ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » ጥያቄ መጠያየቂያ
Email this page to a friend   Monday, 25 January 2021
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ፥ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።“
(መዝሙረ ዳዊት 27:14)

rss

Today's verse

መጽሐፍ ቅዱስ መጠጥ ስለመጠጣት ( ሐጢያት ) ስለመሆኑ ምን ያስተምረናል ?? አስረዱኝ አመሰግናለሁ፡፡

Mar 21, 2011 መንፈሳዊ ስም-አልባ የተጠየቀ

3 መልሶች

0 ድምጾች
አዎ!ያስተምራናል.መጠጣት ሀጣት ነው!
Mar 21, 2011 ኩምላ ነደ (190 ነጥቦች) የተመለሰ
ኩምላ ጎበዝ ከቃሉ አስደግፈና እስቲ ነገረን ። ጥሩ አጀማመር ነው።
+2 ድምጾች
በዚህ ጉዳይ እኔ ሁለት አመለካከቶች አሉኝ። እነዚህን ሁለት አመለካከቶች በሁለት ክፍል ከፍዬ ላቀርባቸው እወዳለሁ።
    1ኛ - እኔ ራሴ መጠጥ አልጠጣም፤ ሰውም ከሚጠጣ ባይጠጣ ይመረጣል እላለሁ። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ፤ ለቃሉ ታማኝ መሆን አለብኝ ብዬ ደግሞ አምናለሁ። ስለዚህ ባጭር ቃል ጥያቄውን ለመመለስ፤ መጽሐፍ ቅዱስ መጠጥ ወይም አልኮሆል ያለው መጠጥ መጠጣት ኃጢአት ነው ብሎ አያስተምርም። መጠጥ መጠጣት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የትም ቦታ ኃጢአት እንደሆነ የሚያስተምር ቦታ የለም።

    2ኛ - ሆኖም ኢትዮጵያዊ የሆነ አማኝ ወይም የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ፤ መጠጥ መጠጣት የለበትም ብዬ አምናለሁ። ይህም አለመጠጣቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው እላለሁ።

እነዚህን ሁለት አመለካከቶቼን መጽሐፍ ቅዱስን ተመርኩዤ በሁለት ክፍል ለማብራራት እሞክራለሁ። በቅድሚያ ግን ስካር ወይም መስከር ኃጢአት እንደሆነ ባማያሻማና ግልጽ በሆነ መልኩ በአዲስ ኪዳን እንደተጻፈ ለማስመር እወዳለሁ።
Quote:
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6
9 ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ
10 ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።
Quote:
ወደ ገላትያ ሰዎች 5
19 የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥
20 መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥
21 መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።

ስለዚህ የምንነጋገረው መጠጥ መጠጣት ኃጢአት ነው አይደለም በሚለው ላይ ነው እንጂ፤ ስካር ላይ እንዳልሆነ ግልጽ ሊሆን ይገባል።

ክፍል 1 - መጠጥ በመጽሐፍ ቅዱስ

የሃይማኖት መነጽርና መጽሐፍ ቅዱስ

ብዙ ጊዜ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ከሆኑ ወገኖቼ ጋር ስለ ማርያም ሲነሳ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ወገኖቼ ላይ የማየው ተደጋጋሚ ችግር፤ የተጻፈውን ቃል ከመቀበል ይልቅ፤ ከልጅነት ጀምሮ የሰሙትን የሃይማኖታቸውን ባህልና እምነት፤ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግድ ለማስገባት መሞከር ነው። ይህ ደግሞ ቃሉ ያላለውን በግድ እንዲል ስለሚያስገድዱት፤ ቃሉ ላይ እንዲጨምሩ ወይም ከቃሉ እንዲቀንሱ ያደርጋቸዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ደግሞ ብዙ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታይ ወገኖቼ መጠጥን የመሳሰሉ ጉዳዮች ሲነሱ፤ በቃሉ ከተጻፈው ይልቅ፤ የራሳቸውን ደጋግመው በየስብከቱ የሰሙትን የሃይማኖታቸውን ባህል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማስገባት ይሞክራሉ። ልክ እንደ ኦርቶዶክስ ተከታይ ወገኖቼ መጽሐፍ ቅዱስ ያላለለውንና ያላዘዘውን እንዲልና እንዲያዝ ስለሚይስገድዱት፤ በዚህ ጉዳይ ለቃሉ ታማኝ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል።

