ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች » ኤፌሶን » ጥናት 22 (ኤፌሶን 6፣10-24) የእግዚአብሔር ጦር ዕቃ
Email this page to a friend Printer-friendly   Tuesday, 20 October 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦“
(የዮሐንስ ራእይ 3:14)

rss

Today's verse

ጥናት 22 (ኤፌሶን 6፣10-24) የእግዚአብሔር ጦር ዕቃ

pdf version

ይህ ዛሬ የምናጠናው ክፍል የኤፌሶን መልእክት የመጨረሻ ሃስብንና የመልእክቱን መደምደሚያ የያዘ ነው:: እንደሚከተለውም ከፍለን እናጠናዋለን:-

 

1.              የእግዚአብሔር ጦር ዕቃ 6፣10-20

2.              መደምደሚያ 6፣21-24

 

1.              የእግዚአብሔር ጦር ዕቃ

ጳውሎስ በዚህ መልእክቱ መጨረሻ ላይ የሚያስተላልፈው መልእክት በመንፈስ ስለ መበርታትና ስለ መጠንከር ነው:: “በቀረውስ [በተረፈ] በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ” ቁ. 10::

 

·       መበርታት/መጠንከር

የአንድ ነገር ብርታት ወይም ጥንካሬ የሚለካው በሚቋቋማቸው ማንኛውም ዓይነት ውጪያዊ ግፊቶችና ፈተናዎች ነው:: ብረት ከሸንበቆ መጠንከሩ የሚታወቀው በቀላሉ የማይሰበርና ከሸንበቆ ይልቅ ብዙ ውጪያዊ ግፊቶችን መቋቋም በመቻሉ ነው:: ጳውሎስም በዚህ ክፍል የሚናገረው ብርታት ውጪያዊ ግፊቶችንና ፈተናዎችን ተቋቁሞ ለመቆም ስለሚያስችል የውስጥ መንፈሳዊ ጥንካሬ ነው:: ይህም ደግሞ በሰው ብርታትና ትግል ወይም ጥረት የሚገኝ ሳይሆን ብርቱ ከሆነው ከጌታ ከራሱ የሚገኝ የጌታ የራሱ ብርታትና ጥንካሬ ነው:: “በተረፈ በጌታና ብርቱ በሆነው ኃይሉ ጠንክሩ” ቁ. 10 (አዲሱ መደበኛ ትርጉም/አ.መ.ት)::

 

·       የመንፈሳዊ ትግል/ውጊያ ምንነት

ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊ ጥናካሬና ብርታት ሲናገር መንፈሳዊ ትግልን በማሰብ ነው:: “መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፣ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ሥፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ::” ቁ.12:: ጳውሎስ በዚህ ክፍል “መጋደላችን” ብሎ የጠቀሰው ቃል በእንግሊዝኛው wrestling ተብሎ የተተረጎመ ቃል ነው:: ይህም የኤፌሶን መልእክት በተጻፈበት ዘመን አንባቢዎቹ በቀላሉ የሚረዱትና የሚያውቁት የትግል አይነት ነው:: ትግሉም በሁለት ሰዎች መካከል የሚደረግ ሲሆን፣ አንዱ ሌላውን መሬት ላይ ለመጣል የሚደረግ ግብግብ ነው:: አሸናፊ የሚሆነውም ተጋጣሚውን መሬት ላይ ጥሎ እጁን በተጋጣሚውን አንገት ላይ ወደታች መያዝ የቻለ ነው:: ስለዚህ በትግሉ ላለመሸነፍ ከተጋጣሚው የሚመጣውን ማናቸውም አይነት የመጣል ሙከራ ተቋቁሞ ሳይወድቁ ጸንቶ መቆሙ እጅግ አስፈላጊ ነው:: ይህ ደግሞ ብርታትንና ጥንካሬን የሚጠይቅ ነገር ነው::

 

ጳውሎስ በዚህ ክፍል እንግዲህ መንፈሳዊ ብርታትና ጥንካሬን ከመንፈሳዊ ትግል ጋር አያይዞ ነው የሚጠቅሰው:: ልክ በዚያን ዘመን በሁለት ተጋጣሚዎች መካከል እንደ ነበረ በክርስትናም ሕይወት መንፈሳዊ ትግልና ውጊያ እንዳለና ለዚያም መጠንከርና መበርታት እጅግ አስፈላጊ ነው:: ትግሉ በመድከምና በመዛል የምንወጣው ሳይሆን በጌታ በሆነው ኃይል በመበርታትና በመጠንከር በመጽናትም ድል የሚገኝበት ነው::

 

·       መንፈሳዊ ትግል/ውጊያ ከማን ጋር?

“መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፣ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ሥፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ::” ቁ.12:: የአማኞች ትግል ወይም ውጊያ ሥጋና ደምን ማለትም ሰዎችን በመቃወም ከሰዎች ጋር የሚደረግ ግብግብ ሳይሆን በመንፈስ በመንፈሳዊው ዓለም ካሉ የጨለማ ኃይላት ወይም የሰይጣን ጭፍራዎች ጋር የሚደረግ ግጥሚያ ነው:: ስለዚህም የትግሉ ይዘት፣ ትጥቁም፣ ዘዴውም ሁሉ መንፈሳዊ እንጂ በሥጋዊ ትጥቅና ዘዴ ድል የሚገኝበት ውጊያ አይደለም:: በዚህ ክፍል ጳውሎስ የአማኞችን ጠላቶች ሲዘረዝር “አለቆች፣ ሥልጣናት፣ ገዦች እና ሠራዊት” የሚሉትን ቃላት በመጠቀም ነው:: ይህም ልክ እንደ ማንኛውም ምድራዊ የጦር ሠራዊት በጨለማውም ዓለም ውስጥ የሥልጣንና የደረጃ ተዋረድ እንዳለ ያሳየናል:: የጨለማው ሠራዊት ሁሉ ዋና መሪና አለቃም ዲያብሎስ ራሱ ነው::

 

·       የመንፈሳዊ ትግል/ውጊያ ዓላማና ግብ

“የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ::” ቁ. 11:: “ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፣ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ::” ቁ. 13:: በቁ. 11 እና በቁ. 13 ላይ ጳውሎስ  በመንፈሳዊ ትግል/ውጊያ ውስጥ የአማኞች ዓላማና ግብ ምን እንደሆነ በግልጽ ያስቀምጥልናል:: በቁ. 11 ላይ ስለ መጨረሻ ግቡ ሲጠቅስ “ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ” ይላል:: በቁ. 13 ደግሞ “በክፉው ቀን ለመቃወም” እና “ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ” በማለት በትግሉ/በውጊያው ውስጥ የአማኞች የመጨረሻ ግብ ምን እንደሆነ ይገልጻል:: ይሄ በሁለቱም ክፍሎች በአማርኛው ትርጉም “ትቃወሙ ዘንድ” እና “ለመቃወም” ተብሎ የተተረጎመው ቃል በብዙዎቻችን ዘንድ ፈጽሞ በተሳሳተ ሁኔታ የተረዳነው ቃል ነው:: በአማርኛው ትርጉም እንደ “መቃወም” ስለተተረጎመ ብዙዎቻችን ይሄንና ተመሳሳይ ክፍሎችን ስናነብ ወደ አዕምሮአችን የሚመጣልን ነገር መገሠጽ የሚለው መረዳት ብቻ ነው:: ስለዚህም በተመሳሳይ ሁኔታም በ1ኛ ጴጥ ላይ ያለውን “ዲያብሎስን... ጸንታችሁ በእምነት ተቃወሙት” 1 ጴጥ 5፣9 የሚለውንና ከያዕቆብ መልእክት ብዙ ጊዜ የሚጠቀሰውን “...ዲያብሎስን ግን ተቃወሙት ከእናንተም ይሸሻል...” ያዕ 4፣7 የሚሉትን ጥቅሶች ስናነብ ቶሎ ብሎ የሚገባን፣ ክፍሎቹ ስለ መገሠጽ እንደሚናገሩ ነው:: በዚህ በምናጠናው የኤፌሶን መልእክት ላይም ይሁን በ1ኛ ጴጥሮስና በያዕቆብ መልእክትም ላይ ስለመቃወም የሚናገሩት ክፍሎች ጨርሶ ስለ መገሠጽ የሚያወሩ አይደሉም:: ጸሐፊዎቹ እነዚህን ክፍሎች ሲጽፉ አሁን በአበሻ አማኞች ዘንድ ልማድ እንደሆነው በኢየሱስ ስም እያሉ ሰይጣንን ስለ መገሠጽ ለመናገር ፈልገው አይደለም:: እንዲህ አይነቱ የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ማለትም አሁን ከሁለት ሺህ ዓመታት በኋላ ያለንን የእኛን ልምምዶች ወደ መጽሐፍ ቅዱሱ ውስጥ በግድ ማስገባት ብዙ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና የሚያስቸግረን ነገር ነው:: ጸሐፊዎቹ ግን እነዚህን ክፍሎች በሚጽፉበት ወቅት “መቃወም” ተብሎ በአማርኛ በተተረጎሙት ክፍሎች ሁሉ አንድም ቦት አሁን በአበሻ አማኞች ዘንድ ልማድ የሆነውን መገሠጽን ጨርሶ ማለታቸው አይደለም::

