ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » ጥያቄ መጠያየቂያ
Email this page to a friend   Sunday, 29 November 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ፥ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።“
(መዝሙረ ዳዊት 27:14)

rss

Today's verse

በራእይ መጽሃፍ ተጽፎአል - 24ቱ ሽማግለዎች እነማን ናቸው?

24ቱ ስማግለዎች አከሊላችውን አስክምተው ክዱስ ክዱስ እያሉ ይስግዱ ነበር. እነሱ እነማን ናቸው? የበጉ ህዋርያትስ?
Feb 2, 2013 መንፈሳዊ ስም-አልባ የተጠየቀ
Feb 8, 2013 ተመልካች ታርሟል

4 መልሶች

–2 ድምጾች
የጋራ መጠርያቸው ሱራፊል ይባላል.የሰማይም ካህናት ናቸው.እሺ!
Feb 4, 2013 ስም-አልባ የተመለሰ
መልሱ በትክስ ቢደገፍ መልካም ነበር:-) እንዲት መልዓክት ስማግሊዎች ሊሆኑ ቻሉ?ሊያብራሩ ክቻሉ መልካም ነው:-)
0 ድምጾች
ክፍል አንድ

ሰላም

ከጠየቅኻቸው ሁለት ጥያቄዎች በቅድሚያ ቀላሉንና ሁለተኛውን ልመልስ። ይኸውም የበጉ ሃዋርያትን በተመለከት የጠየቅኸውን ማለት ነው።
Quote:
የዮሐንስ ራእይ
21፥14 ለከተማይቱም ቅጥር አሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩአት፥ በእነርሱም ውስጥ የአሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር።

በራእይ መጽሃፍ የበጉ ሃዋርያት ተብሎ የተጠቀሰው ቃል የሚገኘው አንድ ቦታ ሲሆን ይህም በራእይ 21፡14 ላይ ነው። ጥቅሱም "የበጉ ሃዋርያት" ብቻ ሳይሆን የሚናገረው ስለ "አስራ ሁለቱ የበጉ ሃዋርያት ነው"። ስለዚህ ኢየሱስ ራሱ በምድር በተመላለሰ ጊዜ የሾማቸውን አስራ ሁለቱን ሃዋርያት የሚያመለክት ነው። ከአስራ ሁለቱ ሌላ በአዲስ ኪዳን ሌሎችም እንደ ጳውሎስ ያሉና ኢየሱስ ከሞተና ከተነሳ በኋላ ሃዋርያት የተበሉ ሰዎች አሉ። ሆኖም ለሎቹ ሃዋርያት የበጉ ሃዋርያት ወይም አስራ ሁለቱ ሃዋርያት ተብለው አይጠሩም። የበጉ ሃዋርያት ኢየሱስ በምድር ላይ ለሰራው ስራ፣ ለሞቱና ለትንሳኤው የአይን እማኞችና ምስክሮ ስለሆኑ ከሃዋርያነት አገልግሎት በተጨማሪ የተለየ ስፍራና ሾመት አላቸው። ይህ ብቻ አይደለም በአንድ ሺህው የክርስቶስ መንግስት በአስራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ የሚገዙ ሰዎች ናቸው።
Quote:
የሉቃስ ወንጌል 6
13 በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ጠራ፥ ከእነርሱም አሥራ ሁለት መረጠ ደግሞም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤

የማቴዎስ ወንጌል 19
27 በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፦ እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን? አለው።
28 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ

ቁጥራቸውም ይግድ ከአስራ ሁለት መብለጥ ወይም ማነስ ስለሌለበት ነው፤ ከአስራ ሁለቱ ሃዋርያት አንዱ የነበረው የአስቆሮጡ ይሁዳ ከሞተ በኋላ ሃዋርያት እጣ አውጥተው ማትያስን የመረጡት (የሐዋ 1፡15-26)

