ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ የሚከተለው ነው፦ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻው ላይ ጥሩ ዘር ከዘራ ሰው ጋር ይመሳሰላል። ነገር ግን ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ ጠላቱ መጥቶ በስንዴው ላይ እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። ቡቃያው አድጎ ፍሬ ባፈራ ጊዜ እንክርዳዱም አብሮ ታየ። ስለሆነም የባለቤቱ ባሪያዎች ወደ እሱ ቀርበው ‘ጌታ ሆይ፣ በእርሻህ ላይ የዘራኸው ጥሩ ዘር አልነበረም እንዴ? ታዲያ እንክርዳዱ ከየት መጣ?’ አሉት። እሱም ‘ይህን ያደረገው አንድ ጠላት የሆነ ሰው ነው’ አላቸው። እነሱም ‘ታዲያ ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህ?’ አሉት። እሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ ‘አይ፣ አይሆንም፤ ምክንያቱም እንክርዳዱን ስትነቅሉ ስንዴውንም አብራችሁ ልትነቅሉ ትችላላችሁ። ተዉት፣ እስከ መከር ጊዜ ድረስ አብሮ ይደግ፤ የመከር ወቅት ሲደርስ አጫጆቹን፣ በመጀመሪያ እንክርዳዱን ሰብስቡና እንዲቃጠል በየነዶው እሰሩ፤ ከዚያም ስንዴውን ሰብስባችሁ ወደ ጎተራዬ አስገቡ እላቸዋለሁ።’”—ማቴ. 13:24-30
በእርሻው ላይ ጥሩ ዘር የዘራው ሰው ማነው? ኢየሱስ ቆየት ብሎ የምሳሌውን ትርጉም ለደቀ መዛሙርቱ ባብራራላቸው ጊዜ “ጥሩውን ዘር የዘራው የሰው ገጽ 20ልጅ ነው” በማለት መልሱን ተናግሯል። (ማቴ. 13:37) “የሰው ልጅ” ተብሎ የተጠራው ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነባቸው ሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ እርሻውን አለስልሶ ለዘር አዘጋጅቷል። (ማቴ. 8:20፤ 25:31፤ 26:64) ከዚያም በ33 ዓ.ም. ከተከበረው የጴንጤቆስጤ ዕለት አንስቶ ጥሩ ዘር የሆኑትን ‘የመንግሥቱን ልጆች’ መዝራት ጀመረ። ይህ የመዝራት ሥራ የተከናወነው ኢየሱስ የይሖዋ ወኪል ሆኖ በደቀ መዛሙርቱ ላይ መንፈስ ቅዱስን ማፍሰስ በጀመረበትና የአምላክ ልጆች አድርጎ በቀባቸው ጊዜ እንደነበረ ግልጽ ነው።* (ሥራ 2:33) ከጊዜ በኋላ ጥሩው ዘር ማለትም ስንዴው አድጎ ጎመራ። ስለዚህ ጥሩ ዘር የሚዘራበት ዓላማ ከኢየሱስ ጋር በመንግሥቱ ተባባሪ ወራሾችና ገዥዎች የሚሆኑት ሰዎች ቁጥር እስኪሟላ ድረስ እነሱን በጊዜ ሂደት ለመሰብሰብ ነው።
ጠላት የተባለው ማን ነው? እንክርዳድ የተባሉትስ እነማን ናቸው? ኢየሱስ ጠላት የተባለው “ዲያብሎስ ነው” በማለት ተናግሯል። እንክርዳዶቹ ደግሞ “የክፉው ልጆች” እንደሆኑ ተገልጿል። (ማቴ. 13:25, 38, 39) እንክርዳድ መርዛማ እህል ሲሆን በቡቃያነት ደረጃ ከስንዴ ጋር በጣም ይመሳሰላል። የመንግሥቱ ልጆች እንደሆኑ ቢናገሩም እውነተኛ ፍሬ የማያፈሩ አስመሳይ ክርስቲያኖች በእንክርዳድ መመሰላቸው ምንኛ የተገባ ነው! እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የክርስቶስ ተከታይ እንደሆኑ የሚናገሩት እነዚህ ግብዝ ክርስቲያኖች የሰይጣን ዲያብሎስ ‘ዘር’ ክፍል ናቸው።—ዘፍ. 3:15
በእንክርዳድ የተመሰሉት እነዚህ ክርስቲያኖች መታየት የጀመሩት መቼ ነው? በእንክርዳድ የተመሰሉት እነዚህ ክርስቲያኖች መታየት የጀመሩት “ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ” እንደሆነ ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴ. 13:25) ይህ የሆነው መቼ ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ሽማግሌዎች እንደሚከተለው ብሎ በተናገረው ሐሳብ ላይ መልሱን እናገኛለን፦ “እኔ ከሄድኩ በኋላ ጨካኝ ተኩላዎች በመካከላችሁ እንደሚገቡና መንጋውን በርኅራኄ እንደማይዙ አውቃለሁ፤ ከእናንተ ከራሳችሁ መካከል እንኳ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር የሚናገሩ ሰዎች ይነሳሉ።” (ሥራ 20:29, 30) ቀጥሎም እነዚህን ሽማግሌዎች ምንጊዜም በመንፈሳዊ ንቁ እንዲሆኑ አሳስቧቸዋል። ክህደት እንዳይገባ ‘አግደው’ የነበሩት ሐዋርያት በሞት ካንቀላፉ በኋላ በርካታ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ አንቀላፍተው ነበር። (2 ተሰሎንቄ 2:3, 6-8ን አንብብ።) ታላቁ ክህደት የተጀመረው በዚህ ጊዜ ነው።
ኢየሱስ እዚህ ምሳሌ ላይ ስንዴው ተቀይሮ እንክርዳድ ይሆናል አላለም፤ ከዚህ ይልቅ እሱ የተናገረው በስንዴው መካከል እንክርዳድ እንደተዘራ ነው። በመሆኑም ይህ ምሳሌ ከእውነት የወጡትን እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሰይጣን ክፉ ሰዎች ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ሰርገው እንዲገቡ በማድረግ ሆን ብሎ ጉባኤውን ለመበከል የሚያደርገውን ጥረት ያመለክታል። የመጨረሻ ሐዋርያ የነበረው ዮሐንስ ዕድሜው በገፋበት ወቅት ክህደቱ በግልጽ መታየት ጀምሮ ነበር።—2 ጴጥ. 2:1-3፤ 1 ዮሐ. 2:18