ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » ጥያቄ መጠያየቂያ
Email this page to a friend   Tuesday, 24 November 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ፥ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።“
(መዝሙረ ዳዊት 27:14)

rss

Today's verse

የሚያስጨንቀኝ አንድ ነገር አለ፡፡

በጌታ የተወደዳችሁ ወገኖች ሰላም ለናንተ ይሁን!

እኔና ባለቤቴ ከተጋባን አስር ዓመት የሆነን ሲሆን አራት ልጆችንም ወልደናል፡፡ይህንን ያህል ጊዜ አብረን ስንኖር በመሃላችን የጎላ ጸብ ተፈጥሮ አያውቅም፡፡ እርሱ በባህሪው ጊዜያዊ አኩራፊ ቢሆንም በተቻለኝ አቅም ስህተቴን አርሜና የእርሱ ጥፋትም ከሆነ በሌላ ቀን እንድንነጋገር አድርጌ ክፍተታችንን እሞላዋለሁ፡፡

ነገር ግን በኑሮአችን ውስጥ ከባድ ሚስጥር የሆነና እኔን በብዙ የሚያስጨንቀኝ አንድ ነገር አለ፡፡

በወሲብ ጊዜ አልፎ አልፎ የሚጠይቀኝ ያልተለመደና ወጣ ያለ ለኔም ምቾትን የሚነሳኝና ህመም ያለው የግንኙነት ፍላጎት አለው፡፡ “ተው አይሆንም!” ስለው ፈጽሞ ደስተኛ አይደለም፡፡ ስሜቴን ገደልሽብኝ ብሎ ይቆጣል፡፡ ኋላ ቀርና ያልሰለጠንኩ አድርጎም ያስበኛል፡፡

በዚህ የተነሳ በውስጤ ከባድ የሆነ ፍርሃት አድሮብኛል፡፡ ”ባለቤቴን ይህን ድርጊቱን እንደማልወደው ረገጥ አድርጌ ብነግረው ይጠላኝ ይሆን? ወደሌላ ነገርስ አይገፋፋውም?“ ብዬ እጨነቃለሁ፡፡ በዝምታ እንዳልቀጥል ደግሞ ውስጤ ፈጽሞ ደስታ እያጣ ከሱ ጋር መተኛቱን ሁሉ እየጠላሁ ነው፡፡ አልጋችንን ሳስበውም ድብር ይለኛል፡፡ አምላክስ ቢሆን ምን ይላል ብዬ ውስጤ ይረበሻል፡፡

ከቤት የሚያርቀው ጉዳይ በመጣ ቁጥር ውስጤን የሚሞላው ደስታ እኔና ፈጣሪ ነን የምናውቀው፡፡ ባለቤቴ እንዳያውቅብኝ ግን ትክዝ እላለሁ፡፡

እባካችሁ ወገኖች በዚህ ሁኔታ መቀጠሉ እየከበደኝ ነው፡፡ ትዳሬን የማጣት ስጋትም እየገባኝ ነውና ምክራችሁን እሻለሁ፡፡
May 10, 2012 መንፈሳዊ ስም-አልባ የተጠየቀ

