ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » ጥያቄ መጠያየቂያ
Email this page to a friend   Tuesday, 24 November 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ፥ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።“
(መዝሙረ ዳዊት 27:14)

rss

Today's verse

የኢት. ኦርቶዶክስ ቤ/ክ በ1984 ባሳተመችው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቅሶች የተቀየሩት ለምንድነው?

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በ1984 ባሳተመችው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንድ ጥቅሶች በ1954 ከታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉት ጋር አንድ አይደሉም፣ ወይም ተቀይረዋል። ለዚህም አንዳንድ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ።

በመጽሐፉ መግቢያ ላይ "ከቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ውጪ የሆኑ ባዕዳን ቃላት" ከመጽሐፍ ቅዱሱ እንደተወገዱና የተዘለሉ ካሉም በአንባብያን ጥቆማ ዳግም 'እንደሚስተካከሉ' ይገልጻል። ይህም የግለሰቦች ሳይሆን የሲኖዶሱ እጅ እንዳለበት ጭምር ስለሚናገር በቀላል የሚታይ ጉዳይ አይደለም።

በመጽሐፉ የውስጥ ገጾች ውስጥ እነዚህ ባእዳን ተብለው ከተቀየሩት አብዛኞቹ ከሌላኛው ጽሁፍ ደመቅ ብለው ይታያሉ። ይህም የቅርጸ-ቁምፊ (ፎንት) ልዩነት ያመጣው ውጤት እንደሆነ መጠርጠር ይቻላል።

ከተለወጡት ጥቅሶች አብዛኞቹ ከሥላሴ እምነት ጋር የማይጣጣሙ በመሆናቸው እንደሆነ በቀላሉ መገንዘን ይቻላል። (2 ቆሮንቶስ 1፡3፣ ኤፌሶን 1፡3፤ 1ጴጥሮስ 1፡3፤ ራዕይ 3፡14፤ ራዕይ 14፡1፤ ፊልጵስዩስ 2፡5፣6፤ ወዘተ) አንዳንዶቹም ከማርያም ጋር የተያያዙ ናቸው።

የዚህ ለውጥ መሰረት ምን ነበር? የ1954ቱ አማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ እትም ከስህተት የጸዳ ነው የሚል አመለካከት የለኝም። የተርጓሚዎቹ እምነት ተጽዕኖ አሻሚ በሆኑ ቦታዎች ላይ በመጠኑም ቢሆን እንዳለበት የሚካድ አይደለም። የዚህኛው ግን አይን ያፈጠጠ ክህደት እንደሆነ መገንዘብ ቀላል ነው።

የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የተጻፈበት ቋንቋ ግሪክኛ ነው። ምናልባት አንዳንዶች በግሪኩ የተጻፈውን ቃል በትክክል ለማሰቀመጥ ነው ይሉ ይሆናል። ነገሩ ግን እንዲያ አይደለም። ከላይ በጠቀስኳቸው ጥቅሶች ላይ የተሰራውን ለውጥ በሚመለከት የግርጌ ማስታወሻዎች ገብተዋል። እነዚህ የግርጌ ማስታወሻዎች "በግሪኩ እንዲህ ይላል" በማለት አሁን በመጽሐፍ ቅዱሳችን (1954ቱን ማለቴ ነው) ላይ ያለው ትክክል እንደነበር ይገልጻሉ! "በግሪኩ" የሚለውን አገላለጽ የማይረዱ ብዙዎች ስለ እውነታው ምን እንደሚያስቡ ገምቱ።

እናንተስ ምን ትላላችሁ?


ሰላም
Aug 1, 2013 መንፈሳዊ ኦፍቲ (1,250 ነጥቦች) የተጠየቀ 1 ሪፖርት

2 መልሶች

0 ድምጾች
ውድ "ኦፍቲ" ጥያቄ እየጠየቁ ነው ወይስ እራሶ ጠይቀው እዚው እርሶ እየመለሱ?

መደምደሚያዎት ደግሞ የራሶን አስተሳስብ ብቻ እንዲነዳው ፈቅደዋል፡ ለምሳሌም "(1954ቱን ማለቴ ነው) ላይ ያለው ትክክል እንደነበር ይገልጻሉ!.."

