ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች » ኤፌሶን » ጥናት 16 (ኤፌሶን 4፣17-32 ሀ) ከአሕዛብ የተለየ አካሄድ - ክፍል 1
Email this page to a friend Printer-friendly   Tuesday, 20 October 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦“
(የዮሐንስ ራእይ 3:14)

rss

Today's verse

ጥናት 16 (ኤፌሶን 4፣17-32 ሀ) ከአሕዛብ የተለየ አካሄድ - ክፍል 1

pdf version

ይህን “ከአሕዛብ የተለየ አካሄድ” ያልነውን ጥናት ለሁለት ከፍለን እናጠናዋለን:: በዚህ በክፍል አንድ ጥናታችን ላይ ኤፌ 4፣17-24 ያለውን የምንመለከት ሲሆን፣ በሚቀጥለው በክፍል ሁለት ጥናታችን ደግሞ ኤፌ 4፣25-32 ያለውን ክፍል እንመለከታለን::

 

ክፍል 1 (ኤፌ 4፣17-24)

 

በብሉይ ኪዳንም ይሁን በአዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር ፈቃድ ሕዝቡ ከአሕዛብ በተለየ ሁኔታ እንዲመላለስ/እንዲኖር ነው:: የእግዚአብሔር ሕዝብ ከአሕዛብ የተለየ አኗኗር መኖር ስለሚገባው፣ ጳውሎስም በዚህ ክፍል የኤፌሶን ሰዎች ልክ እንደ አሕዛብ እንዳይመላለሱ/እንዳይኖሩ አጥብቆ ያሳስባቸዋል:: “...በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ::” ቁ. 17:: ይሄ “እመሰክራለሁ” ተብሎ በአማርኛ የተተረጎመው ቃል to conjure (አበክሮ መለመን/መጠየቅ), beseech as in God's name (በእግዚአብሔር ስም በአስቸኳይ ሁኔታ አጥብቆ መጠየቅ), exhort solemnly (አበክሮ መምከር/ማሳሰብ) ማለት ነው:: ስለዚህ ጳውሎስ የጌታን ስም በመጥራት በጣም አስቸኳይ በሆነ ሁኔታ የኤፌሶን ሰዎች ከአሕዛብ የተለየ አኗኗር እንዲኖሩ አጥብቆ ያሳስባቸዋል:: በዚህ ክፍል አሕዛብ የሚለው ቃል ያላመኑትን አሕዛብ የሚያመለክት ነው 1ቆሮ 10፣32::

 

ሀ)አሕዛብ ያሉበት ሁኔታ ቁ. 17-19

በዚህ ክፍል ጳውሎስ አማኞች እንደ አሕዛብ እንዳይመላለሱ ወይም የአሕዛብን አኗኗር እንደ ምሳሌ አድርገው ለራሳቸው ሕይወት እንዳይወስዱ የሚያስጠነቅቅበትንና የሚያሳስብበትን ምክንያት መሠረት የሚያደርገው በአሕዛብ ውስጣዊ የሕይወት በሽታና ችግር ነው:: አንድ ሐኪም በሽተኛን መርምሮ የምርመራውን ውጤት እንደሚናገር፣ ጳውሎስም በአሕዛብ ሕይወት ላይ የሚታዩትን ችግሮችና በሽታዎች እንደሚከተለው ይዘረዝራቸዋል::

 

