ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች » ኤፌሶን » ጥናት 8 (ኤፌሶን 2፣11-22 ለ) በክርስቶስ አንድ መሆን – ክፍል 2
Email this page to a friend Printer-friendly   Tuesday, 20 October 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦“
(የዮሐንስ ራእይ 3:14)

rss

Today's verse

ጥናት 8 (ኤፌሶን 2፣11-22 ለ) በክርስቶስ አንድ መሆን – ክፍል 2

pdf version

ይህን የጥናታችንን ክፍል በሚከተሉት አራት ነጥቦች ከፍለን ማጥናት ጀምረናል:: እነዚህም:-

1.              የቀድሞው የአሕዛብ ሁኔታ/state

2.              የቀድሞው የአሕዛብና የአይሁድ ግንኙነት

3.              እርቅና ሰላም በክርስቶስ

4.              አዲሱ ሕብረት

ናቸው::

 

ከላይ ከ1 እስከ 3 የተዘረዘሩት ነጥቦች በክፍል አንድ ጥናታችን የተመለክትን ሲሆን፣ አራተኛውን ነጥብ ደግሞ በዚህ በክፍል ሁለት ጥናታችን እናየዋለን::

 

4.አዲሱ ሕብረት

ክርስቶስ በሁለቱ መካከል የነበረውን ጥል ገድሎ፣ አሕዛብ እንደ አይሁድ እንዲሆኑ ወይም አይሁድ እንደ አሕዛብ እንዲሆኑ አላደረገም:: ነገር ግን ሁለቱንም የሚያቅፍ አንድ አዲስ ሕብረትና አዲስ ሕዝብ ወይም ወገን ነው የመሠረተው:: በዚያም የሥጋ ማንነት ምንም ሚና የማይጫወትበት ሕብረት ነው:: ስለዚህ በክርስቶስ ስለተፈጠረው ስለ አዲሱ አንድነት በዚህ ክፍል ውስጥ ጳውሎስ በሚከተሉት መግለጫዎች ያብራራዋል:-

 

·       አንድ መሆን ወይም መዋሐድ ቁ. 14:- “ሁለቱን ያዋሐደ” የሚለው አባባል በግሪኩ “ሁለቱን አንድ ያደረገ” የሚለውን ስንኝ ነው:: ክርስቶስ የፈጠረው አዲሱ አንድነት ከመዋሐድ በላይ የሆነ አንድ መሆን ነው:: ተመልሶ ሊለያይ እስከማይችል ድረስ አንድ መሆን:: ሁለት ሕዝብ ወይም ሁለት ወገን በክርስቶስ የለም፣ ነገር ግን ሁለቱም በክርስቶስ አንድ ሆነዋል:: እግዚአብሔር በክርስቶስ ያቀደውና የፈጠረው አንድነት እኛ ከምናስበውና ከምንገምተው አንድነት፣ ምን ያህል ያለፈና የጠበቀ ለመሆኑ በዮሐንስ ወንጌል ላይ የተጻፈው የጌታ ጸሎት ያሳየናል “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፣ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፣ አንተ እንደ ላክኽኝ ዓለም ያምን ዘንድ፣ አንተ፣ አባት ሆይ፣ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፣ እነርሱም ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምንሃለሁ:: እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ...” ዮሐ 17፣20-22:: በዚህ ክፍል ላይ ጌታ የሚጸልየው፣ የአማኞች አንድነት ልክ አብና ወልድ ያላቸው አንድነት አይነት የጠበቀ እንዲሆን ነው:: የአብና የወልድ አንድነትና ሕብረት ደግሞ ለዘላለም የነበረና ከማንኛውም አንድነት በላይ የጠበቀ ነው:: ስለዚህ ጌታ በቤተክርቲያን ሊፈጥር የፈለገው የአንድነት አይነት አብሮ ተስማምቶ ጎን ለጎን ከመኖር እጅግ ያለፈ አንድነት ነው::

 

