ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች » ኤፌሶን » ጥናት 21 (ኤፌሶን 5፣21-6፣9 ለ) በክርስቶስ ፍርሃት መገዛት - ክፍል 2
Email this page to a friend Printer-friendly   Tuesday, 20 October 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦“
(የዮሐንስ ራእይ 3:14)

rss

Today's verse

ጥናት 21 (ኤፌሶን 5፣21-6፣9 ለ) በክርስቶስ ፍርሃት መገዛት - ክፍል 2

pdf version

ይህን “በክርስቶስ ፍርሃት መገዛት” ብለን የሰየምነውን ጥናት በ3 ክፍሎች ከፍለን ማጥናት ጀምረናል:: ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌ 5፣21 ላይ “ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ” በማለት ነው ለዚህ ለምናጠናው ክፍል መሪ ሃሳቡን የገለጸው:: እስከ ኤፌ 6፣9 ድረስ በዚህ መሪ ሃሳብ ሥር ጳውሎስ ሦስት ዓይነት ግንኙነቶችን ያብራራል:: እነዚህም:-

 

1.              ሚስቶችና ባሎች 5፣22-33

2.              ልጆችና ወላጆች 6፣1-4

3.              ባሮችና ጌቶች 6፣5-9

 

ባለፈው ጥናታችን ላይ ቁ. 1ን የተመለከትን ሲሆን፣ በዚህ በክፍል ሁለት ጥናታችን ደግሞ ቁ. 2ን እና 3ን እንመለከታለን::

 

2.ልጆችና ወላጆች 6፣1-4

 

ሀ)ለልጆች የተሰጠ ምክር

·       ለወላጆቻችሁ ታዘዙ ቁ.1

·       እንዴትና ለምን?

       በጌታ ታዘዙ ቁ. 1:- ልጆች ለወላጆቻቸው እንዲታዘዙ የሚመከሩት እንዲሁ ቁጣንና ቅጣትን በመፍራት ሳይሆን፣ ጌታን ደስ የሚያሰኘው ስለሆነ፣ ስለ ጌታ ሲሉ እንዲታዘዙ ነው:: ልጆች እንግዲህ ስለ ጌታ ብለው ለወላጆቻቸው እንዲታዘዙ ታዲያ ጌታን በትክክል እንዲያውቁና በግልም ከጌታ ጋር ሕብረት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል:: በዚህም ረገድ መርዳት የወላጆች ኃላፊነት ነው::

