ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » ጥያቄ መጠያየቂያ
Email this page to a friend   Sunday, 29 November 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ፥ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።“
(መዝሙረ ዳዊት 27:14)

rss

Today's verse

በ ዘፍ 6 ላዪ የስው ልድ የ አምላክ ልዽ አገቡ ዪላል .የ አምላክ ልዽ የተአባሉ ኢነማንናችው ?

Dec 17, 2012 መንፈሳዊ ስም-አልባ የተጠየቀ

6 መልሶች

0 ድምጾች
በዘፍጥረት 6 ላይም ሆነ በኢዮብ 2 ላይ የአምላክ ልጆች የተባሉት እግዚአብሔርን የሚከተሉ ሰዎች ናቸው። ካሁን ቀደም በሰፊው ስለ ተመለሰ እዚህ በመጫን ያንብቡ።
Dec 18, 2012 ስም-አልባ የተመለሰ
0 ድምጾች
እግዚአብሔር መላእክትን "ብዙ ተባዙ" አላለም። ስለዚህ መላእክት አያገቡም፣ አይወልዱም፣ አይሞቱም። እንደ እኛ ስለማይሞቱ ከቁጥር አይጎድሉም። ስለማይወልዱም በቁጥር አይጨምሩም። ጾታም የላቸውም። ስጋ ለባሾችም አይደሉም። በምግብ እና በውሃ እንደማይኖሩ ሁሉ በወሲብም አይደሰቱም፡፡ ያንተ ወንድነት ወይም ያንቺ ሴትነት ለእነርሱ ምንም አይነት ስሜት አይሰጣቸውም።

እግዚአብሔር መላእክትን ሲፈጥር ብዙ "ሚሊዮኖችን" በአንድ ጊዜ ፈጠራቸው። እንጂ ተቃራኒ ጾታ አድርጎ ሁለት መላእክትን ብቻ አልፈጠረም። ሁሉም መላእክት አንድ አይነት መናፍስት ናቸው እንጂ በእነርሱ መካከል የጾታ ክፍፍል /ጐራ/ የለም።

ነገር ግን እግዚአብሔር ሰዎችን (ስጋ ለባሾችን) ሲፈጥር፣ ብዙ "ሚሊዮኖችን" በአንድ ጊዜ አልፈጠረም። ሁለት ሰዎችን ብቻ (አንድ ወንድ እና አንድ ሴት) ለመዋለድ ከሚያስፈልጉ ስነ ጾታዊ ስርዓቶች ጋር ፈጠረ፡፡ ከዚያም በስልጣኑ ቃል "ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት" ሲል ባረካቸው። እንግዲህ መብዛት እና መባዛት፣ ማግባት እና መውለድም ለሰዎች (ለእግዚአብሔር ልጆች) የተሰጠ ምድራዊ በረከት ነው። እንጂ ለመላእክት አልተሰጠም።

ኦርጂናሌው የእብራይስጥ መጽሓፍ በዘፍ 6 ላይ "የእግዚአብሔር ልጆች" ብሎ ስለሚል፣ ዘግየት ብለው ይህን ቃል "መላእክት" በሚል የተኩ ትርጉሞች ሊያምታቱን አይገባም። በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈው ኦርጂናሌው ብቻ ነው።

መላእክት የእግዚአብሔር ልጆች ከቶ አልተባሉም። ሰዎች ግን የእግዚአብሔር ልጆች ከመባል አልፈው አማልክት ተብለዋል። ቅዱሳን መላእክት ከቶ አማልክት አልተባሉም።

መዝሙረ ዳዊት 82 የአሳፍ መዝሙር።
1 እግዚአብሔር በአማልክት (ገዢዎች፣ ፈራጆች፣ አለቆች) ማኅበር ቆመ፥ በአማልክትም (ገዢዎች፣ ፈራጆች፣ አለቆች) መካከል ይፈርዳል።
2 እስከ መቼ ሐሰትን ትፈርዳላችሁ? እስከ መቼ ለኃጢአተኞች ፊት ታደላላችሁ?
3 ለድሆች እና ለድሀ አደጎች ፍረዱ፤ ለችግረኛው እና ለምስኪኑ ጽድቅ አድርጉ።
4 ብቸኛውን እና ችግረኛውን አድኑ፤ ከኃጢአተኞችም እጅ አስጥሉአቸው።
5 (እነዚህ አማልክት ግን...) አያውቁም፥ አያስተውሉም፣ በጨለማ ውስጥ ይመላለሳሉ፤ የምድር መሠረቶች ሁሉ ተናወጡ።
6 እኔ (አሳፍ) ግን ፦ አማልክት ናችሁ፥ ሁላችሁም የልዑል ልጆች (የእግዚአብሔር ልጆች) ናችሁ፤
7 ነገር ግን እንደ ሰው ትሞታላችሁ ፥ ከአለቆችም እንደ አንዱ ትወድቃላችሁ አልሁ። (መላው ንባቡ ሟች ስለሆኑት ስለ ሰዎች ነው፤ እንጂ ስለ መላእክት አይደለም)
8 አቤቱ (እውነተኛው አምላክ /እግዚአብሔር/ ሆይ) ተነሥ፥ በምድር ላይ ፍረድ፥ አንተ አሕዛብን ሁሉ ትወርሳለህና።

እነዚህ አማልክት /gods/ የተባሉት ሰዎች የልዑል ልጆችም /children of the Most High/ ናቸው። እነርሱም ነገስታት፣ ነቢያት ...ወዘተ ሲሆኑ የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸው ሰዎች ናቸው። ለምሳሌ ነብዩ ሳሙኤል በመጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 28፡13 ላይ ለጠንቋይቱ "አማልክት" ተብሏል። እንዲሁም የሐዋርያት ሥራ 14፥11 ላይ በርናባስ እና ጳውሎስ ለአህዛባውያን፣ ኦሪት ዘጸአት 7፡1 ላይ ነብዩ ሙሴ ለፈርኦን "አማልክት" ተብለዋል። እነዚህ ሁሉ አማልክት ተባሉ እንጂ አማልክት አልሆኑም፣ አይደሉምም። አምላክ አንድ ብቻ ነው።

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 8
4 እንግዲህ ለጣዖት (ለአማልክት) የተሠዋውን ሥጋ ስለ መብላት፥ ጣዖት (አማልክት) ሁሉ በዓለም ከንቱ እንደ ሆነ ከአንዱም በቀር ማንም አምላክ እንደሌለ እናውቃለን።
5 መቼም ብዙ አማልክት እና ብዙ ጌቶች (የሚባሉ) አሉ፤ ነገር ግን በሰማይ ሆነ በምድርም ሆነ አማልክት የተባሉ ምንም ቢኖሩ፥
6 ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ፣ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ፣ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።
7 ነገር ግን ይህ እውቀት በሁሉ ዘንድ አይገኝም።