መጠጥ በአይሁድ ባህልና ሃይማኖት

በቅድሚያ የወይን ጠጅ ወይም አልኮሆል ያለበት መጠጥ መጠጣት በብሉይ ኪዳንም ይሁን ኢየሱስ በነበረበት ዘመንም፤ እስከ አሁንም ድረስ በአይሁድ ባህልና እምነት ክልክል ወይም ኃጢአት አይደለም። በአገራችን በገጠሩ አካባቢ ጠላ የእለት ተዕለት መጠጥ እንደሆነ ሁሉ፤ እንዲሁ በተለይ የወይን ጠጅ በጣም የተለመደ መጠጥ ነው። በይበልጥ ደግሞ በዓላት ሲከበሩ ያለ ወይን ጠጅ አይሆንም። አይሁድ የፋሲካን በዓልም ሲያደርጉም የሚጠጡት ወይን፤ ጭማቂ ሳይሆን የወይን ጠጅ ነው።

ከሁሉ አስቀድመን እንግዲህ አዲስ ኪዳንም ይሁን ብሉይ ኪዳን በተጻፈበት በአይሁድ ባህልና ሃይማኖት በትኛውም ህግ፤ የወይን ጠጅ መጠጣት እንዳልተከለከለ መገንዘብ አለብን። ከዚህም በላይ ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታዮች እንዳልነበሩ በቅድሚያ ልንረዳ ያስፈልጋል። ስለዚህ በግድ ደቀመዛሙርቱን "ጴንጤ" እንዳናደርጋቸው ልንጠነቀቅ ይገባናል። ;) ደቀመዛሙርት በአይሁድ ባህል ውስጥ እንጂ በፕሮቴስታንት ወይም በኦርቶዶክስ ባህል ውስጥ አልኖሩምና።

በሕግ ስላልተከለከለና መጠጣት ኃጢአት ነው ተብሎ ስላልተጻፈም፤ በብሉይ ኪዳን ስለ ወይን ጠጅ መልካምነትም ጎጂነትም ተጽፎ እናገኛለን። መጠጣት ክልክል ስላልሆነ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጎጂነቱ እንደ ህግ ሳይሆን እንደ ምክር የሚሰጠው።
Quote:
መዝሙረ ዳዊት
104፥15 ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል፥ ዘይትም ፊትን ያበራል፥ እህልም የሰውን ጕልበት ያጠነክራል።

መጽሐፈ ምሳሌ 20
1 የወይን ጠጅ ፌዘኛ ያደርጋል፥ ብርቱ መጠጥም ጠበኛ ያደርጋል በዚህም የሳተ ሁሉ ጠቢብ አይደለም።

መጽሐፈ ምሳሌ 23
29 ዋይታ ለማን ነው? ኀዘን ለማን ነው? ጠብ ለማን ነው? ጩኸት ለማን ነው? ያለ ምክንያት መቍሰል ለማን ነው? የዓይን ቅላት ለማን ነው?
30 የወይን ጠጅ በመጠጣት ለሚዘገዩ አይደለምን? የተደባለቀ የወይንን ጠጅ ይፈትኑ ዘንድ ለሚከተሉ አይደለምን?
31 ወደ ወይን ጠጅ አትመልከት በቀላ ጊዜ፥ መልኩም በብርሌ ባንጸባረቀ ጊዜ፥ እየጣፈጠም በገባ ጊዜ።
32 በኋላ እንደ እባብ ይነድፋል፥ እንደ እፉኝትም መርዙን ያፈስሳል።
33 ዓይኖችህ ጋለሞታዎችን ያያሉ፥ ልብህም ጠማማ ነገርን ይናገራል።

እነዚህ ለምሳሌ ያህል ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች፤ የወይንን መልካምነት እንዲሁም ደግሞ ጎጂነት የሚናገሩ ናቸው። ጎጂነቱን የተጻፈው ግን እንደ ህግና እንደ ኃጢአት በመከልከል ሳይሆን መጠጥ ወዴት እንደሚያመራ በማሳየትና በመምከር ነው።