2 መልሶች

0 ድምጾች
ውድ እህታችን ጭንቀትሽ ከባድ መሆኑ ይሰማኛል። በእርግጥም ውጥረት የነገሰበት ሁኔታ ውስጥ ነሽ። ምንም እንኳን የባለቤትሽ የወሲብ አፈጻጸም ፍላጎት ምን እንደሆነ መግለጽ ባትፈልጊም በአጠቃላይ ከተለመደው ኢትዮጵያዊ ባህልና ወግ ወጣ ያለ የዘመኑ የወሲብ አደራረጎች ተነስተን ልንገምተው የምንችለው ነገር ስላለ ያንን ተመርኩዤ ጥቂት ለማለት እወዳለሁ።የምንነጋገረው ማኅበራዊ የትዳር አኗኗር ምስጢርን በመሆኑ ጉዳዩን በግልጽ እንነጋገር።
ስለወሲብ አፈጻጸም መንገዶች መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው ምንም ነገር የለም። እርግጥ ነው በክርስትናው አስተምህሮ ግብረ ሰዶማዊ (በዓይነ ምድር መውጫ) ወሲብን መጠቀም እጅግ ከባድ ኃጢአት እንደሆነ ነው። ግብረ ሰዶም የተመሳሳይ ጾታ ግብረ ሥጋ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን በወንድና በሴት መካከል ሊደረግ የሚገባውን ጾታዊ ግንኙነትም እግዚአብሔር ለዚሁ አገልግሎት በፈጠረው በዘር መራቢያ አካል ሳይሆን ሲቀር እንደሆነም እንገነዘባለን። በሴትና በወንድ መካከል የሚደረገውን ጾታዊ ግንኙነት እንደቅቡል ድርጊት ወስደን (አዳምም ሚስቱን ሔዋንን አወቀ ፀነሰችም፥ ቃየንንም ወለደች። እርስዋም፦ ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር አገኘሁ አለች) ዘፍ 4፤1አፈጻጸሙን በተመለከተ ብንቃኝ በኑሮአችን ውስጥ ተቀባይነት ያላቸውና ያልተለመዱ ተብለው የሚለዩት የሕብረተሰብ አመለካከቶች አሉ።
ነገር ግን የወሲብ አደራረጎች ከቤተሰብ፣ ከማኅበረሰብና ከህብረተሰብ ብሎም ከአንድ ሕዝብ አኗኗር፤ ባህል፤ ወግና እምነት ጋር የሚያያዝ እንደሆነ የስነ ልቡና ሊቃውንት ይናገራሉ። ከዚህም የተነሳ ከአንድ አካባቢና ሀገር የሌላው ባህል የተለየ ነው።
እኛ ግን እህታችን ከላይ ካቀረበችው ጥያቄ አንጻር እንደኢትዮጵያው ባህልና እንደክርስቲያናዊ አመለካከት የትዳር ጠንቅ አፈጻጸሞችን ለማቃናት ስንሞክር፤
1/ክርስቲያን ባለትዳሮች በምንም ዓይነት መልኩ ዘርን ከሚተኩበት፤ አዳምና ሔዋን ከተዋወቁበት የመራቢያ አካላቸው ውጪ ወሲብ መፈጸም የለባቸውም። ከዚህ ውጪ ያለው ግብረ ሰዶም ነው። ይህንን አስረግጠን መናገር ይገባናል። ምክንያቱም እኛ ለወሲብ የተቀበልነው የአዳምና የሔዋንን የዘር መንገድ ብቻ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናልና ነው።