እንግዲህ አስራ ሁለቱ የበጉ ሃዋርያት የሚለው ኢየሱስ ራሱ በምድር ሲመላለስ የሰየማቸውን አስራ ሁለቱን ሃዋርያት መሆኑ ግልጽ ከሆነልን አሁን ደግሞ ሃያ አራቱን ሽማግሌዎች ማን ናቸው ወደሚለው ወደ መጀመሪያው ጥያቄህ እንመለስ።

ይህንን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ስለ ዮሃንስ ራእይ መጽሃፍ አንዳንድ ነገሮች ግልጽ ሊሆኑልን ይገባል። አንደኛ የዮሃንስ ራእይ መጽሃፍ የምሳሌና የምልክት መጽሃፍ ነው። ማለትም በአብዛኛው ነገሮችን የሚገልጽበት ቋንቋ ስእላዊ ነው። አውሬ ሲል ወይም ዘንዶ ሲል ወይም ፈረስ ሲል ወዘተ የእውነት አውሬዎችን ወይም እንስሶችን ማለቱ ሳይሆን እነዚህ እንስሶች ምልክቶች ብቻ ናቸው እናም የሚያመለክቱት እውነተኛው ነገር አለ ማለት ነው።

ሌላ ምሳሌ ለመጨመር፤ ምእራፍ 5ትን ብንመለከት ስለ ታረደ በግ ይናገራል፤ ያም በግ ማህተሙን ሊፈተ የሚችልና በብዙ መላእክት የሚመለክ በግ ነው። ይህ ማለት በሰማይ እንደዚያ ያለ የሆነ አንድ በግ አለ ማለት አይደለም ነገር ግን የታረደውን ኢየሱስን የሚያመለክት ነው። በጉ ስእላዊ ምልክት ብቻ ነው። ምልክት እንደመሆኑ ወደ እውነተኛው ነገር የሚያሳይ ወይም የሚያመለክት ስእል ብቻ ነው። እውነተኛውና በበግ የተመሰለው ኢየሱስ ራሱ ነው።

ልክ እንደዚሁም ሃያ አራቱ ሽማግሌዎችም በሰማይ የተቀመጡ በቁጥርም ልክ ሃያ አራት ብቻ የሆኑ ሽማግሌዎች አሉ ብለን ማሰብ የለብንም። እነዚህ ሽማግሌዎች ምልክቶች ናቸው፤ የሚያመለክቱት እውነተኛ ነገር አለ። ምን እንደሚያመለክቱ ለመረዳት ግን፤ ሽማግሌዎቹ የተገለጹበትን ስእላዊ መግለጫ ቋንቋ አንድ በአንድ መመልከትና መጽሃፍ ቅዱስ ራሱ ስለ እነዚህ ስእላዊ መገለጫዎች የሚሰጠውን ማብራሪይ መፈለግ ይገባናል። እኛ በራሳችን እንደፈለግነው መገርጎም አንችልም። ሽማግሌዎቹ የተገለጹበትን ቋንቋ ከመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ መፈለግ ነው ያለብን።

ሌላው የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ የትንቢት መጽሐፍ መሆኑን መዘንጋት የለብንም።
Quote:
የዮሐንስ ራእይ 1
1 ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፥
2 እርሱም ለእግዚአብሔር ቃልና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ላየውም ሁሉ መሰከረ።
3 ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው።

ይህም ማለት እንደ ብሉይ ኪዳን የትንቢት መጽሐፍት ሁሉ ይህም የዮሐንስ ራእይ አሁን ስላለው ነገር ብቻ ሳይሆን በአብዛኛው ወደፊት ሊመጣ ስላለውም ነገር የሚተነብይ መጽሐፍ ነው።
Quote:
የዮሐንስ ራእይ 1
19 እንግዲህ ያየኸውን አሁንም ያለውን ከዚህም በኋላ ይሆን ዘንድ ያለውን ጻፍ።

