ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » ጥያቄ መጠያየቂያ
Email this page to a friend   Saturday, 8 May 2021
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ፥ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።“
(መዝሙረ ዳዊት 27:14)

rss

Today's verse

አንድ ሰው ከዳነ በኋላ ደህንነቱን ሊያጣ አይችልም ወይ?

አንድ ሰው ከዳነ በኋላ ደህንነቱን ሊያጣና ሊፈረድበት ይችላል? ወይስ አንድ ጊዜ በክርስቶስ አምኖ የዳነ ሰው በምንም ሁኔታ ደህንነቱን ሊያጣ አይችልም?
Feb 27, 2011 መንፈሳዊ ስም-አልባ የተጠየቀ
ጥቅስ የምታበዙበት ምክንያት ለምንድን ነው። ስለምትናገሩት ነገር እርግጠኛ ስላልሆናችሁ ነው እንዴ።
አይደለም ነገር ግን ሰዎች ከእኛ እርግጠኛ ቃል ይልቅ እምነታቸው በጌታ ቃል ላይ እንዲቆም ነው። የእግዚአብሔር ቃል እንጂ የእኛ ቃል በፈተና አይቆምምና። ሆኖም ስለ ገንቢ አስተያየቱ እናመሰግናለን። ወደፊት በተቻለ መጠን ጥቅሶችን ላለማብዛት እንሞክራለን።
ጥቅሱን ማብዛት ለመማር ይጠቅመናልና እባካችሁ ጨማምራችችሁ አስተምሩን:: ሊያነብ የማይፈልግኮ ግድ የለበትም!
ህውታችህን የተመሰረተው በእግዛበር ቃል ሲለሆነ ቢበዛሚ ችግሪ የለውም

4 መልሶች

+2 ድምጾች
አንድ ሰው ከዳነ በኋላ ደህንነቱን ሊያጣ እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምራል።
Quote:
የዮሐንስ ራእይ 3
1 በሰርዴስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስትና ሰባቱ ከዋክብት ያሉት እንዲህ ይላል። ሥራህን አውቃለሁ ሕያው እንደ መሆንህ ስም አለህ ሞተህማል። 2 ሥራህን በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትምና የነቃህ ሁን፥ ሊሞቱም ያላቸውን የቀሩትን ነገሮች አጽና። 3 እንግዲህ እንዴት እንደ ተቀበልህና እንደ ሰማህ አስብ፥ ጠብቀውም ንስሐም ግባ። እንግዲያስ ባትነቃ እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ በማናቸውም ሰዓት እንድመጣብህ ከቶ አታውቅም። 4 ነገር ግን ልብሳቸውን ያላረከሱ በሰርዴስ ጥቂት ሰዎች ከአንተ ጋር አሉ፥ የተገባቸውም ስለ ሆኑ ነጭ ልብስ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ። 5 ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጐናጸፋል፥ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም፥ በአባቴና በመላእክቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ። 6 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።

ከላይ የተቀመጠው ክፍል ጌታ ኢየሱስ ለሰርዴስ ቤተ ክርስቲያን የላከውን መልዕክት የያዘ ነው። በራእይ 1:11 እንደተገለጸው ይህ መልዕክት ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ራእይ በእስያ ለሚገኙት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ከላከው መልዕክት ውስጥ አንዱ ነው። መልዕክቱ እንግዲህ ለአብያተ ክርስቲያናት ማለትም በክርስቶስ አምነው ለዳኑና ክርስቶስም የእኔ ናቸው ለሚላቸው አማኖች የተላከ ነው።

በዚሁ ለአማኞች በተላከ መልዕክት ጌታ ሲናገር "ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጐናጸፋል፥ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም" ይላል። ይህ ክፍል ያለ ጥርጥር የሚያሳየን በሕይወት መጽሐፍ መጻፍ እንዳለ ሁሉ፡ ከሕይወት መጽሐፍ መደምሰስም እንዳለ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን የሕይወት መጽሐፍን የዳኑ ሰዎች የሚጻፉበት መጽሐፍ እንደሆነና በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፉ ደግሞ እንደሚጠፉ ይነገረናል። የዳኑ ሰዎች ብቻ የሚጻፉበት መጽሐፍ ስለሆነም "የበጉ ሕይወት መጽሐፍ"ም ተብሎ ይጠራል።
Quote:
የዮሐንስ ራእይ
20፥15 በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ።

21፥27 ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር፥ ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኵሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ እርስዋ ከቶ አይገባም።

ስለዚህ ከሕይወት መጽሐፍ መደምሰስ ማለት ደህንነትን ማጣትና ፍርድን መቀበል ማለት ነው።

ደህንነትን ከማጣት ጋር በተያያዘ የምንመለከተው ሌላው ክፍል የዮሐንስ ወንጌል 15ን ነው።
Quote:
የዮሐንስ ወንጌል15
1 እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው። 2 ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል። 3 እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፤ 4 በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም። 5 እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። 6 በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል

በዚህ ክፍል ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን እንደ እውነተኛ የወይን ግንድ ይመስላል። አብን ደግሞ እንደ የወይኑ ገበሬ። አማኞችን ደግሞ በወይኑ ግንድ ማለትም በክርስቶስ ላይ እንዳሉ ቅርንጫፎች። በዚህ ክፍል ጌታ ሊያስተላልፈው የሚፈልገው መልዕክት ያለ ክርስቶስ አማኞች ከግንዱ እንደ ተለየ ቅርንጫፍ ብቻቸውን ሕይወት ሊኖራቸው እንደማይችልና ያለ ክርስቶስ ሊያፈሩ እንደማይችሉ ነው።

በቁጥር ሁለት ላይ ጌታ "ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል“ ይላል። ልክ ቅርንጫፍ ከግንዱ ሊቆረጥ እንደሚችል እንዲሁ ከክርስቶስ መወገድ ወይም መቆረጥ እንዳለ በግልጽ ያሳየናል። መወገድ ብቻ ሳይሆን ከመወገድ ጋር ተያይዞ ደግሞ መድረቅና ተሰብስቦ ወደ እሳት መጣል እንዳለም በቁጥር 6 ያስጠነቅቃል። "በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል።" እዚህ ጋር ልብ ማለት ያለብን ከክርስቶስ ስለመወገድ፡ ወደ ውጭ ስለመጣል እንዲሁም በእሳት ስለመቃጠል ጌታ የሚያወራው በዓለም ስላሉ ዓለማውያን ሳይሆን በክርስቶስ ስላሉ ቅርንጫፎች ማለትም ስለ አማኞች ነው።

ሰው ወንጌልን ተቀብሎ ከዳነ በኋላ ደህንነቱን ሊያጣ እንደሚችል የሚያስጠነቅቀን ሌላው ክፍል የሚገኘው ደግሞ በዕብራውያን 10 ላይ ነው።
Quote:
ወደ ዕብራውያን 10
26 የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርልንምና፥ 27 የሚያስፈራ ግን የፍርድ መጠበቅ ተቃዋሚዎችንም ሊበላ ያለው የእሳት ብርታት አለ። 28 የሙሴን ሕግ የናቀ ሰው ሁለት ወይም ሦስት ቢመሰክሩበት ያለ ርኅራኄ ይሞታል፤ 29 የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኵስ ነገር የቆጠረ የጸጋውንም መንፈስ ያክፋፋ፥ እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል? 30 በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ያለውን እናውቃለንና፤ ደግሞም፦ ጌታ በሕዝቡ ይፈርዳል። 31 በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነው።

ይህ ክፍል ከዳኑ በኋላ ወደው ወይም ሆን ብለው ኃጥያትን ለሚለማመዱ ሰዎች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ ነው። ወንጌልን ተቀብለው ንስሐ ከገቡና በክርስቶስ መሥዋዕት ምህረትን ካገኙ በኋላ ወደው ኃጥያትን የሚለማመዱ ከእንግዲህ ወዲህ መሥዋዕት እንደማይቀርላቸውና ይልቁንም የሚያስፈራ ፍርድ እንደሚጠብቃቸው የሚያሳይ ክፍል ነው። እንደነዚህ አይነት ሰዎች ስለሚጠብቃቸው ፍርድም ሲናገር "ተቃዋሚዎችንም ሊበላ ያለው የእሳት ብርታት“ ይላል። አዲሱ መደበኛ ትርጉም ይህን ክፍል "የሚቀረው ግን የሚያስፈራ ፍርድና የእግዚአብሔርን ጠላቶች የሚበላ ብርቱ እሳት መጠበቅ ብቻ ነው።“ ይለዋል።
Quote:
ወደ ዕብራውያን 10 (አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
26 የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ሆን ብለን በኅጢአት ጸንተን ብንመላለስ፤ ከእንግዲህ ለኅጢአት የሚሆን ሌላ መሥዋእት አይኖርም። 27 የሚቀረው ግን የሚያስፈራ ፍርድና የእግዚአብሔርን ጠላቶች የሚበላ ብርቱ እሳት መጠበቅ ብቻ ነው

ይህ ማለት እንግዲህ እነዚህን ሰዎች የሚጠብቀው ፍርድ እኛ ብዙ ጊዜ እንደምናስበው ለአማኞች ብቻ የሆነ ለስለስ ያለ ፍርድ ሳይሆን፡ ልክ የእግዚአብሔር ጠላቶች/ተቃዋሚዎች ወይም ያልዳኑ ሰዎች የሚያገኙትን እኩል ፍርድ እንደሆነ ነው። ይህም ደህንነታቸውን እንደሚያጡ በግልጽ ያሳየናል።

ይቀጥላል ...
Feb 27, 2011 iyesus (7,430 ነጥቦች) የተመለሰ
Feb 27, 2011 iyesus ታርሟል
+2 ድምጾች
... ካለፈው የቀጠለ

እዚህ ጋር ግን ልብ ማለት ያለብን መጽሐፍ ቅዱስ፤ አማኞች ኃጥያት ቢያደርጉ ንስሐ መግባትና መመለስ እንደሚችሉ ያስተምረናል።
Quote:
1ኛ የዮሐንስ መልእክት 1
8 ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። 9 በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። 10 ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።

ሆኖም ኃጥያትን ወደን መለማመድ ወይም በኃጥያት ጸንቶ መኖር ግን ደህንነትን እንደሚያሳጣና ፍርድ እንደሚያስከትል መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምረናል።
Quote:
ወደ ሮሜ ሰዎች 6
1 እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ በኃጢአት ጸንተን እንኑርን? አይደለም። 2 ለኃጢአት የሞትን እኛ ወደ ፊት እንዴት አድርገን በእርሱ እንኖራለን?

