ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች » ኤፌሶን » ጥናት 15 (ኤፌሶን 4፣1-16 ሠ) ለጥሪው የሚገባ አካሄድ - ክፍል 5
Email this page to a friend Printer-friendly   Tuesday, 20 October 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦“
(የዮሐንስ ራእይ 3:14)

rss

Today's verse

ጥናት 15 (ኤፌሶን 4፣1-16 ሠ) ለጥሪው የሚገባ አካሄድ - ክፍል 5

pdf version

ጳውሎስ “ለተጠራችሁበት መጠራት እንደሚገባ” ብሎ የጠቀሰውን ሃሳብ እንደሚከተሉት በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ከፍለን ማጥናት ጀምረናል::

 

1.              የጥሪው ምንነት

2.              የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ መትጋት

3.              ሰባቱ የአንድነት መሠረቶች

4.              የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማውቅ ወደሚገኝ አንድነት ማደግ

 

በክፍል 1 ጥናታችን ላይ ቁጥር አንድንና ሁለትን የተመለከትን ሲሆን፣ በክፍል 2፣ 3 እና 4 ጥናታችን ደግሞ ቁጥር ሶስትን በሙሉና አራትን ደግሞ እንደሚከተለው ከፍለን በከፊል ተመልክተናል::

 

4.የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማውቅ ወደሚገኝ አንድነት ማደግ ቁ. 7-16

 

በዚህ በቁጥር 4 ሥር፣ ማለትም በኤፌ 4፣7-16 ባለው ክፍል ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎት ወይም የአገልግሎት የጸጋ ሥጦታዎች በአንድነታችን ወይም በሕብረታችን ላይ ያላቸውን ሚና ያብራራል:: ይህንንም ሃሳብ እንደሚከተሉት ከፍለን ማጥናት ጀምረናል:-

 

ህ)የጸጋ ስጦታዎች ቁ. 7-10

ለ)የአምስቱ ስጦታዎች ምንነት ቁ. 11

ሐ)አምስቱ ስጦታዎች የተሰጡበት ዓላማና በአካሉ ላይ የሚያስገኙት ውጤት ቁ. 12-16

 

በክፍል 2 ጥናታችን ላይ ከላይ ከተጠቀሱት ውስጥ ሀ)ን ተመልክተናል:: በክፍል 3 እኛ 4 ጥናታችን ደግሞ ለ)ን በከፊል የተመለከትን ሲሆን፣ በእነዚህም ጥናቶች ከአምስቱ ስጦታዎችም ውስጥ የሐዋርያትን፣ የነቢያትን፣ የወንጌላዊያንና የእረኞችን ምንነት ለማየት ሞክረናል:: በዛሬው ጥናታችን ላይ በመጀመሪያ የአስተማሪዎችን ምንነት በመመልከት ከላይ ከተጠቀሱት ውስጥ ለ)ን እንጨርሳለን:: ከዚያም ሐ)ን በማጥናት ክፍል 4ን በሙሉ እናጠናቅቃለን::

 

ለ)የአምስቱ ስጦታዎች ምንነት ቁ. 11

 

·       ሐዋርያት (ጥናት 13ን ይመልከቱ)

 

·       ነቢያት (ጥናት 14ን ይመልከቱ)

 

·       ወንጌላውያን (ወንጌልን ሰባኪዎች) (ጥናት 14ን ይመልከቱ)

 

·       እረኞች/ፓስተሮች (pastors/shepherd) (ጥናት 14ን ይመልከቱ)

 

·       አስተማሪዎች:-

የግሪኩ ቃል didaskalos ሲሆን ቃሉ didasko (ማስተማር) ከሚለው የግሪክ ቃል ጋር የተዛመደ ነው:: didasko (ማስተማር) የሚለው ቃል የሚከተሉት ትርጉሞች አሉት:- to hold discourse with others in order to istruct them (ለሌሎች ትምህርትን ወይም መመሪያን ለመስጠት የሚደረግ ንግግር), to deliver didactic discourses (ሌሎችን ለማስተማር የሚደረግ ንግግር), to impart instruction (ትምህርትን ወይም መመሪያን ለሌሎች ማካፈል ወይም መስጠት), instil doctrine into one (አስተምህሮትን ወይም ትምህርትን ተራ በተራ ወይም ቀስ በቀስ ማስተዋወቅ), to explain (ማስረዳት ወይም ማብራራት), expound (ነገሮችን በጥልቀት በማብራራት ማስረዳት)::

 

እንደ ቤተክርስቲያን የአካል ብልቶች ሁላችን እርስ በርስ ልንማማር ብንችልም፣ በዚህ ክፍል ግን የምናየው ለዚሁ ለማስተማር ሥራ የተለየ ጸጋ ጌታ ስላስታጠቃቸው ሰዎች ነው::

 

·       የአስተማሪዎች ብቃት:- አስተማሪዎች እንግዲህ የጌታን አስተምህሮት (ትምህርት) ለሕዝቡ ተራ በተራ በጥልቀት የሚያብራሩና የሚያስረዱ ሰዎች ናቸው:: ከቃሉ ማብራሪያ እንደምንረዳው፣ አስተማሪነት ሶስት ዋና ዋና ብቃቶችን ያካተተ ነው:-