የዮሐንስ ራእይ እንግዲህ አሁን ስላለው ወይም ዮሐንስ በጻፈበት ጊዜ ስለነበረው ብቻ ሳይሆን ወደፊት ስለሚሆነውም የሚተነብይ መጽሐፍ ነው። እንዲያውም ከምዕራፍ 4 ጀምሮ ያለው ክፍል ወደፊት ሰለሚሆነው የሚተነብይ ስለወደፊት የሚናገር ትንቢት እንደሆነ በግልጽ ተጠቅሶአል።
Quote:
የዮሐንስ ራእይ 4
1 ከዚያ በኋላም አየሁ፥ እነሆም በሰማይ የተከፈተ ደጅ፥ እንደ መለከትም ሆኖ ሲናገረኝ የሰማሁት ፊተኛው ድምፅ፦ ወደዚህ ውጣና ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚያስፈልገውን ነገር አሳይሃለሁ አለ።

ስለዚህ ከምእራፍ አራት ጀመሮ በዮሃንስ ራእይ የተጻፉት ነገሮች አሁን እየተከሰቱ ያሉ ነገሮች ሳይሆኑ፤ ወደፊት የሚሆኑ ትንቢቶች ናቸው። የሃያ አራቱ ሽማግሌዎችም የተጠቀሰው በምእራፍ አራት ስለሆነ፤ ወደፈት ሊሆን ስላለው ነገር እንደሆነ መርሳት የለብንም።
Feb 13, 2013 ስም-አልባ የተመለሰ
0 ድምጾች
ክፍል ሁለት

ይህንን ያህል ስለ ዮሃንስ ራእይ መጽሃፍ ካልን እስቲ ሽማግሌዎች የተጠቀሱበትን ስእላዊ መገለጫ ቋንቋ አንድ በአንድ እንመልከት።
Quote:
የዮሐንስ ራእይ 4
4 በዙፋኑ ዙሪያም ሀያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፥ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሀያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር።

በቅድሚያ እነዚህ ሽማግሌዎች፤ "ሽማግሌዎች" elders ተብለው ነው የተጠሩት። ሽማግሌ ደግሞ በመጽሃፍ ቅዱስ በብሉይም ይሁን በአዲስ ኪዳን የሰማይን ፍጥረታት ማለትም መላእክትን፣ ሱራፌልና ኪሩቤልን ወዘተ አንድም ቦታ አያመለክትም። የትኛዎቹም የሰማይ ፍጥረታት "ሽማግሌዎች" ተብለው በመጽሃፍ ቅዱስ ተጠርተው አያውቁም። ሽማግሌዎች ተብለው በመጽሃፍ ቅዱስ የተጠቀሱት በብሉይም ይሁን በአዲስ ኪዳን ሰዎች ናቸው። በብሉይ ኪዳን የእስራኤል ሽማግሌዎች በመባል የሚታወቁና በአዲስ ኪዳን ደግሞ የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች ተብለው የሚታወቁ የእግዚአብሔር ህዝብ መሪዎች ናቸው። ሽማግሌ የሚለው ቃል እንግዲህ በመጽሃፍ ቅዱስ ሁልጊዜም ማለት ይቻላል ለሰዎች የተሰጠ መጠሪያ እንጂ የመላእክት መጠሪያ አይደለም። በእርግጥ ትንቢተ ዳንኤል ምእራፍ 7 ላይ እግዚአብሔር "በዘመናት የሸመገለው" ተብሎ ተጠርቷል፤ ይህ ማለት ግን ሽማግሌ ነው ወይም elder ነው የሚል ትርጉም ግን የለውም። ይህ ክፍል ያሚለው ለዘላለም የኖረው ወይም ዘላለማዊው ማለት ነው። እንግዲህ ሽማግሌ የሚለው ቃል በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ሁልጊዜም ሰዎችን ብቻ የሚያመለክት ነው።