አያችሁ? ብሉይ ኪዳንን ያጻፈው ያው አንዱ መንፈስ (መንፈስ ቅዱስ) በወንድማችን በጳውሎስ በኩል ሲናገረን አማልክት የተባሉትን ሁሉ ሠርዞ (ደምስሶ)፣ አንድ አምላክ አንድ ጌታ ብቻ እንዳለ ይናገራል። ይሄውም አብን ወልድን እና ራሱን ተናጋሪውን (መንፈስ ቅዱስን) ብቻ ነው- አንድ እውነተኛ ጌታ ብሎ የሚነግረን።

ከዚህ ውጭ ያሉትን ሁሉ፣ አማልክት የተባሉትን ነገር ግን በባህርያቸው ሟች እና ወዳቂ የሆኑትን፣ ጠፊ እና አጥፊ የሆኑትን ሁሉ በኃያል ቃሉ ይደመስሳቸዋል። (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 8፡4) አዎን አሜን። ክብር፣ ምስጋና፣ ውዳሴ ለኤልሻዳዩ ለእውነተኛው አምላክ ለዘላለማዊ አባታችን (ኢሳ 9፡6) ለእርሱ ይሁንለት፤ አሜን።

ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር ሆኖ "ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ፣ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ፣ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን" ሲል እውነትን አስተማረን። እንጂ አንዳች አላጎደለም ወይም አላስቀረብንም። እኛም ከእርሱ የተማርነውን እውነት መልሰን እናስተጋባለን።

እንግዲህ ከላይ እንዳየነው "አማልክት" የተባሉት ሟች /ሞት የሚይዛቸው/ ሰዎች ናቸው። ብቻውን ያለው እውነተኛ አምላክ የሆነው ህያው እግዚአብሔር (ክርስቶስ) ግን ሞት ሊይዘው አልቻለም።

የዮሐንስ ወንጌል 10
24 አይሁድም እርሱን ከብበው "እስከ መቼ ድረስ በጥርጣሪ ታቆየናለህ? አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ ገልጠህ ንገረን" አሉት።
25 ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል፦ ነገርኋችሁ አታምኑምም፤ እኔ በአባቴ ስም የማደርገው ሥራ ይህ ስለ እኔ ይመሰክራል፤
26 እናንተ ግን እንደ ነገርኋችሁ ከበጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም።
27 በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ ይከተሉኝማል፤
28 እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም።
29 የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም።
30 እኔና አብ አንድ ነን።

31 አይሁድ ሊወግሩት ደግመው ድንጋይ አነሡ።
32 ኢየሱስ፦ ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ ስለ ማናቸው ሥራ ትወግሩኛላችሁ? ብሎ መለሰላቸው።
33 አይሁድም፦ ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ፣ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ፣ ብለው መለሱለት።

34 ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። "እኔ አማልክት ናችሁ አልሁ" ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን?
35 መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና፤ እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥
36 የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን ትሳደባለህ ትሉታላችሁን?
37 እኔ የአባቴን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ፤
38 ባደርገው ግን፥ እኔን ስንኳ ባታምኑ፣ አብ በእኔ እንደ ሆነ፣ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ።

ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻውን እውነተኛ አምላክ ነው።

ኦሪት ዘጸአት 15
11 አቤቱ፥ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው?

1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5
20 የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።
21 ልጆች ሆይ፥ ከጣዖታት (ከሃሰተኛ አማልክት) ራሳችሁን ጠብቁ።


እርሱን እንዳትክዱና እንዳትጠፉ ተጠንቀቁ።

የይሁዳ መልእክት 1
4 ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ፤ ንጉሣችንን እና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ።

ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ፣ በክብርና በገናናነት የሚኖር ልዑል አምላክ እስቲ ይታያችሁ። ክርስቶስ ማለት ያ ነው።

ወደ ሮሜ ሰዎች 9
5 ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ /God ነው፤ አሜን።

ወደ ተነሳንበት ነጥብ ስንመለስ በዘፍጥረት 6 ላይ የእግዚአብሔር ልጆች እንዳገቡና እንደወለዱ እናነባለን። ስለዚህ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች በርግጠኝነት ሰዎች ናቸው። እንጂ መላእክት አይደሉም።

ኦሪት ዘዳግም 14
1-2 እናንተ የአምላካችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ

መዝሙረ ዳዊት 82
6 ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ።

መዝሙረ ዳዊት
29፥1 የአምላክ ልጆች ሆይ፥ ለእግዚአብሔር አምጡ። ክብርንና ምስጋናን ለእግዚአብሔር አምጡ።

የሉቃስ ወንጌል
6፥35 ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ ምንም ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ፥ ዋጋችሁም ታላቅ ይሆናል፥ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፥ እርሱ ለማያመሰግኑ ለክፉዎችም ቸር ነውና።

መዝሙረ ዳዊት 89
17 የኃይላቸው ትምክሕት አንተ ነህና፥ በሞገስህም ቀንዳችን ከፍ ከፍ ይላልና።
18 ረድኤታችን ከእግዚአብሔር ከንጉሣችንም ከእስራኤል ቅዱስ ነውና።
19 በዚያ ጊዜ ለልጆችህ (ለእግዚአብሔር ልጆች) በራእይ ተናገርህ። እንዲህም አልህ "ረድኤቴን በኃይል ላይ አኖርሁ፤ ከሕዝቤ የተመረጠውን ከፍ ከፍ አደረግሁ..."

