ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች » ኤፌሶን » ጥናት 7 (ኤፌሶን 2፣11-22 ሀ) በክርስቶስ አንድ መሆን – ክፍል 1
Email this page to a friend Printer-friendly   Tuesday, 20 October 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦“
(የዮሐንስ ራእይ 3:14)

rss

Today's verse

ጥናት 7 (ኤፌሶን 2፣11-22 ሀ) በክርስቶስ አንድ መሆን – ክፍል 1

pdf version

በምዕራፍ ሁሉት ከቁጥር 1-10 ባለው ክፍል የሐዋርያው ጵውሎስ መልዕክት ያተኮረው በጸጋ በሆነው በግለሰብ ድነት ላይ ነበር:: አሁን በምንመለከተው ክፍል ደግሞ ትኩረቱ በክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር በግል ስላለ መታረቅ ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን ወደ ጎን ሰው ከሰው ጋር በክርስቶስ ስለተፈጠረው አዲስ አንድነት ነው::

 

ይህን የጥናታችንን ክፍል ለአራት ከፍለን እናየዋለን:-

1.              የቀድሞው የአሕዛብ ሁኔታ/state

2.              የቀድሞው የአሕዛብና የአይሁድ ግንኙነት

3.              እርቅና ሰላም በክርስቶስ

4.              አዲሱ ሕብረት

 

ከላይ ከ1 እስከ 3 የተዘረዘሩት ነጥቦች በዚህ በክፍል አንድ ጥናታችን ተመልክተን፣ አራተኛውን ነጥብ ደግሞ በክፍል ሁለት ጥናታችን እናየዋለን::

 

1.              የቀድሞው የአሕዛብ ሁኔታ/state

ሐዋርያው ጳውሎስ ከክርስቶስ በፊት የነበረውን ጊዜ “አስቀድሞ” ቁ.11 ወይም “በዚያ ዘመን” ቁ. 12 በማለት ይገልጸዋል:: ከክርስቶስ በፊት የነበረውን የአሕዛብ ሁኔታ/state ወይም እንደ ሕዝብ አሕዛብ በብሉይ ኪዳን የነበራቸውን ቦታ እንደሚከተለው ያስቀምጠዋል:-

 

·       በሥጋ አሕዛብ:- የብሉይ ኪዳን ተካፋይ ለመሆን የመጀመሪያው መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታ በሥጋ ከእስራኤል መወለድ ነው:: በሥጋ ከእስራኤል ያልተወለደ ሁሉ አሕዛብ ነው:: በዚህ በጥናታችን ክፍል እንግዲህ አሕዛብ ስንል በሥጋ ከእስራኤል ያልተውለዱትን ሌሎችን ሕዝቦች ሁሉ ለማመልከት ነው:: አንዳንድ ጊዜም በአዲስ ኪዳን “የግሪክ ሰው” የሚለው ቃል አሕዛብን ለማመልከት ያገለግላል:: በሥጋ የተወለድንበት ዘር ወይም ትውልድ በብሉይ ኪዳን እንግዲህ ከእግዚአብሔር ጋር ለሚኖረን ግንኙነት ወሳኝነት አለው:: ሰው በሥጋው ከአይሁድ አለመወለዱ ብቻ ከእግዚአብሔር ሕዝብነት ውጪ ያደርገዋል:: አሕዛብ እንግዲህ ከእስራኤል ባለመወለዳቸው ብቻ ከእግዚአብሔር ሕዝብነት ውጪ የሆኑ ነበሩ ማለት ነው:: ስለዚህ የሥጋ ዘር ወይም የሥጋ ማንነት ወይም የሥጋ ወገን በብሉይ ኪዳን ትልቅና መካከለኛ ሚና ይጫወት ነበር::

 