·       የአእምሮአቸው ወይም የአስተሳሰባቸው መበላሸት

ሰው ኃጢአትን ጸንቶ በተለማመደ ቁጥር አእምሮው እየተበላሸና ትክክለኛ ሚዛኑን እያጣ እንደሚሄድ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል ሮሜ 1፣20-23:: በዚህም ክፍል የምንመለከተው የአሕዛብ ዋና ችግር የአእምሮ መበላሸት ነው:: በቁ. 17 “በአእምሮአቸው ከንቱነት” የሚለው ቃል vanity (what is devoid of truth and appropriateness) of the mind ማለት ሲሆን በአማርኛ ደግሞ እውነት ወይም ትክክለኛና ተገቢው ነገር የሌለው አእምሮ ማለት ነው:: ወይም በሌላ አነጋገር ከእውነትና ከትክክለኛ ነገር ነጻ የሆነ ወይም እውነትና ትክክለኛው ነገር የማይገኝበት አእምሮ ማለት ነው:: አሕዛብ እንግዲህ ያለ ምንም የህሊና ወቀሳ መልካም ያልሆነውን ሁሉ እያደረጉ የሚኖሩበት አንዱ ምክንያት እውነትና ተገቢው ነገር በአእምሮአቸው ውስጥ ስለሌለ ነው:: ክፉውን ነገር አእምሮአቸው ክፉ ብሎ ስለማይቆጥረውና የትክክለኛ ነገር ሚዛናቸው ስለተበላሸ ነው::

 

ከዚሁ ጋር ተያይዞ አሕዛብ የእውቀትም ችግር እንዳለባቸው በዚህ ክፍል ተጠቅሷል “እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ...” ቁ. 18:: ይሄ “አለማወቅ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል በእንግሊዝኛው ignorance የሚለው ቃል ነው:: ይህም በአሕዛብ ዘንድ ስላለ የክፋ አላዋቂነት ያመለክታል:: ምንም እንኳን አሕዛብ ራሳቸውን እንደ አዋቂና ጥበበኛ ቢቆጥሩም የእግዚአብሔር ቃል ግን፣ በአሕዛብ ዘንድ ስላለ አላዋቂነትና ስለ ጥበባቸውም ከንቱነት ነው የሚነገረን:: “ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ” ሮሜ 1፣22 1ቆሮ 1፣18-31::

 

አእምሮን በተመለከተ ሌላው የአሕዛብ ችግር የልቦና መጨለም ነው:: “ልቡናቸው ጨለመ...” ቁ. 18:: ይሄንን ክፍል የእንግሊዝኛው ኢንተርሊኒየር መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ይተረጉመዋል:- having been darkened in the intellect ማለትም የማሰብ ችሎታቸው ወይም ማስተዋላቸው ጨለመ ማለት ነው:: “...እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ::” ሮሜ 1፣20-21:: የአስተሳሰብ ችሎታው ወይም ማስተዋሉ የመጨለ ሰው በብርሃን እንዳለ ሰው ሁሉን ነገር በግልጽ ለማመዛዘን አይችልም:: በጨለማ ያለ ሰው ሁሉንም ነገር አጥርቶ ማየት እንደማይችል፣ እንዲሁ አስተሳሰቡ ወይም ልቡናው የጨለመ ሰውም ነገሮችን በትክክለኛውና በተገቢው መንገድ መረዳትና ማመዛዘን አይችልም::

 

በአጠቃላይ አሕዛብ አእምሮን፣ እውቀትንና አስተሳሰብን በተመለከተ በእግዚአብሔር አይን ከፍተኛ ችግር እንዳለባቸው ይህ ክፍል ያሳያል::

 

·       የልባቸው መደንደን

ሌላው የአሕዛብ ችግር የልባቸው መደንደን ነው:: “...በልባቸውም ደንዳንነት ጠንቅ” ቁ. 18:: መደንደን ጥንቃሬን ነው የሚያሳየው:: የሰው ልብ ሲደነድን፣ ያ ሰው በሚያደርገው የተሳሳተ ነገር ወይም በሚሄድበት የተሳሳተ መንገድ ላይ ጸንቶ እንዲቀጥልበትና ያለ ፍርሃት እንዲገፋበት ያደርገዋል:: የልብ መደንደን ምክርን፣ እርማትንና ማስጠንቀቂያን ሁሉ ላለማዳመጥ ሰዎች ጆሮዎቻቸውን እንዲዘጉ የሚያደርግ በጥፋት መንገድ ሰውን የሚያጸና ክፉ በሽታ ነው:: በአብዛኛው አሕዛብ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ነገር እንዳይሰሙና እንዳያስተውሉ የሚገኙበትንም አደገኛ መንገድ እንዳይመለከቱና በዚያው እንዲጸኑ የሚያደርጋቸው አንዱ በሽታ የልባቸው መደንደን ነው::