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6
1 ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ጋር ሙግት ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፋንታ በዓመፀኞች ፊት ሊፋረድ ይደፍራልን? 2 ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? በዓለምስ ላይ ብትፈርዱ ከሁሉ ይልቅ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርዱ አትበቁምን? 3 የትዳር ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኳ እንድንፈርድ አታውቁምን? 4 እንግዲህ ስለ ትዳር ጉዳይ የፍርድ ቤት ቢያስፈልጋችሁ በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጆች አድርጋችሁ ታስቀምጣላችሁን? 5 አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ። እንደዚህ ነውን? በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን? 6 ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ይከሳል፥ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋልን? 7 እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጉድለት ነው። ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን? 8 ነገር ግን እናንተ ትበድላላችሁ ታታልሉማላችሁ፥ ያውም ወንድሞቻችሁን። 9 ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ 10 ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።

ከላይ በተቀመጠው በ1ቆሮ 6 ላይም ጳውሎስ የቆሮንቶስን ሰዎች "አትሳቱ" እያለ ሲያስጠነቅቅ እንመለከታለን። ለማስጠንቀቂያው መነሻ የሆነው በመካከላቸው የነበረው የርስ በርስ በደልና ሙግት ነው። አንደኛ አማኞች ሆነው የእግዚአብሔር መንፈስ በሌለባቸው በዓለማውያን ፊት ይካሰሱ ነበር። በተጨማሪም እርስ በርስም ይበዳደሉና ያታልሉም ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ ግልጽ የሆነ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው እናያለን። ዓመጸኞች፡ ሴሰኞች ሌቦች ወዘተ የእግዚአብሔርን መንግስት አይወርሱም! እና እናንተም ወደ ድሮ ኑሮአችሁ ከተመለሳችሁና እንዲሁ ከሆናችሁ የእግዚአብሔርን መንግስት ልትወርሱ አትችሉም የሚል ማስጠንቀቂያ ነው። "አትሳቱ" ወይም ራሳችሁን አታታሉ ወይም አይምሰላችሁ በማለት ነው ጳውሎስ በኃጥያት ጸንተው እየኖሩ የእግዚአብሔርን መንግስት መውረስ አለ ብለው እንዳይታለሉ የሚያስጠነቅቀው።

አሁንም እዚህ ጋር አንዴ በስህተት ስለ ሴሰኑና ንስሐ ስለገቡበት ጉዳይ ወይም አንዴ ስለ ሰከሩና ተጸጽተው ንስሐ ስለገቡበት ጉዳይ አይደለም የሚያወራው። ነገር ግን ስለሆኑ ስዎች ነው። ማለትም አንዴ በስህተት ስለመስከር ሳይሆን ሰካራም ስለሆኑ ሰዎች ነው የሚያወራው። አንዴ በስህተት ስለ አመነዘሩና ስለተመለሱ ሰዎች ሳይሆን አመንዝሮች ስለሆኑ ሰዎች ነው የሚያወራው። ማለትም ኃጥያትን ጸንተው የሚለማመዱ ስዎች ካመኑም በኋላ ቢሆን የእግዚአብሔርን መንግስት እንወርሳለን ብለው ራሳቸውን እንዳያስቱ ነው የሚያስጠነቅቀው።

በገላትያ መልዕክቱም ላይ ጳውሎስ እንደዚሁ የሥጋ ሥራዎች ምን እንደሆኑ ከገለጸ በኋላ እነዚህን እያደረጉ የእግዚአብሔርን መንግስት እወርሳለሁ ብለው እራሳቸውን እንዳያታልሉ በተመሳሳይ ሁኔታ ሲያስጠነቅቅ እንመለከተለን። እግዚአብሔር አይዘበትበትምና ማለትም እግዚአብሔርን ማታለለ (መሸወድ) ወይም ማሞኘት አይቻልምና።
Quote:
ወደ ገላትያ ሰዎች 5
17 ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም። 18 በመንፈስ ብትመሩ ግን ከሕግ በታች አይደላችሁም። 19 የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ 20 መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ 21 መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም

ወደ ገላትያ ሰዎች 6
7 አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ 8 በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል።

እዚህ ላይ መርሳት የሌለብን ነገር፡ የገላትያም ይሁን የቆሮንቶስ መልዕክት ከነማስጠንቀቂያው የተጻፈው ለዓለማውያን ሳይሆን ለዳኑ ለአማኞች መሆኑን ነው።

የሚከተለቱም ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ደህንነትን ማጣት እንደሚቻልና ይህም መጨረሻው ወደ ፍርድ እንደሚያደርስ በግልጽ የሚያሳዩና የሚያስጠነቅቁ ናቸው።
Quote:
ወደ ዕብራውያን 6
4 አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን 5 መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል የቀመሱትን 6 በኋላም የካዱትን እንደገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ የማይቻል ነው፤ ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና ያዋርዱትማልና። 7 ብዙ ጊዜ በእርስዋ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የምትጠጣ መሬት፥ ለሚያርሱአትም ደግሞ የምትጠቅምን አትክልት የምታበቅል፥ ከእግዚአብሔር በረከትን ታገኛለችና፤ 8 እሾህና ኵርንችትን ግን ብታወጣ፥ የተጣለች ናት ለመረገምም ትቀርባለች፥ መጨረሻዋም መቃጠል ነው።

2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2
20 በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል። 21 አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና። 22 ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፥ ደግሞ። የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል።

እንግዲህ ከላይ ከተቀመጡትም በላይ ሌሎችንም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አማኝ ደህንነቱን ሊያጣ እንደሚችል የሚያስተምሩ ጥቅሶችን መጥቀስ ይቻላል። ሆኖም ከላይ የተቀመጡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በቀጥታና በማያሻማ ሁኔታ ደህንነት በነጻ የሚገኝ ይሁን እንጂ ርካሽ ግን እንዳልሆነና "አንዴ ድኛለሁና እንደፈለግሁት በኃጢአት ብኖር ደህንነቴን አላጣውም" ብለን ራሳችንን እንዳናስትና ከማያምኑ ጋር ለፍርድ እንዳንቀርብ የሚያሳስቡና የሚያስጠነቅቁ ጥቅሶች ስለሆኑ ጥያቄውን ይመልሳሉ ብለን እናምናለን።
Feb 27, 2011 iyesus (7,430 ነጥቦች) የተመለሰ
+1 ድምጽ
የዚያን ጊዜም። ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ። Mat 7-23
Is the key verse I want to use to show that salvation is not so cheap that is lost on whim... If you read Mat 7የማቴዎስ ወንጌል 7
17 እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፥ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል።
18 መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፥ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም።
19 መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል።
20 ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።
21 በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።
22 በዚያ ቀን ብዙዎች። ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል።
23 የዚያን ጊዜም። ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።
24 ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል።
25 ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም።
26 ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል።
27 ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት መታው፥ ወደቀም፥ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ።

The person who did all the Christain deeds like we see in the example has never been a CHristain..or in other words was never saved...ከጌታ ጋር ያለው ግንኙነት must have been superficial ... It was not real... .. many refer to this verse as አላውቃችሁም..The English version is clear what Jesus said.. "‘I never knew you. Away from me, you evildoers!’ So these people were never saved to start with..ፍስሐ
Mar 2, 2011 ስም-አልባ የተመለሰ
ስለ ዮሐንስ ወንጌል 6፥37 ጥያቄ
አንድ ሰው ከዳነ በኋላ ደህንነቱን እንደማያጣ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል።
ከላይ ለተገለጸው ሃሳብ ትክክል አይመስለኝም፡ ድነት ዘላለማዊ እንጂ ግዜአዊ አይደለም ከዚህ ቀጥሎ ያለው ሓሳብ ያብራራልናል።

መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ነው፣ እሱም፣ ደኅንነት በጸጋ ብቻ፣ በእምነት በኩል ብቻ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው (ዮሐንስ 3፡16፤ ኤፌሶን 2፡8-9፤ ዮሐንስ 14፡6)። አንድ ሰው በእውነት በኢየሱስ ክርስቶስ ባመነበት ቅጽበት፣ እሱ ወይም እሷ ድነዋል፤ እናም በዛ ደኅንነት ተጠብቀዋል። ደኅንነት በእምነት ይገኛል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይሄንን ጉዳይ በተመለከተ በገላትያ 3፡3 እንዲህ በማለት ይጠይቃል፣ “እንዲህን የማታስተውሉ ናችሁ? በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋ ትፈጽማላችሁን?” በእምነት ከዳንን፣ ደኅንነታችን የሚጠበቀውም ሆነ የሚረጋገጠው በአምነት ነው። የራሳችንን ደኅንነት በመልካም ስራችን ልንጠብቀውም
አንችልም። ስለሆነም፣ በራሳችን የደኅንነታችንን ማረጋገጫ ልናገኝም አንችልም። ደኅንነታችንን የሚያረጋግጥ እግዚአብሔር ነው (ይሁዳ 24)። በራሱ ሃይል አጽንቶ የሚጤብቀኝ የእግዚአብሔር ራሱ ነው (ዮሐንስ 10፡28-29)። የእግዚአብሔር ፍቅር ነው፣ ምንም ነገር ከእሱ እንዳይለየን ያደረገው (ሮሜ 8፡38-39)

ማንኛውም ዓይነት የዘላለም ደኅንነት ክህደት፣ በመሠረተ ሐሳቡ፣ የራሳችንን ደኅንነት በራሳችን መልካም ሥራና ጥረት ማግኘት አለብን ከሚል እምነት የነጨ ነው። ይህም ባጠቃላይ ደኅንነት በጸጋ የሚለውን የሚጻረር ነው። የዳንነው በክርስቶስ ሥራ ምክንያት ነው፣ በራሳችን አይደለም (ሮሜ 4፡3-8)። በርግጥ ነው የእግዚአብሔርን ቃል መታዘዝ አለብን፣ ወይም መልካም ሕይወትን መኖር አለብን፣ ነገርግን የራሳችንን ደኅንነት ለማግኘት ወይም ድነታችንን ለመጠበቅ በመልካም ስራችን ነው የሚል ክርክር ማቅረብ፣ የኢየሱስ ሞት የኃጢአታችንን ዋጋ ለመክፈል አይበቃም ማለት ነው። የኢየሱስ ሞት የኃጢአታችንን ዋጋ ለመክፈል ፈጽሞ በቂ ነው— ያለፈውን፣ የአሁኑን፣ እና የወደፊቱን፣ሃጥያታችንን ሁሉ ነው በመስቀል ላይ ባፈስ ስው ደሙ ያስወገደው ይህም ቅድመ-ደኅንነት እና ከደኅንነት በኋላ ያለውን ያጠቃልላል(ቆላስያስ 1፡14 ፣ 2፡13 ሮሜ 5፡8፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡3፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡21)

ይሄንን ማለት ክርስቲያን እንደፈለገው ቢኖርም አሁንም ድኗል ማለት ነውን? ይህ በመሠረቱ መላምታዊ ጥያቄ ነው፣ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ እንዳደረገው እውነተኛ ክርስቲያን “እሱን እንዳፈቀደው” መኖር ስለማይችል ነው። ክርስቲያኖች አዲስ ፍጥረት ናቸው (2ኛ ቆሮንቶስ 5፡17)። ድነት የሃጥያት ሥርየትን ማግኝት ብቻ አይደለም አዲስ ሕይወትን መቀበልን በአዲስ ሕይወት ለመኖርን ነው፡ ክርስቲያኖች የመንፈስ ፍሬ ያፈራሉ (ገላትያ 5፡22-23)፣ የሥጋ ድርጊት ያልሆኑትን (ገላትያ 5፡19-21)። አንደኛ ዮሐንስ 3፡6-9 በግልጽ እንደሚያስቀምጠው እውነተኛ ክርስቲያን ቀጣይነት ባለው ኃጢአት አኖርም። ጸጋ ኃጢአትን ያበዛል የሚለውን ክስ በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ገልጿል፣ “እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ በኃጢአት ጸንተን እንኑርን? አይደለም። ለኃጢአት የሞትን እኛ ወደ ፊት እንዴት አድርገን በእርሱ እንኖራለን?(ሮሜ 6፡1-2)

የዘላለም ሕይወት ወይም ደኅንነት መቀበል ኃጢአትን ለመፈጸም ፍቃድ አይደለም። ይልቁን፣ የእግዚአብሔር ፍቅር እሱም በክርስቶስ ለሚያምኑት የሆነውን ማስረገጫና የደኅንነት እውቀት ነው። የእግዚአብሔርን ታላቅ የሆነ የደኅንነት ስጦታ ማወቅና መረዳት መቻል ለኃጢአት ፍቃድ መስጠት ከሚለው በተጻራሪው ነው። ማንም ቢሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ የከፈለውን ዋጋ አውቆ እንዴት አድርጎ፣ በኃጢአት ሕይወት ሊቀጥል ይችላል (ሮሜ 6፡15-23)? ማንም ቢሆን የእግዚአብሔርን ያልተጠበቀና የተረጋገጠ ፍቅር እሱም ለሚያምኑት የሆነውን፣ ከተረዳ በኋላ፣ ያንን ፍቅር መልሶ በእግዚአብሔር ፊት ይወረውራል? እንዲህ ዓይነቱ ሰው የሚያሳየው የዘላለም ደኅንነት የኃጢአት ፍቃድ እንደሰጠው አይደለም፣ ነገር ግን ይልቁን እሱ ወይም እሷ በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ደኅንነት በትክክል እንዳልተረዱት ነው። “በእርሱ የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፤ ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ አላየውም አላወቀውምም” (1ኛ ዮሐንስ 3፡6)