 

ስለዚህ የጥንቱን የቃሉን ምንነትና ጸሐፊዎቹም በዚያ ሊያስተላልፉት የፈለጉትን መልእክት በሚገባ መረዳቱ በመንፈሳዊ ትግል/ውጊያ ውስጥ ድል ለመንሣት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው:: በዚህ በምናጠናው በኤፌ 6፣11 ላይ “ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል በግሪኩ histemi የተባለው ቃል ነው:: ይህም ጸንቶ መቆምን በእንግሊዝኛውም able to stand የሚለው ትርጉም ያለው ሲሆን፣ ሃሳቡም ጽኑነትን (steadfastness) የሚያመለክት ነው:: ሳይወድቁና ሳይንገዳገዱ ጸንቶ መቆምን ያሳያል::

 

በኤፌ 6፣13 ፣ በ1ኛ ጴጥ 5፣9 እና በያዕ 4፣7 በአማርኛው ትርጉም ስለ መቃወም የሚናገሩት ክፍሎች በሙሉ ከግሪኩ anthistemi ከሚለው ቃል የተተረጎሙ ናቸው:: ይህም ቃል anti እና histemi የሚሉትን ቃላት የያዘ ነው:: anti መጻረርን ወይም መቃረንን የሚያመለክት ሲሆን ይህም በእንግሊዝኛው against ማለት ነው:: histemi የሚለው ቃል ከላይ የተመለከትነው ጸንቶ መቆምን የሚያሳየው ቃል ነው:: anthistemi የሚለው ቃል ትርጉሙ እንግዲህ የአንድ ነገር ተጻራሪ ወይም ተቀናቃኝ ሆኖ መቆመን ወይም በእንግሊዝኛው አንድን ነገር resist ወይም withstand ማድረግን የሚያመለክት ነው:: የሁለቱም ቃላቶች ዋና ይዘት ለመጣል ከውጭ የሚመጣ አንድን ግፊትና ፈተና ተቋቁሞ ሳይወድቁ ጸንቶ መቆምን የሚያሳዩ ናቸው:: ስለዚህ “መቃወም” ከሚለው ቃል ይልቅ “ጸንቶ መቋቋም” የሚለው ቃል የበለጠ የግሪኩን ቃል ይዘት ይገልጠዋል:: ስለዚህም ኤፌ 6፣11ን እና ኤፌ 6፣13ን አ.መ.ት “መቋቋም” የሚለውን ቃል በመጠቀም ነው የሚተረጉመው::

 

የአማኞች መንፈሳዊ ትግል/ውጊያ የመጨረሻ ግብ ምን እንደሆነ የሚያመለክተው ሌላው ቃል ያለው እዚያው በኤፌ 6፣13 ላይ ነው:: በዚያም “ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ” የሚል ዓ/ነገር እናገኛለን:: ይሄም ክፍል ከውጊያው/ከትግሉ መጨረሻ ላይ ተሸንፎና ወድቆ ሳይሆን ሳይወድቁ ቆሞ መገኘትን የሚያሳይ ነው::

 