       “መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትና እናትህን አክብር” እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት ቁ.2-3:- ይህን ጥቅስ ጳውሎስ የወሰደው ከብሉይ ኪዳን ነው (ዘጸ 20፣12):: ሃሳቡም አባትና እናትን የማክበር ትእዛዝ ከዓሥርቱ ትእዛዛት አንዱ ሲሆን፣ ይህ ትእዛዝ ደግሞ ትእዛዝ ብቻ ሳትሆን ለሚታዘዙ ሁሉ የተስፋ ቃልንም ያዘለ ትእዛዝ ነው:: ይሄውም “ዕድሜህ በምድር ላይ እንዲረዝም” የሚል ተስፋ አብሮ የያዘ ነው:: ስለዚህ አባትና እናትን ማክበር ከብሉይም ጀምሮ እግዚአብሔር የሚወደውና የሚፈልገው ጉዳይ ነው:: የተስፋ ቃልንም አብሮ ያዘለ ስለሆነ ልጆችም በደስታ እንዲታዘዙ የሚያነቃቃ ነው:: ሕጉ ልጆችን ከማስፈራራት ይልቅ የሚያነቃቃ፣ የሚያበረታታና የሚያደፋፍር ነው:: ይሄ ክፍል በሕብረት ሲጠና ተደጋግሞ የሚነሳ ጥያቄ አለ:: ይሄውም ታዲያ ወላጆቻቸውን በሚገባ ቢያከብሩም እንኳን ዕድሜአቸው ግን ሳይረዝም በአጭሩ የሚቀጩም ሰዎች አሉ፣ ይህ ለምን ይሆናል የሚል ነው:: እዚህ ላይ ግን መሠረታዊ ሕጎችንና የእያንዳንዱን ሰው የሕይወት ታሪክና ሂደት ለያይተን ማየት አለብን:: ሰዎች በግል የሚደርስባቸውን ማናቸውንም የሕይወት ገጠመኝ ሁሉ በአንድ መሠረታዊ ሕግ ለመተርጎም ከሞከርን ትልቅ ችግር ውስጥ እንገባለን:: ለምሳሌ በዮሐ 9፣1-3 ከመወለዱ ጀምሮ ዕውር የነበረውን ሰው የጌታ ደቀመዛሙርት ሲያዩ ወዲያው ጌታን የጠየቁት ጥያቄ ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ያደረገው የማን ኃጢአት ነው? የሚል ነው:: በእነርሱ አስተሳሰብ አንድ የሚያውቁት መሠረታዊ ሕግ አለ:: ይሄውም በሰው ላይ ክፉ ነገር የሚደርሰው ራሱ ወይም ወላጆቹ ከሠሩት ኃጢአት የተነሣ ነው የሚል ነው:: ይህ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ነው:: ሆኖም ግን የእያንዳንዱን ግለሰብ የሕይወት ገጠመኝን ሁሉ በዚህ ሕግ ለመተርጎም መሞከር ትልቅ ስህተት ነው:: ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው እኛ የማናውቀውና እግዚአብሔር ብቻ የሚያውቀው የራሱ ምክንያትና ታሪክ አለው:: በዮሐንስ ወንጌል ላይም የተጠቀሰው ሰው እውር ሆኖ እንዲወለድ ምክንያት የሆነው እግዚአብሔር ብቻ የሚያውቀው የራሱ የሆነ ምክንያት ነበረው:: ይሄውም የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም:: ስለዚህ አንድን መሠረታዊ ሕግ ወስደን በዚያ ብቻ የእያንዳንዱን የግለሰብ ሕይወት ከመተርጎም መቆጠብ ይኖርብናል::

 

ለ)ለአባቶች የተሰጠ ምክር

·       በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው ቁ. 4:- ይሄን ምክር ባጠቃላይ ወላጆችን በተለይም አባቶችን የሚመለከት:: ይህም በልጆች አስተዳደግ ላይ በተለይ አባቶች ሊጫወቱት የሚገባውን ከፍተኛ ሚና ያመለክታል:: የቤቱ ራስ እንደመሆናቸው አባቶች ልጆቻቸው ጌታን የሚያውቁና እግዚአብሔርን የሚታዘዙ ሆነው እንዲያድጉ ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው:: ከላይ እንደገለጽነው ልጆች ስለ ጌታ ብለው ወላጆቻቸውን እንዲታዘዙ በመጀመሪያ ደረጃ በግላቸው ጌታን ሊያወቁት ይገባል:: ይህ እንዲሆን ደግሞ ወላጆች በተለይም አባቶች በጌታ ምክርና ተግሳጽ የማሳደግ ኃላፊነት አለባቸው:: በቁጣና በኃይል ልጆችን ማስቆጣቱና ማስመረሩ ልጆች ከወላጆች ልባቸው እንዲርቅ ያደርጋል፣ አመጸኛም እንዲሆኑ ይገፋፋል:: በእውነት ከልባቸው ነገሮችን እንዲያደርጉ የጌታ ምክር በልባቸው ሊቀረጽ ይገባል:: ይህ ሥራ ምንም እንኳን እጅግ ከባድ፣ ብዙ ጥበብና ዲስፕሊን የሚጠይቅ ሥራ ቢሆንም፣ እግዚአብሔር ግን የልጆችን መልካም አስተዳደግ እንደ ዋና ነገር ከወላጆች የሚፈልገው ነገር ነው:: በዚህ ምክንያት ከእግዚአብሔር ምስጋና ያገኙ እንደ እነ አብርሃም ያሉ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሰዋል “ጽድቅንና ፍርድን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤቱን እንዲያዝዝ አውቃለሁና ይህም እግዚአብሔር በአብርሃም ላይ የተናገረውን ነገር ሁሉ ያመጣ ዘንድ ነው::” ዘፍ 18፣19:: በተቃራኒውም ካህኑ ዔሊ በልጆቹ መጥፎ ሥነ ምግባር ምክንያት እግዚአብሔር ሲነቅፈውና ሲፍርድበትም በመጽሐፍ ቅዱስ እንመለከታለን 1ሳሙ 2፣12-36:: ስለዚህ ልጆች የጌታን ምክር ተረድተውና በልባቸውም አምነውበት በዚያ ምክር እንዲያድጉ፣ ወላጆች በተለይም አባቶች ልጆቻቸውን የጌታን ቃል የማስተማር፣ የማስረዳትና የመምከር ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው::

