጠራው ማቴ 3፣11 የሐዋ 1፣5 የሐዋ 11፣16::

 

እንግዲህ “አንዲት ጥምቀት” ብሎ ጳውሎስ የሚናገረው ስለ ውሃ ጥመቀት መሆኑን ከተስማማን፣ ታዲያ ይህች ጥምቀት ምንድን ናት? አማኞች ሁሉ የሚጠመቁት ይህ የውሃ ጥመቀት የሚከተሉት ዋና ዋና ባህርያት አሉት:-

·       ቃሉ በግሪኩ baptisma ሲሆን፣ ትርጉሙ ደግሞ መጥለቅ ወይም መስጠም (immersion, submersion) ማለት ነው:: ስለዚህ ጥምቀት በውሃ ውስጥ ተሰጥሞ ወይም ጠልቆ የሚደረግ እንጂ በመረጨት የሚደረግ አይደለም::

·       በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ወይም በኢየሱስ ስም የሚደረግ ነው ማቴ 28፣19-20 የሐዋ 8፣15-16 የሐዋ 19፣5::

·       ከወንጌል መስማትና ከእምነት በኋላ የሚደረግ የሐዋ 8፣36-37 ማር 16፣15-16 የሐዋ 8፣12:: በመጽሐፍ ቅዱስ የትም ቦታ ጥምቀት ወንጌልን ከመስማትና ከእምነት በፊት ሲደረግ አንመለከትም:: በአዲስ ኪዳን፣ ከእምነት ውጪ የሚደረግ ነገር ሁሉ ዋጋ የለውም ሮሜ 14፣23::

 

የአዲስ ኪዳን ጥምቀት ትርጉም ከዮሐንስ ጥምቀት የተለየ ነው:: የዮሐንስ ጥምቀት ንስሐ መግባትን የሚያሳይ የንስሐ ጥምቀት ብቻ ነው ማቴ 3፣1-6 ማቴ 3፣16 ሉቃ 3፣3-6 የሐዋ 19፣4:: በጌታ አምነን የምንጠመቀው ግን ዋናው ትርጉሙ ከክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ጋር መተባበራችንን የሚያመለክት ነው ሮሜ 6፣3-4 ቆላ 2፣12:: ነገር ግን ለመጠመቅ በጌታ ማመን እንጂ የጥምቀቱን ትርጉም በጥልቀት መረዳት ግዴታ አይደለም:: ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ አማኞች የሚጠመቁት የጥምቀት ትምህርት ተምረው ሲጨርሱ ሳይሆን፣ የጌታን ወንጌል ሲሰሙና ሲያምኑ ወዲያው ነበር::

 

እንግዲህ ሁላችን አንዱን ጌታ አምነን፣ ከሞቱና ከትንሳኤው ጋር ለመተባበር ተጠምቀናል:: ሁላችንም የምንተባበረው አንዱን ጌታ ነው::

 