 

·       ከእግዚአብሔር ሕይወት መራቃቸው

ሌላው በአሕዛብ ሕይወት የሚታየው ትልቅና ዋና ችግር፣ ከእግዚአብሔር ሕይወት መራቅ ነው:: “ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ” ቁ. 18:: ይህ “ራቁ” ተብሎ በአማርኛ የተተረጎመውን ቃል የግሪኩ ሌክሲከን እንደሚከተለው ይተረጉመዋል:- alienate, estrange, to be rendered an alien, to be shut out from one's fellowship and intimacy ማለትም አሕዛብ ለእግዚአብሔር ሕይወት ባዕዳን፣ ጨርሶ ቅርበትና ሕብረት የሌላቸው እና ከእግዚአብሔር ፈጽመው እጅግ የራቁ እንደሆኑ የሚያሳይ ነው:: ስለዚህም አስተሳሰባቸውና አኗኗራቸው ከእግዚአብሔር ሃሳብና ቃል ጋር የማይጣጣም፣ የማይቀራረብና የማይገጥም ነው:: የእግዚአብሔርም ሃሳብና ቃል ለእነርሱ እጅግ የተለየና ጨርሶ ባዕድ ነው:: ይህ እንግዲህ በእግዚአብሔር ያለው ሕይወትና አሕዛብ ምን ያህል እርስ በርስ እንደተራራቁና እርስ በርስ ባዕዳን እንደሆኑ ያሳያል::

 

·       መደንዘዛቸው

ጳውሎስ የአሕዛብን ሕይወት መንፈሳዊ የምርመራ ውጤት ዝርዝሩን በመቀጠል፣ ስለ መንፈሳዊ የስሜት ሕዋሶቻቸው ሲናገር “ደንዝዘውም” ቁ. 18 የሚለውን ቃል ነው የሚጠቀመው:: ይህ ቃል በግሪኩ የሚከተሉት ትርጉሞች አሉት to cease to feel pain or grief (ሕመም ወይም ስቃይ ምንም ሳይሰማ ሲቀር), to bear troubles with greater equanimity (በጸጥታ ያለ ምንም መናወጥ ችግሮችን መሸከም), cease to feel pain at (የሕመም ስሜት መሰማት ማቆም), to become callous (እንደ አዞ ቆዳ ምንም ዓይነት ስሜት የማይሰማው ወይም ግድ የማይለው), insensible to pain (የሕመም ስሜት የማይሰማው), apathetic (ግድየሌሽነት):: በዚህ ክፍል መደንዘዝ የሚለው ቃል፣ ልክ በሐኪም ቤት አንድ ሰው ቀዶ ጥገና ከማግኘቱ በፊት ሕመም እንዳይሰማው በማደንዘዣ የስሜት ሕዋሳቶቹ እንደሚደነዝዙ አይነት የሆነ መንፈሳዊ መደንዘዝ ነው:: ሰው መንፈሳዊ ሕይወቱና ሕሊናው ከደነዘዘ የሚኖርበት የኃጢአት ኑሮና በእግዚአብሔር ፊትም ያለውን አጸያፊነት ሁሉ ለመገንዘብ አይችልም:: የደነዘዘ ሕሊና ካለው ክፉውና ቆሻሻው ነገር ጨርሶ አያጸይፈውም:: ሕሊና ኃጢያትን በተደጋጋሚ ከመለማመድ የተነሳ የሚደነዝዝ መንፈሳዊ የአካል ክፍል ነው:: አሕዛብም እንግዲህ የፈለገው አይነት ኃጢያት አጸያፊነቱና ቆሻሻነቱ የማይሰማቸው ቆሻሻነቱን የሚያሳውቀው መንፈሳዊ የስሜት ሕዋሶቻቸው ከመደንዘዛቸው የተነሳ ነው::