·       በሥጋ ያልተገረዙ:- በሥጋ መገረዝ የተጀመረው በአብርሃም ሲሆን ይሄውም እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ለገባው ቃል ኪዳን ምልክት ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘው ትእዛዝ ነው ዘፍ 17፣9-11:: ስለዚህም እስራኤላዊ የሆነ ወንድ ሁሉ ይገረዝ ነበር:: ይህም ሕዝቡ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝብ እንደሆነ የሚያሳይ እድሜውን ሁሉ በሥጋው ላይ የሚሸከመው ምልክት ነበር:: ይሄ ምልክት በሥጋው ላይ የሌለው ሁሉ ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ውጪ ወይም ከእግዚአብሔር ሕዝብ ውጪ እንደሆነ ይታይ ነበር:: እንዲያውም ያልተገረዘ እስራኤላዊ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ተለይቶ እንዲገደል እግዚአብሔር አዝዟል ዘፍ 17፣14:: አብዛኞቹ አሕዛብ ይህን አይነቱ የመገረዝ ልምድ ስለሌላቸው በአይሁዶች ዘንድ “ያልተገረዙ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶአቸው ነበር 1ሳሙ 17፣26/36 ሐዋ 11፣3:: ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ ከሥጋ መገረዝ ሌላ በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ እንዳለና ይህም እውነተኛው መገረዝ እንደሆነ ቢያስተምረንም (ሮሜ 2፣28-29 ቆላ 2፣11)፣ በብሉይ ኪዳኑ ግን በእጅ የሚደረገው የሥጋ መገረዝ ትልቅ ስፍራ አለው:: እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባን የሥጋ ትውልድም ይሁን የሥጋ መገረዝ ወይም በአጠቃላይ ሥጋ በበሉዩ ኪዳን ከፍተኛ ሥፍራ መያዙን ነው:: እንግዲህ አሕዛብ ይህ የቃል ኪዳን ምልክት የሆነው የመገረዝ ሥርዓት ስለሌላቸው፣ ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ውጪ ነበሩ::

 

·       ከእስራኤል መንግስት መራቅ:- እስራኤል ከአሕዛብ ሁሉ ተለይታ በእግዚአብሔር የበላይ ገዢነት የተመሠረተችና እርሱም ባወጣው ደንብና ሥርዓት የምትተዳደር አገር ነበረች:: ከእስራኤል መንግስት መራቅ የሚለው ቃል ከእስራኤል የዜግነት መብት ውጪ መሆንን ያመለክታል:: ይህም ማለት እስራኤል እንደ እግዚአብሔር ሕዝብ ካላት መብት ተካፋይ ያለመሆንን ያሳያል:: ይህንን የእስራኤልን የዜግነት መብት ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ ላይ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል:- “እነርሱ እስራኤላዊያን ናቸውና፣ ልጅነትና ክብር ኪዳንም የሕግም መሰጠት የመቅደስም ሥርዓት የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና፣ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፣ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፣ አሜን::” ሮሜ 9፣4-5::

 


 

·       ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች መሆንና በዚህ ዓለም ተስፋን ማጣት:- እግዚአብሔር ከአብርሃም በፊት ጀምሮ ለሰው ልጆች የገባው ቃል ኪዳንና አይሁድም ከአብርሃም ጊዜ አንስቶ በነብያትም ዘመን ሁሉ ሲጠብቁት የነበረው ትልቁ የቃል ኪዳን ተስፋ የመሲሑ ወይም የክርስቶስ መምጣት ነበር ዮሐ 8፣56 ማቴ 13፣17:: ስለዚህም እስራኤላዊያን በብዙ ውጣ ውረድ ሲያልፉ ሁል ጊዜ ተስፋ የሚሰጣቸው ነገር፣ አንድ ቀን መሲሑ መጥቶ የእስራኤልን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚያቃልልና አዲስን መንግስት በምድር ላይ እንደሚመሠርት የተገባላቸው ተስፋ ነበር ዮሐ 1፣20 ሉቃ 24፣21 ዮሐ 4፣25-26:: አሕዛብ ግን ለዚህ ተስፋ እንግዶች ወይም ባዕዳን ስለነበሩና ስለዚህ ተስፋ ምንም ስለማያውቁ፣ በዚህ ዓለም ያለ እውነተኛ የእግዚአብሔር ተስፋ ነበሩ:: በመሲሑ/በክርስቶስ አማካኝነት ወደ እግዚአብሔር የመቅረብና የእግዚአብሔር ሕዝብ የመሆን መብት አንድ ቀን እንደሚያገኙ የሚያውቁት ነገር አልነበረም::