የግርጌ ማስታወሻዎች የገቡት አንባቢው ከቀድሞ የእህትመት ጋር ያለውን ልዩንት ሳይሸፋፈን እንዲረዳው ነው እንጂ። እንደርሶ አመልካከት ያውም " ምን እንደሚያስቡ ገምቱ።" መማለት ነገሮችን ለመሸፋፈን አይደለም።

በነገራችን ላይ እርስዎ በኦርቶዶክስ ቤ/ክ ለምን አንዳነጣጠሩ ባይታወቅም የፕሮቴስታንት አማኞች ህብረት መጽሃፍ ቅዱስ በቀላል ቋንቋ በሚል በብዙ የአገራችን ቋንቋ ጥቅሶችን በመቀየር እንዳስተመ ግልጽ እንዲዎንሊዎ ይገባል። የጌታስ ቃል የሚለው አጥርተህ እንድታይ መበጀመርያ በአይንህ ያለውን ምሶስ አውጣ አይደልምን?

"የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የተጻፈበት ቋንቋ ግሪክኛ ነው።" የሚለው እንዳለ ለመቀበል በጣም ነው የሚያዳግተው፤ በተለይም አራቱ ወንጌላት ለምሳሌም ረቡኒ፤ ላምሰብቅታኒ... ሁሉም የአዲስ ኪዳን መጻህፍት በግሪክኛ ለመጻፉ ምንም ኦርጅናል ማስራጃ የለም። ያሉት ቅ. መጻህፍት ሁሉ ኮፒ ናቸውና።

ስለወነም በመጀመርያ ቅ. መጻፍቱ ሲጻፉ እንደጸሃፊው የቋንቋ ችሎታና አላማ ተደርጎ አንደተጻፈለት ማህበርሰብ የተጻፈበት ቋንቋ ግሪክኛ፤ እብራይስጥኛ ወይም አረማይክ ሊሆን ይችላል።

ኢየሱስ ክርስቶስ የጌቶች ጌታ፤ የአማልክት አምላክ፤ የነገስታት ንጉስ ነው!
Aug 1, 2013 ስም-አልባ የተመለሰ
አመሰግናለሁ ስም-አልባ

እንደኔ አመለካከት የዚህ መድረክ ዓላማ፣ ጥያቄ መጠየቅ - መልስ መስጠት አይመስለኝም። ከዚህ ይልቅ ሰዎችን የሚያወያይ፣ እውቀት የሚሰጥ፣ ግንዛቤን የሚያሰፋ መድረክ ማድረግ ይመስለኛል።

ለጠየቁኝ ግን መልሴን ከታች ማግኘት ይቻላል።

ሰላም
+1 ድምጽ
በዚህ ጉዳይ ሐሳቤን በደንብ ግልጽ ማድረግ ይኖርብኛል።

1) ይህ ማለት ሁሉም ንጹህ ሆነው የ1986ቱ ተበላሸ እያልኩኝ አይደለም።
በአማርኛ የተዘጋጁ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አሉ። ከነዚህም መካከል።

- የ1879ኙ እትም፦ በኪንግ ጄምስ ቨርዥን የእንግሊዝኛ ትርጉም ላይ መሰረት ያደረገ ስራ ነው። አንዳንድ እንደ 1 ዮሐንስ 5፡7 የመሳሰሉ የኪንግ ጄምስ ቨርዥን ችግሮችን እንዳለ የያዘና ለዘመናችን አማርኛ ተናጋሪ የማይገቡ ቃላትን የሚጠቀም የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ከዚህም ባሻገር ይዘቱ በብዛት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ጋር እንዲስማሙ ተደርጎ ብዙ ጥቅሶች እንደተጻፉ መመልከት ይቻላል።

- በ1954 የታተመው (አሁን በአብዛኛው የምንጠቀምበት) የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በኢትዮጵያ መጽሀፍ ቅዱስ ማህበር የታተመ ሲሆን ከዕብራይስጥና ግሪክኛ በኩረ-ጽሁፎች በቀጥታ እንደተተረጎመ ይነገርለታል። ተርጓሚዎቹ በነፍስ ጽንሰ ሐሳብ፣ በሥላሴ፣ በገሃነምና ሲኦል፣ እና በሌሎች አንዳንድ ነገሮች ላይ የነበራቸው እምነት በትርጉሙ ላይ የተወሰነ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ባይካድም ለኢትዮጵያውያን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ግንዛቤ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በትርጉም ሥራ ቀጥተኛ (normal) የሚባለው ዓይነት ትርጉም ነው።

