ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች » ኤፌሶን » ጥናት 5 (ኤፌሶን 1፣15-23) የመጀመሪያው የጳውሎስ ጸሎት
Email this page to a friend Printer-friendly   Tuesday, 20 October 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦“
(የዮሐንስ ራእይ 3:14)

rss

Today's verse

ጥናት 5 (ኤፌሶን 1፣15-23) የመጀመሪያው የጳውሎስ ጸሎት

pdf version

1.              ስለዚህ

ይህ ቃል፣ ከቁጥር 15 ጀምሮ ያለው የጳውሎስ ጸሎት እስከ አሁን ባየነው ክፍል ላይ የተመሠረተ እንደሆነ የሚገልጽ ነው:: ጳውሎስ የተገለጠለትን ለቅዱሳን የሆነውን የእግዚአብሔርን ሰማያዊ በረከትና እግዚአብሔር በክርስቶስ ሊሠራው ያለውን የእግዚአብሔርን ሃሳብ እስከ ቁጥር 14 ድረስ ለማስረዳት ሞክሮአል:: ነገር ግን ይህ ለጳውሎስ የተገለጠለት ሰማያዊ ጥበብና እውቀት ለሌሎች በመንገርና በመስተማር ብቻ በእርግጥ ሊረዱትና ሕይወት ሊሆንላቸው ስለማይችል፣ ስለዚህ ቅዱሳንም ልክ እንደ ጳውሎስ ይህ ምስጢር እንዲገለጥላቸውና በእርግጥም ተረድተውት ሕይወት እንዲሆንላቸው ጸሎት ያስፈልጋል::

 

2.              ስለ ኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን የተሰማው ነገር

መልካምም ይሁን ክፉ ስለ ማናቸውም አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚሰማ ነገር አለ:: ምንም እንኳን የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን በራሱ በጳውሎስ የተመሠረተች ብትሆንም፣ እንዲሁም ጳውሎስ በኤፌሶን ባይኖርም፣ ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ግን ይሰማ ነበር:: ስለዚህች ቤተ ክርስቲያን ሁለት ነገሮች ጳውሎስ ሰምቷል:-

 

·       እምነት

በጌታ በኢየሱስ     ያላቸው እምነት:: ይህም በጌታ ላይ የጸና እምነት እንዳላቸውና በእምነታቸው ወደ ኋላ እንዳላፈገፈጉ የሚያሳይ ነው::

 

·       ፍቅር

ለቅዱሳን ሁሉ ያላቸው ፍቅር:: እዚህ ላይ ፍቅር ተብሎ የተተረጎመው ቃል በግሪኩ agape/አጋፔ የሚለው ቃል ነው:: agape በአዲስ ኪዳን ፍቅርን ለመግለጽ ጥቅም ላይ ከዋሉት ሁለት የግሪክ ቃላት አንዱ ሲሆን ሌላው ደግሞ phileo/ፊሌዎ ነው::

 

·       agape/አጋፔ መለኮታዊውንና በሰዎች ዘንድ ከሚታወቀው መደበኛ መዋደድ የተለየውን ፍቅር ለመግለጽ መንፈስ ቅዱስ በተለየ ሁኔታ የተጠቀመበት ስለሆነ፣ የዚህ ቃል ፍቺና ምንነት ከአዲስ ኪዳን ውጪ  በሌሎች የግሪክ ድርሰቶችና ጽሑፎች የማይገኝ ነው:: አጋፔ መለኮታዊ የሆነ የእግዚአብሔር ፍቅርን የሚያሳይ ነው:: ይህም ፍቅር ፍጹም የሆነ፣ የማያቋርጥ፣ ከተወዳጁ ማንነት የተነሣ ወይም በእርስ በርስ መሳሳብ (በወዳጅነት፣ በመግባባት፣ በመቀራረብ፣ በጸባይ ወዘተ) ላይ ያልተመሠረተ ፍቅር ነው::  agape/አጋፔ በተለይ በሚከተሉት ሁኔታዎች ውስጥ ጥቅም ላይ ውሏል:-

