ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች » ኤፌሶን » ጥናት 2 (ኤፌሶን 1፣3-14 ሀ) መንፈሳዊ በረከቶች - ክፍል 1
Email this page to a friend Printer-friendly   Tuesday, 20 October 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦“
(የዮሐንስ ራእይ 3:14)

rss

Today's verse

ጥናት 2 (ኤፌሶን 1፣3-14 ሀ) መንፈሳዊ በረከቶች - ክፍል 1

pdf version

 

ማሳሰቢያ:- መንፈሳዊ በረከቶች ብለን በሰየምነው በዚህ ጥናት ውስጥ በዝርዝር ልናይ የምንፈልገው መንፈሳዊ በረከቶቹን ብቻ ነው:: ይህም ማለት በረከቶቹን በማን በኩል እንደተባረክንና ይህንንስ ለማድረግ እግዚአብሔርን ያነሳሳው (motive) ምን እንደሆነ አሁን አንመለከትም:: እነዚህን ነገሮች በኋላ ላይ እንመለከታቸዋለንና::

 

1.              በዚህ ክፍል ውስጥ የሚከተሉት መንፈሳዊ በረከቶች ተዘርዝረዋል:-

1.    አለም ሳይፈጠር መረጠን

2.    አስቀድሞ ወሰነን (የእርሱ ልጆች እንሆን ዘንድ)

3.    ቤዛነትና የበደል ስርየት አገኘን

4.    ጸጋውን አበዛልን/አትረፈረፈልን

·       በጥበብና በአእምሮ ሁሉ

·       የፈቃዱን ምስጢር አስታወቀን

5.    ርስትን ተቀበልን

6.    በመንፈስ ቅዱስ ታተምን

 

ማሳሰቢያ:- ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩት በረከቶች ውስጥ በዚህ በክፍል 1 የምናየው ከ1-3 ያሉትን ብቻ ነው:: የተቀሩትን በክፍል 2 ጥናታችን እንመለከታቸዋለን::

 

2.              አለም ሳይፈጠር መምረጥ (አስቀድሞ መምረጥ) እና አስቀድሞ መወሰን

 

·       ሀ) የቃላት ፍቺዎች

·       አስቀድሞ መምረጥ

መምረጥ ማለት ለምርጫ ከቀረቡ እጩዎች ውስጥ የተውሰኑትን መለየት ወይም ለራስ ማድረግ ማለት ነው:: እግዚአብሔርም እንግዲህ ለራሱ እንሆን ዘንድ ለይቶናል ወይም መርጦናል:: ይህንን ምርጫ ግን ያካሄደው እኛ በጌታ ያመንን ቀን ሳይሆን፣ አለም ሳይፈጠር በፊት ወይም በሌላ አገላለጽ አስቀድሞ ነው::

 

·       አስቀድሞ መወሰን

በእንግሊዝኛ to predestine, to predetermine, decide beforhand, forordain

በአማርኛ:- አስቀድሞ መቁረጥ (የተቆረጠ ሃሳብ)፣ አስቀድሞ መደንገግ፣ አስቀድሞ ማዘዝ፣ አስቀድሞ ማጨት

 

እግዚአብሔር እኛ ልጆቹ እንድንሆን አስቀድሞ የወሰነው ወይም የደነገገው ጉዳይ ነው:: እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው፣ እግዚአብሔር የወሰነው ማን እንደሚድንና ማን እንደማይድን ሳይሆን፣ አስቀድሞ የመረጣቸውን ሰዎች፣ የእነርሱን የወደፊት ዕጣ ነው፣ ይሄውም የእርሱ ልጆች እንዲሆኑ:: ይህ አስቀድሞ መወሰን የሚለው ቃል በሌሎችም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ይገኛል (ሮሜ 8፣29 ሐዋ 4፣28 1ቆሮ 2፣7)::

 