- በ1980 የታተመውና በቀላል አማርኛ የቀረበው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ለሌሎቹ ዘመናዊ ትርጉሞች ፈር ቀዳጅ ቢሆንም ለማብራራት ሲባል በየጥቅሱ ላይ የተጨመሩት ብዙ ቃላት ጠንካራ ምርምር ለማድረግ የማይመችና የአንድ ጎንን እምነት የሚያንጸባርቅ አድርጎታል። በዚህም ምክንያት ከፕሮቴስታንቱ ዓለም ባለፈ ጥቅም ላይ ሳይውል ቀርቷል። በትርጉም ሥራ ጥራዝ ነጠቅ (paraphrased) የሚባለው ዓይነት ትርጉም ነው።

- በ1992(?) አካባቢ የታተመው አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አ.መ.ት) በእንግሊዝኛው ኒው ኢንተርናሽናል ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመስርቶ የተሰራ ነው። በእንግሊዝኛ የተዘጋጀው ኒው ኢንተርናሽናል ቨርዥን በመጽሐፍ ቅዱሱ በኩረ ቃላት ውስጥ ብዙ ባዕዳን ቃላትን የጨመረ ሲሆን፣ የአማርኛውም የዚያኑ አካሄድ ተከትሏል። ይሁን እንጂ ከ1954ቱ ይበልጥ የበኩረ ጽሑፉን ቃላት ሳይቀይር እንደያዘ መገንዘብ ይቻላል። በመሆኑም ለምርምር የሚበቃ የትርጉም ሥራ ሆኗል። በትርጉም ሥራ ተለዋዋጭ (dynamic) የሚባለው ዓይነት ትርጉም ነው።

- የ1984ቱ እትም ግን ራሱን የቻለ የትርጉም ሥራ አይደለም። መሰረት ያደረገው የ1954ቱን እትም ሲሆን የተደረጉት ለውጦች አሻሚ በመሆናቸው ወይም በ1954ቱ ውስጥ በስህተት በመቀመጣቸው አይደለም። ከዚያ ይልቅ በመግቢያው ላይ እንደተገለጸውና የተለወጡትን ጥቅሶች በማየት በግልጽ መገንዘብ እንደሚቻለው ጉዳዩ ከቤተ-ክርስቲያኒቱ እምነቶች ጋር ለማስማማት ሲባል ነው። ለውጦቹ በአብዛኛው በሥላሴ እና በማርያም እምነቶች ላይ ያተኮሩ በመሆናቸው ትኩረት ይስባሉ። እንደኔ እንደኔ ግን የ1897ኙን ትርጉም በዘመናዊ አማርኛ ለመድገም ይመስላል።


2) ለግንዛቤ ያህል አንድ ጥቅስ እናንሳና እነዚህ ትርጉሞች እንዴት እንዳስቀመጡት እንመልከት።

- ለምሳሌ ያህል አንድን ጥቅስ (በ1984ቱ ከተቀየሩት ውስጥ) እናንሳና ከበኩረ-ጽሑፉ ጋር በማወዳደር የትኛው / የትኞቹ መስመር እንደሳተ/እንደሳቱ እንመልከት።
2 ቆሮንቶስ 1፡3
Quote:
በግሪክኛ፡ "Εὐλογητὸς ὁ θεὸς καὶ πατὴρ τοῦ κυρίου ἡμῶν Ἰησοῦ Χριστοῦ ὁ πατὴρ τῶν οἰκτιρμῶν καὶ θεὸς πάσης παρακλήσεως"

ቀጥተኛ (ቃል-በቃል) ትርጉም፡ "ይባረክ ያ አምላክ እና አባት የ ጌታ የኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ያ አባት የ ርህራሄ እና አምላክ የሁሉ መጽናናት"

1879፡
Quote:
"እግዚአብሔር ይመስገን የጌታችን የየሱስ ክርስቶስ አባት የምህረት አባት የመጽናናትም አምላክ።"

1954፡
Quote:
"የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።"

