ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች » ኤፌሶን » ጥናት 20 (ኤፌሶን 5፣21-6፣9 ሀ) በክርስቶስ ፍርሃት መገዛት - ክፍል 1
Email this page to a friend Printer-friendly   Tuesday, 20 October 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦“
(የዮሐንስ ራእይ 3:14)

rss

Today's verse

ጥናት 20 (ኤፌሶን 5፣21-6፣9 ሀ) በክርስቶስ ፍርሃት መገዛት - ክፍል 1

pdf version

ይህን “በክርስቶስ ፍርሃት መገዛት” ብለን የሰየምነውን ጥናት በ3 ክፍሎች ከፍለን እናጠናዋለን:: ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌ 5፣21 ላይ “ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ” በማለት ነው ለዚህ ለምናጠናው ክፍል መሪ ሃሳቡን የገለጸው:: እስከ ኤፌ 6፣9 ድረስ በዚህ መሪ ሃሳብ ሥር ጳውሎስ ሦስት ዓይነት ግንኙነቶችን ያብራራል:: እነዚህም:-

 

1.              ሚስቶችና ባሎች 5፣22-33

2.              ልጆችና ወላጆች 6፣1-4

3.              ባሮችና ጌቶች 6፣5-9

 

በዚህ በክፍል አንድ ጥናታችን ላይ ቁ. 1ን የምንመለከት ሲሆን፣ የተቀሩትን ደግሞ በሚቀጥሉት ጥናቶቻችን ላይ በተከታታይ እናያቸዋለን::

 

ብዙ ሰዎች ይህንን ጥናት ሲያጠኑ ወይም ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሲያነቡ አንዳንድ የመረዳት ችግሮች ይገጥማቸዋል:: ለዚህም ምክንያት የሆነው በመጀመሪያ ራሱ መገዛት የሚለው ቃል ነው:: ይሄ ቃል በብዙዎች ዘንድ አሉታዊ (negative) የሆነ ትርጉም ነው ያለው:: ምክንያቱም በዓለም ታሪክ ውስጥ መገዛት የሚለው ቃል ከጭቆና፣ ከመረገጥ፣ ከመገፋት፣ ከግዴታ ወዘተ ጋር የተያያዘ ስለሆነ ነው:: ስለዚህ መገዛት በሚለው ቃል ሥር ብዙ ጊዜ ቶሎ መልካም ነገርን ለማሰብ ያቅተናል:: እዚህ ላይ ግን ልብ ማለት ያለብን፣ ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ መገዛት የሚለውን ቃል ይጠቀም እንጂ፣ ይህን ሲል ግን በዓለም እንዳለው ዓይነት የጭካኔ አገዛዝ ወይም ጭቆናን ማለቱ እንዳልሆነ መገንዘብ አለብን::

 

መገዛት ተብሎ በአማርኛ የተተረጎመው የቃሉ ትርጉም እንደሚከተለው ነው:- (primarily a military term – to rank under) to arrange under, to subordinate, to subject, put in subjection, to subject one's self, to obey, to submit to one's control, to yield to one's admonition or advice ማለትም በመጀመሪያ ደርጃ ቃሉ በሚሊቴሪ ውስጥ ስላለ የሥልጣን ወይም የደረጃ ተዋረድ የሚገልጽ ነው:: ያንን ተዋረድ አክብሮ ራስን በትክክለኛው መደብ ማስገባት:: ማለትም ሃምሳ አለቃው ለመቶ አለቃው እውቅናን በመስጠት፣ ራሱን እንደ ሃምሳ አለቃ እንጂ እንደ መቶ አለቃ አለመቁጠር፣ ራሱን ባለው የደረጃ ተዋረድ ውስጥ ማስገባት፣ ከበላይ ላለው የሥልጣን ተዋረድ ራስን መስጠት፣ መታዘዝ፣ ከበላይ የሚመጣውን ተግሣጽና ምክር መቀበል ወዘተ ማለት ነው::

 