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ አባታችን ነው።

ትንቢተ ኢሳይያስ 9፡6 ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት (ዘላለማዊ አባት ETERNAL FATHER)፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።

እኛም ልጆቹ ነን።
ወደ ዕብራውያን 2፥
14-15 እንግዲህ ልጆቹ በሥጋ እና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ (ክርስቶስ) ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ።


የሐዋርያት ሥራ 17፡30 እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል።

G.G.A.A. 2ooo
Dec 24, 2012 ስም-አልባ የተመለሰ
Dec 25, 2012 ታርሟል
የማርቆስ ወንጌል 12 ፤29 እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው።
0 ድምጾች
አንድ ነገር ማስተዋል አለብን። መላእክት የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው ቢባል ኖሮ እኛ ሰዎች የእግዚአብሔር ልጆች ልንባል ከቶ አንችልም ነበር። ምክንያቱም ሁለታችንም (ማለት ሁለቱ የተለያዩ ወገኖች- ሰዎች እና መላእክት) የእግዚአብሔር ልጆች ልንባል አይቻልምና። ነገር ግን አዲስ ኪዳን በይፋ እንደሚያውጀው፣ በብሉይ ኪዳን የተጻፈውንም ምስጢር ገልጦ እንደሚያብራራው እኛ የእግዚአብሔር (የክርስቶስ) አማኞች የእግዚአብሔር ልጆች ተብለናል፤ እንባላለን፤ እንዲሁም ነን። እንደ ልጆችም እንድንሆን (እንድንኖር) ተመክረናል። (ማቴዎስ 5፡ 9። ማቴዎስ 5፡ 43-48። ገላትያ 4፡5።)

ታዲያ ልናስተውል የሚገባን ነገር፣ በወንጌል የተጠራነው የመላእክትን (የእነ ገብርኤልን) ክብር ለማግኘት አይደለም። የራሱን የእግዚአብሔር (ወልድን) ክብር ልንወርስ ተጠርተናል እንጂ። ስለዚህም የእግዚአብሔር ልጆች ተባልን፤ በቀኙም ተቀመጥን።

2ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 2፥14 ለዚህም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር ለማግኘት በወንጌላችን ጠራችሁ።

የዮሐንስ ወንጌል 17፥22-23 እኛም (አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ) አንድ እንደ ሆንን፣ አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ፣ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ፣ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል።

2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2፥10 (ጳውሎስ ሲናገር) ስለዚህ እነርሱ ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን መዳን ከዘላለም ክብር ጋር እንዲያገኙ ስለ ተመረጡት በነገር ሁሉ እጸናለሁ።

ወደ ዕብራውያን 2፥10 ብዙ ልጆችን (የእግዚአብሔር ልጆችን) ወደ ክብር ሲያመጣ የመዳናቸውን ራስ በመከራ ይፈጽም ዘንድ ከእርሱ የተነሣ ሁሉ፣ በእርሱም ሁሉ ለሆነ፥ ለእርሱ ተገብቶታልና።

እንግዲህ ምን ይሻላችኋል? በእምነት ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር ትቀበላላችሁ ወይስ ከሰው የሆነ ክብር ይሻላችኋል? በጥንቃቄ ምረጡ።

የዮሐንስ ወንጌል 5፥44 እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ፣ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ?

የዮሐንስ ወንጌል 12፥43 ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና።

ሲጀመር፣ ሰው የተፈጠረውም እኮ በአምላክ አምሳል እና መልክ፣ በአምላክ ክብር ነበር። መላእክት ግን እንዲህ አይደሉም። ዋው! ጌታ ምን ያህል ክብር ለልጆቹ እንደ ሰጠ ተመልከቱ። ለዚህም ነው እነ አዳም "የእግዚአብሔር ልጆች" ይባሉ የነበሩት። (ሉቃስ 3፡38። ኢዮብ 38፡7።) በኃጢአታችን ምክንያት የጎደለብንም ይሄው የእግዚአብሔር ክብር ነበር። በክርስቶስ ቤዛነት ይሄው ክብር ተመለሰልን። ክብር፣ ምስጋና፣ ውዳሴ ለአምላክ (ለክርስቶስ) ይሁንለት (ራእይ 1፡6)፤ አሜን።

ወደ ሮሜ ሰዎች 3፥23-24 ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ።

እንግዲህ በዚህ ምድር ስንኖር ይህን የጌታን ክብር ለሌሎች እያሳየን እንኖራለን።
2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 3፥18 እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን፣ መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን (የክርስቶስን) መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን።

ይሁን እንጂ በጌታ የተሰጠን ይህ ክብር በሙላት፣ በሙሉ ድምቀት የሚገለጠው ከጌታ ጋር በትንሳኤ ስንገናኝ ነው። ለእኛ በሙላት ይገለጥ ዘንድ ያለውን ያን ክብር ስናስብ በደስታ እንሞላለን።

ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3፥4 ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ።

ወደ ሮሜ ሰዎች 8፥18 ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ።

እንግዲህ እነርሱም እንደ እኛ የእግዚአብሔርን ክብር አግኝተዋልና በጌታ ወንድሞቻችን (ወይም እህቶቻችን) የሆኑትን በጥልቅ ልናከብራቸው እና ልናፈቅራቸው ይገባናል።
ወደ ሮሜ ሰዎች 15፥7 ስለዚህ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር እንደ ተቀበላችሁ እንዲሁ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ።

2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 8፥23 ስለ ወንድሞቻችን የሚጠይቅ ቢኖርም የአብያተ ክርስቲያናት መልእክተኞች እና የክርስቶስ ክብር ናቸው።

እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ በተደረገልን ቤዛነት ምን ያህል ታላቅ ክብር እንዳገኘን ተመልከቱ። ከዚህ የተነሳም ሁልጊዜ በዕድሜያችን ዘመን ሁሉ በምስጋና ልንፈነድቅ ይገባናል።

ከላይ ያየናቸው ጥቅሶች በሙሉ መላእክት ያላገኙትን አማኙ ያገኘውን የእግዚአብሔርን ክብር ያሳያሉ። መላእክትን በተመለከተ ግን፣ እነርሱ መዳንን የሚወርሱትን ሰዎች (የእግዚአብሔርን ልጆች) የሚያገለግሉ አገልጋይ መናፍስት ናቸው።
ወደ ዕብራውያን 1
13 ነገር ግን ከመላእክት፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ ከቶ ለማን ብሎአል?
14 ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ፣ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?


"አይደለም፤ እግዚአብሔር በቅድሚያ መላእክት የእግዚአብሔር ልጆች እንዲባሉ አስቦ ነበር፤ ነገር ግን መላእክቱ የሰውን ልጆች አግብተው ስለ በደሉት ልጅነትን ከእነርሱ ነጥቆ ለሰዎች ሰጠ" እንዳንል እግዚአብሔር አምላክ ሁሉን አስቀድሞ አዋቂ ነው እንጂ እንደ እኛ አእምሮውን make up አድርጎ አሳቡን እንደገና የሚቀይር ሰው አይደለም። እግዚአብሔር ስለ እኛ ያለው እቅዱም ከጥንት የነበረ "የዘላለም አሳቡ" ነበር። (ኤፌሶን 3፥11)

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 1
4 ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳን እና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን።
5 በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን።

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 1
11 እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ፣ እንደ እርሱ አሳብ አስቀድመን የተወሰንን በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን።