ሰ)አንድ አባት

የጌታችንና የእኛም ሁላችን አባት የሆነው አብ ነው:: መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን ማንም እንዳላየው ነገር ግን በእቅፉ የነበረ ልጁ እንደተረከው ይነገረናል ዮሐ 1፣18:: ይህም ማለት ሌሎቹ ነብያት ሁሉ ሙሉ በሙሉ እግዚአብሔርን ተረድተውና አይተውት አይደለም ስለ እርሱ ያስተማሩት:: ነገር ግን የተገለጠላቸውን አስተላለፉ:: ኢየሱስ ግን ከማንም በላይ በአብ ዘንድ የነበረና አብንም የሚያውቅ ስለሆነ፣ ሙሉ በሙሉ የተረከው እርሱ ነው ዕብ 1፣1-2 ማቴ 11፣27:: የብሉይ ኪዳን ነብያት ስለ እግዚአብሔር ፈጣሪነት፣ ሁሉን ቻይነት፣ የሠራዊት ጌታ ስለ መሆኑ ወዘተ ገልጸዋል:: የኢየሱስን አገላለጽ ከእነርሱ ለየት የሚያደርገው፣ ከሁሉም በላይ በዋነኛ ደረጃ የእግዚአብሔርን አባትነት መግለጹ ነው:: ኢየሱስ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” እያለ አልተናገረም፣ ነገር ግን “አባታችሁ” ወይም “አባቴ” ነው የሚለው (ለምሣሌ:- ማቴ 5፣16/43-48 ማቴ 6፣3-18/26/32 ማቴ 7፣11 ማቴ 11፣25-27):: የእግዚአብሔር መንፈስ አብን “አባ” ብለን እንድንጠራ የሚያስችለን መንፈስ ነው ሮሜ 8፣15:: ስለዚህ በክርስቶስ ሙሉ በሙሉ የተገለጠው የአብ ትልቁ መገለጥ አባትነቱ ነው:: ከ“አባ” ወይም ከ”dady” ወይም ከ“አባብዬ” የበለጠና የጠለቀ ሌላ መገለጥ ለአብ የለም:: ክርስትናንም ከሌሎች ሃይማኖቶች አንዱ የሚለየው ዋና ነገር ይሄ ነው::

 

ትልቁ የአብ መገለጥ እንግዲህ አባትነቱ ከሆነ፣ ትልቁም ስለ እርስ በርሳችን ያለን መረዳት ወንድማማችነት፣ የአንድ አባት ልጅነትና ቤተሰብነት ነው:: ሁላችንም ለዘላለም የአንድ አባት ልጆች ነንና::

 


 

ማጠቃለያ:-

ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉ እንግዲህ አማኞች ሁሉ በጌታ ያላቸው ነገሮች ናቸው:: እነዚህ ለሁላችንም እኩል የሆኑና ሁላችንም በእኩል ደረጃ የምንካፈላቸው የአንድነታችን መሠረቶች ናቸው:: ሕብረታችን በእነዚህ ሰባት የጸኑ ገመዶች የታሠረ ነው:: እንደዚህ በጸኑ መንፈሳዊ ነገሮች የታሠረና የተቆራኘ ሕዝብ ወይም ቤተሰብ በምድር ላይ አልነበረም አሁንም የለም:: ይህ መቆራኘት እጅግ የጠበቀ፣ የጠለቀ እና ዘላለማዊ ነው:: ስለዚህ በሕብረትና በመስማማት ቤተክርስቲያን መኖር ካቃታት ማን ሊስማማ ይችላል? እንደዚህ የተቆራኘ ሕዝብ ካልተዋደደ ማን ሊዋደድ ይችላል? ለሕብረትና ለአንድነት የሚያስፈልግ ነገር ሁሉ ከተደረገለት ከእግዚአብሔር ሕዝብ ሌላ ማን እውነተኛ ሕብረትንና ፍቅርን መለማመድ ይችላል? ሰው በሥጋ ከአንድ አገር ስለሆነ ብቻ ወይም ከአንድ ዘር ስለሆነ ብቻ ይፈላለጋል፣ ይግባባልም:: እኛ ግን በሰባት ገመድ የተገመደ ሕብረት ያለን ሰዎች እንዴት አብልጠን አንፈላለግ? እንዴት አንግባባ? ጳውሎስ የመንፈስን አንድነት ከመጠበቅ ጋር እነዚህን ሰባት የመቆራኛ ገመዶች ሲዘረዝር ሊለው የሚፈልገውም ይሄንኑ ነው:: በአንዱ ነገር እንኳን እንለያያለን ብንል፣ በሌሎቹ ስድስት ገመዶች ተቆራኝተናል:: በእውነት ለመለያየት በእውነት ለመጠላላት በእርግጥም ሰባቱንም ገመዶች መፍታት አለብን:: እምነታችንም የተለያየ ነው፣ አባታችንም የተለያየ ነው፣ ጌታችም የተለያየ ነው፣ ተስፋችም የተለያየ ነው፣ በእኛ ውስጥ የሚሠራውም መንፈስ የተለያየ ነው፣ ጥምቀታችንም የተለያየ ነው፣ የአንድ አካል ብልቶችም አይደለንም እስካላልን ድረስ በእርግጥ የምንጠላውና የምንገፋው ወንድማችንን ነው:: እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን አንድነት ሲል ያላደረገው ምን አለ? የሁላችንን መልክ አንድ አይነት ቀለም ከመቀባት በቀር፣ ለአንድነትና ለሕብረት የሚያስፈልገውን ሁሉ ጌታ አድርጎአል:: እንደ አንድ ቤተሰብ በቤተክርስቲያን ሕብረት ውስጥም መጋጨት ሊኖር ቢችልም፣ ይህ ግን ቶሎ በፍጥነት በይቅርታ፣ በንስሐና በእርቅ ሊወገድ የሚገባው ጉዳይ እንጂ እንደ መደበኛ ሁኔታ መወሰድ የለበትም:: በአሁኑ ጊዜ ደጋግሞ እንደሚታየው የቤተክርስቲያን ሕብረት መደበኛ ሁኔታው ጸብ፣ ጥላቻ፣ መናቆርና መለያየት መሆን አይገባውም:: ነገር ግን “ያመኑትም አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው...” የሐዋ 2፣32 የሚለው  ነው የቤተክርስቲያን መደበኛው ሕብረት:: ስለዚህ የተጠራንበትን ታልቅና ዘላለማዊ የአንድነት ጥሪ የሚመጥንና የሚገባ የሕብረትና የፍቅር ኑሮ ልንኖር ይገባናል::