ከላይ በዘረዘርናቸው ክፍሎች ሁሉ እንግዲህ በመንፈሳዊ ውጊያ/ትግል የአማኞች የመጨረሻ ግብ ሰይጣንና በሰማያዊ ሥፍራ ያሉትን ጭፍሮቹን ሁሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ደምሶሶ ለማጥፋት ሳይሆን ወይም በየጸሎቱ ሁሉ ሰይጣንን ለመገሰጽ ብቻ ሳይሆን፣ ሰይጣን አማኞችን ለመጣልና ከጌታ መንገድ ለማውጣት የሚያደርገውን ተንኮልና ዘዴ፣ ፈተናና ግፊት ተቋቁሞ መጽናትና ሳይወድቁ መቆም ነው:: “የዲያብሎስን የተንኮል ሥራ [ሽንገላ] መቋቋም ትችሉ ዘንድ...” ኤፌ 6፣11 አ.መ.ት:: የውጊያው ማዕከላዊ ነገር ያለው እንግዲህ መከላከል ላይ ነው:: ልክ በዚያን ዘመን ይታወቅ እንደነበረው የትግል ውድድር (wrestling) በተጋጣሚው ሳይወድቁ ጸንቶ ለመቆምና ላለመሸነፍ የሚደረግ ግብግብ ነው:: ዲያቢሎስ የሚያመጣውን የተንኮል ሃሳብ፣ ዘዴና ፈተና እንቢ ብሎ በጌታ መንገድ ላይ መጽናቱ ነው ዋናው ድል:: ይሄ ሳይሆን ግን በጸሎት ጊዜ ብቻ በመገሠጽ ፈተናውን እሸናፊዎች ነን ማለት ራስን ማታለል ነው:: ብዙ አማኞች ዲያብሎስ በሕይወታቸው የሚያመጣውን የኃጢአት ፈተና፣ ወንድምን የመጥላት ፈተና፣ የትዕቢት ፈተና፣ ሥጋዊ ክብርንና ዝናን የመፈለግ ፈተና፣ ገንዘብን የማምለክ ፈተና፣ ቂም የመያዝን ፈተና ወዘተ ሁሉ እምቢ ብለው በሕይወታቸው ሳይቋቋሙ በቤተክርቲያን ፕሮግራም ላይ ግን ሰይጣንን በመገሠጽ አንደኛ ናቸው:: ይሄ ግን መቃወም አይደለም:: ሰይጣን ባመጣው የተንኮል ፈተና በሕይወት ወድቆና ተሸንፎ በፕሮግራም ላይ መገሰጽ ብቻ በጠላት በታላቅ ሁኔታ መታለልንና የመንፈሳዊ ውጊያን ምንነት ጨርሶ አለመረዳትን የሚያሳይ ነው::

 

ስለዚህ መንፈሳዊ ውጊያ/ትግል የሚካሄደውና ጠላትም ድል መደረግ ያለበት በዋናነት በዕለት ተለት ሕይወት ሰይጣን በሚያመጣው ፈተናና ተንኮል ላይ ነው::

 

·       የመንፈሳዊ ትግል/ውጊያ ሥልቶች

የአማኞችን የመንፈሳዊ ውጊያ ሥልት ከማየታችን በፊት ትንሽ የዲያቢሎስን እንመልከት:: በቁ. 11 ላይ “የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ [ትቋቋሙ] ዘንድ እንዲቻላችሁ...” የሚል ቃል እናገኛለን:: ሽንገላ ማለት በማታለልና በማደናገር የሚደረግ ክፉ ሥራ ነው:: ውስጡ ብልሃት ያለው ቢሆንም ክፉ ሥራ ለመሥራትና ለመጉዳት የተውጠነጠነ ብልሃት ነው:: ልክ እባብ ሔዋንን በተንኮል እንዳሳታት አይነት ማለት ነው:: ውስጡ ማታለል፣ ውሸትና ተንኮል ያዘለ ለመጉዳት የሚደረግ መሠሪ ሥራ ነው:: በዘፍ 2፣1 ላይም ስለ እባብ “እባብም እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠረው ከምድር አውሬ ሁሉ ይልቅ ተንኮለኛ ነበረ::” የሚል እናገኛለን:: ስለዚህ ከጥንት ጀምሮ የነበረውና ጌታንም የፈተነበት ዋናው የሰይጣን መሣሪያ መዋሸት፣ ማታለል፣ በዘዴ ማሳት፣ መሸንገል፣ በብልሃት መጥለፍ ወዘተ የመሳሰሉት ናቸው:: ጳውሎስም በዚህ ክፍል የሚናገረው ይሄንን ተቋቁሞ ማለፍን ነው:: “የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ [ትቋቋሙ] ዘንድ እንዲቻላችሁ...” ቁ. 11::

 

አማኞች እንግዲህ ይህንን የዲያብሎስን ውሸት፣ ተንኮልና ማታለል ድል መንሳት የሚችሉት በራሳቸው ወይም በሰይጣን ትጥቅና ዘዴ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ በመልበስ ነው:: “የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ [ትቋቋሙ] ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ::” ቁ. 11:: “ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም [ጸንቶ ለመቋቋም]፣ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ::” ቁ. 13:: አማኞች እንግዲህ እንደ መፍትሔና እንደ ውጊያ ትጥቅና ሥልት የተሰጣቸው ከእግዚአብሔር የሆነ የጦር ዕቃ ነው:: የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር በሙሉ (God's whole/complete armor) አንድም ሳይቀር ከላይ እስከ ታች ድረስ መልበስ ያስፈልጋል:: ያለ እግዚአብሔር የጦር ትጥቅ ግን በሥጋዊ አሠራርና ዘዴ ወይም በመገሠጽ ብቻ ሰይጣንን ተቋቁሞ ሳይወድቁ ጸንቶ ለመቆም አይቻልም:: ሰይጣን ውሸት ሲጠቀም እኛም ውሸት እየተጠቀምን፣ ሲያታልል እኛም እያታለልን፣ ክፉ ሲሠራ እኛም ክፉ በመሥራት ወዘተ መንፈሳዊን ውጊያ በድል እንወጣለን ማለት በሰይጣን የጦር ዕቃ ሰይጣንን ለማሸነፍ እንደ መሞከር ነው::

 

·       የመንፈሳዊ ትግል/ውጊያ የጦር ዕቃዎች

ጳውሎስ የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃዎችን አማኞች ራሳቸው እንዲለብሱ ነው የሚነግራቸው::  “...የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ” ቁ. 11 “...የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ” ቁ. 13:: ስለዚህ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ስንል አማኞች በጌታ ሲያምኑ ወዲያ የለበሱትና የታጠቁት ነገር ሳይሆን በዚህ ክፍል ጳውሎስ የሚናገረው አማኞች ራሳቸው መልበስና ማንሳት ስላለባቸው ትጥቆች ነው:: በቁ. 14-17 ላይ አማኞች ሊለብሷቸው የሚገቡ የእግዚአብሔር ጦር ዕቃዎችና ትጥቆች ተዘርዝረዋል:: እነዚህም እንደ ወገብ መታጠቂያ (ቀበቶ) የሆነ እውነት፣ እንደ የደረት ጥሩር የሆነ ጽድቅ፣ እንደ ጫማ የሆነ ወንጌልን የመስበክ ዝግጅት፣ እንደ ጋሻ የሆነ እምነት፣ እንደ ራስ ቁር (helmet) የሆነ ድነት (salvation) እና እንደ ሰይፍ የሆነ የእግዚአብሔር ቃል ናቸው:: በዚህ ክፍል የተጠቀሰው የአለባበሱ ምሳሌያዊ አገላለጽ የሮማውያን ወታደሮችን አለባበስ የሚያስታውስ ነው:: የሮማውያን ወታደሮች ከራስ ቁር እስከ እግር ጫማ ድረስ የታጠቁትን ሙሉ ትጥቅና በእጆቻቸውም ያይዙአቸውን ጋሻና ሰይፍን ያስታውሳል::  እዚህ ላይ የተጠቀሰው አለባበስ ምሳሌያዊ አገላለጽ መሆኑን መዘንጋት የለብንም:: ለምሳሌ በ1ተስ 5፣8 ላይ እምነትና ፍቅር እንደ ጥሩር፣ የመዳን ተስፋ ደግሞ እንደ ራስ ቁር ተጠቅሰዋል:: ስለዚህ የአለባበሱን ምሳሌዎች ስንመለከት በጣም አጥብቀን ማየት ያለብን ሊተላልፍ የተፈለገው መልእክት ላይ እንጂ በግድ መንፈሳዊ እውነቶቹን ከተሰጠው የአለባበስ ምሳሌ ጋር አንድ ለአንድ ማዛመዱ ላይ አይደለም:: ስለዚህ የጽድቅ ጥሩር ሲል በይበልጥ በጽድቅ የሆነ ሕይወት ላይ ነው ማተኮር ያለብን እንጂ ዋናው ትኩረቱ ጥሩሩ ላይ መሆን የለበትም::

 

እንግዲህ ጳውሎስ በዚህ ክፍል የሚናገረው ስለሚለበስ እና በውጪም ስለሚታይ ነገር ነው:: ጽድቅ አለን፣ እውነት አለን፣ እምነት አለን ወዘተ ማለት ብቻ መልበስን አያሳይም:: ነገር ግን ውሸትን ጠልቶ በየዕለቱ እውነት የተሞላ ሕይወት መኖር ነው እውነትን መታጠቅ ማለት:: ክፉ ሥራን ጠልቶ በጽድቅና እግዚአብሔር በሚወደው መንገድ በየዕለቱ መሄድ ነው ጽድቅን መታጠቅ ማለት:: ምንም እንኳን በጌታ አማኞች የጸደቁ ቢሆንም፣ በዚህ ክፍል የሚናገርው ግን እንደ ጸደቀ ሰው፣ ጽድቅን በዕለት ተለት ኑሮ መለማመድን ነው:: እንደ ጌታ ልጆች ከክፋት ርቆ በጽድቅ መመላለስን ነው በዚህ ክፍል የሚናገረው:: ዲያብሎስም ወደ ሕይወታችን የሚያመጣውን ፈተናና ተንኮል ልንቋቋም የምንችለው በሕይወታችን በጽድቅና በእውነት በዕለት ተለት ስንመላለስ እንጂ በውሸትና በክፋት እየተመላለስን በጌታ ሁሉ አለኝ እያልን ስንፎክር አይደለም:: የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃ ማንሳትና መልበስ የአማኞች የዕለት ተለት ኃላፊነት ነው::

