ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች » ኤፌሶን » ጥናት 13 (ኤፌሶን 4፣1-16 ሐ) ለጥሪው የሚገባ አካሄድ - ክፍል 3
Email this page to a friend Printer-friendly   Tuesday, 20 October 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦“
(የዮሐንስ ራእይ 3:14)

rss

Today's verse

ጥናት 13 (ኤፌሶን 4፣1-16 ሐ) ለጥሪው የሚገባ አካሄድ - ክፍል 3

pdf version

ጳውሎስ “ለተጠራችሁበት መጠራት እንደሚገባ” ብሎ የጠቀሰውን ሃሳብ እንደሚከተሉት በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ከፍለን ማጥናት ጀምረናል::

 

1.              የጥሪው ምንነት

2.              የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ መትጋት

3.              ሰባቱ የአንድነት መሠረቶች

4.              የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማውቅ ወደሚገኝ አንድነት ማደግ

 

በክፍል 1 ጥናታችን ላይ ቁጥር አንድንና ሁለትን የተመለከትን ሲሆን፣ በክፍል 2 ጥናታችን ደግሞ ቁጥር ሶስትን በሙሉና አራትን ደግሞ እንደሚከተለው ከፍለን በከፊል ተመልክተናል::

 

4.የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማውቅ ወደሚገኝ አንድነት ማደግ ቁ. 7-16

 

በዚህ በቁጥር 4 ሥር፣ ማለትም በኤፌ 4፣7-16 ባለው ክፍል ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎት ወይም የአገልግሎት የጸጋ ሥጦታዎች በአንድነታችን ወይም በሕብረታችን ላይ ያላቸውን ሚና ያብራራል:: ይህንንም ሃሳብ እንደሚከተሉት ከፍለን ማጥናት ጀምረናል:-

 

ህ)የጸጋ ስጦታዎች ቁ. 7-10

ለ)የአምስቱ ስጦታዎች ምንነት ቁ. 11

ሐ)አምስቱ ስጦታዎች የተሰጡበት ዓላማና በአካሉ ላይ የሚያስገኙት ውጤት ቁ. 12-16

 

በክፍል 2 ጥናታችን ላይ ከላይ ከተጠቀሱት ውስጥ ሀ)ን ተመልክተናል:: በዚህ በአሁኑ ጥናታችን ደግሞ ለ)ን በከፊል መመልከት እንጀምራለን:: ከአምስቱ ስጦታዎችም ውስጥ በዚህ ጥናት ሐዋርያትን የምንመለከት ሲሆን፣ የተቀሩትን ደግሞ በሚቀጥሉት ጥናቶቻችን ላይ በተከታታይ እናጠናቸዋለን::

 

ለ)የአምስቱ ስጦታዎች ምንነት ቁ. 11

ማሳሰቢያ:- ስለ አምስቱ ስጦታዎች ስናጠና አንድ በጣም ልብ ማለት ያለብን ነገር፣ በአሁኑ ጊዜ በየትኛውም ቤተክርስቲያን እየተሠራበት ያለውን አሠራር ሁሉ ለትንሽ ደቂቃ ረስተን፣ መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ስጦታዎች እንዴት እንደሚያያቸው ለመመልከትና አዲስም ነገር ለመማር ክፍት መሆን አለብን:: በትክክል መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ከፈለገን፣ በአሁኑ ጊዜ ካሉት አሠራሮች ሣይሆን መነሳት ያለብን፣ ነገር ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ከራሱ ነው:: ምክንያቱም እንደ ኦርቶዶክስና ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት፣ የፕሮቴስታንትና የጴንጤም የቤተክርስቲያን አሠራሯ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ብቻ ሳይሆን ታሪካዊም መሠረቶች ስላሉት ነው:: የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን በሉተር ዘመን ስትጀመር በእርሱ በኩል ለቤተክርስቲያን የተመለሰላት እውነት የድነት እውነት ብቻ ነበር:: ይሄውም “መዳን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባለ እምነት ብቻ እንጂ በሥራ አይደለም” የሚል ነው:: የቤተክርስቲያን አወቃቀርና አሠራር ግን ከሉተርም በኋላ በመጡት የመንፈስ ቅዱስ እንቅስቃሴዎችም ቢሆን፣ መሠረታዊ ለውጥ ሳያገኝና ታሪካዊ መሠረቶቹን ሳይለቅ እስከ አሁን ድረስ አለ:: ስለዚህ ምንም እንኳን የጴንጤ እምነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ቢሆንም የቤተክርስቲያን አወቃቀሩና አሠራሩ ግን በአብዛኛው ታሪካዊ እንጂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ስለሌለው፣ ይህንን ክፍል ስናጠና ግዴታ አሁን ያለው አይነት አሠራር በመጽሐፍ ቅዱስ ለማግኘት መጣር የለብንም::