 

·       ለምኞት፣ ለርኩሰትና ለሴሰኝነት ራሳቸውን አሳልፈው መስጠታቸው

ከላይ ከተጥቀሱት የመንፈሳዊ ሕይወት በሽታዎችና ችግሮች የተነሳ እንግዲህ አሕዛብ ለምኞት፣ ለርኩሰትና ለሴሰኝነት ራሳቸውን አሳልፈው እንደሰጡ ጳውሎስ በዚህ ክፍል ይገልጻል:: “እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ በልባቸውም ደንዳንነት ጠንቅ ልቡናቸው ጨለመ፣ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ ደንዝዘውም በመመኘት ርኩሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ::” ቁ. 19:: በዚህ ክፍል መመኘት ተብሎ በአማርኛ የተተረጎመው ቃል በግሪኩ ኃይለኛ የሆነ ገንዘብንና ቁሳዊ ነግሮች የማግኘት ስግብግብነትንና ምኞትን የሚያመለክት ነው:: እንዲያውም ይሄው ቃል በሉቃስ 12፣15 ላይ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ሁኔታ “መጎምዠት” ተብሎ ተተርጉሞአል:: በዚህ ክፍል ርኩሰት የሚለው ቃል ደግሞ መንፈሳዊ ንጽሕና ማጣትንና መንፈሳዊ መቆሸሽን (uncleannes/ impurity) የሚያሳይ ሲሆን፣ “ሴሰኝነት” ተብሎ በአማርኛ የተተረጎመው ቃል ደግሞ unbridled sensuality [give up to, the pleasures of the senses; self-indulgent in regard to food and drink and sexual enjoyment], lust ወይም በአማርኛ ከቅጥ ባለፈ፣ መረን በለቀቀና ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ ሥጋዊ ስሜቶችን ለማሟላት ራስን መስጠት ማለት ነው:: ይህ አሕዛብ ለስግብግብነት ወይም ለመጎምዠት፣ ቆሻሻ ለሆነ ሕይወትና ሥጋዊ ስሜቶቻቸውን ሁሉ ያለ ገደብ ለማሟላት ራሳቸውን እንዴት አሳልፈው እንደሰጡ ያሳየናል:: ይህም የሆነበት ምክንያት ከላይ የተዘረዘሩት ሚዛን መጠበቂያና መቆጣጠሪያ መንፈሳዊ የአካል ክፍሎች ስለተበላሹ ነው::

 

ጳውሎስ እንግዲህ የኤፌሶን አማኞችን የሚያሳስበውና የሚያስጠነቅቀው፣ እንደዚህ ያሉ የአእምሮ ከንቱነት፣ አለማወቅ፣ የልቡናና የአስተሳሰብ መጨለም፣ የልብ ድንዳኔ፣ ለእግዚአብሔር ሕይወት ባዕድነትና መንፈሳዊ የስሜት ሕዋሶች መደንዘን ወዘተ... ያሉ በሽታዎች ያሉባቸውንና ከዚህም የተነሳ ለስግብግብ ምኞት፣ ለቆሻሻ ሕይወትና ልቅ ለሆነ ለሥጋ ፍላጎት ራሳቸውን የሰጡትን አሕዛብን ምሳሌ አድርጋችሁ እንደ እነርሱ እንዳትኖሩ ማለቱ ነው:: እንደዚህ ከባድ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ምሳሌ አድርጋቸሁ አትከተሉ ወይም የእነርሱን የአኗኗር ዘይቤ የእናንተ ምሳሌ አታድርጉት ማለቱ ነው::

 


 