ምንም እንኳን መታዘዝ የሚለው ቃል ግዴታን በውስጡ ያዘለ ቢመስልም፣ በዚህ ክፍል ግን ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች እያስረዳቸው ያለው በግዴታ ስለሚሆን ጭቆና ሳይሆን ስለ ክርስቶስ ሲባል፣ ክርስቶስን ከመፍራትና ከማክበር የመነጨ በፈቃደኝነት ራስን በተቀመጠው የመደብ ተዋርድ ውስጥ ማስገባትን ነው:: “ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ” ቁ. 21:: ጳውሎስ ሴቶችን፣ ልጆችንና ባሮችን ሲመክር ሁል ጊዜ የጌታን ስም በመጥራት ነው:: “ሚስቶች ሆይ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ” ኤፌ 5፣22 “ልጆች ሆይ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ” ኤፌ 6፣1 “ባሮች ሆይ፣ ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ ... በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑ ታዘዙ” ኤፌ 6፣5:: ስለዚህ ለሁሉም ዓይነት መታዘዝ ወይም መገዛት መሠረቱ ክርስቶስ እንጂ ግዴታ አይደለም::

 

ከላይ እንደገለጽነው ምንም እንኳን መገዛት የሚለው ቃል ቶሎ አሉታዊ (negative) ትርጉም የሚሰጠው ቢሆንም፣ ጳውሎስ ምን ለመናገር እንደፈለገ በትክክል ስንረዳ ግን፣ ይህ ክፍል ስለ ጭቆናንና በግዴታ ስለሆነ መረገጥ ጨርሶ እንደማያወራና ይልቁንም ለሚስቶችና ለባሎች፣ ለልጆችና ለወላጆች እንዲሁም ለባሮችና ለጌቶቻቸው እጅግ መልካምና በጎ የሆነን ቅን ምክር ያዘለ እንደሆነ እንገነዘባለን:: ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ሊል እንደፈለገ በጥንቃቄ ሳናጠናና ሳንመረምር አንድ ቃል ብቻ ይዘን ወደ መደምደሚያ ከመድረስ መቆጠብ ይገባናል::

 

በተጨማሪ በዚህ ክፍል የተዘረዘሩት ሶስቱም ግንኙነቶች የቤት ውስጥ የዕለት ተለት ኑሮን እንጂ በቤ/ክ ፕሮግራም ጊዜ የሚደረግን ነገር እንደማያመለክቱ መገንዘብ አለብን:: ባልና ሚስት፣ ልጆችና ወላጆች እንዲሁም ጌቶችና ባሮች በየዕለቱ በቤት የሚገናኙና አብረው የሚኖሩ ናቸው:: ስለዚህ እንደ ጌታ በሆነ የእርስ በርስ መልካም ግንኙነት መኖር ያለባቸው በቤተክርስቲያን ፕሮግራም ላይ በሰው ፊት ለታይታ ሳይሆን እቤታቸው በጌታ ፊት ነው::

 


 

1.              ሚስቶችና ባሎች 5፣22-33

 

ባልና ሚስት እርስ በርስ ሊኖራቸው ስለሚገባው የሃላፊነት ድርሻ/role የሚያብራራው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲጠና ብዙውን ጊዜ በሚያጠኑት ሰዎች ዘንድ የሚንጸባረቅ አንድ ክስተት አለ:: ይሄውም ገና ክፍሉ ከመጠናቱ በፊት ሴቶችና ወንዶች ለሁለት ተቃራኒ ለሆኑ ሃሳቦች መወገን (polarization) እና በሁለት ጎራ መከፈል ናቸው:: ገና ከመጠናቱ በፊት ብዙ ወንዶች ይህ ክፍል የአገራችንን ወይም በአብዛኛው በሶስተኛው ዓለም ያለውን የወንዶች በሴቶች ላይ ያላቸውን ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ የሚደግፍ ስለሚመስላቸው፣ ለዚያ ትልቅ ድጋፍና ማረጋገጫ እንዳገኙ አድርገው ይቆጥሩታል:: ብዙ ሴቶች ደግሞ ትክክለኛ አኗኗር ብለው የሚያምኑት በሴቶችና በወንዶች መካከል ምንም ዓይነት የደረጃ ተዋረድ የለም የሚለውንና በሰለጠነው ዓለም በብዛት የተለመደውን ሃሳብ ነው:: ስለዚህ ይህ ክፍል ሲጠና ብዙ ወንዶች የሶስተኛውን ዓለም ባሕል በመደገፍ፣ ብዙ ሴቶች ደግሞ ያንን በመጻረርና የሰለጠነውን ዓለም ባሕል በመደገፍ በሁለት ተቃራኒ ጎራዎች ይከፈላሉ:: እንዲህ ዓይነቱ ለሁለት ባሕሎች ቶሎ ብሎ የመወገን አዝማሚያ ትክክለኛ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስን ሃሳብ ለማየት እንዳንችል ያደርገናል:: ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ክፍል የሚናገረው የወንዶች ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ የሆነውን  የሶሰተኛውን ዓለም ባሕል እየደገፈ ነው? ወይስ በሴቶችና በወንዶች መካከል ምንም ዓይነት የደረጃ ወይም የሃላፊነት ድርሻ/role የለም የሚለውን የሰለጠነውን ዓለም ባሕል እየደገፈ ነው? በዚህ ክፍል ጳውሎስ ሊያብራራ የሚፈልገው ከሁለቱም ባሕሎች ጨርሶ የተለየና ሰማያዊ የሆነ የእግዚአብሔርን ሃሳብ ነው:: ስለዚህ ከሁለቱ የሰው ባሕሎች ወጥተን ጌታ ሊያሳየን የሚፈልገውን አዲሱንና ሶስተኛውን መንገድ ለማየት ልባችን መከፈት አለበት::