 

·       አምስቱ ስጦታዎች የአካሉ ስጦታዎች እንጂ በእያንዳንዱ አጥቢያ ቤተክርስቲያን የሚገኙ አይደሉም:-

በኤፌሶን መልእክት መግቢያ ላይ እንደተመለከትነው፣ የኤፌሶን መልእክት ስለ ቤተክርስቲያን ሲናገር ጠቅላላውን የክርስቶስን አካል የሚመለከት እንጂ ስለ አንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን (local church) እንደማይናገር አይተናል:: በዚህም ክፍል ጳውሎስ ስለ አምስቱ ስጦታዎች ሲናገር ስጦታዎቹ ለአካሉ የተሰጡ እንጂ በእያንዳንዱ አጥቢያ ቤተክርስቲያን አምስቱም ስጦታዎች ይኖራሉ ማለት እንዳይደለ በቅድሚያ መገንዘብ ያስፈጋል:: በመጽሐፍ ቅዱስም የምናገኛቸውም እያንዳንዱ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት አምስቱም ስጦታዎች የሚገኙባቸው አልነበሩም::

 

·       ሰዎች እንጂ ክፍት የሥራ ቦታዎች ወይም offices አይደሉም:-

“እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ ሌሎቹም ነቢያት፣ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፣ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ” ኤፌ 4፣11:: ይሄንኑ ክፍል የኦርጂናሉ የግሪክ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ያስቀምጠዋል:- “and He gave some apostles, some prophets, some evangelists, some pastors and teachers”. ይሄም የሚያሳየው ኢየሱስ ክርስቶስ ለአካሉ የሰጠው ሰዎቹን እንደሆነ ነው:: ሰዎችን ሐዋርያት ወይም ነቢያት ወዘተ አድርጎ ለቤተክርስቲያን እንደሰጣቸው ነው የሚናገረው:: ስለዚህ ሰዎቹ ራሳቸው ናቸው ስጦታዎቹ:: በአንደኛ ቆሮንቶስ መልእክት ላይ ደግሞ ልክ እንደ ልሳንና እንደ ሌሎቹ ስጦታዎች እነዚሁ ሰዎችም አብረው እንደ ስጦታ ሲቆጠሩ እንመለከታለን “እግዚአብሔርም በቤተክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፣ ሁለተኛም ነቢያትን፣ ሦስተኛም አስተማሪዎችን፣ ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን፣ ቀጥሎም የመፈወስ ስጦታ፣ እርዳታንም፣ አገዛዝንም፣ የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጎአል::” 1ቆሮ 12፣28:: ልክ ልሳን ወይም የመፈወስ ስጦታ ለቤተክርስቲያን ጌታ የሚሰጠው ስጦታ እንደሆነ ሁሉ፣ ሐዋርያትም እንዲሁ ለቤተክርስቲያን የተሰጡ ስጦታዎች ናቸው:: አምስቱ ስጦታዎች እንደ ልሳን ካሉት ስጦታዎች የሚለያቸው፣ ሌሎቹ መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠው የአገልግሎት ትጥቅ ሲሆኑ አምስቱ ግን ጌታ የአገልግሎት ጸጋ ያስታጠቃቸው ሰዎች ናቸው::

 

ስለዚህ ስለ አምስቱ ስጦታዎች ስንነጋገር፣ ጌታ ለቤተክርስቲያን ስለሰጠው ስዎች እንጂ፣ በቤተክርስቲያን ስላለ ሹመት ወይም ቦታ ወይም office አይደለም የምንነጋገረው:: ጌታ የሐዋርያነትን ወይም የነቢይነትን ወይም የእረኝነትን ክፍት ቦታ ወይም office አይደለም ለቤተክርስቲያን የሰጠው:: ጌታ የሰጠውና የሚሰጠው ሐዋርያ ወይም ነቢያ ወዘተ የሆኑ ሰዎችን ነው:: በአሁኑ ጊዜ በብዙ አብያተ ክርስቲያናት ትልቅ ችግርና ግራ መጋባት የሚከሰተው አማኞች እነዚህን አምስቱን ስጦታዎች፣ ሰዎች እንደሆኑ ሳይሆን በቤተክርስቲያን እንዳሉ ክፍት የሥራ ቦታዎች ወይም offices አድርገው ስለሚረዱአቸው ነው::