 

·       የትምህርቱ (የአስተምህሮት/doctrine) ይዘት ወይም ምንነት:- የአንድ አስተማሪ ጸጋ በመጀመሪያ ደረጃ በትምህርቱ (አስተምህሮት/doctrine) ምንነት የሚለካ ነው:: በአዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ ሊማረው የሚገባው ትምህርቱ (አስተምህሮቱ/doctrine) በሐዋርያት አስቀድሞ ተሰጥቶአል:: በአዲስ ኪዳን ላይ የነበሩትንም ቅዱሳን ስንመለከት የሚማሩት ትምህርት ይሄንኑ በሐዋርያት የተሰጠውን ትምህርት ነበር:: የሚከተሉትን ጥቅሶች በሚገባ ስናጠና፣ በአዲስ ኪዳን ቅዱሳን ሊማሩት የሚገባው ትምህርት (አስተምህሮት/doctrine) ከጌታ ከራሱ ለሐዋርያት የተሰጠውን የራሱን ትምህርት (አስተምህሮት/doctrine) ብቻ እንደሆነ እንገነዘባለን:: “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው...” ማቴ 28፣19-20:: በዚህ ክፍል ሐዋርያቱ ምን ማስተማር እንዳለባቸው ጌታ መመሪያ ሲሰጣቸው እንመለከታለን:: ምን እናስተምር ብለው ልዩ ጭንቀት ውስጥ መግባት የለባቸውም፣ የሚያስተምሩትን ነገር ለማግኘት የትም መውጣትና መውረድ የለባቸውም:: የትምህርቱ ይዘትና ምንነት በግልጽ ተቀምጦአል፣ ይህም “ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው” የሚል ነው:: ስለዚህ የሐዋርያት ትምህርት ከየትም ከየትም ወጥተውና ወርደው የሚያገኙት ሳይሆን ከጌታ ከራሱ የተሰጣቸውን ብቻ እንዲያስተምሩ ነው የታዘዙት:: ትምህርታቸው እንግዲህ ልዩ የሆነ አዲስ ነገር ሳይሆን፣ ጌታ ቀድሞውኑ የሰጣቸውን ብቻ ነው:: በአሁኑ ዘመን እንደምናስበው የሆነውንም ያልሆነውንም እንደፈለግነው የማስተማር መብት ያለን እንደሚመስለን ሳይሆን፣ ሐዋርያት እንኳ ጌታ ከሰጣቸው ውጭ፣ የፈለጉትን የማስተማር ፈቃድ አልነበራቸውም:: በሐዋርያት ሥራ ላይም የመጀመሪያዎቹ አማኞች ምን እንደተማሩ ስንመለከት የሚከተለውን እናገኛለን:- “ቃሉን የተቀበሉ ተጠመቁ፣ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ፣ በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቁረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር::” የሐዋ 2፣41-42:: በዚህም ክፍል የምናየው፣ የመጀመሪያዎቹ አማኞች ይማሩት የነበረው ትምህርት፣ መጨረሻ የሌለው ተረት (2ጢሞ 4፣3-4) ወይም የሰው ሎጂክ ሳይሆን የሐዋርያትን ትምህርት ነበር:: በአዲስ ኪዳን ትምህርቱ (አስተምህሮቱ/doctrine) ጌታ ለሐዋርያት፣ ሐዋርያቱ ደግሞ ለአማኞች የሰጡትና ቀድሞውንም ያለና የተመሠረተ ትምህርት ነው:: የአስተማሪዎች ሥራ አዲስ ትምህርት (አስተምህሮት/doctrine) ማምጣት ወይም የሰውን ሎጂክ ማስተማር ሳይሆን፣ አስቀድሞ በሐዋርያት የተሰጠውን ትምህርት (አስተምህሮት/doctrine) አማኞች እንዲጨብጡት በሚገባ ማስረዳት ነው:: ጢሞቴዎስም አስተማሪዎችን እንዲያዘጋጅ ጳውሎስ ሲመክረው የምንመለከተው ተመሳሳይ ነገር ነው:: “ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ::” 2ጢሞ 2፣2:: ስለዚህ ጢሞቴዎስ አደራ የሚላቸው ሰዎች፣ የጳውሎስን ማለትም የሐዋርያትን ትምህርት እንዲያስተምሩ ነው እንጂ እንዲሁ አስተማሪ ሆነው የመሰላቸውን ሁሉ ለሕዝቡ እንዲያስተላልፉ አይደለም:: እንግዲህ በአዲስ ኪዳን ማንም የራሱን ወይም የሰዎችን ሎጂክና ሃሳብ ወይም መጨረሻ የሌለውን ተረት ወዘተ ማስተማር በመሠረቱ አልተፈቀደለትም:: በአዲስ ኪዳን ያለው ትምህርት አንድ ብቻ ነው:: ይሄውም የሐዋርያት ትምህርት ነው:: የአስተማሪዎች ሥራ እንግዲህ የሐዋርያትን ትምህርት በመጀመሪያ በትክክል (accrate) ለራሳቸው ከተረዱ በኋላ፣ አማኞች በሚገባቸው መንገድ ይሄንኑ ትምህርት ማስተላለፍና ማስረዳት ነው::

 