 

·       ሀ)እግዚአብሔር ለልጁ ለኢየሱስ ያለውንና (ዮሐ 17፣26) ለሰው ልጆችም ባጠቃላይ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ ዮሐ 3፣16 ሮሜ 5፣8

 

·       ለ)ቅዱሳን እርስ በርስ ሊኖራቸው ስለሚገባው የፍቅር ግንኙነት ለመግለጽ ዮሐ 13፣34

 

·       ሐ)ሰዎች ለእግዚአብሔር ሊኖራቸው ስለሚገባው ፍቅር ለመግለጽ ማቴ 22፣37 ሮሜ 8፣28::

 

·       መ)የእግዚአብሔርን ባሕርይ ወይም ማንነት ለመግለጽ 1ዮሐ 4፣8

 

እንግዲህ እዚህ ላይ ልብ የምንለው ነገር፣ ጳውሎስ ስለ ኤፌሶን የሰማው ነገር እጅግ መልካምና ቤተ ክርስቲያኒቱም ያላትን ከፍ ያለ መንፈሳዊ እድገት የሚያሳይ ነው:: ጳውሎስ የሰማው ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳው ሕይወት እንጂ ስለሚያካሂዱት የጉባኤ ፕሮግራም አይደለም:: የጉባኤ ፕሮግራም መድመቁና ማማሩ ብቻ የአንድን አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ሕይወት ብስለት አይገልጽምና:: ጳውሎስ ስለ ቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን  የሰማውን ነገር ማየቱ ለንጽጽር ይረዳናል 1ቆሮ 1፣11/5፣1::

 


 

3.              የጳውሎስ ጸሎት

ከላይ እንደተመለከትነው፣ የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ምንም እንኳን ከፍ ያለ የመንፈሳዊ ሕይወት ደረጃ ላይ የደረሰች ቢሆንም፣ ጳውሎስ ለእነርሱ መጸለይን አልተወም ኤፈ 1፣16:: ከደረሱበት በላይ ወደ ሌላ መንፈስዊ እድገት እንዲገቡ ይጸልያል:: የጸሎቱም ይዘት መንፈሳዊ ሕይወታቸውን እንጂ ምድራዊ ኑሮአቸውን ማዕከል ያደረገ አይደለም:: ጸሎቱ በሁለት የተከፈለ ነው:-

·       ምስጋና፣

·       ስለ እነርሱ ስለሰማው መልካም ምስክርነት ምስጋና::

·       ምልጃ ወይም ልመና

·       በዚህ ክፍል ጳውሎስ የሚለምነው ነገር አንድ ነው:: ይሄውም እግዚአብሔር ለኤፌሶን ቅዱስን እግዚአብሔርን ይበልጥ በማወቅ ሂደት ውስጥ አብ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣቸው ነው::

·       የጥበብና የመገለጥ መንፈስ

·       ጥበብ

·  ጥናት 3 ቁጥር 2ለ ይመልከቱ

·       መገለጥ

·  ያለ፣ ነገር ግን ለአይን የተሸፈነን፣ የተጋረደን፣ የማይታይን፣ የተሰወረን ነገር መግለጥ ወይም ለእይታ ማብቃት ማለት ነው::