 

ሀ)ለሚስቶች የተሰጠ ምክር

 

·       ለባሎቻችሁ ተገዙ ቁ.22

·       እንዴት ነው መገዛት/መታዘዝ ያለባቸው?

       ለጌታ እንደምትገዙ ቁ. 22:- ይህም ማለት መታዘዛቸው ባል መልካም ሰው ስለሆነ ሳይሆን ጌታን በማክበር፣ ለጌታ የሚያደርጉት እንደሆነ በማሰብ “እንዲሁም፣ እናንተ ሚስቶች ሆይ፣ ከባሎቻችሁ አንዳንዱ ለትምህርት የማይታዘዙ ቢኖሩ፣ በፍርሃት ያለውን ንጹሑን ኑሮአችሁን እየተመለከቱ ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው ኑሮ እንዲገኙ ተገዙላቸው::” 1ጴጥ 3፣1-2

       ቤተክርስቲያን ለጌታ እንደምትገዛ ቁ. 24

 

·       ለመገዛት/ለመታዘዝ መሠረታዊ ምክንያቱ ምንድነው?

       ባል የሚስት ራስ ስለሆነ ቁ. 23:- ጳውሎስ ሚስቶች ለባሎቻቸው ለምን መገዛት/መታዘዝ እንዳለባቸው ሲያብራራ የሚሰጠው ምክንያት፣ የአይሁድ ባሕል ስለሆነ ወይም የተለመደ ስለሆነ የሚል አይደለም:: ነገር ግን “ክርስቶስ ደግሞ የቤተክርስቲያን ራስ እንደሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደሆነ ባል የሚስት ራስ ነው::” ቁ. 23 የሚል ነው:: ጳውሎስ በዚህ አባባሉ የሚያሳየው እንግዲህ ይህ የባሕል ጉዳይ ወይም የአመለካከት ጉዳይ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር በባልና በሚስት ግንኙነት ውስጥ የጾታ ድርሻ (gender role) እና የአሠራር ሥርዓት እንዳስቀመጠ ነው:: እግዚአብሔር እንዲህ አይነቱን የደረጃ ወይም የአሠራር ሥርዓት (order) ያስቀመጠው በባልና በሚስት ግንኙነት ብቻ አይደለም:: በዚያው በቁ. 23 ላይ እንደተጠቀሰው እንዲህ አይነቱ ሥርዓት በቤተክርስቲያንና በክርስቶስም መካከል ያለ ነው:: ይህም ብቻ አይደለም በእግዚአብሔርና በክርስቶስ መካከል እንኳን ይሄ ሥርዓት እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል:: “ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴትም ራስ ወንድ፣ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደሆነ ልታውቁ እወዳለሁ::” 1ቆሮ 11፣3:: ከዚህም በተጨማሪ የራሳችንን አካል ብንመለከት፣ ጭንቅላታችን የአካላችን ራስና መሪ እንዲሆን አድርጎ ያስቀመጠው እግዚአብሔር ነው:: ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር የክርስቶስ ራስ መሆኑ መልካም ነገር እንጂ ምንም መጥፎ ነገር እንደሌለው እንቀበላለን:: ክርስቶስም የቤተክርስቲያን ራስ መሆኑም ፈጽሞ በጎና ጥሩ ነገር እንጂ መጥፎ ነገር እንዳልሆነ እናምናለን:: በሰውነታችንም ያለው የጭንቅላታችን ራስ መሆን ላይም ምንም ጥያቄ የለንም:: ነገር ግን ልክ ይሄው አይነቱ የአሠራር ሥርዓት ወደ ባልና ሚስት ሲመጣ ብዙ ጊዜ እንደ በጎ ነገር ለመቀበል ይከብደናል:: ነገር ግን የራስና የአካል ሥርዓት በሌሎች ከላይ በተጠቀሱት ሁሉ እጅግ መልካምና በጎ እንደሆነ፣ ጨርሶም ጭቆናና ፈላጭ ቆርጭነት እንደሌለው ሁሉ፣ በባልና በሚስት እግዚአብሔር ያስቀመጠው የራስና የአካል ሥርዓትም እንዲሁ ከክፉ አገዛዝና ጭቆና ፈጽሞ የተለየ እጅግ መልካምና ፍጹም የሆነ ሥርዓት ነው:: ይሄንን ሃሳብ በተለይ ራስ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ወደ ታች ሄደን በተግባር ስንመለከተው፣ እግዚአብሔር ያስቀመጠው የአሠራር ሥርዓትና የጾታ ድርሻ እጅግ ግሩም እንደሆነ እንረዳለን:: እዚህ ላይ ግን ልብ ማለት ያለብን ይህ ሥርዓት ወይም የደረጃ ተዋረድ ያለው ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው ባላቸው ግንኙነት ውስጥ እንጂ በግል በእግዚአብሔር ፊት ባገኙት ድነትና ባላቸው ቦታ ሁለቱም እኩል እንደሆኑ መገንዘብ አለብን:: በክርስቶስ ባገኘነው ድነትና በሚጠብቀንም ውርስ በጌታ ፊት ሴትም ይሁን ወንድ እኩል ናቸው:: “በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና:: አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፣ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፣ ወንድም ሴትም የለም ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና:: እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ::” ገላ 3፣26-29:: ይህ ክፍል በእምነት የእግዚአብሔር ልጆችና በክርስቶስ ወራሾች በመሆን ረገድ ሴትና ወንድ ፍጹም እኩል እንደሆኑ ያሳያል:: ይህ ክፍል ግን በባልና በሚስት ስላለ ግንኙነት የሚያስረዳ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ስላለን ቦታ ነው:: በተቃራኒው አሁን እያጠናን ያለነው በኤፌ 5 ላይ የሚገኘው ክፍል ግን የሚያወራው ሴትና ወንድ በክርስቶስ ድነት ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ስላላቸው ቦታ ሳይሆን፣ በትዳር ውስጥ እርስ በርስ ሊኖራቸው ስለሚገባው ግንኙነት ነው:: ስለዚህ ሴትና ወንድ በክርስቶስ ባላቸው እምነትና የእግዚአብሔር ልጅነት፣ በሚጠባቃቸውም የዘላለም ውርስ በእግዚአብሔር ፊት ምንም አይነት ልዩነት የላቸውም:: በትዳር ውስጥ እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ግን እግዚአብሔር ያስቀመጠው የአሠራር ሥርዓት፣ የደረጃ ተዋረድና የጾታ ድርሻዎች አላቸው:: ይሄውም እግዚአብሔር ባልን የሚስት ራስ፣ ሚስትን ደግሞ የባል አካል አድርጎ ማስቀመጡ ነው::

 

·       በምን በምንድን ነው ለመገዛት/ለመታዘዝ ያለባቸው? - በሁሉ “ዳሩ ግን ቤተክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ በሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ::” ኤፌ 5፣24

 

·       ባልዋን ትፍራ ቁ. 33 to reverence, venerate, to treat with deference or reverential obedience (በአክብሮት አይን ማየት፣ ይህም እግዚአብሔር ለባል የሰጠውን የራስነትን ቦታ መቀበልና ለዚያ እውቅናን መስጠት ነው):: “እንዲሁም ሣራ ለአብርሃም:- ጌታዬ ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት...” 1ጴጥ 3፣6::

 

ለ)ለባሎች የተሰጠ ምክር

 

·       ሚስቶቻችሁን ውደዱ ቁ. 25

·       እንዴት ነው መውደድ ያለባቸው?

       ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን እንደወደዳት ቁ. 25-26

       እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል ቁ. 28

·       ክርስቶስ ለቤተክርስቲያን ያሳየው ፍቅር ምን ይመስላል?

       ራሱን አሳልፎ ስለ እርስዋ ሰጠ ቁ. 26

·       ራሱን የሰጠበት ዓላማ ምንድነው?

       በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ቁ.26:- ይሄ አባባል በጣም ግልጽ ባይሆንም፣ ነገር ግን ክርስቶስ ለቤተክርስቲያን ስለሚያደርግላት እንክብካቤ የሚያሳይ ነው:: አንድ ጊዜ በውኃ ክርስቲያኖች ስለሚጠመቁት ጥምቀት ይልቅ ክርስቶስ ሁልጊዜ በቃሉ ስለሚያደግላቸው የውስጥ መንጻት የሚያሳይ ይመስላል:: “እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ” ዮሐ 15፣3

       እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ ቁ. 27

·       እንደ ገዛ ሥጋው መውደድ ማለት ምን ማለት ነው?

       ራሱን እንደሚወደው ወይም እንደ ራሱ አድርጎ መውደድ “የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳይል ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና” ቁ. 28

       ክርስቶስ ለቤተክርስቲያን እንደሚያደርገው አይነት እንክብካቤ ባልም ለሚስቱ ማድረግ ማለት ነው “ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፣ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተክርስቲያን እንዳደረገላት ይመግበዋል ይንከባከበውማል::” ቁ. 30

    

መጽሐፍ ቅዱስ ባል የሚስት ራስ ነው ሲል፣ በአዕምሮአችን ቶሎ ብሎ የሚመጣው ምናልባት የጭቆና፣ በግድ የመግዛት፣ የማስመረር ወዘተ ሊሆን ይችላል:: ነገር ግን ባል የሚስት ራስ ነው ሲል በተግባር ሲተረጎም ምን ማለት እንደሆነ ከላይ በተዘረዘሩት ነጥቦች በሚገባ ያብራራል:: ከላይ እንደተዘረዘረው የባል ራስነትና ገዢነት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ሃሳብ ሚስትን አስጨንቆ መግዛት፣ ማማረር፣ መጨቆን ወዘተ ከሚሉት የሰው ሃሳቦች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም:: ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱስ ባልን እንደ ራስ ሲመለከት፣ ልክ ክርስቶስ በቤተክርስቲያን ላይ ያለውን የራስነት ቦታን በማሰብ ነው:: የዚህ አይነቱ ራስነት ዋና ባሕርይ ደግሞ ፍቅር ነው:: ክርስቶስ ራስ መሆንን በተግባር ያሳየው፣ ለቤተክርስቲያን ደህንነት ሲል ነፍሱን እንኳን አሳልፎ በመስጠትና ቤተክርስቲያን ነጽታና ተቀድሳ ያለ አንዳች እንከን እንድትሆን የሚገባውን እንክብካቤ ሁሉ በማድረግ ነው እንጂ ቤተክርስቲያንን በማስጨነቅ ወይም በኃይልና በግድ በመግዛት ወይም በዛቻና በማስፈራራት አይደለም:: በጳውሎስ መረዳት ራስነት ማለት እንደ ፊውዳል በሆነ የሥልጣን መንበር/ዙፋን ላይ ተቀምጦ ማዘዝና መገልገል ማለት ሳይሆን ይልቁንም ክርስቶስ ለቤተክርስቲያን ደህንነትና ጥቅም ሲል የሚያስፈልጋትን ሁሉ እያደረገ እንዳገለገላትና እግር እስከ ማጠብ ድረስ ዝቅ እንዳለ፣ ራስን ዝቅ አድርጎ ለሚስት ደህንነትና ጥቅም የሚገባውን እንክብካቤ ሁሉ ማደረግ ማለት ነው::