·       የትምህርቱ (አስተምህሮቱ/doctrine) ትክክለኝነት (accuracy):- ሌላው የአስተማሪ ብቃት መለኪያ፣ የሐዋርያትን ትምህርት (አስተምህሮት/doctrine) ራሱ በትክክል (accurate) መረዳቱ ነው:: “እርሱ የጌታን መንገድ የተማረ ነበረ፣ የዮሐንስንም ጥምቀት ብቻ አውቆ በመንፈስ ሲቃጠል ስለ ኢየሱስ ይናገርና በትክክል ያስተምር ነበር::” የሐዋ 18፣25:: ትምህርት (አስተምህሮት/doctrine) የእምነትና የሕይወትን አቅጣጫ የሚወስንና መንገድንም የሚያሳይ ስለሆነ፣ የትምህርቱ ይዘት ወይም ምንነትና ትክክለኛነት እጅግ ወሳኝ ነው:: ስለዚህ በመጀመሪያ ደረጃ አስተማሪው ራሱ የእግዚአብሔርን ቃል በትክክል ካልተረዳ፣ ራሱም ስቶ ሌሎችንም ወደ ተሳሳተ መንገድና የሕይወት አቅጣጫ ይመራል:: ስለዚህ የአስተማሪነት ሥራ የሰውን ሕይወትና እምነት አቅጣጫ የሚወስን ስለሆነ እጅግ ጥንቃቄ የሚጠይቅና በጌታም ዘንድ በፍርድ የሚያስጠይቅ ነው ያዕ 3፣1::

 

·       የማስረዳትና የማስተላለፍ ችሎታ:- የአንድ አስተማሪ ጸጋ የሚለካበት ሌላው ነገር፣ ራሱ በትክክል የተረዳውን የሐዋርያትን ትምህርት (አስተምህሮት/doctrine) ሌሎች በሚገባቸው ሁኔታ ማቅረብ፣ ማስረዳትና ማስጨበጥ በመቻሉ ነው:: ይህ እጅግ አስፈላጊ የሆነ የአስተማሪ ብቃት ነው:: ሰው ምንም ያህል አንድን ነገር ቢረዳና ቢያውቅ፣ የተረዳውን ነገር ሌሎች በቀላሉ እንዲገባቸውና እንዲረዱት አድርጎ ማስተላለፍ ካልቻለ፣ ለሌሎች ምንም አይጠቅምም:: የተረዱትን መንፈሳዊ ነገር ለሌሎች በቃላት ገልጾ ማስተላለፍ ቀላል ነገር አይደለም:: ጌታ መንፈሳዊውን ነገር ሌሎች በሚገባቸውና ሊረዱት በሚችሉት መንገድ ነበር በጥበብና በምሣሌ የሚያስተላልፈው:: ምንም እንኳን ነገሮቹ መንፈሳዊ ቢሆኑም፣ የጌታ ምሣሌዎች ግን ሕዝቡ በዕለት ተለት ኑሮው የሚያውቃቸው ነበሩ:: የተረዱትን በጥበብና በምሣሌ አድርጎ ሰሚዎቹ ሊረዱት በሚችሉት መንገድ ማስተላለፍና ማስረዳት፣ ይህ እንግዲህ አስተማሪዎች ሊኖራቸው የሚገባ አንዱ ብቃት ነው::

 

·       በአዲስ ኪዳን የተጠቀሱ ምሣሌዎች:- በአዲስ ኪዳን ብዙ ያስተማሩ ስዎች ቢጠቀሱም በቤተክርስቲያን ግን አስተማሪ ወይም መምህር ተብለው የተጠሩት በየሐዋ 13፣1 ላይ የተጠቀሱት በአንጾኪያ ቤተክርስቲያን የነበሩት አገልጋዮች ናቸው:: ከእነዚህም ውስጥ ጳውሎስና በርናባስ ይገኙበታል:: ጳውሎስና በርናባስም ያቺን ቤተክርስቲያን ለአንድ አመት ያህል አስተምረዋል የሐዋ 11፣26::

 

·       የማነጽ ሥራ:- የአስተማሪዎች ሥራ እንደ ሐዋርያት ቤተክርስቲያንን የመመሥረት ላይ ያተኮረ ሳይሆን፣ የተመሠረተውን የማነጽ ላይ ያተኮረ ነው 1ቆሮ 3፣6/10:: የአንጶኪያን ቤተክርስቲያንም ስንመለከት፣ ጳውሎስና በርባስ ወደዚያ ሄደው ከማስተማራቸው በፊት ቤተክርስቲያኒቷ ቀድማ ተመሥርታ ነበር:: ትምህርት ላመኑት የሚሰጥ፣ ከመሠረት በኋላ ያለ የግንባታ ሥራ ነውና::

 

 

ሐ)አምስቱ ስጦታዎች የተሰጡበት ዓላማና በአካሉ ላይ የሚያስገኙት ውጤት ቁ. 12-16

 

በኤፌ 4፣11 ላይ የአምስቱን ስጦታዎች ምንነት ጌታ በረዳን መጠን ተራ በተራ ተመልክተናል:: በዚህ ክፍል ደግሞ ስጦታዎቹ የተሰጡበትን ዓላማና በአካሉ ወይም በቤተክርስቲያን ላይ የሚያስገኙትን ውጤት እንመለከታለን::