 

 

4.             የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማውቅ ወደሚገኝ አንድነት ማደግ ቁ. 7-16

 

በዚህ በቁጥር 4 ሥር፣ ማለትም በኤፌ 4፣7-16 ባለው ክፍል ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎትን ወይም የአገልግሎት የጸጋ ሥጦታዎች በአንድነት ወይም በሕብረታችን ላይ ያላቸውን ሚና ያብራራል:: ይህንንም ሃሳብ እንደሚከተሉት ከፍለን እንጠናለን:-

 

ህ)የጸጋ ስጦታዎች ቁ. 7-10

ለ)የአምስቱ ስጦታዎች ምንነት ቁ. 11

ሐ)አምስቱ ስጦታዎች የተሰጡበት ዓላማና በአካሉ ላይ የሚያስገኙት ውጤት ቁ. 12-16

 

በዚህ በአሁኑ ጥናታችን ላይ ከላይ ከተጠቀሱት ውስጥ ሀ)ን የምንመለከት ሲሆን፣ በሚቀጥሉት ተከታታይ ጥናቶቻችን ደግሞ የተቀሩትን በተራ እናያቸዋለን::

 

ህ)የጸጋ ስጦታዎች ቁ. 7-10

ስለ ጸጋ ስጦታዎች (ጸጋ በግሪኩ charis ወይም ነጻ ስጦታ ነው) ጳውሎስ ለመናገር ሲጀምር “ነገር ግን” ብሎ ነው:: “ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን::” ቁ. 7:: ይሄ “ነገር ግን” የተባለው ስንኝ፣ ከቁ. 7 በፊት የነበረውን ሃሳብ የሚያያይዝና ሃሳቡ ከዛ የቀጠለ እንደሆነ የሚያሳይ ነው:: ጳውሎስ ከቁ. 1 ጀምሮ ስለ ሕብረትና አንድነት፣ የመንፈስን አንድነት ስለመጠበቅ ገልጾ፣ ከቁ. 4-6 ባለው ደግሞ ሁላችን በእኩል ደረጃ ስላለን ስለ ሰባቱ የአንድነት መሠረቶች ተናግሮአል:: በቁ. 7 የሚናገረው የጸጋ ስጦታ የአገልግሎትን ጸጋ የሚያመለክት ስለሆነና ሁላችንም እንደ ሰባቱ የአንድነት መሠረቶች፣ አንድ አይነትና በእኩል ደረጃ የአገልግሎት ጸጋ እንደማይኖረን ለማሳየት ነው ጳውሎስ ሃሳቡን በ“ነገር ግን” የጀመረው::