1980፡
Quote:
"የምህረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ ለሁነውና እንዲሁም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ለሆነው አምላክ ምስጋና ይሁን" - የግርጌ ማስታወሻ "አዲስ ኪዳን በተጻፈበት በግሪክኛው ቋንቋ 'የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይመስገን' ይላል" ይላል።

አ.መ.ት፡
Quote:
"የርኅራኄ አባት፣ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።"

1984፡
Quote:
"የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ይባረክ።" - የግርጌ ማስታወሻ "በግሪኩ 'የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት' ይላል" ይላል።

ግሪክኛውን በትክክል ያስቀመጠው የቱ ነው? በግልጽ ማየት እንደሚቻለው 1954ቱ እና አ.መ.ት በትክክል አስቀምጠውታል። የ1879ኙ፣ የ1980ው እና 1984ቱ ግን በግሪኩ ውስጥ የተጠቀሱ ሁለት አምላክ የሚሉ ቃላት ቢኖሩም አንዱን አጥፍተዋል፤ በዚህም ለቃሉ ታማኝ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
(ተመሳሳይ የሆኑትን ጥቅሶች ኤፌሶን 1፡3፣ 1 ጴጥሮስ 1፡3 ተመልከቱ)

ሌላም ጥቅስ እናክል
ራዕይ 14፡1 ላይ "የበጉ ሥምና የአባቱ ሥም" የሚለውን ሁሉም የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ግሪክኛው በሚያስቀምጠው መልክ ሲያስቀምጡ
የ1984ቱ ግን "የመንፈስ ቅዱስም ሥም" የሚል ሃረግ ጨምሯል። የ1879ኙ ደግሞ በተቃራኒው "የበጉ ሥምና" የሚለውን ሃረግ አውጥቶ ጥሏል።


ኤፌሶን 1፡3፣ 17 ላይ "የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ..." የሚሉ ቃላትን ግሪክኛው ቢጠቀምም
የ1879ኙ "አምላክ" የሚለውን "አባት" በሚል ያለምንም ማብራሪያ አልፎታል።
የ1980ው "አምላክ" የሚለውን "አባት" በሚል ተክቶ በግርጌ ማስታወሻው "አምላክ" መባል እንዳለበት ጠቅሶ አልፏል።
የ1984ቱ ግን የ1954ቱን ምንም ሳይቀይር አልፎታል።


የእኔ ነጥብ አሁን ግልጽ የሆነ ይመስለኛል። የ1984ቱን የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን እትም ነጥሎ የተሳሳተ ነው ወደሚል መደምደሚያ ለመሄድ ሳይሆን በጉዳዩ ላይ የውይይት ሃሳብ ለመጫር፣ እንዲሁም የአንባብያንን የአመለካከት አድማስ ለማስፋት ነው።

እንደኔ እንደኔ ግን የ1954ቱ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የበኩረ ጽሑፉን (የግሪክኛውን) ቃላት በትክክል በማስተላለፍ ረገድ ሚዛን ይደፋል። ከስህተት የጸዳ ነው እያልኩ አይደለም፤ ይሁንና ከሌሎቹ ሁሉ የተሻለ ደረጃ ላይ ነው ማለት ይሻላል። ከ1954ቱ ቀጥሎ የሚቀመጠው አ.መ.ት ነው። ይህም ብዙ ጥቅሶችን በማወዳደርና የበኩረ ጽሑፉን (የግሪክኛውን) ይዘት በማስተያየት ሊገኝ የሚችል ውጤት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈ ከ100 ብዙም በማይበልጡ ዓመታት ውስጥ የነበሩ የእምነት ሰዎች ስለ አዲስ ኪዳን መጽሐፍት ብዙ ያሉት ነገር ትኩረት የሚስብ ነው። በሙሉ ስምምነት ለማለት ይቻላል፣ ማቴዎስ በ41 ዓ.ም ወንጌሉን በዕብራይስጥ ቋንቋ ለአይሁዳውያን የጻፈ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ወደ ግሪክኛ እራሱ የተረጎመ ሲሆን የተቀሩት 26 መጽሐፍት ግን ከጅምራቸው በተራው ሰው ግሪክኛ (ኮይነ ግሪክኛ) እንደተጻፉ ሙሉ እምነት ነበራቸው።