ለማጠቃለል ፡ ድነት የዘላለም ነው አይጠፋም፡ በእኛ መልካም ስራ የጀመረው ጌታችን ይፈስመዋል ከእርሱ እጅ የሚነጥቀን ምንም ሃይል የለምና ( ፊልጵስዪስ 1፡6፣ ዮሓንስ 10፡27-29)
በትክክል ተገልጽዋል ደህንነት የሚጠፋ ከሆነ ደህንነት በሥራ እንጂ በፀጋ ወይም በዕምነት እንዳልሆነ ነው የሚያሳየን። የዳነ ስው ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየኛል። የሚለውን መርህ በደንብ የሚተገብር እንጂ ለአልባሌ ነገር ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ አይደለም!!! ባጭሩ የዳነ(የዘላለም ህይወት ያገኘ) ሰው ለኃጢዓት የሞተ ነው።ለፅድቅና ለቅድስና የሚኖር ማለት ነው። እንደ አስቆርቱ ይሁዳ አይነት ሰው አይደለም!!!!!!
ይሄ እኮ ነው እኔ አንድ ጎን ይዞ መሮጥ የምለው። እስከ አሁን ድረስ እንዳየሁት መጽሃፍ ቅዱስን በተመለከተ ሰው የሚሳሳተው አንዱን ጎን ብቻ ይዞ ስለሚሄድ ነው። ወደ አንድ ጎን የማጋደል ኃይለኛ ችግር አለብን፤ እኛ ሰዎች ስንባል። ለምን እንደሆነ አላውቅም። አንዱን ማጉላት ሌላውን መሸፋፈንና ማፈን እንወዳለን። ሁለቱንም ጎን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማየትና ይዞ መሄድ የሚባል ነገር ፈጽሞ ይከብደናል።

በጸጋ መዳን የሚለውን ብቻ አንዱን ጎን ወስደን፤ መጽሃፍ ቅዱስ አማኞችን የሚያስጠነቅቀውን ሌላውን ማስጠንቀቂያ ሁሉ ወደ ጎን በመተው ወይም በመሸፈን የሚመጣ እውነት የለም። ግማሽ እውነት ሙሉ እውነት ሆኖ አያውቅም።

ድነት ልክ ነው በጸጋ የሚገኝ ነው፤ በሥራ ሳይሆን። ሆኖም እውነተኛ እምነት ከሆነ ያለን፤ እውነተኛ ፍሬ እናፈራለን። እውነተኛ ፍሬ የማያፈራ ከሆነና ይባሱንም ደግሞ ክፉ ፍሬ የሚያፈራ ከሆነ፤ ቀድሞውንም ድነቱ ትክክለኛ አልነበረም። ይሄንን ነው መጽሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረን።

እንዴ፤ የምንነጋገረው እኮ ስለ ርካሽ ጸጋ አይደለም፤ ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር ጸጋ ነው። የእግዚአብሔር ጸጋ ደግሞ ምን አይነት ነው? በእግዚአብሔርስ ጸጋ በእውነት ድነን ከሆነ፤ ጸጋውስ ምን አይነት ጸጋ ነው? መጽሃፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦

"ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤" ቲቶ 2፥12-13

በእውነተኛው በእግዚአብሔር ድነንስ ከሆነ፤ ያ ጸጋ የሚያስተምረን ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት እንድንክድና ራሳችንን እንድንገዛ ነው እንጂ፤ አይ ምንም ችግር የለውም ኃጢአትን ብንሠራም መዳን ይቻላል እያለ አይደለም። ከሁሉ በፊት በጸጋ መዳን ማለት ምን ማለት እንደሆነና፤ የእግዚአብሔር ጸጋ ምን ባህርያት እንዳሉት ከቃሉ ልንማር ይገባል። ምን አይነት ጸጋ እንደተቀበልንም ራሳችንን እንጠይቅ!

ኢየሱስ ራሱ ደግሞ በራእይ መጽሃፍ ከህይወት መጽሃፍ መደምሰስም እንዳለ አስጠንቅቆናል።

"ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጐናጸፋል፥ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም" ራእይ 3፡5። ከህይወት መጽሃፍ መደምሰስ ካለ እንግዲህ ድነትን ማጣት አለ ማለት ነው።

በሌላ ቦታ ደግሞ መጽሃፍ ቅዱስ፤ ፍሬ የማያፈራው በኢየሱስ ያለውን ቅርንጫፍ እንደሚቆረጥና እንደሚቃጠል ያስጠነቅቀናል። ልብ እንበል እዚህ ላይ የሚናገረው በኢየሱስ ስላሉ ቅርንጫፎች ነው፤ ማለትም ስለ ዳኑ ሰዎች ነው።

"እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ" ዮሐ 15:5
"ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል።" ዮሐ 15:2

"በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል።" ዮሐ 15:6

"የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ሆን ብለን በኅጢአት ጸንተን ብንመላለስ፤ ከእንግዲህ ለኅጢአት የሚሆን ሌላ መሥዋእት አይኖርም። የሚቀረው ግን የሚያስፈራ ፍርድና የእግዚአብሔርን ጠላቶች የሚበላ ብርቱ እሳት መጠበቅ ብቻ ነው።" ዕብ 10፡26-27 (አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

ስለዚህ ጉዳይ መጽሃፍ ቅዱስ ሲናገር "አትሳቱ" እያለ እያስጠነቀቀ ነው። አትሞኙ፤ ራሳችሁን አታታልሉ። እግዚአብሔር አይዘበትበትም ወይም እግዚአብሔርን ማታለል አይቻልም። ገላ 6፡7 እንዲሁም 1ቆሮ 6፡9

እና እነዚህንና ሌሎችንም ለአማኞች የተሰጡ ማስጠንቀቂያዎች ሁሉ እናዳፍናቸው? እንደሌሉ እንቁጠራቸው? እንሸፋፍናቸው?

ወገኖቼ ድነት ርካሽ ነገር አይደለም። በነጻ ያገኘነው እኮ በምንም ዋጋ ሊከፈል የማይችል እጅግ ታላቅ ነገር ስለሆነ ነው እንጂ በነጻ ስለሆነ ርካሽ ነው ብለን የምናስብ ከሆነ ተሳስተናል። አንዴ ድኛለሁና እንደፈለግሁ በኃጢአት እየተመላለስኩ ብኖር ችግር የለውም የምንል ከሆነ እጅግ ተሳስተናል። በእርግጥም ከመጀመሪያውኑም እንዳልዳንን ነው የሚያሳየው። ምክንያቱም እኛ በጸጋ ድነን ለኃጢአት የሞትን እንዴት በኃጢአት ጸንተን እንኖራለን?

"እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ በኃጢአት ጸንተን እንኑርን? አይደለም። ለኃጢአት የሞትን እኛ ወደ ፊት እንዴት አድርገን በእርሱ እንኖራለን?" ሮሜ 6፡1-2

ስለዚህ በኃጢአት ላይ ድል ስለማይሰጥ ርካሽ ጸጋ አይደለም መጽሃፍ ቅዱስ የሚያወራው። ነገር ግን፤ ኃጢአትን ድል እንድናደርገው የሚረዳ ጸጋ ነው። እንዲህ ያለ ጸጋ ካልሆነ የተቀበልነው፤ እንግዲያውስ ቀድሞውኑም ጸጋው የእግዚአብሔር ጸጋ አይደለም።
ስላም ወንድማችን ጸጋው ይብዛልህ

ከጌታችን በእምነት የተቀበልነው ድነት የዘላለም ነው አይጠፋም ብሎ ማመን አንድ ጎን ይዞ መሮጥ አይደለም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የስጠን ሕይወት የዘላለም ሕይወት ነውና።
ሃጢያት መሥራትን ፀጋው አያስተምረንም ይልቁንም ፀጋው ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል እንጂ፡

ከላይ ለተሰነዘረው ሃሳብ መልስ ካስፈለገ፤

1ኛ/ "ኢየሱስ ራሱ ደግሞ በራእይ መጽሃፍ ከህይወት መጽሃፍ መደምሰስም እንዳለ አስጠንቅቆናል።"

ጌታችን ያለው " ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም፥ በአባቴና በመላእክቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ። " ራእይ 3፡5 በማለት የበለጠ ማረጋገጫ ሰጠን እንጂ ።

ስለዚህ በትክክል ይነበብ አልደመስስም ነው የሚለው


2ኛ/ "ፍሬ የማያፈራው በኢየሱስ ያለውን ቅርንጫፍ እንደሚቆረጥና እንደሚቃጠል ያስጠነቅቀናል። ልብ እንበል እዚህ ላይ የሚናገረው በኢየሱስ ስላሉ ቅርንጫፎች ነው፤ ማለትም ስለ ዳኑ ሰዎች ነው።"

ስለ አልዳኑ ሰዎች ነው "ይቆረጣሉ ይቃጠላሉ " የሚለው እንጂ ስለ ዳኑ አይደለም፡ የሚቆረጡት ስላላፈሩ ነው፤ ሊያፈሩ የቻሉት ደግሞ በፀጋው ላይ ስላልተደገፉ ነው። በስራው ላይ የሚደገፍ ሁሉ ማለትም ለመዳንም ሆነ ድነቱን ለመጠበቅ በመልካም ስራው ላይ የሚታመን ውጤቱ መጥፋት ብቻ ነው። እምነታችንን በሥራችን ማድረጋችንን ትተን በጌታችን ላይ ስናደርግ መልካም ፍሬ ማፍራት እንችላለን፤ እንዳንቆረጥ በእምነት ከወይኑ ግንድ ጋር እንጣበቅ ። በመጀመሪያ ዛፉን መልካም አድርጉ ፍሬውም መልካም ይሆናል (ማቴ 12፡33) "ዛፍ ከፍሬዋ ትታወቃለችና ዛፍዋን መልካም፥ ፍሬዋንም መልካም አድርጉ፥ ወይም ዛፍዋን ክፉ ፍሬዋንም ክፉ አድርጉ።"

ሃይማነተኞች ዋናው ስራችው በፀጋው ከመደገፍ ይልቅ በስራቸው ላይ ይደገፋሉ ውጤቱም ያለ ፍሬ ይቀራሉ መጨረሻቸውም ጥፋት ነው። የእግዚአብሔር ቃል የሚለው ግን በሮሜ 1፡17 " ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና። ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና። " ስለዚህ ፃድቅ የሆንነውም ሆነ ፍሬ በማፍራት መኖር የምንችለው በእምነት ብቻ ነው።
መልካም ስራ እድንሰራ ነው የዳንነው ነገር ግን መልካም ስራ የምንሰራው ስለ ዳንን ነው እንጂ ለመዳን ወይንም ድነታችንን ልናጣ እንችላለን በማለት ከፍርሃት የተነሳ አይደለም ይልቁንም ያዳነንን ጌታ ስለ ምንወደው እና በእኛ ውጽጥ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ችሎታችን ብቃታችን ሰለ ሆነ እንጂ።ክርስትና ሕይወት በጌታ የተሰጠን የእረፍትና የልብ እርግጠኝነት ጉዞ ነው።
ሰዎች ክርስቶስን እንደ አዳኛቸው ወደ ማወቅ ሲመጡ የዘላለማዊ ዋስትናቸውን እና አስተማማኛ ወደሚያደርግ ከእግዚአብሔር ጋር ወደሆነ ህብረት መጥቷዋል፡፡ የይሁዳ መልዕክት 24 “ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ፥ በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው” እያለ ያውጃል፡፡ የእግዚአብሔር ኃይል አማኞችን ከውድቀት ሊጠብቃቸው ይችላል፡፡ እኛን በክብሩ ፊት ማቆም የእሱ እንጂ የእኛ ፈንታ አይደለም፡፡ የእኛ ዘላለማዊ ዋስትና እግዚአብሔር እኛን የመጠበቁ ውጤት እንጂ እኛ የራሳችንን ድነት የማቆየቱ ጉዳይ አይደለም፡፡

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም።” (የዮሐንስ ወንጌል 10፤28-29) አብም ኢየሱስም ሁለቱም በእጃቸው ውስጥ አጥብቀው ይዘውናል፡፡ ከአብ እና ከልጁም ከሁለቱም እጅ ውስጥ ሊለየን የሚችል ማነው?