2/ በተራቁጥር 1 ላይ የተጠቀሰው የዘር መራቢያ ሩካቤ እንደተጠበቀ ሆኖ ባህላዊውና ልምዳዊው የወሲብ አፈጻጸም በመኝታ ላይ በጎን ወይም ወንድ ከላይ ሆኖ የሚፈጸመው የወሲብ ዓይነት በኢትዮጵያችን ሕዝቦች ማኅበራዊ አኗኗር ሥነ ልቦናዊ ተቀባይነት ያለው ስለሆነ ይኼው ይደገፋል።
3/ ከላይ እንደጠቀስነው ወሲብ ባህልን፤ወግን፤ እውቀትንና እና ሥነ ልቡናን መሰረት የሚያደርግ እንደመሆኑ መጠን ሁለት ባለትዳሮች የወሲብ አፈጻጸማቸውን ጤናማ ማድረግ የሚችሉት የጋራ ግንዛቤና ስምምነት ሲኖራቸው ብቻ ነው። ሴቷ ከላይ ሆና ወንዱ ከሥር ለመተኛት ቢፈልግ ሴቷ ላትቀበል ትችላለች። በወሲብ እንቅስቃሴ ወቅት የጋራ እንቅስቃሴ መኖር አስፈላጊ ሆኖ ሳለ የወንዱ የብቻ ድርሻ አድርጋ ሴቷ ልትቆጥር ትችላለች። ይህን አመለካከት የወንዱን ስሜት ሊጎዳ ወይም ወሲብ የጋራቸው ሳይሆን የግሉ እዳ እንደሆነ ሊቆጥረው ይችላል። በስሜት መጎዳት ውስጥ ሆኖ ሚስቱ ምንም ግድ የማይሰጣት እቃ የሆነች ያህል ሊያስባትም ይችላል። የ40 ዓመት ጎልማሳ የሆነው ካናዳዊው ሪኪ ሞንተሮማን ስለሚስቱ የወሲብ ፍላጎት ምቹ አለመሆን «እኔን በሚመቸኝ ወይም ሁለታችንንም በሚያስደስተን ወሲብ አደራረግ ላይ ሚስቴ ግድ የላትም» ሲል ገልጾ በዚህም ትዳሩን መጥላቱን ለትዳር አማካሪው አስረድቷል። በመቀመጥ ወይም በመቆም ወይም በማጎንበስ ወሲብ ማድረግ ሲፈልግ የሚስቱ ዳተኝነት ወደፍቺ እንያደርሰው ስጋቱን ጨምሮ ገልጿል። ሚስት ቀድሞ ባልለመደችው ዓይነት ወሲብ ለማድረግ የባል ጫና ለትዳር መናጋት ወይም ትዳር አይሉት ደባልነት አስቸጋሪ በሆነ የኑሮ ሕይወት ሊጋብዝ ይችላል።
4/ «one flesh» በተሰኘው መጽሐፋቸው ኤሚሊያና ግሪግ ክሌርክ የክርስቲያን ወሲብ አፈጻጸም በ1ኛ ቆሮ 7፣3-5 ያለውን በማብራራት «
ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፥ እንደዚሁም ደግሞ ሚስቲቱ ለባልዋ።ሚስት በገዛ ሥጋዋ ላይ ሥልጣን የላትም፥ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ደግሞ ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም፥ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ።
ለጸሎት ትተጉ ዘንድ ተስማምታችሁ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፥ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ ደግሞ አብራችሁ ሁኑ»