 

ጳውሎስ በስምንተኛ ደረጃ የሚጠቅሰው ለአገልግሎት የሚሰጠውን የጸጋን ሥጦታ ነው:: ይሄ ስምንተኛው ከሰባቱ ጋር የሚመሳሰልበትም የሚለያይበትም አንዳንድ ባሕርያት አሉት:-

 

·       የአገልግሎት ጸጋ ስጦታዎች ምንነት:- የአገልግሎት ጸጋ ስጦታዎች ወይም በተለምዶ የጸጋ ስጦታዎች ብለን የምንጠራቸው፣ ጌታን ከመቀበላችን በፊት በተፈጥሮ የነበሩንን ችሎታዎች ሳይሆን፣ ጌታ ያሰበልንን በመንፈስ የሚሆን የአዲስ ኪዳን አግልግሎትን ለማከናወን ከድነት በኋላ፣ ጌታ ብቻ ስለሚሰጠን ትጥቅና ብቃት ነው:: ምንም እንኳን ሰዎች እነዚህን በተለያዩ ስሞች ቢከፍሎአቸውም (ለምሣሌ:- ዘጠኙ የጸጋ ስጦታዎች፣ አምስቱ የአገልግሎት ስጦታዎች/five fold ministries ወዘተ) ሁሉም በጸጋ ወይም በነጻ የሚገኙ የጌታ ስጦታዎች ስለሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ሁል ጊዜ እኛ እንደምናስበው እየለያየና እየከፋፈለ አያስተምረንም 1ቆሮ 12፣28:: በመጽሐፍ ቅዱስ ከ20 የሚበልጡ የአገልግሎት ጸጋዎች ወይም ስጦታዎች ተጠቅሰዋል ሮሜ 12፣3-8 1ቆሮ 12፣4-11 1ቆሮ 12፣28 ኤፌ 4፣11:: ስለዚህ የአገልግሎት ጸጋ ብለን ስንል በአጥቢያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለ ሹመት ማለታችን አይደለም:: ወይም ብዙ ሰዎች እንዲሚመስላቸው ስለ አጥቢያ ቤተክርስቲያን የሹመት እርከን አይደለም የምንነጋገረው:: ነገር ግን የአዲስ ኪዳን አገልግሎትን ለማከናወን የሚያበቃ፣ በመንፈስ ጌታ ስለሚሰጠው ብቃትና ትጥቅ ነው የምንነጋገረው 2ቆሮ 3፣4-6:: እንግዲህ የአገልግሎት ጸጋ ብለን በሚቀጥሉትም ጥናቶች ስንነጋገር፣ በአጥቢያ ቤተክርስቲያን ስላለ ሹመት ጨርሶ እንዳልሆነ መረዳት ይኖርብናል::

 