 

ይህን ክፍል ማለትም ኤፌ 4፣12-16 ላይ ያለውን ክፍል ከቀድሞው መጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አ.መ.ት) በይበልጥ የመልእክቱን ይዘት ግልጽ ስለሚያደርገው፣ በአዲሱ መደበኛ ትርጉም ብናጠናው ሊተላለፍ የተፈለገውን መልእክት የበለጠ ልንረዳው እንችላለን:: ስለዚህ እኛም ይህን ክፍል የምናጠናው በአዲሱ መደበኛ ትርጉም (አ.መ.ት) ይሆናል::

 

1ኛ. አምስቱ ስጦታዎች የተሰጡበት ዓላማ:-

“አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ እንዳንዶቹ ነቢያት፣ እንዳንዶቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፣ ሌሎቹ ደግሞ እረኞችና አስተማሪዎች ይሆኑ ዘንድ የሰጠ እርሱ ነው፣ ይኸውም የክርስቶስ አካል ይገነባ ዘንድ፣ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ለማዘጋጀት ሲሆን፣ ይህም የሚሆነው፣ ሁላችንም የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት በመምጣትና ሙሉ ሰው በመሆን፣ በክርስቶስ ወዳለው ፍጹምነት ደረጃ እስከምንደርስ ነው::” ኤፌ 11-13 (አ.መ.ት):: በዚህ ክፍል ላይ ጌታ አምስቱን ስጦታዎች የሰጠበት ምክንያት ተገልጿል:: ይሄውም “የክርስቶስ አካል ይገነባ ዘንድ፣ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ለማዘጋጀት” ነው:: ይሄንኑ ክፍል ማለትም ቁ. 12ን የAmplified መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ይተረጉመዋል:- “His intention was the perfecting and the full equipping of the saints (His consecrated people), [that they should do] the work of ministering toward building up Christ's body (the church)”:: ከሁለቱም ትርጎሞች የምንረዳው ዋና ነገር፣ የክርስቶስ አካል ይገነባ ዘንድ ወይም ሊገነባ እንዲችል ወይም እንዲታነጽ ቅዱሳን ለአገልግሎት ሥራ መዘጋጀት ወይም መታጠቅ አለባቸው:: ምክንያቱም አካሉ የሚገነባውና የሚታነጸው በቅዱሳን (በብልቶቹ ሁሉ) ስለሆነ ነው:: “ከእርሱም የተነሣ፣ አካል ሁሉ በሚያገናኘው ጅማት እየተያያዘና እየተጋጠመ፣ እያንዳንዱ ክፍል የራሱን ሥራ እያከናወነ በፍቅር ያድጋል፣ ራሱንም ያንጻል::” ኤፌ 4፣16 (አ.መ.ት):: ይህም ማለት አካል የሚታነጸውና የሚገነባው፣ እያንዳንዱ ብልት የራሱን ሥራ በማከናወን፣ በራሱ በብልቶቹ ነው “ራሱንም ያንጻል”:: የአምስቱ ስጦታዎች ሥራ እንግዲህ ቅዱሳን (ብልቶቹ) ይሄንን አካሉን የማነጽና የመገንባትን ሥራ ማድረግ ይችሉ ዘንድ፣ እነርሱን ለሥራው ማዘጋጀትና ማስታጠቅ ነው:: ስለዚህ ቅደም ተከተሉ እንደሚከተለው ነው:- አምስቱ ስጦታዎች ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ያዘጋጃሉ (ያስታጥቃሉ)፣ ቅዱሳን ደግሞ አካሉን ይገነባሉ::

 

ስለዚህ አምስቱ ስጦታዎች፣ አካሉን የመገንባት ሥራን ከቅዱሳን እንዲነጥቁና ቅዱሳንን ሥራ ፈት ወይም passive እንዲያደርጉ የተሰጡ ሳይሆኑ፣ ይልቁንም ቅዱሳን አካሉን የማነጽ ሥራን እንዲሠሩ ቅዱሳንን የሚያዘጋጁ፣ የሚያስታጥቁና የሚያበቁ ናቸው:: የአዲስ ኪዳን አገልግሎት ከብሉይ ኪዳን እጅግ የተለየ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ይሄ ነው:: የአዲስ ኪዳን አገልግሎት፣ እንደ ብሉይ ኪዳን ለዚያ ነገር ለተለዩና ለተሾሙ ለካህናትና ለሌላዋውያን ብቻ የተሰጠ ነገር አይደለም:: ሕዝቡም እንደ ብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር አገልጋዮች እና ሌላው ሕዝብ ተብሎ በሁለት መደብ የተከፈለ አይደለም:: በአዲስ ኪዳን ያለው የአካል ብልቶች አገልግሎትና ተግባር ነው:: ይህ እያንዳንዱ ብልት ጌታ ያሰበለትን ተግባር ይፈጽም ዘንድ፣ ለዚያ ማብቃት ነው እንግዲህ የአምስቱ ስጦታዎች ዓላማ:: በተቃራኒው እስኪሞቱ ድረስ አካሉ በእነርሱ ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ ማድረግ ግን የአምስቱ ስጦታዎች ዓላማና ግብ አይደለም::