ለ)አዲሱን ሰው ልበሱ ቁ. 20-24

በዚህ ክፍል ክርስቶስና የክርስቶስ ትምህርት ከአሕዛብ አስተሳሰብና አኗኗር እጅግ የተለየ እንደሆነ ጳውሎስ ይገልጻል:: “እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም በእርግጥ ሰምታችሁታልና፣ እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል” ቁ. 20-21:: ጳውሎስ በዚህ ክፍል የኤፌሶን ሰዎች ከክርስቶስ ጋር ትውውቅ እንዳላቸው፣ ከእርሱ እንደተማሩና እርሱንም እንደሰሙ ነው የሚጠቅሰው:: ምንም እንኳን በሥጋ ተገልጦ ክርስቶስ ባያስተምራቸውም ጌታን በወንጌል አማካኝነት በግል ተዋውቀውታል፣ እርሱም አስተምሯቸዋል:: ጳውሎስ “እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም” ሲል እንግዲህ በአንባቢዎቹ ላይ የሚያስነሳው ጥያቄ አለ:: ይሄውም እያንዳንዱ ምን አይነት ክርስቶስን እንደተዋወቀና እንደተማረ እንዲጠይቅ የሚያደርግ ነው:: ምን አይነት ክርስቶስ ነው የተዋወቅሁት? እንደ አሕዛብ አይነት ኑሮ መኖርን የማይቃወም ወይም ይባስ ብሎ የሚደግፍ ክርስቶስ ነው ወይስ በአሕዛብ አይነት ኑሮ የማይደሰትና የሚጠላው? በተጨማሪ ጳውሎስ “በእርግጥ ሰምታችሁታልና፣ እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል” ሲልም እንዲሁ በአንባቢዎቹ ዘንድ የሚፈጥረው ጥያቄ አለ:: ይሄውም አንደኛ በእርግጥ ክርስቶስን ሰምቼዋለሁ ወይ? ከእርሱስ ተምሬአለሁ ወይ? ያስተማረኝስ ምንድነው? ስለ አሕዛብ አይነት ኑሮስ ምን ብሎ ነው ያስተማረኝ? እንግዲህ የኤፌሶን ሰዎች ክርስቶስን የሚያውቁና ከእርሱም የተማሩ ከሆኑ የአሕዛብ አይነትን ኑሮ አማኞች እንዲኖሩ ጌታ እንደማይፈልግ በእርግጥ ያውቃሉ:: እውነቱም በክርስቶስ ያለው እንጂ በአሕዛብ አእምሮ የሚለካ እንዳልሆነው ያምናሉ ማለት ነው::

 

እንግዲህ የክርስቶስ ትምህርት እንደ አሕዛብ መኖር የሚል ሳይሆን አሮጌውን ሰው ማስወገድና አዲሱን ሰው መልበስ የሚል ነው:: “ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ” ቁ. 22:: አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አ.መ.ት) ይህን ክፍል እንደሚከተለው ይተረጉመዋል “ቀድሞ ስለነበራችሁበት ሕይወትም፣ በሚያታልል ምኞቱ የጎደፈውን አሮጌ ሰውነታችሁን አውልቃችሁ እንድትጥሉ ተምራችኋል”:: ጳውሎስ በዚህ ክፍል እንግዲህ የቀድሞውን ሕይወት በተመለከተ የክርስቶስ ትምህርት ምን እንደሆነ ነው የሚገልጸው:: የቀድሞውን ባሕሪያችንንና አኗኗራችንን “በሚያታልል ምኞቱ ምክንያት የሚጠፋ አሮጌ ሰው” ብሎ ነው ጳውሎስ የሚጠራው:: ይሄ “የሚጠፋ” ወይም “የጎደፈ” ተብሎ በሁለቱ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱሶች በተለያየ ሁኔታ የተተረጎመው ቃል to destroy by means of corrupting, and so bringing into a worse state ወይም በአማርኛ:- አንድ ነገር ከመበላሸቱ የተነሣ ከጥቅም ውጭ መሆኑ ወይም መጥፎ ሁኔታ ላይ መገኘቱን የሚያመለክት ትርጉም ነው ያለው:: ስለዚህ አሮጌው ማንነታችን ከሚያታልል ምኞቱ ወይም አታላይ ከሆነ ምኞቱ የተነሣ መበላሸቱን፣ መጉደፉንና መጥፎ ሁኔታ ላይ ያለ መሆኑን ነው የሚያሳየን:: ልክ ልብስ ከመቆሸሹ፣ ከማርጀቱና በብልም ከመበላቱ የተነሣ ከጥቅም ውጭ ሆኖ እንደሚበላሽ፣ አሮጌውም ባሕሪያችን ወይም አሮጌው ሰው እንደማይሻሻል ሆኖ እንደተበላሸ ይህ ክፍል ያስረዳናል:: ይህንን ባሕርይ ልክ እንደተበላሸ ልብስ ገፋችሁ አስወግዱ ወይም አውልቁ ነው ጳውሎስ የሚለን::