2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 1
9 ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፥ ይህም እንደ ራሱ አሳብ እና ጸጋ መጠን ነው እንጂ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም፤ ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፥
10-11 አሁን ግን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ታይቶአል። እርሱ ሞትን ሽሮአልና፤ እኔ ሰባኪ እና ሐዋርያ፣ አሕዛብንም አስተማሪ እንድሆን በተሾምሁበት በወንጌል ሕይወትን እና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን አውጥቶአል።

ወደ ሮሜ ሰዎች 8
28 እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን። (ለምን? ምክንያቱም...)
29 ልጁ (ክርስቶስ) በብዙ ወንድሞች (በእግዚአብሔር ልጆች) መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና
30 አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው
31 እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?
32 ለገዛ ልጁ ያልራራለት (ያልሳሳለት) ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም?
33 እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኰንንስ ማን ነው? (ነገር ግን በወንድሞች መካከል በኩር የሆነው እርሱ...)
34 የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2 ፡10 እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን።

እግዚአብሔር (ወልድ) ራሱ በስጋ ተገልጦ ሲመጣ (1ጢሞ 3፡16)፣ የመጣበት አላማ የእግዚአብሔርን ልጆች (ሰዎችን) ሊረዳቸው እና ሊቀድሳቸው (ሊያነጻቸው) ነበር። በዚህም ምክንያት ነው እግዚአብሔር (ወልድ) ራሱ "የእግዚአብሔር ልጅ" የተባለው። ስለዚህ እርሱ አንድ ጊዜ እንደ ወንድም "ወንድሞቼ"፣ አንድ ጊዜ እንደ አባት "ልጆቼ" ይለናል።

ምክንያቱም እርሱ ዘላለማዊ አምላክ እንደ መሆኑ ዘላለማዊ አባታችን ነውና "ልጆቼ" ይለናል። (ኢሳይያስ 9፤6። ዮሐንስ 21፡5)። ደግሞም በስጋ ተገልጦ ስለመጣ እኛን መስሎአልና፣ ራሱም "የእግዚአብሔር ልጅ" ተብሏልና በኩር ወንድማችን ሆኗል። ስለዚህ እርሱ ራሱ "ወንድሞቼ"፣ "ወዳጆቼ" ብሎ ሊጠራን አያፍርብንም። (ዮሓንስ 15፡12-15)። ክብር ለስሙ ይሁንለት፤ አሜን።

ወደ ዕብራውያን 2
10 ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ሲያመጣ የመዳናቸውን ራስ በመከራ ይፈጽም ዘንድ፥ ከእርሱ የተነሣ ሁሉ፣ በእርሱም ሁሉ ለሆነ፥ ለእርሱ ተገብቶታልና።
11-12 የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሁሉ ከአንድ ናቸውና፤
13 ስለዚህም ምክንያት፦ ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ፤ በማኅበርም መካከል በዜማ አመሰግንሃለሁ፤ ደግሞም፦ እኔ በእርሱ እታመናለሁ፤ ደግሞም፦ እነሆኝ እኔን እግዚአብሔር የሰጠኝንም ልጆች ሲል ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም።
14-15 እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ (ክርስቶስ) ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ።
16 የአብርሃምን (የሰዎችን) ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም
17 ስለዚህ የሕዝብን (የሰዎችን) ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምር እና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው።
18 እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን (ወንድሞቹን) ሊረዳቸው ይችላልና።

ታድያ ክቡር የሆነው እርሱ "ወንድሞቼ"፣ "ወዳጆቼ" ብሎ ሊጠራን ካላፈረብን፣ እኛም መልሰን ወንድማችን፣ ወዳጃችን ልንለው አንሣቀቅም፤ አናመነታም።

ክርስቶስ የእግዚአብሔር መሎኮታዊ ልጅ ሲሆን፣ እኛ የክርስቶስ አማኞች ደግሞ የእግዚአብሔር (የአብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ) ሰብአዊ ልጆች ነን። ስለ እኛ ሲናገር መጽሓፍ "እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሰማይን እና ምድርን ፈጠረ፤... ከምድር አፈር ሰውን አበጀ፤... አፈርም ስጋ ሆነ፤" ይላል። ስለ እርሱ ሲናገር ግን "በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ... ቃልም ራሱ እግዚአብሔር ነበረ፤ ... ሁሉ በእርሱ ተፈጠረ፤ ...ቃልም ስጋ ሆነ፤" ይላል። እንግዲህ ልዩነቱ ምን ያህል ሰፊ እንደ ሆነ ተመልከቱ።

ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር (አብ) መሎኮታዊ ልጅ ነው ስንል ምን ማለታችን ነው? ይህ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እግዚአብሔር ነው ማለት ነው። የአንበሳ ልጅ አንበሳ እንደሆነ፣ የሰው ልጅ ሰው እንደሆነ ሁሉ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስም እግዚአብሔር ነው። ይህም መጽሓፍ ቅዱስ የሚያረጋግጠው እውነት ነው። ለምሳሌ ያህል በሓሥ.20፡28፣ ኢሳ 40፡3 (ዮሓ 1፡23)፣ ኢሳ 8፡13 (1ጴጥ 3፡15)፣ ዮሓ 1፡1፣ 1ዮሓ 5፡20 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር /God/ ተብሎ ተገልጾአል። ይህ ነው የአብ መሎኮታዊ ልጅ ማለት። እኛ ሰዎች ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በማመናችን የእግዚአብሔር (ሰብአዊ) ልጆች ሆነናል (ገላ 3፡26)

ሆኖም እዳችንን ለመክፈል ሲል፣ አምላክ የሆነው እርሱ ወርዶ፣ የአምላክ ልጅ ተብሎ የአምላክ ልጆች እንድንባል አደረገን። እርሱ የሰው ልጅ ተብሎ ሰው አደረገን። ክብር ለዘላለም ለስሙ ይሁን፤ አሜን።
የዮሐንስ ወንጌል 1
12 ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤
13 እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።

የአምላክ ልጆች የሆንነው በእኛ ጽድቅ ሳይሆን ክርስቶስ በሰራልን የቤዛነት ሥራ ነው።
ወደ ኤፌሶን ሰዎች 1
4 ዓለም ሳይፈጠር (ገና እኛ ሳንኖር)፥ በፊቱ ቅዱሳን እና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን።
5 በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን።