 

office ወይም ክፍት የሥራ ቦታ እና ሰዎች የሚለውን ነገር በይበልጥ ለማብራራት የሚከተለውን ምሳሌ እንመልከት:: የትኛውም አገር ውስጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ይኖራል:: ከመሥሪያ ቤቱ ጋር አብሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ቦታና ሹመት ደግሞ አለ:: መንግስት ቢለዋወጥም ቦታው ሁል ጊዜ አለ፣ ነገር ግን በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ለቦታው የሚፈልገውን ሰው ይሾምበታል:: ስለዚህ መንግስት በተለዋወጠ ቁጥር በቦታው ላይ የሚሾሙት ሰዎች ቢለዋወጡም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትነት ቦታ ወይም office ሁል ጊዜ አለ:: ልክ እንደዚሁ ብዙ ስዎች ስለ አምስቱ ስጦታዎች ሲያስቡ ጌታ የሐዋርያነትን፣ የነቢይነትን፣ የወንጌላዊነትን፣ የአስተማሪነትንና የእረኝነትን ቦታ ወይም office በቤተክርስቲያን የከፈተ ነው የሚመስላቸው::  ጌታ እንደነዚ ያሉ ቦታዎችን ወይም offices አልከፈተም:: ነገር ግን ሐዋርያት፣ ነቢያት፣ ወንጌላዊያን፣ አስተማሪዎችና እረኞች ያደረጋቸውን ሰዎች ነው ለቤተክርስቲያን የሚሰጠው::

 

የሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳስ አሠራርን አመጣጥ ስንመለከት፣ ለስህተቱ ትልቁ መንስኤ ጌታ የሰጠው ሰው እንጂ ቦታ ወይም ሹመት ወይም office እንዳልሆነ አለመረዳት ነው:: ጴጥሮስን ዋና ሐዋርያ ያደረገው ጌታ ነው:: ጌታ ጴጥሮስን ዋና ሐዋርያ ሲያደርግ የዋና ሐዋርያነት ቦታ ወይም office ግን በቤተክርስቲያን ውስጥ መክፈቱ አልነበረም:: ልክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ቦታ ወይም ሹመት ወይም office በየትም አገር እንዳለ ሁሉ፣ የሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያንም የዋና ሐዋርያነት ቦታን ወይም office ጌታ በቤተክርስቲያን የሰጠ ስለመሰላት፣ በዛ ቦታ ወይም office ገብተው የሚሠሩ ጳጳሳትን እስከ ዛሬ ድረስ ትሾማለች::

 

በፕሮቴስታንቶች/በጴንጤዎችና በኦርቶዶክሶችም ተመሳሳይ ችግሮች ይታያሉ:: እነዚህ አምስቱ ክፍት የሥራ ቦታዎች ወይም በቤተክርስቲያን ያሉ ሹመቶች ወይም offices ስለሚመስላቸው፣ ሰዎች ያንን ቦታ ለማግኘት ሲጋፉና ሲሽቀዳደሙ ይታያሉ:: አማኞች ተሽቀዳድመው የሚይዙት አምስት ክፍት የሥራ ቦታዎችን ወይም offices እግዚአብሔር በቤተክርስቲያን አልከፈተም፣ ነገር ግን በጸጋቸውና በትጥቃቸው አካሉን የሚጠቅሙ ሰዎችን ነው ለቤተክርስቲያን የሰጠው፣ የሚሰጠውም:: ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምስቱ ስጦታዎች ሲናገር በቤተክርስቲያን ስላለ ሹመት ወይም ቦታ ወይም office እንዳልሆነ መገንዘብ፣ ከብዙ ግራ መጋባት፣ ከተሳሳተም መረዳትና አካሄድ ይጠብቀናል::

 

·       አምስቱ ስጦታዎች ኢየሱስ የሚሰጠው እንጂ ቤተክርስቲያን የምትሾመው ሹመቶች አይደሉም:-

ባለፈው ጥናታችን በተለይ በኤፌ 4፣7-10 ላይ ጳውሎስ የአገልግሎት ጸጋን ሰጪ የሞተው፣ ከሙታንም የተነሣውና ወደ ሰማይ ያረገው ጌታ ኢየሱስ ብቻ እንደሆነ ገልጿል:: በመንፈስ ቅዱስ የሚሆኑ ስጦታዎቹንም ለመስጠት ጌታ ሞትን ድል አድርጎ መነሣት ብቻ ሳይሆን ወደ ሰማይ ማረግም ያስፈልገው እንደ ነበር አይተናል:: ስለዚህ መንፈስ ቅዱስን ለመስጠትም ይሁን በመንፈስ ቅዱስ ሰዎችን ለማጥመቅ፣ እንዲሁም የአገልግሎት ስጦታዎችን ለመስጠት ብቁ (qualified) የሆነ እርሱ ብቻ እንደሆነ ተመልክተናል::

