ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች » ኤፌሶን » ጥናት 6 (ኤፌሶን 2፣1-10)
Email this page to a friend Printer-friendly   Tuesday, 20 October 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦“
(የዮሐንስ ራእይ 3:14)

rss

Today's verse

ጥናት 6 (ኤፌሶን 2፣1-10)

pdf version

ይህን ክፍል በሶስት ክፍሎች ከፍሎ ማየቱ መልዕክቱን በሚገባ ለመገንዘብ ይረዳል:: እነዚህም:-

 

1.              የአማኞች የቀድሞ የሕይወት ሁኔታ፣ይዞታ (state/condition) ቁ.1-3

በዚህ ክፍል ጳውሎስ አማኞች በክርስቶስ ከመሆናቸው በፊት የነበሩበትን የቀድሞውን የሕይወት ሁኔታ/ይዞታ (state) እንደሚከተለው ያስቀምጠዋል:-

 

ሀ)ሙታን መሆን

ከበደል ወይም ከመተላለፍና ከኃጢያት የተነሳ መሞት ሮሜ 6፣23:: ሞት የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ የሕይወት ወይም የሕያውነት ተቃራኒ የሆነውን ሁኔታ/ይዞታ/state የሚገልጽ እንጂ፣ አለመኖርን ወይም አለመሆንን (nonexistenceን) አያመለክትም:: ይህም ማለት የሞተ ሰው መኖሩን አለ፣ ነገር ግን በሌላ አይነት ሁኔታ ነው ያለው፣ ወይም ከሕያዋን በተለየ ሁኔታ ነው ያለው::

 

በኃጢአት ምክንያት የሚመጡ ሶስት አይነት ሞቶች እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል:: እነዚህም:- የሥጋ ሞት ወይም ነፍስ ከሥጋ መለየት (ሮሜ 5፣12-14)፣ ከመጨረሻው ፍርድ በኋላ ያለው የእሳት ባህር ወይም ሁለተኛው ሞት (ራእ 20፣6/14 ራእ 21፣8) እንዲሁም በሥጋ ሳይሞቱ ነገር ግን በመንፈስ ከእግዚአብሔር መለየት ወይም መንፈሳዊ ሞት (ዘፍ 2፣17 ማቴ 8፣22 ቆላ 2፣13) ናቸው:: በዚህ ክፍል እንግዲህ በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ ሲል፣ መንፈሳዊ ሞትን ለማመልከት እንጂ በሥጋ የሞቱ እንደነበር የሚያመለክት አይደለም::

 

እኛ እንግዲህ ከኃጢአት የተነሳ በመንፈስ ከእግዚአብሔር ተለይተን፣ መንፈሳዊ አይኖቻችን የማያዩ፣ መንፈሳዊ ጆሮቻችን የማይሰሙ ሆነው፣ በሥጋዊው አለም ብቻ እየኖርን፣ ከእግዚአብሔር ሕልውና ግን ርቀን እንገኝ ነበር:: ሞት የመጨረሻው ከፍተኛ የመለየት ደረጃ ነው:: የነበርንበት ሁኔታ መንፈሳዊ ስህተት ወይም መንፈሳዊ በሽታ ብቻ አልነበረም፣ ነገር ግን መንፈሳዊ ሞት እንጂ:: በመሠረቱ የተሳሳተን ወይም የታመመን ምናልባት መርዳት ይቻል ይሆናል፣ የሞተ ግን ከእግዚአብሔር በቀር ምንም አይነት እርዳታ የማይመልሰው ነው::

 

ለ)በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ መመላለስ

ሌላው በቀድሞው ሕይወታችን የነበርንበት ሁኔታ በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ መመላለስ ነው:: እዚህ ላይ በአየር ላይ ሥልጣን ያለው ወይም በማይታዘዙ ልጆች ላይ አሁን የሚሠራው መንፈስ አለቃ ተብሎ የተጠቀሰው ዲያቢሎስ ነው ዮሐ 12፣31 2ቆሮ 4፣4:: እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባን ይህ የዲያቢሎስንና የክፉ መናፍስትን ፈቃድ እያደረጉ መኖር የዚህ አለም መደበኛው/normal ኑሮ እንደሆነ ነው:: “...በዚህ አለም እንዳለው ኑሮ...” ኤፌ 2፣1-2:: ይህ መንፈስ የጌታ ባልሆኑ ወይም “በማይታዘዙ ልጆች” ላይ የሚሠራ መንፈስ ነው:: “...በማይታዘዙ ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ” ኤፌ 2፣1-2:: ስለዚህ ለእግዚአብሔር ያልሆነ ሁሉ ወደደም ጠላም የዲያቢሎስን ፈቃድ ከማድረግ አያመልጥም:: እግዚአብሔርንም ሰይጣንንም አለመታዘዘ የሚባል መካከለኛና ነጻ የሆነ ሕይወት የለም:: ለእግዚአብሔር በማይታዘዙ ሁሉ የዲያቢሎስ መንፈስ በእነርሱ ይሠራል ዮሐ 8፣44:: በጌታ ከመሆናችን በፊት እንግዲህ በዚህ አለም እንዳለው ኑሮ እኛም በዲያቢሎስ ፈቃድ ተጽዕኖ ውስጥ የእርሱን ፈቃድ እያደረግን እንኖር ነበር::