 

       እውነት

“እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ...” ቁ. 14:: እውነት ከውሸትና ከሐሰት የራቀ ሕይወትን ያሳያል:: የተመሰለውም እንደ መታጠቂያ ወይም ቀበቶ ነው:: ይህ መልእክት በተጻፈበት ዘመን የሰዎች ልብስ ሰፋ ያለ አንድ ወጥ ቀሚስ መሰል ነገር ነበር:: ከቤት ወጥቶ ሊሄድ ወይም አንድን ነገር ለማድረግና እንደ ልብ ጎምበስ ቀና ለማለት የሚፈልግ ሁሉ በመጀመሪያ ወገቡን በቀበቶ ይታጠቅ ነበር:: ያለበለዚያ ወገቡን ሳይታጠቅ በዘርፋፋ ቀሚሱ ሊጓዝ ወይም ሥራ ሊሠራ የሚሞክር ልብሱን ሊረግጥና በራሱ ልብስ ሊጠለፍ ይችላል:: ስለዚህም ወገብን መታጠቅ ተነስቶ አንድን ነገር ለማድረግ የመዘጋጀት ምልክትም ነው ሉቃ 12፣37 ሉቃ 17፣8:: እንግዲህ ከእውነት ይልቅ ውሸትን እንደ ዋና መሣሪያ በሕይወቱ የሚለማመድ ሰው በራሱ ልብስ ተጠልፎ እንደሚወድቅ ሰው ይቆጠራል:: እንዲህ ያለውን ሰው ለመጣልና ለማሸነፍ ለሰይጣን በጣም ቀላል ነው:: ምክንያቱም ውሸት የእግዚአብሔር ጦር ዕቃ ሳይሆን የሰይጣን የራሱ መሣሪያ ነውና ዮሐ 8፣44::

 

 

       ጽድቅ

“...የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ” ቁ. 14:: ጽድቅ በእግዚአብሔር ፊት ትክክለኛና ደስ የሚያሰኝ ሕይወት ነው:: አማኞች ሁሉ የእግዚአብሔርን ጽድቅ በክርስቶስ ያገኙ ቢሆንም፣ በዚህ ክፍል ግን የሚናገረው ያገኙትን ጽድቅ በሕይወታቸው መለማመድ እንዳለባቸው ነው:: የጸደቀ ሰው ክርስቶስ በውስጡ ያስቀመጠውን የጽድቅ ሕይወት በዕለት ተለት ሕይወቱ ሊያሳየው ይገባል:: ወይም በሌላ አነጋገር የጸደቀ ሰው እንደ ጸደቀ ሰው ሊኖር ይገባዋል እንጂ ጨርሶ ጽድቅ የሚባል ነገር በአጠገቡ እንዳላለፈ ክፉና አመጸኛ ሰው ሊመላለስ አይገባውም:: ስለዚህ ጽድቅን መልበስ ከክፋትና ከአመጻ፣ ፍትሕና እውነት ከሌለው አኗኗር መራቅና ኃጢአትንም መጥላት ማለት ነው:: ያለበለዚያ ግን በክፋትና በአመጻ በኃጢአትም እየኖሩ፣ የዲያብሎስን ሽንገላ ድል አደርጋለሁ ማለት ደረቱ ምንም ሳይሸፈን ለጥቃት እንደተጋለጠ ሆኖ ወደ ውጊያ የሚገባ ወታደርን መምሰል ነው:: በጠላት ላይ እውነተኛ ድል ያለው ወደ ክፋትና ወደ አመጽ የሚያመራውን የሰይጣንን ማታለል ዕለት ተዕለት መቋቋሙ ላይና ጸንቶ እምቢ ማለቱ ላይ ነው እንጂ የጸሎት ፕሮግራም ላይ ብቻ በኃይል መገሠጹ ላይ አይደለም:: እውነተኛው ጦር ሜዳ ላይ ድል እየተነሱና እየተሸነፉ እንዲያው ብቻ መገሠጽ፣ ከባዶ ፉከራነት አያልፍም::

 