·       አንድ አዲስ ሰው ቁ. 14-15:- ክርስቶስ የፈጠረው የዚህ አዲስ ሕብረት ሌላው መግለጫ/ማብራሪያ ስም “አዲስ ሰው” የሚል ነው:: “ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ”:: እዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገባን “ሁለታቸው” የሚለው ቃል አሕዛብንና አይሁድን የሚያመለክት ነው:: ምንም እንኳን አሕዛብ በቁጥር ብዙ ሰዎች ቢሆኑም እንደ አንድ በመቁጠርና አይሁድንም እንዲሁ እንደ አንድ በመቁጠር “ሁለታቸው” ይላቸዋል:: ከሁለታቸው የተፈጠረውንም አዲስ ሕብረት ምንም እንኳን በውስጡ አሕዛብንም አይሁድንም ያቀፈ የብዙዎች ሕብረት ቢሆንም፣ “አንድ አዲስ ሰው” ብሎ ይጠራዋል:: ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎችም እንደሚሉት ይህ አባባል እያንዳንዳችን በግል በክርስቶስ ስለምንፈጠረው አዲስ ፍጥረትነት የሚናገር ሳይሆን፣ አዲስ የተፈጠረውን የአማኞች ሕብረት ወይም ቤተክርስቲያንን የሚያመለክት ነው:: ቤተክርስቲያን እንግዲህ በፊት ያልነበረች አሁን ግን በጌታ ደም የተፈጠረች “አንድ አዲስ ሰው” ናት:: ይህ አዲስ ሰው በፊት ያልነበረ ማንነት ነው ያለው:: ስለዚህ በዚህ በአዲስ ሰው ውስጥ ሌላ የሥጋ ማንነት ወይም አሮጌ ማነንት ወይም መለዮ የለም:: ሰለዚህ ቤተክርስቲያን ድሮ አሕዛብና አይሁድ ተብሎ ተክፍሎ ከነበረው ሌላ አዲስ ሕብረት እንደሆነች ነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸው “...ለአይሁድም ለግሪክም ሰዎች ለእግዚአብሔርም ቤተክርስቲያንም ማሰናከያ አትሁኑ::” 1ቆሮ 10፣33:: “አዲስ ሰው” በሚለው ስንኝ “አዲስ” የሚለው ቃል ራሱ ከአሮጌው ማንነታችን የተለየ አዲስ ማንነት እንዳገኘን የሚያሳይ ነው:: “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፣ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፣ ወንድም ሴትም የለም ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና::” ገላ 3፣28:: ልክ አንድ ሰው አንድ አምላክ፣ አንድ ዓላማ፣ አንድ ማንነት ወዘተ እንዳለው ሁሉ፣ በክርስቶስም የተፈጠረው ይህ አዲስ ሰው ሊለያይ እስከማይችል የጠበቀ ሕብረት ያለውን የቤተክርስቲያንን ሕብረትና አንድነት የሚገልጽ ነው::

 

·       አንድ አካል ቁ. 16:- በክርስቶስ የተፈጠረው በቤተክርቲያን ያለ ሕብረት ሌላው መግለጫ/ማብራሪያ “አንድ አካል” የሚል ነው:: “ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው”:: ይህ “አካል” የሚለው ሐዋርያው ጳውሎስ የቤተክርስቲያንን ሕብረት ለመግለጽ ደጋግሞ የተጠቀመበት አባባል ነው ኤፈ 1፣23 ኤፌ 4፣12 ቆላ 1፣18 ሮሜ 12፣5 1ቆሮ 12፣27:: አካል ድርጅት/organisation ሳይሆን organism ነው:: organism ለሚለው ቃል ፍቺ የoxford እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት እንደሚከተለው ያብራራዋል:- “living being with parts which work together; ...with parts dependent upon each other” ወይም በአማርኛ “በሕብረት/በቅንጅት አብረው የሚሠሩ ወይም እርስ በርስ ጥገኛ የሆኑ የአላል ክፍሎች ወይም ብልቶች ያሉት ሕይወት ያለው ነገር” ማለት ነው:: ምንም እንኳን በቤተክርስቲያን በተለይም በአጥቢያ ቤተክርስቲያን የተደራጀ ነገር ቢኖርም፣ ቤተክርስቲያን ግን አካል እንጂ ድርጅት ስላይደለች፣ አካል ከድርጅት የሚለይበትን አንዳንድ መለዮዎች ልብ ማለት ይገባናል:-