 

ሐ)የሥጋን ምኞትና የልቦናችንን/የአእምሮአችንን ፈቃድ ማድረግ

በዚህ ክፍል ሥጋ የሚለው ቃል የሚያመለክተው ሰውነትን ወይም የሰው አካልን አይደለም:: ስለዚህም የሥጋ ምኞት ሲል ሰውነታችን ወይም አካላችን የሚያስፈልገውን ነገሮች ለምሳሌ እንደ ልብስ፣ መጠለያ፣ ምግብ ወዘተ ያሉትን ነገሮች ለማለት አይደለም:: ሥጋ የሚለው አባባል ግን የሚያመለክተው በሰው ውስጥ ያለ አዳማዊ ባህርይ ያለውን አሮጌውን ሰው፣ ወይም ክፉ ምኞቶችን የሚመኘውን የሰውን ተፈጥሮ ለማመልከት ነው:: “የክርስቶስ የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ::” ገላ 5፣24 ገላ 5፣19-21::

 

እንግዲህ እኛ በክርስቶስ ከመሆናችን በፊት የሰይጣንን ፈቃድ እያደረግን በእርሱ ተጽዕኖ ውስጥ የምንኖር ብቻ ሳይሆን “የሥጋችንን ምኞት እያረካን፣ መንገዱንም እየተከተልን” (ኤፌ 2፣3 በአዲሱ መደበኛ ትርጉም) ክፉ በሆነው የሥጋ ፈቃድ/አዳማዊ ባሕርይ/የተበላሸ ተፈጥሮ ባሪያዎች ሆነን እንኖር ነበር:: ዲያቢሎስ ብቻ ሳይሆን የእኛም አዳማዊ ተፈጥሮ ራሱ ለእግዚአብሔር የማይታዘዝ ተፈጥሮ ነውና::

 

 


 

መ)ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች መሆን

ሌላው የቀድሞ የሕይወት ሁኔታችን/ይዞታችን/state ከፍጥረታችን የቁጣ ልጅ መሆን ነው:: እዚህ ላይ ችግሩ ያለው የአሮጌው ሰው ወይም የአሮጌ ማንነታችን ተፈጥሮ ላይ ነው:: ይህ ማንነት በኃጢአት የተበላሸ ስለሆነ፣ እግዚአብሔርን ማስደሰትና መታዘዝ የማይችል ነው:: ልክ የወይን ተክል ወይን ፍሬ የሚያፈራው  የወይን ተክል ከመሆኑ የተነሳ እንደሆነ፣ እኛም የሥጋችን ምኞት ክፉ የሆነው ከአሮጌው ማንነታችን የተበላሸ ተፈጥሮ የተነሳ ነው:: ስለዚህም ጳውሎስ “...እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን::” ይላል ኤፌ 2፣3:: እዚህ ላይ ፍጥረታችን የሚለው ቃል፣ ተፈጥሮችንን/natureን የሚያመለክት ነው:: ይህም በተፈጥሮ የቁጣ ልጅ መሆን (children of wrath by nature) ማለት ነው::

 

ቁጣ/wrath የሚለው ቃል መናደድ ከሚለው ከፍ ያለና እግዚአብሔር በማይታዘዙ ልጆች ላይ ወደፊት ሊያመጣ ያለውን ቅጣትና ፍርድ የሚያመለክት ነው (ማቴ 3፣7 ሮሜ 1፣18 ሮሜ 2፣5/8 ሮሜ 3፣5 ሮሜ 5፣9 ሮሜ 12፣19 ኤፌ 5፣6 ቆላ 3፣6 1ተሰ 1፣10 1ተሰ 5፣9):: የቁጣ ልጅ የሚለው አባባል እንግዲህ ለእግዚአብሔር የቁጣ ቀን መጠበቅን፣መታጨትን ወዘተ ያሳያል::

