ዋና ገጽ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   ትምህርቶች   የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች   የነጻ መዝሙሮች   ነጻ ዳውንሎድ   ያግኙን   ጥያቄ መጠያየቂያ 
website search (GO!)
 
ዋና ገጽ » ጥያቄ መጠያየቂያ
Email this page to a friend   Wednesday, 8 December 2021
ዋና ገጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ
የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ
አዮታ ሶፍትዌር
ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
የነጻ መዝሙሮች
ነጻ ዳውንሎድ
ያግኙን Contact us
ጥያቄ መጠያየቂያ Q&A
የእገዛ ገጽ Help

“እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ፥ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።“
(መዝሙረ ዳዊት 27:14)

rss

Today's verse

ጥምቀት ያድናል ወይስ አያድንም? በማን ስምስ መጠመቅ አለብኝ?

Jun 27, 2011 መንፈሳዊ ስም-አልባ የተጠየቀ

2 መልሶች

0 ድምጾች
1) የጥምቀት ትርጉሙ በአጭሩ
Quote:
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች
10፥2 ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፤

የሐዋርያት ሥራ 19
1 አጵሎስም በቆሮንቶስ ሳለ ጳውሎስ በላይኛው አገር አልፎ ወደ ኤፌሶን መጣ፥
2 አንዳንድ ደቀ መዛሙርትንም አገኘ። ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን? አላቸው። እርሱም፦ አልተቀበልንም መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ስንኳ አልሰማንም አሉት።
3 እንኪያ በምን ተጠመቃችሁ? አላቸው። እርሱም፦ በዮሐንስ ጥምቀት አሉት።
4 ጳውሎስም፦ ዮሐንስስ ከእርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድ ለሕዝብ እየተናገረ በንስሐ ጥምቀት አጠመቀ አላቸው።
5 ይህንም በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ፤

በቅድሚያ ጥምቀት የሚለው የግሪክ ቃሉ የሚያሳየው በውሃ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ መስጠምን/መጥለቅን ነው እንጂ በውሃ መረጨትን አይደለም። በውሃ መስጠምና መጠመቅ በክርስትና የተጀመረ ብቻ አልነበረም። ለምሳሌ አንድ አሕዛብ የአይሁድን እምነት ለመከተል ሲወስን ይጠመቅ ነበር። ማለትም አሮጌውን ሕይወት ትቶ አዲስ ሕይወትና መንገድ እንደጀመረ የሚያሳይ ነገር ነው።

መጥምቁ ዮሐንስም ቢሆን ሰዎች ከድሮ ክፉ ሥራቸው ንስሐ ገብተው አዲስን ሕይወት እንዲጀምሩ ነበር የንስሐ ጥምቀት ያጠምቅ የነበረው።

ከላይ ባለው 1ቆሮ ክፍል ላይም ጳውሎስ የእስራኤል ሕዝብ ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በባሕር እንደተጠመቁ ይናገራል። ያም ባህር ቀይ ባህር ነው። በግብጽ ይኖሩበት ከነበረው አሮጌ ሕይወታቸው ወጥተው አሁን እግዚአብሔርን ለመታዘዝ አዲስ ኑሮ እንደጀመሩ የሚያሳይ ጥምቀት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ጥምቀት መተባበርን ወይም መሪውን መከተልን ያመለክታል። እስራኤላውያን ሲጠመቁ ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ (baptised into Moses ) ተጠመቁ።

የዮሐንስንም ጥምቀት የተጠመቁት እርሱ ከእግዚአብሔር እንደተላከ በማመን እርሱን በመተባበር ነበር።

ኢየሱስን በማመንም የሚጠመቁት እንዲሁ እርሱን በማመን፤ አሮጌ ኑሮአቸው ሞቶ አዲስ ሕይወት እንደሚኖሩ በማመንና ከክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ጋር እንደተባበሩ በማመን የሚጠመቁት ነው።

2) በማን ስም እንጠመቀ?