·       መንፈስ

·       ይህን አባባል ለመረዳት ኢሳ 11፣1-2 ያለውን መመልከቱ ይጠቅማል:: “የእግዚአብሔር መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኃይል መንፈስ፣ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል::” ኢሳ 11፣2:: በዚህ ክፍል ላይ በመሲሁ በክርስቶስ ላይ የሚያርፍበት መንፈስ ተዘርዝሮአል:: በአዲስ ኪዳን ደግሞ በጌታ ላይ ያረፈበት መንፈስ፣ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ተገልጾአል ሉቃ 3፣21-22:: ስለዚህ በኢሳይያስ ላይ በተለያየ መጠሪያ የተጠራው መንፈስ ራሱ መንፈስ ቅዱስ ነው:: ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ራሱን በሰዎች በተለያየ መልክ ስለሚገልጥ፣  እነዚያ ሁሉ የእርሱ መገለጫዎች/manifestations ናቸው:: መንፈስ ቅዱስ የኃይል መንፈስ ብቻ አይደለም፣ የጥበብና የእውቀት፣ የማስተዋልና የምክርም መንፈስ እንጂ:: በሶምሶን ራሱን በኃይል የገለጠ(manifest) ያ መንፈስ (መሳ 14፣5-6)፣ ቤተ መቅደሱን ይሠራ ዘንድ በባስልኤል ደግሞ በጥበብና በማስተዋል፣ በእውቀትም ራሱን ገልጿል ዘጸ 35፣30-33:: ስለዚህ ጳውሎስ የጥበብና የመገለጥ መንፈስ ሲል፣ ለማስተላለፍ የሚፈልገው፣ ከመንፈስ ቅዱስ ሌላ የተለየ መንፈስ የኤፌሶን ቅዱስን እንዲቀበሉ ሳይሆን፣ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ በጥበብና ሰማያዊውን ምስጢር በመግለጥ በይበልጥ እንዲሠራ ነው::

 

·       ምንም እንኳን ጳውሎስ የሚለምነው አንድ ነገር ቢሆንም፣ ይህን የሚለምነው ግን የልባቸው አይኖች በርተው ሶስት ዋና ዋና መንፈሳዊ እውነቶችን እንዲያዩና እንዲያውቁ ነው:: እነዚህም:- የመጥራቱ ተስፋ፣ በቅዱሳን ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነትና ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ትላቅነት ናቸው::

 

·  የልብ አይን መብራት

·       ስለ አንድ ክስተት ከርቀት ሆኖ ከመስማት ይልቅ በቦታው ተገኝቶ ማየት፣ ስለ ጉዳዩ የተሻለ መረጃ ለማግኘት ያስችላል:: በመስማት ያገኘነው መረጃ/information፣ ከእኛ በፊት ለነገሩ ቅርበት ያለውና ነገሩን ያየ ሰው መኖሩንና እኛ መረጃውን በቦታው ተገኝተን ያገኘነው እንዳልሆነ፣ ነገር ግን ከዚያ ካየው ሰው መስማታችንን ያመለክታል:: ስለዚህ የምናገኘውም መረጃ ከምንጩ በቀጥታ ወይም first hand information አይደለም:: መስማት እንደማየት ነገሩን ሙሉ በሙሉ መግለጽ አይችልም:: የሳባ ንግሥት ከሰማችው ይልቅ ያየችው እጅግ ይበልጥ ነበር 1ነገሥ 10፣6-7:: አገር ቤት በነበርን ጊዜ ስለ ውጪ አገር ከሌሎች የሰማነውና አሁን ደግሞ ካየን በኋላ ያለን መረዳት ብዙውን ጊዜ በጣም የተለያየ ነው:: ስለዚህ የጳውሎስ ጸሎት በማየት ላይ ያተኮረ ነው:: ከማየት የመነጨ እውቀት:: ልክ በምድራዊው አለም ያሉትን ነገሮች ለማየት ጤናማ አካላዊ አይን እንደሚያስፈልግ፣ መንፈስዊውን ምስጢር ለማየት ውስጣዊ ወይም የልብ አይን ያስፈልጋል:: ይህ በአእምሮ መረጃን ከማግኘት ያለፈ፣  የውስጥ መረዳትና እውቀት ነው:: በአእምሮ መረጃ ማግኘት ብቻ እንደ ማየት ሕይወት አይሆንምና:: ስለዚህ ነው ጳውሎስ በመንፈስ ከተገለጠለትና ለእነርሱም ከነገራቸው በላይ፣ ልክ እርሱ እንዳየ እነርሱም እንዲያዩ የሚጸልየው:: “መስማትንስ በጆሮ መስማት ሰምቼ ነበር፣ አሁን ግን ዓይኔ አየችህ” ኢዮ 42፣5::