የባል ስጋ የሚስት፤ የሚስት ስጋ የባል እንደመሆኑ መጠን እርስ በእርስ ሳይከላከሉ ነገር ግን የጋራ ስምምነትና ፈቃድን የተከተለ መሆን እንዳለበት አበክረው ያስረዳሉ።
አለበለዚያ ወሲብ የሚያደርጉት እርስ በእርሳቸው ከወሲብ የሚገኘውን የእግዚአብሔር ስጦታን በእርካታ ለመፈጸምና ፈጣሪን የሚባርክ ትውልድ ለማስቀረት መሆኑ ይቀርና ስሜታቸው የሚመኘውንና የሚነዳቸውን ፍላጎት ለመተግበር የሚጠቀሙበት ቁስ ወደ መሆን ይሻገራል» ሲሉ ጨምረው ይናገራሉ። ስለዚህ በዚህ መካከል ችግር ካለ ቁጭ ብለው እንደእግዚአብሔር ሰዎች ሊነጋገሩ የተገባ ነው ይሉናል። የሰው ልጅ የወሲብ የሆርሞን አወቃቀር የተለያየና መጠኑ ከፍና ዝቅ ያለ ስለሆነ ከወሲብ የሚገኘውን እርካታ ለማግኘት ክርስቲያን ባለትዳሮች በደንብ መተዋወቅና መናጋገር ይገባቸዋል ሲሉ ያሰምሩበታል።
5/ ከላይ በዝርዝር እያየን እንደመጣነው እህታችን የጠየቀችውን ሃሳብ ስንመዝንና ባልየው ለወትሮው የማያውቀውንና የማያደርገውን አዲስ የወሲብ ስርዓት መጀመሩን፣ ይህንንም ያልተቀበለች ሚስትን ስልጣኔ እንደጎደላት መመልከቱና እሱ ግን ነገር ሁሉ እንደገባው፤ ሚስትም እሱን ለማስደሰት ስትል ብቻ ህመም የሚሰማትን ወሲብ ለመፈጸም እንደተገደደች ነገር ግን ምንም ደስታ እንዳጣችበት የሰጠችንን ፍንጭ ስንገመግም፤
ሀ/ ባል አሁን አዲስ ወሲብ ወደማወቅ ያደረሰው መንገድ እና ለአዲሱ እውቀት የመረጃ ምንጭ ያለው መሆኑን፤
ለ/ ከለመዱት ውጪ ከሚስቱ ጋር ለሚያደርገው ወሲብ እንደክርስቲያን እርስ በእርስ ሳይከላከሉ ለመስማማት ባለመሞከር ይልቁንም የሚስቱን ግርታ እንደእውቀት ማነስ መቁጠሩ፤
ሐ/ በሚስቱ ላይ ካሳደረው ስነ ልቡናዊ ተጽእኖ ባሻገር ድርጊቱ ከወትሮ በተለየ ህመም የተቀላቀለበት መሆኑ
በአንኳር የሚነሱ ነጥቦች ናቸው። ከግብረ ሰዶማዊ ድርጊት ውጪ በሆነው የወሲብ አፈጻጸሞች አንጻር ፣ሀ-ሐ ያሉትን ስንመለከት ጥያቄ አቅራቢ እህታችን ትዳርንሽ አደጋ ላይ ከመውደቁ በፊት ቁጭ ብለሽ ልትነጋገሪበት ይገባል። ይህንን እውቀት ከየት እንዳመጣው፤ ለምን መፈጸም እንዳለባችሁ፣ ህመሙ ምንና እንዴት እንደሆነ መፍትሄውስ ምን መምሰል እንዳለበት በግልጽ መነጋገር ይገባችኋል። የምትነጋገሩት አንዱ የአንዱን ድክመት ለመተንተን ሳይሆን ስጋችሁን በእግዚአብሔር ፈቃድ ላይ አኑራችሁ ልትረኩበት መሆን ይገባዋል። የባለቤትሽ ክርስቲያንነት የት ድረስ እንደሆነም ግልጽ ባለማድረግሽ እነዚህን ጥያቄዎች ብታቀርቢለት የሚሰማውን ስሜት ለማወቅ ይከብዳል። ያንን ስናስብ ደግሞ በመነጋገር መፍትሄ ላይ ለመድረስ ከእኛ ግምት ይልቅ ያንቺ ግምገማ ወሳኝ ስለሆነ እሱንም አስቢ። ግን ያለሽበትን አጣብቂኝ ለመፍታት ከመነጋገር ውጪ ለችግርሽ የቅርብ መፍትሄ የለም። ከቅርብ ጓደኞችወይም የሚውልባቸው ተያያዥ ቦታዎች፤ ወሲብ ቀስቃሽ ፊልሞች፤ ፖርኖግራፊ(የወሲብ ፊልሞች) ወሲባዊ መጋዚኖች የመሳሰሉት ሁሉ ከሰው አእምሮ ጋር የሚያያዝ ተጽእኖን የማሳደር ብቃት ስላላቸው እነዚህን አካሄዶችንም ማጥናት ተገቢ ነው። ሰይጣን በዚህ ዘመን ክርስቲያኖችን ከሚዋጋበት መንገድ አንዱ እነዚህ የውጊያ ስልቶቹ ስለሆኑ በዚህ ጦር ላለመወጋቱ ምን ያህል እርግጠኛ ነሽ? ክርስቲያኖች ስጋችን እግዚአብሔርን ለመባረክ የተፈጠረ መሆኑን ካመንን ሀገራችን በዚህ የእርካታ ዓለም የሚያበቃ እንዳይደለም መረዳቱ የግድ ነው። ስለዚህ ባልሽ «እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ» ፊልጵ 2፤4 የሚለውን እስከየት ይቀበለዋል?
ይህንን የግል ማብራሪያ ማስረዘም ያስፈለገው ችግሩ የጠያቂ እህታችን ብቻ ሳይሆን ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ችግር ያለባቸው ሰዎች ያጋጠመኝ ስለሆነ ለጋራ ግንዛቤ እንዲረዳ ከማሰብ ነው። ለሚያርም ማስረጃን የተመረኮዘ ሃሳብ ዝግጁ ነኝ።
May 10, 2012 ብርሃን (1,840 ነጥቦች) የተመለሰ
0 ድምጾች
ሰላም እህቴ