 

በዚህ አሁን በምናጠናው ክፍል በኤፌ 4፣11 ላይም እነዚህን አምስቱን ስጦታዎች የሰጠውና የሚሰጠው ሌላ ማንም ሳይሆን ጌታ እንደሆነ ጳውሎስ ይገልጽልናል “እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ ሌሎቹም ነቢያት፣ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፣ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ”:: ሰውን ሐዋርያ ወይም ነቢይ ወይም ወንጌላዊ ወይም አስተማሪ ወይም እረኛ ማድረግ የሚችል ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው:: ይህ የቤተክርስቲያን ወይም የቲዎሎጂ ኮሌጆች ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶች ሥራና ስልጣን ጨርሶ አይደለም:: ቤተክርስቲያን ነቢይ ስለሚያስፈልጋት ብቻ፣ አንድን ነቢይ መሾምና ማድረግ አትችልም:: ሐዋርያ ወይም ወንጌላዊ ወይም እረኛ ማረግም ስልጣኑም ችሎታውም የላትም:: ይሄንን ሥራ እንድትሠራ አልተጠራችም:: ስለዚህ ሰዎችን እንዲህ ለመሾም መጨነቅም ይሁን መልፋት የለባትንም:: በማያገባት ነገር ውስጥም ገብታ፣ ለኢየሱስ ብቻ የተሰጠውን ሥራ ከእጁ ለመንጠቅ መጣር የለባትም:: አንዳንድ ጊዜ እንኳን ሰዎች ከእነዚህ ከአምስቱ ስጦታዎች አንዱን እንድታደርጋቸው ወደ ቤተክርስቲያን ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ በመጀመሪያ ደረጃ ይህ የኢየሱስ ሥልጣን እንጂ የቤተክርስቲያን ሥልጣን እንዳልሆነ ማስገንዘም ቤተክርስቲያን ይገባታል::

 

ብዙ ቦታ በአብያተ ክርስቲያናት የሚታየው በአገልግሎት መስክ ያለው አለመግባባት የሚመነጨው አንዱም ይህንን መሠረታዊ ነገር ካለመረዳት ነው:: ስለዚህ አምስቱን ስጦታዎች ለመሆን ተጠርተና የሚሉም ሰዎች፣ ቤተክርስቲያን የምትሾማቸው ስለሚመስላቸው የሹመት ጥያቄአቸውን ይዘው ለዚህ ሥራ ብቃቱም ሥልጣኑም ወዳልተሰጣት ወደ ቤተክርስቲያን በማቅረብ ቤተክርስቲያንን ያስጨንቃሉ:: ሙሉ ትጥቅን አስታጥቆ ሰዎችን ሐዋርያት፣ ነቢያት፣ ወንጌላዊያን፣ አስተማሪዎችና እረኞች የሚያደርግ ግን፣ ለዚህ ነገር ብቁ የሆነው፣ ከሙታንም የተነሣውና ወደ ሰማይ ያረገው፣ ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው::

 

ስለዚህ አምስቱ ስጦታዎች በቤተክርስቲያን ያሉ፣ ቤተክርስቲያንም ለምትወደው የምታድለው ሹመቶች አይደሉም:: እነዚህ ለተጠሩበት ነገር በጌታ ጸጋ የታጠቁ ሰዎች ናቸው:: በዚህ ረገድ ግን ቤተክርስቲያን፣ ጌታ ለዚህ ነገር ለጠራቸው ሳይሆን ለሆኑት (ማለትም ለምሳሌ ለወንጌላዊነት የተጠሩትን ሳይሆን ወንጌላዊ ለሆኑት) እውቅና መስጠት ትችላለች:: ከሁሉም በላይ ግን ሳይሆኑ ነን ከሚሉት ሰዎች መንጋዎችዋን መጠበቅ ይህ አንዱ ሥራዋ ነው ራእይ 2፣2 የሐዋ 20፣28-30::

 