እንግዲህ ከላይ እንደጠቀስኩት ጥምቀት መሪውን ተባብሮ አዲስ ሕይወትን ለመጀመር የሚደረግ መስጠም ነው። ስለዚህም በሃዋርያት ሥራ እንደምንመለከተው ሁሉም ጥምቀቶች የተካሄዱት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። ማለትም ከክርስቶስ ጋር እንተባበራለን፤ አሮጌው ሕይወታችን በመስቀሉ ከክርስቶስ ጋር ሞቶ፤ ከክርስቶስ ጋር በአዲስ የትንሳኤ ሕይወት እንኖራለን የሚል ነው። በኢየሱስ እናምናለን፤ እርሱንም እንከተላለን በሚል እምነት የሚደረግ ነው። ስለዚህ በሐዋርያት ሥራ ላይ ያሉትን ደቀመዛሙርቱ ያካሄዱትን ጥምቀቶች በሙሉ ስንመለከት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተደረገ ጥምቀት ነው።
Quote:
የሐዋርያት ሥራ
2፥38 ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።

8፥16 በጌታ በኢየሱስ ስም ብቻ ተጠምቀው ነበር እንጂ ከእነርሱ በአንዱ ላይ ስንኳ ገና አልወረደም ነበርና።

10፥48 በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው። ከዚህ በኋላ ጥቂት ቀን እንዲቀመጥ ለመኑት።

19፥5 ይህንም በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ፤

ይሄ ትክክልና ደግሞ የጥምቀትን ምንነት ለሚረዱ ለዚያ ዘመን ሰዎች ምንም ጥያቄ የሚፈጥር አልነበረም። ኢየሱስን ተከትዬ አዲስ ሕይወት ጀምሬአለሁ ማለት ነው ትርጉሙ። ስለዚህም የሚጠመቁት በኢየሱስ ስም ነበር።

ብዙ ጊዜ ጥያቄ የሚፈጥረው በማቴዎስ ወንጌል 28፡19-20 ያለውና "እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው" የሚለው ስንኝ ነው። አንዳንዶች ይህ ስንኝ የስላሴ ትምህርት ከመጣ ከብዙ ዓመታት በኋላ የተጨመረ ስንኝ ነው እንጂ ኢየሱስ እንዲህ አልተናገረም ይላሉ። እንዲህ ተናግሮ ቢሆን ኖሮ ደግሞ ደቀመዛሙርቱ በኢየሱስ ብቻ አያጠምቁም ነበር ይላሉ። የሚያስኬድ ማብራሪያ ይመስላል። ሆኖም ግን ርግጠኛ ሆኖ ለመናገር አይቻልም።

አንዳንዶች ደግሞ ይህ የሚያሳየው የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ ስም ኢየሱስ ነው ብለው ያምናሉ። በእኔ ግምት ይህ ጨርሶ የሚያስኬድ አይደለም። ይህንን አንድ ጥቅስና ሐዋርያት ሥራ ላይ ያለውን በኢየሱስ ስም መጠመቅ አንድ ላይ አገናኝቶ የእግዚአብሔር ስም ኢየሱስ ነው ወደሚል ድምዳሜ መድረስ በፍጹም መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጓምን የተከተለ አይደለምና በእኔ እምነት የተሳሳተ መደምደሚያ ነው።

3) ጥምቀት ያድናል ወይ?

አንድ እዚህ ጋር ግልጽ ማድረግ ያለብን ነገር ያለ ይመስለኛል። በአዲስ ኪዳን ሰዎች ሲያምኑ ነበር የሚጠመቁት። ማለትም ባመኑበት ቀን ይጠመቃሉ እናም ጥምቀቱ እምነታቸውን የሚገልጹበት ነገር ነበር። እምነታቸውና ጥምቀታቸው ወዲያው አብሮ የሚሆን ነገር ነበር። ስለዚህ ተጠመቁ ማለት እምነታቸውን ገለጹ ማለት ነው እንጂ የጥምቀት ትምህርት ተምረው መጨረሳቸውን ማሳያ አልነበረም። ስለዚህ ጥምቀት የማመናቸው ምልክት ነው እንጂ በራሱ የመዳኛ መንገድ አይደለም።