ታሪክ የሚነግረን ይህንን ነው። ኢየሱስ አንዳንድ ቃላትን በዕብራይስጥ ሌሎቹንም በአረማይክ ቋንቋ እንደተናገረ ወንጌሎች ይመሰክራሉ። ይህ መሆኑ ወንጌሎቹ የተጻፉት በአረማይክ ወይም በዕብራይስጥ እንደተጻፉ ያረጋግጣል? እንዲያ ከሆነ እነዚያን የኢየሱስ ቃላት እንደ ባዕድ ቋንቋ መተርጎም ለምን አስፈለገ?
Quote:
የማርቆስ ወንጌል 5፥41 "የብላቴናይቱንም እጅ ይዞ። ጣሊታ ቁሚ አላት፤ ፍችውም አንቺ ብላቴና ተነሽ እልሻለሁ ነው።"
"ጣሊታ ቁሚ" (Talitha cumi) የዕብራይስጥ ሀረግ ሲሆን ማርቆስ "ፍቺውም" በማለት ፍቺ መስጠት ያስፈለገው ወንጌሉን የጻፈው በዕብራይስጥ ስላልሆነ እንደሆነ ይጠቁማል።
Quote:
የማርቆስ ወንጌል 15፥34 "በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ፦ ኤሎሄ፥ ኤሎሄ፥ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? ማለት ነው።"
ይህ ሀረግ አረማይክ ሲሆን ማርቆስ መተርጎም አስፈልጎታል። ይህም ማርቆስ ወንጌሉን የጻፈው በአረማይክ እንዳልሆነ ይጠቁማል። ማቴዎስም በተመሳሳይ ማድረጉ ወንጌሉን በአረማይክ እንዳልጻፈው ብቻ ሳይሆን ኢየሱስም ሙሉ በሙሉ በአረማይክ ወይም በዕብራይስጥ ይናገር እንዳልነበር ከዚያ ይልቅ ግን በአንዳንድ አጋጣሚዎች በነዚህ ቋንቋዎች ይጠቀም ነበር ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው።
Quote:
የዮሐንስ ወንጌል 1፥39 "እርሱም፦ ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ ትርጓሜው መምህር ሆይ ማለት ነው።"
"ረቢ" የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን ዮሐንስ ትርጓሜ መስጠቱ ወንጌሉን የጻፈው በዕብራይስጥ እንዳልሆነ ይጠቁማል።

እኛም በተመሳሳይ በቋንቋችን ውስጥ የሌላን ቋንቋ አባባል እንጠቀማለን። ለምሳሌ "ጉራቻ" የኦሮምኛ ቃል ሲሆን የአማርኛን ያህል እንጠቀምበታለን። ሌሎች ምሳሌዎችን ማንሳት ይቻላል።


ጥቂት የአረማይክና ዕብራይስጥ ቃላት አሉ ተብሎ የአዲስ ኪዳን መጽሐፍት ስለተጻፉበት ቋንቋ ጥርጣሬ መንዛት "ፔስሚስት" መሆን አይመስልዎትም?

በታሪክ ረገድ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ተሽለን ከሁለት ሺህ ዓመታት በኋላ እንዲህ ነበር ወይም አልነበረም ብለን በሙሉ አፋችን መናገር የምንችል አይመስለኝም።

በጥቅሉ ግን የኔ ሐሳብ፣ በአንድ ትርጉም ሥራ ላይ ሂስ ማቅረብ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በአማርኛ ቋንቋችን የተሻለና ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዲገኝ የየራሳችንን ሐላፊነት እንወጣ ለማለት ነው።


ሰላም።
Aug 12, 2013 ኦፍቲ (1,250 ነጥቦች) የተመለሰ
ውድ ኦፍቲ

በአመልካከቶ ላይ ምንም ችግር የለብኝም፡ ነገር ግን ለጥያቄዎ የተጠቀሙበት ርእስና መልሶን የደመደሙብት አካሄድ የሚጋጭ ነው፡ ምክንያቱም በ1980 የታተመውና በቀላል አማርኛ በሚል በፕሮቴስታንቱ የቀረበው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ በጣም ብዙ ጥቅሶች ተቀይረው ሳለ፡ እርሶ ጥያቄና ቀጥለውም የሰጡት ማብራሪያ (systematically attacks the Orthodox Church, Protestants leaders, followers and other observers know this practice very well: at least the last fifty years).