 

3.ባሪያዎችና ጌቶች 6፣5-9

ጳውሎስ ይህን መልእክት በጻፈበት ዘመን በሮማውያን ግዛት ውስጥ በጣም ብዙ ባሪያዎች ነበሩ:: በአንድ ባሪያና በጌታው መካከል የነበረው ግንኙነትም፣ ጌታው እንደፈለገ እየጨቆነና እየረገጠ ባሪያውን ይገዛዋል፣ ባሪያው ደግሞ የሚያደርገውን ሁሉ በጌታው ፊት ካልሆነ ከልቡ አያደርገውም:: ጌታው በማያየው ጊዜ ማልመጥ ባሪያው ጌታውን የሚበቀልበት ብቸኛ መንገድ ነበር:: በዚህ ክፍል በጳውሎስ የተሰጠው መመሪያ በጊዜው የነበረውን የባሪያ ሥርዓተ ማኅበርን በአመጽ የሚቀይር ሳይሆን፣ ወደ ጌታ የመጡትን የባሮችንና የጌቶችን ግንኙነት መልካም በማደረግና ከጠላትነት ግንኙነት ይልቅ ወደ እርስ በርስ የመጠቃቀምና የመተሳሰብ ግንኙነት በመለወጥ የባሪያ ሥርዓቱን የሚሸረሽርና የሚያዳክም ነው::

 

ሀ)ለባሪያዎች የተሰጠ ምክር

·       ጳውሎስ በዚህ ክፍል ባሪያዎች እንዲከተሉት የሚመክራቸው አንድ መሠረታዊ መርህ (principle) አለ:: ይሄውም ባሪያዎች ከበላያቸው ምድራዊ ጌታ እንደሌለ እንዲቆጥሩና የሚያደርጉትንም ሁሉ እንደ ክርስቶስ ባሪያ ለእግዚአብሔር እንዲያደርጉት ነው የሚመክራቸው “ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ...” ቁ. 5 “የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች...” ቁ. 6 “ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምትገዙ...” ቁ. 7:: ስለዚህም የሚያደርጉትን ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የክርስቶስ ባሪያ ስለሚያደርጉት አንደኛ በልዩ ጥንቃቄና በልብ ቅንነት እንዲያደርጉት (“...በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ በልባችሁ ቅንነት ለጌቶቻችሁ ታዘዙ” ቁ. 5)፣ ሁለተኛ በማልመጥና ለታይታ ባልሆነ ሁኔታ እንዲያደርጉት(“...ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ” ቁ. 6)፣ በመጨረሻም በትጋትና በበጎ ፈቃድ እንዲገዙ እንጂ በግድ እንደሚገዙ እንዳያስቡ ይመከራሉ (“...በትጋትና በበጎ ፈቃድ ተገዙ”) ቁ. 7:: ምክንያቱም ጌታን እያዩ ለጌታ ብለው ለሰው የሚያደርጉትን መልካም ነገር ሁሉ ጌታ ስለሚቆጥርላቸው ነው “ባሪያ ቢሆን ወይም ጨዋ ሰው [ባሪያ ያልሆነ ነጻ ሰው]፣ እያንዳንዱ የሚያደርገውን መልካም ነገር ሁሉ ከጌታ በብድራት እንዲቀበለው ታውቃላችሁና” ቁ. 8:: ባሪያዎች እንግዲህ ይህን መርህ ወይም መመሪያ ከተከተሉ የሚሠሩት ሁሉ የዘላለም ፍሬ ስለሚያፈራና ለእነርሱ የሚጠቅም ስለሆነ ሥራቸውን ያቀልልላቸዋል፣ ሁለተኛ በቅንነትና ለጌታ ብለው ለሰው መልካም ስለሚያደርጉ ጌታ የሚቀበለው ሥራ ይሆናል፣ በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ በሥጋ ጌታቸው የሆኑት ደግሞ በደንብ ስለሚገለገሉ ይደሰታሉ ይጠቀማሉም ዘፍ 39፣1-6::