       የሰላም ወንጌል

“በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ” ቁ. 15:: ይህ ክፍል ከሁሉም ለመረዳት ከበድ ያለና ግልጽ ያልሆነ ቢሆንም ሃሳቡ ግን ወንጌልን ለመስበክና የምስራቹን ለማውራት ሁል ጊዜ የተዘጋጀን ሕይወት ያሳያል ኢሳ 52፣7:: እንዲህ አይነት ሰው እግሮቹ እንቅፋት እንደማይጎዳቸው በጫማ እንደተሸፈኑ እግሮች ይመሰላሉ:: እግሮቹ ሁል ጊዜ መልካሙን የሰላም ወንጌል ለማድረስ የተዘጋጁ ናቸው እንጂ ክፉውን ለማውራት፣ ለማማትና ለመሳሰሉት የሚሮጡ አይደሉም::

 

       እምነት

“በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ” ቁ. 16:: እምነት በዚህ ክፍል እንደ ጋሻ ነው የተመሰለው:: በሮማውያን ዘመን ይጠቀሙበት የነበረው ጋሻ እኛ በአገራችን ከምናውቀው ክብና አነስተኛ ጋሻ የተለየ ነው:: ጋሻው በቆዳ የተለበጠ ሲሆን ሰውነትን ሁሉ የሚሸፍን ነው:: ከተቃራኒ የሚላኩትን እሳት የተለኮሱ ፍላጻዎች/ቀስቶች/darts ለማጥፋት እንዲችል ቆዳው በውሃ ይነከር ነበር:: ሰይጣን በአማኞች ሕይወት የሚልካቸው መንፈሳዊ ሕይወትን ሊያቃጥሉና ሊለበልቡ የሚችሉ በእግዚአብሔርና በቃሉ ላይ እንዲጠራጠሩ የሚያደርጉ ብዙ ፍላጻዎች አሉት:: እምነት፣ አይሆንም ይሄ የሐሰት ዜና ነው እንድንልና የሚመጣውን ክፉ ሃሳብ እንዳናስተናግድ የሚያደርግ፣ ብዙ ክፉ ሃሳቦችን የሚያከሽፍ ዋና የመከላከያ መሣሪያ ነው:: ሰይጣንም በተቻለው ሁሉ ይህንን ጋሻ አማኞች እንዲጥሉ ይሞክራል ሉቃ 22፣31-32::

 

       መዳን/ድነት

“የመዳንንም ራስ ቁር ... ያዙ” ቁ. 17:: ይህ ክፍል ድነት/salvation ሁል ጊዜ በአማኝ ሕይወት ዋና ሚና መጫወት ያለበት እንደሆነ የሚያመለክት ነው:: ድነቱን የጣለና እንደ ዋና ነገር ያልያዘ ሁሉ ራሱን ሳይሸፈን ወደ ጦርነት የገባን ወታደር ይመስላል:: ይህም ለሞት እንደተጋለጠ ሰው መሆን ነው::

 

       የእግዚአብሔር ቃል

“የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው::” ቁ. 17:: ከተዘረዘሩት የጦር ዕቃዎች ውስጥ እንደ ዋና ማጥቂያነት የተጠቀሰ የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው:: ይህም ከላይ እንደገለጽነው የመንፈሳዊ ውጊያ ዋናው እምብርት መከላከልና ሳይወድቁ መቆም እንደሆነ በይበልጥ ያረጋግጥልናል:: በዚህ ክፍል የተጠቀሰው የእግዚአብሔር ቃል የመንፈስ ቅዱስ ሰይፍ እንደሆነ ተገልጿል:: ማለትም የእግዚአብሔር ቃል በአማኞች ሕይወት ውስጥ፣ በሰገባ እንዳለ ሰይፍ በሙላት ሲኖር፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በሚያስፈልግ ጊዜና ሁኔታ እንደ ሰይፍ እየመዘዘ የጠላትን ክፉ ሃሳብና ፈተና ለመቁረጥ ይጠቀምበታል:: ይህን አይነቱን የመንፈስ ቅዱስ አጠቃቀም ለመረዳት በተለይ የጌታን ፈተና መመልክቱ ይረዳል ማቴ 4፣1-11:: ጌታ በእግዚአብሔር ቃል የተሞላ ስለነበር በሚፈተነው ፈተና ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ለጊዜው የሚያስፈልገውን ቃል እንደ ሰይፍ እየመዘዘ ይሰጠው ነበር:: በዚህም ጠላት ድል ተደረገ::

 

       ጸሎት

“በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፣ በዚህም ሃሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ፣ ደግሞ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ፣ ስለ ወንጌል በሰንሰለት መልእክተኛ የሆንሁ፣ መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጥ እናገር ዘንድ ለምኑ::” ቁ. 18-20::

 