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፤30 አማኞች “ለቤዛ ቀን እንደታተሙ” ይነግረናል፡፡ አማኞች የተቀበሉት ይህ ማህተም ዘላለማዊ ዋስትና ካልሆነ በእውነት ማህተሙ ለቤዛ ቀን ሊሆን አይችልም ነገር ግን ኃጥአት ለሚደረግበት ቀን ብቻ ይሆናል፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያምን ማንም ሰው “የዘላለም ህይወት እንዳለው” የዮሐንስ ወንጌል 3፤15-16 ይነግረናል፡፡ አንድ ስው ዘላለማዊ ህይወት ተስፋ የተገባው ከሆነ ነገር ግን ደግሞ ቢወሰድበት ለመጀመር ያህል ፈጽሞ “ዘላለማዊ” አልነበረም፡፡ መንፈሳዊ ዋስትና እውነት ካልሆነ በመጽሐፍ ቅዱ ውስጥ ያሉ የዘላለም ህይወት ተስፋዎች ስህተት ይሆናሉ፡፡

ለዘላለማዊ ዋስትና የተመስረተው በ እግዚአብሔር ፍቅር ላይ ነው ሮሜ 8፤38-39 ነው፤ “ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።” የእኛ ዘላለማዊ ዋስትና እርሱ ለተበዣቸው መሠረት ያደረገው በእግዚአብሔር ፍቅር ላይ ነው፡፡ የእኛ ዘላለማዊ ዋስትና በክርስቶስ ቤዛነት፤ በአብ ተስፋ ተገብቷል፤ እና በመንፈስ ቅዱስ ታትሟል፡፡
የሚያምን ሁሉ ይህ ዘላለማዊ ተስፋ አለው
ሰላም ወንድሜ

ጸጋን ከሃማኖተኝነት ጋር አነጻጽረህ ጸጋን መምረጥህ እጅግ አድርጌ የምደግፈው ነገር ነው። አንተ እንዳልከው ጸጋን በሃይማኖት ለመተካት የሚፈልጉ በጣም ብዙ እጅግ ብዙ ናቸው። በዚህ በኩል መቶ በመቶ ከአንተ ጋር ነኝ።

የእኔ ችግር ያለው እዚያ ላይ አይደለም። ችግሬ ያለው ሰው አንዴ ከዳነ በኋላ የፈለገውን ያህል የኃጢአት ኑሮ ቢኖር ችግር የለውም ድነቱ አይጠፋም የሚለው ፈጽሞ መጽሃፍ ቅዱሳዊ ያልሆነና ሰዎችን ከጸጋው እንዲወድቁ የሚያደርገው ትምህርት ላይ ነው። ወደ ሃጢያት የሚመራና የሚጋብዝ ጸጋ እግዚአብሔር አልሰጠንምና፤ እንዲህ ሰዎች በሃጢአት እንዲጠመዱና ከጸጋው እንዲወድቁ የሚያደርጉ ትምህርቶችን ነው አጥብቄ የምቃወመው፤ ምክንያቱም በከንቱ ተስፋ በኃጢአት እንዲታለሉ የሚገፋፋና የሚያበረታታ ትምህርት ስለሆነ ማለት ነው።

ጸጋው ሃጢያተኝነትን ክደን እግዚአብሔርን በመምሰል እንድንኖር የሚያስችል ሃይል ነው እንጂ በኃጢአት እንድንጨማለቅ የሚገፋፋና የሚጋብዝ ሃሰተኛ መንፈስ አይደለም። ከጸጋ በታች ሆንን ወይም ጸጋው በዛልን ማለት፤ ኃጢአት አይገዛንም፣ ኃጢአትን ድል እንድናደርግ ያስችለናል ማለት ነው እንጂ በኃጢአት ጸንቶ መኖር ማለት አይደለም የጸጋ መብዛት ምልክት፤ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፦
Quote:
ወደ ሮሜ ሰዎች
6፥14 ኃጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና።
6፥15 እንግዲህ ምን ይሁን? ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላይደለን ኃጢአትን እንሥራን? አይደለም።

ከአንተ አባባል ግን አንድ ነገር ብቻ ላርምህ እወዳለሁ። ይሄውም ኢየሱስ በዮሐንስ 15 ላይ "ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል" ወይም "በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል" ሲል የሚያወራው ስለ አልዳኑ ሰዎች ነው ይህ ክፍል የሚያወራው ብለህ ያልከው ነገር ፈጽሞ ቅንነት የሌለው አባባል ነው። እስቲ ራስህ ዓውዱን ዮሐንስ ምዕራፍ 15፡1-6 ያለውን በሙሉ አንብበውና ህሊናህ ሳይፈርድብህ በእውነት ይህ የሚናገረው ስለ አልዳኑ ሰዎች ነው ማለት ትችል እንደሆን እይ?

ክፍሉ ራሱ ስለ ወይኑ ግንድ፣ ስለ ቅርንጫፎቹና ስለ ገበሬው ምንነት በግልጽ ጽፎልናል። የወይን ግንዱ ኢየሱስ፤ ገበሬው እግዚአብሔር፣ ደቀመዛሙርቱ ደግሞ ቅርንጫፎች እንደሆኑ ራሱ ክፍሉ ይናገራል። ታዲያ ፍሬ የማያፈራ ቅርንጫፍ ገበሬው እንደሚያሳወግደውና ከወይኑ ግንድ ጋር ደግሞ ያልሆነ ቅርንጫፍ እንደሚደርቅና ተሰብስቦ እንደሚቃጠል ነው የሚናገረው። ቅርንጫፍ ነው የሚቃጠለው የሚለው፤ ቅርንጫፍ ደግሞ ደቀመዛሙርቱን እንደሚያመለክት ራሱ ክፍሉ ገልጿል። መጽሃፍ ቅዱስን በአንድ ጎን ብቻ ለመተርጎም መፈለግ በቅንነት ቃሉን ሁሉ እንዳናይ ይጋርድብናል። ሁሉንም የሚስማማንንም የማይስማንንም መዋጥ ነው መፍትሄው። እንደሚመር መድኃኒት መፍትሄ የሚሆነው እንዲህ ሲሆን ብቻ ነው እንጂ የሚጣፍጠንን ብቻ ስንወስድ ወይም ቃሉን ስናጣምም አይደለም። እስቲ ራስህ አንብበው፤ በቅን ህሊና ራስህ ፍረድ፦
Quote:
የዮሐንስ ወንጌል 15
1 እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው
2 ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል።
3 እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፤
4 በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ፦ ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም።
5 እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል።
6 በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል
ሰላም ወንድሜ ( ከላይ ሃሳብ ያቀረክብልኝ )

በመጀመሪያ ይህንን የመወያያ መድረክ ላዘጋጁልን ወገኖቼ ከልብ የሆነ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
ከዚህ እንደሚከተለው እኔ የተረዳሁትን አቀርባለሁ በየዮሐንስ ወንጌል 15፡1-6 ያለውን ቃል

"እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው። ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል። እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፤ በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ፦ ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም። እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል።
በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል።"

ከአንተ አባባል "ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል" ወይም "በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል" ሲል የሚያወራው ስለ ዳኑ ሰዎች ነው ብለህ ያልከውን እኔ አልተቀበልኩትም ምክንያቱም ፍሬ ማፍራት ያልቻሉት በክርስቶስ ውስጥ ስላልሆኑ ወይንም ለማፍራት የሚያስችለውን ማንኛውንም ምግብ ለመቀበል ከግንዱ ጋር አልተጣበቁም ( በእምነት አማካኝነት የውስጥ ግንኙነት ዓላደረጉም) ለምን ቢባል የስም ክርስቲያኖች ናቸው እንጂ የልብ ወይም የውስጥ ለውጥ የላቸውም። ልብ ብለን የጌታን እንመልከት ፣

ቁ.6 " በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል"

ያለማፍራት ችግር ከግንዱ ሳይሆን የቅርንጫፍ በግንዱ ውስጥ አለመኖሩ ነው ማለትም በእምነት በግንዱ ውስጥ ( በክርስቶስ ውስጥ) አለመገኝቱ ነው። ፍሬ የማያፈራ ቅርንጫፍ ደግሞ ተቆርጦ ይጣላል፤

ቁ4 "በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ፦ ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም።"

እኛ ልናፈራ የምንችለው ደግሞ በክርስቶስ ውስጥ ስንኖር ብቻ ነው፣ " በእኔ ኑሩ " ተብለናል በክርስቶስ ውስጥ መኖር ማለት በእምነት ለመዳናችንም ሆነ ፍሬ ለማፍራት ራሳችንን በእርሱ ላይ መጣል ነው። ምክንያቱም እኛ በክርስቶስ ውስጥ ስንኖር እርሱ ደግሞ በእኛ ውስጥ ይኖራል፤ " በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ " ፍሬ የማፍራታችን ሚስጥሩ የክርስቶስ በእኛ ውስጥ መኖር ነው፡ ( ሚስጥሩም የክብር ተስፋ የሆነው ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ መኖሩ ነው )

ለማጠቃለል፤ እውነተኛ ክርስቲያን ዳግም የተወለደ / አዲስ ፍጡር ማለትም አዲስ ሰው የሆነ/ የዘላለም ሕይወት ያለው / የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነ / ክርስቶስ በውስጡ የሚኖር / ውድ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ስለዚህ ኩነኔ የለበትም ። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ የሚፈረድበት በማያምን ነው።
ሰላም ወንድሜ
የሰጠኸው ማብራሪያና ምላሽ ላይ ምንም ጥያቄ የለኝም።

ነገር ግን ይህ የዮሐንስ 15 ታሪክ አንድ ነገርን ግልጽ እንደሚያደርግልን ብቻ ነው መግለጽ የምፈልገው። አንድ በክርስቶስ ላይ ያለ ቅርንጫፍ በክርስቶስ ባይኖር ከክርስቶስ ተለይቶ ሊወድቅና ሊቆረጥ፣ ሊደርቅና ድነቱን ሊያጣ እንደሚችል ብቻ ነው። ይህ ምሳሌ በስዕላዊ መልክ የሚያሳየንም፣ የሚያስተምረንም መልእክት የዳኑ አማኞች በክርስቶስ ተጣብቀው ካልኖሩ ልክ እንደ ቅርንጫፍ እንደሚቆረጡ፣ እንደሚደርቁና ይባስ ብሎም ለፍርድ እንደሚቀርቡ የሚያሳይ ስዕላዊ ምሳሌ ነው። ከክርስቶስ ውጪ ሆኖ መዳን የለምና።

ስለዚህ ከላይ መጀመሪያ ለተጠየቀው ጥያቄ ማለትም አማኝ ድነቱን ሊያጣ ይችላል ወይ ለሚለው ጥያቄ መልሱ አዎን በክርስቶስ ካልሆነ በደንብ ድነቱን ሊያጣ ይችላል የሚል ነው። ቃሉ ይሄንን ነውና የሚያስተምረን። ሆኖም በክርስቶስ መሆን ማለት ግን ሃይማኖታዊ አክቲቪትዎችን ማድረግ ማለት ግን አይደለም። በእምነትና በመንፈስ ቅዱስ ከክርስቶስ ጋር ህብረት በማድረግ ከግንዱ ከክርስቶስ ጋር መጣበቅ ማለት እንጂ። ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ አክቲቪቲ ክርስቶስን ሊተካ አይችልምና።

