ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » ጥያቄ መጠያየቂያ
Email this page to a friend   Wednesday, 25 November 2020
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ፥ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።“
(መዝሙረ ዳዊት 27:14)

rss

Today's verse

ቀኝህን ለሚመታህ ግራህን ስጥ የሚለውን ጥቅስ ብታብራሩልኝ?

ሰላም

በመጽሐፍ ቅዱስ ቀኝህን ለሚመታህ ግራህን ስጥ የሚል ጥቅስ አለ። እናም የሚያውቅ ሰው ይሄንን ጥቅስ ቢያብራራልኝ። ይሄስ ጥቅስ ራስን ከመከላከል ጋር እንዴት ሊሄድ ይችላል።
Feb 27, 2011 መንፈሳዊ ስም-አልባ የተጠየቀ
Feb 27, 2011 ታርሟል

1 መልስ

+1 ድምጽ
የጥያቄው መነሻ የሆነው ጥቅስ የሚገኘው በማቴዎስ 5፥39 ላይ ነው።
Quote:
የማቴዎስ ወንጌል 5
38 ዓይን ስለ ዓይን ጥርስም ስለ ጥርስ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።
39እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤
40 እንዲከስህም እጀ ጠባብህንም እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤
41 ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ።

ይህ ክፍል የተራራው ስብከት ተብሎ በሚጠራውና ከማቴዎስ 5፥1 የሚጀምረው ረዘም ያለ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ውስጥ የሚገኝ ክፍል ነው። ክፍሉም ክፋት ከሚያደርጉብን ሰዎች ጋር እንዴት መመላለስ እንዳለብን የሚያስተምር ነው። ሆኖም በወንጌል ስብከት ምክንያት ስለሚመጣ ስደት ሁሉ ግን በዚህ ክፍል አልተጻፈም። ለምሳሌ አንዱ ከተማ ስደት ሲነሳ ወደ ሌላኛው ስለመሸሽና(ማቴ 10፥23) ሌሎችንም በስደት ጊዜ ክርስቲያኖች ሊያደርጓቸው የሚችሉትን ነገር ሁሉ ወዘተ የሚያስተምር ክፍል አይደለም። ይልቁንም አንድ ክፉ ሰው በእኛ ላይ ስለሚያደርገው ክፋትና ይሄንንም ሁኔታ እንዴት ማስተናገድ እንዳለብን የሚያስተምር ክፍል ነው።

በቁጥር 38 ላይ በመጀመሪያ ጌታ ኢየሱስ በሙሴ ሕግ የተጻፈውን በማስታወስ በብሉይ ኪዳን ዓይን ስለ ዓይን ጥርስም ስለ ጥርስ በሚለው ሕግ ይመሩ እንደነበር አሳስቦ እርሱ ግን ከዚህ የበለጠና የተሻለ ነገር እንዳለ ሲያስተምር እንመለከታለን።
Quote:
ኦሪት ዘሌዋውያን
24፥20 ስብራት በስብራት ፋንታ፥ ዓይን በዓይን ፋንታ፥ ጥርስ በጥርስ ፋንታ፥ ሰውን እንደ ጐዳ እንዲሁ ይደረግበት።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገር የብሉይ ኪዳኑ ሕግ ጽድቅና ቅድስት ናት ይላል።
Quote:
ወደ ሮሜ ሰዎች
7፥12 ስለዚህ ሕጉ ቅዱስ ነው ትእዛዚቱም ቅድስትና ጻድቅት በጎም ናት።

ይሄ ጽድቅ የሚለው ቃል ትክክለኛ ወይም ፍትሐዊ የሆነ ማለት ነው። ጥርስ የሰበረ ሰው ጥርሱ ይሰበር፤ እንዲሁም የሰው ዓይን ያጠፋ ሰው አይኑ ይጥፋ የሚለው የብሉይ ኪዳን ትእዛዝ እንድግዲህ ፍትሐዊና ትክክለኛ ነው። እንዲህ አይነቱንም ፍርድ የብዙ ሰዎች ሕሊናም እንደ ፍትሕ ሊቀበለው የሚችለው ነው።

ኢየሱስ ግን ትክክለኛውንና ፍትሐዊውን ከማድረግ ያለፈ ነገር ነው ከላይ ባለው በማቴዎስ 5፥39 ላይ የሚናገረው። ይሄንን ጥቅስ የሚጀምረው "እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ክፉውን አትቃወሙ" በሚለው ማሳሰቢያ ነው። የኢየሱስ "ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት“ የሚለውና ለብዙ ሰዎች ፍትሐዊነቱን ለመቀበል የሚከብደን ትምህርት የተመሠረተውና ትኩረቱን ያደረገው በዚህ "ክፉውን አትቃወሙ" በሚለው መርሕ ላይ ነው። ይሄ "ክፉውን" የሚለውን ቃል አዲሱ መደበኛ ትርጉም "ክፉ አድራጊውን ሰው" በማለት ነው የሚተረጉመው። በተመሳሳይ ሁኔታም ብዙዎቹ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንደዚሁ "evil person“ በማለት ነው የሚተረጉሙት።