መጠጥ በአዲስ ኪዳን

በአዲስ ኪዳንም የወይን ጠጅ የተጠቀሰበትን ክፍሎች ስንመለከት መጠጣት ኃጢአት ስለመሆኑ የተጻፈ አንዳችም ቃል አናገኝም። ይልቁን እንደ ብሉይ ኪዳን ወይን ማብዛት እንደሌለብን ነው የምንመከረው። ሆኖም በአይሁድ ባህል በአዲስ ኪዳንም ቢሆን ወይን ጠጅ የእለት ተለት መጠጥ እንደመሆኑ፤ አትጠጡ ወይም መጠጣት ኃጢአት ነው የሚል ትዕዛዝ የለም።

ከዚህ በታች እስቲ አንዳንድ የአዲስ ኪዳን ክፍሎችን እንመልከት። እዚህ ላይ ልብ ልንል ከሚገባን ነገሮች አንዱ በአዲስ ኪዳን የወይን ጠጅ ብሎ ሲናገር አንዳንድ ሰባኪዎች እንደሚናገሩት አዲስ ኪዳን በተጻፈበት በግሪኩ ሁለት የተለያዩ ቃላቶችን እየተጠቀመ እንዳልሆነ ነው። አንዳንዴ የሚያስክረውን የወይን ጠጅ፤ አንዳንዴ ደግሞ የማያሰክረውን የወይን ጭማቂ እያለ እንዲህ እየለያየ አይደለም አዲስ ኪዳን የሚናገረው። በአዲስ ኪዳን ብዙ ጊዜ የወይን ጠጅ ተብሎ የተጻፈው የግሪኩ ቃል oinos የተባለው ነው። ይሄም ቃል የሚናገረው የሚያሰክረውን የወይን ጠጅ እንደሆነ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ያረጋግጣሉ።

ስለዚህ ራሳችን ለማመዛዘን እንዲረዳን ከዚህ በታች በምናያቸው ክፍሎች ሁሉ ወይን ጠጅ ተብሎ በአማርኛው በተተረጎመበት ጎን የግሪኩን ቃል በቅንፍ አስገብቼዋለሁ።
Quote:
ወደ ኤፌሶን ሰዎች
5፥18 መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ(oinos) አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና፤

ከላይ ባለው ክፍል ጳውሎስ በኤፌሶን የሚገኙትን አማኞች፤ በወይን ጠጅ እንዳይሰክሩ ይልቁንም በዚያ ፈንታ መንፈስ እንዲሞላባቸው ሲያሳስባቸው እንመለከታለን። በዚህ ክፍል እንደሚያሰክር ጳውሎስ የሚናገረው የወይን ጠጅ በአዲስ ኪዳን ብዙ ጊዜ የተጠቀሰው የግሪኩ oinos የተባለው ቃል ነው። ይህ ክፍል በግልጽ እንደሚያስቀምጠው oinos የወይን ጭማቂ ሳይሆን ሊያሰክር የሚችል የወይን ጠጅ ነው።
Quote:
የዮሐንስ ወንጌል 2
1 በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፥ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤
2 ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ።
3 የወይን ጠጅም(oinos) ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት። የወይን ጠጅ(oinos) እኮ የላቸውም አለችው።
...
9 አሳዳሪውም የወይን ጠጅ(oinos) የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ።
10 ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ(oinos) ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ(oinos) እስከ አሁን አቆይተሃል አለው።

ከላይ በዮሐንስ 2 የሚገኘውና ኢየሱስ በሠርግ ላይ ተገኝቶ ውሃን ወደ ወይን የቀየረበትን ታሪክ ስናነብብ አሳዳሪው ኢየሱስ የቀየረውን ወይን ከቀመሰ በኋላ "ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል" ነው ያለው። ከማለቁ በፊት ሰዎች ያሰከረውንም ይሁን ኢየሱስ የቀየረው ወይን ሁለቱም በግሪኩ oinos የሚባለው አንድ ቃል ናቸው። ስለዚህ አንዱ የወይን ጠጅ ነበር አንዱ ግን የወይን ጭማቂ ማለት አንችልም። መጽሐፍ ቅዱስ ለሁለቱም የተጠቀመበት ቃል ያው አንድ ቃል ነውና።