 

·       ከእግዚአብሔር መለየትና ያለ ክርስቶስ መሆን:- በቁ. 12 ላይ “ከእግዚአብሔር ተለይታችሁ” የሚለው ቃል በግሪኩ atheos በእንግሊዝኛው ደግሞ atheist/አቴይስት የሚለው ቃል ነው:: ይህ ቃል በዘመናችን የእግዚአብሔርን መኖር ለማያምኑና ምንም አይነት ሃይማኖት ለማይከተሉ ሰዎች የተሰጠ ስም ቢሆንም፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ግን ይህ ቃል እውነተኛውን አምላክ እግዚአብሔርን ለማያመልኩ ሁሉ የሆነ መጠሪያ ነው:: ምንም እንኳን ሃይማኖት ቢኖራቸውም፣ ሌሎችን አማልክት እስካመለኩ ድረስና እውነተኛውን አምላክ እስካላወቁ ድረስ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ አቴይስት ናቸው:: የዚህ ቃል ምንነት በተለይ በገላትያ 4፣8 በግልጽ ተብራርቷል:: እንግዲህ አሕዛብ ያለ ክርስቶስ በሆኑበት ወቅት፣ አቴይስትም ነበሩ፣ ወይም ያለ እውነተኛውም አምላክ ነበሩ::

 

 

2.              የቀድሞው የአሕዛብና የአይሁድ ግንኙነት

ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች መሠረት የአሕዛብና የአይሁድ ግንኙነት በጣም የሻከረና እንዲያውም የጠላትነት ነበር:: “..ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ...” ቁ.16:: ቀደም ብለን እንዳየነው የሁለቱ ወገኖች የልዩነት መሠረት በሥጋ ማንነት ላይ የተመሠረተ ነው:: በሥጋ ከእስራኤል መወለድ ወይም አለመወለድ፣ በሥጋ መገረዝ ወይም አለመገርዝ ላይ የተመሠረተ ነበር:: በሥጋ ማንነት ወይም በትውልድ ወይም በቋንቋ ወይም በጾታ ወዘተ በግለሰቦችና በሕዝቦች መካከል ጠላትነትና መለያየት መፈጠሩ ይህ የተለመደ ነገር ነው:: በአሕዛብና በአይሁድ መካከል የነበረው መለያየት ከዚህ ከመደበኛው የዘር መለያየት የሚለየው፣ የብሉይ ኪዳን ሕግ የደነገገውና የሚፈቅደው መለያየት ስለሆነ ነው:: “በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ” ኤፌ 2፣14-15 ዘጸ 34፣12-17 ዘዳ 7፣1-5:: አይሁድ ከአሕዛብ ጋር ምንም አይነት ሕብረት እንዳያደርጉ፣ ጋብቻ እንዳይፈጽሙ፣ ቃል ኪዳን ከአሕዛብ ጋር እንዳይፈጽሙ ወዘተ ሕጉ ያዛቸው ነበር:: አላማውም አይሁድ ከአሕዛብ ጋር በማይመች አይነት መተሳሳር ተሳስረው ከእውነተኛው አምላክ ርቀው የአሕዛብን ጣኦታት እንዳያመልኩ ለመከላከል ነው:: ከዚህ የተነሣ አሕዛብና አይሁድ ምንም ሕበረት እንዳያደርጉ ሕግ የሚፈቅደው በመካከላቸው “ግድግዳ” ቁ.14-15 ነበረ የሐዋ 10፣28 የሐዋ 11፣2-3:: ስለዚህ አንድ ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ ጋር ሊኖረው ከሚችለው ጥላቻና መለያየት በላይ የሆነ እጅግ የጠበቀ መለያየትና በሕግ የተደነገገና የተለያየ አምላክ ከማምለክ የመነጨ ጥል በመካከላቸው እንደነበረ እናያለን::

 