ቅዱስ ቃሉ "ነው" ብሎ ያለውን "ነው" ከማለት ወደ ኋላ አንልም። "አይደለም" ብሎ ያለውንም "አይደለም" ከማለት ወደ ኋላ አንልም። ምክንያቱም የቃሉ አንባቢዎች ብቻ ሳንሆን የቃሉ አማኞች ነን። ካመንን ደግሞ ያመንነውን እንናገረዋለን። (2ቆሮንቶስ 4፡13)

በዚህም መሰረት ከዘፍጥረት- ሚልክያስ ድረስ "የአምላክ ልጆች" ብሎ የሚጠራው፦
የእግዚአብሔርን መንገድ (ዮሓንስ 14፡6) የተከተሉ፣
በዘፍጥረት 3፡15 የተነገረውን ተስፋ መሲሁን ያመኑ (ሓሥ 13፡32-33)
ከአቤል ጀምሮ በመሲሁ ሲያምኑ የኖሩ (ዕብ 11፡4)
ሲያምኑት እና ሲጠብቁት ኖረው የተስፋውን ዘር (ገላ 3፡16፣19) ሳያገኙ፣ (ማለት ክርስቶስን ሳያዩ) የሞቱ ሰዎችን (ዕብ 11፡ 13፣39)፣ /በብሉይ ኪዳን/

እንዲሁም የተስፋውን ቃል ያገኙ (ሉቃስ 2፡25-32። ሉቃስ 10፡23-24። ኢሳ 40፡5።) እንደ እኛ ያሉ ሰዎችን /በአዲስ ኪዳን/ ያመለክታል። እንጂ መላእክትን አያመለክትም።

እኛ አማኞች (የእግዚአብሔር ልጆች) ከመሎኮት ባህርይ ተካፋዮች ልንሆን ተጠርተናል። (2ጴጥ 1፡4) ከእግዚአብሔር መወለድ ማለት ባህርዩን መካፈል ማለት ነው። መላእክት ግን ይህ አልተሰጣቸውም። በርግጥም አምላክ መንፈሳችንን ወልዷልና ባህርዩን አካፍሎናል። (ዮሓ 3፡6። ዮሓ 1፡13።) ስለዚህ የአምላክ ልጆች ነን። (1ዮሓ 3፡1። 1ዮሓ 5፡1። 1ዮሓ 2፡29።)
የአምላክ ልጆች በመሆናችንም...

ይቀጥላል...

(W.G.E.D 2002)
Dec 31, 2012 ስም-አልባ የተመለሰ
Jan 2, 2013 ታርሟል
0 ድምጾች
...የቀጠለ

የአምላክ ልጆች በመሆናችንም ስልጣን ተሰጥቶናል። ለምሳሌ ያህል በወደቁት መላእክት ላይ ለመፍረድ ስልጣን ተሰጥቶናል።

ሉቃስ 10፡17-20። ሰብዓውም በደስታ ተመልሰው ኢየሱስን ፦ ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል አሉት። እንዲህም አላቸው፦ ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። እነሆ፥ እባቡን እና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም። ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፥ ስማችሁ ግን በሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።

ይህ ማለት ከሰይጣን ጋር ግብግብ እንድንፈጥር ጡንቻ ወይም ጉልበት ተሰጠን ማለት አይደለም። ነገር ግን የአምላክ ልጆች እንደ መሆናችን ሰይጣንን ለማዘዝ (ለማባረር፣ ለማሰር...) የምንችልበት ስልጣን AUTHORITY (ማቴ 8፡9) ተሰጠን ማለት ነው። ልብ ብለን ካየነውም፣ ይህ ስልጣን ሌላ ነገር ሳይሆን፣ ከስሞች ሁሉ በላይ የሆነው (ኤፌሶን 1፡21)፣ የሠራዊት አዛዥ የአባታችን የእግዚአብሔር ስም ነው። (ሉቃስ 10፡17 ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል )


በወደቁት መላእክት ላይ ብቻም አይደለም። ድንገት አጥፍተው ቢገኙ በቅዱሳን መላእክት ላይም ለመፍረድ የሚያስችል ስልጣን ተሰጥቶናል።


(1) ሮሜ 8፡ 35-39። ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።

(2) ገላትያ 1፡8-9። ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።

(3) 1ቆሮንቶስ 6፡2-3። ቅዱሳን /አማኞች/ በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? በዓለምስ ላይ ብትፈርዱ ከሁሉ ይልቅ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርዱ አትበቁምን? የትዳር ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኳ እንድንፈርድ አታውቁምን?


ያ ብቻም አይደለም። በመጨረሻው ቀን ከንጉሱ አባታችን ጀርባ፣ በዙፋኖች ተቀምጠን፣ ክርስቶስን ባላመኑ ሰዎች ላይም ለመፍረድ /ለመበየን/ ስልጣን ተሰጥቶናል። (ራእይ 2፡26-27። ራእይ 3፡21።)


(1) ሉቃስ 22፡29-30። (ኢየሱስ ሲናገር) አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ በመንግሥቴ ከማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፥ በአሥራ ሁለቱ በእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በዙፋኖች ትቀመጡ ዘንድ ለመንግሥት እሾማችኋለሁ

(2) ራእይ 4፡4። በዙፋኑ ዙሪያም ሀያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፥ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሀያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር።

(3) ማቴ 19፡28። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ (ኢየሱስ ክርስቶስ) በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ።

(4) ራእይ 20፡4። ዙፋኖችንም አየሁ፥ በእነርሱም ላይ ለተቀመጡት ዳኝነት ተሰጣቸው፤ ስለ ኢየሱስም ምስክር እና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቈረጡባቸውን ሰዎች ነፍሳት፥ ለአውሬው እና ለምስሉም ያልሰገዱትን፣ ምልክቱንም በግምባራቸው በእጆቻቸውም ላይ ያልተቀበሉትን አየሁ፤ ከክርስቶስም ጋር ሺህ ዓመት ኖሩና ነገሡ።


ይህ ሁሉ መሲሁን አምነን የአምላክ ልጆች በመሆናችን ብቻ፣ ከእርሱ ጋር እንድንነግስ የተሰጠን ክብር ነው።

() ራእይ 20፡6። በፊተኛው ትንሣኤ (በጻድቃን ትንሣኤ) ዕድል ያለው (በክርስቶስ ያመነ) ብፁዕ እና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፥ ዳሩ ግን የእግዚአብሔር እና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ

() ራእይ 22፡5። (በመንግስተ ሰማይ) ከእንግዲህም ወዲህ ሌሊት አይሆንም፥ ጌታ አምላክም በእነርሱ ላይ ያበራላቸዋልና የመብራት ብርሃን እና የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣሉ።

ማንም ሌላ "አምላክ" ወይም የትኛውም ሌላ ሓይማኖት እንዲህ አይነት ክብር አይሰጣችሁም። እንኳን ለእናንተ ሊሰጥ፣ ለራሱም የለውም።

ቤተ ጣዖታትም ሆነ የሓይማኖት ድርጅቶች የራሳቸውን ካህናት መሾም ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን ኢየሱስ የሰጠንን እንዲህ አይነቱን አምላካዊ ስልጣን ሊሰጡ ከቶ አይችሉም። እንዲህ አይነቱን ስልጣን የሚሰጣቸውን ቢያገኙ፣ እነርሱ ራሳቸውም ይፈልጉት ነበር። ታዲያ ምን አለ? ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ (እና ብቻ) ቢያምኑ?