ሌላው እነዚህ ሽማግሌዎች ነጭ ልብስ እንደለበሱ ነው የተጻፈው። በራእይ መጽሃፍ ነጭ ልብስ 7 ጊዜ ያህል ተጽፎአል (3:4 3:5 3:18 4:4 6:11 7:9 19:14)፤ በሁሉም ቦታ ነጭ ልብስ የሚያሳየው በበጉ ደም ልብሳቸውን ስላነጹ ወይም በክርስቶስ ስለዳኑ ሰዎች ብቻ ነው። አንድም ቦታ በዮሃንስ ራእይ ነጭ ልብስ ስለ መላእክት ወይም ስለ ብሉይ ቅዱሳን ወይም ስለ ሌላ ሰዎች ሲጠቀስ አናይም።

በሶስተኛ ደረጃ እነዚህ ሽማግሌዎች በራሳቸው ላይ የወርቅ አክሊል እንደደፉ ተጽፎአል። የዮሃንስ ራእይ አንዳንዴ ስለ አክሊል (በግሪኩ stephanos) አንዳንዴ ደግሞ ስለ ዘውድ (በግሪኩ diadema) ይናገራል። እነዚህ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ዘውድ የንጉሳዊ ቤተሰብነው ከመሆን በውርስ ወይም በሹመት የሚሰጥ ነገር ሲሆን አክሊል ግን የራእይ መጽሃፍ በተጻፈበት በግሪክ ባህል እንደ ዛሬው ዘመን ሜዳሊያ ማለት ነው። ማለትም የሆነ ውድድርን ወይም ፈተናን ላሸነፉ አሸናፊዎች የሚሰጥ ነገር ነው። ለምሳሌ የመጀመሪያዎቹ የኦሎምፒክ ስፖርት ውድድሮች ከዛሬ 2500 ዓመታት በፊት በግሪክ ሲደረጉ አሸናፊዎች እንደ ሜዳሊያ የሚሰጣቸው ከቅጠል የተሰሩ አክሊሎች ነበሩ። ስለዚህ አክሊል በአዲስ ኪዳን የሚያመለክተው በሆነ ውድድር ወይም ፈታኝ ነገር ውስጥ አልፈው ድል የነሱ ሰዎች የሚያገኙትን ሜዳሊያ ነው።

ስለዚህ እነዚህ ሽማግሌዎች የሰማይ መላእክት ሳይሆኑ በሆነ ውድድር ወይም ፈተና አልፈው ድል የነሱና ለዚህም ይገባችኋል ተብለው የአክሊክ ሜዳሊያ የተቀበሉ ሰዎች ናቸው። በራእይ መጽሃፍም ይሁን በአዲስ ኪዳን የክርስቶስ አማኞች የተለያዩ አይነት አክሊሎች እንደሚያገኙ ተስፋ ተሰጥቶአቸዋል። የድል አክሊል፣ የህይወት አክሊል፣ የማይጠፋ አክሊል፣ የክብር አክሊል ወዘተ

እስከ አሁን ስለ ሽማግሌዎቹ ያየናቸው በተለይ ነጭ ልብስና አክሊል እንግዲህ፤ በንጉሳዊ ቤተሰብነውና በውርስ የተገኘ ዘውድ ሳይሆን በውድድርና በፈተና ታልፎ ድል ለነሱ የሚሰጥ አክሊል ማድረጋቸው መላእክት ወይም የሰማይ ፍጥረታት ሳይሆኑ ሰዎች እንደሆኑ ሲያመለክት፤ ነጭ ልብስ መልበሳቸው ደግሞ በክርስቶስ የተዋጁ አማኞች መሆናቸውን የሚያሳይ ነው።