ጌታ ይባርክህ!
የጌታ ጸጋ ይብዛልህ ወንድሜ

እኔ የምረዳው እውነተኛ አማኝ ድነቱን ሊያጣ ከቶ አይችልም ። አማኝ ማለት በስም ክርስቲያን የሆነ ብቻ ካልሆነ በስተቀር እርሱ ደግሞ ቀድሞውንም አልዳነም ነበር።
እውነተኛ ክርስቲያን ማለት ደግሞ ፤
ድነትን በእምነት የተቀበለ /ዳግም የተወለደ / አዲስ ፍጡር የሆነ ማለትም አዲስ ሰው የሆነ/ የዘላለም ሕይወት ያለው / የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነ / ክርስቶስ በውስጡ የሚኖር / ውድ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ማለት ነው። እውነተኛ ክርስቲየን የሚኮነው ደግሞ በሥራ ሳይሆን በእምነት ብቻ ነው፡፡ ክርስቶስ በሰራው ስራ ብቻ ማለትም በሞቱና በትንሳዔ በማመን ብቻ የምንቀበለው ነው። ይህ ድነት ደግሞ የዘላለም ነው እንጂ የሚጠፋ አይደለም ለዚህም ነው የዘላለም ሕይወት ተብሎ የሚጠራው፤ ዮሓ 10፡27-29

"በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤
እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም"

ክርስቲያን በጌታ ጥበቃ ውስጥ ስለሆነ አይጠፋም ስለዚህም በእግዚአብሔር ቤት ለዘላለም ይኖራል፤ ደግሞም " አልተውህም ፤ አልጥልህም " ብሎናል ስለዚህም በእርሱ እንተማመናለን።


ተባረክ ወንድሜ
ክርስቲያን በኢየሱስ ጥበቃ መሆኑን ትክክል ብለሃል ቃሉም እንዲሁ ይላልና። ሆኖም ይሄ ማለት ግን እግዚአብሔር የሰውን ፈቃድ ሙሉ በሙሉ ይነጥቃል ማለት አይደለም። ሰው በፈቃዱ እምነቱን ሊተውና ከክርስቶስ ሊለይ ይችላል። አንዱን ሃሳብ ብቻ ማየት የለብህም ሁለቱንም የመጽሃፍ ቅዱስ ሃሳብ ነው ማመዛዘን ያለብህ።

ያለበለዚያማ የወይኑ አትክልት ምሳሌ እንዲያው በከንቱ ነበራ። በክርስቶስ ያሉ ቅንጫፎች እንዴት ከክርስቶስ ሊለዩና ሊደርቁ እንደሚችሉ ወዘተ የሚናገረው ምሳሌ ምንም ፋይዳ የለውማ። በክርስቶስ ማለትም በግንዱ አንዴ ከነበሩ በኋላ ከዚያ ከግንዱ ማለትም ከክርስቶስ መለየት የማይቻል ከሆነ ምሳሌውና ማስጠንቀቂያው ሁሉ ከንቱ ነዋ። ሊሆን የማይችል ነገር ነው ኢየሱስ ሲናገር የነበረው ማለት ነው?

ሙሉን የቃሉን ዓውድ በትክክል ከተጠና፤ ጥናቱ ወደሚያመራው ወደ ትክክለኛው መደምደሚያም መድረስ ግድ ነው። በክርስቶስ የነበሩ ቅርንጫፎች ከክርስቶስ ሊለዩና ሊደርቁ እንደሚችሉ ቃሉን አጥንቶ በኋላ "የለም አንዴ በክርስቶስ የሆነ ከክርስቶስ ሊለይ አይችልም" ወደሚል መደምደሚያ መድረስ ጨርሶ መሳት ነው። በትክክል ማጥናት ከዚያም ጥናቱ ወደሚያመራው መደምደሚያ መድረስ ነው የሚያዋጣው እንጂ፤ ያለዚያ ሳላጠናው በፊት ያለኝን ሃሳብ ለመቀየር ፈቃደኛ ካልሆንኩኝ ማጥናቱ እኮ ድሮውንም ምን ይጠቅማል?

አየህ አሁንም እያደረግህ ያለኸው ብዙ ጥቅሶችን በአንዳንድ በሌላ ጥቅሶች ለመሻር ነው። ይሄ አይነት ማዳፈንና አንዱን ብቻ ይዞ መሮጥ አያዋጣም ነው የምለው። ሁሉንም ሚዛናዊ አድርገን እንቀበለው፤ አንዱን ጎን ብቻ ይዘን አንሸምጥጥ።

ልብ በል እኔ እያወራው ያለሁት በሥራ ስለመዳን አይደለም። ከዚያ ጋር አታምታታው። መዳን በእምነት እንደሆነ እኮ ግልጽ ነው ሆኖም እምነት የምትለው እኮ ራሱ ሊጠፋ የሚችል ነገር ነው። ሰው ከፈተና ብዛት እምነቱን ሊያጣ ይችላል።

የሉቃስ ወንጌል
22፥32 እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና አለ።

ከኃጢአትም ብዛት ከክርስቶስ ሊርቅና ከህይወት መጽሃፍ ሊሰረዝ ይችላል። ለምን ታዲያ ኢየሱስ ድል ለነሳው ከህይወት መጽሃፍ ስሙን አልደመስስም አለ፤ ከህይወት መጽሃፍ መደምሰስ ከሌለ?

የዮሐንስ ራእይ
3፥5 ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጐናጸፋል፥ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም፥ በአባቴና በመላእክቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ።

አንተ እያልክ ያለኸው እኮ እነዚህንና ተመሳሳይ ጥቅሶችን እንሸፋፍናቸው፤ ወይም ከሌሎቹ እኩል አንያቸው ወዘተ እያልክ ነው በተዘዋዋሪ። ይሄ ደግሞ ሊሆን አይችልም። ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ፣ በአዲስ ኪዳን የኢየሱስን ትምህርት ደግሞም የሃዋርያቱንም ጨምረህ ተመልከት፣ ከኋጢአት ንስሐ ሊገቡ የማይፈልጉና በኃጢአት ጸንተው የሚኖሩ የዘላለም ሕይወት አይወርሱም። ሰው ደግሞ በክርስቶስ ከሆነ በኋላም በፈቃዱ በኋጢአት ተፈትኖ ወይም የዚህ ዘመን የዓለም ኑሮ አታልሎት ከክርስቶስ ሊለይ ይችላል። ያለዚያማ ሰይጣን ለምን ይፈትነናል እኛ ፈጽሞ ልንወድቅ የማንችል ከሆነ? ሰው እምነቱንም እንኳን ሊያጣ ይችላል። ከዳነበትና ከተመዘገበበት ከህይወት መጽሐፍ ሊደመሰስ ይችላል። ቃሉ ይሄንንም ይናገራል። በእምነትና በመንፈስ ጀምሮ በስጋና በህግ ሊጨርስ ይችላል እንደ ገላትያ ሰዎች።

ወደ ገላትያ ሰዎች 5
2 እነሆ፥ እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ። ብትገረዙ ክርስቶስ ምንም አይጠቅማችሁም።
3 ሕግንም ሁሉ እንዲፈጽም ግድ አለበት ብዬ ለሚገረዙት ሁሉ ለእያንዳንዶች ደግሜ እመሰክራለሁ።
4 በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል

ለምንስ በክርስቶስ ለሆኑ አማኞች ጳውሎስ እንደሚከተሉት ያሉ ማስጠንቀቂያዎች ይጽፋል፤ መወደቅና ከክርስቶስ መለየት የማይቻል ከሆነ?

ወደ ገላትያ ሰዎች 5
17 ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም
18 በመንፈስ ብትመሩ ግን ከሕግ በታች አይደላችሁም።
19 የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥
20 መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥
21 መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም

አሁንም የምመክርህ አንዳንድ ጥቅሶችን ብቻ ሳይሆን ሙሉውን የኢየሱስንና የሃዋርያቱን ትምህርት እንድታጠናውና እንድትቀበለው ነው። በተለይ ደግሞ እንደ ወንድም በጌታ ፍቅር የምለምንህ ይሄ አንተ እያልከው ያለኸው ትምህርት ለብዞዎች በኃጢአት ውስጥ ለመኖር የሚገፋፋ ሊሆን ይችላልና ለብዙዎች ህይወት መሰናክል ሆነህ ተጠያቂ እንዳትሆን እባክህን ትንሽ ቃሉን በሰፊው እስክታጠና ድረስ ቢያንስ ቢያንስ ሌሎችን በዚህ ትምህርት አትሳባቸው። እውነት እልሃለው፤ አንተ የምትለው ትምህርት በኃጢአት የሚጨማለቁ "ክርስቲያኖችን" ከማፍረት የተለየ ሌላ ፍሬ አያመጣምና!

ድነትን ማጣት የለምና እንግዲያውስ ኑ እንብላና እንጠጣ ወደሚል አስተሳሰብ ውስጥ የሚከትት ነው።

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች
32 እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ከታገልሁ፥ ሙታንስ የማይነሡ ከሆነ፥ ምን ይጠቅመኛል? ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ
33 አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች
9፥27 ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ።

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10
1 ወንድሞች ሆይ፥ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፤
2 ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፤
3 ሁሉም ያን መንፈሳዊ መብል በሉ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤
4 ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ ዓለት ጠጥተዋልና፥ ያም ዓለት ክርስቶስ ነበረ

5 እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ በሚበዙት ደስ አላለውም፥ በምድረ በዳ ወድቀዋልና።
6 እነዚህም ክፉ ነገር እንደ ተመኙ እኛ ደግሞ እንዳንመኝ ይህ ምሳሌ ሆነልን።
7 ሕዝብም ሊበሉ ሊጠጡም ተቀመጡ ሊዘፍኑም ተነሡ ተብሎ እንደ ተጻፈ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖትን የምታመልኩ አትሁኑ።
8 ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንደ ሴሰኑ በአንድ ቀንም ሁለት እልፍ ከሦስት ሺህ እንደ ወደቁ አንሴስን።
9 ከእነርሱም አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑት በእባቦቹም እንደ ጠፉ ጌታን አንፈታተን።
10 ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጎራጎሩ በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታንጐርጕሩ።
11 ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፥ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ
12 ስለዚህ እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ
በድጋሚ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን

ውድ ወንድሜ በመጀመሪያ ስለ ጸጋ ማስተማር አንተ እንደምትለው ሰውን ወደ ሃጢያት የሚገፋፋ ሳይሆን ይልቁንም ሰውን ከሃጢያት የሚያድን እና የቅድስናን ሕይወት የሚያኖር ብቸኛ የእግዚአብሔር መንገድ ነ፡፡
በኃጢአት ውስጥ ለመኖር የሚገፋፋ እና ለብዙዎች ህይወት መሰናክል የሚሆነው ጸጋን ከህግ ጋር እየደባለቅን በማስተማራችን ምክንያት ራሳችንን እና የሚሰሙንን ግራ እያጋባን ወንጌሉን እናጣምመዋለን።

ሮሜ 11፡6 " በጸጋ ከሆነ ግን ከሥራ መሆኑ ቀርቶአል፤ ጸጋ ያለዚያ ጸጋ መሆኑ ቀርቶአል።"
ከመጀመሪያም እስከመረቻ ጸጋ ነው እንጂ የስው ሥራ የለበትም፡
በጸጋ ስንድን አዲስ ሰው እንሆናለን አዲስ ሕይወት ስላለን በጽድቅ እንመላለሳለን፡ በቅድስና የምንመላለስው ቅዱሳን እድንሆን ሳይሆን በጸጋው ቅዱሳን ስለሆንን ነው እንጂ።
በመጀመሪያ ስንድን ወይንም ዳግም ስንወለድ ፍፁም የሆነውን የእግዚአብሔርን ጽድቅ ተቀብለናልእና።
ሮሜ 3፡ 21 " 21 አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፥ 22 እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው "
የእግዚአብሔር ጽድቅ ስላለን ስለዚህ እኛ በጸጋው ቅዱሳን ፤ ፃድቃን፤ ነን፤ ያዳነን በቅዱስም የጠራን እራሱ እግዚአብሔር ነውና። የክርስትናን ሕይወት የምንኖረው ስለሆንን ነው እንጂ ለመሆንን አይደለም። ይህ ሕይወት የጌታ ዘላለማዊ ነፃ ሥጦታ ነው ። የዘላለም ሕይወት የተባለውም ስለማይጠፋ ነው።