 

ለ)ለጌቶች የተሰጠ ምክር

·       እንዲሁ አድርጉላቸው ቁ. 9:- ምድራዊ ጌታ የሆኑትም የሚመከሩት ልክ ለባሪያዎቹ የመከራቸውን መሠረታዊ መርህ (principle) እንዲከተሉ ነው:: ዛቻና ማስፈራራትን ትተው ለባሪዎቻቸው ለጌታ ብለው መልካም እንዲያደርጉላቸው ይመከራሉ “እናንተም ጌቶች ሆይ፣ ዛቻውን ትታችሁ እንዲሁ አድርጉላቸው...” ቁ. 9:: ምክንያቱም መልካም ያደረገ መልካም፣ ክፉም ያደረገ ክፉ መቀበል የሚለው መርህ በጌታ ዘንድ ለባሪያ ቢሆን ወይም ለጨዋ እንደሚሠራ ያሳስባቸዋል “...በእነርሱና በእናንተ ላይ የሚገዛው ጌታ በሰማይ እንዳለ ለሰው ፊትም እንዳያደላ ታውቃላችሁና” ቁ. 9:: ኢየሱስ ክርስቶስ የባሪያዎችም የጌቶችም ጌታ ነውና:: ጌቶች እንግዲህ እንደ ባሪያዎች ይህን መርህ ቢከተሉ አንደኛ ለጌታ ብለው ለባሪያዎቻቸው መልካም ስለሚያደርጉና የዘላለም ፍሬ ስለሚያፈራላቸው ራሳቸው ይጠቀማሉ፣ ሁለተኛ ይህ መልካም ሥራቸው በጌታ ፊት ተቀባይነት ያገኛል፣ በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ባሮቻቸው ይጠቀማሉ::

 

ሐ)ማጠቃለያ

ባሪያዎችም ጌቶችም ይህንን የክርስትናን መርህ ከተከተሉ፣ እርስ በርስ በመጎዳዳት እና እንደ ጠላት በመተያየት ላይ የተመሠረተው የባርነትን አገዛዝ፣ ወደ ወንድማማች መጠቃቀምና መተሳሰብ ይለወጣል:: ስለዚህ ይህ ምክር የባሪያ ሥርዓተ ማኅበርን የሚያጠናክር ሳይሆን እንዲያውም የሚሸረሽርና የሚያዳክም ነው:: በመጨረሻም በአሁኑ ዘመን ምንም እንኳን የባሪያ ሥርዓተ ማኅበር ባይኖርም፣ ይህንን መርህ በአሠሪና በሠራተኛ መካካል ላለው ግንኙነት ልንጠቀምበት ይገባናል:: ነገርን ሁሉ ለሰው ሳይሆን እንደ ክርስቶስ አገልጋዮች ለእግዚአብሔር ብለን በቅናነት ብናደርግ፣ ከጌታ ብድራታችንን እንቀበላለን፣ ሠራተኛም እንሁን አሠሪ::


“ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ።“
(መጽሐፈ ምሳሌ 3:3-4)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us