·       ለ) ሁለቱ መሠረቶቻቸው

አንድ ሰው አንድን ነገር ከሌሎች ለይቶ ሲመርጥ የተለያዩ መስፈርቶችን ይጠቀማል:: እነዚህ መስፈርቶችም ለሚወስደው ምርጫ መሠረቶች ይሆኑለታል:: ለምሳሌ:- ከአንድ ኪሎ ሙዝ ውስጥ አንድ ሰው ሁለት ሙዞችን ቢመርጥ፣ ምርጫውን መሠረት ያደረገው ምናልባት በጣም ያልበሰሉ ወይም በጣም ጥሬ ያልሆኑ በሚሉት ላይ ሊሆን ይችላል:: እነዚህ መስፈቶች እንግዲህ ለምርጫው መሠረት ሆነውለታል ማለት ነው:: ለእግዚአብሔር አስቀድሞ ምርጫና አስቀድሞ ውሳኔ መሠረት የሆኑ ሁለት ዋና ዋና ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰው እናገኛለን::

 

1.              አስቀድሞ ማወቅ

“... አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና ...” ሮሜ 8፣29

በዚህ ክፍል እንደምንመለከተው አስቀድሞ ለመወሰኑ መሠረት የሆነው አስቀድሞ ማወቁ እንደሆነ ነው:: እግዚአብሔር ወንጌል ሲደርሳቸው የትኞቹ ሰዎች እንደሚቀበሉ አስቀድሞ እንደሚያውቅ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል::

“... በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፣ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበርና::” ማቴ 11፣20-24

“... ነገር ግን ተናገር ዝምም አትበል፣ በዚህ ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና አለው::” ሐዋ 18፣9-10

 

እግዚአብሔር እንግዲህ አስቀድሞ ስለሚያውቅ አስቀድሞ መወሰንና መምረጥ ይችላል:: እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን፣ በሮሜ 8፣29 እንደተጠቀሰው አስቀድሞ ያወቃቸውን ነው የልጁን መልክ እንዲመስሉ የወሰናቸውም፣ የመረጣቸውም:: ስለዚህ አስቀድሞ ማወቁ አስቀድሞ ለመወሰንም ይሁን አስቀድሞ ለመመረጥ መሠረት ሆኖለታል ማለት ነው::

 

2.              የእግዚአብሔር ሉዓላዊ (sovereign) ስልጣን ወይም መብት

እግዚአብሔር አስቀድሞ እንዲመርጥና አስቀድሞ እንዲወስን መሠረት የሚያደርገው ሌላው ነገር ደግሞ የራሱ የእግዚአብሔር ሉዓላዊ መብቱ ወይም ስልጣኑ ነው:: በሮሜ 9፣10-16 ላይ ያዕቆብና ኤሳው ገና ሳይወለዱ፣ ክፉና በጎ ሥራ ሳይሠሩ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዕቆብን እንደመረጠውና በታላቁ በኤሳው ላይም እንዲገዛ አስቀድሞ እንደወሰነ እንመለከታለን:: በዚሁ ክፍል ቁ. 15-16 ላይ ደግሞ እግዚአብሔር የፈለገውን ሊምርና ሊራራለት መብት እንዳለውና ምሕረት ከሚምር ከእግዚአብሔር የሆነ ጸጋ እንጂ ምሕረትን ለፈለገ ወይም ለሮጠ ሁሉ እንዳልሆነ ተጠቅሱዋል:: ይሄ አይነቱ ምርጫ ግን ለተለየ (special) የእግዚአብሔር አላማ (ለምሳሌ ፈርኦን ሮሜ 9፣17-18) የሚጠቀምበት እንጂ መደበኛው የደህንነት መንገዳችን እንዳልሆነ ልናስተውል ይገባል:: በሮሜ 8፣29 እንደተመለከትነው በክርስቶስ የተደረገው አስቀድሞ ውሳኔና ምርጫ መሠረቱ አስቀድሞ ማወቅ ነው::

 

·       ማጠቃለያ

·       ሰዎች ሁሉ ይድኑ ዘንድ እግዚአብሔር ይወዳል:: 1ጢሞ 2፣3-4 ዮሐ 3፣16

·       በክርስቶስ አለም ሳይፈጠር በፊት ለሆነው አስቀድሞ ምርጫና አስቀድሞ መወሰን ዋናው መስፈት አስቀድሞ ማወቅ ነው::

·       እግዚአብሔር ሉዓላዊና ባለ ሙሉ ሥልጣን ስለሆነ ምንም እንኳን በአንዳንድ ለየት ባሉ ሁኔታዎች ላይ (special cases) ይጠቀመብት እንጂ፣ በመሠረቱ የፈለገውን የመምረጥና የፈለገውን ለፈለገው ነገር የመወሰን መብት አለው::