ጥያቄዎና ቀጥለውም የሰጡት ማብራሪያ "የ1984ቱን የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን እትም" ነጥሎ የተሳሳተ ነው የሚል ድምዳሜ አንባቢው እንዲወስድ አላማ ያደረገ እንደወነ ለማረጋገጥ ደግምው ያንብቡት።

ከሰላምታ ጋር
ሰላም ስም-አልባ

ስለ አስተያየቱ በጣም አመሰግናለሁ። እርግጥ ነው የጥያቄዬ መግቢያ ይህን ዓይነት ስሜት ሊጭር ይችላል። ለስህተቱ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ይህን ዓይነት ውይይት በመፈጠሩም ደስተኛ ነኝ። በሁለተኛው መልሴ ላይ ግን ሃሳቤን በደንብ የገለጽኩ ይመስለኛል።

እርስዎ ስለ ጉዳዩ ያሎት አስተያየት ምንድነው? ከ1954ቱ በተሻለ መልኩ የመጽሐፍ ቅዱሱን መልእክት በትክክል የሚያስተላልፍ፣ ከተርጓሚው እምነት ተጽዕኖ የጸዳ፣ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አያስፈልገንም ይላሉ?

በዚህ ጉዳይ ላይ መወያየት (ለእንዲህ ዓይነቱ ትርጉም መዘጋጀት ግብዓት ይሆናል ብዬ አምናለሁ) በአማርኛችን መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ የተሰገሰጉ ለመጽሐፍ ቅዱስ እንግዳ የሆኑ የአብያተ ክርስቲያናት ትምህርቶች እንዲጋለጡ መንገድ ይከፍታል ብዬ አስባለሁ።

በ1984ቱ እትም ላይ እንደተጠቀሰው "ለቤተክርስቲያን እምነት ባዕዳን የሆኑ" የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላትን ሳይሆን ለመጽሐፍ ቅዱስ እምነት ባዕዳን የሆኑትን የቤተክርስቲያን እምነቶችን ልናጋልጥ ይገባናል ብዬ አምናለሁ።


ሰላም።
2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 3፥6
እርሱም ደግሞ በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን፤ ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል።
ፊደል ይገድላል መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል። ይላል የእግዚአብሔር ቃል ።
ዝም ብለህ ፀልይ አባቶቻችን ፊደል በመሰንጠቅ ፣ፀጉር በመሰንጠቅ ነገር በመጎንጎን አይደለም የፀደቁት ወንደም። በፍፁም ልብህ ፣ በፍፁም ነፍሰህ መድህን እየሱስ ክርስቶስን ፣ አጋዝሕት ዓለም ሥላሴን፣ እመን።
እንድህ ይላል ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ፣

የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው( ==መንፈስ ቅዱስ )
አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው(==ወልድ ዋህድ እየሱስ ክርስቶስ )
አሠራርም ልዩ ልዩ ነው፥ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው( == አብ)
ደግሞ እንዲህ ይላል የእግዚአብሔር ቃል፣

ኦሪት ዘጸአት
23፥2
ክፉውን ለማድረግ ብዙ ሰዎችን አትከተል ፍርድንም ለማጥመም ከብዙ ሰዎች ጋር ተስማምተህ አትመስክር።
ደግሞም፣
እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤አለች ክብርት፣ምርጥ ዕቃ፣ የጌታ እናት ፣ ድንግል ማርያም ።
ድሞ፤
ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።
አየህ እኛ የምናመልከው ንጉስ እየሱስ ክርስቶስ እግዝኣብሄር ነው ብለን ስሙን ማን ሰየመችው በለኝ ? እመቤታችን ።
የተሸከመችህ ማኅፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው አለችው።ሉቃ ፩፩,፪፯
መጽሐፈ ምሳሌ 14፡15 "የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል።"

1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፡15 "ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።"

ከዚህስ አንጻር እንዴት ታየዋለህ? መጀመሪያ የተጻፈውን ካልተጻፈው ለይ፣ ከዚያ በኋላ ጌታን እውነቱን ግለጽልኝ ብለህ ለምን። ያን ጊዜ ሁሉም ይገለጽልሃል።

የቲፎዞ እምነት አያድምን!
“እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ።“
(መዝሙረ ዳዊት 33:12)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us
...