ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች » ኤፌሶን » ጥናት 17 (ኤፌሶን 4፣17-32 ለ) ከአሕዛብ የተለየ አካሄድ - ክፍል 2
Email this page to a friend Printer-friendly   Tuesday, 20 October 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦“
(የዮሐንስ ራእይ 3:14)

rss

Today's verse

ጥናት 17 (ኤፌሶን 4፣17-32 ለ) ከአሕዛብ የተለየ አካሄድ - ክፍል 2

pdf version

ይህን “ከአሕዛብ የተለየ አካሄድ” ያልነውን ጥናት ለሁለት ከፍለን ማጥናት ጀምረናል:: በክፍል አንድ ጥናታችን ላይ ኤፌ 4፣17-24 ያለውን የተመለከትን ሲሆን፣ በዚህ በክፍል ሁለት ጥናታችን ደግሞ ኤፌ 4፣25-32 ያለውን ክፍል እንመለከታለን::

 

ክፍል 2 (ኤፌ 4፣25-32)

 

ባለፈው ጥናታችን ላይ አሮጌውን ሰው እንደ ልብስ አውልቀን አዲሱን ሰው እንድንለብስ ጳውሎስ እንደሚያሳስብ ተመልክተናል:: በዚህ ጥናት ደግሞ ይህ አሮጌውን ሰው ማውለቅና አዲሱን ሰው መልበስ ማለት በተግባር ወይም በዕለት ተለት ኑሮ ሲተረጎም ምን ማለት እንደሆነ እንመለከታለን::

 

·       ውሸትን አስወግዶ እውነትን መነጋገር ቁ. 25

ውሸት ወይም ሐሰት ማለት ሰዎችን ለማሳት ሆን ተብሎ እውነት ያልሆነ ነገርን እውነት አስመስሎ መናገር ወይም ማቅረብ ማለት ነው:: ውሸት አንዱ የአሮጌው ሰው ባህርይ ነው:: የውሸት ወይም የሐሰት ምንጭና አባት ደግሞ ዲያብሎስ እንደሆነ ጌታ ተናግሮአል:: “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ:: እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነገረ፣ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም:: ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፣ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና::” ዮሐ 8፣44:: የውሸትን ባህርይ በሚገባ ለመረዳት፣ ሰዎች ለምንድነው ውሸትን የሚናገሩት ወይም ለመዋሸት የሚያስገድዳቸው ወይም የሚገፋፋቸው ነገር ምንድነው? ብለን ራሳችን መጠየቁ ተገቢ ነው:: ሰዎች ውሸትን የሚናገሩበት ምክንያት ምንም እንኳን ብዙ ቢሆንም፣ ዋና ዋናዎቹን ግን እንደሚከተለው ለማየት እንሞክራለን::

 

እውነት ሁሉ በቀላሉ ሊቀበሉት የማይችሉትና ዋጋም የሚያስከፍል እንደሆነ ብዙዎቻችን ከሕጻንነታችን ጀምሮ የተለማመድነው ነገር ነው:: በሕጻንነት እድሜአችን እንኳን አንዳንድ ጊዜ ለወላጆቻችን እውነቱን ብቻ ብንናገር፣ ቅጣትና ችግር እንደሚገጥመን ስለምናምን ከዚህ ሁሉ ጣጣ በቀላሉ ውሸትን ተናግረን ከቅጣት ማምለጥ እንደምንችል እንለማመዳለን:: ስለዚህ እውነትን ተናግረን ሊገጥመን ከሚችለው ከብዙ አጣብቂኝና ችግር የሚያስመልጥ አጭሩ መንገድ ውሸት እንደሆነ ከልጅነት ጀምሮ ስለተማርን፣ ይህን ልምድ ጌታን ከተቀበልንም በኋላ አውቀን እንደ አሮጌ ልብስ አውልቀን ካልጣልነው በስተቀር ከእኛ ጋር ይከተለናል:: ስለዚህ በእውነት ምክንያት ዋጋ የሚያስከፍል ነገር ሲመጣ፣ እውነቱን ተናግሮ የሚመጣውን ሁሉ ከመጋፈጥ ይልቅ፣ በአጭሩ ውሸትን ለወንድሞቻችንን ተናግረን ማምለጥን እንመርጣለን:: ከልጅነታችን ጀምሮ ያደግንበት ሕብረተሰብ ወይም በጌታ ከሆንንም ጀምሮ የክርስቲያኖች ሕብረት ስለ እውነት ያላስተማረን ነገር ቢኖር፣ እውነት ምንም መራራ ቢመስል የተሻለ መንገድ እንደሆነና፣ እውነትን የሚናገር ሰው ከቅጣት ይልቅ ምህረትንና ድጋፍን እንደሚያገኝ ነው:: ስለዚህ ውሸትን እንድንለማመድ በአብዛኛው የሚያደርገን በመጀመሪያ ደረጃ እውነትን ከተናገርን በኋላ ሕብረተሰቡ ወይም በጌታ ያሉ ወገኖቻችን ሊያደርሱብን የሚችሉት ምህረት የሌለው ፍርድና ሊከተለን የሚችለው አደጋ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ራሳችን እውነትን ተናግረን የሚመጣውን ሁሉ ለመቀበልና ለመጋፈጥ፣ እውነትም የሚያስከፍለውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል ፈቃደኛ አለመሆናችን ነው::