ጳውሎስ ለእንዲህ አይነት ሰዎች መፍትሄውን ይጠቁማል።

(1) ሮሜ 10፡ 2-4። (ሃይማኖተኞች) በእውቀት አይቅኑ እንጂ ለእግዚአብሔር እንዲቀኑ እመሰክርላቸዋለሁና። የእግዚአብሔርን ጽድቅ (ክርስቶስን) ሳያውቁ የራሳቸውንም ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ፥ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም። የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና።

(2) ሮሜ 3፡ 21-26። አሁን ግን በሕግ እና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል። እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነበኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው። ልዩነት የለምና፤ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል። በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ። እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው። ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው። ራሱም ጻድቅ እንደሆነ (ያህል) በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው።

እንግዲህ እነርሱ ያልሰጡን ስልጣን ስለሆነ፣ እነርሱ ሊከለክሉን አይችሉም። ጌታ ፈቅዶ የሰጠንን ይህን ስልጣን ማንም ሊነጥቀን፣ ሊነፍገን፣ ወይም ሊገፍፈን መብት የለውም። ስለዚህ አብዝተን በናዝሬቱ ኢየሱስ እንመካለን። በእርሱ በማመናችን ብቻ ይህን ሁሉ ክብር አግኝተናልና። (ዕብራውያን 10፡ 14። ዮሓንስ 1፡12። ሮሜ 3፡22።)

2ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 2፡14 ለዚህም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር ለማግኘት በወንጌላችን ጠራችሁ።

በመጨረሻም የአምላክ ልጆች መሆናችንን አውቀን በጽድቅ፣ በስልጣን እና በድል ህይወት እንድንኖር፣ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት እና በእምነት እንድንመላለስ እጋብዛለሁ። እጅግ ትሁት የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ልጆች መሆናችንን አውቀን በትህትና እንመላለስ። የአባት ጸጋ እና ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን።

W.G.E.D 2002
Jan 2, 2013 ስም-አልባ የተመለሰ
Jan 2, 2013 ታርሟል
0 ድምጾች
መላእክት ትዕዛዙን የሚፈጽሙ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ናቸው እንጂ ልጆች አይደሉም። (መዝሙር 103፡20።)

መላእክት የእግዚአብሔር ልጆች ያልሆኑበት ምክንያት፡

(1) ባህርዩን መካፈል ስላልተሰጣቸው ነው።

ሰዎች ግን... 2ጴጥሮስ 1፡4፦ ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብር እና በጎነት፣ የተከበረ እና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን።

(2) (ሞት እና) ትንሳኤ ስለሌለባቸው ነው። በኩር ልጁን መምሰል አይችሉም።

ሰዎች ግን... ሉቃስ 20፡36-38፦ የትንሣኤም ልጆች ስለ ሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። ሙታን እንዲነሡ ግን ሙሴ ደግሞ በቍጥቋጦው ዘንድ ጌታን "የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅም አምላክ፣ የያዕቆብም አምላክ" በማለቱ አስታወቀ። ሁሉ ለእርሱ ሕያዋን ስለ ሆኑ፥ የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም።

(3) የቅጣቱ ተካፋዮች ስላልሆኑ ነው። መላእክት መናፍስት ስለሆኑ አንድ ጊዜ ቢሳሳቱ ለዘላለም ይቀጣሉ እንጂ እንደ ሰው የንስሃ ዕድል አልተሰጣቸውም። ወይም የቅጣት ተካፋዮች አይደሉም።

ሰዎች ግን... ዕብራውያን 12፡5-12፦ እንደ ልጆችም ከእናንተ ጋር፦ ልጄ ሆይ፥ የጌታን ቅጣት አታቅልል፥ በሚገሥጽህም ጊዜ አትድከም፤ ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋልና፥ የሚቀበለውንም ልጅ ሁሉ ይገርፈዋል ብሎ የሚነጋገረውን ምክር ረስታችኋል። ለመቀጣት ታገሡ፤ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? ነገር ግን ሁሉ የቅጣት ተካፋይ ሆኖአልና ያለ ቅጣት ብትኖሩ ዲቃላዎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም። ከዚህም በላይ የቀጡን የሥጋችን አባቶች ነበሩን። እናፍራቸውም ነበር። እንዴትስ ይልቅ ለመናፍስት አባት (መንፈሳችንን ለወለደው) አብልጠን ልንገዛና በሕይወት ልንኖር በተገባን? እነርሱ መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበርና፥ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል። ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፥ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል። ስለዚህ የላሉትን እጆች የሰለሉትንም ጉልበቶች አቅኑ።

በሰማይ ያሉ መላእክት የእግዚአብሔር ልጆች ቢሆኑ ኖሮ፣ ስለ ክርስቶስ "አንድያ ልጅ" ብሎ መናገሩ ባላስፈለገም ነበር።
ዮሓንስ 3፡16። በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።

በአጠቃላይ፣ መጽሓፍ ቅዱስ የሚያስተምረን፡
እግዚአብሔር በሰማይ ብዙ ልጆች እንዳልነበሩት፣
አንድያ/ብቸኛ/አንድ ብቻ/ ልጅ እንደነበረው (ምሣሌ 30፡4። ዮሓንስ 3፡16፣ 17፣ 36። ዮሓንስ 6፡40)
ይህም ልጅ "በኩር ልጅ" ሆኖ ወደ ምድር እንደ መጣ (ዕብራውያን 1፡6። ሮሜ 8፡29)
በምድርም ሌሎችን ብዙ የእግዚአብሔር ልጆችን እንዳፈራ (ዮሓንስ 1፡12። ገላትያ 3፡26)
ገና የሚመጣውን መሲህ ያመኑት ሰዎች (በብሉይ ኪዳን) እና የመጣውን መሲህ ያመኑት (ሉቃስ 2፡36-38) ሰዎች (በአዲስ ኪዳን) የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን፣ እና
የልጅነት ክብራቸውም በሙላት የሚገለጠው በትንሳኤ መሆኑን (ቆላስይስ 3፡4። ሮሜ 1፡4። ሮሜ 8፡23-25። ፊልጵስዩስ 3፡20-21። ) ያስተምረናል።