መዳን በእምነት እንደሆነ የሚያሳዩ እጅግ በጣም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ አሉ። ስለዚህ መዳን በኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኛ አዳኝነትና በመስቀሉ ሥራ ማመን እንደሆነ ምንም የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም። ከክርስቶስ ጋር ተሰቅሎ የነበረው ወንበዴን ለምሳሌ ብንወስድ በክርስቶስ አምኖ ድኗል ነገር ግን አልተጠመቀም። የቆርኔሌዎስ ቤተሰዎችን በሐዋርያት ሥራ 10 ላይ ብንመለከት መንፈስ ቅዱስ የተሞሉት ገና ሳይጠመቁ ቃሉን ስላመኑ ብቻ ነው። ስለዚህ ጥምቀት በልብ ያለን እምነት መግለጫ እንጂ ድርጊቱ በራሱ አያድንም።

ጳውሎስ ራሱ በ1ቆሮንቶስ 1፡17 ሲጽፍ "ለማጥመቅ ክርስቶስ አልላከኝምና፥ ወንጌልን ልሰብክ እንጂ" ይላል። ማለትም ጥምቀት ዋና የመዳኛ መንገድ ቢሆን ኖሮ ጳውሎስ እንዲህም ባለለ ምክንያቱም የሰዎች መዳን ነበረና የእርሱ ዋናው የአገልግሎቱ እምብርት።

ከማዳን ጋር የተጠቀሰበትንም ቦታዎች በአዲስ ኪዳን ስናነብብ ማሰብ ያለብን፤ ባመኑበት ቀን እንደሚጠመቁ ነው። ስለዚህ ስለ ጥምቀት ማዳን የሚናገረው ስለ እምነቱ ነው። ለምሳሌ በማርቆስ 16፡16 ላይ "ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል" ይላል። ይሄ ያመነና የተጠመቀ የሚለው አንድ ነገር ነው። ያመነ ወዲያው ይጠመቃልና ስለዚህ የሚለያይ ነገር አይደለም። እምነቱን በጥምቀቱ ስለሚገልጸው ማለት ነው። ነገር ግን የሚፈረድበት ያልተጠመቀ አይደለም ነገር ግን ያላመነ ነው። ሰው በእምነት እንደሚድን ከሚናገሩት ከአብዛኛው የአዲስ ኪዳን ክፍሎች ጋር ይሄም ይስማማል። ያመነ ይድናል ያላመነ ይፈረደብታል። ያመነ ማለት ደግሞ ወዲያው ይጠመቃል።

ከዚህ ባለፈ ግን ጥምቀቱን ራሱን የመዳኛ ሥርዓት አድርገን የምንወስድ ከሆነ የአዲስ ኪዳንን ፍሬ ነገር አልተረዳነውም ማለት ነው። አዲስ ኪዳን የልብ ኪዳን ነው እንጂ የውጪያዊ ሥርዓት ኪዳን አይደለም። በውጪያዊ መገረዝ፤ ወይም ውሃ ውስጥ በመጠመቅ ወዘተ የመዳንና ያለመዳን ነገር የሚወሰንበት ኪዳን አይደለም። አዲስ ኪዳን በልብ አምኖ የሚዳንበትና የልብና የመንፈስ ለውጥ የሚደረግበት ኪዳን ነው።
Quote:
ትንቢተ ኤርምያስ 31
31 እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር
32 ከግብጽ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፦
33 ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል እግዚአብሔር ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል።
34 እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን፦ እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ አያስተምርም ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል እግዚአብሔር፦ በደላቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና።