 

ማጠቃለያ:- ከላይ የተጠቀሱትን የቀድሞውን የሕይወታችንን ይዞታ/state ስንመለከት እጅግ አስከፊና አደገኛ እንደሆነ እናስተውላለን:: በመንፈሳዊ ሞት፣ የሰይጣንንና የሥጋን ፈቃድ በማድረግ ከእግዚአብሔር ጋር መጣላትና ለታልቁ ለእግዚአብሔር የፍርድ ቀን መታጨት እጅግ የሚያሳዝንና ተስፋ የሌለው ሁኔታ ውስጥ እንደነበርን ያሳያል:: ራሳችንን ልንረዳ ወይም ሌላ ሰው በምንም መንገድ ሊረዳን በማይችልበት ሁኔታ ነበርን:: ከመንፈሳዊ ሞት አስነስቶ፣ ከሰይጣንና ከሥጋ ኃይል እኛን ነጻ የሚያወጣና ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቀን ረዳት ከወዴት ይገኛል? የሰው ልጅ በሙሉ ያለ ክርስቶስ የሚገኝበት ሁኔታ እንደዚህ የከፋና ተስፋ ቢስ በመሆኑ፣ መፍትሔው ከየትኛውም ነብይ ወይም የሃይማኖት መሪ ሊመጣ አይችልም:: የሃይማኖት መሪውም ራሱ እኛው ባለንበት ሁኔታ ስለሚገኝ ግዴታ መፍትሔው ከእግዚአብሔር ብቻ ነው መምጣት የሚችለው::

 

2.              የአማኞች የአሁን የሕይወት ሁኔታ፣ይዞታ (state/condition) ቁ. 4-9

 

·       ነገር ግን

ጳውሎስ የነበርንበትን የቀድሞ አስከፊ የሕይወት ሁኔታ ከዘረዘረ በኋላ፣ ታሪካችን እንደዚሁ እንዳልተዘጋ ለማመልከት በቁ. 4 ላይ “ነገር ግን” ብሎ ይቀጥላል:: ያ የከፋ የቀድሞ ሕይወታችን እንደዚያው እንዳያልቅ ከላይ የተዘረዘሩትን ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎች የሚለውጡ ከነገር ግን በኋላ የሚመጡ ሁለት ነገሮች ተጠቅሰዋል:: እነዚህም:- እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለጠጋ መሆኑና የወደደን ታልቅ ፍቅሩ ናቸው:: እግዚአብሔር በምሕረት ባለጠጋ ሳይሆን ነገር ግን የምሕረት ድሃ ቢሆን ወይንም ለእኛ ታላቅ ፍቅር ባይኖረውና እንደተቆጣብን ቢቀር ኖሮ፣ በቁ. 4 ከተጠቀሰው “ነገር ግን” በኋላ የሚመጣው ታላቅ ለውጥ ባልተገኘም ነበር:: ስለዚህ የእግዚአብሔር የባሕርይው ማንነት የእኛን ሕይወት ለመገልበጥ ዋናውና ወሳኙ ነው::

 

·       ከክርስቶስ ጋር ሕይወትን ሰጠን

ለሙታን ከሕይወት የተለየ ሌላ እርዳታ አያስፈልጋቸውም:: እግዚአብሔር በመንፈስ ሞተን ለነበርን ለእኛ የሰጠን ሕይወትን ነው፣ ይሄውም የዘላለምን ሕይወት ሮሜ 6፣23:: ለመንፍሳዊ ሙታን ሃይማኖታዊ ሥርዓትም ይሁን የአእምሮ ትምህርት ሕይወትን አይሰጣቸውም፣ የሕይወት ምንጭ እግዚአብሔር ነውና:: እዚህ ክፍል ላይ ሕይወት ብሎ የሚናገረው፣ በመንፈስ ሕያው ስለመሆን ወይም ከመንፈስዊ ሞት ስለ መንቃት ነው እንጂ ወደፊት አንድ ቀን የሚጀመር ኑሮን ለማመልከት አይደለም:: “...ከእርሱ ጋር አስነሣን...” ቁ.7:: መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወት ወይም በግሪኩ zoe የሚለው፣ በውስጣችን ስላለ ሕይወት እንጂ ገና ወደፊት ስለሚጀመር ኑሮ አይደለም:: የእንግሊዝኛውም zoo/zoology የሚገልጸውም በእንስሳት ውስጥ ስላለ ሕይወት ነው:: ምድራዊው ሕይወታችን የሚጀምረው ልክ በተወለድንበት ቀን እንደሆነ ሁሉ፣ ይህም እግዚአብሔር የሰጠን የዘላለም ሕይወታችን የሚጀምረው በጌታ ካመንበት ጊዜ አንስቶ ነው:: “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምጽ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፣ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ::” ዮሐ 5፣25 ዮሐ 5፣24 ዮሐ 3፣15:: ይህንን ከሞት ወደ ሕይወት መሻገር መጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ ሁኔታ ይገልጸዋል:- እንደ ዳግመኛ ልደት (ዮሐ 1፣12-13/3፣5-6/1ጴጥ 1፣23) እንዲሁም እንደ አዲስ ፍጥረትነት (ኤፌ 2፣10/2ቆሮ 5፣17)::