 

በዚህ ክፍል ልብ ማለት ያለብን አንደኛ አሮጌ ሰው የሚለው ቃል ጌታን ከመከተላችን በፊት የነበረንን የቀድሞውን ባሕርይ የሚያመለክት እንጂ ልዩ የሆነን ምስጢራዊ ነገር የሚያመለክት አይደለም:: አዲሱ ሰውም ተብሎ የሚጠቀሰውም እንዲሁ በባሕርይ የሚታይ ክርስቶስን የመሰለ አዲሱን ሕይወታችንን የሚያመለክት ነው:: ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሁለቱ አይነት ሰዎች ሲናገር ለማስረገጥ የሚፈልገው በተለይ የባሕርይን ጉዳይ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልገናል:: በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ “አሮጌውን ሰው አስወግዱ” ብሎ ጳውሎስ ሲናገር በአለም ላይ ካሉት ማናቸውም ሰዎች ክርስቲያን ብቻ ይሄ ስልጣን እንዳለው በማወቅ ነው:: አሮጌ ባሕርይን ለማስወገድና የኃጢያትን ኃይል ተቋቁሞ እንቢ ለማለት የሚችል በምድር ላይ ክርስቲያን ብቻ ነው:: ምክንያቱም በክርስቶስ ሞት ምክንያት አሮጌው ሰው ስለተሰቀለና ከኃጢአት ኃይልና ሥልጣን ክርስቲያን ነጻ ስለ ወጣ ነው:: “ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፣ ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን...” ሮሜ 6፣5-6 “ኃጢአት አይገዛችሁምና ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና::” ሮሜ 6፣14 “ኢየሱስም መለሰ፣ እንዲህ ሲል:- እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባሪያ ነው:: ባሪያም ለዘላለም በቤት አይኖርም ልጁ ለዘላለም ይኖራል:: እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ::” ዮሐ 8፣34-36:: የክርስቶስ ትምህርት እንግዲህ እንደ አሕዛብ አይነት ኑሮ መኖር የሚል ሳይሆን ስለ አሮጌው ሰው መሰቀል፣ ከኃጢአት ኃይል ነጻ ስለ መውጣትና ስለ አርነት የሚያወራ ነው::

 

