Quote:
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 5
5 መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው።
የዚህን ጥቅስ ምንነት ለመረዳት በመጀመሪያ ደረጃ ይሄ ቁጥር 5 ላይ ያለው ዓረፍተ ነገር ፍርድ እንደሆነ መረዳት ይኖርብናል። ጳውሎስ እንደዚህ ኃጢአት የሚለማመድን ሰው እንዴት ዝም አላችሁት ብሎ በመጀመሪያ የቆሮንቶስ ሰዎችን ነው የገሰጸው። ጳውሎስ ታዲያ የቆሮንቶስ ሰዎችን እንዴት ዝም አላችሁት ብሎ መገሰጽ ብቻ ሳይሆን፤ ምን መደረግ እንዳለብትም ወስኖ ከእነርሱ ጋር ተስማምቶ ፍርድ ሲሰጥ ነው የምናየው። ሲፈርድም ራሱ ብቻውን ሳይሆን "እናንተና መንፈሴም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ጋር ተሰብስበን" ነው የሚለው በቁጥር 4.
እናንተ የሚለው ደግሞ የቆሮንቶስን የቤተክርስቲያን መሪዎች ብቻ አይደለም። ነገር ግን የቆሮንቶስ አማኞችን በሙሉ ነው።
Quote:
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1
2 በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት፥ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት፤
ስለዚህ ይህ ጉዳይ ቤተክርስቲያን በሙሉ በአንድነት ከጳውሎስና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመሆን በአማኞች መካከል ይህን ኃጢአት በሚለማመድ ላይ የተሰጠ ፍርድ ነው።
ጳውሎስ ታዲያ ስለ ፍርዱ ሲገልጽ "መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ" በማለት ነው ለምን ፍርድ እንዳስፈለገ የሚያብራራው። ስለዚህ ቁጥር 5 የሚለው፤ "መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን እንድትድን፤ ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው" ነው የሚለው። ማለትም ሰውየው እየተፈረደበት ያለው ለመንፈሱ ደህንነት
(ድነት
) ሲባል ነው። ይሄ ሰው አሁን ባይፈረድበት መንፈሱ በጌታ ቀን አትድንም። ስለዚህ መንፈሱ በጌታ ቀን እንድትድን አሁኑኑ ሥጋው ለፍርድ መሰጠት አለበት። ለምን
? ንስሐ ገብቶ እንዲመለስ። ፍርድ ባይፈረድበት ይህ ሰው በጌታ ቀን ነፍሱ ልትድን አትችልም፤ ምክንያቱም ምንም ንስሐ ስለማይገባ። አሁን ግን ፍርድ ተፈርዶበት በሥጋው መከራ ሲያመጣበት፤ ያን ጊዜ ንስሐ የመግባት እድል ያገኛል። ይህም መንፈሱ እንድትድን ይረዳዋል።
ስለዚህ ይህንን ጥቅስ የምንረዳው
1. ጳውሎስ የቆሮንቶስ ቤተክርሲትያን አማኞች ይህንን ሰው ለምን ዝም እንደሚሉት ይገስጻቸዋል
2. ጳውሎስ ከቤተክርስቲያን አማኞች ጋር ሆኖ ይፈርድበታል
3. ለምንድነው የሚፈርድበት
? መንፈሱ በጌታ ቀን እንድትድን። ባይፈረድበት በዚሁ ኃጢአት ይኖርና መንፈሱም ልትድን ስለማትችል። ስለዚህ ፍርድ ያስፈልገዋል።
"መንፈሱ እንድትድን ... ፈርጄበታለሁ" እያለ ነው ጳውሎስ። ፍርዱ ያስፈለገው መንፈሱ ያለዚህ ፍርድ ስለማትድን ነው። ፍርዱ ወደ ንስሐ እንዲመጣ እድል ይሰጠዋልና።
ታዲያ በ2ኛ ቆሮንቶስ ላይ ጳውሎስ ይህ ሰው ንስሐ ገብቶአልና አሁን ተቀበሉት፤ ፍቅርም ከእርሱ ጋር አጽኑ ብሎ የቆሮንቶስን አማኞች ሲመክራቸው እናነብባለን።
Quote:
2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2
5 ነገር ግን ማንም አሳዝኖ ቢሆን፥ እንዳልከብድባችሁ፥ በክፍል ሁላችሁን እንጂ እኔን ያሳዘነ አይደለም።
6 እንደዚህ ላለ ሰው ይህ ከእናንተ የምትበዙት የቀጣችሁት ቅጣት ይበቃዋልና እንደዚህ ያለው ከልክ በሚበዛ ኀዘን እንዳይዋጥ፥
7 ይልቅ ተመልሳችሁ ይቅር ማለትና ማጽናናት ይገባችኋል።
8 ስለዚህ ከእርሱ ጋር ፍቅርን እንድታጸኑ እለምናችኋለሁ፤
9 ስለዚህ ደግሞ ጽፌ ነበርና፤ በሁሉ የምትታዘዙ እንደ ሆናችሁ የእናንተን መፈተን አውቅ ዘንድ አሳቤ ነበር።
10 እናንተ ግን ይቅር የምትሉትን እኔ ደግሞ ይቅር እለዋለሁ፤ እኔም ይቅር ካልሁ፥ ይቅር ያልሁትን ስለ እናንተ በክርስቶስ ፊት ይቅር ብዬአለሁ፥
11 በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱን አሳብ አንስተውምና።
ጥያቄው ከተጠየቀበት ከ1ኛ ቆሮንቶስ 5 የምንማረው አንዱ ትልቁ ቁም ነገር፤ ቤተክርሲያን በአንድ አማኝ ላይ ፍርድ ስትሰጥ፤ ሁለት ነገሮችን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መሆን አለበት። አንደኛ የተፈረደበት ሰው ንስሐ እንዲገባ ለመርዳትና የቤተክርስቲያንዋን ጤንነት ለመጠበቅ
("ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንዲያቦካ አታውቁምን
?" ቁ.6
) ታስቦ ነው ፍርድ መሰጠት ያለበት። ብዙ ጊዜ በኃጢአት ለሚመላለሰው ሰው ሕይወት ስለማይታዘን፤ ወይ ዝም ይባላል ወይም ከተቀጣም ለእርሱ ሕይወት ታስቦ አይደለም። ከኃጢአቱም ከተመለሰ በኋላም እርሱን በፍቅር መቀበል ለብዙዎች ይከብዳል።
ሌላው የሚያስተምረን፤ ፍርድ የሚሰጠው አንዴ በኃጢአት ወድቀው ንስሐ ለገቡ ሰዎች አይደለም። ነገር ግን ከኃጢአታቸው እንዲመለሱ አሁን ኃጢአት በሚለማመዱ ሰዎች ላይ ነው። ብዙ ጊዜ አንዴ ኃጢአት አድርገው ከኃጢአታቸውም ንስሐ ገብተው አሁን ነገሩ ስለተሰማ ብቻ ባለፈውና ንስሐ በገቡበት ኃጢአት ይቀጣሉ። ይህ ትክክል አይደለም። አሁን ከሚለማመዱበት ኃጢአት ወደ ንስሐ ለማምጣት ነው የቤተክርስቲያን ቅጣት የሚያስፈልገው።