 

ስለዚህ በጌታ ወገኖች መካከል እውነትን የሚናገር ሰው ከፍርድ ይልቅ፣ ምህረትና ማጽናናትን ከጭፍን ወቀሳ ይልቅ ማበረታታትን ሊያገኝ ይገባዋል:: ይህ ካልሆነ የፍርድ ልብ ባለበት ሁኔታ እውነትን እርስ በርስ እንደ አካል ለመነጋገር ለብዙዎች ሊከብድ ይችላል::

 

ሌላው እንድንዋሽ ከሚያደርጉን ምክንያቶች አንዱ ያሰብነውን አላማ ለማሳካት ከመፈለግና በማናቸውም መንገድ ያንን አላማ ለማሳካት ወይም ያቀድነውን ነገር ለማግኘት ከመፈለግ ነው:: አንድን ነገር አጥብቀን ከፈለግንና እንደ ጣኦት ከሆነብን፣ ያንን ነገር በጽድቅ መንገድም ባይሆን በማታለልና በውሸትም ቢሆን ለማግኘት እንጣጣራለን:: ይህ ስግብግብ የሆነ ሥጋዊ ፍላጎታችንን ለማሟላት የሚደረግ ከጽድቅ የራቀ መንገድ ነው:: ከዚህ አይነት ውሸት ለመራቅ እንግዲህ ምንም ነገር ቢሆን በእውነትና በጽድቅ መንገድ ካልሆነ ይቅርብኝ ለእኔ አይረባኝም ብሎ ከሚገኙት ጥቅሞች ይልቅ እውነትንና እግዚአብሔርን ማስደሰተን መምረጥ ይኖርብናል ማለት ነው:: በዚህም በዚያም ቢሆን እውነትን እየተናገሩ የጌታን ጽድቅ መንገድ ለመሄድ ዋጋ ያስከፍላል:: በአሁኑ ዘመን በስፋት ያለ የብዙዎች ክርስቲያኖች አቋም፣ ያለ ምንም ዋጋ ጌታን መስሎ መኖርና በጽድቅ መንገድ መሄድ መፈለግ ነው:: ይህ ደግሞ ጨርሶ ሊሠራ የማይችልና በሕይወታችንም ብዙ ጊዜ ተፈትኖ የከሸፈ መንገድ ነው:: “በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ::” 2ጢሞ 3፣12::

 