በሌላ በኩል የሚያሰክረውን የወይን ጠጅ መጠጣት ኃጢአት ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ ውሃውን ወደ ወይን ባልለወጠላቸውም ነበር። ይልቁንም ገሥጾ ያስተምራቸው ነበር።
Quote:
የሉቃስ ወንጌል 7
33 መጥምቁ ዮሐንስ እንጀራ ሳይበላ የወይን ጠጅም(oinos) ሳይጠጣ መጥቶ ነበርና። ጋኔን አለበት አላችሁት።
34 የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጥቶአልና። እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ አላችሁት።

ከላይ ባለው ክፍል ኢየሱስ መጥምቁ ዮሐንስንና እርሱን ራሱን እያወዳደረ ሲናገር፤ ዮሐንስ እንጀራ እንዳልበላና የወይን ጠጅ (እዚህም ልብ እንበል የሚያሰክረውን ማለት ነው) ሳይጠጣ እንደመጣ፤ ኢየሱስ ግን እየበላና እየጠጣ እንደመጣ ይገልጻል። መጥምቁ ዮሐንስ ከልጅነቱ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ እንደሚሆን ስለተጻፈ (ሉቃስ 1፡15) መጠጥ አይፈቀድለትም ነበር ስለዚህም አልጠጣም። ኢየሱስ ግን በናዝሬት ከተማ ያደገ የናዝሬቱ እንጂ ጸጉሩን የማይላጭና የወይን ጠጅ የማይጠጣ ናዝራዊ አልነበረም። ስለዚህ የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ ነው የመጣው ይላል ጌታ ሲናገር። ምንድነው የበላው? ምንድነውስ የጠጣው ስንል፤ ከላይ ቁጥር 33 እንደሚያሳየን የሚናገረው ስለ እንጀራና ሊያሰክር ስለሚችለው የወይን ጠጅ ነው። የወይን ጠጅም ይጠጣ ስለነበር ነው ከላይ በቁጥር 34 እንደምናነብበው "በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ" ብለው የሃይማኖት ሰዎች ይከሱት የነበረው።
Quote:
1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ
5፥23 ስለ ሆድህና ስለ በሽታህ ብዛት ጥቂት የወይን ጠጅ(oinos) ጠጣ እንጂ፥ ወደ ፊት ውኃ ብቻ አትጠጣ።

በዚህም ክፍል የምንመለከተውና ጢሞቴዎስ ጥቂት እንዲጠጣ ጳውሎስ የሚመክረው የወይን ጠጅ ያው በዮሐንስ ወንጌል ላይ ያሰክራል የተባለው oinos የተባለው ቃል ነው። ስለዚህ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እያለ ያለው፤ ስለ ሆድህ ሕመም ጥቂት የወይን ጭማቂ ጠጣ ሳይሆን፤ በአማርኛው በትክክል እንደተተረጎመው ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ እያለ ነው። የወይን ጠጅ መጠጣት ኃጢአት ቢሆን ኖሮ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንዲህ ያለ ምክር ባልመከረው።
Quote:
1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ
3፥8 እንዲሁም ዲያቆናት ጭምቶች፥ በሁለት ቃል የማይናገሩ፥ ለብዙ ወይን ጠጅ(oinos) የማይጎመጁ፥

ከላይ ባለው ክፍል ደግሞ ጳውሎስ ዲያቆናት ምን ባሕርያት ሊኖራቸው እንደሚገባ ሲናገር፤ "ለብዙ ወይን ጠጅ የማይጎመጁ" ወይም not given to excessive drinking ወይም ከልክ ላለፈ የወይን ጠጅ ያልተሰጡ መሆን አለባቸው ይላል። የወይን ጠጅ መጠጣት የተከለከለ ቢሆን ኖሮ፤ የወይን ጠጅ የማይጠጡ ነው እንጂ ማለት ያለበት ጳውሎስ "ለብዙ ወይን ጠጅ የማይጎመጁ ወይም ያልተሰጡ" ማለት አልነበረበትም።

በተመሳሳይ ሁኔታም ስለ አሮጊቶችም ጳውሎስ ሲናገር እንዲሁ የማይጠጡ ሳይሆን የሚለው "ለብዙ ወይም ከልክ ላለፈ ወይን ጠጅ የማይገዙ" ነው የሚለው።
Quote:
ወደ ቲቶ
2፥3 እንዲሁም አሮጊቶች ሴቶች አካሄዳቸው ለቅዱስ አገልግሎት የሚገባ፥ የማያሙ፥ ለብዙ ወይን ጠጅ(oinos) የማይገዙ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ ይሁኑ፤