 

በአሁኑ ዘመን የሚታየው የቤተክርስቲያን አሠራርና አወቃቀር፣ ከአዲስ ኪዳኑ ይልቅ ለብሉይ ኪዳኑ የቀረበ ነው:: ምክንያቱም ብዙ ጊዜ አካሉን የማነጽ ሥራ ሲሠሩ የሚታዩት እንደ ብሉይ ኪዳን አይነት ለሥራው የተሾመ አንድ ካህን/ቄስ/ፓስተር እና ከአካሉ እጅግ ጥቂቱ ክፍል ብቻ ናቸው:: በተለይ በአጥቢያ ቤተክርስቲያን የምዕመኑ ቁጥር ሲጨምር፣ አካሉን የማነጽ ሥራን የሚሠሩ የአካሉ ብልቶች ከ20% እንደማይበልጥ ይህንን በተለያዩ ቦታዎች ያጠኑ ይናገራሉ:: የተቀሩት አማኞች፣ ፕሮግራም መጥተው እድሜ ልካቸውን የቄሱን/የካህኑን/የፓስተሩን ስብከት ከመስማት ውጭ፣ እውነተኛ ተግባራቸውን አያከናውኑም:: ይህ ከአዲስ ኪዳን ይልቅ ለብሉይ ኪዳን የቀረበ አሠራር ነው::

 

እዚህ ላይ የአካሉ እያንዳንዱ ብልት ጌታ ያሰበለትን ሥራ መሥራት ይችል ዘንድ፣ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ማስታጠቅ ሲባል፣ በአንድ አጥቢያ የሚገኙትን አማኞች ሁሉ በተለያዩ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ክፍሎች መደልደል ማለት ግን አይደለም:: እዚህ ላይ የምንነጋገረው ከውጪ ወደ አማኞች ስለሚደረግ የአገልግሎት ድልደላ ወይም በየአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ ስለሚደረግ ምደባ ሳይሆን፣ በኤፌ 4፣7 መሠረት እያንዳንዱ ብልት ጌታ በሰጠውና በውስጡ ጌታ ባስቀመጠው ጸጋ አካሉን ማነጽ ይችል ዘንድ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ማዘጋጀት ማለታችን ነው::

 

ስለዚህ የአምስቱ ስጦታዎች ዋና ዓላማ፣ እንደ ብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔርን ሥራ ለሕዝቡ የሚሠሩለት ሰዎች መሆን እና ሕዝቡንም እድሜ ልክ የእነርሱን ስብከት ሰሚ ማድረግ ሳይሆን፣ ቅዱሳን የአካሉ ገንቢዎች እንዲሆኑ እነርሱን ለአገልግሎት ሥራ ማዘጋጀትና ማስታጠቅ ነው:: ቅዱሳን ከተገልጋይነት ወጥተው ራሳቸው በሚገባ ሥራቸውን ወደ መሥራት ደረሱ ማለት፣ የአምስቱ ስጦታዎች ግብ ተሳካ ማለት ነው:: ስልልስ ስለዚህ አምስቱ ስጦታዎች ለተወሰነ ሕዝብ የሚያደርጉት አገልግሎታቸውና የሕዝቡም በእነርሱ ላይ ያለው ጥገኝነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እንጂ እየጨመረ መሄድ የለበትም:: በእነ ጳውሎስ፣ በእነ ጢሞቴዎስ፣ በእነ ሲላስ ወዘተ የምናየውም ይሄንኑ ነው:: አንድ ቦታ ተተክለው እድሜ ልካቸውን ቄስ/ካህን/ፓስተር በመሆን፣ ሁል ጊዜ እሁድ እሁድ ሊሰብኳቸው ይችሉ ነበር:: እነርሱ ግን የአዲስ ኪዳን እንጂ የብሉይ ኪዳን አገልጋዮች ስላይደሉ፣ አላማቸውም ሕዝቡ ራሱ ሊሠራው የሚገባውን አካሉን የመገንባትን ሥራ ከሕዝቡ መንጠቅ ስላልነበረ፣ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ አብቅተው፣ ሥራውን እንዲሠሩ ትተዋቸው ነበር የሚሄዱት::

 

ስለዚህ የአምስቱ ስጦታዎች ስኬታማነት ዋና መለኪያ፣ ብልቶች ምን ያህል ጌታ ያሰበላቸውን ሥራና ተግባር እንዲያከናውኑ አድርገዋቸዋል የሚል ነው:: ጳውሎስ የተከላቸው አብያተ ክርስቲያናት፣ ጳውሎስ ከመካከላቸው ከሄደም በኋላ ያለ ጳውሎስ ይሰበሰቡ ነበር፣ ያለ ጳውሎስ እርስ በርስ ይተናነጹ ነበር፣ ያለ ጳውሎስ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን ይለማመዱ ነበር፣ ያለ ጳውሎስ የጌታን እራት ያደርጉ ነበር፣ ያለ ጳውሎስ ወንጌልንም ይሰብኩ ነበር:: ይህ የስኬታማ አገልግሎት አንዱ ምልክት ነው::

 