ሽማግሌዎቹ የተገለጹበት ሌላ መገለጫ በዙፋን ላይ መቀመጣቸው ነው። ይህ በጣም የሚገርም ነገር ነው። ምክንያቱም በምእራፍ 4፡2-3 እና 4፡8-11 ላይ በሰማይ አንድ ዙፋን እንዳለና በዙፋኑም የተቀመጠው እግዚአብሔር እንደሆነ ተገልጿል። በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሔር ዙፋን ባለበት ሌላ ፍጥረት ዙፋን ላይ ወይም በእግዚአብሔር ጎን ስለተቀመጠ ፍጥረት ከኢየሱስ በስተቀር አናነብብም። ኢየሱስ ብቻ ነው በእግዚአብሔር ቀኝ እንደተቀመጠ መጽሃፍ ቅዱስ የሚነግረን (ማር 16፥19)። ሌሎቹ ፍጥረታት ሁሉ የእግዚአብሔር ዙፋን ባለበት በዙፋን ላይ ሲቀመጡ አናነብብም። እነዚህ ነጭ ልብስ የለበሱና በራሳቸው የወርቅ አክሊል የደፉ ሽማግሌዎች ግን የእግዚአብሔር ዙፋን ባለበት በዙፋን ላይ ተቀምጠው ነበር። እንዲህ አይነት በሰማይ በዙፋን ላይ መቀመጥ ቃል የተገባላት በመጽሃፍ ቅዱስ ቤተክርስቲያን ወይም የክርስቶስ አማኞች ብቻ ናቸው። በዚያው በራእይ መጽሃፍ ይህንን ለክርስቶስ አማኞች የተገባውን ቃል እናገኛለን።
Quote:
የዮሐንስ ራእይ 3
21 እኔ ደግሞ ድል እንደ ነሣሁ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፥ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ

ይህ ቃል የተገባላት ቤተክርስቲያን የሎዶቅያ ቤተክርስቲያን ናት። ከቃሉ እንደምናየው፤ ኢየሱስ የራሱን ልምምድ እንደ ምሳሌ አድርጎ ነው የሚናገረው። "እኔ ደግሞ ድል እንደ ነሣሁ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ" ነው የሚለው፤ ማለትም ኢየሱስ ድል ነስቶ በሰማይ በአባቱ ዙፋን በእግዚአብሔር ቀኝ እንደተቀመጠ እንዲሁ "በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ" ነው የሚለው። ስለዚህ ይህ በዙፋን ላይ የመቀመጥ ተስፋ ልክ ኢየሱስ እንዳደረገው በሰማይ ስለሚደረግ መቀመጥ እንጂ ወደፊት ኢየሱስ በምድር ሲገዛ እንደ አስራ ሁለቱ ሃዋርያት በነገዶች ላይ ለመግዛት በምድር የሚደረግ መቀመጥ አይደለም።

ልክ እንደ ኢየሱስ በሰማይ ላይ በዙፋን መቀመጥ ከክርስቶስ አማኞች ውጪ ለሰማይ ፍጥረት ቢሆን ወይም ለሌሎች ሰዎች የተሰጠ የተስፋ ቃል በመጽሃፍ ቅዱስ አናገኝም።

እነዚህ ሽማግሌዎች ድል ነስታችኋል ተብለው አክሊል መቀበላቸው ሳያንስ በዙፋን ደግሞ ተቀመጠዋል፤ ይህ ሁሉም ክብር ከጠበቁት በላይና እነርሱ ካደረገት በላይ እንደሆነና እንደማይገባቸውም ለማሳየት ይመስላል በቁጥር 10 እና 11 ላይ ከተቀመጡበት ዙፋን ወርደው እየገዱና አክሊላቸውን እያወለቁ እግዚአብሔርን የሚያመልኩት። ይሄ ሁሉ ለእኛ አይገባም፤ የሆነልን ከአንተ የተነሳ ነው የሚሉ ይመስላሉ።
Quote:
የዮሐንስ ራእይ 4
10-11 ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በዙፋን ላይ በተቀመጠው ፊት ወድቀው፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው እየሰገዱ፦ ጌታችንና አምላካችን ሆይ፥ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል እያሉ በዙፋኑ ፊት አክሊላቸውን ያኖራሉ