·       ሀ)አካል፣ በዓለም እንዳለ ድርጅት ወይም ፓርቲ በፈለግነው ጊዜ የአባል መታወቂያ በማግኘትና ሲያሻንም መታወቂያውን በመመለስ የምንገባበትና የምንወጣበት ነገር አይደለም:: የአካል ብልት፣ እርሱ እኔ የአካል ክፍል አይደለሁም ስላለ ብቻ የአካሉ ብልት መሆኑ አይቀርም:: “እግር:- እኔ እጅ አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ብትል፣ ይህን በማለትዋ የአካል ክፍል መሆንዋ ይቀራልን?” 1ቆሮ 12፣15:: ስለዚህ እንደ ድርጅት በአንዳንድ ነገር ስንስማማ የአካል ብልት፣ ሳንስማማ ደግሞ ከአካል ብልትነት ውጭ መሆን አይቻልም::

 

·       ለ)አካል እንደ ድርጅት ሰው በሚፈልገው መንገድ የሚያደራጀው አይደለም:: የእድገቱን አቅጣጫና የብልቶቹንም ስፍራ እንደ ድርጅት በሰው ፕላን መወሰን አይቻልም:: አካል እግዚአብሔር እንዳሰበለት የሚያድግ ነው:: ብልትም እንደዚሁ ጌታ ወዳሰበለት ተግባር ያድጋል እንጂ በሰው ፕላን አይሆንም:: አካል organisation ሳይሆን organism ነውና:: እድገቱንና የብልቶችን ተግባር ሰው መወሰን አይችልም:: “አሁን ግን እግዚአብሔር እንደ ወደደ ብልቶችን እያንዳንዳቸው በአካል አድርጎአል::” 1ቆሮ 12፣18

 

·       ሐ)በአካል ውስጥ እያንዳንዱ ብልት እርሱ ብቻ ሊሠራው ያለ የራሱ ሥራ ወይም ተግባር አለው:: እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን፣ በአካል ሁለት የቀኝ አይን ወይም ሁለት የቀኝ ጆሮ ወይም ሁለት የቀኝ እግር ወይም ሁለት የቀኝ እጅ እንደሌለ ሁሉ፣ እንዲሁም በቤተክርስቲያን በአንድ ቦታና ጊዜ ለአንድ ለተወሰነ አገልግሎት ወይም ሥራ የሚሽቀዳደሙ ሁለት ብልቶች መኖር አይገባቸውም:: ሁለት የቀኝ ጆሮ ያለው ሰው ብንመለከት፣ በዚያ ሰው አካል አንድ የተዛባ ነገር እንዳለ እንገነዘባለን:: ስለዚህ በቤተክርስቲያንም አንድ ሥራ ሁለት ብልት የሚባል ነገር የለም:: ቢሆንም ይህ የብልቶችን መዛባት የሚያመለክት ነው:: “አካል ሁሉ አይን ቢሆን መስማት ወዴት በተገኘ? ሁሉም መስማት ቢሆን ማሽተት ወዴት በተገኘ? አሁን ግን እግዚአብሔር እንደ ወደደ ብልቶችን እያንዳንዳቸው በአካል አድርጎአል:: ሁሉም አንድ ብልት ቢሆንስ አካል ወዴት በሆነ?” 1ቆሮ 12፣17-19::

 