ወደ ሮሜ ሰዎች
10፥10 ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና።
Jun 27, 2011 ስም-አልባ የተመለሰ
ወገኔ ጌታ እራሱ በማን ስም እንድናጠምቅ ተናግርዋል በማቲ28፡19
"እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ " ሃዋርያት በጌታ ስም አጠመቁ በሎ የሚናገረን ከዛበፊት በዮሃንስ ጥምቀት የተጠምቀው እንደገና መጠመቃቻውን ስገልጽ ነው እንጂ ሐዋርያት የጌታን ትእዛዝ ሽረዋል ለማለት አይደለም። ትእዛዙ የመጣው ከጌታችን መድሃኒታችን ነው። ከዘህ በፊት መልስ የሰተሀው ወንድ/እህት ከ ሃዋርያ በፊት ወንጌልን መመርማር ተሰኖ ሳይሆን (you are try to show us what your foundation is) I hope and pray i yesus does not equal to 1 Jesus on the other hand to show us one/only Jesus/ yesus if not sorry just a thought.
መልሱን በትክክል አንብበኸው ቢሆን ኖሮ እንዲህ የሚል ዓረፍተ ነገር ታገኝ ነበር

"አንዳንዶች ደግሞ ይህ የሚያሳየው የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ ስም ኢየሱስ ነው ብለው ያምናሉ። በእኔ ግምት ይህ ጨርሶ የሚያስኬድ አይደለም"

ማለትም በዚህ ዓረፍተ ነገር Only Jesus የሚለውን ሐሳብ የሚቃረን ነገር ነው የጻፍኩት።

ሆኖም ግን ሐዋርያት ያጠመቁት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነበር ለማለትም አይቻልም። ምክያቱም ከላይ ባየነው የሐዋርያት ሥራ ላይ በሙሉ አንድም ቦታ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አላጠመቁም። ሁል ጊዜም በኢየሱስ ስም ነው ያጠመቁት። ይህ ደግሞ እንደ በሐዋርያት ሥራ 19 ላይ እንዳለው የዮሐንስን ደቀመዛሙርት ሲያጠምቁ ብቻ አይደለም። ሁሉ ጊዜም ነው እንዲህ ያደረጉት።

እኔ የOnly Jesusም ይሁን የሌሎች ፕሮቴስታንት አማኞች ደጋፊ አይደለሁም ቃሉ ላይ ያለውንና የማምነውን ነው የጻፍኩት። የጻፍኩት ደግሞ የOnly Jesus ተከታዮችንም ይሁን ሌሎች ፕሮቴስታንቶችን እንደማያስደስት አውቃለሁ፤ ምክንያቱም ሁለቱም ወገኖች ያዛቡት ጉዳይ አለ ብዬ ስለማምን ነው።

በዚህ ጉዳይ የOnly Jesus ተከታዮችን ሃሳብ ስለማልደግፍ ብቻ ሐዋሪያት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው ያጠመቁት ብዬ የሌለ ታሪክ ልናገር አልችልም።

ጌታ ይባርክህ!
3) ጥምቀት ያድናል ወይ?
ከክርስቶስ ጋር ተሰቅሎ የነበረው ወንበዴ ተገርዞ ነበር በዛን ጊዜ የክርስትና ጥምቀት አልነበረም ዘፍ 17፤ 10- መግረዝ የጥምቀት ምሳሌ ነበር ቆላ 2፤11-12
የክርስትና ጥምቀት የተሰጠው ጌታ ካረገ በዋላ ነው ማቴ 28፤19።