·       የበቤተክርስቲያን እውቅና:-

በመጽሐፍ ቅዱስ የምንመለከተው እውቅና ሁለት ባሕርያት አሉት:: አንደኛ ሰዎቹ አምስቱን ስጦታዎች ለመሆን ስለተጠሩ ሳይሆን ለሆኑ ወይም ሆነው ለተገኙ የሚሰጥ ነው:: የእውቅና መሠረት ተጠራሁ የሚለው ሰው ያየው ራእይና ሕልም አይደለም ወይም ስለ እርሱ የተነገረ ትንቢት አይደለም ወይም የቴዎሎጂ ኮሌጅ ሰርተፊኬትም አይደለም:: ፊልጶስ ወንጌላዊ ተብሎ የተጠራው፣ ለወንጌላዊነት እንደተጠራ ቤተክርስቲያን አስቀድማ ጥሪውን ስላወቀች አይደለም:: እንዲያውም ቤተክርስቲያን የሾመችው ለዲቁና ነበር:: ፊልጶስ ወንጌላዊ ተብሎ የተጠራውና በቤተክርስቲያንም እውቅና ያገኘው ወንጌላዊ ሆኖ ስለተገኘና የወንጌላዊን ሥራ ስለሚሠራ ነው:: አጋቦስም እንደ ነቢይ እውቅና የተሰጠው ነቢይ ሆኖ ስለተገኘ እንጂ ቤተክርስቲያን ልዩ የነቢይነት ሹመት ከሰጠችው በኋላ አይደለም ነቢይ የሆነው:: ጳውሎስና በርናባስም ለሐዋርያነት ቀድመው ተጠርተዋል:: “...መንፈስ ቅዱስ:- በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ::” የሐዋ 13፣2:: ለጠራኋቸው ሥራ የሚለው ስንኝ፣ ለሐዋርያነት ቀድመው እንደተጠሩ ያሳያል:: ቢሆንም ግን ቤተክርስቲያን እስከዚያን ጊዜ የምታውቃቸው እንደ ነቢያትና አስተማሪዎች ብቻ ነበር ሐዋ 13፣1:: ምክንያቱም እስከዚያን ጊዜ ድረስ ሆነው የተገኙት እንደ ነቢያትና መምህራን ብቻ ነበር:: ምንም እንኳን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ለተጠሩበት ሥራ የተለዩ ቢሆኑም፣ የተጠሩትም ለሐዋርያነት ቢሆንም የሐዋርያትን ሥራ እስከሚሠሩበት ጊዜ ድረስ ቤተክርስቲያን ሐዋርያት ብላ አልጠራቻቸውም:: የሐዋርያነትን እውቅና ያገኙት ሐዋርያት ሆነው ከተገኙ በኋላ ነው የሐዋ 14፣4/14::

 

ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያተኩረው ሆኖ መገኘት ላይ እንጂ ተብሎ መጠራት ላይ አይደለም:: ሐዋርያም ይሁን ነቢይ ወይም ወንጌላዊ ወዘተ ሆኖ ለመገኘት የቤተክርስቲያን እውቅናና ሹመት አያስፈልግም:: በአብዛኛው በአሁኑ ዘመን በየአብያተ ክርስቲያናት የሚታየው ሽኩቻ ተብሎ መጠራት ላይ ያተኮረ ነው:: በመጽሐፍ ቅዱስ ግን ተብሎ ከመጠራት በፊት ሆኖ መገኘት ይቀድማል:: በመጽሐፍ ቅዱስ ተብለው ሳይጠሩና የአገልግሎት ጸጋቸውም ስም ሳይሰጠው ነገር ግን ሆነው ተገኝተውና እውነተኛ አገልግሎትን ሰጥተው ያለፉ፣ እንደ እስጢፋኖስ፣ ቲቶና አጵሎስ አይነት ብዙ እውነተኛ የጌታ ባሪያዎች አሉ:: ቤተክርስቲያን ስም አልሰጠቻቸውም፣ ነገር ግን ሆነው ተገኝተዋል:: ሆነው ለመገኘት ደግሞ ተብሎ መጠራቱ ወይም መድረክ የሚያዘጋጅላቸው አላስፈለጋቸውም::

 

በሁለተኛ ደረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ በብዛት የምንመለከተው formal (ኦፊሲዬላዊ፣ በሥነ ሥርዓትና በሥነ በዓል) የሆነ እውቅና ሳይሆን informal (ኦፊሲዬላዊ ያልሆነ፣ ያለ ልዩ ሥነ ሥርዓትና ሥነ በዓል የሆነ) ነው:: በርናባስና ጳውሎስ እንዴት ነቢያትና መምህራን እንደተባሉ ስንመለከት (የሐዋ 13፣1)፣ እንደ ፊልጶስ፣ እስጢፋኖስ፣ አጋቦስ፣ ሲላስ፣ ጢሞቴዎስ፣ ቲቶ ወዘተ ያሉትንም ስናያ፣ አንዳቸውም በቤተክርስቲያን የሹመት ሥነ ሥርዓት ተደርጎ ኦፊሲዬላዊ እውቅና ያገኙ አልነበሩም:: ነገር ግን ተገልጋዩ ማለት ቤተክርስቲያን፣ እነርሱ ላይ ከሚያየው ጸጋ የተነሳ ያለ ምንም ኦፊሲዬላዊ ሥነ ሥርዓት ነበር የተቀበላቸው፣ እውቅናንም የሰጣቸው::