·       መ)ስለዚህ በአካል ውስጥ ፉክክር የለም:: አካል በአንድነት ተቀናጅቶ የሚሠራ ሕያው ነገር/organism እንጂ እግር ከእጅ ጋር አይን ከጆሮ ጋር የሚፎካከሩበት፣ የሚወዳደሩበትና የሚገፋፉበት ስታዲየም አይደለም:: ይህ ምናልባት በድርጅት ወይም በአንድ ፓርቲ ውስጥ ወይም በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ ሊከሰት ይችላል:: አካል የተለየ በሽታ ካልያዘው በስተቀር፣ የአካል ብልቶች እርስ በርስ ሊፎካከሩና ሊገፋፉ በፍጹም አይችሉም:: ይህንን አይነት ነገር ማናችንም በአካላችን ብልቶች ላይ አላየንም:: ይህ የአካል ጠባይ አይደለም:: ይልቁኑ “አፍንጫ ሲመታ አይን ያለቅሳል” እንዲሉ፣ በብልቶች የሚሠራው መርሕ “አንድም ብልት ቢሠቃይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሠቃያሉ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል::” 1ቆሮ 12፣26 የሚል ነው:: ስለዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ “አካል” በሚለው የቤተክርስቲያን አንድነት መግለጫ ውስጥ ሊያስተላልፈው የሚፈልገው አንዱ መልእክት፣ በሕብረትና በመስማማት በአንድነት በመቀናጀት እንደ አካል ለአንድ አላማ መሥራት እንጂ መገፋፋትና መፎካከር ይባስ ብሎም ጥል በአንድ አካል ጨርሶ የማይገመት መሆኑን ለማሳየት ነው:: “ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው” የሐዋ 4፣32::

 

·       በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት ቁ. 18:- በቀድሞው ኪዳን የአይሁዳዊ ሕብረትና አንድነት መሠረቱ በሥጋ ወገንነት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ፣ የአዲሱ ሕብረት ዋና መሠረት አንድ መንፈስ ወይም መንፈስ ቅዱስ ነው:: “አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና:: ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል::” 1ቆሮ 12፣13:: አዲሱን ሕብረት እንደ አካል የሚያያይዝና የሚያስተሳስር፣ ዘር ወይም ቋንቋ ወይም የትምህርት ደረጃ ወይም የኑሮ ደረጃ ወይም የሥጋ መገረዝ ወዘተ ሳይሆን፣ በብልቶች ሁሉ ውስጥ የሚኖር መንፈስ ቅዱስ ነው:: ስለዚህ በአዲሱ ሕብረት የተለያየ መንፈስ ሳይሆን አንድ መንፈስ ስለሚሠራ፣ እውነተኛ አንድነትና ትብብር ሊኖር ይችላል:: በተቃራኒው ግን የተለያየ መንፈስ ካለ፣ ስምምነት ሊኖር አይችልም:: “...እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግስት ሁላ ትጠፋለች፣ እርስ በርሱ የሚለያይ ከተማም ሁሉ ወይም ቤት አይቆምም:: ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያወጣ ከሆነ፣ እርስ በርሱ ተለያየ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች?” ማቴ 12፣25-26 “እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፣ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች::” ማቴ 12፣28:: እግዚአብሔር መንፈስ ነውና ወደ አብም የምንገባው ወይም ወደ ፊቱ የምንቀርበው በሌላ መንገድ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ብቻ ነው:: ይህም ያንን መንፈስ የጠጣን ሁሉ አንድ አምላክና አባት የሆነ አብ እንዳለን ያመለክታል::

 