ውሸት በአንድ ሰው ሕይወት ሲደጋገም ለችግር ጊዜ ማምለጫ ከመሆን አልፎ፣ ዝናን ሞገስንና ምስጋናን ከሰዎች ማግኛ መሣሪያና ክፉ ልምድ ወይም ጠባይ ይሆናል:: አንዳንድ ሰዎች ውሸትን ከመለማመዳቸው ብዛት ያለ ምንም  ችግር፣ ምንም የሚያስዋሽ ነገር ሳይኖር መዋሸትን ጠባያቸው አድርገውት ይታያሉ:: ሲዋሹም ልክ እውነትን የሚናገር ሰው ያለ ምንም መጨነቅና የሕሊና ወቀሳ እንደሚናገር ሁሉ፣ በቀላሉ እንደ ዲያብሎስ ውሸትን ይናገራሉ:: ይህ የሰው ጠባይ ወይም ልምድ የሆነ አደገኛው የውሸት ደረጃ ነው::

 

ውሸት ብዙ ጊዜ የአጭር ጊዜ ጥቅምን የሚያስገኝ በረጅሙ ግን የእኛንና የወገኖቻችንን በአጠቃላይ የሕብረታችንን ጤንነት እጅግ የሚጎዳ ነገር ነው:: በአካል ብልቶች ውስጥ እርስ በርስ እውነት መነጋገር ከሌለ መተማመን አይኖርም:: በመተማመን ፋንታ ጥርጣሬ እያለ አብሮ በሕብረት ለመጓዝና ተደጋግፎ የጌታን ሥራ እንደ አካል ለመሥራት ፈጽሞ የማይቻል ነው::

 

ጳውሎስ የኤፌሶን ሰዎች የአሮጌው ሰው ጠባይ የሆነውን ውሸትን እንዲያስወግዱ ብቻ ሳይሆን፣ በዚያ ፋንታም እውነትን እንዲነጋገሩና እንዲለማመዱ ነው የሚያሳስባቸው:: “ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፣ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ::” ኤፌ 4፣25:: ይህም ማለት ባልንጀራህን፣ የቅርብ ወገንህን፣ በጌታ ወንድምህን፣ የአንድ አካል ብልት የሆናችሁትን ሰው አትዋሸው፣ ሐሰትን ከእርሱ ጋር አትነጋገር፣ እውነት ያልሆነ ነገርን እውነት አስመስለህ አትንገረው፣ ነገር ግን የቅርብ ወንድምህ ነውና ከእርሱ ጋር እውነትን ብቻ ተነጋገር ማለት ነው::

 

·       ያለ ኃጢአት የሆነ ቁጣ ቁ. 26-27

ጳውሎስ በዚህ ክፍል ስለ መቆጣት ሲናገር የኤፌሶን ሰዎች እንዲቆጡ ትእዛዝ እየሰጣቸው ሳይሆን ነገር ግን “ስትቆጡ ኃጢአት አትሥሩ ወይም በምትቆጡበት ጊዜ ኃጢአት አትሥሩ” ማለቱ ነው:: እዚህ ክፍል ላይ ጳውሎስ የሚናገረው ቁጣ ባህርይው ስለሆነ ሰው ሳይሆን፣ ማንም ሰው በአንዳንድ ተገቢ ምክንያቶች የተነሣ ሊቆጣ እንደሚችልና ነገር ግን በሚቆጣበት ጊዜ ኃጢአትን መሥራት እንደሌለበት ለማሳሰብ ነው:: ለምሳሌ ያህል በማር 3፣1-6 ላይ ያለውን ብንመንለከት፣ ጌታ ሲቆጣ ወይም ፈሪሳውያንን በቁጣ አይን ሲመለከታቸው እናነብባለን:: በሰንበት ጌታ ሰውን መፈወሱና ከችግሩ ማላቀቁን እንደ ኃጢአት ቆጥረው ሊከሱት ስለፈለጉ ጌታ “ስለ ልባቸውም ድንዛዜ አዝኖ ዙሪያውን እየተመለከተ በቁጣ አያቸው...” ማር 3፣5:: እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን አንደኛ ጌታ በመሠረቱ ቁጠኛ ወይም ቁጡ ባህርይ እንደሌለውና በትንሹም በትልቁም ቁጣ ቁጣ የሚል ጠባይ እንደሌለው መገንዘብ አለብን:: በሌላ በኩል ደግሞ ምንም እንኳን ቢቆጣም፣ ተቆጥቶ በሽተኛውን ከመፈውስ በስተቀር ኃጢአትን አልሠራም::