ይህ ብቻ አይደለም ዙፋን ከዚህም በተጨማሪ ስልጣንን ወይም መንገስን ወይም መንግስትን መቀበልንም የሚያመለክት ነው፤ ይህንን የሚቀጥለውን ካየን በኋላ እንመለሰብተላልን።
Feb 13, 2013 ስም-አልባ የተመለሰ
እግዚአብሄር ይባርካችሁ
0 ድምጾች
ክፍል ሶስት

በመጨረሻም ሽማግሌዎቹ ሃያ አራት እንደሆኑ ተጽፎአል። ይህም በመጽሃፍ ቅዱስ የታወቀ ቁጥር ነው። ልክ አስራ ሁለት ቁጥር በአዲስም ይሁን በብሉይ ኪዳን አስራ ሁለቱን የእስራኤል ነገዶች ወይም እስራኤልን እንደሚያመለክት ሁሉ፤ ሃያ አራትም በመጽሃፍ ቅዱስ ካህናትን የሚያመለክት ቁጥር ነው። ይህንን ለመረዳት በብሉይ ኪዳን የካህናትን ቤቶች ወይም ክፍሎች መረዳት ያስፈልጋል። ልክ እስራኤል በአስራ ሁለት ነገድ እንደሚከፈሉ፤ ካህናትም በብሉይ ኪዳን በሃያ አራት ቤቶች ወይም የቤተሰቦቻቸው ነገዶች ይከፈሉ ነበር። ካህናት ብዙ ስለነበሩ ሁሉም በቤተመቀደስ በአንዴ አያገለግሉም ነበር፤ ነገር ግን በሃያ አራቱ የቤተሰቦቻቸው ክፍሎች ተመድበው በተራ ነበር በመቅደስ የሚያገለግሉት። ይህንን የካህናት ክፍል የመደባቸው ደግሞ ዳዊት ነበር፤ የታሪኩ አመጣጥና እንዴት ካህናት ለሃያ አራት እንደተመደቡ 1ዜና 24፡1-19 ተመልከት።

ይህ የካህናት በካህናት ቤተሰቦች መመደብ እስከ አዲስ ኪዳን ዘመንም የቀጠለ ነበር። በሉቃስ ወንጌል ምእራፍ አንድ ላይ ስናነብብ፤ የመጥምቁ ዮሃንስ አባት ዘካርያስ ካህን እንደነበረና "በክፍሉ ተራ" ተመድቦ ማለትም ከሃያ አራቱ የካህናት ክፍሎች በአንዱ ተመድቦ ሲያገለግል እንደነበር እናገኛለን።
Quote:
የሉቃስ ወንጌል 1
5 በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ልጆች ነበረች፥ ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ።
6 ሁለቱም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ።
7 ኤልሳቤጥም መካን ነበረችና ልጅ አልነበራቸውም፤ ሁለቱም በዕድሜያቸው አርጅተው ነበር።
8 እርሱም በክፍሉ ተራ በእግዚአብሔር ፊት ሲያገለግል፥
9 እንደ ካህናት ሥርዓት ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን ዕጣ ደረሰበት

በመጽሃፍ ቅዱስ እንግዲህ ሃያ አራት ቁጥር ካህናትና የሚያሳይ ነው፤ በራእይ መጽሃፍ የምናገኛቸው እነዚህ ሽማግሌዎች እንግዲህ በዙፋን የተቀመጡና መንግስትን የተቀበሉ ብቻ ሳይሆን፤ የክህነት አገልግሎትም የተሰጣቸው ካህናት ናቸው ማለት ነው።

ይህ መንግስትንና የክህነንት አገልግሎት መቀበል በራእይ መጽሃፍ ለክርስቶስ አማኞች የተሰጠ እንደሆነ እዛው በራሱ በራእይ መጽሃፍ ላይ እናገኛለን። በራእይ ምእራፍ አንድ ላይ፤ ዮሃንስ ራሱ ስለ ራሱና ስለ ክርስቶስ አማኞች ሲናገር ኢየሱስ ከሃጢአታችን እንዳጠበን፤ እንዲሁም መንግስትን እንደሰጠንና ካህናትም እንዳደረገን ይናገራል።
Quote:
የዮሐንስ ራእይ 1
4-5 ዮሐንስ በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት፤ ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም፥ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት፥ ከታመነውም ምስክር ከሙታንም በኵር የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን
6 መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን።