አንተ እንደ ምትለው "በኃጢአት የሚጨማለቁ "ክርስቲያኖችን" የመኖር ምክንያት ጸጋው እና ሕግን በማደባለቅ ስላምናስተምር እውነተኛ ክርስቲያን ሳይሆን ሃይማኖተኞችን ስለ ምናፈራ ነው። በእምነት ነው የዳንነው የምናፈራውም በእምነት ነው፡

ሮሜ 1፡17 ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና። ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና።

ጌታ ያዳነን የተቀበልነውን የእርሱን ጽድቅ በእምነት ወደ ውጭ በተግባር እድንገልጠው ነው። ይህም ደግሞ በመንፈሳዊ ሕይወታችን በእድገት የሚገለጽ ነው።

ገላትያ 6፡13-18
በሥጋችሁ እንዲመኩ ልትገረዙ ይወዳሉ እንጂ የተገረዙቱ ራሳቸው እንኳ ሕግን አይጠብቁም። ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። በዚህም ሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ላይ በእግዚአብሔር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን። እኔ የኢየሱስን ማኅተም በሥጋዬ ተሸክሜአለሁና ከእንግዲህ ወዲህ አንድ ስንኳ አያድክመኝ።

ወንድሞች ሆይ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን። አሜን።


( ብዙ ልጽፍ እፈልግ ነበር ግን የአማርኛ ፊደል ታይፕ ማድረግ ችግር አለብኝ )
ሰላም ወንድሜ

እኔ ያላልኩትን ለምን እንዳልኩ አስመስለህ ትናገራለህ። ስለ ጸጋ ማስተማር ወደ ኃጢአት መገፋፋት ጨርሶ አይደለም። ሊሆንም አይችልም። አንተ እያስተማርክ ያለኸው ግን ከዚያ የተለየ ነው። አንዴ በክርስቶስ ከሆናችሁ ምንም ብታደርጉ ድነታችሁን አታጡም ማለት ስለ ጸጋ ማስተማር አይደለም። መጽሃፍ ቅዱስ የማያስተምረውንና የማይሰጠውን ዋስትና ለሰዎች እየሰጠህ ነው። ሰው ከዳነ በኋላማ መማርም ያለበት ስለ ጸጋ ነው። ጸጋው ግን ኃጢአትን ድል አድርጎ ለመኖር የሚያስችል ኃይል ነው እንጂ ጸጋ ማስተማር ማለት ምንም ብታደርግ ድነትህን አታጣውም እያሉ ወደ ኃጢአት ሰዎችን በተዘዋዋሪ መገፋፋት ማለት አይደለም። የትም ቦታ ጸጋው እንደፈለጋችሁ ብትኖሩም ድነታችሁን አታጡትም ብሎ አያስተምርም። ይሄ የአንተ እንጂ የጸጋው ትምህርት አይደለም።
ሰላም በድጋሚ
ወንድሜ እኔ የጻፍኩት ክርስቲያኖች እንደፈለጉ ይኑሩ የሚል ፈጽሞ አይደም ነገር ግን ሰው ጌታ ሲያድነው አዲስ ፍጥረት አድርጎታል፤ አዲስ ሕይወት ሰጥቶታል ስለዚህም በአዲስ ሕይወት ለመመላልስ እና የመንፈስ ቅዱስን ፍሬ ለማፍራት በእምነት ድነትን እንደ ተቀበለ ሁሉ አሁንም በእምነት መኖር አለብት ነው ያልኩት። ለዚህም በቂ የቃሉን ማስረጃ በማቅረብ ነው።
ደግሞም " መጽሃፍ ቅዱስ የማያስተምረውንና የማይሰጠውን ዋስትና ለሰዎች እየሰጠህ ነው።" ላልከው ዮሓ 10፡ 28 " በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ሉኝማል፤
እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም። " በማለት ጌታችን ዋስትና ሰጥቶናል። ድነታችንን በስራችን አላገኘነውም ደግሞም በስራችን አንጠብቀውም ይልቁንም በራሳችን ላይ ትኩረታችንን ማድረጋችንን ትተን የእምነታችንን ጀማሪ እና ፈፃሚውን ወደ ሆነው ጌታ ብናተኩር " ሰላማችን እንደ ወንዝ ጽድቃችን ደግሞ እንደ ባህር ሞገድ" ይሆልናል። እኛ ያለ እርሱ ምንም ማድረግ አንችልም እና።

ድል አድራጊ ክርስቲያን የምንሆነው በእምንት ብቻ ነው፤
"ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው?

1 ዮሓ 5፡4-5
ሰላም ወንድሜ

አንተ የምትለው ላይ እኮ ማንም ጥያቄ ያለው አይመስለኝም። ጥያቄው እኮ የሚያተኩረው አንዴ ባመኑና በጸጋና በእምነት ስለሚመላለሱ ሰዎች አይደለም። ነገር ግን አንዴ በግንዱ ላይ ማለትም በክርስቶስ ከነበሩ በኋላ ከዚያ ስለ ወደቁ ወይም ሊወድቁ ስለሚችሉ ነው። እንደገባኝ አንተ እያልክ ያለኸው አንዴ በክርስቶስ ከሆነ በኋላ ሰው፤ በፍጹም መውደቅ የሚባል ነገር የለም እያልክ ነው። ይህ ደግሞ በተዘዋዋሪ አንዴ በክርስቶስ የሆኑ ሰዎች እንደፈለጉ ቢኖሩም ድነታቸውን አያጡም ማለት ነው። እናም የምንነጋገረው ድል ስለሚነሱ ሰዎች ሳይሆን፤ ድል ስላልነሱት ነው። ከክርስቶስ በፈቃዳቸው ስለተለዩት።

አንድ በጣም ትልቁ የምንስትበት ነገር ያለው፤ ድነት ሁለት ዳይሜንሽን መሆኑን ስለምንዘነጋ ነው። ወይም ልክ ድነት የሰው ስራ እንደሆነ ብቻ አድርገን በሰው ጥረት ብቻ እንደሚሆን ጸጋውን ጥለውን ወደ ሰው ስራ እናጋድላለን ወይም ሰው ምንም አይነት ሃላፊነት እንደሌለበት አድረገን፤ ሰው የሚያደርገውና የሚኖረው ኑሮ ፍጻሜው ላይ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ አድርገን ሰውን ካለበትም ሃላፊነት ነጻ ለማውጣት እንሞክራለን።

መጽሃፍ ቅዱስ ሚዛናዊ ነው። አዎ ድነት ፍጹም የጸጋና የእግዚአብሔር ስራ ነው። ነገር ግን ከዳንን በኋላ ግን በመንፈስ እንድንመላለስ ኃላፊነት አለብን። የስጋን ስራ እንዳንስራና በስጋ እንዳንመላለስ ሃላፊነት አለብን። የምንዘራውን እንደምናጭድ ቃሉ ጽፎልናልና። ከቅርንጫፉ ከክሮስቶስ በራሳችን ተነሳሽነት ልንለይ እንደምንችልም፣ ከህይወት መጽሃፍ መደምሰስም እንዳለም ሁሉ ቃሉ ይናገራል። ስለዚህ ቃሉ ሚዛናዊ እንደሆነ እኛም ሚዛናዊ ልንሆን ይገባናል እንጂ እንደው ወደ አንዱ ብቻ ያጋደለ ገዳዳ አካሄድ መሄድ የለብንም።

ወደ ሮሜ ሰዎች
8፥13 እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ።

ወደ ገላትያ ሰዎች 6
7 አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤
8 በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል።
ሰላም ወንድሜ
ልክ ነው መጽሓፍ ቅዱስ እንደሚያስረዳን በእውነት ዳግም የተወለደ ክርስቲያን ለዘላለም ነው የዳነው፤ ክርስቲያን በህይወቱ ሊደክም ይችላል ይሆናል ነገር ግን ለዘለአለም አይጠፋም ጌታ እንደተናገረው ይጠብቀዋል፤ ዳግም የተወለደ ክርስቲያን ሃጢያቱ ሁሉ ይቅር ተብሎለታል ደግሞም ፍጹም የሆነውን የጌታ ጽድቅ በእምነት ተቀብሎአል ፃድቅና ቅዱስ ሆናል፤ ስለዚህም ኩነኔ የለበትም፤ ( 1ቆሮ 1፡30፣ ሮሜ 8፡1 ፤ 1ቆሮ 6፡11 )

ክርስቲያን መልካም ሥራ የሚሰራው ድነቱ እንዳይወሰድበት ወይም በጌታ ተቀባይነት ለማግኘት ሲል አይደለም ነገር ግን እግዚአብሔር ሕይወቱን ስለቀየረው እና የጌታ ፍቅር ግድ ስለሚለው ነው፤ በውስጡ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ የጽድቅን ፍሬ እንዲያፈራ ችሎታው ስለሆነ ነው እንጂ፡፡
ድነታችን ግን እስከዛሬ ድረስ በሰራነው ወይም ወደፊት በምንሰራው በእኛ ሥራ ላይ የተመሰረተ ፈጽሞ አይደለም። ድነት ነጻ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፤ " የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።" ሮሜ 6፡23

ብዙ ፍሬ እድናፈራ በጌታ ተሹመናል "እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ አብም በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንዲሰጣችሁ፥ ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ፍሬአችሁም ሊኖር ሾምኋችሁ።" ዮሃ 15፡16 ደግሞም ፍሬ የምናፈራው በእምነት ከወይኑ ግንድ ጋር ስንጣበቅ ነው፤ በራሳችን ምንም ማድረግ አንችልም እና " በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ ውስጥ እኖራለሁ" ቅርንጫፍ ከግንዱ ጋር ካልተጣብውቀ በስተቀር በራሱ ማፍራት እንደ ማይችል ሁሉ እኛም ያለ ጌታ ማፍራት አንችልም፤
ነገር ግን በእምነት ከወይኑ ግንድ ጋር ያልተጣበቀ ቅርንጫፍ የስም ክርስቲያን እንጂ ዳግም ያልተወለደ ስለሆነ ፍሬ ማፍራት ስለማይችል ተቆርጦ ይጣላል፤ ዋናው ችግር እውነተኛ እምነት አለመኖሩ ነው፤ ደጋግሞ በእኔ ኑሩ በማለት ጌታችን ያስተማረው፤ "በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል።" ቁ. 6 በክርስቶስ ውስጥ የምንኖረው በእምነት ነው ያለ እምነት ማንም ሰው በራሱ ማፍራት አይችልም እና፤
በመንፈስ ስንኖር የስጋን ምኞት አንፈጽምም " በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ።" ገላ 5፡25 ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማስኘት አንችልምና።
ሰላም ወንድሜ

እንግዲህ ነገሬን ጨርሻለሁ፤ የመጨረሻ ከልቤ የሆነና ከወንድማዊ ፍቅር የመነጨ አንድ ነገር ብቻ ላሳስብህ እወዳለሁ። እንድትታገስና ሁሉንም እንድታነበብው በጌታ ፍቅር እለምንሃለሁ። ከልብ ከወንድማዊ ፍቅር የመነጨ እንጂ ክርክር ለማሸነፍ በመፈለግ አይደለም። የትምህርትህ ውጤቱ ስለሚታየኝ ብቻ ነው ይሄንን የመጨረሻ ማሳሳቢያ የምጽፍልህ።

