ሞኑን የከተማችን ወሬ ሆኖ የከረመው አንድ አስገራሚ(እንደዚህ ጸሐፊ እምነት አሳፋሪ) ክስተት ነበር፡፡ ክስተቱ አንድ ዜግነቱ የማላዊ የሆነ “ነብይ” ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ በሚሊኒየምና እንዲሁም በነጋታው ‹‹መድህን ዲኮር›› በተባለ አዳራሽ የታየ “ሕዝባዊ ውርደት” ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ አይነት ክስተቶችን ልብ ብሎ ለተመለከተ ሃገሪቱ ጠባቂ የሌላትና ማንም እንደፈለገ እየገባና እየወጣ የሚፈነጭባት ‹‹መሰማሪያ›› ትመስለዋች፡፡ በተለይም ደግሞ የሕዝብ ድህነት ፤ መጎምዥት ፤ መንፋሰዊ ክስረትና ውድቀትን ተገን አድርጎ በየስፍራው የሚነሳው “ሃገር በቀል ቦጥቧጭ” አልበቃ ብሎ ‹‹አለም አቀፉን›› ደግሞ እየጋበዙ በማምጣት እንዲህ ሕዝብን መጫወቻ ማድረግን ስንሰማ ከዚህ በላይ ሕዝብ የራሱን ክብር ከጭቃ የሚጥልበት ትንሽነት ከወዴት ሊመጣ ይችላል? በማለት ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡
በአንድ ወቅት ‹‹ፓስተርና ፖስተር›› ሲባልበት የነበረው ከተማ ዛሬ “ወደ ነቢያት ጉባኤ” ተቀይሮ ሁሉ በየፊናው የነብይነት ካባን በየአደባባዩ እየተጎናጸፈ የሕዝቡን መጎምዥትና ጭንቀት ተገን አድርጎ መቆምን አስተማማኝ የትርፍ መስክ ሲያደርገው “ኧረ ሃይ ባይ የለም ወይ?” የሚያስብል ሆኗል፡፡ እርግጥ ነው ትውልድና ዘመን ብዙ ዓይት መልክ ያለው ክስረት ውስጥ ለመግባቱ በድፍረት ብቻ ሳይሆን በተሰበረ ልብ እንናገራለን፡፡ ዛሬ የመንፈሳዊነት አገልግሎት በኢትዮጵያ ከሰማዩ ይልቅ የምድራዊውን ሕይወት ጥያቄ ምላሽ በመስጠት የተያዘ የትርፍ መስክ ያደረገውም ይኽው ክስረታችን ነው፡፡ ደርግ የሃይማኖት ነጻነትን ነፍጎ ሕዝቡን ኮሚኒስት (ኢ-አማኒ) ለማድረግ ሲታትር በዚያ ዘመመንና ትውልድ በመንፈሳዊነት ጸንተው ዋጋ የከፈሉ በርካቶች ነበሩ፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ መጣና “የሃይማኖት ነጻነት” በማለት ሲያውጅ “ዋጋ የተከፈለበት” መንፈሳዊነት “ዋጋ የሚያስከፍሉበት” ሆኖ ቀረ፡፡ በመሆኑም ለዚህ አይነቱ በሀገር ላይ ለመጣ መንፈሣዊ ብቻ ሳይሆን የማንነት ውድቀት ተጠያቂው ማነው? ወዴትስ እየሄድን ይሆን ?
ከዓመት በፊት በ “ቢቢሲ” የቴሌቪዥን ጣበያ የተሰራጨ አንድ አስገራሚ ሪፖርት አስታውሳለሁ፡፡ ሪፖርቱ በአውሮፓ ሀገር አንዳንድ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት በሰባኪ እጥረት መቸገራቸውንና ምዕመናንም እንዲሁ ወደ ቤተክርስቲያን መሄድ በማቆማቸው ባዷቸውን እንደቀሩ የሚያሳይ ነበር፡፡ ታዲያ በዚሁ ሰባኪ መጥፋት ምክንያት እነዚሁ ባዷቸውን የቀሩ ምዕመናን ከመካከላቸው እየተመራረጡ መጽሐፍ ቅዱስ በመስበክ ሰንበትን እንሚያሳልፉም ጋዜጠኛው አክሎ አቀረበልን፡፡ በዚህ ሪፖርት ላይ አስገራሚው ክስተት የሰባኪ መጥፋት ወይም የምዕመናን ቁጥር መመናመን ብቻ አልነበረም ፤ ነገር ግን ቀሩትም ምዕመናንም ቢሆኑ በዕድሜ እጅግ የሸመገሉ የመሆናቸው ነገር ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ መንፈሳዊ ክስረት በዚች ሀገር ወደፊት አለመድረሱን እርግጠኛ ሆኖ ማስተማመኛ መያዝ አይቻልም፡፡ ይልቁንም ዛሬ የተያዘው መንፈሳዊ መሳይ ‹‹ሸቀጣ›› ነገ ሕዝቡ እጁን ለዘመናት ከዘረጋበት አምላክ ወደ ራሱ መሻትና ፍላጎት በመቀሰር የእርስ በእርስ መተሳሰቡና መከባበሩ እንደ ጉም እንዳያበነው ስጋት ገብቶናል፡፡ መጽሐፉ ‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች››ይላል የሰሞኑን ውጥንቅጥ ከዳር ቆሞ ለታዘበ ደግሞ እጆቹን ወደ አምላኩ ሳይሆን ወደ ገንዘብ የዘረጋው ትውልድን መመልከት ፤ ከስጠኝና ባርከኝ ጋር የተቆራኝ ‹‹የመጎምዥት ልክፍት›› በትውልዱ ላይ ማየት በጣም ያሳዝናል፡፡