 

·  እንዲያዩትና እንዲያውቁት የተፈለገው ሶስቱ መንፈሳዊ እውነቶች

·       ህ)የመጥራቱ ተስፋ

·       ተስፋ ወደፊት ሊመጣ ያለ መልካም ነገር ነው:: “በተስፋ ድነናልና ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፣ የሚታየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቃለን::” ሮሜ 8፣24-25:: ተስፋ ሰዎች ለአንድ አላማ የተለያዩ እንቅፋቶችን እንዲያልፉና በጀመሩት ጎዳና ላይ እንዲጸኑ የሚያደርግ ነው:: ሰው ተስፋ ሲቆርጥ ካሰበውና ከጀመረው መንገድ ወደ ኋላ ይመለሳል:: የኤማሁስ መንገደኞችም ከኢየሩሳሌም ወደ ኤማሁስ የተመለሱት ተስፋ በመቁረጣቸው ነው:: “እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር...” ሉቃ 24፣21:: ጌታን ከመከተል እንዳይመለሱ፣ ጌታ ራሱ ተስፋቸውን ማደስ ነበረበት:: እግዚአብሔር ከአብርሃም ጊዜ በፊት ጀምሮ የተስፋ አምላክ ነው:: እግዚአብሔር ተስፋ የሚሰጥና የሰጠውንም የተስፋ ቃል የሚፈጽም አምላክ ነው:: ስለዚህ በጌታ ያለን ተስፋ ሕያው ተስፋ ነው 1ጴጥ 1፣3:: የጳውሎስም ጸሎት እግዚአብሔር የጠራቸው ለምን የመጨረሻ ግብ፣ ዓላማ፣ መዳረሻ እንደሆነ እንዲያውቁ ነው:: ጥሪው ከድነትና ከይቅርታ ያለፈ የዘላለም ተስፋ ያለው እንደሆነና፣ የዚህንም ተስፋ ምንነት በሙላት እንዲረዱ::

 

·       ለ)የርስት ክብር ባለጠግነት

·       ርስት፣ ጥናት 3 ቁጥር 3 ይመልከቱ:: ክብር፣ ጥናት 4 ቁጥር 1መ ይመልከቱ:: እግዚአብሔር ለቅዱሳን ያዘጋጀውን የርስት ክብር ብዛትና ባለጠግነት እንዲያውቁ ሌላው የጳውሎስ ጸሎት ነው:: እግዚአብሔር ያዘጋጀውን የርስቱን ታላቅነትና ትክክለኛ ዋጋ መረዳት ከምድራዊ ርስትና በምድር ልናገኘው ከምንችለው ማናቸውም ባለጠግነትና ክብር ጋር ለማወዳደር ይረዳናል:: ያለዚያ የምድሩን ክብርና ባለጠግነት ንቀን የሰማዩን ለመፈለግና በክርስትና ሕይወታችንም ለጌታ ዋጋ ለመክፈል ይከብደናል::

·       “...ለእኛምለለ ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ::” ሮሜ 8፣17-18

·       “ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፣ ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና፣ ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፣ ብድራቱን ትኩር ብሎ ተመልክቶአልና::” ዕብ 11፣24፣26

 