ከነዚህም ክፍሎች በተጨማሪ፤ በአዲስ ኪዳን ሌሎችንም ክፍሎች ብንመለከት የወይን ጠጅ ብሎ የሚለው በአዲስ ኪዳን የሚያሰክረውን ጠጅ እንጂ የወይን ጭማቂን እንዳልሆነ በግልጽ መመልከት እንችላለን።

ከዚህ ብዙ ጊዜ በአዲስ ኪዳን በግሪኩ የወይን ጠጅ ተብሎ ከተጠቀሰው oinos ውጪ gleukos የሚልው ቃል አንድ ጊዜ ብቻ ተጠቅሷል። ይህም ሐዋርያቱ በመጀመሪያ መንፈስ ቅዱስ በወረደባቸው ጊዜ የተመለከቱት ሰዎች በሐዋ 2፡13 ላይ "ጉሽ የወይን ጠጅ(gleukos) ጠግበዋል" ሲሉ የተጠቀሙበት ቃል ነው። ይህ ቃል እዚህ ቦታ ላይ ብቻ ነው የተጠቀሰው፤ እንዲህም ሆኖ ሰዎቹ የሚናገሩት ስለ ስካር እንደሆነ በቁጥር 15 ላይ ከጴጥሮስ ንግግር ማየት ይቻላል። "ለእናንተ እንደ መሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም፥ ከቀኑ ሦስተኛ ሰዓት ነውና፤" ቁ.15 ብሎ ይናገራልና። ምንም እንኳን ከሌሎች በተለየ ሁኔታ አንድ ጊዜ ይሄ gleukos የሚባለው ቃል ቢጠቀስም፤ ይህም ቃል በአዲስ ኪዳን ስለሚያሰክር ወይን እንጂ ስለ ጭማቂ እንደማይናገር ከምንባቡ መረዳት እንችላለን።

ስለዚህ በአዲስ ኪዳን ከልክ ያለፈ መጠጣትና መስከር ነው እንጂ፤ የትም ቦታ መጠጣቱ ብቻ እንዳልተከለከለ ወይም ኃጢአት አንዳልሆነ እንመለከታለን።

ሆኖም ኢትዮጵያዊ አማኝ ወይም የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ መጠጥ መጠጣት የለበትም እላለሁ። ለምን? ይህን በሚቀጥለው ክፍል ከመጽሐፍ ቅዱስ ለማብራራት እሞክራለሁ።

ይቀጥላል...
Mar 22, 2011 በቃሉ (2,230 ነጥቦች) የተመለሰ
Mar 22, 2011 በቃሉ ታርሟል
+2 ድምጾች
ክፍል 2 - ኢትዮጵያዊ የሆነ አማኝ ወይም የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ፤ መጠጥ መጠጣት የለበትም፤ ለምን?

አዲስ ኪዳን እንደ ብሉይ ኪዳን የሚበላና የማይበላይ፣ የሚደረግና የማይደረግ፣ ንጹሕና የረከሰ እያለ የሕግጋት ዝርዝር አልሰጠንም። አንዳንድ ሰዎች ሲጋራ ኃጢአት ነውን? ጫት መቃምስ? ዲስኮ መሄድስ? ወዘተ እያሉ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ የኃጢአት ዝርዝር እንዲያሳዩአቸው የሚፈልጉ አሉ። ምንም እንኳን በማያሻማ መልኩ አንዳንድ ድርጊቶች ኃጢአት እንደሆኑ ቢጠቀስም፤ በአዲስ ኪዳን እንደዚህ በኃጢአት ዝርዝር አይደለም የሚሠራው።

በአዲስ ኪዳን የሚሠራበት አሠራር ፍቅርና ማነጽ የሚል ነው።
Quote:
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች
6፥12 ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን አይጠቅምም። ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሠለጥንብኝም።

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች
10፥23 ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም፤ ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም።

ስለዚህ ስለ መጠጥም ስንነጋገር፤ በአዲስ ኪዳን ጥያቄው ተፈቅዷል አልተፈቀደም የሚለው ሳይሆን፤ እኔንና የሚያዩኝን ያንጻል? እኔንና ስጠጣ የሚያዩኝን ይጠቅማል? በእኔ ላይ ይሰለጥናል? የሚለው ነው።