·       ለእያንዳንዳችን የሚሰጥ ነው:- የአገልግሎት ጸጋ ስጦታ ለተወሰኑ የተመረጡ ቅዱሳን የሚሰጥ ሳይሆን፣ ለእያንዳንዳችን የሚሰጥ ነገር ነው:: አካል ብዙ ብልቶች እንጂ አንድ ብልት እንዳይደለ፣ እንዲሁም እኛ ሁላችን የክርስቶስ አካልና እርስ በርሳችንም ብልቶች ስለሆንን እያንዳንዳችን እንደ ብልቶች ጌታ የወሰነልን አገልግሎትና ተግባር አለን:: ይህንን አገልግሎት ለመፈጸም እያንዳንዳችን ጸጋ ያስፈልገናል:: ስለዚህም የአገልግሎት ጸጋ ስጦታ የሚሰጠው ለእያንዳንዳችን ወይም ለሁላችን ነው:: የክርስቶስ ብልት ሆኖ ጸጋ የሌለው የለም:: እውነተኛውን ክርስትና ከሌሎች ሃይማኖቶች የሚለየው አንዱ ነገርም እንደሌሎች ሃይማኖቶች “መንፈሳዊን” ሥራና አገልግሎት የሚያከናውኑት እንደ ብሉይ ኪዳን ለዛ ብቻ የተለዩ “ካህናት” ወይም “መንፈሳዊያን” ወይም “ቄሶች” ብቻ አለመሆናቸው ነው:: በአዲስ ኪዳን clergy (መፈሳዊውን ሥራ ለመሥራት የሚችሉና የሚፈቀድላቸው ሹሞች) እና layman (መንፈሳዊን ሥራ ለመሥራት የማይችሉና የማይፈቀድላቸው ተራ አባላት ወይም ተገልጋይ ብቻ) የሚባል ልዩነት የለም:: ቤተክርስቲያን ሕያው አካል እንጂ መንፈሳዊ ድርጅት ስላይደለች፣ በአዲስ ኪዳን የምንመለከተው የአካል አገልግሎት ወይም እያንዳንዱ ብልት እርስ በርስ የሚተናነጽበት አገልግሎት ነው:: ይህን ሃሳብ በቁ. 12-13 ባሉት ክፍሎች ውስጥ በስፋት እንመለከታለን::

 

·       አንድ አይነት አይደለም:- ቀደም ብለን እንዳየነው የአገልግሎት ጸጋ ስጦታ፣ ለእያንዳንዳችን የተሰጠ ቢሆንም እንደ ሰባቱ የአንድነት መሠረቶች ሁላችንም ተመሳሳይ ነገር አይኖረንም:: አካል እያንዳንዱ ብልት የተለያየ ተግባር እንዳለው፣ እንዲሁ እኛም እያንዳንዳችን የተለያየ አገልግሎት ነው ያለን:: አካል የተለያየ ተግባር ያለው አንዱ ብልት መሥራት የማይችለውን ሌላው እንዲሠራና እንዲደጋገፉ ነው እንጂ በልዩነታቸው  እንዲጣሉበት አይደለም:: ጳውሎስ የአገልግሎት ጸጋ ስጦታን ከሰባቱ የአንድነት መሠረቶች ጋር አብሮ የሚጠራውም ለዚሁ ነው:: ምንም እንኳን የተለያየ ጸጋ ጌታ ለእያንዳንዱ ቢሰጥም፣ አካል እርስ በርስ እንዲተናነጽና እንዲደጋገፍ የሚያደርግ እንጂ መፎካከሪያና መለያያ አይደለም:: የአገልግሎት ልዩነትን ያደረገ እግዚአብሔር ነው 1ቆሮ 12፣4-6:: በዛ ምክንያት መለያየት ግን የሥጋ ሥራ ነው ገላ 5፣21::

 