በዛው በራእይ መጽሃፍ ምእራፍ 5 ላይም እንደዚሁ፤ ስለ ኢየሱስ ሲናገር፤ ኢየሱስ በደሙ ሰዎችን እንደዋጀና የእግዚአብሔር "መንግስትና ካህናት" እንዲሆኑ እንዳደረገ ይናገራል።
Quote:
የዮሐንስ ራእይ
5፥9-10 መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፥ ታርደሃልና፥ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፥ በምድርም ላይ ይነግሣሉ እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ።

እንግዲህ የሽማግሌዎቹ ማንነት የተገለጸበትን መገለጫ ቃላት አንድ በአንድ ስንመለከትና ትርጉሙኑም መጽሃፍ ቅዱስን ብቻ ተጠቅመን ስንመለከት፤ የምናገኘው ሽማግሌዎቹ ቤተክርስቲያንን እንደሚያመለክቱ ነው።

አንደኛ ሽማግሌዎች እንደሆኑ መጠቀሱ ሰውን እንጂ መላእክትን ወይም የሰማይ ፍጥረታትን አያሳይም። ሁለተኛ ነጭ ልብስ መልበሳቸው በራእይ መጽሃፍ ሁሉ እንደተገለጸው በክርስቶስ ደም መዋጀታቸውን ወይም መዳናቸውን የሚያሳይ ነው። ሶስተኛ በቤተሰብ የሚወረስ ዘውድ ሳይሆን አክሊል ወይም በአሁኑ ዘመን መረዳት "ሜዳልያ" ማግኘታቸው ድል የነሱት ነገር በህይወታቸው እንደ ነበርና የተፈተኑ ወይም በህይወት ውጣ ውረድ ያለፉ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ከላይ እንዳየነው ደግሞ ቤተክርስቲያን ብዙ አይነት አክሊሎች ነው ቃል የተገባላት። የህይወት አክሊል፣ የክብር አክሊል፣ የማይጠፋ አክሊል ወዘተ። በአራተኛ ደረጃ እነዚህ ሽማግሌዎች ከሌሎች ፍጥረታት በተለየና ባልታየ ሁኔታ የእግዚአብሔር ዙፋን ባለበት በሰማይ በዙፋን ላይ ተቀምጠዋል። ይህም ከላይ እንዳየነው ልክ ኢየሱስ ድል ነስቶ በአባቱ ዙፋን በሰማይ እንደተቀመጠ እንዲሁ በክርስቶስ ዙፋን እንደሚቀመጡ ተስፋ የተሰጣቸው በመጽሃፍ ቅዱስ የክርስቶስ አማኞች ብቻ ናቸው። ከዚህም በላይ ዙፋኑና ቁጥራቸው ሃያ አራት መሆናቸው መንግስትንና የክህነትን አገልግሎት የተቀበሉ እንድሆኑ፤ ይህም ደግሞ ለቤተክርስቲያን ማለትም ለክርስቶስ አማኞች የተሰጠ እንደሆነ በዚያው በራእይ መጽሃፍ አይተናል።

ስለዚህ እነዚህ ሽማግሌዎች ድል የነሳች ቤተክርስቲያንን ወይም የክርስቶስ አማኞችን የሚያመለክቱ ናቸው።
Feb 13, 2013 ስም-አልባ የተመለሰ
ያልገባህ ነገር ቢኖር ሱራፊል የሰማይ ካህናት እንጂ መላእክት አይደሉም.
“እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ።“
(መዝሙረ ዳዊት 33:12)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us
...