 

·       በሰማያዊ ስፍራ አስቀመጠን

በሰማያዊ ስፍራ ከክርስቶስ ጋር መቀመጥ ከፍተኛ የሥልጣን ቦታን ነው የሚያሳየው:: በጥናት 5 እንደተመለከትነው ክርስቶስ ከአለቅነትና ከሥልጣናት ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ እንደተቀመጠና ሁሉ ከእግሩ በታች እንደሆነ አይተናል:: እግዚአብሔር እንግዲህ እኛን ከመንፈስዊ ሞት ወደ ሕይወት ማሻገር ብቻ ሳይሆን፣ ፈቃዱን እያደረግን ስንመላለስበት ከነበረው ከዚህ ዘመን አለቃ፣ ከዲያቢሎስና ከሠራዊቱ በላይ የሆነን ሥልጣን ነው የሰጠን:: መቀመጥ ሥልጣንን የሚያመለክት ነውና::

 

·       ይህን ያደረገበት ምክንያት

እግዚአብሔር ከማንወጣበትና ተስፋ ከሌለው ሁኔታ ያወጣንና ወደ ሕይወት የመለሰን የራሱን ማንነትና ባሕርይ በእኛ ገልጾ፣ ፍጥረት ሁሉ ማንነቱን እንዲያከብሩ ነው:: “በሚመጡት ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባደረገው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳይ ዘንድ...” ቁ.6:: እግዚአብሔር ለእኛ በሚሠራው ነገር ሁሉ የራሱን ማንነት ለመግለጽና ለማሳየት እንደሚፈልግ፣ በዚህ በኤፌሶን መልዕክት ላይ ተደጋግሞ ተጠቅሷል ኤፌ 1፣6 ኤፌ 1፣12 ኤፌ 1፣14:: ታሪካችን እንዲለወጥ ምክንያት የሆነው የእርሱ ቸርነትና የጸጋው ባለጠግነት ስለሆነ፣ ይህንን ማንነቱን እንድናስተውልና እንድናከብረው እግዚአብሔር ይፈልጋል::

 

·       በጸጋ መዳን

በጥናት 4 ላይም እንደተመለከትነው፣ በዚህም ክፍል ከሞት ወደ ሕይወት በክርስቶስ በኩል የመለሰን እግዚአብሔር ራሱ እንጂ ከእኛ ሥራ አይደለም:: “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፣ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፣ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም::” ቁ.8-9:: እግዚአብሔር የሰጠንን የዘላለም ሕይወት ያገኘነው የራሱ ፍቅር ስላነሳሳው ብቻ ነው:: ለሙታን ሕይወትን መስጠትን እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራ ማስቀመጥን የሠራው ራሱ ብቻ ነው:: የእኛ ድርሻ ልክ በጥናት 4 ላይ እንደተመለከትነው አሁንም ሰምቶ ማመን ብቻ ነው፣ ማመንም ደግሞ ሥራ አይደለም ሮሜ 10፣17 ሮሜ 4፣4::

 

ሥራ ሠራተኛው እንዲከበር የሚያደርግና እርሱም እንዲመካ የሚገፋፋ ነገር ነው:: እግዚአብሔር ሥራውን ሠርቶ እንደሚከበረው፣ እኛም በዚህ ታላቅ ሥራ ውስጥ ድርሻ ቢኖረን ኖሮ፣ እግዚአብሔርን ከማክበር ይልቅ የራሳችንን ሥራ እያየን፣ በሠራነው እንመካ ነበር:: ነገር ግን ማንም እንዳይመካ የዘላለም ሕይወት በሥራ ሳይሆን በነጻ ስጦታ ሆኗል:: “ትምክህት እንግዲህ ወዴት ነው? እርሱ ቀርቶአል::” ሮሜ 3፣27 1ቆሮ 1፣30-31::