እንደ እኔ አመለካከት አሁን ባለቤትሽ የሚያልፍበትን ለየት ያለ የወሲብ ፍላጎት ልክ ትልቅ ጉድ እንደመጣብሽ አድርገሽ ባታይው መልካም ነው እላለሁ። ምክንያቱም ብዙ ወንዶች በተለያየ የእድሜ ደረጃ ላይ የተለያየ የወሲብ ልምምድ ፍላጎትና የተለያዩ ነገሮችን የመሞከር (experiment) ባህርይ ይታይባቸዋል። ምንም እንኳን ግልጽ አድርገሽ የባለቤትሽን ፍላጎት ባትገልጪውም ትንሽ ከጠቀስሻቸው ቃላቶች የባለቤትሽን ፍላጎት በደንብ የተረዳሁት ይመስለኛል። ይህ ደግሞ በጣም ልዩ የሆነና እንዲያው የሚያስበረግግ አዲስ ክስተት አድርገሽ አትመልከችው። እንዲህ ያለ ለየት ያለ የወሲብ ፍላጎት በአሁኑ ሰዓት ስላለውም ብቻ ይህንን ፈልጎ ሌላ ሴት ጋ ይሄዳል ብለሽ ብዙም አታስቢ።

ወደ መፍትሄው ስንመጣ፤ አንደኛ አንቺ እንዲህ ያለውን የወሲብ ልምምድ በፍጹም የማትፈልጊ ከሆነ በሰላም ጊዜ ማለትም ምንም ዓይነት የወሲብ ፍላጎትና ሃሳብ በሌለው ቀንና ሰዓት ስለዚህ ጉዳይ በግልጽ አነጋግሪው። የእርሱን ፍላጎት በመውቀስ ወይም እንዲያው ልዩ ጉድ እንደሆነ አድርገሽ በመናገር ሳይሆን፤ አንቺ የሚሰማሽን የውስጥ ስሜትና የአካል ህመም በግልጽ ንገሪው። እርሱን ምንም ሳትነቅፊ፤ ይህ አዲስ ነገር ምን ያህል የአንቺን የውስጥ ስሜትና የወሲብ ፍላጎት እንደጎዳ፤ ምን ያህል ደግሞ አካላዊ ህመምም እንዳለው ወዘተ አንቺ ራስሽ የሚሰማሽን ሁሉ በመንገር እርሱ ለአንቺም እንዲያስብና የአንቺም ነገር እንዲሰማው ለማድረግ ሞክሪ።

እንዲህ ያለው አሁን በእርሱ ያለው የወሲብ ስሜት ከላይ እንዳልኩት በተወሰነ እድሜ የተወሰነ ጊዜ ሊወስድ ይችላልና ትንሽ ታገሺው፤ እርግጠኛ ነኝ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ይህንን ነገር እርግፍ አድርጎ እንደሚተወው።

ሌላው የምመክርሽ ነገር ሃሳቡ ብዙ ወደ መንፈሳዊ ነገር እንዲሆን ጊዜውን በተለይ የእግዚአብሔር ቃልን የሚማርበትና የሚያጠናበት ሁኔታዎችን ብታመቻቺ ወይም ሄዶ መጽሃፍ ቅዱስን የሚያጠናበት መንገዶችን ብታደርጊ ደግሞ ሃሳቡ ከወሲብ ልምምድ ሙከራዎች ወደ መንፈሳዊ ነገር ዘወር እንዲል ይረዳዋልና ይህንን ለማመቻቸት ሞክሪ።