ቆላስይስ 3፡4፦ ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ

ሮሜ 1፡4 ... እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ሮሜ 8፡23-25፦ ... ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን።
24 በተስፋ ድነናልና፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል?
25 የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቃለን።

ፊልጵስዩስ 3፡20-21፦ እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።


ለምሳሌ በብሉይ ኪዳን "ልጅነት" ለእስራኤላውያን ነበር።
ሮሜ 9፡4። እነርሱ እስራኤላውያን ናቸውና፥ ልጅነት እና ክብር፣ ኪዳንም፣ የሕግም መሰጠት፣ የመቅደስም ሥርዓት፣ የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና።
ዘጸአት 4፡22። (እግዚአብሔር ለፈርዖን ሲናገር) እስራኤል የበኵር ልጄ ነው፤ ይገዛልኝ ዘንድ ልጄን ልቀቅ አልሁህ። አንተም ትለቅቀው ዘንድ እንቢ አልህ፤ እነሆ እኔ የበኵር ልጅህን እገድላለሁ።

በአዲስ ኪዳንም የአብርሃም የእምነት ልጆች የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው።
ወደ ሮሜ 9፡
6 ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል የተሻረ አይደለም። እነዚህ ከእስራኤል የሚወለዱ ሁሉ እስራኤል አይደሉምና፤ የአብርሃምም ዘር ስለሆኑ ሁላቸው ልጆች አይደሉም፥
7 ነገር ግን፦ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል ተባለ።
8 ይህም፥ የተስፋ ቃል ልጆች ዘር ሆነው ይቆጠራሉ እንጂ እነዚህ (የአብርሃም) የሥጋ ልጆች የሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች አይደሉም ማለት ነው።
9 ይህ፦ በዚህ ጊዜ እመጣለሁ፤ ለሳራም ልጅ ይሆንላታል፤ የሚል የተስፋ ቃል ነውና።
26 እናንተ ሕዝቤ አይደላችሁም በተባለላቸውም ስፍራ በዚያ የሕያው እግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉ ይላል።

ዕብራውያን 1፡4-14።
4 (ክርስቶስ) ከመላእክት ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ስምን በወረሰ መጠን እንዲሁ ከእነርሱ አብዝቶ ይበልጣል።
5 ከመላእክትስ፦ አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፥ ደግሞም፦ እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል ያለው ከቶ ለማን ነው? (ለማንም አላለም።)
6 ደግሞም በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ፦ የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ ይላል።
7 ስለ መላእክትም፦ መላእክቱን መናፍስት አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ ይላል።

8 ስለ ልጁ ግን፦ አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው።
9 ጽድቅን ወደድህ፤ ዓመፅንም ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከጓደኞችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ ይላል።
10 ደግሞ (ልጁን)፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤
11 እነርሱም ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥
12 እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ፤ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም ይላል።

13 ነገር ግን ከመላእክት፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ ከቶ ለማን ብሎአል? (ለማንም አላለም።)
14 ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው (ስለ አማኞች) ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?


ስለዚህ በዘፍጥረት 6፡2፣ 4፤ በኢዮብ 1፡6፤ 2፡1፤ 38፡7፤ በመዝሙር 29፡1፤ በጥንታዊው የዕብራይስጥ ብሉይ ኪዳን ላይ እንደተጻፈው "የአምላክ /የእግዚአብሔር/ ልጆች" ተብሎ መነበብ አለበት። ይህም "እግዚአብሔርን የተከተሉ ሰዎችን" የሚያመለክት መሆኑን ልንረዳ ይገባል።
ሰላም!

G.G.A.A
Jan 2, 2013 ስም-አልባ የተመለሰ
Jan 2, 2013 ታርሟል
0 ድምጾች
ለዚህ ጥያቄ የተሰጡት መልሶች አጥጋቢ አይደሉም።

እስቲ በዚህ መልክ እንየው።

"የእግዚአብሔር ልጅ" የሚለው አገላለጽ በዋናነት የሚያመለክተው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። ሌሎቹ "የእግዚአብሔር ልጆች" የሚሉት አገላለጾች ግን በእግዚአብሔር የተፈጠሩትን የማሰብ ችሎታ ያላቸውን መንፈሳዊ አካላት፣ አዳም ሃጢአት ከመስራቱ በፊት፣ እግዚአብሔር ከነርሱ ጋር ልዩ ቃልኪዳን የገባላቸውን ሰዎችም ሊያመለክት ይችላል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ "የእግዚአብሔር ልጆች" የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በዘፍጥረት 6፡2-4 ላይ እናገኛለን። እነዚህም የእግዚአብሔር ልጆች፣ ከጥፋት ውሃው በፊት 'የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደ ሆኑ አዩ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ' በማለት ይነግረናል።

ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች እነዚህ 'የእግዚአብሔር ልጆች' ራሳቸው ሰዎች ናቸው፣ እነዚህም ከሴት የትውልድ መስመር የነበሩ ዝርያዎች ናቸው የሚል እምነት አላቸው። እንደ ምክንያት የሚያነሱት ደግሞ የአምላክ ወዳጅ የሆነው ኖህ ከሴት ትውልድ የመጣ መሆኑና የተቀረው በሙሉ ከአዳም የመጡ የቃየን ልጆች እና የእነርሱ የልጅ ልጆች (ዘፍጥረት 5፡3፣4) በኖህ የጥፋት ውሃ የጠፉት ናቸው። በመሆኑም "የሰውን ሴቶች ልጆች" "የእግዚአብሔር ልጆች" አገቡ የሚለው አገላለጽ ሴታውያን ከክፉው ቃየን የተወለዱትን ማግባት ጀመሩ ማለት እንደሆነ ይናገራሉ።