2ኛ) አምስቱ ስጦታዎች በአካሉ ላይ የሚያስገኙት ውጤት

አምስቱ ስጦታዎች ከላይ እንደጠቅስነው አካሉ ራሱን እንዲያንጽ ቅዱሳንን የማስታጠቅና ለአገልግሎት የማዘጋጀት ሥራቸውን በሚገባ ሲወጡ፣ ትልቁ የሚመጣው ውጤት የአካል እድገት ነው:: እውነተኛ እድገት ጥቂት አማኞችን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ብልቶችን ሁሉ የሚያቅፍ የአካል እድገት ነው:: የዚህ አይነቱ እድገት እንዲገኝ፣ እያንዳንዱ ብልት ጌታ ያሰበለትን ሥራ በመሥራት እርስ በርስ መተናነጽና መያያዝና ያስፈልገዋል:: “ከእርሱም የተነሣ፣ አካል ሁሉ በሚያገናኘው ጅማት እየተያያዘና እየተጋጠመእያንዳንዱ ክፍል የራሱን ሥራ እያከናወነ በፍቅር ያድጋል፣ ራሱንም ያንጻል::” ኤፌ 4፣16 (አ.መ.ት):: በዚህ ክፍል እንደተጠቀሰው የአካሉ አስተዳደግ እርስ በርስ በመያያዝ/በመገጣጠምና እያንዳንዱ ክፍል/ብልት የራሱን ሥራ በማከናወን ነው::

 

old structure

 

 

old structure

 

 


እንደዚህ አምስቱ ስጦታዎች ትክክለኛ ተግባራቸውን ሲያከናውኑና አዲስ ኪዳናዊ የአካል ብልቶች ሁሉ ክንዋኔ (function) ሲኖር፣ አካሉ በሚከተሉት አቅጣጫ ያድጋል:-

 

·       የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት:- “ይህም የሚሆነው፣ ሁላችንም የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት በመምጣትና...” ቁ. 13 (አ.መ.ት):: በኤፌ 4፣3 ላይ የተገለጠው የመንፈስ አንድነት ቀድሞውንም የተመሠረተና ያለ፣ ሁላችን በጌታ ስለሆንን ብቻ የሚገኝ አንድነት ነው:: እዚህ ላይ የተገለጸው አንድነት ግን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ የሚገኝ አንድነት ነው:: ይህ አንድነት በጌታ ላይ ያለን እምነትና የማንነቱ እውቀት እያደገ ሲመጣ የሚገኝ አንድነት ነው:: እያንዳንዱ ብልት ከጌታ ጋር ያለው ግንኙነት እየጠበቀና እያደገ ሲመጣ፣ እርስ በርስም ያለው እውነተኛ መጣበቅና መቀራረብ ይጨምራል:: በተቃራኒው ደግሞ እያንዳንዳችን ከጌታ በራቅን ቁጥር፣ ያለን የእርሱ ማንነት እውቀታችንና በእርሱ ላይ ያለን መታመን እየቀነሰ ስለሚሄድ፣ ሁላችንም ወደየራሳችን እውቀትና ማስተዋል ስለምንመለስ እውነተኛ አንድነትና ሕብረት ለማድረግ ይከብደናል:: ስለዚህ እውነተኛ የሆነ የአካል አገልግሎት፣ በይበልጥ ክርስቶስን እንድናውቅ ስለሚረዳንና አስተሳሰባችንንም ከግል ሎጂክ ወደ እርሱ ሃሳብ ስለሚያስገባን፣ እርስ በርስ ለመቀራረብና በአንድ አላማ ለመተሳሰር ያስችለናል:: እዚህ ላይ እንግዲህ አብረን ልብ ማለት ያለብን፣ ጳውሎስ ይሄን የአንድነት ሃሳብ ከኤፌ 4፣1 ጀምሮ ሲያብራራ ቆይቶ፣ ከቁ. 4-6 ደግሞ ሰባቱን የአንድነት መሠረቶቻችንን ከገለጸ በኋላ፣ በስምንተኛ ደረጃ የገለጸው የአገልግሎት ጸጋችንን ነው:: በጥናት 12 ላይም እንደተመለከትነው፣ እነዚህ ሰባቱ የአንድነታችን መሠረቶች፣ ለሁላችንም እኩል የሆኑና ሁላችንም በእኩል ደረጃ የምንካፈላቸው ሲሆኑ ስምንተኛ የሆነው የአገልግሎት ጸጋ ከሰባቱ የሚለይበት አንዱ ባሕርይ ደግሞ ለሁላችን በጅምላና በእኩል ደረጃ የሚሰጠን ሳይሆን ለእያንዳንዳችን በግል እንደሚሰጥ ተመልክተናል “ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን::” ኤፌ 4፣7:: ምንም እንኳን የተለያየ የአገልግሎት ጸጋ ለእያንዳንዳችን ቢሰጠንም፣ በዚህ ክፍል በጠቀስነው በቁ. 13 ላይ የምንመለከተው ግን ያሄው የተለያየ ተደርጎ የተሰጠን ስጦታ፣ እርስ በርስ እንድንተናነጽበትና የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት እንድንመጣበት ነው እንጂ እንድንለያይበት አይደለም:: ስለዚህ አገልግሎት አካሉ እርስ በርስ እንዲተሳሰሩና እንዲያያዙ ይረዳ ዘንድ ወደ በለጠ አንድነትና ሕብረት የሚያመጣ እንጂ ለመለያየት ታስቦ የተሰጠ አይደለም::