እኔ በመሰረቱ ፈጽሞ ሙሉ በሙሉ የጸጋ አማኝ ነኝ፤ ሆኖም ግን ሃዋርያቱ በአዲስ ኪዳን እንዳስተማሩት አይነት ጸጋ ማለቴ ነው። በሃይማኖታዊ ስርዓትና በስራ ለመዳን የሚደረግን ማንኛውንም ሙከራ ፈጽሞ እቃወማለሁ፤ ምክንያቱም መጽሃፍ ቅዱስ እንደሚል ይህ ከጸጋ መወደቅ ነውና። እናም ስለ ጸጋ ደጋግመህ መጻፍ አያስፈልግህም፤ የሮሜም ይሁን የገላትያ መልእክት የክርስትና ህይወት በመንፈስ በመመላለስና በእምነት የምንኖረው እንደሆነ ግልጽ ያደርጋሉ። ጥያቄው ያ አይደለም። ከዋናው ጥያቄ ለምን ትሸሻለህ። ስለ ጸጋ ትምህርትና በመንፈስ ስለመመላለስ፤ በራሳችን ምንም ማድረግ እንደማንችል ወዘተ እዚህ ላይ ማንም ጥያቄ የለውም። ይህንን እንደምንቃወም አድርገህ አታቅርብ።

አንተና እኔን የሚለያየን ጥያቄ አንድና አንድ ብቻ ነው። ሰው እውነተኛ ድነት ካገኘ በኋላ እንደፈለገው ቢኖር ድነቱን ሊያጣ ይችላል ወይስ አይችልም የሚለው ላይ ነው። እኔ ሊያጣ ይችላል እላለሁ አንተ ደግሞ የእርሱ ኑሮ ድነቱን አይለውጠውም ትላለህ። ስለዚህ በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ብቻ ነው ማተኮር ያለብን። ከዚህ ውጪ ባለው የጸጋ ትምህርት ላይ ምንም ተቃውሞ የለኝም።

እንደ እኔ እንደ እኔ የአንተ ትምህርት እጅግ አደገኛ ነው እላለሁ። ይሄንን ደግሞ በሂደት በምታስተምራቸው ሰዎች ህይወት ውስጥ ወጤቱን check ካደረግህ ልትመሰክረው ትችላለህ። በጌታ ፍቅር የምልህ ይህ ነው። ይሄ ትምህርት በኋጢአት የሚጨማለቁ ክስቲያኖችን ከማፍራት ሌላ፤ ሌላ ውጤት አያመጣም። ይሄንን ደግሞ በአንተም በምታስተምራቸውም ሰዎች በሂደት ምን ፍሬ እንደምታፈሩ ታየዋለህ። እነ ጳውሎስ ጸጋን ያስተማሩት እንዲህ አይደለም። ሄደህ ሙሉን ቃሉን አንብብ፤ እነርሱ በምን ያህል ማስጠንቀቂያ የጸጋን ትምህርት እንዳስተማሩ መርምር። "ጸጋ ማለት ነጻ ስጦታ ማለት ነው" የሚለውን በጣም ጥልቀት የሌለውን ትርጉም ብቻ ይዘህ ከሄድክ የአዲስ ኪዳንን ጸጋ አልተረዳኸውም ማለት ነው። እነ ጳውሎስ ጸጋን ሲያስተምሩ ምን ያህል ስለ ኋጢአት እንዳስጠነቀቁ በደንብ አጥና።

እኔ ይቅርታ አድርግልኝና ለብዙ ዓመት መጽሃፍ ቅዱስን አጥንቼአለሁ፤ እናም አንተ በተዘዋዋሪ እያልክ ያለኸው መጽሃፍ ቅዱስ የማያስተምረውና ፈጽሞ አደገኛ ትምህርት እድርጌ ነው የምቆጥረው። ምክንያቱም በተዘዋዋሪ እያልክ ያለኸው ሰው ከዳነ በኋላ በኋጢአት የተጨማለቀ ኑሮ ቢኖርም እንኳን ድነቱን የሚያሰጋው ነገር የለም እያልክ ነው። ከዚህ የበለጠ ወንጌል ላይ የሌለና አማኞች በኋጢአት እንዲጨማለቁ የሚገፋፋ ትምህርት ያለ አይመስለኝም። ይሄ የአዲስ ኪዳን የጸጋ ትምህርት ፈጽሞ አይደለም፤ ቃሉን አጥናው። አንተ እንደምታደርገው ከድነት በኋላ አንድ አማኝ ምንም አይነት ኑሮ ቢኖር ሊጠፋ አይችልም የሚል እንኳን በቀጥታ በተዘዋዋሪ መልክ እንኳን አዲስ ኪዳን አይናገርም። ምክንያቱም እንዲህ ያለው ትምህርት ከኢየሱስና ከሃዋሪያቱ ትምህርትና መንፈስ ጋር ፈጽሞ የሚቃረን ነው።

በመጨረሻም እባክህን ዮሐ 15 ላይ ያለውን ስለ ወይኑ ግንድና ስለ ቅርንጫፎቹ የሚያወራውን በንጹህ ህሊና እንደገና አንብበው።

የስም ሳይሆን እውነተኛ ድነት ካገኘን በኋላ ከክርስቶስ ጋር እንድንጣበቅ፣ በመንፈስ እንድንሞላ፣ በመንፈስ እንድንመላለስ፣ ወዘተ መጽሃፍ ቅዱስ የሚያሳስበን እኮ የእኛም ሃላፊነት ስላለበት ነው። ከእውነተኛ ድነት በኋላ በመንፈስ መመላለስ ወይም በስጋ መመላለስ ስለሚቻል ነው እኮ ገላትያ "የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም" የሚለው።

በክርስቶስ የሆነና በእውነተኛ ግንዱ ላይ የተጣበቀ ብቻ እኮ ነው ቀድሞውንም ቅርንጫፍ ተብሎ የሚጠራው። "እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ" ነው እንጂ ኢየሱስ ያለው፤ በስም ክርስቲያን የሆኑ ቅርንጫፎች ናቸው አላለም። ለምን ቃሉን እንጠመዝዛለን? እንዲህስ በማድረግ እውነተኛ ውጤት ይገኛል? ስለዚህ በዮሐ 15 ላይ ቅርንጫፍ ብሎ የሚጠራቸው እናንተ ብሎ ስለሚጠራቸው ስለ ደቀመዛሙርቱ እንጂ ስለ ስም ክርስቲያኖች አይደለም። ቅርንጫፍ ማለትም እውነተኛ ከግንዱ ከክርስቶስ ጋር የነበረ ሰው ከግንዱ ጋር በመንፈስ ካልተጣበቀ ሊቆረጥና ሊደርቅ እንዲሁም ሊቃጠል ይቻላል ነው የሚለው። ቀድሞውኑም ከግንዱ ጋር ያልነበረ ታዲያ እንዴት ነው ሊወገድ የሚችለው? ቀድሞውኑስ እርጥብ ያልነበረ እንዴት ነው ሊደርቅ የሚችለው? ለምን የተጻፈውን አናነብብም።

"ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ" 1 ጢሞ 4፡16።

ጨርሻለሁ!
ሰላም ወንድሜ ስላልተመቸኝ በቶሎ መልስ ባለመስጠቴ በቅድሚያ ይቅርታ እጠይቃለሁ

ከላይ ለጠየቅኽኝ ጥያቄ --
" ሰው እውነተኛ ድነት ካገኘ በኋላ እንደፈለገው ቢኖር ድነቱን ሊያጣ ይችላል ወይስ አይችልም ? "
ላልከው የእኔ መልስ በአጭሩ "እውነተኛ ድነት" የተቀበለ አዲስ ሰው ሆኖአል
2ቆሮ 5፡17 " ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።" ስለዚህ በሃጢይኣጥ የሚጨማለቁ አዲሱን ሕይወት ያልተቀበሉ አልያም ጸጋው ያልገባቸው በራሳቸው ጥረት የክርስትናን ሕይወት ለመኖር የሚጥሩ ናቸው፤ ድነት የሚገኝው በእምነት እንደ ሆነ ሁሉ የጽድቅ ሕይወት ወይም እውነተኛ የክርስትና ኑሮ የሚኖረው በእምነት ነው፤ ጌታ "ያለ እኔ ምንም ማድረግ አትችሉም " ብሎናልና በሌላ ቦታ ደግሞ "ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና።"

የዘላለማዊ ደኅንነት አስተምህሮት ተደጋጋሚ ተቃውሞ የሚሆነው፣ ሰዎች እንደፈቀዱት ሊኖሩ ይችላሉ ከሚል ፍርሃት የተነሳ ነው። ይህ “ውጭውን” ሲታይ እውነት ይመስላል በተጨባጭ ግን እውነት አይደለም። በኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት የተዋጀ ሰው፣ ቀጣይነት ባለው የፍቃድ ኃጢአት ባሕርይ ሊኖር አይችልም። በደንብ መገንዘብ ያለበን ክርስቲያን እንዴት መኖር እንዳለበትና፣ ደኅንነትን ለመቀበል አንድ ሰው ምን ማድረግ እንዳለበት መሐል ያለውን ልዩነት ነው።

መጽሐፍ ቅዱሳችን እንደሚያስተመን ደኅንነት በጸጋ ብቻ፣ በእምነት በኩል ብቻ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው (ዮሐንስ 3፡16፤ ኤፌሶን 2፡8-9፤ ዮሐንስ 14፡6)። አንድ ሰው በእውነት በኢየሱስ ክርስቶስ ባመነበት ቅጽበት፣ ድነዋል፤ እናም በዛ ደኅንነት ተጠብቀዋል። ደኅንነት በእምነት ይገኛል፣ ከዚያ በኋላ በዚያው እምነት ሲኖር መልካም ፍሬ ያፈራል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይሄንን ጉዳይ በተመለከተ በገላትያ 3፡3 እንዲህ በማለት ይጠይቃል፣ “እንዲህን የማታስተውሉ ናችሁ? በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋ ትፈጽማላችሁን?” በእምነት ከዳንን፣ ደኅንነታችን የሚጠበቀውም ሆነ የሚረጋገጠው በአምነት ነው። የራሳችንን ደኅንነት ልናገኝ አንችልም። ስለሆነም፣ በራሳችን የደኅንነታችንን ማረጋገጫ ልናገኝም አንችልም። ደኅንነታችንን የሚያረጋግጥ እግዚአብሔር ነው (ይሁዳ 24)። በራሱ ጭብጥ አጽንቶ የያዘን የእግዚአብሔር እጅ ነው (ዮሐንስ 10፡28-29)። የእግዚአብሔር ፍቅር ነው፣ ምንም ነገር ከእሱ እንዳይለየን ያደረገው (ሮሜ 8፡38-39)

ማንኛውም ዓይነት የዘላለም ደኅንነት ክህደት፣ በመሠረተ ሐሳቡ፣ የራሳችንን ደኅንነት በራሳችን መልካም ሥራና ጥረት ድነታችንን እንጠብቀዋለን ከሚል የተሳሳተ ትምህርት የመነጨ ነው። ይህም ባጠቃላይ ደኅንነት በጸጋ የሚለውን የሚጻረር ነው። የዳንነው በክርስቶስ ሥራ ምክንያት ነው፣ በራሳችን አይደለም (ሮሜ 4፡3-8)። እንዲሁ የእግዚአብሔርን ቃል በመታዘዝ መልካም ሕይወትን መኖር የምንችለው በእምነት ብቻ ነው ነገር ግን፣ የራሳችንን ደኅንነት የምንጠብቀው በሥራችን ነው የሚል ክርክር ማቅረብ፣ የኢየሱስ ሞት የኃጢአታችንን ዋጋ ለመክፈል አይበቃም ማለት ነው። የኢየሱስ ሞት የኃጢአታችንን ዋጋ ለመክፈል ፈጽሞ በቂ ነው— ያለፈውን፣ የአሁኑን፣ እና የወደፊቱን፣ ይህም ቅድመ-ደኅንነት እና ከደኅንነት በኋላ ያለውን ያጠቃልላል(ሮሜ 5፡8፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡3፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡21)