 

ሰው በሚቆጣበት ሰዓት ሌሎችን በቃላት ለመጉዳት፣ ቂም ለመያዝና ክፉ ለማድረግ ወዘተ ባጠቃላይ ኃጢአትን ለማድረግ ያለው እድል ከፍተኛ በመሆኑ ቁጣችን ያለ ኃጢአት እንዲሆን ነው ጳውሎስ የሚያሳስበን:: ልክ መልካም አባት ልጁን በታረመ አንደበት በቃላትም እንዳይጎዳው እየተጠነቀቀ እንደሚናገር፣ የአዲሱ ሰውም ቁጣ እንዲሁ ያለ ኃጢአት ነው:: በተለይ ቁጣችን ውሎ እንዳያድርና ወደ ቂም እንዳይለወጥ፣ በዛም ለዲያብሎስ ፈንታ እንዳንሰጠው ጳውሎስ ያሳስበናል:: “በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፣ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት::” ቁ.27:: ይህም ማለት የዛሬ ቁጣ ዛሬ ይለቅ፣ ለነገ አይደር ማለት ነው:: የተቆጣንበትን ነገር ብዙ ካሰላሰልነው ዲያብሎስም ብዙ ክፉ ሃሳቦችን ሊያቀብለን ስለሚችል ቶሎ እንድንረሳውና እንዳናሰላስለው እንመከራለን::

 

·       በስርቆሽ ፈንታ ለጎደለው ማካፈል ቁ.28

መስረቅ ማለት ሕጋዊ ወይም ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ የሌላ ሰውን ንብረት በድብቅ መውሰድ ማለት ነው:: እዚህ ላይ ንብረት ስንል ብዙ ነገሮችን ያጠቃላል:: ብዙ ጊዜ ስለ መስረቅ ስናስብ በአእምሮአችን የሚመጣው በኪስ የሚገባ ነገር ብቻ ነው:: ነገር ግን ስርቆሽ በመሥሪያ ቤት የሥራ ሰዓትን፣ ስልክንና ሌሎችንም ንብረቶች ያለ ፈቃድ ለግል ጥቅም ማዋልንም ያጠቃልላል:: ሳንታመም ታምመናል ብለን ያለ አግባብ ያልለፋንበትን ገንዘብ ከመሥሪያ ቤት ማግኘትም ስርቆሽ ነው:: ስርቆሽ እንግዲህ በቅርበት ሲታይ ሰፋ ያለና ማናቸውም ያለ አግባብ በድብቅና በሐሰት የምናገኘውን የሌሎችን ንብረቶች ሁሉ የሚያጠቃልል ነው::

 

በዚህ ክፍል ጳውሎስ የሚመክረው ግን፣ ስርቆሽ የአሮጌው ሰው ባህርይ ስለሆነ ይህንን አስወግደን በዚያ ፈንታ የአዲሱ ሰው ባሕርይ የሆነውን እንድንለብስ ነው:: ይሄውም ከሰዎች ከመውሰድ ፈንታ፣ ለጎደላቸው ማካፈል:: ከሌሎች እየሰረቁ የራስን በመሙላት ፈንታ፣ የሌሎችን ጉድለት ለመሙላት መድከም:: ሌሎችን በማራቆት ፈንታ፣ ሌሎችን በሚያስፈልጋቸው መርዳት:: “የሰረቀ ከእንግዲህ አይስረቅ፣ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም::” ኤፌ 4፣28:: ይህ ካለመስረቅ ያለፈ እውነተኛ የአዲሱ ሰው የሕይወት ፍሬ ነው::

 