በተረፈ ከላይ እንዳልኩሽ ይሄን ያህል በዚህ ምክንያት ወደ ሌላ ሴት ይሄዳል ወይም ትዳሩን ይተዋል ብለሽ መስጋት አያስፈልግሽም።
May 11, 2012 ስም-አልባ የተመለሰ
ከሰጠኸው አስተያየት ላይ የተወሰደ «እንዲህ ያለው አሁን በእርሱ ያለው የወሲብ ስሜት ከላይ እንዳልኩት በተወሰነ እድሜ የተወሰነ ጊዜ ሊወስድ ይችላልና ትንሽ ታገሺው፤ እርግጠኛ ነኝ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ይህንን ነገር እርግፍ አድርጎ እንደሚተወው»
ይህን ስትል ምን ማለትህ ነው? ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንደሚተወው ምን ያህል እርግጠኛ ነህ?
ለተወሰነ ጊዜ ድርጊቱን እንድትታገስ ስታደፋፍር፤ ለጉዳዩ ያለህ ሚስጢራዊ እውቀት እስከየት ድረስ ነው? የድርጊቱን ልምምድ እስክትዋሃድ ድረስ ባልየው ጊዜ እንዲያገኝ መፍቀድህ ነው? ልትሸከመው የምትችለው የትኛውን የወሲብ ልምምድ ነው? በተለያየ እድሜ ውስጥ ያሉ ወንዶች experiment ማድረግ የሚፈልጉት የወሲብ ዓይነት ከማን ጋር፤ እንዴትና ለምን የሚል መጠይቅ ከሌላኛው ወገን ቢቀርብስ መፍትሄው ምንድነው? አስተያየትህ አስገራሚ ነው!!
ቀጣይ አስተያትህ እንዲህ የሚል ነው።
«በተረፈ ከላይ እንዳልኩሽ ይሄን ያህል በዚህ ምክንያት ወደ ሌላ ሴት ይሄዳል ወይም ትዳሩን ይተዋል ብለሽ መስጋት አያስፈልግሽም»
እንዳትሰጋ የሚያደርጋትን ዋስትና አንተ በምን ማረጋገጫ ልትሰጣት ትችላለህ?
አዲስ ወሲብ ለመፈጸም ከባለቤቱ ጋር ለመስማማትና ለመነጋገር ያልቻለን ሰው ቢያሰጋት እንዴት ምክንያታዊ እንዳልሆነች ይቆጠራል? እንደማይተዋት ወይም ሌላ ዐመል እንደማያመጣ ዋስትና ለመስጠት የሚችል ሰው ቢኖር ጉዳዩን በይበልጥ የሚያወቅ መሆን አለበት እላለሁ። በግሌ አሁንም ደግሜ የምሰጠው አስተያየት ባልና ሚስቶቹ በስጋቸው እግዚአብሔርን እንዲያከብሩ፤ የወሲብ ግንኙነታቸውን በፍቅርና በስምምነት እንዲያከብሩ፤ ትዳራቸውን እንዲያከብሩ፣ ልጆቻቸውን በፍቅር እንዲያከብሩ በግልጽና በግልጽ መነጋገር አለባቸው። ሚስት በአዲስ ነገር እየተጨነቀች፤ በህመም እየተሰቃየች፤ መኝታዋን ጠልታ፤ ትዳሯ እንዳይፈርስባት ሰግታ፤ በባልዋ ላይ ያላትን እምነት አጥታ «የተወሰነ ፣ ጊዜ ሊወስድ ይችላልና ታገሺው» የሚል ምክር በእሷ ቦታ ራስን አስቀምጦ ያለማየት ችግር ነው። ትእግስት ማድረጓ፣ ለባሏ ስሜት ስትል ደስ ባትሰኝም መፈጸሟ፣ ለትዳሯ ያላትን ጭንቀት ማሰቧ በእውነት የሚያስደንቅ ክርስቲያን መሆኗን ያሳያልና ቀጥይበት ስላት በጉዳዩ ላይ ግን ፊት ለፊት መነጋገር ይገባታል። ባልየው በክርስቶስ ላይ ያለው እምነት ደካማ እስካልሆነ ድረስ በንግግር ሁለቱንም የሚያስማማ ውሳኔ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ። በጸሎት ወደ እግዚአብሔር አሳስቢ፤ ለትዳር ክቡርነት ስትይ በመነጋገር ለመስማማት ዋጋ ክፈይ፤ ግን ሁሉም በፍቅር ይሁን!!!!!!!
ወገኔ