·       ምሕረትም ይሁን ወንጌልን መስማት የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ፣ የምሕረትም ሆነ ወንጌልን የመስማት መብት የለም:: ዛሬ በአለም ላይ ከ3 ቢሊየን የሚበልጡ ሕዝቦች ኢየሱስ የሚለውን ስም እንዳልሰሙ ይገመታል:: ማንም ዕዳ ያለበት ሰው አበዳሪው ሲወድ ይምረዋል እንጂ ተበዳሪው ራሱ የዕዳ ምሕረት መብት እንደሌለው ሁሉ፣ የሰው ዘርም ሁሉ በደለኛና ባለ ዕዳ ስለሆነ፣ በመሠረቱ የምሕረት መብት የለውም::

·       ሰለዚህ አዲስ ኪዳን፣ እግዚአብሔር አለም ሳይፈጠር እንደመረጠንና እንደወሰነን ሲናገር፣ ሊያስተላልፈው የሚፈልገው ዋናው መልእክት፣ የደህንነት ሥራ የተጀመረው ልክ አማኞች ጌታን ሲቀበሉ ሳይሆን ወይም ከአማኞች መልካምነት ወይም ከአማኞች መልካም ሥራ ሳይሆን፣ ወንጌልን መስማትን ጨምሮ ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ የተመሠረተ ነው፣ የሚለውን ሃሳብ ነው::

 

3.              የምርጫው የመጨረሻ ግብ/ዓላማ/ዕጣ/መዳረሻ

·       በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን እንሆን ዘንድ

ቅዱስ (የጥናት አንድ ማብራሪያ ቁጥር 4 ተመልከት)

 

ነውር የሌለው:- የሚለው ቃል የሚያመለክተው የሚያጸይፍ ነገር አለመኖርን፣ አንዳች እንከን አለመገኘትን፣ አንዳች የተበላሸ ነገር ወይም ጉድለት አለመኖርን፣ ንጹሕ መሆንን ወዘተ ነው:: ይህ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለይ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መስዋዕትን አስመልክቶ የመስዕዋቱን እንከን ወይም ጉደለት አልባነት ለመግለጽ የሚያገለግል ቃል ነው:: ዘሌ 22፣20-22 1ጴጥ 1፣18-19 ዕብ 9፣14

 

በፊቱ:- በሰው ፊት ምናልባት ነውር የሌለው ሆኖ ለመቅረብ ይቻል ይሆናል፣ በእግዚአብሔር ፊት ነውር የሌለው መሆን ግን እጅግ ድንቅ ነው:: እግዚአብሔር መርምሮ አንዳች እንከንና ጉድለት ወይም ጸያፍ ነገር የማያገኝባቸው ሰዎች እንድንሆን ነው እግዚአብሔር ለሕይወታችን ያለው የመጨረሻ አላማና ግብ::

 


 

4.              አስቀድሞ የተወሰነው ውሳኔ

·       ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን (predestined us to adoption ... to himself)

ቀደም ብለን እንዳየነው እግዚአብሔር አስቀድሞ የውሰነን ልጆቹ እንድንሆን ነው እንጂ ማን እንደሚድንና ማን እንደሚጠፋ አይደለም:: በዚህ ክፍል “ለእርሱ ልጆች ልንሆን” የሚለው ቃል በግሪኩና በእንግሊዘኛው የሚያወራው ስለ ማደጎ/ጉዲፈቻ/አዳብሽን/adoption ነው:: መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅነታችንን በዳግመኛ ልደት (ዮሐ 1፣12-13/3፣5-6/1ጴጥ 1፣23) እንዲሁም እንደ አዲስ ፍጥረትነት (ኤፌ 2፣10/2ቆሮ 5፣17) ገልጾታል::

 

እዚህ ክፍል ላይ ግን ጳውሎስ ይህንን የእግዚአብሔር ልጅነት የገለጸው ማደጎ (adoption) የሚለውን ቃል በመጠቀም ነው:: የእግዚአብሔር ልጅነታችን በማደጎ/በአዳፕሽን ሲመሰል ይህ የመጀመሪያው አይደለም:: በሮሜ 8፣15 እና በገላ 4፣5 ላይም የተጠቀሱትና በአማርኛ “ልጅነት” ተብለው የተተረጎሙት ክፍሎች የሚያወሩት ስለማደጎነት ወይም ስለ አዳፕሽን ነው::