ይሁንና በዚህን ወቅት እግዚአብሔር በቤተሰብ መስመሮች መካከል ልዩነት እንዳደረገ የሚገልጽ ምንም ማስረጃ የለም። የሴት ዘሮችና የቃይን ዘሮች የሚያደርጉት ጋብቻ፣ በቁጥር 4 ላይ እንደምናገኘው "ሃያላን" የሚወለዱበት ነው የሚለው ሃሳብ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ይጎድለዋል። እርግጥ ነው "የሰዎች ልጆች" የሚለው አገላለጽ "የእግዚአብሔር ልጆች" ከሚለው አገላለጽ ጋር በተቃራኒው የተጠቀሰ ቢሆንም ይህ ግን በቋሚነት የተያዘ ሃሳብ አይደለም። - መዝሙር 4፡2፤ 57፡4፤ ምሳሌ 8፡22፣ 30፣ 31፤ ኤርምያስ 32፡18፣ 19፤ ዳነል 10፡16ን ማወዳደር እንችላለን።

መላእክት እንደ እግዚአብሔር ልጆች
በቅዱሳን ጽሑፎች ለዚህ አጥጋቢ ምክንያት እናገኛለን። "የእግዚአብሔር ልጆች" የሚለው አገላለጽ ቀጥሎ የምናገኘው በኢዮብ 1፡6 ላይ ነው። በእግዚአብሔር ፊት መቅረባቸውና ሰይጣንም በመካከላቸው እንደነበረ መጠቀሱ በእርግጠኛነት የሚያወራው ስለ መንፈሳዊ የእግዚአብሔር ልጆች ነው። (ኢዮብ 1፡7፤ ምዕራፍ 2 ቁጥር 1 እና 2ንም ይመልከቱ) እንደገናም በኢዮብ 38፡4-7 ላይ "የእግዚአብሔር ልጆች" እግዚአብሔር የምድርን የመሰረት ማዕዘን ድንጋይ ሲያቆም እልል እንዳሉ የሚገልጸው ዘገባ የተጠቀሱት የእግዚአብሔር ልጆች ሰማያዊ (መላእክት) እንጂ ምድራዊ እንዳልነበሩ ግልጽ ነው።

በዘፍጥረት 6፡2-4 ላይ የተጠቀሱትን "የእግዚአብሔር ልጆች" መላእክት ናቸው የሚለውን የሚቃወሙ ሰዎች በዙሪያው ያለው ሃሳብ ከሰው ልጆች አጠቃላይ ክፋት ጋር አያይዞ ይገልጸዋል ይላሉ። ይሁንና የክፋት መንፈሳዊ አካላት ተጽዕኖ ያን ያህል ክፋት እንዲስፋፋ ምክንያት ሊሆን ስለሚችል ይህ ተቃውሞ ትክክል አይደለም። በአካል ባይገለጡም ኢየሱስ በምድር ሳለ እንዳደረጉት አጋንንት ይህን ያህል በሰው ላይ የክፋትን ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ።

ይህንን ሐሳብ በመደገፍ ሐዋርያው ጴጥሮስ "በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት (መናፍስት) ... የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም" በማለት ሁኔታውን ይገልጻል (1 ጴጥሮስ 3፡19-20) እንዲሁም "እግዚአብሔር ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት" በማለት "በቀደመውም ዓለም" በኖህ ዘመን የነበረውን ያወሳል። (2 ጴጥሮስ 2፡4-5) ይሁዳም በተመሳሳይ "መኖሪያቸውንም የተዉትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት" በማለት ጠቅሷል። (ይሁዳ 6) በዘፍጥረት 6፡2-4 ላይ የተጠቀሱት "የእግዚአብሔር ልጆች" መንፈሳዊ ፍጡራን ካልሆኑ፤ እነዚህ ክርስቲያን ጸሐፊዎች ከኖህ ዘመን ጋር አያይዘው የመላእክትን አለመታዘዝ ያብራሩት ነገር ለመግለጽ የሚከብድ ሌላ ምስጢር ይሆን ነበር።

መላእክት በአንዳንድ አጋጣሚዎች የሰው አካል ለብሰዋል፣ በልተዋል፣ ጠጥተዋል። (ዘፍጥ 18፡1-22፣ 19፡1-3) ኢየሱስ ሰለትንሳኤ ሲያብራራ እንዳለው "መላእክት አያገቡም፣ አይጋቡም" (ማቴዎስ 22፡30) ይህ ማለት ግን እነዚህ መንፈሳዊ ፍጡራን ሰብዓዊ አካል ለብሰው ከሰዎች ሴቶች ልጆች ጋር አይጋቡም ማለት አይደለም። ይሁዳ መኖሪያቸውን ወይም ቦታቸውን ያልጠበቁ ብሎ ስለመላእክቱ ከጠቀሰ በኋላ በሰዶምና ገሞራ ጊዜ የተከሰተውን "እንደዚሁም" ማለቱ ከተፈጥሯቸው ውጪ የሄዱ መሆናቸውን ያጎላል። (ይሁዳ 6፣ 7) በመሆኑም በቅዱሳን ጽሑፎች የቀረበው ማስረጃ ድምር ውጤት እንደሚያሳየው ከመንፈሳዊ ተፈጥሯቸው በተቃራኒ የመላእክት ክህደት በኖህ ዘመን እንደተካሄደ ነው።

አዳም የእግዚአብሔር የፍጥረት ስራ በመሆኑ በእግዚአብሔር ላይ ከማመጹ በፊት "የእግዚአብሔር ልጅ" መባሉን እናስተውላለን። (ሉቃስ 3፡38) ይህንንም መብት እሱም ሆነ ልጆቹ በሃጢአት ምክንያት እንዳላገኙት ከዮሐንስ 1፡12-13 እንረዳለን። ዮሐንስ እንደተናገረው ኢየሱስን የተቀበሉት "የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣን" ተሰጥቷቸዋል። ከዚህ እንደምንረዳው በውልደት ሳይሆን በስጦታ የሆነ የእግዚአብሔር ልጅነት በእስራኤልም ላይ እንመለከታለን። (ዘጸዓት 4፡22፣ 23) መላው የእስራኤል ህዝብ ለእግዚአብሔር የተለየ ወገን የተደረገ በመሆኑ "ልጅ" በመባል ተጠርቷል። (ዘዳግም 14፡1፣ 2) የህይወታቸው ምንጭ እርሱ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ለአብርሃም ቃል በተገባው መሰረት እግዚአብሔር "ፈጣሪያቸው"፣ "ሰሪያቸው" እንደሆነ ከመጠቀስም አልፎ "አባታቸው" ተብሏል። - መዝሙር 95፡6፣7፣ 100፡3፤ ኢሳይያስ 43፡1-7፣ 15፣ 45፡11፣ 12፣ 18፣ 19፤ 63፡16


ሰላም
Aug 13, 2013 ኦፍቲ (1,250 ነጥቦች) የተመለሰ
“እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ።“
(መዝሙረ ዳዊት 33:12)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us
...