ነገሩን እኮ ልክ እንደ ልዩ ነገር እንደመጣ አድርጎ በማጥበቅና በማክረር እኮ ትዳር ታፈርስ ይሆናል እንጂ ምንም የምታመጣው ነገር የለም። ይልቁን ሁኔታውን ረጋ ብሎ ይዞና ተነጋግሮ በጥበብ ማሳለፉ ነው የሚበጀው። እንዲያው ሁሉን ነገር እናክርር ካልን ትዳር አንድ ቀን አይቆምም።
ትዳር ሁለት ሰዎች ተስማምተው የሚኖሩበት የእግዚአብሔር ተቋም እንጂ ሁለት ሰዎች በግድ ውሳኔ የሚኖሩበት ጣሪያ አይደለም። እየተናጋገርን ያለነው ስለማጥበቅና ስለማላላት አይደለም። እግዚአብሔር የፈቀደውን ይህን የሁለት ሰዎች አንድ ሥጋ የመሆን ተቋም ችግሮች በመንቀስ ቀጣይ እንዲሆኑ ለማስቻል ነው እንጂ እንዲለያዩ በምንም መልኩ የምንደግፈው ነገር አይደለም። ግን ሁለቱ ሰዎች አንድ ስጋ መሆን እንዳልቻሉ እያየህ ማክረርና ማጥበቅ በሚል ቃላት ፍራቻ አንድ እንዲሆኑ ለማድረግ ችግሩን ከሚያባብሰው በቀር መፍትሄ አያመጣም። በግልጽ አማርኛ ቁጭ ብላችሁ ተነጋገሩ! በእግዚአብሔር አጋዥነት ወደ መፍትሄ ድረሱ። አንዳችሁ ለአንዳችሁ ሳትከላከሉ ተስማሙ ነው እያልን ያለነው!!
«ያልተጋባች ሴትና ድንግል በሥጋም በነፍስም እንዲቀደሱ የጌታን ነገር ያስባሉ፤ የተጋባች ግን ባልዋን እንዴት ደስ እንድታሰኘው የዓለምን ነገር ታስባለች» 1ኛ ቆሮ 7፤34
ባሏን እንዴት ደስ ማሰኘት እንደምትችል የስጋዋን ነገር በማሰብ የነፍሷን ነገር ልታጣ ይገባል? ባልስ የስጋውን ደስታ ብቻ እያሰበ የነፍሱን ነገር መዘንጋት አለበትን?
እኛስ እንደዚህ አይሁን ብለን ልንናገር እንዴት አይገባን? አሁንም አስረግጠን ሁሉም በአገባብና በስርዓት ይሁን እንላለን። ስናጠቃልል ትዳርን የሚያጠብቀው «ማክረርና ማጥበቅ» የተባሉትን ቃላት በመሸሽ ሳይሆን መተማመን፤ መነጋገር፤ መግባባትና መስማማት ሲኖር ብቻ ነው። እኔ ትዳር አለኝ። ችግር ያጋጥመኛል። ችግሬን የምፈታው በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብዬ በመነጋገር፤ በመወያየት ነው እንጂ ትዳሬ ይፈርሳል ብዬ ነገሮችን ሁሉ በመቅበር አይደለም።መቻቻልም ተገቢ መሆኑ ሳይዘነጋ ነው።
“እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ።“
(መዝሙረ ዳዊት 33:12)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us
...