የሐዋርያት ሥራ
2፥38 ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።
ከላይ ስናይ ሕዝቡ አምኖ ነበር ነገር ግን አቲያታቸው ይሰረይ ዘንድ መጠመቅ ነበረባቸው
እንዲሁም በሐዋርያት ሥራ 8፡36-38 አምኖ ነበር
የሐዋርያት ሥራ 19፡ 1-5 እምነታቸውን የሚገልጹበት ነገር እንዳሎነ መረዳት ነበረብ የዮሐንስን ጥምቀት ተጠምቀው ነበር በሓዋርያው ጳውሎስም እጅ ከንደገና ተጠመቁ ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው አልነበረም እና። ጥምቀት አስፈላጊ ነው (ሥራ 10፡44-48) መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎው ነበር ነገር ግን ጥምቀት አስፈላጊ ስለሆነ ተጠመቁ
ገላትያ 3፡27 እምነታቸውን የሚገልጹበት ነገር ከሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ማለት ፈልጎ ነው ?ሮሜ 6፤3-4 ጌታ ሞትን ድል ነስቶ ከመቃብር እንደወጣ እኛም በጥምወት ዳግም እንወለዳለን ኤፌሶን 5፤26 ቲቶ 3፡5 ዮሐ 3፡5
ጥምቀት ያድናል።
መላሹ ራስህ ያልተረዳሃቸው ብዙ ነገሮች አሉብህ። እናም "አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ"፣ "የሚያስኬድ ማብራሪያ ይመስላል" እያልህ መላምቶችን ወይም ደግሞ የራስህን አረዳድ ጽፈሃል። ጥቂት ፍሬ ባይታጣበትም መላውን መልስህን መቀበል አስቸጋሪ ይሆናል።
"ከክርስቶስ ጋር ተሰቅሎ የነበረው ወንበዴ ተገርዞ ነበር"..... እባክዎ ጥቅሱን?

"የክርስትና ጥምቀት የተሰጠው ጌታ ካረገ በዋላ ነው".....ጌታ ካረገ በኋላ በሰማይ ሆኖ ነው የክርስትና ጥምቀትን የሰጠው? ወይስ ሳያርግ በፊት በምድር እያለ ነው?

"ኃቲያታቸው ይሰረይ ዘንድ መጠመቅ ነበረባቸው"... ኃጢያታቸው የተሰረየው በውሃ በመጠመቅ ሳይሆን ስለ ስሙ ነው (በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው)

1ኛ የዮሐንስ መልእክት 2፡12 ልጆች ሆይ፥ ኃጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና እጽፍላችኋለሁ።

የሐዋርያት ሥራ
2፥38 ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ "በኢየሱስ ክርስቶስ ስም" ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።
የጌታችን ጸጋ እና ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን።

"ከክርስቶስ ጋር ተሰቅሎ የነበረው ወንበዴ ተገርዞ ነበር" ብለሃል።... ወዮ! መዳን በግርዘት ሆነ? አብርሃም የዳነው እኮ በእምነት ብቻ ነው። ማለት ሳይገረዝ በፊት ነው የዳነው (ዘፍጥረት 15፡6።)

አብርሃም ያመነው ገና ዘፍጥረት 12 ላይ፣ ከሃገሩ ሲወጣ ነው።

ወደ ዕብራውያን 11
8 አብርሃም የተባለው ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ስፍራ ለመውጣት "በእምነት" ታዘዘ፥ ወዴትም እንደሚሄድ ሳያውቅ ወጣ።
9 ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን ኖሮ፥ ያን የተስፋ ቃል አብረውት ከሚወርሱ ከይስሐቅ እና ከያዕቆብ ጋር፥ እንደ መጻተኛ "በእምነት" ተቀመጠ፤
10 መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር የሠራትን እና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና።

ታድያ ይህ ያመነው እና የጸደቀው አብርሃም፣ ከብዙ ጊዜ በኋላ በዘፍጥረት 17 ላይ ነው ግርዘትን የተቀበለው። ስለዚህ ግርዘት ያልዳኑ ሰዎች እንዲድኑበት የተሰጠ አይደለም። ነገር ግን አምነው ለዳኑት ሰዎች የተሰጠ ስርዓት ነው።