·       ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ቁ. 19:- ይህ “ባላገሮች” የሚለው ቃል የአንድ አገር ዜጎች ወይም የአንድ አገር ልጆች ማለት ነው:: አሕዛብ በፊት ከእስራኤል መንግስት የራቁ፣ ለተስፋውም ቃል እንግዶች ነበሩ:: አሁን ግን በአዲሱ ሕብረት አሕዛብም አይሁድም የአንድ አገር ልጆችና የአንድ ቤተሰብ አባላት ሆነዋል:: እርስ በርስ እንደ እንግዶች(ባዕዳን/የውጪ ዜጎች) እና እንደ መጻተኞች(ስደተኞች ወይም በሚኖርበት አገር ውስጥ ሙሉ የዜግነት መብት የሌለው) አይተያዩም:: ነገር ግን የአንድ አገር ልጆችና ዘመዳሞች ከዚህም በላይ የአንድ አባት ልጆችና ወንድማማቾች ሆነዋል:: ሰው የራሱን አገር ልጅ የሚያይበት አይንና የሚቀርብበት አቀራረብ የሌላውን ዜጋ ከሚያይበት አይንና ከሚቀርብበት አቀራረብ ብዙ ጊዜ ይለያል:: ከአንድ አገር ልጅ ጋር ቶሎ መቀራረብና ሕብረት ማድረግ ይቻላል:: ከአንድ አገር ልጅነት በላይ ደግሞ የአንድ አባት ልጅነት ወይም ቤተሰብነት እጅግ ይበልጣል:: ቤተሰብ ተለያይቶ የማይለያይ፣ ከማንም በላይ እርስ በርስ የሚደራረስና የሚደጋገፍ፣ አንዱ ለአንዱ የመቆርቆር ስሜት ያለው ነው:: የሥጋ ቤተሰብነት በምርጫ የሚመጣ ሳይሆን በትውልድ ነው:: የመንፈስም ቤተሰብነት የቤተሰብን አካል በመምረጥ የሚመጣ ሳይሆን ከአንድ አባትነት የመንጨ ወንድማማችነት ነው:: በሰዎች ዘንድ ካለው መተሳሰርና ሕብረት ሁሉ፣ ከቤተሰብ የቀረበ አንድነትና ሕበረት የለም:: የቤተሰብ ሕብረት እንደ ጓደኛ እርስ በርስ በመግባባት ላይ ብቻ የተመሠረተ ሳይሆን በደም የተሳሰረ ዝምድና ስላለ፣ እድሜ ልክ የሚቆይ ሕብረት ነው:: በክርስቶስ የተመሠረተው አዲሱ ሕብረት እንግዲህ፣ ከአንድ አባት የተነሳ ለዘላለም የሚቆይ የጠበቀ ሕብረትና መተሳሰር ነው::

 

 

·       ሕንጻ/ቅዱስ ቤተ መቅደስ/የእግዚአብሔር መኖሪያ ቁ. 21-22:- አዲሱ በክርስቶስ የተመሠረተውን ሕብረት ጳውሎስ የሚገልጽበት/የሚያስረዳበት የመጨረሻው መግለጫ ደግሞ ሕንጻ ወይም ቅዱስ ቤተ መቅደስ ወይም የእግዚአብሔር መኖሪያ የሚለውን ነው:: በአንድ ሕንጻ ውስጥ ያሉ ድንጋዮች የአንድ ቤተ አካል እንደመሆናቸው፣ አሕዛብና አይሁድም እንደዚሁ በክርስቶስ የአንድ ሕንጻ አካል ሆነዋል:: ይህ ሕንጻ የሚከተሉት ባሕርያት አሉት:-

·       የሐዋርያትና የነብያት መሠረትነት:- ይህ አዲሱ ሕብረት የተመሠረተው ሐዋርያትና ነብያት በተገለጠላቸው በክርስቶስ ላይ ነው::  እዚህ ላይ የተጠቀሱት ነብያት የብሉይ ኪዳን ይሁኑ የአዲስ ኪዳን ባይገለጥም፣ ኤፌ 3፣5-6 ላይ ያለውን ስንመለከት፣ በዚህም ክፍል የተጠቀሱት ነብያት የአዲስ ኪዳን ነብያት ሳይሆኑ አይቀርም የሚል ግምት እንደንይዝ ያደርገናል:: በሐዋርያትና በነብያት መሠረት ላይ ወይም በተገለጠላቸው የክርስቶስ ሚስጥር መገለጥ ወይም በእነርሱ ትምህርት ላይ መመሥረት በጣም ወሳኝነት አለው:: የመጀመሪያዋን ቤተክርስቲያን ስንመለከት “በሐዋርያት ትምህርት” ይተጉ እንደነበር እናያለን የሐዋ 2፣42:: ጢሞቴዎስም ሌላ ትምህርት ሳይሆን ከጳውሎስ የሰማውን ትምህርት ለሌሎች እንዲያስተላልፍ ይመከራል 2ጢሞ 2፣2:: ስለዚህ የቤተክርስቲያን መሠረት የሐዋርያት ትምህርት ነው እንጂ ከሰው አስተሳሰብና ግምት የሚመንጭ ሃሳብ አይደለም:: በጥሩ መሠረት ላይም ያልተመሠረተ ሕንጻ ጸንቶ ሊቆም እንደማይችል በሐዋርያት መገለጥና ትምህርት ላይ ሳይሆን በሰዎች ጥበብና ልምምድ ላይ የተመሠረተ ሕብረት ሁሉ የጸና ሊሆን አይችልም::