·       ሐ)ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ትላቅነት

·       እግዚአብሔር ለሚያምኑ የሆነ ከሁሉ የሚበልጥ ታልቅ ኃይል እንዳለው እንዲያውቁ ሶስተኛው የጳውሎስ ጸሎት ነው:: እዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገባን ይህ ኃይል ለሚያምኑ ወይም ለአማኞች ሁሉ የሆነ መሆኑን ነው:: ይህ ኃይል ከሁሉ ይሚበልጥ ያስባለውና ታላቅነቱ የታየው በክርስቶስ ትንሣኤ ነው:: በምድር ላይ ሰዎችን ከሚያሸንፉ ኃይላት ሁሉ በላይ የሆነው የመጨርሻው ትልቁ ኃይል ሞት ነው:: በምንም ትምህርት፣ ሥልጣንና ኃይል የሰው ልጅ ከሞት ኃይል ግዛት ሊያመልጥ አይችልም:: ይህንን ኃይል ሰብሮ ክርስቶስን ማስነሳቱ ይህ የእግዚአብሔርን ታላቅ ኃይል ያሳያል ዕብ 2፣14-15 ራእ 1፣17-18:: የኢየሱስ ትንሳኤ በብሉይና በአዲስ ኪዳን ከሞት ከተነሱት ሰዎች ሁሉ የተለየ የመጀመሪያው እውነተኛ ትንሳኤ ነው:: ሌሎቹ ምንም እንኳን ከሥጋቸው የተለየው ነፍሳቸው ወደ ሥጋቸው የተመለሰ ቢሆንም (ለምሳሌ አልአዛር ዮሐ 11፣43-44 ዮሐ 12፣9) በሕይወት ዘመናቸው መጨረሻ ተመልሰው ሞተዋል:: የትንሳኤ በኩር የሆነው ኢየሱስ ግን፣ ሞት ሁለተኛ እንዳይገዛውና በእርሱ ላይ ሥልጣን እንዳይኖረው፣ ሞትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ድል አድርጎ ነው የተነሣው:: በተጨማሪም ኢየሱስ የማይሞተውንና የማይበሰብሰውን የትንሳኤ አካል ለብሶ ነው የተነሣው:: ስለዚህም ኢየሱስ የትንሳኤ በኩር ነው 1ቆሮ 15፣20-23/ቆላ 1፣18/ሮሜ 6፣9:: እግዚአብሔር የሰው ዘርን ሁሉ የሚገዛውን የሞትን ኃይልና ሥልጣን በክርስቶስ ሰብሮታል፣ በዚህም የእግዚአብሔር የኃይሉ ታላቅነት ይታያል:: ይህ ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን ሰዎችን ለዘመናት ከገዙት በሰማያዊ ስፍራ ከሚገኙት መንፈሳዊ የክፋት ሠራዊቶች ሁሉ በላይ፣ ከአለቅነትና ከሥልጣናት፣ ከኃይልም ከጌትነትም ከስምም ሁሉ በላይ በቀኙ ማስቀመጡና ሁሉን ከእግሩ በታች ማስገዛቱ፣ የእግዚአብሔርን ኃይል የሚቋቋም ምንም ኃይልና ሥልጣን እንደሌለ ያሳያል:: ማቴ 28፣18

 

·       ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ

·           እንግዲህ ይህንን ከጌቶች ሁሉ በላይና ሁሉም ከእግሩ በታች የተገዛለትን ጌታ ነው፣ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን ራስ እንዲሆን ያደረገው:: ቤተ ክርስቲያን በእርሱ (ማንነት፣ ሥልጣን፣ ጸጋ ወዘተ) የተሞላች የክርስቶስ አካል ናት ወይም የክርስቶስ ሙላት ናት:: አካሉ ከሆነች ደግሞ ትልቅ የሚባለው ኃይል ሁሉ ከቤተ ክርስቲያን በታች ነው ማለት ነው:: ስለዚህ የጌታ ኃይልና ስልጣን በምድር ላይ እውን የሚሆነውና የሚተገበረው በአካሉ ነው:: ጳውሎስ የኤፌሶን ሰዎች ይህንን የቤተ ክርስቲያን ስልጣንና እግዚአብሔር ያስታጠቃትን ኃይል እንዲያውቁ ይፈልጋል:: ይህም እውቀት ምንም አይነት ኃይልና ስልጣን፣ ምንም አይነት የጠላት ተቃውሞ እኛን ከእግዚአብሔር ሊለየን እንደማይችል ያረጋግጥልናል:: ሮሜ 8፣35-39


“ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ።“
(መጽሐፈ ምሳሌ 3:3-4)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us