 

·       ከሕጻንነት ሙሉ ሰው ወደ መሆን:- “...ሙሉ ሰው በመሆን፣ በክርስቶስ ወዳለው ፍጹምነት ደረጃ እስከምንደርስ ነው:: ከእንግዲህ በማዕበል ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየተነዳን፣ በልዩ ልዩ ዓይነት የትምህርት ነፋስ፣ በሰዎችም ረቂቅ ተንኮልና ማታለል ወዲያና ወዲህ እየተንገዋለልን ሕጻናት አንሆንም::” ኤፌ 4፣13-14 (አ.መ.ት):: የሕጻንነት አንዱ ምልክት በቀላሉ መታለል ነው:: በቀላሉ የሚታለሉትም ካለመብሰልና ካለማወቅ የተነሣ ነው:: እውነተኛ የሆነ የሁሉም ብልቶች ክንውን (function) ሲኖር በሰው ሎጂክ ሳይሆን በሐዋርያት ትምህርት ላይ የተመሠረተ ክርስትና ስለሚኖረን፣ መልካም በሚመስል ነገር ሰዎች ለራሳቸው ጥቅም በተንኮል በሚያመጡት የትምህርት ንፋስ ሁሉ አንወሰድም:: በቀደሙት ዘመናት በአሜሪካ አገር እውነተኛውን ዶላር ከሃሰተኛው የመለየት ሥራ የነበራቸው ሰዎች በባንክ ይሠሩ እንደነበር ይነገራል:: ሃሰተኛውን ዶላር ከሕጋዊው ለመለየት የሚጠቀሙበት ዋና ዘዴ፣ የትክክለኛውን ዶላር ባህርያትና መልክ፣ በላዩም ላይ ያለውን እያንዳንዷን ሕትመት ሁሉ በጥንቃቄ ማጥናት ነበር:: ኦርጂናሉንና ሕጋዊውን ዶላር አጥርተው ስለሚያውቁ፣ ከሕጋዊው ዶላር ጥቂት ለየት ያለ ነገር ያለው ሃሰተኛ ዶላር ሲያገኙ፣ ወዲያው ለማወቅ ይችሉ ነበር:: ክርስትናም እንዲሁ ነው፣ የአካል ብልቶች በእውነተኛና በኦርጂናሉ የሐዋርያት ትምህርት ላይ ከተመሠረቱና በጥናቃቄም በዛ ላይ ከታነጹ፣ ከዚያ ትንሽም እንኳን ዘነፍ ያለ ትምህርት ሲመጣ ወዲያው ሊለዩ ይችላሉ:: እውነተኛ የአካል አገልግሎት ከሕጻንነት፣ የበሰለ ሙሉ ሰው ወደ መሆን፣ በክርስቶስ እንዳለ ፍጹም ብስለት ደረጃ እንድንደርስ የሚያግዝ ነው::

 

·       በእውነትና በፍቅር ማደግ:- “ይልቁን እውነትን በፍቅር እየተናገርን” ቁ. 15:: በእውነተኛው የሐዋርያት ትምህርት እየተመሠረትንና እየታነጽን ስንሄድ፣ እውነትን በይበልጥ እያወቅንና እየያዝን እንሄዳለን:: እውነት ሲታወቅ ደግሞ ከብዙ የውሸት እሥራት፣ የባህልና የሃይማኖት ትብታብ ሁሉ አርነት የሚያወጣ እጅግ የሚያስገርም ኃይል ነው:: “ኢየሱስም ያመኑትን አይሁድ:- እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው::” ዮሐ 8፣31:: ጌታ ላመኑት አይሁድ እንዳላቸው እውነትን ለማወቅና በይበልጥ ለመረዳት ቃሉን ማወቅና በቃሉ ደግሞ መኖር ያስፈልጋል:: ያለ እግዚአብሔር ቃል እውነት ሊታወቅ አይችልም:: እውነት የሰው ሎጂክና ባሕል ውጤት ሳይሆን ራሱ ጌታ ኢየሱስ ነውና ዮሐ 14፣6:: በቃሉና በመንፈሱ ከተመሠረተ የእግዚአብሔር ልጅ እውቀት ውጪ እውነት የሚባል ነገር የለም:: ስለዚህ በኦርጂናሉ የሐዋርያት ትምህርትና በእግዚአብሔር ቃል መመሥረት፣ እውነትን ለማወቅ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፣ በተቃራኒው ደግሞ ከእግዚአብሔር ቃልና ከሐዋርያቱ ትምህርት ይልቅ የሰዎችን ሎጂክና ባሕል ማስተናገድ እውነትን ላለመያዝና ለመሳት አውራ ጎዳና ነው:: እውነት የሰውን ሕይወት እጅግ የሚነካ ስለሆነ በፍቅር ከተያዘ የሕይወትን አቅጣጫ የሚያስቀይር ኃይል አለው:: ያለ ፍቅር ብቻውን ግን ሊሠራና ፍሬያማ ሊሆን ግን አይችልም:: ፍቅርም በእውነት ላይ ካልተመሠረተ ግብዝነት ብቻ ነው:: ስለዚህ እውነተኛ እድገት ሁለቱንም ያቀፈ ነው:: ከእውነትም ዘነፍ አይልም፣ ነገርን ሁሉ ግን በፍቅር ያደርጋል::