3.              እርቅና ሰላም በክርስቶስ

በቁ. 13 ላይ “አሁን ግን” ብሎ ጳውሎስ ከላይ የተዘረዘረው የአሕዛብና የአይሁድ ሁኔታ በዛው እንዳልቀረና አሁን በክርስቶስ ፈጽሞ እንደተለወጠ ያመለክታል:: እዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገባን በአሕዛብና በአይሁድ መካከል የነበረውን ጠላትነት ለመለወጥና ሁለቱን አንድ ለማድረግ ብቸኛና ዋና የእግዚአብሔር መፍትሔ ክርስቶስ ነው እንጂ፣ ዲፕሎማሲ ወይም ፖለቲከኞች ወይም ከሁለቱ የተውጣጡ የሕዝቦች መሪዎች አይደሉም:: ምክንያቱም የአሕዛብና የአይሁድ ጥል የተለመደና መደበኛ የሕዝቦች ግጭት ሳይሆን ሶስት ዋና ዋና መንስኤዎች ያሉት ነው:: እነዚህም የሥጋ ትውልድ ወይም የሥጋ መገረዝ ወይም ባጠቃላይ በሥጋ ያለ ልዩነት፣ ከዚህም የተነሣ ደግሞ የተለያዩ አምላኮችን ማምለክና ስለዚህም በሕግ የተደነገገ መለያየት ወይም ሕግ የሚፈቅደው ግድግዳ ናቸው:: ክርስቶስ ለእነዚህ ሁሉ መሠረታዊ ችግሮች ነው በመስቀሉ ላይ መፍትሔ የሰጠው::

 

·       የክርስቶስ ደም:- ክርስቶስ በመስቀሉ የሠራው የመጀመሪያው ነገር የሰዎች ኃጢአት በደሙ እንዲሰረይ በማድረግ ከእግዚአብሔር ጋር ማስታረቅ ወይም ወደ እግዚአብሔር “ማቅረብ” ነው:: “በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል::” ቁ.13:: “...ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም::” ዕብ 9፣22:: የመጀመሪያው ሥራ እንግዲህ እግዚአብሔርን የሚያውቁትንም እስራኤላዊንን እንዲሁም እግዚአብሔርን የማያውቁትን አሕዛብ ከእግዚአብሔር ጋር ማስታረቅ ነው “ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው::” ቁ.16:: ይህ ሁለቱንም ከእግዚአብሔር ማስታረቁ ሁለቱም አንድ አምላክ እንዲያመልኩ የሚያደርግ ነው:: ይህም በፊት ለነበረባቸው የተለያየ አምላክ የማምለክ ችግር መፍትሔ ነው::

 

·       የክርስቶስ ሥጋ:- ክርስቶስ በመስቀሉ የሠራው ሌላው ነገር በሥጋው የሠራው ሥራ ነው:: ይሄውም በክርስቶስ ሞት አሮጌው ማንነታችን ወይም ሥጋችን አብሮ መሞቱና እኛ መሰቀላችን ነው:: የክርስቶስ ሞት እንግዲህ አሮጌውን ማንነታችንንም ያጠቃለለ ሞት በመሆኑ:-

·       ከሕግ እንድንፈታ አድርጎናል:- “እንዲሁም፣ወንድሞቼ ሆይ፣ እናንተ ደግሞ በክርስቶስ ሥጋ ለሕግ ተገድላችኋል፣ ለእግዚአብሔር ፍሬ እንድናፈራ፣ እናንተ ለሌላው፣ ከሙታን ለተነሣው፣ ለእርሱ ትሆኑ ዘንድ::” ሮሜ 7፣4:: ባልና ሚስት ከሁለት አንዱ ሲሞት ከትዳር ሕግ እንደሚፈቱ (ሮሜ 7፣1-3)፣ እንዲሁም እኛ በክርስቶስ ሥጋ ስለተገደልን ከታሠርንበት ሕግ ተፈትተናል “...አሁን ግን ለእርሱ ለታሰርንበት ስለ ሞትን፣ ከሕግ ተፈትተናል፣ ስለዚህም በአዲሱ በመንፈስ ኑሮ እንገዛለን እንጂ በአሮጌው በፊደል ኑሮ አይደለም::” ሮሜ 7፣6 “በአዋጅ የተነገሩትን የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ” ቁ.14-15:: በክርስቶስ ሞት ምክንያት አይሁድም አሕዛብንም የሚያጠቃልል አዲስ ኪዳን ውስጥ እንጂ አሮጌው ኪዳን ውስጥ ስለሌለን፣ በብሉይ ኪዳን በአዋጅ የተደነገገው በሥጋ የሆነ የአሕዛብና የአይሁድ መለያየትና ግድግዳ በአዲሱ ኪዳን ውስጥ አይሰራም:: አዲሱ ኪዳን መንፈስ ላይ እንጂ ሥጋና ትውልድ ላይ ያተኮረ ኪዳን አይደለምና::