ቆይ ለመሆኑ፣ ጥምቀት የተሰጠው እኮ ለወንዶች ብቻ ነው (ዘፍጥረት 17፡10)። ታድያ ቅዱሳት ሴቶች ሁሉ እነ ሣራ፣ ርብቃ፣ ዲቦራ፣ ራኬብ፣ የሙሴ እህት ማርያም ... ወዘተ አልተገረዙምና አልዳኑም ማለት ነውን? ወይስ የመዳን መንገድ ሁለት ነውን? ማለትም መዳን ለወንዶች በመገረዝ፣ ለሴቶች በእምነት ነውን? አረ በፍጹም! የመዳን መንገድ አንድ ብቻ ነው። ያም በብሉይ ኪዳን ያህዌ የተባለውን በአዲስ ኪዳን ኢየሱስ ክርስቶስ የተባለውን እውነተኛውን አምላክ በማመን፣ በእምነት ብቻ ነው። ስለዚህ ነው ወደ ዕብራውያን 11 ፡ እነዚህ ሴቶች በእምነት እንደዳኑ የሚነግረን።

መገረዝ እኮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠው ለአብርሃም ነው፤ ዘፍጥረት 17። ታድያ ከአብርሃም በፊት የነበሩ ቅዱሳን እነ አቤል፣ ሄኖክ፣ ኖህ... ወዘተ ጭራሽ መገረዝ ምን እንደ ሆነ አያውቁምና ስለዚህ ጠፍተዋላ? አይደለም። ወይስ እነርሱ በመገረዝ ሳይሆን በሌላ መንገድ ዳኑ? አዎን በእምነት ዳኑ ይላል፤ ወደ ዕብራውያን 11፡1-7።

ሮሜ 4 በሙሉ እናንብብ።

ወደ ሮሜ ሰዎች 4
1 እንግዲህ በሥጋ አባታችን የሆነ አብርሃም ምን አገኘ እንላለን?
2 አብርሃም በሥራ (በግርዘት) ጸድቆ ቢሆን የሚመካበት አለውና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ዘንድ አይደለም።
3 መጽሐፍስ ምን አለ? አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት።
4 ለሚሠራ ደመወዝ እንደ ዕዳ ነው እንጂ እንደ ጸጋ አይቈጠርለትም፤
5 ነገር ግን ለማይሠራ፥ ኃጢአተኛውንም በሚያደድቅ (በክርስቶስ፣ እርሱም እግዚአብሔር ነው) ለሚያምን ሰው፣ እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል።
6 እንደዚህ ዳዊት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ሥራ ጽድቅን ስለ ሚቆጥርለት ስለ ሰው ብፅዕና ይናገራል እንዲህ ሲል፦
7 ዓመፃቸው የተሰረየላቸው፣ ኃጢአታቸውም የተከደነላቸው ብፁዓን ናቸው፤
8 ጌታ ኃጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ብፁዕ ነው።
9 እንግዲህ ይህ ብፅዕና ስለ መገረዝ ተነገረ? ወይስ ደግሞ ስለ አለመገረዝ? እምነቱ ለአብርሃም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት እንላለንና።
10 እንዴት ተቆጠረለት? ተገርዞ ሳለ ነውን? ወይስ ሳይገረዝ? ተገርዞስ አይደለም፥ ሳይገረዝ ነበር እንጂ።
11 ሳይገረዝም በነበረው እምነት ያገኘው የጽድቅ ማኅተም የሆነ የመገረዝን ምልክት ተቀበለ፤ ይህም እነርሱ ደግሞ ጻድቃን ሆነው ይቆጠሩ ዘንድ ሳይገረዙ ለሚያምኑ ሁሉ አባት እንዲሆን ነው፥
12 ለተገረዙትም አባት እንዲሆን ነው፤ ይኸውም ለተገረዙት ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን አባታችን አብርሃም ሳይገረዝ የነበረውን የእምነቱን ፍለጋ ደግሞ ለሚከተሉ ነው።
13 የዓለምም ወራሽ እንዲሆን ለአብርሃምና ለዘሩ የተሰጠው የተስፋ ቃል በእምነት ጽድቅ ነው እንጂ በሕግ (በመገረዝ ህግ) አይደለም።
14 ከሕግ የሆኑትስ ወራሾች ከሆኑ፣ እምነት ከንቱ ሆኖአል፤ የተስፋውም ቃል ተሽሮአል፤
15 ሕጉ መቅሠፍትን ያደርጋልና (ባትገረዝ ትቀሰፋለህ። ዘፍጥረት 17)፤ ነገር ግን ሕግ በሌለበት መተላለፍ የለም።
16-17 ስለዚህ ከሕግ ብቻ ሳይሆን፣ ከአብርሃም እምነት ደግሞ ለሆነ ለዘሩ ሁሉ የተስፋው ቃል እንዲጸና፣ እንደ ጸጋ ይሆን ዘንድ በእምነት ነው፤ እርሱም፦ ለብዙ አሕዛብ አባት አደረግሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ለሙታን ሕይወት በሚሰጥ የሌለውንም እንዳለ አድርጎ በሚጠራ ባመነበት በአምላክ ፊት የሁላችን አባት ነው።
18 ዘርህ እንዲሁ ሊሆን ነው እንደ ተባለ፥ ተስፋ ባልሆነው ጊዜ የብዙ አሕዛብ አባት እንዲሆን ተስፋ ይዞ አመነ።
19 የመቶ ዓመትም ሽማግሌ ስለ ሆነ፣ እንደ ምውት የሆነውን የራሱን ሥጋና የሳራ ማኅፀን ምውት መሆኑን በእምነቱ ሳይደክም ተመለከተ፤
20-21 ለእግዚአብሔርም ክብር እየሰጠ፥ የሰጠውንም ተስፋ ደግሞ ሊፈጽም እንደሚችል አጥብቆ እየተረዳ፥ በእምነት በረታ እንጂ በአለማመን ምክንያት በእግዚአብሔር ተስፋ ቃል አልተጠራጠረም።
22 ስለዚህ ደግሞ (እምነቱ) ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት።
23 ነገር ግን፦ ተቈጠረለት የሚለው ቃል ስለ እርሱ ብቻ የተጻፈ አይደለም፥ ስለ እኛም ነው እንጂ፤
24-25 ስለ በደላችን አልፎ የተሰጠውን፣ እኛን ስለ ማጽደቅም የተነሣውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሣው ለምናምን ለእኛ (ጽድቅ) ይቈጠርልን ዘንድ አለው።