 

·  ክርስቶስን ማዕከላዊ ያደረገ እድገት:- “ይልቁንም እውነትን በፍቅር እየተናገርን፣ ራስ ወደ ሆነው ወደ እርሱ በነገር ሁሉ እናድጋለን፣ እርሱም ክርስቶስ ነውከእርሱም የተነሣ፣ አካል ሁሉ በሚያገናኘው ጅማት እየተያያዘና እየተጋጠመ፣ እያንዳንዱ ክፍል የራሱን ሥራ እያከናወነ በፍቅር ያድጋል፣ ራሱንም ያንጻል::” ኤፌ 4፣15-16 (አ.መ.ት):: በዚህ ክፍል ከአካሉ ፊት ለፊት ያለ የእድገት አቅጣጫ ተገልጾአል፣ እርሱም ክርስቶስ ነው:: ትክክለኛ የአካል እድገት፣ አካሉ ፊት ለፊቱ ክርስቶስን እያየ እርሱን ለመምሰል የሚያደርገው እድገት ነው:: በእውነተኛ እድገት፣ አካሉ ሌላ ምድራዊ ተቋማትንና ድርጅቶችን እየመሰለ ሳይሆን የሚሄደው ክርስቶስን ምሳሌ እያደረገ፣ የክርስቶስም ባሕርይ በአካሉ እያንጸባረቀ ነው የሚያድገው:: “ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኩር ይሆን ዘንድ፣ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወስኖአልና”ሮሜ 8፣29:: እውነተኛ የአካል እድገት ክርስቶስን ከፊት ለፊት እያደረገ የሚያድግ ብቻ ሳይሆን፣ እድገቱንም ከኋላ የሚገፋውና የእያንዳንዱን ብልት ተግባር ወሳኝ ክርስቶስ ነው:: “ከእርሱም የተነሣ፣ አካል ሁሉ በሚያገናኘው ጅማት እየተያያዘና እየተጋጠመ፣ እያንዳንዱ ክፍል የራሱን ሥራ እያከናወነ በፍቅር ያድጋል፣ ራሱንም ያንጻል::” ቁ.16:: የአካል ብልት አስተዳደግን ስናስብ፣ አንድ መርሳት የሌለብን ነገር ለቤተክርስቲያን ደሙን ያፈሰሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ እንዳልቀረ ነው:: ጌታ ሙታን አይደለም! ኢየሱስ ተነስቶአል! ስለዚህ የአካሉን ብልቶች የሚያገጣጥምና የሚያያይዝ የሚያሳድግም እርሱ ነው:: እርሱ አሁንም የአካሉ ራስና አለቃ ነው:: እርሱ “...በዚችም ዓለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ...” (ማቴ 16፣18) አለ እንጂ፣ ቤተክርስቲያኔን ወይም ቤተክርስቲያናችሁን እናንተ ትሠራላችሁ አላለም:: የአካል ሕይወት እድገት ዋና አንቀሳቃሽና ሠራተኛ ጌታ ነው:: እኛ ጌታ ቤተክርስቲያኑን ሲሠራ አብረን የምናግዝ የአካል ብልቶች ብቻ ነን:: እኛ ብቻ የምንሠራው ቤተክርስቲያን ሕያው አካል በፍጹም ሊሆን አይችልም፣ ሃማኖታዊ ድርጅትም ከመሆን አያልፍም:: በአዲስ ኪዳን ያለው ክርስቶስና አካል የሚባል አገልግሎት ነው:: አካል ሕይወት ያለው ሕያው ነገር ነው:: ስለዚህ ያለ ሕይወት ሰጪ ጌታ ሊታነጽ አይችልም:: ክርስቶስ በአካሉ ያለውን ማዕከላዊ ቦታ ካህናት/ቄሶች/ፓስተሮች ወዘተ ሊተኩ አይችሉም:: እካሉንም የማያያዝና የማሣደግ ዋና ሥራ ከክርስቶስ እጅ ተነጥቆ ለእነርሱ ሊሰጥ አይገባውም:: ይሄ በተደረገበት ቦታ ሁሉ፣ በሕያው አካል ፋንታ የሙታን ሃይማኖታዊ ድርጅት ይተካል:: ጳውሎስም ቤተክርስቲያን በተከለበት ቦታ ሁሉ አካሉንና ጌታን ነው አገናኝቶ የሚሄደው እንጂ የጌታን ቦታ ለአንድ ካህን/ቄስ/ፓስተር አያስረክብም ነበር:: ይህ ለአካሉ እድገትና ሕያው ሆኖ ለመኖር ወሳኝ ነውና:: “አሁንም ለእግዚአብሔርና ያንጻችሁ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ መካከል ርስትን ይሰጣችሁ ዘንድ ለሚችል ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ::” የሐዋ 20፣32::  ኢየሱስ ሕያው ነውና፣ ሞቶ እንደቀረና እንደሌለ አድረገን እንዳንመላለስ ጌታ ይርዳን::


“ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ።“
(መጽሐፈ ምሳሌ 3:3-4)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us