አሮጌውን ሰው ወይም ባሕርይ እንደ ልብስ ከማውለቅ ጋር አያይዞ ጳውሎስ የኤፌሶንን ሰዎች ሌሎች ሁለት ምክሮችን ይመክራቸዋል:: የመጀመሪያው ምክር በአእምሮአቸው መንፈስ እንዲታደሱ ነው:: “በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ” ቁ.23:: ይሄንን ስንኝ የAmplified መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ይተረጉመዋል:- And be constantly renewed in the spirit of your mind [having a fresh mental and spiritual attitude] ይህም ማለት በማያቋርጥ ሁኔታ ሁል ጊዜ የአስተሳሰብ፣ የመንፈሳዊ አቋምና አመለካከት እድሳት ማድረግ ማለት ነው:: መታደስ የሚለው ቃል አዲስ የሚለውን ቃል በውስጡ ያዘለ ነው:: አዲስ የሚለው ቃል ደግሞ አሮጌ ወይም ያረጀ ከሚለው ተቃራኒ ነው:: አንድ ነገር ሁል ጊዜ መታደስ ካለበት፣ የማርጀትና አሮጌ የመሆን አዝማሚያ አለው ማለት ነው:: አስተሳሰባችሁ፣ መንፈሳዊ አመለካከታችሁና አቋማችሁም ሁሉ ጊዜ ይታደስ ብሎ ጳውሎስ ሲናገር እንግዲህ አስተሳሰባችሁና መንፈሳዊ አመለካከታችሁ ከአሮጌው ሰው አመለካከትና አስተሳሰብ እየተለየ፣ የእግዚአብሔርን ቃልና የክርስቶስን ትምህርት አይነት አስተሳሰብ እየመሰለ ይምጣ ማለቱ ነው::

 

አስተሳሰብና መንፈሳዊ አመለካከት ሁል ጊዜ በእግዚአብሔር ቃል እያታደሰ ካልሄደ፣ የማርጀቱና የአሮጌውን ሰው አይነት የተበላሸ አስተሳሰብና አመለካከት የመያዙ አደጋ ከፍተኛ ነው:: ከላይ ስለ አሕዛብ በተመለከትነው ክፍል ደግሞ የአስተሳሰብ ወይም የአእምሮ መበላሸት ሰው ራሱን ለኃጢአት አሳልፎ እንዲሰጥ ዋና ምክንያት እንደሆነ አይተናል:: ስለዚህ የቀድሞውን አይነት አስተሳሰብ ይዞ አዲሱን ሕይወት መኖር ፈጽሞ አይቻልም:: አስተሳሰብ የአሕዛብ አይነት ከሆነ፣ ሕይወትም የእነርሱን ይመስላል:: “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ[በአእምሮአችሁ] መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ::” ሮሜ 12፣2:: የማያቋርጥ የአስተሳሰብና የመንፈሳዊ አመለካከት ለውጥ፣ አዲሱን ሕይወት ለመኖር እጅግ ወሳኝ ነገር ነው::

 

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሌላው ሁለተኛው ምክር ደግሞ አዲሱን ሰው እንዲለብሱ ነው:: “እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው እንድትለብሱ ነው::” ቁ.24 (አ.መ.ት):: በክርስቶስ ያገኘነው አዲስ ሕይወት ወይም አዲሱ ሰው የእግዚአብሔር አይነት ባሕርይ ያለውና በእውነተኛ ጽድቅና ቅድስና የተፈጠረ ነው:: ጽድቅና ቅድስና ከአዲሱ ሰው ጋር እንዲያው የሚሰጡ የእግዚአብሔር ስጦታዎች እንጂ እኛ የምንፈጥራቸው ነገሮች እንዳልሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል 1ቆሮ 1፣30-31:: በዚህ ክፍል እንግዲህ የጳውሎስ ምክሩ አንድ ነው:: ይሄውም አዲሱ ሰው እውነተኛ ቅድስናና ጽድቅ ያለውና የእግዚአብሔርም አይነት ባሕርይ ስላለው፣ ይሄንን ሰው ልበሱት የሚል ነው:: ልክ እንደ ልብስ አሮጌውን ሰው እንድናወልቅ ከላይ እንዳሳሰበን እንዲሁ አዲሱን ሰው ደግሞ ልክ እንደ ልብስ እንድንለብሰው በዚህ ክፍል ያሳስበናል:: በሚቀጥለው ጥናታችን ማለትም ከቁ. 25 ጀምሮ አዲስን ሰው መልበስ ማለት በተግባር ወይም በዕለት ተለት ኑሮ ሲተረጎም ምን ማለት እንደሆነ እንመለከታለን::

 


“ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ።“
(መጽሐፈ ምሳሌ 3:3-4)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us