·       ሰጪው ጌታ ብቻ ነው:- የአገልግሎት ጸጋን የሚሰጥ ጌታ ብቻ ነው:: ማን የትኛውን ጸጋ እንዲሚያገኝ እንዲሁም መጠኑንም ሁሉ የሚወስን ጌታ ነው:: “ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን::” ቁ. 7 1ቆሮ 12፣11:: ምንም እንኳን የአገልግሎት ጸጋዎችን እንድንፈልግና እንድንጸልይ ብንበረታታም፣ ሁል ጊዜ ከአይናችን ፊት መለየት የሌለበት እውነት ግን፣ የእነዚህ የጸጋ ስጦታዎች ሰጪ ጌታ ብቻ መሆኑን ነው:: ቤተክርስቲያን ልተሰጠን አትችልም፣ የቤተክርስቲያን ሹመት ሊሰጠን አይችልም፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጆች ሊሰጡን አይችሉም:: ስለዚህ የአገልግሎት ጸጋን በመንፈሱ የሚሰጠው ከሰማይ የወረደውና የሞተው በኋላም ከሙታን በድል የተነሣውና ወደ ሰማይ ተመልሶ ያረገው ኢየሱስ ብቻ እንደሆነ ጳውሎስ ከቁ.8 እስከ 10 ባለው ክፍል ላይ ያመለክታል:: በዚህ ክፍል ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ድል አድራጊነት ሲገልጽ መዝ. 68.18ን በመጥቀስ ነው:: በእርግጥ ጳውሎስ እንዴት አደርጎ በመዝሙረ ዳዊት ካለው ጥቅስ ጋር እንዳገናኘው ግልጽ ባይሆንም፣ ሃሳቡ ግን አንድ ነው:: የአገልግሎት ጸጋ ስጦታን የሚሰጥ ከሙታን በመነሣት ጠላትን ድል የነሣውና ወደ ሰማይ ያረገው ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው የሚል ነው ቆላ 2፣15:: እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባን ነገር፣ የኢየሱስ ወደ ሰማይ ማረግ፣ ጌታ መንፈስ ቅዱስንም ይሁን የአገልግሎትን ስጦታ እንዲሰጠን ያበቃው (qualify ያደረገው) ነገር ነው:: ጴጥሮስ በበዓለ ሃምሳ ቀን የመንፈስ ቅዱስን መውረድ ሲያስረዳም የሚያብራራው ሃሳብም ይሄንኑ የሚገልጽ ነው:: “ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው::” የሐዋ 2፣33:: በዚህ ክፍልም ጳውሎስ እንድንረዳ የሚፈልገው፣ የአገልግሎትን ጸጋ ለሰዎች ለመስጠት ብቁ (qualified) የሆነ ጌታ ኢየሱስ ብቻ መሆኑን ነው:: ለዚህ ነገር ብቃት ያለውና የሚገባው ሌላ ማንም የለም:: ማን የትኛውን የአገልግሎት ጸጋ በምን ያህል መጠን ማግኘት እንዳለበት እየወሰነ መደልደል የጌታ ሥራ እንጂ የቤተክርስቲያን ወይም የቤተክርስቲያን መሪዎች ሥራ አይደለም::

 

·  የጸጋ ስጦታ የቸርነት ስጦታ ነው:- ምንም አይነት ጸጋ ጌታ ይስጠን፣ የድነትም ይሁን (ኤፌ 2፣8) ወይም የአገልግሎት ይህ የሚያሳየው የሰጪውን መልካምነት፣ ቸርነት፣ በጎነትና ርህራሄ እንጂ የተቀባዮን ማንነት አይደለም:: ጸጋ ራሱ ጸጋ የሚሆነው ተቀባዩ የማይገባው ሲሆን ብቻ ነው:: ተቀባዩ የሚገባው ከሆነ ጸጋ ሳይሆን ደሞዝ ነው የሚባለው ሮሜ 4፣4-5:: ስለዚህ እግዚአብሔር ምህረትና ቸርነትን በእኛ አሳይቶ የአገልግሎትን ጸጋ ሰጠን ማለት፣ እኛ ከሁሉ የምንበልጥ እንደሆንን እያረጋገጠልን አይደለም:: ጸጋ የሚያሳየው የራሳችንን ማንነት ሳይሆን የሰጪውን ማንነት ነው:: ከጳውሎስ ሕይወትም የምንማረው አንዱ ትልቅ ነገር፣ የተሰጠውን ጸጋ እና የራሱን ማንነት ለያይቶ ማየቱ ነው:: ስለ ተሰጠው ጸጋ ታላቅነት ቢናገርም፣ ስለ ራሱ ግን ትንሽነት ነው የሚናገረው ኤፌ 3፣8-9:: ጸጋው የሰጪውን እንጂ የራስን ማንነት እንደማይገልጽ ጠንቅቆ የተረዳ ሰው ነው::


“ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ።“
(መጽሐፈ ምሳሌ 3:3-4)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us