በኢትዮጵያውያኖች ዘንድ ማንም አማኝ ወይም የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ነኝ የሚል መጠጥ ቢጠጣ ኃጢአት እንደሠራ ነው የሚቆጠረው። እንደዚህ የሚቆጥሩት ራሳቸው የእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆኑ ከእምነቱ ውጪ የሆኑ ሰዎችም ጭምር ናቸው። አንድ አማኝ ወንጌል የመሰከረለት ሰው፤ መስካሪው መጠጥ ሲጠጣ ቢያየው፤ ወንጌሉ ከንቱ እንደሚሆን ግልጽ ነው። መጠጥ የጠጣው አማኝ ኃጢአት ስላደረገ አይደለም። ነገር ግን በኢትዮጵያኖች ዘንድ ይህ የተለመደ አመለካከት ስለሆነ ነው። ይህ ብቻ አይደለም፤ አንድ መጠጥ የሚጠጣ አማኝ፤ ምንም አይነት ጸጋ ቢኖረው አገልግሎቱ በሌሎች አማኞች ዘንድ በፍጹም ተቀባይነት አይኖረውም፤ ስለዚህም ጸጋውን እንዳይጠቀምና እንዲያባክን ያደርገዋል።

ስለዚህ ሌሎች በዚህ ምክንያት እንዳይሰናከሉ፤ የሚጠጣው አማኝ መጠጣቱን ማቆም ይኖርበታል።
Quote:
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች
8፥13 ስለዚህም መብል ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ፥ ወንድሜን እንዳላሰናክለው ለዘላለም ከቶ ሥጋ አልበላም።

ሥጋ መብላት ምንም አልተከለከለም ኃጢአትም የለምበትም፤ ሆኖም ጳውሎስ ከላይ እንደሚናገርው ወንድምን የሚያሰናክል ከሆነ "ለዘላልም ከቶ ሥጋ አልበላም" ይላል።
Quote:
ወደ ሮሜ ሰዎች
14፥21 ሥጋን አለመብላት ወይንንም(oinos) አለመጠጣት ወንድምህም የሚሰናከልበትን አለማድረግ መልካም ነው።

ምናልባት አንዳንዶች፤ ኢትዮጵያዊ አማኞችን መጠጣት ኃጢአት እንዳይደለ ማስተማር አይቻልም ወይ? ብለው ሊጠይቁ ይቻላሉ። ሆኖም መብል ወይም መጠጣት በአዲስ ኪዳን ይሄን ያህል ዋና ነገር አይደለም። መጠጥ ተፈቅዶአል የሚል ትምህርት ደግሞ ብዙ ክርክሮችና ክፍፍሎች ሊያስነሳ እንደሚችል መገመት ይቻላል። ስለዚህ ይህ ዋና የእምነት ጉዳይ ባልሆነ ነገር መንፈሳዊ ሕይወቶችን መጉዳት አያስፈልግም።
Quote:
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች
8፥8 መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላም ምንም አይጎድለንም ብንበላም ምንም አይተርፈንም።

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች
6፥13 መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሥጋ ነው፤

በሌላ በኩል ደግሞ፤ መጠጥ የማይጠጣው ሰዎችን ላለማሰናከልና ሕይወታቸውን ላለመጉዳት ከሆነ፤ ታዲያ በድብቅ ለብቻ ቢጠጣስ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ከላይ እንዳልኩት መጠጣትን መጽሐፍ ቅዱስ አይከለክልም። ሆኖም በድብቅ መጠጣት፤ እንደ እኔ እንደ እኔ ሌላ የባሰ ችግር ያመጣል። ይሄውም ግብዝነት ነው። ግብዝነት ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱን ካስጠነቀቃቸውና ብዙ ጊዜ ፈሪስውያንን ከሚከስበት ኃጢአቶች ዋነኛው ነው።
Quote:
የሉቃስ ወንጌል
12፥1 ... አስቀድማችሁ ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠበቁ፥ እርሱም ግብዝነት ነው።