 

·       የማዕዘን ራስ ድንጋይና የሕንጻ መጋጠም:- በድሮ ጊዜ የሚገነቡት ሕንጻዎች ሁሉ የማዕዘን ድንጋዮች (cornerstone) ነበሩአቸው:: እነዚህ ድንጋዮች ሁለት ግድግዳን የሚያያይዙ በማዕዘን ወይም በመጋጠሚያ ላይ የሚውሉ ድንጋዮች ናቸው:: ከነዚህ ድንጋዮች ውስጥ ሕንጻው ሲታነጽ በመጀመሪያ ላይ የሚውለው የመጀመሪያው ድንጋይ “ዋና የማዕዘን ድንጋይ” ወይም “የማዕዘን ድንጋዮች ሁሉ ራስ/ዋና” ወይም “የማዕዘን ራስ ድንጋይ” (chief cornerstone) ይባላል:: እዚህ ላይ “ራስ” የሚለው ቃል ዋና ወይም አለቃ የሚለውን ለማመልከት እንጂ የሕንጻውን ከፍተኛ ቦታ ወይም የሕንጻውን አናት ለማመልከት አይደለም:: እንዲያውም የማዕዘን ራስ ድንጋይ ሕንጻው ሲታነጽ የመጀመሪያው ድንጋይ በመሆኑ፣ ከሕንጻው ታችኛው ክፍል ላይ ነው የሚውለው:: የማዕዘን ራስ ድንጋይ (ዋና የማዕዘን ድንጋይ) በተለይ ሁለት ዋና ዋና ተግባራ አሉት:: እነዚህም:- ድንጋዩ ማዕዘን ላይ ስለሚውል ሁለት ግድግዳዎችን ያያይዛል፣ እንዲሁም የሕንጻው ታችኛው የመጀመሪያው ክፍል ስለሆነ ወደ ጎንም ይሁን ወደ ላይ የሚገነቡት ድንጋዮች ቅርጽ ምን እንደሚሆን ይወስናል ወይም በሌላ አነጋገር፣ ሌሎቹ ድንጋዮች በሙሉ ከእርሱ ጋር እንዲገጥሙ ተደርገው መጠረብ አለባቸው:: አሕዛብና አይሁድ አብረው በሚሰሩበት በእግዚአብሔር መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ወይም ቤተክርስቲያን፣ የማዕዘኑ ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ነው:: እርሱ ነው አሕዛብና አይሁድን ያገጣጠመው ወይም አንድ ያደረገው:: እርሱ ነው የሕንጻውን ቅርጽ የሚወስነው:: ይህም ማለት እኛ ሁላችን የእርሱን ቅርጽ እንድንመስል እንጠረባለን ማለት ነው:: “በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል” ቁ. 21::

 

 

 

cornerstone

 

 

 


·       ማጠቃለያ:- ቤተክርስቲያን እንግዲህ አህዛብም አይሁድም በመንፈስ አንድ ሆነው፣ ለእግዚአብሔር ማደሪያነት በመንፈስ የሚገጣጠሙበትና የሚሠሩበት/የሚታነጹበት አንድ ትልቅ የእግዚአብሔር መንፈሳዊ ማደሪያ ናት:: በብሉይ ኪዳን በእስራኤል አንድ ቤተ መቅደስ እንደነበረ፣ እንዲሁም በአዲስ ኪዳን አማኞች ሁሉ እንደ ድንጋይ የሚታነጹበት ብቸኛው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቤተክርስቲያን ናት:: እዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገባን፣ ሕንጻው ሁሉንም አማኞች የሚያቅፍ አንድ ብቻ እንደሆነ ነው:: እያንዳንዳችንም የሕንጻው ድንጋዮች ነን:: “በሰውም ወደ ተጣለ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠና ክቡር ወደ ሆነው ወደ ሕያው ድንጋይ ወደ እርሱ እየቀረባችሁ፣ እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ::...” 1ጴጥ 2፣4-6::

 

 

 


“ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ።“
(መጽሐፈ ምሳሌ 3:3-4)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us