ጸሎት ምንም እንኳን እንደሚለበስ መንፈሳዊ ዕቃ ጦር ባይጠቀስም በመንፈሳዊ ውጊያም ይሁን ለአጠቃላይ መንፈሳዊ ሕይወት ሁሉ ዋና ማገርና ምሰሶ ነው:: በዚህ ክፍል በአማርኛው “በጸሎትና በልመናም ሁሉ” የሚለው አባባል በእንግሊዝኛው in all prayer and petition ተብሎ ተተርጉሞአል:: ይህም ሁሉንም የጸሎት አይነት ሁሉ የሚያጠቃልል ነው:: ለግል የሚደረግን ማንኛውም አይነት ጸሎትን (በአዕምሮ ወይንም በመንፈስ/በመንፈስ ቅዱስ/በልሳን የሚደረግን ይሁዳ 20 1ቆሮ 14፣14-15) እንዲሁም ለሌሎች ቅዱሳን የሚደረግ ምልጃንና መማጸንን ሁሉ ያጠቃልላል:: ጳውሎስ አማኞች አንድ አይነት ብቻ ጸሎት ሳይሆን ሁሉንም አይነት ጸሎት ሁል ጊዜ ያለ ማቋረጥ እንዲጸልዩ ነው የሚመክረው::

 

በተለይ ምልጃን በተመለክተ ከሌሎቹ የጦር ዕቃዎች ሁሉ የሚለየው፣ የግል መከላከያ መሣሪያ ሳይሆን ሌሎች ቅዱሳንን ለማገዝ ለሌሎች የሚደረግ እርዳታ መሆኑ ነው:: ይህም መንፈሳዊ ሕይወትና ውጊያ በግል ብቻ የሚወጡት ነገር ሳይሆን የጋር ትግል እንደሆነና መደጋገፍና መያያዝ እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ ነው:: ስለምልጃ የአማርኛው ትርጉም ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ መልእክቱን ግልጽ ባያደርግልንም፣ ሃሳቡ ግን በአንድ ጉዳይ ላይ በመጽናት ለቅዱሳን እንዲጸልዩ ነው ጳውሎስ የሚመክረው:: ይህንን ክፍል ኦርጂናሉ የግሪክ ትርጉም እንደሚከተለው ያስቀምጠዋል:: “via all prayer and petition, praying at every time in the spirit, and to same thing this watching in all perserverance concerning all the saints” 18:: ስለዚህ ሃሳቡ ስለ አንድ ጉዳይ ሳይታክቱ በመጽናት ለቅዱሳን መማለድን የሚያመለክት ሃሳብ ነው::

 

ጳውሎስ ለቅዱሳን ብቻ ሳይሆን የወንጌልን ምስጢር በግልጥ/በድፍረት መናገር ይችል ዘንድ እግዚአብሔር ቃል እንዲሰጠው ስለ ራሱም የቅዱሳንን የጸሎት እርዳት ሲጠይቅ እንመለከታለን:: መንፈሳዊ አገልግሎትም ይሁን ሕይወት ያለ ጸሎት ተገቢውን ፍሬ እንደማያፈራ ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነው:: ይህም እርስ በርስ በሌላ ነገር መረዳዳት ሁኔታዎች ባይፈቅዱልን እንኳን በጸሎት መረዳዳትና መደጋገፍ ግን ሁሉ ጊዜ የሚቻልና እጅግም አስፈላጊ ነገር እንደሆነ የሚያሳየን ነው:: ጳውሎስ የጸሎት እርዳት ካስፈለገው እኛማ ይልቁን እንዴት አብልጦ ያስፈልገን::

 

 

2.              መደምደሚያ

 

·       ቲኪቆስ ቁ. 21:: ስማቸው በብዛት ከማይታወቁ ነገር ግን ጌታን በታማኝነት አገልግለው ካለፉ ሰዎች አንዱ ቲኪቆስ ነው:: የጳውሎስ ረዳት በመሆን ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ ያገለገለ ወንድም ነው ቆላ 4፣7 2ጢሞ 4፣12 ቲቶ 3፣12 ሐዋ 20፣4::

 

·            የመጨረሻ ባርኮት ቁ. 23-24:: በተለይ ቁ. 24 ላይ “ባለመጥፋት” የሚለው ቃል ትንሽ ሊያደናገር ይችላል:: ነገር ግን አዲሱ መደበኛ ትርጉም ይህን ክፍል በይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል:: “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን::” ቁ. 24 (አ.መ.ት)::


“ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ።“
(መጽሐፈ ምሳሌ 3:3-4)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us