 

ስለዚህ አምስቱን ስጦታዎች የሚሠጥና የሚያደርግ ጌታ ስለሆነ፣ ቤተክርስቲያን ይህንን ሥራ ከጌታ ለመንጠቅ መሞከርም ይሁን ያልተሰጣትን ሸክም መሸከም አያስፈልጋትም:: እነዚህን ስጦታዎች ለመሆን ተጠራሁ የሚል ካለ፣ ሆኖ ይገኝ:: ሆኖ ለመገኘት ደግሞ መድረክም፣ ተብሎ መጠራትም፣ የቤተክርስቲያን ሥነ ሥርዓትም አያስፈልግም:: ሆኖ የተገኘን ሰው አማኞች ከሚያዩት ጸጋ የተነሣ፣ እውቅናን ይሰጡታል:: የእውቅና ስም ባይሰጠውም እንኳን እንደ እስጢፋኖስና እንደ አጵሎስ ይህ ሥራውን ከመሥራት አያግደውም::

 

·       ሐዋርያት

ቃሉ በግሪኩ apostolos ሲሆን ትርጉሙም የተላከ (one sent forth) ማለት ነው:: ቃሉ በዋናነት እንግዲህ ላኪው ለአንድ ለተወሰነ (specific) ሥራ የላካቸው ወኪሎችን ወይም አምባሳደሮችን ወይም እንደራሴዎችን የሚያመለክት ነው:: ሐዋርያ የበላይ ላኪ ያለው ነው እንጂ በራሱ ተነሳሽነት የሚሄድ አይደለም:: መልእክቱንም የተወሰነ (specific) ሥራውንም ከላኪው የተቀበለ እንጂ የራሱን መልእክትና የፈቀደውን የሚሠራ አይደለም:: ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደርና ላኪውን ተክቶ ወይም ልክ እንደ ላኪው ሆኖ በእርሱ ፈንታ እንደራሴ ሆኖ ስለሚሠራ፣ ላኪው የሚያስፈልገውን ትጥቅና ሙሉ ስልጣን የሰጠው ሰው ነው እንጂ ያለ ትጥቅና ስልጣን ወይም በራሱ ትጥቅና ሥልጣን የሚሄድ አይደለም::

 

የመጀመሪያው ሐዋርያ ራሱ ጌታ ኢየሱስ ነው ዕብ 3፣1 ዮሐ 17፣3:: አብ በሙሉ ስልጣን ለአንድ ለተወሰነ ተግባር የላከው በመሆኑ ጌታ የአብ መልክተኛ ወይም ሐዋርያ ነው::

 

በአዲስ ኪዳን ጌታ ሐዋርያ ያደረጋቸው የተለያዩ አይነት ሐዋርያት ነበሩ:: በመጀመሪያ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት  ወይም የበጉ ሐዋርያት ተብለው የሚጠሩት ናቸው ሉቃ 6፣13 ራእይ 21፣14:: እነዚህ ጌታ በምድር ዘመኑ ሲመላለስ አብረው የነበሩ፣ ሞቱንና ትንሣኤውንም ያዩ፣ ወደፊትም ጌታ ሲመጣና በምድር ላይ ሲገዛ በአሥራ ሁለቱ የእሥራኤል ነገዶች ላይ የሚገዙ እና በአዲሲቷም ኢየሩሳሌም ልዩ ስፍራ ያላቸው ናቸው የሐዋ 1፣21-22 ማቴ 19፣27-28 ራእይ 21፣14:: ስለዚህ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ከሌሎቹ ሐዋርያት በተለየ ሁኔታ ልዩ የሹመት ቦታ ያላቸው ስለሆኑ ቁጥራቸውም ሊቀንስም ሊጨምርም አይችልም::

 

