መጽሃፍ ቅዱስ በእውነትና ከልብ እንድንጸልይ እንጂ የዓይን አጨፋፈን ወይም አከፋፈት ትዕዛዝ አልሰጠንም። ስለዚህ ዓይንን መጨፈንም ይሁን መግለጥ የሚጸልየው ሰው እንደተመቸው ማድረግ ይችላል። አዲስ ኪዳን ግድ የሚለው የሥርዓት ጉዳይ ሳይሆን የልብ ጉዳይ ነው። መጸለዩ አይደለም ቁምነገሩ፤ ይህንንማ እንደ ሥርዓትና ተደጋጋሚ ልምድ ብዙ የሚጸልዩ ሰዎች አሉ። ቁም ነገሩ ግን የጸለይነው መሰማቱ ላይ ነው። የሚሰማው ደግሞ ከልብና በእውነት ስንጸልይ ብቻ ነው እንጂ ዓይናችንን ስለከፍትን ወይም ስለዘጋን አይደለም። ብንፈልግ ተንበርክከን፣ አለዚያም ቆመን ወይም ተቀምጠን መጸለይ እንችላለን። ስንፈልግ አይናችን ከፍተን ወይም ደግሞ ጨፍነን መጸለይ እንችላለን። የቦታም ጉዳይ አይደለም ነገሩ፤ ማለትም ቤተክርስቲያን ወይም ሩቅ ቦታ ሄዶ መጸለዩ ወይም የገዛ ቤት ውስጥ ሆኖ መጸለዩም አይደለም ዋናው ጉዳዩ። ይህ ሁሉ ውጪያዊ ሥርዓት ነው፤ በዚህ ወደ እግዚአብሔር አንቀርብምም፤ ከእግዚአብሔርም አንርቅም። በእውነትና በመንፈስ እግዚአብሔርን ማምለኩ ነው ቁም ነገሩ።
Quote:
የዮሐንስ ወንጌል 4
19 ሴቲቱ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ።
20 አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተም። ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው።
21 ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል።
22 እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን።
23 ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤
24 እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።
እንግዲህ በጸሎት ላይ ዓይን የሚጨፍንም ይሁን ዓይን የሚገልጥ ምንም ያጠፋው ወይም የሰራው ስህተት የለም። ብቻ በእውነትና ከልብ ይሁን!