 

·       ጥልን ገድሏል:- ከላይ ባየናቸው ክፍሎች እንደተመለከትነው የጥል ሁሉ ምንጭ በሥጋ ያለ ማንነታችን እንደሆነ ተመልክተናል:: የጥሉ መንስኤ ሥጋ ስለሆነ፣ የሥጋ ትውልድ፣ ማንነትና ትምክህት እስካልተገደለ ድረስ ጥል አይገደለም:: በክርስቶስ ሞት ጥል የተገደለው ለጥል መንስኤ የሆነው የሥጋ ማንነታችንና ትምክህታችን ከክርስቶስ ጋር አብሮ ስለተሰቀለ ነው ሮሜ 6፣1-11:: ሥጋ ሳይሰቀል ጥል ሊጠፋ አይችልም:: አይሁድም ድሮ የሚመኩበት አይሁዳዊነት አሕዛብም ድሮ የነበሩበት አሕዛብነት በክርስቶስ መስቀል ላይ ፍጻሜ አግኝቶአል ፊል 3፣3-7:: የክርስቶስ መስቀል የሥጋ ፍጻሜ ነውና ገላ 6፣13-15:: በድሮው ኪዳን ውስጥ እጅግ ይጠቅም የነበረው የሥጋ አይሁዳዊነትና የሥጋ መገረዝ፣ ባጠቃላይ የሥጋ ማንነት በአዲሱ ኪዳን ምንም ጥቅም የለውም:: “በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና::” ገላ 6፣15

 

ማጠቃለያ:- ክርስቶስ በአሕዛብና በአይሁድ መካከል የነበረውን መለያየትና ጥል አስወግዶ በሁለቱ መካከል እውነተኛ ሰላም ፈጥሮአል:: ጥል እያለ ሰላም የለም! ጥል ሳይገደል ሰላም ሊኖር አይችልም! ክርስቶስ ግን ሰውን ከእግዚአብሔርና እርስ በርሱ የሚያስታርቅ እውነተኛ ሰላማችን ነው:: “እርሱ ሰላማችን ነውና” ቁ. 14:: እውነተኛ እርቅ የሚመጣው በይቅርታ ነው:: የይቅርታና የምሕረት ሁሉ መሠረት ከሆነው ከክርስቶስ መስቀል ውጪ እውነተኛ እርቅና ሰላም አይመጣም:: የሰላም አለቃ ከሆነው ከራሱ ከክርስቶስ ውጪ ሰላምና እርቅ የለም ኢሳ 9፣6::

 

በኤፌ 1፣9-10 እንዳየነው፣ የእግዚአብሔር ትልቁ ፈቃዱ በሰማይና በምድር ያሉትን በክርስቶስ ራስነት ሥር አንድ ማድረግና ማዋሃድ ነው:: ትልቁ የእግዚአብሔር የዘላለም አላማ የተለያዩና የተጣሉትን በክርስቶስ ማስታረቅና ወደ ሕብረት ማምጣት ወይም መጠቅለል ነው:: ወንጌል የእርቅና የሰላም ምሥራች ነው:: “መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፣ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ” ቁ. 17::

 

“ነገር ግን የሆነው ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው፣ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፣ በእኛም የማስታረቅን ቃል አኖረ:: እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች ነን ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን::”2ኛ ቆሮ 5፣18-20

 


“ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ።“
(መጽሐፈ ምሳሌ 3:3-4)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us