ከአሥራ ሁለቱ ሌላ በመጽሐፍ ቅዱስ ሐዋርያ ተብለው የተጠሩ ሌሎችም ነበሩ:- ጳውሎስና በርናባስ (የሐዋ 14፣4/14)፣ አንዲራኒቆንና ዩልያን (የሐዋ 16፣7)፣ ሁለት ስማቸው ያልተጠቀሰ ሐዋርያት (2ቆሮ 8፣23 በዚህ ክፍል “መልእክተኞች” ተብሎ በአማርኛ የተተረጎመው apostolos ወይም ሐዋርያ የሚለው የግሪክ ቃል ነው)፣ አፍሮዲጡ (ፊልጵ 2፣25 እዚህም ላይ “መልእክተኛ” ተብሎ በአማርኛ የተተረጎመው ቃል፣ ያው apostolos ወይም ሐዋርያ የሚለው የግሪክ ቃል ነው):: በ1ተሰ 2፣6 ላይ ደግሞ ልክ እንደ ጳውሎስ በተለያየ ቦታ እየዞሩ ከእርሱ ጋር የሐዋርያትን ሥራ የሚሠሩት ሲላስና ጢሞቴዎስ እንደ ሐዋርያት ሲጠሩ እንመለከታለን:: “ጳውሎስና ስልዋኖስ(ሲላስ) ጢሞቴዎስም፣ በእግዚአብሔር አብ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም ወደምትሆን ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች ቤተክርስቲያን...” 1ተሰ 1፣1:: “የክርስቶስ ሐዋርያት እንደ መሆናችን ልንከብድባችሁ ስንችል፣ ከእናንተ ቢሆን ወይም ከሌሎች ክብርን ከሰው አልፈለግንም::” 1ተሰ 2፣6::

 

·       በሐዋርያት ላይ የሚታዩ ዋና ዋና ባሕርያት

·       ሐዋርያት የተላኩ ስለሆኑ ለአንድ የተወሰነ ሕዝብ ተልዕኮ (mission) ያላቸው ሰዎች ናቸው ገላ 2፣8:: ይሄንንም ጠንቅቀው የሚያውቁና ያንን ተልዕኮ እስከሚያሳኩ የማያርፉ ናቸው::

·       ተልእኮአቸው ለብዙ አብያተ ክርስቲያናትን እንጂ ለአንድ አጥቢያ ስላይደለ በአንድ ቦታ ተደላድለው የሚቀመጡ ሰዎች ሳይሆኑ ተዘዋዋሪ ወይም ተጓዦች ናቸው:: የሐዋርያትን ተልዕኮ ለማስፈጸም ከሐዋርያት ጋርም አብረው ሲሰሩ የነበሩትም እንደ ጢሞቴዎስ፣ ሲላስና ቲቶ ያሉትም እንዲሁ ተጓዦችና ያንን ተልዕኮ በብዙ አብያተ ክርስቲያናት የሚያስፈጽሙ እንጂ በአንድ አጥቢያ ተሹመው የሚያገለግሉ አልነበሩም::

·       ሐዋርያት ከላኪያቸው ከጌታ ከኢየሱስ ጋር እጅግ የቀረበ ግንኙነት የነበራቸውና አስተምህሮታቸውንም/ትምህርታቸውን/doctrine ከእርሱ ያገኙ ናቸው ገላ 1፣11-12 ማቴ 28፣19-20::

·       አስተምህሮታቸው/ትምህርታቸው/doctrine ክርስቶስን ማዕከላዊ ያደረገና ጠቅላላውን የእግዚአብሔርን የድነት ምስጢር የሚገልጥ እንጂ በፈውስ ወይም በብልጥግና ወይም በእምነት ወዘተ በሆኑት ቁንጽል ሃሳቦች ላይ ብቻ የተመሠረተ አልነበረም::

·       ምንም አይነት የሐዋርያት መገለጥ ከቀደሙት የሐዋርያት ትምህርት ጋር የሚስማማ ነው ገላ 2፣1-2/7-10::

·       ሐዋርያትና ነቢያት ከድነት ምስጢር በተጨማሪ የቤተክርስቲያን ወይም የአካሉ ምስጢር በይበልጥ የተገለጠላቸው ሰዎች ናቸው ኤፌ 3፣3-6::

·       ስለዚህም ሐዋርያትና ነቢያት ጌታ እንደሚፈልገው አይነት የሆኑ የአጥቢያ ቤተክርስቲያናት ተካዮችና ትክክለኛ መሠረት መሥራቾች ናቸው ኤፌ 2፣20 1ቆሮ 3፣6/9:: “የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአንጺ አለቃ (skillful architect and master builder) መሠረትን መሠረትሁ፣ ሌላውም በላዩ ያንጻል::...” 1ቆሮ 3፣10:: ስለዚህ ሐዋርያት ጌታ እንደሚፈልገው አይነት አብያተ ክርስቲያናትን በመመሥረት ባለሙያተኞች፣ ጠቢባንና አዋቂዎች ናቸው:: በዚህ ዘመን ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ጠቅላላ አወቃቀራቸና አሠራራቸው ምን ያህል ከመጽሐፍ ቅዱሱ የቤተክርስቲያን አወቃቀርና አሠራር እንደሚርቅ ስንመለከት፣ በአብዛኛው ባለሙያ ባልሆኑ ሰዎች የተመሠረቱ እንደሆኑና የሐዋርያትና የነቢያትም አገልግሎት በአሁኑ ዘመን እጅግ እንደሚያስፈልገን ያስገነዝበናል::