 

ክርስቶስ ለቤተክርስቲያን ነፍሱን እንኳን እስከ መስጠት ድረስ የሚያስፈልጋትን ሁሉ ሲያደርግላት በልቡ የነበረው ትልቅ ነገር የእርሷ ጉዳይ እንጂ ለእርሱ እንደ ራስነቱ የሚያገኘው ጥቅም አይደለም:: ፍቅር ስለሌላው ደህንነትና ጥቅም እንጂ ስለራስ ደህንነትና ጥቅም አይደለም የሚያስበው:: ኑኃሚንን ለመከተል በሞከሩት በሩትና በኦርፋ መካከልም ያለው ትልቁ ልዩነት ይሄ ነበር:: ኑኃሚን እርሷን ቢከተሉ ራሳቸውን ከመጉዳትና የወደፊት እድላቸውን  ከማበላሸት በቀር ምንም ጥቅም እንደማያገኙ በግልጽ ስትነገራቸው ኦርፋ በልቡዋ ከኑኃሚን ጉዳይ ይልቅ የራሷ ነገር ስላሳሰባት ወደ ዘመዶቿ ተመለሰች:: ሩት ግን ከራሷ ጉዳይና ጉዳት ይልቅ የኑኃሚን ችግርና መከራ ስለበለጠባት፣ ለራሷ ምንም ሳታስብ ኑኃሚንን ለመርዳት ተከትላት ሄደች ሩት 1፣1-18:: እውነተኛ ፍቅር ከራስ ይልቅ የሌላውን ያስባልና::

 

ስለዚህ እግዚአብሔር ክርስቶስን የቤተክርስቲያን ራስ ሲያደርገው ለቤተክርስቲያን እንክብካቤና ደህንነት እንደሆነ እንዲሁ ባል የሚስት ራስ መሆኑ እንደ እግዚአብሔር ሃሳብ ለሚስት መልካምና በጎ ነገር ነው:: የሚያስፈልጋትን ሁሉ ስለሚያደርግላት፣ የክርስቶስ ራስነት ለቤተክርስቲያን እጅግ ይጠቅማታል እንጂ አይጎዳትም:: ለአካል ስለሚያስብለትና የራሱን አካል ጨርሶ ስለማይጎዳ የጭንቅላታችንም በሰውነታችን ላይ ራስ መሆኑ ለአካል እጅግ ጠቃሚ ነገር ነው:: የባል ራስነትም እንዲሁ ለሚስት ትርፍና ጥቅም እንጂ ጉዳት መሆን የለበትም::

 

 

ሐ) የባልና የሚስት ሞዴል

ከላይ እንደተመለከትነው ጳውሎስ በዚህ ክፍል የሚገልጸው የባልና የሚስት ሞዴል በሶስተኛው ዓለም ከሚታየው የወንዶች አስከፊ አገዛዝ ወይም በሰለጠነው ዓለም ከተለመደው በባልና በሚስት መካከል ምንም ዓይነት የጾታ ድርሻ (gender role) እና የአሠራር ሥርዓት የለም ከሚለው አስተሳሰብ ሁሉ የተለየና ፍጹም ሰማያዊ የሆነን ነገር ነው:: በባልና በሚስት መካከል ያለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥርዓት እግዚአብሔር ያስቀመጠው ገና ከፍጥረት ነው:: “ስለዚህ ሰው አባትና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ቁ. 31:: በዚህ ክፍል ይተባበራል ተብሎ የተጠቀሰው ቃል፣ በዘፍ 2፣24 ላይ ይጣበቃል ተብሎ የተጠቀሰው ቃል ነው:: መጣበቅ ማለት cling, cleave, keep close. ሁለት ነገሮች በማስቲሽ ወይም በማጣበቂያ እንደማይለያዩ ሆነው መያያዝንና መጋጠምን የሚያመለክት ነው:: ከተጣበቁ በኋላ እነዚያ ነገሮች ሁለት መሆናቸው አቁሞ አንድ የሚሆኑበት ነው:: “ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም:: እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው::” ማቴ 19፣6:: ስለዚህ በእግዚአብሔር ዓይን ትዳር ሁለት ሰዎች አንዱ አንዱን እንደ ባዕድ እያየ፣ እየገፋና እያሳዘነ የሚኖርበት የፉክክር ሜዳ ሳይሆን፣ ባልና ሚስት እርስ በርስ እንደ ራሳቸው የአካል ክፍል እየተያዩ የሚተዛዘኑበትና የሚተባበሩበት እጅግ የጠበቀ ሕብረት ነው:: እግዚአብሔር አንድ ስላደረጋቸው ከእንግዲህ የወደፊት ዕድል ፈንታቸው ሁሉ የተቆራኘበት ሕብረት ነው:: የባል መከራና ውርደት የሚስትም መከራና ውርደት፣ የሚስትም መክበርና መደሰት የባልም መክበርና ደስታ የሚሆንበት ሕብረት ነው:: ባል ለሚስቱ የሚያደርገውም ለራሱ እንደሚያደርገው የሚቆጥርበት መልካም ሕብረት ነው:: “የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፣ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና” ቁ. 29:: ክርስቶስም እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም ነውር የሌለባት ያልተጎሳቆለች ቅድስትና ክብርት ቤተክርስቲያንን ማየት እንደሚፈልግ እንዲሁ ባሎችም የራሳቸው ሥጋ ስለሆነች ያልተጎሳቆለችና ደስተኛ ሚስትን ማየት መፈለግና ለዚያም የሚገባውን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል::