ይሄንን ማለት ክርስቲያን እንደፈለገው ቢኖርም አሁንም ድኗል ማለት ነውን? ይህ በመሠረቱ መላምታዊ ጥያቄ ነው፣ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ እንዳደረገው እውነተኛ ክርስቲያን “እሱን እንዳፈቀደው” መኖር ስለማይችል ነው። ክርስቲያኖች አዲስ ሕይወት አግኝቶአል። ክርስቲያኖች የመንፈስ ፍሬ ያፈራሉ (ገላትያ 5፡22-23)፣ የሥጋ ድርጊት ያልሆኑትን (ገላትያ 5፡19-21)። አንደኛ ዮሐንስ 3፡6-9 በግልጽ እንደሚያስቀምጠው እውነተኛ ክርስቲያን ቀጣይነት ባለው ኃጢአት አኖርም። ጸጋ ኃጢአትን ያበዛል የሚለውን ክስ በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ገልጿል፣ “እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ በኃጢአት ጸንተን እንኑርን? አይደለም። ለኃጢአት የሞትን እኛ ወደ ፊት እንዴት አድርገን በእርሱ እንኖራለን?(ሮሜ 6፡1-2)

የዘላለም ደኅንነት ኃጢአትን ለመፈጸም ፍቃድ አይደለም። ይልቁን፣ የእግዚአብሔር ፍቅር እሱም በክርስቶስ ለሚያምኑት የሆነውን ማስረገጫና የደኅንነት እውቀት ነው። የእግዚአብሔርን ታላቅ የሆነ የደኅንነት ስጦታ ማወቅና መረዳት መቻል ለኃጢአት ፍቃድ መስጠት ከሚለው በተጻራሪው ነው። ማንም ቢሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ የከፈለውን ዋጋ አውቆ እንዴት አድርጎ፣ በኃጢአት ሕይወት ሊቀጥል ይችላል (ሮሜ 6፡15-23)? ማንም ቢሆን የእግዚአብሔርን ያልተጠበቀና የተረጋገጠ ፍቅር እሱም ለሚያምኑት የሆነውን፣ ከተረዳ በኋላ፣ ያንን ፍቅር መልሶ በእግዚአብሔር ፊት ይወረውራል? እንዲህ ዓይነቱ ሰው የሚያሳየው የዘላለም ደኅንነት የኃጢአት ፍቃድ እንደሰጠው አይደለም፣ ነገር ግን ይልቁን እሱ በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ደኅንነት በትክክል እንዳልያዙት ነው። “በእርሱ የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፤ ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ አላየውም አላወቀውምም” (1ኛ ዮሐንስ 3፡6)
ይቅርታ አድርግልኝና አንተ ለቃሉም ይሁን ለራስህ ህይወት ቅንና እውነተኛ (honest) አይደለህም። አንተ አሁን ራስህን ብትመለከት እንደፈለግሁት መኖር አልችልም ልትል ነው? ኃጢአት እየሰራህ መኖር በእርግጥ አትችልም? ለምን እውነተኞች አንሆንም። ለቃሉና ለራሳችን ህይወት ቅንነትና እውነተኝነት ከሌለንና ዝም ብለን መጽሃፍት ላይ ያነበብነውን ብቻ የምንናገር ከሆነ ዋጋ የለውም። ትርፉ ድካም ብቻ ነው። በህይወት በተጨባጭ practically የማይገለጽ ትምህርት፤ እንዲሁ በቲዎሪ ብቻ ሲሰብኩት ቢኖሩ ምን ይጠቅማል? አየር ላይ ከመንሳፈፈ በስተቀር ምንም አይረዳም።
ውድ ወንድሜ ይቅርታ አድርግልኝ ስላልክ ይቅር ብዬሃሁ ለሰጠኽው አስተያየት ግን መልስ መስጠት ስላለብኝ ስለ ራሴ ሳይሆን ስለ ወንጌል እውነት እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
ክርስትናችን አንተ እንዳልከው በህይወት በተጨባጭ practically የማይገለጽ ትምህርት ወይንም እንዲሁ በቲዎሪ ብቻ የሚሰበክ ምንም የማይጠቅም ፤ አየር ላይ ከመንሳፈፈ በስተቀር በተግባር ላይ የማይገለጽ ኑሮ ሳይሆን በራሴ ሕይወት ተግባራዊ መሆኑን ቀምሼ ያየሁት የተለማመድኩትን ፤ ልክ ጌታችና መድሓኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው ፤ ማንም ሊሰጠው የማይችለውን ሰላም ፤ ደስታ ፤ እርካታ፤ እረፍት፤ የልብ እርግጠኝነትና የሕይወት ለውጥ አግኝቼአለሁ። የተጠራነው በጽድቅ በቅድስና እየኖርን እድናገለግለው ነው እንጂ ሃጢያትን እንደፈለግን እያደረግን እድንኖር አይደለም፡፤ በመጀመሪያ ዳግም የተወለደ የተቀበለው አዲስ ሕይወት እና በውስጡ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ወደ ቅድስና እንጂ ወደ ሃጢያት አይመራውም ። የዳነ ክርስቲያን የክርስቶስ ልብ አለውና። ብዙዎቻችን ክርስትና ሃይማኖት እንጂ አዲስ ሕይወት መሆኑን ስላልተረዳን እግዚአብሔር ያደረገልንን ማየት ተስኖን እኛ ስለምናደርገው ላይ ትኩረታችንን እናደርጋለን;፤ ቃሉ የሚለው ግን የእምነታችሁ ጀማሪና ፈጻሚውን ተመልከቱ ነው።
እኔም ለብዙ ዘመን ክርስትና ሳይገባኝ በአታድርግና አድርግ ትምህርት ተይዜ ስኖር ሳለሁ አንድ ቀን ጌታ አይኖቼን ሲከፍትልኝ የክርስትና ሕይወት የሚጀምረው ለካ በተፈፀመው በክርስቶስ ሥራ ላይ በማረፍ መሆኑን ተገጸልኝ። አየህ ወንድሜ ምንም አይነት ሥራ በመስራት ድነታችንን እንደማናገኝውና ወደፊትም ለድነታችን የምንሰራው ሥራ እንደሌለ ስራችንን ሁሉ ጌታችን ሰርቶ የጨረሰልን መሆኑን ካልተረዳን እውነተኛውን የክርስትናን ጉዞ መጀመር አንችልም።
መሰረታዊ እውነቶችን እስቲ እንመልከት፤ ---
ክርስቶስ በሕይወቱ፤በሞቱ፤በትንሳኤው፤እና በእርገቱ ሙሉ በሙሉ አድኖናል
1) ክርስቶስ በሕይወቱ ስለ እኛ ሕግን ፈጽሞልናል
-- የእግዚአብሔር ሕግ ሁሉ መፈፀም አለበት፤
ከሕግ አንዲት ነጥብ ከምትወድቅ ሰማይና ምድር ሊያልፍ ይቀላል። (ሉቃ 16፡17)
-- ሰው ደግሞ ሕጉን መፈፀም አልቻለም
"አፍም ሁሉ ይዘጋ ዘንድ ዓለምም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ይሆን ዘንድ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንዲናገር እናውቃለን፤ ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው" ሮሜ 3፡19፣2
--- ክርስቶስ እኛ መፈጸም ያቃተንን ህግ ፈጸመልን
" የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና። ሮሜ 10፡4
" በአንዱ ሰው (አዳም) አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ ( በክርስቶስ) መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ። " ሮሜ 5፡19

2)ክርስቶስ በሞቱ ኅጢያታችንን ሁሉ አስወግዶልናል
"ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ። እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። ( ዮሓ 1፡29)
"ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና ( 1ጴጥሮስ 3፡18)
--ኅጢያታችን ሁሉ ይቅር ተብሎልናል
"እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ። ( ቆላስያስ 2፡13)
"እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው።( 2ቆሮ 5፡21)
---በሞቱ ከእግዚአብሔር ጋር አስታርቆናል
"እናንተንም ነውርና ነቀፋ የሌላችሁና ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ፥ በፊት የተለያችሁትን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በአሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ።( ቆላስያስ 1፡21 )
---ክርስቲያን ኩነኔ የለበትም ( ዳግም የተወለደ ክርስቲያን አይኮነንም
"እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም። "( ሮሜ 8፡1)
"በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል። ( ዮሓ3፡18)

3) በክርስቶስ ትንሳኤ አዲስ ሕይወት አገኝን
"ዓለም አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ነኝና እናንተ ደግሞ ሕያዋን ትሆናላችሁ። ( ዮሓ 14 ፡29 )
"ኢየሱስም። ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል (ዮሓ 11፤25)
እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥ በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። (ኤፌሶን 2፡4-7 )
--በትንኤው ልጅነትን አገኝን
"ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል።(1ጴጥ1፡3)
--- በትንሳኤው ድነትንና ጽድቅን አገኝን
" ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤ ( ሮሜ 5፡10)
"ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት ተቈጠረለት የሚለው ቃል ስለ እርሱ ብቻ የተጻፈ አይደለም፥ ስለ እኛም ነው እንጂ፤ ስለ በደላችን አልፎ የተሰጠውን እኛን ስለ ማጽደቅም የተነሣውን ጌታንችንን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሣው ለምናምን ለእኛ ይቈጠርልን ዘንድ አለው።(ሮሜ4፡22-25)
----ይህን ሕይወት በነጻ በእምንት ብቻ የምንቀበለው ነው
"የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው። ( ሮሜ 6፡23 )
"እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።" ( ዮሓ 6፡ 47)
---ይህ ሕይወት ዘላለማዊ ነው ( የሚወሰድ ወይም የጊዜአዊ አይደለም)
"እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።(ዮሓ 5፡24)
"እናንተ ግን እንደ ነገርኋችሁ ከበጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም። በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። ( ዮሓ 10፡26-28)

4) በእርገቱ መንፈስ ቅዱስን ተቀበልን
"እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። (ዮሓ 16፡7 )
"ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤
ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። (ሓዋ 2፡32-33)
---በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ ጌታ የሱስ ነው
"ተጎንብሼ የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል።
እኔ በውኃ አጠመቅኋችሁ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል እያለ ይሰብክ ነበር።
(ማርቆስ 1፡7 )
---መንፈስ ቅዱስ የምንቀበለው በእምነት ነው
"ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ። ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና። (ዮሓ 7፡37-39)
"እንዲህን የማታስተውሉ ናችሁ? በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋ ትፈጽማላችሁን?
እንግዲህ መንፈስን የሚሰጣችሁ በእናንተም ዘንድ ተአምራት የሚያደርግ፥ በሕግ ሥራ ነውን ወይስ ከእምነት ጋር በሆነ መስማት ነው? (ገላትያ 3፡3-5)
---መንፈስ ቅዱስ የሚስጠው ለዘላለም ነው
"ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤( ዮሓ 14፡15)

እንግዲህ ከዚህ በላይ እንደተመለከትነው የስው ድርሻ በነጻ የተሰጠውን በእምነት መቀበል ነው፤፡ በመጀመሪያ ስራችንን ሁሉ በፈጸመልን በጌታ ላይ ካረፍን ጌታን ለማገልገልም ሆነ ለተጠራልነት የጽድቅ ፍሬ ለማፍራት ችሎታና ብቃት እናገኛለን። የድነታችን ጉዳይ አልቆአል ለጌታ ክብር ምስጋና ይግባው። ከዚህ ለመዳን ሳይሆን ስለ ዳንን ነው መልካም ስራ የምንሰራ፤፤
በሚቀጥለው ጊዜ ጌታ ቢፈቅድ እንዴት የአሸናፊ የክርስትና ሕይወት መኖር እንደምንችል ከጌታ ቃል እንማማራለን፤። ከላይ ባተነጋገርነው ሃሳብ ላይ ከተስማማን።


ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ፤
አንተ ራሲሂ በአንድ ጎኒ ነው የህድከው
0 ድምጾች
አዎ። ደህነት(የጌታን አደኝነት) በፈቃዳችን እንዳመንን ሁሉ፡ የጌታ አድኝነት መካድ የቻላል። ስለዚህ ደህንነትዎን እዳያጡ ሁል ግዜ መስቀሉን ያሰቡ።
Mar 3, 2011 ስም-አልባ የተመለሰ
“እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ።“
(መዝሙረ ዳዊት 33:12)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2021 by iyesus.com
Terms of use | Contact us
...