·       ሐዋርያት የአብያተ ክርስቲያናት ተካዮችና መሥራቾች ብቻ ሳይሆኑ፣ የተጀመሩትንም አብያተ ክርስቲያናት እውነተኛ መሠረት ላይ የሚያቆሙ ነበሩ:: ስለዚህ የተጀመሩትንም እየዞሩ በመጎብኘት አብያተ ክርስቲያናትን ጌታ የሚፈልገውን አይነት መሠረትና ቅርጽ እንዲይዙ ያደርጉ ነበር::

·       ሐዋርያት የሌሎቹ የአራቱም ጸጋዎች በአገልግሎታቸው ይታያል::


·       የሐዋርያነት ምልክቶች

·       ሐዋርያት በሙሉ ስልጣን የተላኩ ስለሆኑና የወንጌላውያንንም ሥራ ስለሚሠሩ፣ በአገልግሎታቸው ተዓምራትና ምልክቶች ይታያሉ:: “...እኔ ምንም ባልሆን እንኳ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በምንም አልጎድልምና:: በእርግጥ የሐዋርያነት ምልክት በመካከላችሁ በምልክትና በድንቅ ነገር በተአምራትም በሁሉ ትዕግሥት ተደረገ::” 2ቆሮ 12፣11-12:: የሐዋ 2፣33::

·       የመጨረሻው የሐዋርያነት ማረጋገጫና ማህተም ሥራቸውና የሥራቸው ፍሬዎች ናቸው:: “...እናንተስ በጌታ ሥራዬ አይደላችሁምን? የሐዋርያነቴ ማህተም በጌታ እናንተ ናችሁና ለሌሎች ሐዋርያ ባልሆን ለእናንተስ ምንም ቢሆን ሐዋርያ ነኝ::” 1ቆሮ 9፣1-2:: በአዲስ ኪዳን ተደጋግሞ የምናየው፣ የአንድ ሰው ጸጋ ወይም ጥሪ የሚታወቀው በትንቢት ወይም በራዕይ አይደለም:: እኔ ሐዋርያ ነኝ እያለ ሕልሙንና ከሌሎች የተነገረለትን ትንቢት በመቁጠሩ አይደለም:: በ2ቆሮ 3፣1-3 ላይም እንደምንመለከተው ሌሎች በሚጽፉትም ደብዳቤ አይደለም:: ነገር ግን በሰውዬው ላይ በሚታይ የጌታ ትጥቅና የሥራ ፍሬ ነው:: ጌታን ሰዎች እንደ መሲህ የተቀበሉት በየቦታው እየሄደ፣ እንዴት መጥምቁ ዮሐንስ ትንቢት እንደተናገረለት በማወጅ አይደለም:: እግዚአብሔር አብ እንኳን እንዴት ከሰማይ በድምጽ እንዳረጋገጠለት በመናገርም አይደለም:: ነገር ግን ሰዎች እርሱን እንደ መሲሑ የተቀበሉት፣ ከእግዚአብሔር እንደተላከ እንደ መሲሑ ሆኖ በመገኘቱ በእርሱ ላይ በሚያዩት የእግዚአብሔር ትጥቅና የሥራ ፍሬ ነው:: ጳውሎስም ሐዋርያነቱን እንዲቀበሉት በየቦታው ለአሕዛብ የአንጾኪያ ቤተክርስቲያንን ደብዳቤ ይዞ አይደለም የዞረው:: አሕዛብ እርሱን እንደ ሐዋርያ የተቀበሉት ሐዋርያ ሆኖ በመገኘቱ ማለትም የሐዋርያ የጸጋ ትጥቅና የሥራ ፍሬ በሕይወቱ ስለሚታይ ነው:: ስለዚህ የጥሪ ወይም የአገልግሎት ማረጋገጫ ሕልም፣ ራእይና ትንቢት ሳይሆን ሆኖ መገኘት ነው::

 


“ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ።“
(መጽሐፈ ምሳሌ 3:3-4)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us