 

ሰው አባትና እናቱን ትቶ ከሚስቱ ጋር የሚፈጥረው አንድነት እጅግ የጠበቀና አንድ አካል የመሆን ነው:: በአዲሱ አካልም ባል የሚስት ራስ ሚስትም የባል አካል ናት:: “ይህ ምስጢር ታላቅ ነው፣ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተክርስቲያን እላለሁ::” ቁ. 32:: ጳውሎስ በዚህ ክፍል ምስጢሩን በሙሉ ያብራራው ባይመስለም፣ አንድ ግን ልብ ልንለው የሚገባው ነገር፣ በባልና በሚስት ያለው ወይም በክርስቶስና በቤተክርስቲያን ያለው ግንኙነት ከማንናቸውም ዓይነት ግንኙነቶች ሁሉ እጅግ የተለየና ሚስጥራዊ የእግዚአብሔር እጅ እንዳለበት ነው:: ይህ ዓይነቱ እጅግ የጠበቀና አንድ አካል የመሆን ሕብረት፣ ሲያሰኘን የምንጀምረውና ሳይመቸን የምናቆመው አይነት ሕብረት አይደለም:: ይህ አንድ አካል መሆን ስለሆነ፣ አካል እስከ ፍጻሜ ተያይዞ በአንድ የወደፊት ዕድል ፈንታ ሥር አብሮ የሚጓዝበት ሕብረት ነው:: እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን የክርስቶስ አካል ያደረጋት ለዘላለም ነው:: ለዘላለም የወልድ አካልና የገዛ ክፍሉ ናት:: የክርስቶስንም የዘላለም ዕድል ፈንታ ሁሉ ቤተክርስቲያን ትካፈላለች:: የክርስቶስን ውርደት፣ መከራ፣ እንዲሁም የዘላለም ክብሩንና መንግሥቱን ባጠቃላይ እግዚአብሔር ለክርስቶስ ያሰበለትን የዘላለም ዕድል ፈንታ ሁሉ ትካፈላለች:: ይህ ከድነት ወይም እንደ ብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ ብቻ ከመሆን ሁሉ ያለፈና የእግዚአብሔር ልጅ አንድ ክፍል የመሆንና ከወደፊት ዕድል ፈንታው ጋር የመቆራኘት እጅግ የሚያስደንቅ የእግዚአብሔር ሥራ ነው:: ባልና ሚስትም እንዲሁ እስኪሞቱ ድረስ በምድር ኑሮአቸው ሁሉ ዕድል ፈንታቸው የተሣሰረ አንድ አካል ናቸው:: በአንድ አካልም ብልቶች የሚገባቸውን ተግባር እንደሚፈጽሙ እንዲሁ ባልም እንደ ራስ ሚስትም እንደ አካል የሚገባቸውን ተግባር ሊያከናውኑ ይገባቸዋል::


“ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ።“
(መጽሐፈ ምሳሌ 3:3-4)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us