·       በክፉ ቃል ፈንታ በጎ ቃል ቁ. 29

ይሄንን ቁጥር የAmplified መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ይተረጉመዋል:- “Let no foul or polluting language, nor evil word nor unwholsome or worthless talk [ever] come out of your mouth, but only such [speech] as is good and beneficial to the spiritual progress of others, as is fitting to the need and the occasion, that it may be a blessing and give grace (God's favor) to those who hear it.” ይህም ማለት “የተበላሸ፣ የሚበክል፣ ክፉ የሆነ፣ ጤናማ ያልሆነ ወይም ጥቅም የማይሰጥ ቃል/ንግግር ጨርሶ ከአፋችሁ አይውጣ፣ ነገር ግን ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ በረከት እንዲሆን ንግግራችሁ በጎ፣ ለሌሎች መንፈሳዊ ሕይወት እድገት ጠቃሚ የሆነ፣ ለጊዜውና ላለባቸው ችግር የሚስማማ ይሁን” ማለት ነው::

 

በዚህ ክፍል ሁለት አይነት ቃላቶች ወይም ንግግሮች እንዳሉ እንመለከታለን:: አንደኛው በጎ ቃል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ክፉ ወይም የተበላሸ (corrupt) ቃል ነው:: ይህም ብቻ ሳይሆን የክፉ ወይም የበጎ ቃል/ንግግር መለኪያዎያም ተገልጾአል:: ይሄውም ለሚሰሙት የሚሰጠው ጥቅም ወይም በሚሰሙት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ናቸው:: ወይ የሚሰሙትን መንፈሳዊ ሕይወታቸውን የሚያንጽና የሚጠቅም የጸጋ ቃል ነው ወይም የሚሰሙትን ምንም የማይጠቅም ይባስ ብሎም የሚበክል፣ የሚያፈርስና የማያንጽ ክፉ ቃል ነው:: ስለዚህ የንግግር መልካምነት የሚለካው በሰሚዎቹ ላይ በሚያመጣው ውጤት ነው::

 

ቃላት ወይም ንግግር የሰዎችን ሕይወት ሊገነባና ሊያንጽ በተቃራኒውም ሊያፈርስና ሊበክል የሚችል ትልቅ መሣሪያ ነው:: ስለዚህ የንግግሩ ትክክለኝነት ወይም እውነትነት ብቻም የንግግሩ መለኪያ አይደለም:: አንዳንድ ጊዜ ሰዎች እውነትንም ያለ አግባብና ያለ ጊዜው በክፉ ልብ ያለ ፍቅር ሲናገሩት፣ ምንም እንኳን ንግግሩ እውነትን ያዘለ ቢሆንም ውጤቱ ግን የሰውን ሕይወት የሚያፈርስ በመሆኑ፣ ክፉ ቃል ነው:: ብዙ ጊዜም የምንናገረውን ነገር ለእኛ እውነት መሆኑን እንጂ በሌሎች ላይ የሚያስከትለውን የሕይወት ጉዳት ጨርሶ አናስተውልም:: የበጎ ንግግር ወይም ቃል መለኪያ እንግዲህ የሌሎችን መንፈሳዊ ሕይወት ማነጹ ነው::

 

ጳውሎስም በዚህ ክፍል ንግግራችን ሁሉ ሌሎችን የሚያንጽና የሚጠቅም እንዲሆንና በአንጻሩ ድግሞ የሚጎዳ፣ የሚያፈርስና የሚበክል ክፉ ቃል ከአፋችን ጨርሶ እንዳይወጣ ይመክረናል:: የአዲሱ ሰው አንዱ ዋነኛ ባሕርይ የታረመና የሚያንጽ አንደበት ነውና::

 

