እዚህ ላይ ትንሽ ለማስተካከል ያህል የሚከተለውን መጨመር እፈልጋለሁ። ራዕይ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ የነበረው ትርጉምና አሁን መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ካበቃ ከ2000 ዓመታት በኋላ ያለው ትርጉም ትንሽ ይለያያል። እናም የዘመናችንን ትርጉም ወስደን መጽሐፍ ቅዱስም ያንኑ የሚል እንዳይመስለን ያስፈልጋል።
በዘመናችን በክርስቲያኖችም ይሁን በዓለማዊያን ዘንድ ራእይ ማለት ሰው ሊያደርገው ያሰበውና በልቡ ያስቀመጠው አንድ ፕሮጀክት ማለት ነው። ይህንን ታዲያ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ነው በልባችን ያስቀመጠው ብለው ሲያምኑ ዓለማውያን ደግሞ ራሳቸው አውጠተው አውረደው ያሰቡት እንደሆነ ይናገራሉ። ሆኖም ምንም እንኳን ማን በልባቸው እንዳስቀመጠው የክርስቲያኖችና የዓለማዊያን አመለካከት ይለያይ እንጂ በመሠረቱ የሁለቱም መረዳት ተመሳሳይ ነው። ይህም ሰው ሊያደርገው ያሰበው እቅድ ወይም ፕሮጀክት ነው በዚህ ባለንበት ዘመን ራዕይ ተብሎ የሚጠራው። ታዲያ በክርስቲያኖች ዘንድ ብዙ ጊዜ ሊሠራው ያሰበው አንድ እቅድ ያለው ሰው ራሱን ባለራዕይ ብሎም የመጥራት አዝማሚያ አለ።
በመጽሐፍ ቅዱስ ግን ራዕይ ፈጽሞ የተለየ ትርጉም ነው ያለው። ራዕይ ማለት በመጽሐፍ ቅዱስ ሰው ሳይሆን እግዚአብሔር ሊያደርው ያሰበው የወደፊት ሃሳብና እቅድ ነው። ይህንን ታዲያ ብዙ ጊዜ ለነብያቱ ስለሚገልጥ ነብያቱ በተለይ በብሉይ ኪዳን ባለራዕይ ተብለው ይጠራሉ። ታዲያ እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን፤ ነብያቱ ባለራዕይ የሚባሉት ዛሬ ክርስቲያኖች እንደሚመስላቸው እግዚአብሔር በነብያቱ ሕይወት ሊሠራው ስላለው እቅድ ስለገለጠላቸው አይደለም። እንዲያውም ብዙ ጊዜ ለነብያቱ ይገለጥ የነበረው በመጨረሻው ዘመን እግዚአብሔር ስለሚሠራው የመንግሥቱ ጉዳይ እንጂ፤ በነብያቱ ሕይወት ሊሠራው ስላሰበው ወይም እነርሱ እንዲሠርቱለት ስለነገራቸው ጉዳይ ስለገለጠላቸው አይደለም።
መጽሐፍ ቅዱስ እንግዲህ ራዕይ ሲል በሰው ልብ ስለተቀመጠ እቅድ ወይም ፕላን አይደለም የሚያወራው። ነገር ግን በመጨረሻው ዘመን እግዚአብሔር በመንግሥቱ ስለሚሠራው ሥራ ለነብያቱ የሚገለጠውን መገለጥ ነው የሚያወራው። ነብያቱም ባለራዕይ የሚባሉት እግዚአብሔር በእነርሱ ሊሠራው ያሰበውን እቅድ በልባቸው ስላስቀመጠ አይደለም። ዛሬ ዛሬ ምዕመናን የመሰብሰቢያ ሥፍራ ስለጠበባቸው ፓስተሩ አዲስ የመሰብሰቢያ ቤት ለማሰራት ካሰበ እንኳን ይህ እንደ ራዕይ ነው የሚታየው። ፓስተሩም እንደ ባለራዕይ ነው የሚቆጠረው። ይህ በዚህ ዘመን ባለን የራዕይ መረዳት ልክ ሊሆን ይችላል። ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ግን ፈጽሞ እንዲህ አይደለም።