ግብዝነት በድብቅ ሌላ ሰው፤ በውጭ ደግሞ ሌላ ሰው መሆንን የሚያመለክት ነው። ግሪኮች ይህንን ቃል ይጠቀሙበት የነበረው፤ ትልልቅ ማስክ ለብሰውና በመድረክ ላይ ሌላ ሰው መስለው ለሚጫወቱ ቴአትረኞች ነው። በድብቅ መጠጣት፤ በግልጽ ደግሞ ምንም እንደማይጠጡ ማስመሰል፤ ሳናውቀው ለፈሪሳውያን ኃጢአት ሊዳርገን ይችላልና እኔ በድብቅ መጠጣትንም አልመክርም።

በመጨረሻም ሲጋራ ኃጢአት ነውን? ጫት መቃምስ? ዲስኮ መሄድስ? መጠጥስ? ወዘተ የሚሉ ሰዎች ራሳቸውን እንዲጠይቁ የምፈልገው ነገር አለ። ጳውሎስ እኮ መንፈስ ቅዱስን ስለሚሞላና ያም የሕይወት እርካታን ስለ ሰጠው፤ መጠጥ አይደለም ሥጋ እንኳን ወንድሜን የሚያሰናክል ከሆነ ለዘላለም አልበላም ነው የሚለው። ስለዚህ ጥያቄው ያለው በመንፈስ ቅዱስ እየተሞላን የመንፈስ እርካታን አግኝተናል ወይ? የሚለው ላይ ነው። ያ ከሆነ ለሌሎች ብለን ብዙ ነገር ሳይከብደን መተው እንችላለን።
Quote:
ወደ ኤፌሶን ሰዎች
5፥18 መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና፤
Mar 23, 2011 በቃሉ (2,230 ነጥቦች) የተመለሰ
እዝጋብሃር ይባርክህ ጥሩ መልስ ተባረክክክክክክክክክ
ሃይማኞተኝነት ያልታየበት መልካም መልስ..... እግዚአብሄር ይባርክህ።
የፃፍኸውን ልፅፍ ስል መቀደሜን አየኹ። በጣም በጣም አመሰግናለሁ። መልሱ ሁሉ ሊቀበለው የሚገባ ነው ባይ ነኝ። አምላክ ይባርክህ

ከምስጋና ጋር
ወይን ጠጅን በተመለከት የጻፍከው ጽሑፍ እጅግ ሰፊ ነው። ይሁን እንጅ አንድ የጠቀስከው ዓቢይ ነጥብ አለ እርሱም ጌታ ኢየሱስም ሓዋርያትም የብሉይ ኪዳን አማኞች ናቸው። በብሉይ ኪዳን እንደ ሳምሶን ያሉ ናዝራውያን የሚያሰክር ነገር እንዳይቀምሱ (ዮሐንስም የሚያስክር መጠጥ አይጠጣም)የተባሉበት ምክንያቱ ምንድን ነው ትላለህ? የአዲስ ኪዳንን አማኞች ከብሉይ ኪዳን አማኞች ለየት የሚያደርጋቸው በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን በሚገኘው አዲስ ልደት ከእግዚአብሔር በመወለዳቸው (ዮሐ. 1፡12)ያ መንፈሳዊ ማንነት ወይም መንፈስ ቅዱስ በዉስጣቸው ከመኖሩ የተነሳ ይሆን? መጥምቁ ዮሐንስ እንዳይጠጣ የተሰጠው ምክንያት በእናቱ ማህጸን እያለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል (ሉቃስ 1፡15)ስለሚል በመንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሔር የተወለደ፣ የመንፈስ ቅዱስ መኖሪያ ስለሆነ፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ስለሆነ መጠጥም ጫትም፣ መዋሸትም፣ ማመንዘርም፤ ማንኛውም ኃጢአት አብሮ አይሄድም፡ ሰው ሳይሰክርም፣ ሳይሰርቅም፣ ምንም መጥፎ የምንላቸውን ነገሮች ሳያደርግም እንዲሁ ኃጢአተኛ ነው። ወደ ደህንነት ለመጣትና ከገሃነም ለማምለጥ ከላይ የተዘረዘሩትን ነገሮች ከማድረግ በመቆጠብ ሳይሆን፤ ወደገሃነም የሚያስገባው እግዚአብሔር የላከውን የማምለጫ መንገድ አለመቀበል ብቻ ነው (ዮሐ. 3፡18)
“እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ።“
(መዝሙረ ዳዊት 33:12)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2021 by iyesus.com
Terms of use | Contact us
...