·       የእግዚአብሔርን መንፈስ አለማሳዘን ቁ.30

ከክፉ ቃልና ከንግግር ጋር አያይዞ ጳውሎስ ወዲያው የእግዚአብሔርን መንፈስ ስለማሳዘን ይነግረናል:: ጭቃ በሌሎች ላይ የሚወረውር ሰው በመጀመሪያ የራሱ እጆች እንደሚቆሽሹ፣ እንዲሁ ክፉ ቃልና ንግግር የሌሎችን ሕይወት ከመበከሉና ከመጉዳቱም በላይ እኛ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለንን ሕብረት ይበክልብናል:: ወንድሞቻችንን በቃላት ስንጎዳና ስንበክል በዚያ መንፈስ ቅዱስ ያዝናል:: “...ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ” ቁ. 30:: ይሄ በአማርኛ “አታሳዝኑ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል የግሪኩ ሌክሲከን እንደሚከተለው ይተረጉመዋል:- to make sorrowful, to affect with sadness, cause greif, to throw into sorrow ይህም ጥልቅ የሆነ ሃዘን ማሳዘንን፣ ማስከፋትን፣ ወደ ሃዘንና ትካዜ መጣልን የሚያመለክት ነው:: የግሪኩ መዝገበ ቃላት ደግሞ በተመሳሳይ ሁኔታ ይሄንን ቃል እንደሚከተለው ይተረጉመዋል:- to cause pain, or grief, to distress, grieve ማለትም ማሳመም፣ መጉዳት፣ ማሳዘን፣ ትልቅ ጉዳት መፍጠርንና አለመመቸትን ሁሉ የሚያጠቃልል ነው::

 

ስለዚህ ጳውሎስ በዚህ ክፍል ለኤፌሶን ሰዎች የሚሰጣቸው ማሳሰቢያ፣ ክፉ ቃል እየተነጋረቸሁና የወንድሞቻችሁን መንፈሳዊ ሕይወት እያፈረሳችሁ፣ የእግዚአብሔርን መንፈስ አትጉዱ፣ ትልቅ ሐዘንና ትካዜ ውስጥ አትክተቱት፣ እንዳይመቸው አታድርጉት ወዘተ የሚል ነው::

 

በዚህ ክፍል “ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን” የሚለውን ቃል በይበልጥ ለመረዳት ጥናት 2 ቁጥር አምስት እና ጥናት 3 ቁጥር አራትን ይመልከቱ::

 

·       መራርነትን፣ ንዴት፣ ቁጣ ወዘተ ማስወገድ ቁ. 31

በዚህ ክፍል የተጠቀሱት በሙሉ መጥፎ አመልንና ክፉ ባህርይን የሚያመለክቱ ናቸው::

 

በመጀመሪያ የተጠቀሰው ክፉ ጠባይ መራርነት ነው:: ይህ መራርነት/bitterness የሚለውን ቃል ትክክለኛ መጽሐፍ ቅዱስዊ ትርጉሙን ለመረዳት ይህ ቃል በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የተጠቀሰበትን አውደ ምንባብ መመልከቱ ይረዳናል:: “በመራራ መርዝና በዓመፅ እስራት እንዳለህ አይሃለሁና::” የሐዋ 8፣23:: ይህንን ቃል ጴጥሮስ ለጠንቋዩ ሲሞን የተናገረው ቃል ነው:: ይህም ሰውዬው በምን ያህል ጥልቅ የሆነ ክፋት እንደታሰራ ለማሳየት ነው (a condition of extreme wickednes):: በሮሜ 3፣13-14 ላይም ይህ ቃል እንደሚከተለው ተጠቅሷል:- “...የእባብ መርዝ ከከንፈሮቻቸው በታች አለ፣ አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል”:: በዚህም ክፍል አንደበታቸው ምን ያህል ክፉና የሚመር ነገር እንደሚናገር የሚያሳይ ነው:: ልክ እንደዚሁ ሁሉ ዕብ 12፣15 ላይም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መራራ ሥር ይናገራል:: ይህም መልካም ያልሆነ፣ መልካምና ጣፋጭ ፍሬ ሊያፈራ የማይችልን ሥር የሚያመለክት ነው:: ክፉና መራራ ፍሬ የሚያፈራን ሥር ያሳያል:: ከላይ የተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ አውደ ምንባቦች እንግዲህ የሚያሳዩን ቃሉ የመልካም ፍሬ ወይም የበጎ ነገር ተቃራኒ የሆነ ክፉ ወይም ጎምዛዛ ነገርን የሚያመለክት ነው:: በዚህ ክፍል ደግሞ ጳውሎስ መራርነትን አስወግዱ ሲል እንግዲህ ክፉ ወይም ጥልቅ የሆነ ጥላቻን የሚያመለክት ነው (bitter hatred)::

 