እንግዲህ ሃሳቡ ክፉው የሆነውን ሰው ወይም በክፋት የተያዘን ሰው ስለመቃውም ነው የሚያወራው። ክፋት እንደ መልካም ነገር ሁሉ የሚራባና ከሰው ወደ ሰው፤ ከሕዝብ ወደ ሕዝብ፤ ከአገር ወደ አገር የሚዛመድ ነገር ነው። አንድ በክፋትና በጥላቻ የተያዘ ሰው ሌሎችን ሰዎች ሲጠላና ሲጎዳ የተጎዱት ደግሞ እርሱን ሲጠሉና በእርሱ ላይ ክፋት ለማድረግ ሲሞክሩ ወዘተ እንዲህ እያለ ጥላቻና ክፋት እየተራባ ይሄዳል ማለት ነው። ክፋት እንዳይራባና እንዳይዛመድ ምናልባትም ክፉ አድራጊው የራሱን ክፋት እንዲያይና ወደ ሕሊናው እንዲመለስ ክፋትን የምናሸንፍበት መንገድ ባለመቃወም እንደሆነ ነው ኢየሱስ የሚያስተምረው። ይህ አንደኛ እኛም በክፋትና በጥላቻ እንዳንያዝና በሽታው ወደ እኛም እንዳይተላለፍ ያድርገናል፡ በሌላ በኩል ከእኛም አልፎ ለሌሎች እንዳይተላለፍና በአጭሩ እንዲቀጭ ይረዳል።

በዚህ ክፍል የጌታ ትምህርት የሚያተኩረው እንግዲህ ትክክል ወይም ፍትሐዊ ነገርን የማድረግ ወይም ያለማድረግ ላይ አይደለም። ነገር ግን ክፉውን በመልካም ማሸነፍ ወይስ ራስ በክፉት ተይዞ በክፉው መሸነፍ በሚለው ላይ ነው። ከጥፊው መምታት ጋር አብረው የተጠቀሱትም ማቴዎስ 5፥40-41 ያሉትም ጥቅሶች የሚያወሩት ስለ ክፉ ሰዎች ሥራ ነው። በቁጥር 40 ላይ ልብስ ስለ መውሰድ የሚያወራውም በፍርድ ቤት ከሶ በግድ ልብስን ስለመውሰድ ነው የሚናገረው። አዲስ መደበኛ ትርጉምና አብዛኞቹ የእንግሊዝኛ ትርጉሞችም ይሄንን ጥቅስ እንደሚከተለው ነው የሚተረጉሙት፦
Quote:
የማቴዎስ ወንጌል 5፥40

አዲሱ መደበኛ ትርጉም
አንድ ሰው እጀ ጠባብህን ሊወስድ ቢከስህ ካባህን ጨምረህ ስጠው።

NKJV
If anyone wants to sue you and take away your tunic, let him have your cloak also.

ቁጥር 41ም የሚያወራው በዚያን ዘመን የተለመደ የገዢዎቹ የሮማውያውን ወታደሮችን አሠራር ነው። ይሄም ማንንም ሰው አስቁመው የሚፈልጉትን እቃ አሸክመው የፈለጉበት ቦታ እንዲያደርስ ያስገደዱ ነበር። ለዚህም ነው በቁጥር 41 „አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ" የተባለው። ማለትም አንድ ክፉ የሮማ ወታደር እቃ አሸክሞ አንድ ምእራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ጨምረህ ሁለተኛውንም ምእራፍ ከእርሱ ጋር ሂድ ማለት ነው።

ስለዚህ ማቴዎስ 5፥38-41 ያለው ክፉውን በመልካም ስለማሸነፍ የሚያወራ ክፍል ነው። በሰው ዘንድ ትክክል ወይም ፍትሐዊ ላይሆን ይችላል፡ ነገር ግን ይህ ክፉው እንዳይራባና ራሳችንንም እንዳይወርሰን ክፉውን ማሸነፊያ መንገድ ነው።
Quote:
ወደ ሮሜ ሰዎች
12፥21 ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።
Feb 27, 2011 በምሕረቱ (1,510 ነጥቦች) የተመለሰ
“እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ።“
(መዝሙረ ዳዊት 33:12)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2020 by iyesus.com
Terms of use | Contact us
...