 

3.              የአማኞች የወደፊት ሥራ ቁ. 10

ምንም እንኳን አማኞች በጸጋ እንጂ በሥራ ባይድኑም፣ ነገር ግን በጸጋ ውስጥም ሥራ እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል:: “...እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን::” ቁ. 10:: ይሄ “መልካም ሥራ” ተብሎ የተጠራው ምንም እንኳን በዚህ ክፍል ምን እንደሆነ በዝርዝር ባይገለጽም፣ አንዳንድ ባሕርያቱ ግን ተዘርዝረዋል:-

 

·       አማኞች ስለዳኑ የሚያደረጉት እንጂ ለመዳን ወይም የዘላለም ሕይወትን ለማግኘት የሚደረግ አይደለም:: ሰው ለመዳን የሚያደርገው የሕግ ሥራ ሁሉ ወደ ሕይወት የማያመጣ ነገር ግን ሞትን የሚወልድ የሞተ ሥራ ነው ሮሜ 7፣13 ዕብ 6፣1-2 ዕብ 9፣14:: ስለዚህ ይህ መልካም ሥራ በቁ. 9 ከተጠቀሰውና ለመዳን ከሚደረገው ሥራ የተለየ ነው:: ልክ የወይን ፍሬ ለማፍራት የወይን ዛፍ እንደማይጨነቅ፣ እንዲሁም አማኝ በእውነት ከክርስቶስ ጋር ከተጣበቀ መልካምን ፍሬ ያፈራል ዮሐ 15፣1-5:: ያይ

 

·       እግዚአብሔር ከዘመናት በፊት ያዘጋጀው የእግዚአብሔር ሥራ ነው እንጂ የራስ ሥራ አይደለም:: ይህ ሥራ ሰው እግዚአብሔርን ለማስደሰት ተጨንቆና ተጠብቦ ከራሱ አስቦ የሚወልደው የራሱ ሥራ ሳይሆን ሥራው ከእግዚአብሔር የሚመጣ፣ በእርሱም ኃይል የሚሠራ የእግዚአብሔር ሥራ ነው 2ቆሮ 5፣14-15 ማቴ 11፣28-30::

 

·       መልካም ሥራ ነው እንጂ ክፉ አይደለም:: ቀደም ብለን እንደጠቀስነው በክርስቶስ ከመሆናችን በፊት የነበረው አዳማዊው ባሕሪያችንና ማንነታችን ከተፈጥሮው የቁጣ ልጅ እንደነበር፣ ከተፈጥሮው መልካም ማድረግ እንደማይችል፣ ከተፈጥሮው ምኞቱ ክፉ እንደነበር፣ በክርስቶስ የተፈጠረው አዲሱ ሰው ግን ከተፈጥሮው የክርስቶስ ባሕርይ ያለው በመሆኑ መልካም ፍሬን ያፈራል:: ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ወይም መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ እንደማያፈራ፣ እኛም በክርስቶስ መልካም ፍሬን እንድናፈራ ይጠበቅብናል:: ይህ ፍሬ ወይም ይህ መልካም ሥራ መጀመሪያውኑም እምነታችን ትክክል እንደነበረና በእርግጥም የእግዚአብሔር ልጆች እንደሆነን የሚመሰክርና የሚያረጋግጥ የእምነታችን ፍጻሜ ነው ያዕ 2፣22-23:: የወይን ተክል ግን ሎሚ ቢያፈራ፣ የወይን ተክል መሆኑ ራሱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል:: ተክል ሁሉ በፍሬው ይታወቃልና ማቴ 7፣15-20:: “ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁም ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው::” ያዕ 2፣26:: ከኃጢአተኝነት መራቅና መልካሙን ማድረግ፣ ልክ በእምነት እንደመዳን የሆነ የአዲስ ኪዳን የጸጋ ትምህርት ነው:: በእምነት የሚገኘው ድነት የመጨረሻ ግቡም “መልካሙን ለማድረግ የሚቀና ሕዝብ” እንሆን ዘንድ ነው ቲቶ 2፣11-14::

 


“ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ።“
(መጽሐፈ ምሳሌ 3:3-4)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us