በዚህ ክፍል የተጠቀሰው ሌላው መጥፎ ባሕርይ ንዴትና ቁጣ ነው:: ይህ ንዴት ወይም ቁጣ ተብሎ የተጠቀሰው በቁ. 26 እንደተመለከትነው አይነት ኃጢአት የሌለበትና ልምድ ያልሆነ ቁጣ ሳይሆን፣ ይህ ክፍል የሚያወራው ስለ ቁጠኛ ወይም ንዴተኛ ጠባይ ነው (bad temper):: የእግዚአብሔር ሰው ቶሎ ተናዳጅና ጠባየ ቁጡ ሳይሆን፣ ትዕግሥተኛና ቻይ ሊሆን ይገባል:: ቶሎ ቶሎ ቱግ ማለትና ቁጡ ሰው መሆን የአሮጌው ሰው ባሕርይ ነውና::

 

ከዚሁ ጋር ተያይዘው የተጠቀሱት መጥፎ አመሎች እርስ በርስ መጯጯኽ (የጥል ወይም የጭቅጭቅ ጩኸት)፣ ስድብ (slander የሰውን ስም የሚያጠፋ ክፉ ንግግር፣ detraction የሰውን መልካም ስም ማጉደፍ፣ evil speaking ክፉ ንግግር) እና ባጠቃላይ ማናቸውም ክፋት የሆነ ነገር ሁሉ ናቸው::

 

ጳውሎስ እንግዲህ በዚህ ክፍል የተውሰኑትን ክፉ ነገሮች ጠቀሰ እንጂ፣ ሃሳቡ ማናቸውንም ክፉ ነገሮች ሁሉ እንድናስወግድ የሚመክር ነው::

 

·       እርስ በርስ በቸርነት፣ በርኅራኄና በይቅርታ መመላለስ ቁ. 32

የአሮጌው ሰው ባሕርይ የሆኑትን ክፉ ነገሮች ሁሉ ማስወገድ ብቻ ሳይሆን፣ ደጋግሞ ጳውሎስ የሚመክረን አዲሱን ባሕርይም እንድንለብስ ነው:: በዚህ ክፍል ሶስት የአዲሱ ሰው ባሕርያት ተጠቅሰዋል:-

 

ቸርነት:- እርስ በርስ ጠቃሚ፣ የሚረዳዱ፣ በጎ፣ መልካምና ቸር መሆን ወይም አለመጨካከን፣ አለመከፋፋት::

 

ርኅራኄ:- አዛኝ፣ ሩህሩህ፣ ፍቅር ያለው ልብ::

 

ይቅርታ:- ቂም አለመያዝ፣ በደልን መተው፣ ምህረትን ማድረግ:: ይቅርታ የፍርድና የቂም ተቃራኒ ነው:: ፍርድና ቂም የሰውን ጉድለትና ጥፋት ብቻ ያያል:: ስለዚህ የራስን ድካም ማየትና እኛም ብዙ የምንበድል እንደሆንን በጥልቀት መረዳት ይቅርታ ለማድረግ በጣም ይረዳናል:: ጳውሎስም የይቅርታችን መሠረት አድርጎ የጠቀሰውም ነገር የእግዚአብሔር ይቅርታ ነው:: “...እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ::” ቁ. 32:: የራሱን ድካምና በደል የማያይ ሰው ሌሎችን ይቅርታ ማድረግ አይችልም ማቴ 18፣21-35:: የአለም ብርሃን የሆነው ጌታ የራሳቸውን ኃጢአት ወደ ብርሃን እስከሚያወጣው ድረስ፣ በምንዝር በተያዘችው ሴት ላይ ያለ አንዳች ምህረትና ርኅራኄ ፈሪሳውያን ሊፈርዱ የተነሱት፣ የራሳቸውን ድካም ስላላዩና የራሳቸውን ነገር በጨለማ ስለደበቁ ነው ዮሐ 8፣1-12:: የራሱን ድካም የማያይ ሰው በሌሎች ለመፍረድ ይፈጥናል፣ ይህም በጨለማ እንደመቀመጥ ያህል ነው::

 

 


“ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ።“
(መጽሐፈ ምሳሌ 3:3-4)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us