"ከላይ ስናይ ሕዝቡ አምኖ ነበር፤ ነገር ግን ኃጢያታቸው ይሰረይ ዘንድ መጠመቅ ነበረባቸው" ብለሃል። ከላይ ያለውን ሮሜ 4፡6ን እንደገና አንብበውና ተስተካከል።


"ጥምቀት አስፈላጊ ነው" ብለሃል። እዚህ ጋር ትክክል ነህ። ጥምቀት አስፈላጊ ባይሆን ኖሮ ጌታ ይህን ስርዓት ባልሰጠንም ነበር። ጌታ የሰጠንን ስርዓቶችን ሁሉ መፈጸም ተገቢ ነው፤ መልካምም ነው፤ የጽድቅ ሥራም ነው፤ አስተውል የሚያጸድቅ ሥራ ግን አይደለም (ማቴዎስ 3፡15)

ጥምቀት ብቻ ሳይሆን ጸሎትም፣ ጾምም፣ ቃሉን መማር ማንበብ... ሁሉም አስፈላጊ ነው። ይህ ማለት ግን ለመዳን ያበቁናል፤ ወይም ያድኑናል ማለት ሳይሆን፣ አምነን ለዳንን ለእኛ ጸጋን እና በረከትን ይሰጡናል ለማለት ነው። ምክንያቱም እነዚህን ስርዓቶች ጌታ የሰጠን እንድንጠቀምባቸው ነውና።

"መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ነበር፤ ነገር ግን ጥምቀት አስፈላጊ ስለሆነ ተጠመቁ" ብለሃል። ትክክል ነህ የውሃ ጥምቀት አስፈላጊ ነው። ማለትም ለመዳን ሳይሆን፣ አምነን የዳንን እኛ ተጨማሪ የመታዘዝን በረከቶች እንድንጠግብ ነው።