 

ይህ አገላለጽ በዚያን ጊዜ ለነበሩና የሮማውያንን የማደጎ ሥርዓት ለሚያውቁ ሰዎች ብዙ መንፈሳዊ ነገርን በቀላሉ እንዲረዱ ያደርጋል:: በሮማውያን ሕግ መሠረት አንድ ሰው አዳብት ሲደረግ:-

1.             ባለፈው ቤተሰብ ያለውን ማናቸውንም መብት ያጣና የአዲሱ ቤተሰብ ባለ ሙሉ መብት ይሆናል ወይም አዲስ አባት ያገኛል

2.             የአዲሱ አባቱ ወራሽ ይሆናል:: ወራሽነቱን ደግሞ ማንም ሊመልሰው ወይም ሊነጥቀው አይችልም

3.             ያለፈው ሕይወቱ ማለትም ዕዳው፣ የሠራው ወንጀል ወዘተ በሙሉ ከመዝገብ ይሰረዝለታል:: ስሙም ጭምር ተቀይሮ አዲስ ማንነት/identity ይይዛል

4.             ልጅነቱ በሥጋ የአዲሱ አባቱ ከሆኑት ልጆች አይለይም:: ስለዚህ በሥጋ የአዲሱ አባቱ ልጅ የሆነችውን አንዱዋን ሴት ልጅ ለማግባትም አይፈቀድለትም::

5.             ማደጎ ያደረገው አባት ሲሞት የእርሱን ልጅነት እንዲመሰክሩ፣ ማደጎ በሚደረግበት ወቅት ሰባት ምስክሮች ያስፈልጉ ነበር::

 

በዚህ ክፍል እንግዲህ ጳውሎስ ሊያስተላልፈው የሚፈልገው መልእክት፣ ልክ በሮማውያን ዘመን አዳብት እንደተደረገ ልጅ እኛም:- አዲስ አባት እንዳገኘንና ወደ አዲስ ቤተሰብ እንደተቀላቀልን፣ በአዲሱም ቤተሰብ ውስጥ ባለ ሙሉ መብት እንደሆንንና እንደ ልጅነታችንም ሙሉ ወራሾች እንደሆንን፣ ያለፈው ማንነታችን ከእነ ዕዳችን እንደተሰረዘና አዲስ ማንነትን/ስምን/identityን እንዳገኘን ለማሳየት ነው::

 

 

5.              ቤዛነትና የበደል ስርየት

·       ቤዛ የሚለው ቃል:- በተለያየ ምክንያት ባለመብት ከሆነው ከባለቤቱ እጅ ወጥቶ በሌላ ባለቤትነት ሥር የወደቀን ነገር፣ ዋጋ ከፍሎ ነጻ ማውጣት ወይም ወደ መጀመሪያው ባለቤቱ መመለስ ወይም መታደግ ማለት ነው:: መቤዠት፣ ዋጋን/ዕዳን መክፈልንና ነጻ ማውጣትን/መታደግን አንድ ላይ አያይዞ የሚገልጽ ቃል ነው::

 

በብሉይ ኪዳን መቤዠት የሚለውን ቃል ለተሸጠ ርስት (ሌዋ 25፣25-27)፣ እንዲሁም ለባርነት ለተሸጠ ሰው (ሌዋ 25፣47-49) ሲያገለግል እንመለከታለን::

 

እኛም ከአምላካችን ባለቤትነት ስር ወጥተን በጨለማው ኃይላትና በኃጢአት ግዛት ሥር ወድቀን ሳለ፣ በኃጢአታችንም ለእግዚአብሔር የቁጣ ቀን ተጠብቀን ሳለ እግዚአብሔር የክርስቶስን ደም ለእዳችንና ለበደላችን ማስተሰርያ ከፍሎ መልሶ እንደገዛንና እንደገና ለራሱ እንዳደረገን ወይም እንደታደገን የሚያመለክት ነው:: ቆላ 1፣12-14 ሮሜ 3፣23-25 ዕብ 9፣15 1ቆሮ 1፣30-31 (ሮሜ 6፣14 ሮሜ 4፣9)


“ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ።“
(መጽሐፈ ምሳሌ 3:3-4)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us