"ጥምቀት ያድናል" ብለሃል። ይህን ያልተጻፈ የሃይማኖትህን ስብከት ትተህ፣ የተጻፈውን "ኢየሱስ ያድናል" (ሐዋርያት ሥራ 4፡12) የሚለውን የእግዚአብሔርን ቃል በይፋ የምትናገረው መቼ ነው? ቅዱስ መጽሐፍ የሚነግረን መዳን በሌላ በማንም ወይም በምንም እንደሌለ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ብቻ የሚገኝ እንደሆነ ነው። እኔ በክርስቶስ ኢየሱስ ብቸኛ አዳኝነት እና ብቸኛ ጌትነት በማመኔ ለዘላለም ድኛለሁ። የዘላለም ህይወትም እንዳለኝ እርግጠኛ ነኝ። ይህም ትዕቢት ሳይሆን እምነት ነው።

መዝሙረ ዳዊት 116፥10 አመንሁ ስለዚህም ተናገርሁ።
2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፥13 ነገር ግን፦ አመንሁ ስለዚህም ተናገርሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ ያው አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን፥ እኛ ደግሞ እናምናለን ስለዚህም እንናገራለን።

አንተስ አምነሃል? ድነሃል? ወይስ በነፍስህ ጉዳይ እስከ አሁን ጥርጥር ላይ ነህ?
ኢየሱስ አለ፦ የዮሐንስ ወንጌል 6፡
47 እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።
48 የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ።

በኢየሱስ ቃል ታምናለህ ወይስ አታምንም? ምርጫው ያንተ ነው።

1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5
10 በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው፤ በእግዚአብሔር (በክርስቶስ) የማያምን፣ እግዚአብሔር (አብ) ስለ ልጁ የመሰከረውን ምስክር ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል።
11 እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው።
12 ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም።
13 የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ።

የአምላክ ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን። (ራዕይ 22፡ 21)
(G.G.A.A)
አንድ አሕዛብ የአይሁድን እምነት ለመከተል ሲወስን ይጠመቅ ነበር። ይህ ሃሳብ በጥቅስ ከብሉይ ኪዳን ያሳዩን ወይ የተጣመቁበትን ቦታ ይግለሱልን
0 ድምጾች
የሐዋርያት ሥራ
2፥38 ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።
(አስተውል ጴጥሮስ "ተጠመቁ!" አለ እንጂ "አጥምቁ!" አላለም። ይህ ለተጠማቂዎች የተሰጠ ትዕዛዝ ነው።)

የሐዋርያት ሥራ
8፥16 በጌታ በኢየሱስ ስም ብቻ ተጠምቀው ነበር እንጂ ከእነርሱ በአንዱ ላይ ስንኳ ገና አልወረደም ነበርና።
(አስተውል "ተጠምቀው ነበር" ይላል እንጂ "አጥምቀው ነበር" አይልም። ይህም ተጠማቂዎችን የሚያመለክት ነው።)

የሐዋርያት ሥራ
10፥48 በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው። ከዚህ በኋላ ጥቂት ቀን እንዲቀመጥ ለመኑት።
(አስተውል "ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው" ይላል እንጂ "ያጠምቁ ዘንድ አዘዛቸው" አይልም። ይህ ለተጠማቂዎች የተሰጠ ትዕዛዝ ነው።)

የሐዋርያት ሥራ
19፥5 ይህንም በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ።
(አስተውል "ተጠመቁ" ይላል እንጂ "አጠመቁ" አይልም። ይህም ተጠማቂዎችን የሚያመለክት ነው።)


በሌላ ስፍራ የተሰጠ መልስ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ
Dec 26, 2012 ስም-አልባ የተመለሰ
Dec 26, 2012 ታርሟል
“እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ።“
(መዝሙረ ዳዊት 33:12)

rss

Today's proverb

የኒውስ ሌተር ምዝገባ
የእርስዎ ስም ኢሜል አድራሻዎ ኢሜል አድራሻዎ (በድጋሚ)
»የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ   የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፈለጊያ
Copyright © 2004-2021 by iyesus.com
Terms of use | Contact us
...